www.maledatimes.com ላገባ ነው >> (ሉሊት በዓሉ) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

 ላገባ ነው  >> (ሉሊት በዓሉ)

By   /   June 18, 2015  /   Comments Off on  ላገባ ነው  >> (ሉሊት በዓሉ)

    Print       Email
0 0
Read Time:5 Minute, 33 Second

Lulit Bealu

Lulit Bealu

Lulit Bealuĺ

==========

‹‹ምነው ሉሊት ስራ የለም እንዴ?›› አለኝ አለቃዬ፤ በጥርጣሬ አይን አጥንቴ ድረስ ዘልቆ እየተመለከተኝ፡፡ ልብ ብሎ ላየኝ እስትንፋስ ያለብኝ ተንቀሳቃሽ ፍጥረት ሳልሆን እንደ ሎጥ ሚስት የጨው አምድ ሆኜ በወንበሩ ላይ የተተከልኩ ሃውልት እመስል ነበር፡፡

‹‹እ?. . .አለ፤ ኧረ አለ፡፡›› ብዬ ሲሰርቅ እንደተያዘ ሌባ ተደነባብሬ ጠረጴዛዬ ላይ የተዝረከረኩትን ወረቀቶች በተሻለ ሁኔታ አዝረከረኳቸው፡፡ አለቃዬ የሰሞኑ ሁኔታዬ ግራ እንዳጋባው ባይነግረኝም ከፊቱ ላይ ማንበብ ችዬ ነበር ዛሬ ግን ሲብስበት ይመስለኛል. . .

‹‹ሉሊት ሰሞኑን እኮ ልክ አይደለሽም፤ ፍዝዝዝዝ ብለሻል?›› አለኝ

‹‹አውቃለሁ›› እንደማለት ጭንቅላቴን ላይ ታች ወዘወዝኩ፡፡

‹‹ምነው. . . ችግር አለ እንዴ?››

‹‹ ኧረ የለም፡፡›› አልኩ የሆንኩትን ከአይኖቼ ገጽ ላይ እንዳያነብብኝ መሬት መሬቱን እያየሁ፡፡ ምን ብዬ ከሞት የበረታ አስጨናቂ ነገር ከፊቴ ተጋርጦብኝ ነው ልበል? ምን ብዬስ ናቲ ስንት የደበቅኩትን ጉዴን ሳያውቅ የመሞሸሪያ ቬሎዬን ይዞ ሊመጣ ነው ልበል? ምን ብዬስ ይህን ጉዴን አይቶ ከሚለየኝ ከወዲሁ ልርቀው እችል እንደሁ በመንፈስ ከሱ መራቅን እየተለማመድኩ ነው ልበል? ጭንቅንቅ ያለ ነገር፡፡ ሳይታወቀኝ ‹‹ኡፍፍፍ. . . ›› ብዬ በረዥሙ ተነፈስኩ. . .ትንፋሽ ሳይሆን እሳት ከውስጤ ተራምዶ የወጣ ይመስል ከንፈሬ ተለበለበ፡፡

‹‹የአመት ፍቃድሽን ፈርሜልሻለሁ. . .የተደራረቡ ስራዎች ቢኖሩም በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነሽ ፍቃድሽን ለሌላ ጊዜ እንድታራዝሚ ልጫንሽ አልፈለኩም::›› አለኝ ፍጹም ትህትና በተላበሰ አንደበት፡፡

‹‹እሺ አመሰግናለሁ አቶ ስምኦን.›› አልኩት በአመዳም ፈገግታ ፊቴን ላፈካለት እየሞከርኩ. . .የበጀት መዝጊያ ወቅት በመሆኑ የፈረመልኝ የአመት ፍቃዴ እንዲሰጠኝ ሳይሆን ከእድሜው ላይ ዘመን ተቀንሶ እንዲሰጠኝ ነው የመሰለኝ፡፡ ብቻ ትንሽ ቅር የተሰኘሁት በቀኑ ማጠር ነው፤ 15 የስራ ቀን ብቻ ነው የተፈቀደልኝ፡፡ .‹‹ናቲን በእነዚህ ሚጢጥዬ ቀናት ብቻ እንደ አይስክሬም ስልሰው ብከርም እንኳን እንዴት ልጠግበው እችላለሁ?. . .እንዴትስ የፍቅር ጥሜን በእነዚህ ብናኝ ቀናት ብቻ ልቆርጥ እችላለሁ?

ምናለ የተሰጠኝ ፍቃድ የ115 ኣመት ቢሆንና ከናቲ ጋር ከአልጋ ሳንወርድ እንደተቃቀፍን ትውልድ ጥሎን ቢያልፍ? ምናለ ኑሮ ይሉት ጣጣ ‹‹ለሆዳችሁ፣ ለልብሳችሁ፣ ለቅብርጥስያችሁ›› እያለ ጣልቃ እየገባ ባይቀሰቅሰን፡፡›› ስል ተመኘሁ፡፡

‹‹መልካም የእረፍት ጊዜ ይሁንልሽ! አይዞሽ ›› ብሎኝ እየተቻኮለ ሲወጣ. . . ወደ መውጫው በር የሚጣደፉትን እግሮቹን በአይኔ እየተከተልኩ የሃሳብ ፈረሴ ላይ ያለ እርካብ ተወርውሬ ተቀመጥኩ. . . .!!!

‹‹ወይኔ ሉሊት!!! አሁን ምንድነው የሚውጠኝ? ምን ብዬስ ነው ከመምጣቱ በፊት ለናቲ ጉዴን የምነግረው? አትምጣ ልበለው? እንደውም አልሆንህም ብለውስ?. . .ከዚህ ሁሉ በአካል የሚያውቀኝንና ከነጉዳቴ የሚወደኝን ሰው ባገባስ?. . .ወይ ዝርዝር አድርጌ ሁሉንም ነገር ብነግረውስ?>> የሃሳብ ጎተራ ውስጥ ገብቼ የተቀመጥኩ መሰለኝ፤ ነፍ ሃሳብ፣ እልፍ ጭንቀት አስተናገድኩ፡፡

* * * * * * *
ናታንን ያገኘሁት ለፌስቡክ እንግዳ እያለሁ በዚሁ የፌስ ቡክ መንደር ነው. . .ናታን በኔ መመዘኛ ጎበዝ የሚባል ፀኃፊ ነው:: ለዚያውም ላደንቀውና ልወደው የተገደድኩት ጹሁፎቹን እኔ በማልወደው የትረካ አንጻር ‹‹በአንደኛ መደብ የትረካ አንጻር›› እየጻፈ ነው፡፡ . . . የፈጠራ ታሪኮቹን የሚጽፈው ዳር ቆሞ በመታዘብ ሳይሆን እራሱ የታሪኩ ተሳታፊ ሆኖ (እኔ እንዲህ ሆኜ፣ በዚህ ገበቼ፣ በዚህ ወጥቼ፣ እንትናዬን ወድጄ ፣እንትናዬን ጠልቼ) እያለ ነው፡፡ የሚጽፋቸው ፅሁፎች ሁሉ እውነታዊ ምትሃታቸው እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡ በፅሁፎቹ ውስጥ የናቲ ድንቅ ስብእና፣ ጠንካራ አቋሙና ለሰው ልጆች ያለው ቀና አመለካከት ይታየኛል፡፡ ናቲ በጥቅሉ እኔ የምወደው አይነት ሰው ነው፡፡

ናቲን መጀመሪያ የቀረብኩት ልቦለድ ለማንበብ ከነበረኝ ጥልቅ ፍቅር ነው፡፡ ልቦለድ ማንበብ የጀመርኩት ገና የ4ኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ ነው፤ እናቴ አንባቢ ነበረች፤ ገንዘብ ስታገኝ ብርጭቆ ከመግዛት ይልቅ መጽሃፍ መግዛት ያስደስታት ስለነበር፣ እኛ ቤት የረባ መፅኃፍ እንጂ የረባ ብርጭቆ የለም፡፡ 4ኛ ክፍል ስደርስ ማንበብ ልጀምር እንጂ ልጅ ሆኜም እናቴ ስታነብ ጨርሳ እስክትተርክልኝ ፈታ አልሰጣትም ነበር፤ ስታነብ የቀራትን ገፅ እየገላለጥኩ ‹‹ኡ ገና ነሽ እንዴ? ኧረ ማሚዬ ቶሎ ጨርሺና ተርኪልኝ ጨነቀኝ እኮ!›› እያልኩ ውትውት አደርጋት ነበር፡፡ ካደኩ በኋላም ስበላና ስጠጣም ልቦለድ ከእጄ ተለይቶኝ አያውቅም፤ በትምህርት ሰዓት ግን ማንበብ ስለማይፈቀድልኝ ተደብቄ ነበር የማነበው፤ በተለይ ከአባቴ፡፡ ዛሬ ግን አባቴም ምክሩን እና እንደ ረመጥ የሚፋጀውን ትዝታውን፣ እናቴም በእትብትም ባይሆን በጡት ያጋባችብኝ የሚመስለኝን የንባብ ፍቅር አሳቅፈውኝ ላይመለሱ ተያይዘው ራቁኝ፤ ለዚያውም የኔ የምለው አንድም ሰው በሌለበት በዚህ ኦና ምድር፡፡

ይህን የንባብ ልክፍቴን ነበር ወደ ፌስ ቡክ አለም ይዤ ብቅ ያልኩት፡፡ ናታን ጓደኞዬ አልነበረም፤ የሱን ልቦለዶች በምትከታተል አንዲት ፀኃፊ ጓደኛዬ አማከይነት አወኩት፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ፅሁፉን ሳነብ በየምክንያቱ እየመረቀዘ በሚያሰቃየኝ ውስጣቂ ቁስሌ ላይ አንዳች የፈውስ ዘይት ሲንጠባጠብ ታወቀኝ፡፡ ያነበብኩት ታሪክ ከኔ ታሪክ ጋር ተመሳሳይነት ነበረው፤ ተስገብግቤ ነበር የጓደኝነት ጥያቄ ላኩለት፤ ወዲያው ጥያቄዬን ተቀበለ፤ በውስጥ መስመር አመሰገንኩት፤ በብዙ ቃላት አድናቆቴን ገለፅኩለት፤ ጹሁፎቹ ሁሉ ለመንፈሴ ፈውስ እንደሆኑ ነገርኩት፤ ከጠበቅኩት በላይ ሰፍ ብሎ አናገረኝ፡፡ እየዋለ እያደር ስለሱ የሚሰማኝ ስሜት ከአድናቆት የዘለለ ሆነብኝ፤ ገጹ ላየ ተለጥፌ መዋል ማደር ጀመርኩ፤ በየምክንያቱ ማድነቅ፣ ያላንተ አንድም ሰው ለስነጽሁፍ አልተፈጠረም ማለት ጀመርኩ፤ እሱም ጠዋትም ማታም ቀንም ከልቡ የፈለቁ በሚመስሉ ውብ ቃላት ያናግረኛል፣ ያደናንቀኛል፣ ያሽኮረምመኛል፡፡ ለብቸኝነቴ መድሃኒት ያገኘሁ መሰለኝ፤ አነባቸው የነበሩትን መፅሃፍት ከድኜ የእሱኑ ስራዎች ብቻ ማንበብን ስራዬ ብዬ ተያያዝኩት፤ ጽሁፎቹን እያነበብኩ ‹‹የዘመናችን ድንቅ የስነ ጽሁፍ ሃዋሪያ›› ብዬ እስከ ማሞካሸት ደረስኩ፤ ናታን የተለየ ሰው ሆነብኝ፤ ለምሰጠው አድናቆት አጸፋው እልፍ የፍቅር ቃላት ሆኑብኝ፤ እነዛን ሁሉ በፍቅር የታሹ ውብ ቃላት ያን ሁሉ መልካምነቱን መሸከም አቆቶኝ ጎበጥኩ፡፡

ናቲ ‹‹ቆንጆ ነሽ›› እንኳን ሲለኝ በተራ የእለት ተእለት ቃላት አይደለም፤ ስነጽሁፋዊ ውበት በተላበሱ አብረክራኪ ቃላት እንጂ፤ ከልጅነቱ ጀምሮ በውስጡ ‹‹የኔዋ ሄዋን›› ብሎ የሳላት፤ ለትዳር የሚመኛትና የሚያስባት አይነት ሴት እንደሆንኩ ይነግረኛል፡፡

አንዳንዴም አፍቃሪ የወንድ ነፍስ የተላበሰ ገፀሰብ ያለበት ምርጥ ግጥም ይጽፍና ‹‹አሁን የለጠፍኳት ግጥም ላንቺ ናት፤ ደጋግመሽ አንብቢያት›› ይለኛል በውስጥ መስመር፤ (ታዝዤ ነው!!!) ደጋግሜ ግጥሙን እያነበብኩ በማላውቀው እንግዳ ስሜት እሰክራለሁ. . .ሲያናግረኝ ቃል ሳይሆን ህይወትን በውስጤ የሚዘራ ይመስል የሆነ ህይወት ያለው ነገር በውስጤ ይንቀሳቀሳል፡፡ . . . ልቤ ነገር አለሟን ረስታ እሳት ላይ እንደተጣደ የቂቤ ክምር ቅልጥልጥ ትልለታለች፡፡ አንዳንዴም ይደውልና ለሁለት ሰአት ያህል ያወራኛል፤ ጆሮዬ እስኪግል አጫጭር ልቦለዶቹን እያፈራረቀ ያነብልኛል፡፡

አድናቆት ሲደራረብ ወደ ፍቅር ይቀየር እንደሆን እንጃ!. . . ስሜቴ የአድናቆት ብቻ አልመስልሽ አለኝ፤ እሱን ለደቂቃም ለማጣት ያለመፈለግ ስሜት. . .ድምጹን እስክሰማና ኦንላየን እስካገኘው ድረስ እንደረሃብተኛ የመንገብገብ ስሜት፡፡

ውሎ አድሮ እንደወደድኩት ገባኝ፤ መንገር ግን ፈራሁ፡፡ የሴትነት ኩራቴ ይሁን ሌላው ጉዴ እንጃ አንዳች ነገር አፌ በራፍ ላይ ተቀምጦ እንዳልናገር ከለከለኝ፤ ዳር ዳር ስል. . . ሳምጥ. . . ስሽኮረመም፡- እንደወደደኝ ነገረኝና ገላገለኝ፤ ለፍቅር ላይከፈት ተከርችሞ የነበረውን የልቤን መክፈቻ ቁልፍ ከጣልኩበት አንስቼ ያቀበልኩት፡፡ ሳንተያይ ተዋደድን. . በፍቅር ክንፍንፍ ብለን ሰባተኛ ሰማይ ደረስን (በተለይ እኔ!)፡፡

ከሁለት ወራት በፊት ይመስለኛል አንድ ቀን ማለዳ ናቲዬ ደወለልኝ. . እንደሌላው ጊዜ ግጥም አላነበበልኝም፡፡ እንደ ከዚህ በፊቱ ከአጫጭር ልቦለዶቹም አንብቦልኝ << እንዴት ነው ወደድሽው?>> አላለኝም፡፡ ለዚህ ለዛሬው ጭንቀቴና መብሰልሰሌ አቀብሎኝ ስልኩን የዘጋው፡-

‹‹. . .ሉላዬ ከልቤ ወድጄሻለሁ፤ መጥቼ የህይወቴ አጋር ላደርግሽ እፈልጋለሁ፤ እባክሽን ታገቢኛለሽ?›› አለኝ፡፡ በመንፈስ ሳልኩት እግፌ ስር በርከክ ብሎ ሲለምነኝ፤ ስልክ የያዘው እጄ ተንቀጠቀጠ፤ አዞረኝ፤ መልስ እየጠበቀ እንዳለ ቢታወቀኝም ‹‹ታገቢኛለሽ?›› ከሚላው ድንገተኛ ቃል ጋር አብሮ የሆነ የደስታ ይሁን የድንጋጤ ገመድ የወረወረብኝ ይመስል ጉሮሮዬ ታነቀ፤ ለደቂቃዎች የዝምታ አዘቅት ውስጥ ተዘፈቅኩ፤ ስሜቴ ድብልቅልቅ አለ፡፡

‹‹አአ. . ናቲዬ አልሆንህም! በጭራሽ አላገባህም፡፡›› ማለት ቢኖርብኝም ልለው ግን አቅም አጣሁ. . . እራስ ወዳድ የሆንኩ ቢመስለኝም እራስ ወዳድነቴን ወደድኩት፤ ናቲዬን ፈጽሞ ላጣው አልፈልግማ፤ ያለሱ የምራመዳት አንዲትም የህይወት እርምጃ እንድትኖረኝ አልፈልግማ፡፡

‹‹ ሉላ ሰምተሽኛል?›› አለኝ ዝምታዬ ሲበረታበት፡፡

‹‹እ?››

‹‹ታገቢኛለሽ ወይ?››

‹‹ አዎ!›› አልኩ ባጭሩ፤ ውስጤ የሚለው ግን ሌላ ነበር፤ ከነ ጉዳቴ፣ ከነ ጉድለቴ፣ ከነባዶነቴ ከወደድከኝና ከተቀበልከኝ አገባሃለሁ ነበር የሚለው፡፡

‹‹ሃኒዬ ምነው ታዲያ ቅር አለሽ?››

‹‹ናቲዬ እኔ እኮ ግን. . . ›› ሳግ አቋረጠኝ፤ ማንባት የማይታክታቸው አይኖቼ የእንባ ዶፍ ማውረድ ጀምረው ነበር፡፡

‹‹አንቺ እኮ ምን?. . . ደጋግሜ ነግሬሻለሁ እኮ ሃኒ፣ ምንም አይነት ሰው ሁኚ ምንም አይነት የኋላ ታሪክ ይኑርሽ ትሆኚኛለሽ፡፡››

‹‹ እርግጠኛ ነህ?›› አልኩ አፌ ሳላዘው ነበር ቃል ያወጣው፡፡

‹‹እርግጠኛ ነኝ! ትንሽም እንዳትጠራጠሪ፤ ይልቅ የኔ ቆንጆ በጣም ናፍቀሽኛል እስካገኝሽ ቸኩያለሁ፡፡›› አለኝ፡፡ በቅጽበት የሞተ የመሰለኝ ተስፋዬ ሲያንሰራራ፤ በፍቅር ጥም የደረቁ የመሰሉኝ አጥንቶቼ ሲለመልሙ ታወቀኝ፡፡

<<እነዚያን አለንጋ ጣቶችሽን ደግሞ ሳሚልኝ!>> ሲለኝ የቅጽበቱ ደስታዬ እንደ ጉም ከላዬ ላይ በነነ፡፡ አንዳች ነገር የፍቅሬን ካብ የተስፋዬን ክምር ሲንድብኝ ታየኝ፡፡ ናቲ ከሴት ልጅ ውበት ረዥዥም የ እጅ ጣቶችን እንደሚወድ ደጋግሞ ነግሮኛል. .

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 9 years ago on June 18, 2015
  • By:
  • Last Modified: June 18, 2015 @ 8:12 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar