www.maledatimes.com ሐምሌ እና አሚና ከአሚና/ላሊበላ ጋር ጨዋታ አበባየሁ ገበያው - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ሐምሌ እና አሚና ከአሚና/ላሊበላ ጋር ጨዋታ አበባየሁ ገበያው

By   /   August 5, 2015  /   Comments Off on ሐምሌ እና አሚና ከአሚና/ላሊበላ ጋር ጨዋታ አበባየሁ ገበያው

    Print       Email
0 0
Read Time:4 Minute, 41 Second

ጠዋት ሁለት ሰዓት አካባቢ ከቤቴ ስወጣ እንደ መስቀል ወፍ በየሰፈሩ እየገቡ አካባቢውን ሙዚቃዊ ቃና ባለው ሙገሳ/ልመና/ ከሚያደምቁት በእነሱ አጠራር አሚናዎች/ላሊበላዎች ጋር ፊት ለፊት ተገጣጠምን፡፡ ድሮ ድሮ ላሊበላዎች/አሚናዎች በሌሊት በየሰፈሩ
ተዘዋውረው የደንቡን አድርሰው ሳይታዩ ወደ መጡበት ይመለሳሉ:: ዛሬ ግን እስከ እኩለ ቀን በየሰፈሩ ሲዘዋወሩ ይታያሉ፡፡ ከቤቴ በር ላይ ከገጠመችኝ ወጣት ሴት ጋር ተጨዋወትን፡፡
አበበች ጎበና
ሳቂታና ንቅት ያለች ተግባቢ ናት፡፡
ስምሽ ማነው—-?
አበበች ጎበና፡፡
ከየት መጣሽ—-?
ጎጃም ምድር ደጀን ከምትባል ከተማ አካባቢ ታለ መንደር፣ ዓባይ
ሸጥ ሸጡን ይዘን ነው የምንኖር.. ዋናው ስረ መሰረታችን ግን ወሎ
ላሊበላ ነው፡፡
ስማችሁ ምንድን ነው የምትባሉት—?
እዚህ በሽዋ ‹‹ላሊበላ›› ..ነው የሚሉን፤ እኛ አካባቢ ያልሽ እንደሆነ
‹‹አሚና›› ነው የምንባል፡፡
/እጄን አየት አድርጋ/ምነ በቴፕ የምትቀጂኝ..?
በጋዜጣ ላይ ከአንቺ ጋር ያደረግነውን ንግግር ለመጻፍ እንዲመቸኝ ነው፡፡
“የምጠቅምሽ ከሆነ ምን ችግር አለው፡፡ ልማድ የለኝም እንዳላሳስትሽ ስትቀርጪው በወጉ እንድሆን አስረጅኝ፡፡ መቼም የከተማ ሰው
ብልሃት አያጣውም ብዬ ነው፡፡
ላሊበላ/አሚናነትን እንዴት ተማርሽ፣ ትምህርት ያስፈልገዋል..?
ተማሪ ቤት ተገብቶ ማለትሽ ነው?
አይ..ከቤተሰቦችሽ…?
ጉሮሮዋችንም ሆነ ግጥሙ የራሳችን ነው፡፡ ደሞ ምን ትምህርት የሚሻው ሆነና ማቀንቀን መጫዎት መዝፈን..እንኳን እኔ አዋቂትዋ ጉብላሊቱ ሁል እንዴት ያለ ድምፅ አለው መሰለሽ፡፡ ለእኛ ድምፃችን ከዘራችን ያመጣነው ነው፡፡ ይሄን ደሞ ሞያ ብለሽው..አሁን አንቺን አግኝሻለሁ ብዬ አላለምኩም፡፡ ግን እንደዚህ ብዬ ብገጥምልሽ ምን ሞያ ትምህርት አለው፡፡
እመቤትዬ የእኔ መልከ መልካም
በእጅዋ ስራን እንጂ በአፋ ሰው አትነካም
አምላክ አንቺን ሰራ ተጨንቆ ተጠቦ
አንግትዋ የሚመስለው የእንግሊዝ ብርጪቆ
የእኔ ቆንጅትዬ እመቤትየዋ
ፃፍ ፃፍ አድርጊኝ እንደ ወረቀቱ
አንቺ አይደለሽም ወይ የመስራቤት ጌጡ
አንቺማ ተምረሽ ብዙ አገር አየተሸ
ደግሞ እንደማይሞች ታደርጊናለሽ
የእኔ ቆንጅትዬ እመቤትዬን
የእኔ ሴት ወይዘሮ የእኔ ስመ መልካም
በእጅዋ ስራን እንጂ በአፍዋ ሰው አትነካም
ሱሪዋን አጥልቃ ስትል ሞድ ሞድ
ሹጉጥ ያስታጠቅዋት ትመስላለች ወንድ
ለአንቺ ነበር እጂ ሱሪ ማሰፋት
እንደ አዳል ጎረምሳ አትወድም ጥቃት
የእኔ ቆንጅትዬ የእኔ ስመ መልካም
በእጅዋ ስራን እንጂ በአፍዋ ሰው አትነካም
ቅላትዋ እንደ ሸማ ጃኖን እንደዘለቀው
እንኳን ላሊበላ እግዜርም ደነቀው
የጎበዞቹ እህት እመቤትዬን
ቢያኖርሽ ነው እንጂ እኔስ መለመኔ
እንዳሻሽ ሁኝልኝ እንዳይባክን አይኔ
መስጠት የአባትሽ ነው መለመን የአባቴ
እንደ ድሮው ሁኜ እንደመሠረቴ
ይቅርታ ላቋርጥሽ—?
ምን አለ አቋርጪኝ እንጂ..ኃላ እቀጥላለሁ፡፡
መጨረሻ ላይ ያልሽው ግጥም
‹‹መስጠት የአባትሽ ነው መለመን የአባቴ
እንደ ድሮው ሁኜ እንደ መሠረቴ››..ላሊበላ/አሚና ድሮ ቀረ ይባላል ትስማሚያለሽ-?
እንዴት..እነማን ናቸው የሚሉን..በደንብ ያውቁናል ብለሽ ነው…?
ድሮ ድሮ ሊነጋጋ ሲል በየቤቱ ተዟዙረው ለምነው ሳይነጋባቸው ለሰው ሳይታዩ ወደ መጡበት ይሄዳሉ፤ ወደ ሚለምኑበት ቤትም ሲሄዱም የሰውየውን ስማና ማንነት አጥንተው ነው—
እሱማ ዛሬስ መቺ ጠፋን ብለሽ ነው እነየዋ፡፡ ..ልክ ነው፡፡ በፊት ሌባውም ቀማኛውም የለም ነበር፡፡ የአባቶቻችንን ታሪክና ስረ መሰረት ተከትለን እንሄዳለን ለምሳሌ ልጆቹን…፡፡
ስንት ልጆች እንዳሉት—?
እራ ደግሞ ልጅማ እንዴት ይቆጠራል፡፡ ነውር ነው በኛ አገር፡፡ ‹‹ስንት ልጅ አለው›› ብሎ መጠየቅ ግም ነው፡፡ ሴት ወንድ ልጆች፤ ከብት ሃብት ንብረት፤ ዝና፣ ጀግንነት፣ ብልሃቱን..እንደዚያ ነው የሚጠየቅ፡፡ ስሙን አጥንተን ወፉ ‹‹ጪጪጪጪ..›› ከማለቱ በፊት ከደጁ እንደርሳለን ‹‹እንዲህ ነህ፣ እንዲያ ነህ..ጀግናው ጠንበለሉ..›› እያልን መለመን ነው፡፡ ደሞም አዳራችን እዚያው አካባቢ ካለ ጫካ ‹‹የመሸበት አዳሪ›› ብለን አጎራባቹን እንጠይቃለን እቢም የሚለን የለ እንደዛ ነበር፡፡
እዚህ አዲስ አበባ ነው (ክፍለ ሃገር)–?
አዲስ አበባ! እንኳን ሰው ሊያሳድሩ በቅጡም አይሸልሙ፡፡ ሁሉ ሱሪ ታጣቂ ሯጪ..ማን ዞርስ ብሎ ያይሸል አያ!!
በገጠር ሴትዋ እና ወንዱ እየተቀባበሉ ነበር የሚገጥሙት አንቺ ብቻሽነሽ—?
እሱማ ነበር:: ዛሬ ዛሬ ኑሮም ከበደ እና ባለቤቴን‹‹ምነ አንተም ብቻህን፤ እኔም ብቻዬን የማንለምን..›› ብለን ወጣነ ከአገራችን:: እሱ ዘንድሮ ቢቸና ሂድዋል፡፡ እኔ ከልጄ ጋር እዚህ አዲስ አበባ መጣሁ፡፡
ልጅሽም እንዳንቺ ላሊበላ/አሚና ናት—?
ዋ!! ምን ታደርገዋለች፣ የዘርዋ አይደል፡፡ ትልመደው እንጂ፡፡
አምና ጀምሮ አብራኝ ነው የምትወጣ፡፡ /በእጅዋ እየጠቆመችኝ/
ያችውልሽ ድምፅዋን መስማት ከፈለግሽ ሂጂ፡፡
እሰማታለሁ..እኔ የምልሽ ከስንት ዓመትሽ ጀምሮ ነው በላሊበላ/አሚናነት—?
እረ አልቆጠርኩትም፡፡ በጣም ልጅ እያለሁ ጀምሮ ነው፡፡ ደጀን፣ ማርቆስ፣ ባህርዳር፣ ፍኖተ ሠላም፣ አዲስ አበባ፣ ፍቼ፣ ቢቸና፣ደብረወርቅ..ብዙ አገር ሂጃለሁ..በአመት ሁለት ጊዜ መሆኑ ነው…መለመን ግዳችን ነው፡፡ በዚህ ወቅት ደሞ ቀየው ሙሉ ነቅሎ በየሃገሩ የደንቡን ያደርሳል፡፡
ወቅቱ ከሆነማ የምጣችሁበት ቀዬ ባዶውን መክረሙ ነው ማን ያርሳል—?
እርሻም ብዙ የለን ግን ደካሞች/አረጋዊያን፣ ህፃናት፣ ዘልቀው ሌላ አገር መሄድ ማይችሉት ባድማውን ይጠብቃሉ፡፡ ደሞ እሽም አይሉንም ሐምሌንና ጥቅምትን እንቀመጥ ብንል.. ምክንይቱም የዓመሉን ካላደረስን ወረርሽኙ..ህመሙ ስቃዩ ስለሚበረታብን ተያይዘን ከማለቃችን በፊት..በየአገሩ እንጓዛለን፡፡ ያልሽ እንደሆነ ደሞ ስረ መሰረቱ ዘራችን ሁላ ሃምሌ ከከተመ ጀምሮና ከዚያም ጥቅምት ሲጠባ የእኛ አያቶች አባቶች የወጉን ያደርሳሉ፡፡ ከነሱ የወረስነው ነው፡፡
ባለቤትሽ፣ ልጅሽ፣አንቺ..ወደቤት ተመልሳችሁ ያጠራቀማችሁት ብር ስትቆጥሩት ስንት ይሆናል—?
እዚሁ አይደል የሚያልቅ ከቁጥርም አይገባም../ሳቅ/ግን ከአምስት መቶ እስከ አምስት ሺህ ብር ሊደርስ ይችላል፡፡ ምን ዋጋ አለው
ብክን ብሎ አይደል የሚያልቅ፡፡
ከላሊበላ/አሚና ከእናንተ መካከል ዘፈን በካሴት ያወጣ አለ—?
/ሳቅ/ እረ የለም፡፡ ምኑን አመጣሽው!! እኛ ‹‹የደንቡን እንበል›› ብለን እንጂ ድምፃችን ጥሩ ነው ብለሽ ነው፡፡ እንደሱማ ከሆነ እኮ ሁሉም ሊያወጣ ይችላል፡፡ ከልጅ እስከ አዋቂ አሚና/ላሊበላ ነው:: ከደጀን ከተማ ጀርባ አባይ ወንዝ ሸጡን ውስጥ ለውስጥ ይዘን እንወርድና ከሸለቆ ሸለቆ ድምፃችን ሲሰማ፣ ሲያቀነቅን፣ እንዴት ያስገመግማል መሰለሽ፡፡ ቅላፂያቸው ማማር..ግን አንዳንድ ጊዜ በመኪና ተሰቅለን ከአንዱ አንዱ አገር ስንሄድ በመኪናው ውስጥ ቴፑ ሲዘፍን እሰማና፤ እየዘፈኑ ነው እያላገጡ..እላለሁ…ወትሮም ግጥሙ አይሰማ ከበሮው ብቻ ድም ድም..ሲል ይሰማል፡፡ በኛ ያልሽ እንደሆን..ግን አሁን በሬድዮው ክተቱኝ ብል እሽ ሚለኝ አለ/ጠየቀችኝ/
‹‹ጥሩ ድምፅ አለኝ›› ብለሽ ታስቢያለሽ–?
እውነት አይደል የጠየቅሽኝ…ድምፄን አስቤው አላውቅም፡፡ ያውም ለመዝፈን እንጃ..!! ‹‹የደንቡን ላድርስ›› ብዬ ነው፡፡ያልሽ እንደሆን ደሞ..ሰው እማትዘፍኝ..አሚናነትሽን/ላሊበላነትሽን ትተሸ ይሉኛል፡፡ ወዲያ ሂዱ እላቸዋለሁ፡፡ እራ አንቺ እሱን ነገር ልሞክረው ብለሽ..ግን ሳስበው ከዘመዶቼ አንዳቸው ቢሆን ይሄን አጥተውት አልመሰለኝም.. እንዴው ምናምን እርግማን አለው እንደሆን መዝፈን፡፡/ንግግርዋን አቋርጣ/
ተሎ ተሎ ብለሽ በቶሎ ሸኝኝ
ወደ ጎረቤትሽ ልመና አለብኝ
የነጪ ጤፍ ገንፎ ይላል ዋጡኝ ዋጡኝ
አንቺን ስመለከት ሌሎች አመለጡኝ
ለአስሩ ብር ነው ወይ እንዲህ ሽር ጉዱ
አባትሽ ይሰጣል በጉን ከነቀንዱ
የጎበዞች እህት አይባል አንድ ሰው
ስጥት ሰጠት ማድረግ አንጀት የሚያደርሰው
በራፉም ይከፈት ሞላው ይሰናዳ
ልክ የለውም አሉ ለዚህ ቤት እንግዳ
ቢያኖርሽ ነው እንጂ እኔስ መለመኔ
እንዳሻ ሁኝል እንዳይባክን አይኔ
/ከጎኔ ቆማ ንግግራችንን ስታዳምጥ የነበረችው እናቴ ጠቀም ያለ ብር አውጥታ አስጨበጠቻት/
የጎበዞች እህት እመቤትየዋ
እግዚአብሄር ይስጥልን እግዚአብሄር ይስጥልን
ተባረኪልን ውለሽ ግቢልን
ውሎ ለመግባት ሰርቶ ለመብላት አይንፈግብን
የጌታን መንገድ የፅድቅን መንገድ ይስጥልን
አመት አመቱን ያድርስልን ውለሽ ግቢልን
ገበያውን ጥጋብ አገሩን አማን ያድርግልን
የልጆችሽን አበባ ያሳይሽ
መጠን አንጣሽ
ምቀኛሽን እንደባልቴት ጥርስ ያርግፍልሽ፡፡ /ተመራርቀን ተለያየን/

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 9 years ago on August 5, 2015
  • By:
  • Last Modified: August 5, 2015 @ 6:07 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar