www.maledatimes.com ሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስ ጻፉ ክንፉ አሰፋ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስ ጻፉ ክንፉ አሰፋ

By   /   December 22, 2013  /   Comments Off on ሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስ ጻፉ ክንፉ አሰፋ

    Print       Email
0 0
Read Time:20 Minute, 36 Second

ፀሃይ አሳታሚ ድርጅት በታኅሣሥ 16, 2006 ዓ/ም (Dec. 25, 2013) የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩትን የሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስን ‘እኛና አብዮቱ’ የሚል
መጽሃፍ ለገበያ እንደሚያበቃ አስታወቀ። ሻምበል ፍቅረሥላሴ እንደ ደርግ አባልነታቸው በጋራ ያመኑበትን፣ የተማከሩትን፣ የወሰኑትን፣ የሰሩትን፣ የገጠማቸውንና በቅርብ በዓይን ምስክርነት ያዩትን ተንትነው በ‘እኛና አብዮቱ’ ያስነብቡናል። የራሳቸውን ዕይታ ያካፍሉናል።
9781599070780-Perfect.indd
ልጅ ሆነን አንድ አባባል እሰማ ነበር።”አበላል እንደ ደርግ አባል። አለባበስ እንደ ፍቅረሥላሴ ወግደረስ!” – የሚል። በተለይ በኔ ትውልድ ያለን ሰዎች፣ ከዚህ ውጭ ስለኝህ ሰው የምናውቀው ብዙም ነገር አልነበረም። ግና እኝህ ሰው በልባቸው መክሊት ለአመታት የቋጠሩትን መረጃ ጀባ ሲሉን፤”… አጻጻፍም እንደ ፍቅረሥላሴ ወግደረስ” የሚያሰኝ ሆኖ አገኘሁት።

ሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስ ለአስራ አምስት ዓመታት አብዮቱን ሲመሩ ቆይተው ወደ መጨረሻው ከሥልጣን በጡረታ ስም እንዲሰናበቱ ተደርገዋል። ደርግን በጣለው በወያኔ
መንግሥትም ለ፳ ዓመታት ታስረው፣ የሞት ፍርድ የተበየነባቸውና በመጨረሻ ፍርዱ ወደ ዕድሜ ልክ ተዛውሮላቸው ከእሥር ቤት በአመክሮ የወጡ ግለሰብ ናቸው።

ጸሃፊው በድራማ መልክ በመጽሃፋቸው ካሰፈሩዋቸው እውነታዎችና ግለ-ሂሶች ውስጥ አንዳንዶቹን ለአንባቢያን ማካፈሉ አይከፋም። ደርጎች መፈንቅለ መንግስት አድርገው ሲያበቁ ቀዳማዊ ሃይለስላሴ ዘንድ ቀርበው ከንጉሱ የገጠማቸውን አስገራሚ ምላሽ ሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስ በመጽሃፋቸው እንዲህ ሲሉ አስፍረዋል።
የፖለቲካ እሥረኞች በሙሉ እንዲፊቱ የሚለው ጥያቄ እንደተነበበ ንጉሡ ጣልቃ ገብተው “ለመሆኑ የፖለቲካ እሥረኞቹ እነማን ናቸው?” የሚል ጥያቄ አቀረቡ። “በእርግጥ የምናውቃቸው የፖለቲካ እሥረኞች ባይኖሩም ማንኛውም የፖለቲካ እሥረኛ እንዲፈታ ነው የምንጠይቀው” አሉ ሻለቃ ተስፋዬ ገብረኪዳን። ንጉሡ ራሳቸውን ነቅነቅ አድርገው ጽሑፉን የሚያነበውን የደርግ አባል እየተመለከቱ “አልገባችሁም!” ብለው ዝም አሉ። በእርግጥም አልገባንም። ተማሪዎችና የተለየ ዓላማ የነበራቸው የተማሩ ሰዎች የሰነዘሩትን መፈክር ብቻ ነበር ይዘን ንጉሡ ፊት የቀረብነው። በፖለቲካ እሥረኝነት ስም በከፍተኛ ደረጃ ለጣሊያን ወራሪ መንግሥት በባንዳነት አድረው አገራችንን የወጉ፣ ለቅኝ ተገዥነትም የዳረጉትን እንደ ኃይለሥላሴ ጉግሳ ያሉ ወንጀለኞች የፖለቲካ እሥረኞች ተብለው ከግዞትና ከእሥር ቤት አስወጥተን እንደ ጀግና ራሳቸውን እንዲቆጥሩ አደረግናቸው።

የነ ጄነራል ተፈሪ በንቲ ጉዳይን አስመልክቶ የሰፈረው ታሪክ ደግሞ እንዲህ ይነበባል። “በሊቀመንበርነት ስብሰባውን የሚመሩት ጄነራል ተፈሪ ‘የቋሚ ኮሚቴው’በዛሬው ቀን የሚወያይበትን ጉዳይ አስመልክቶ የመቶ አለቃ ዓለማየሁ የደርጉ ዋና ፀሐፊ ይገልጽልናል’ ብለው ስብሰባው መጀመሩን ካበሰሩ በኋላ ዓለማየሁ በአጀንዳው ላይ አጭር ገለጣ ማድረግ ሲጀምር ስልክ ተደወለ። ስልኩ ሌ/ኮሎኔል መንግሥቱ አጠገብ ስለነበር ወዲያው ቅጭል እንዳለ መነጋገሪያውን በማንሳት ሃሎ አሉ።
ከሌላው ጫፍ ማን እንደደወለ አላወቀንም። በኋላ እንደታወቀው ሌ/ኮሎኔል ዳንኤል ነበር የደወለው።
ምን እንደተነጋገሩ አልተሰማም። ሌ/ኮሎኔል መንግሥቱ ብቻ “እሺ እሺ” ብለው ስልኩን ዘጉት። ስልኩን እንደዘጉ “ይቅርታ ስልኩ የተደወለው ከጎንደር ነው። ጎንደር ውስጥ ችግር አለ። እናንተ ቀጥሉ” ብለው ከጀርባቸው ባለው በር በኩል ውልቅ አሉ። በዚህን ጊዜ ዓለማየሁና ሞገስ ጥርጣሬ የገባቸው መሰለ።
ዓለማየሁ ንግግሩን አቋርጦ በመስኮት በኩል ውጭ ውጭዉን መመልከት ጀመረ። ዓይኖቹ አላርፍ አሉ። ግራና ቀኝ ይመለከታል። አጠገቡ ያሉትን ሰዎች ሁሉ በጥርጣሬ ተመለከተ። ሻምበል ሞገስም በር በሩን ይመለከታል። ከአሁን አሁን አንድ ችግር ይከሰታል የሚል ፍርሃት ያደረበት ይመስላል። ሁሉም የኢሕአፓ አባላትና ደጋፊዎች ፈርተዋል። እንደፈሩት አልቀረም ሌ/ኮሎኔል መንግሥቱ ከወጡ ሁለት ደቂቃ እንኳን አልሞላም ከበስተጀርባ ባለው ኮሪደር የወታደሮችን እርምጃ ሰማን። ወታደሮች ሲንቀሳቀሱ በፊት ለፊታችን ባሉት መስኮቶች በኩል ተመለከትን። በዚህን ጊዜ ፍስሐ ደስታ “ተከብበናል” አለ። ወዲያው ሁለቱም በሮች በኃይል ተበረገዱ። ሁላችንም ደነገጥን፣ ቀልባችን ተገፈፈ፣ እጢአችንም የወደቀ መሰለን። ድርቅ ብለን በተቀመጥንበት ቀረን።…

ሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስ ሰለ ልጅ ሚካኤልን አስተዋይነት ሲያስታውሱ እንዲህ የሚል ግለሂስም ያስነብቡናል። እኛ በችኮላ ውሳኔ መስጠታችን፣ ሕዝቡን በደንብ አለማወቃችን፣ ሰፊ የሕዝብ አመራር ልምድ ማጣታችን፣ የአገርና የውጭውን ፖለቲካ ውስብሰባዊ ግንኙነት አለመገንዘባችን፣ የመንግሥትን አሠራር ደንብና ሥርዓት አለመረዳታችን፣ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ጥመርታዊ ግንኙነትን መመልከት አለመቻላችን፣ የተለያየ ገንቢም ሆነ አፍራሽ ተልዕኮ ያላቸው ኃይሎች ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩብ ያለማጤናችን፣ በየዋህነትና በቅንነት ብቻ እንደምንሠራ በመገንዘባቸው ሊሆን ይችላል ልጅ ሚካኤል ከእኛ ጋር መቆየት የሚችሉት ለአጭር ጊዜ ብቻ እንደሚሆን የጠቆሙት…

በወቅቱ ስለ ህዝቡ የእርስ በርስ መጨካከንና መወነጃጀል ባሰፈሩት ክፍል ውስጥ እንዲህ የሚል ታሪክ እናገኛለን።
..የሥራ ዕድገት የተከለከለ፣ በሌብነትም ሆነ በስካር ወይም በሌላ ጥፋት የተቀጣ፣ በግል ጉዳይም ሆነ በመንግሥት ሥራ ከአለቃው ጋር የተጣላ፣ በአጋጣሚው ተጠቅሞ አዲስ ሹመት ወይንም ዕድገት
ለማግኘት የሚፈልግ ሁሉ ጠቋሚ፣ ወንጃይ፣ ከሳሽ፣ ተበዳይ ነው። የተወሰነ ጥቅም ለማግኘት ወይም ሌላውን ለመጉዳት ብለው “ኢትዮጵያ ትቅደምን ይቃወማል፣ ከታሠሩት ባለሥልጣናት ወይም ሚኒስትሮች የቅርብ ዝምድና አለው። ስለሆነም ሥራ ይበድላል፣ ሠራተኛውን ያጉላላል፣ ውሳኔ አይሰጥም” በማለት አለቆቻቸውን የሚከሱ፣ የሚወነጅሉ በርካታ ናቸው። ለደርግ አባላት ቤታቸው ድረስ በመሄድ በማስረጃ የተደገፈ ቢሆንም ባይሆንም ተቆርቋሪ በመምሰል የክስ ማመልከቻ የሚያቀርቡም ነበሩ። እንታሠራለን ብለው በፍርሃት
የተደበቁ ባለሥልጣናትን የቅርብ ዘመዶቻቸው ወይም አሽከሮቻቸው ወይም ጎረቤቶቻቸው ደርግ ጽሕፈት ቤት ድረስ በመምጣት ያጋልጧቸው ነበር። የመሥሪያ ቤቶችን ሰነዶች ፎቶ ኮፒ በማድረግ ወይም ሰነዱን እንዳለ ከፋይሉ አውጥተው በማቅረብ “በመንግሥት ንብረት፣ ሀብት ወይንም ገንዘብ ላይ አላግባብ ተወስኗል” ብለው ጥቆማና መረጃ የሚያቀርቡም ነበሩ።
ሠራተኞች አሠሪዎቻቸውን ይከሳሉ፣ ይወነጅላሉ። ገበሬዎች ለዘመናት በደል አደረሱብን የሚሏቸውን የአካባቢ ባለሥልጣናት ይወነጅላሉ። ውንጀላው በርካታ ነው።

አሽከሮች፣ ዘበኞች፣ ገረዶች… መረጃ ይሰጣሉ፣ ይጠቁማሉ። የተደበቀ የጦር መሣሪያ፣ የተደበቀ ገንዘብ፣ ወደሌላ ቦታ የተወሰደ ወይም የሸሸ ሀብት እንዳለም የሚጠቁሙን እነሱ ናቸው።
በአንድ ቦታ በርከት ያሉ ሰዎች ተሰብስበው ምሽት ከአሳላፉ “ሲያድሙ ነበር” ብለው ከነስም ዝርዝራቸው መረጃውን ደርግ ጽሕፈት ቤት ድረስ ያመጣሉ። “እኛ እስከዛሬ የበይ ተመልካች ነበርን ዛሬ ዕድሜ ለእናንተ እንጀራ ሊወጣልን ነው! ከእናንተ ጎን ተሰልፈን አቆርቋዦቹን እንታገላለን! በማንኛውም ጊዜ ትዕዛዝ ብትሰጡን ለመፈጸም ዝግጁ ነን!” እያሉ ታማኝነታቸውንና ተባባሪነታቸውን የሚገልጡም ብዙዎች ነበሩ። በጣም የሚያስደንቀው አባቶቻቸውን፣ ልጆቻቸውን፣ ወንድሞቻቸውን፣ እህቶቻቸውን፣ ባሎቻቸውን፣ ሚስቶቻቸውን በመክሰስ፣ በመወንጀል፣ በማጋለጥ፣ በመጠቆም ብሎም በማሳሰር ጉዳት ያደረሱ በርካቶች መሆናቸው ነው።

እንግዲህ ስለ አዲሱ ‘እኛና አብዮቱ’ መጽሃፍ ይህንን ካልኩ ቀሪውን ለአንባቢ መተው ይበጃል። ሁሉም ሰው መጽሃፉን አንብቦ የራሱን ፍርድ ይስጥ።

ህይወት በሩጫ ትመሰላለች። የተፈጥሮ ህግጋት ነውና የሰው ልጅ እስትንፋሱ እስኪቋረጥ ይሮጣል። ከዚያም ሩጫውን ይጨርሳል። ሩጫውን ሳይጨርስ በልቡ ቋጥኝ የያዘውን እምቅ ቋጠሮ የሚተነፍስ ደግሞ እድለኛ ነው። በአንጻሩ ደግሞ በአእምሮው የቋጠረውን የእውቀት ምስጢር ሳያካፍል የሚያልፍ ሁሉ ያሳዝናል።
ያለውን የወረወረ ንፉግ አይደለምና መንቀፍም ካለብን የሚወረውረውን ሳይሆን የማይወረውረውን ነው። መተቸት ካለብነም ሃሳቡን እንጂ ግለሰቡን ባይሆን ይመረጣል። በሃሳብ ላይ መወያየትና መተሻሸት ደግሞ አዋቂነት ነው።

በመጨረሻም የመጽሃፉ አርታኢ ኤልያስ ወንድሙ በመግቢያው ላይ ባሰፈረው መልእክት ጽሁፌን ልቋጭ። የተማረ፣ ያወቀና ያደገ ትውልድና ዜጋ ምልክቱ የተጻፈን ማንበቡ፣ ያነበበውን ማብላላቱና ካነበበው ውስጥ ስንዴውን ከእንክርዳዱ መለየቱ ሲሆን፤ እራሱም አስተውሎና አገናዝቦ መጻፉ ደግሞ መማሩን ብቻ ሳይሆን መመራመሩንና ማወቁን የሚያሳይ ታላቅ ተግባር ነው። ለዚህም ደግሞ ግላዊ ነጻነት ያስፈልገዋልና ጫንቃው ላይ ያሉትን ግላዊና ታሪካዊ ቀንበሮች የሰበረ ነጻ ሰው መሆን ይጠበቅበታል። ትምህርትና ዕውቀት አስተዋይነትንና ጥልቀትን ከራስ በላይ ለትውልድ አሳቢነትን የሚያመለክት ታላቅ ኃላፊነት ነው። ለዚህም እንደ ትናንቱ ‘የተማረ ይግደለን’ ሳይሆን፤ የተማረ ያስተምረን፣ ያስተዳድረን ብሎም ይምራን በምንልበት ዘመን ከምናነብበው ውስጥ ያልተስማማንበትን በጨዋነት የመቃወም፣ የፈቀድነውን እንደ ስሜታችን የመደገፍና ተሳሳተ የምንለውን ለእርማት መጠቆም ግላዊ መብታችን
ነው።…

* ፀሃይ አሳታሚ ድርጅት ከዚህ በፊት የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያምን፣ የቀድሞውን የህወሃት መሪ ዶ/ር አረጋዊ በርሄን፣ የቀድሞውን የኢህአፓን አመራር አባል የዶ/ር መላኩ ገኝን፣ የቀድሞው ሚንስትር የአቶ ተካልኝ ገዳሙን መጽሃፍትና ከስልሳ በላይ የሆኑ በኢትዮጵያ ታሪክና ጥናት ላይ ያተኮሩ መጽሃፍትን ማሳታሙ ይታወሳል። ‘እኛና አብዮቱ’ የሚለው ይህ አዲስ መጽሃፍ በwww.tsehaipublishers.com ድረገጽና በቀርቡ በየሱቁ አንደሚገኝ ከሎስ አንጀነሰ
የደረሰን ዘገባ አስታውቋል። ሁላችንም ገዘተን እናንብብ።

መጽሃፉን አንብቤ እንደጨረስኩ በሂሳዊ ግምገማ እመለስበታለሁ።  መጸሃፉን ለማግኘት ይህንን ይጫኑ 

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 10 years ago on December 22, 2013
  • By:
  • Last Modified: December 22, 2013 @ 2:48 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar