www.maledatimes.com ” ቀነኒሳ ሽሻ ቤት????!!” - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

” ቀነኒሳ ሽሻ ቤት????!!” 

By   /   May 1, 2015  /   Comments Off on ” ቀነኒሳ ሽሻ ቤት????!!” 

    Print       Email
0 0
Read Time:4 Minute, 41 Second


ድህነትን በሩጫ አመለጥነው ይሄንንስ ??
(አሌክስ አብርሃም)

ታዋቂው አትሌት ሃይለ ገብረ ስላሴ በአንድ ወቅት ባደረገው ቃለመጠይቅ እንዲህ ብሎ ነበር‹‹ ድህነትን በሩጫ አመለጥኩት!!›› ይህ ንግግሩ ሃይሌ በአንድ ጠጠር ሽ ከሚሊየን የስንፍና ወፎችን ያረገፈበት ነበር ! ሃይሌ በድህነት የሚጠራ ስማችንን በአለም ፊት የተንኮታኮተ ስማችንን በሩጫ በሰባበራቸው ሪከርዶች እንዲያገግሙ አድርጓል ! መሮጥ በወጣትነት ፈተና ከሆኑት መጥፎ ሱሶች ትውልዱን ከመታደጉም በላይ ከነሙሉ ክብሩና ስልጣኑ በድህነት መቃብር ላይ ሃይሌ የሚባል ህያው የስኬት ሃውልት እንዲቆም ሌሎችም እግር በእግር ተከትለው ከድህነትም ከታሪካዊ ጥቁር ድህነትና የርሃብ ታሪካችንም በሩጫ እንዲያመልጡ አርያ ሁኗል !!

ከእነዚህ በህይዎት እያሉ ህያው የኩራት ሃውልቶቻችን ከሆኑት ጀግኖቻችን መካከል አንዱ ደግሞ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ነው ! ቀነኒሳ ለእኔ በአትሌቲክሱ ዓለም ክስተት ነው ! እድል ገጥሞኝ አንዴ ሲሮጥ በአካል አይቸዋለሁ …አጃኢብ አስብሎኛል ! አሯሯጡ ከሩጫ በላይ የሆነ አርት አለው ! የአካልም የስነልቦናም ብርታቱ ለመላው አለም ወጣቶች አርዓያ የሚሆን ወጣት ጀግናችን ነበር ዛሬም ነው !! ቀነኒሳ በቀለ … ከባንዲራችን ስር የሚውለበለብ ሌላው የመልካም ታሪካችን ባንዲራ !

ከሰሞኑ ታዲያ አንድ ወሬ ሰማሁና ‹‹ ሳይቃጠል በቅጠል ›› እንዲሉ …ቀነኒሳን በአደባባይ ልወቅስ ወጣሁ ….ከዛ በፊት ግን ማጣራት ይቅደም …ጀግና ጠላቱ ብዙ ነውና የጥላት ወሬ እንዳይሆን ብየ እስካሁን ጉዳዩን አዘገየሁት …አሁን ግን ማን ያርዳ የቀበረ ማን ይናገር የነበረ በሚለው ብሂላችን መሰረት ያየሁትን ልናገር ይህን ፅሁፍ እነሆ ብያለሁ !
ሲጀመር … አንድ የማይገባበት ስርቻ የሌለው ጓደኛየ የማላምነውን ወሬ ነገረኝ። “አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ሺሻ ቤት ከፈተ” የሚል። እንዴት ላምነው እችላልሁ? ቀነኒሳ እኮ ነው ያለኝ ! ጭራሽ ወዳጀ ጨመረበት ‹‹ ቦሌ በሚገኘውና በስሙ በከፈተው አዲሱ ሆቴሉ ውስጥ ነው ሽሻ ቤቱ የተከፈተው›› ሲል አረዳኝ (ሳላረጋግጥ አረዳኝ አልኩኝ? አማልኝ ማለቴ ነው)። መሀላው ከወትሮው በተለየ ስለበዛብኝ ለማረጋገጥ ወሰንኩ።

በቀነኒሳ ጉዳይ ማንንም አላምንም እራሴ በዓይኔ በብረቱ ካላየሁ ትንፍሽ አልልም በቃ!! መሸት ሲል ጠብቄ ጉዱን ለማየት ቦሌ ወደሚገኘው ቀነኒሳ ሆቴል አመራሁ። ይሄ ሆቴል ሆቴል ብቻ አይደለም …የሃይሌ ቃል ግንብና መስተዋት ለብሶ በአካል የተከሰተበት ሃውልት እንጅ …‹‹ድህነትን በሩጫ ለማምለጣችን ምስክር ሊሆን በግርማ ሞገስ የቆመ ሃውልት ! አትሌቶቻችን፣ በሃይሌ ገ/ስላሴ አርአያነት፤ ዝነኛ ካደረጋቸው ሩጫ ተጨማሪ በተለያዩ ዘርፎች ኢንቬስት በማድረግ በርካታ የስራ እድሎችን (ለህዝባቸው) እየፈጠሩ ይገኛል። ጀግናው ቀነኒሳ በቀለም በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ ከበሬታ የሚሰጠው፤ ስሙም በዚህ መሰል መልካም ስራዎች የሚነሳ ዝነኛ አትሌት ነው። ይሄ ሆቴል ደግሞ ላብን ጠብ አድርጎ ከሰራ ማንም የት እንደሚደርስ የሚያሳይ ማማ ነው !!

የሰማሁትን ላለማመን ስለ መልካምነቱ አብዝቼ አሰብኩ። ቀነኒሳ ሆቴል ከዚህ ቀደም ተስተናግጄ ባውቅም፤ በእንዲህ አይነቱ ሁሉን በሚታዘብ አይን አልነበረም። መግቢያው በር ላይ እንደደረስኩ “ታዛቢው” አይኔ ነገረኛ አደረገኝ። ሆቴሉ የዚህ ታላቅ ሰው ስለመሆኑ ከእንግሊዝኛና ቻይንኛ በቀር በአማርኛ የተጻፈ ምንም ነገር የለም። ቀነኒሳ ሆቴል ይላል ጽሁፉ በሁለቱም የባዕድ አገራት አፍ። ይሁን ከስራ የበለጠ ቋንቋ የለም ! ቀነኒሳ ብቻውን ብርታት የሚባል ቋንቋ ነው !! በደንቡ መሰረት ተዳብሼ (ተፈትሼ) ገባሁ። የእንግዳ መቀበያው ጠረጴዛ ጀርባ የዚህን ታላቅ ሰው ስዕል ተሰቅሎ አየሁት። መልኩ እና ግርማ ሞገሱ እንዳለ ነው። ምንአልባት ቻይንኛ ወይንም አንግሊዝኛ የማያነብ ሰው፤ ትልቁን ምስል ሲያይ ሆቴሉ የሱ መሆኑን እርግጠኛ ሆኖ ሊገምት ይችላል። እኔ ግን ከዛም በላይ አሰብኩ- ሆቴሉ የቀነኒሳ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ ማንኛውም በዚህ ቤት ውስጥ ያሉትን ስራዎች ሀላፊነት ወሳጁ ራሱ መሆኑን።

እንግዲህ የሽሻዋ ነገር ሆድ ሆዴን እየቆረጠችኝ …እዚሁ የእንግዳ መቀበያ ጠረንጴዛ ላይ ((ማጨስ ክልክል መሆኑ)) በእንግሊዝኛ ተፅፎ ስመለከት ትንሽም ቢሆን የሰማሁትን ‘ሀሜት’ ላለማመን ፈለግኩኝ። አንደውም ኩራት ተሰማኝ ! ቀነኒሳ ሆቴል፤ ባለ ሰባት ፎቅ ህንጻ ሊፍቱ ላይ በተደረደሩት ቁጥሮች አወቅኩ። “ወዳጀ” ሲነግረኝ ፎቅ ላይ መሆኑን እንጂ ስንተኛ መሆኑን አጥርቼ አልጠየኩትም ነበር። ሶስተኛ ፎቅ ላይ ወርጄ አሰሳ ጀመርኩ። ሺሻ በአይን ብቻ ሳይሆን በአፍንጫም መፈለግ ስለሚቻል፤ የተዘጉ ክፍሎች ሳይቀሩ እየተጠጋው እንደ ሰላይ ስልጡን ውሻ ማሽተቴን ተያያዝኩት።

ሶስተኛውን ፎቅ በንጹህነቱ አድንቄ፤ ደረጃውን ተወጣጥቼ 4ኛ ፎቅ ደረስኩ። እስከ ስድስተኛ ፎቅ ድረስ አፍንጫዬን በርግጄ፤ ከንፈሬን አሞጥሙጬ፤ እያሸተትኩ እና ከግራ ቀኝ፣ ጫፍ እስከ ጫፍ ከንቱ “ስለላዬን” ባካሂድም ይብስ ብሎ የክፍሎቹ መልካም ጠረን አስደሰተኝ። “እገሌ”ን ለመውቀስ የቀረኝ አንድ ፎቅ ብቻ ነው። ሰባተኛው ፎቅ ላይ ደረስኩ። በጭራሽ ውሸት እንደሰማው ተረዳሁ። ምንም ነገር የለም። ስለምን በቀነኒሳ ላይ እንዲህ አይነት ወሬ በሀሰት አወራልኝ ብዬ ምክንያቱን መመራመር ያዝኩ። ይሄ የወሬ ባህላችን መቸ ይሆን የሚለቀን እያልኩ !! ቀነኒሳን በክፉ በመጠርጠሬ ‹‹አፉ በለኝ›› ልል በልቤ እየከጀልኩ !
ወደ መጣሁበት ለመመለስ ሊፍቱ ጋር ስጠጋ፤ አንድ ወጣት ፊት ለፊት ወንበር ዘርግቶ ተቀምጦ አስተዋልኩ። ምን ሊሰራ ይሆን ወጭ ወራጁን ተቀምጦ የሚያየው ስል ለራሴ ጠየኩና፤ ልቅ፣ ደፋር ሆንኩኝ። 

“ነፍሴ… ሺሻ ቤቱ የቱ ጋር ነው? ሰው ቀጥሮኝ ነበር” አልኩት። 

ከተቀመጠበት ተነስቶ በትህትና እየተሸቆጠቆጠ ሸሸግ ያለችውን የሰባተኛ ቅጥያ ፎቅ መግቢያ ጠቆመኝ። ለማመላከት የተቀመጠ ነው መሰለኝ “ስራ የተፈጠረለት” ይህ ወጣት። ከተቀመጠበት አጠገብ ያለው ግርግዳ በስፖንጅ የተለበጠ ድምጽ ማፈኛ ከለላ ተሰርቶለታል። ከቅጥያ ሰቀላዋ ከሚመጣው የሙዚቃ ድምጽ ለክፍል እንግዶች ጸጥታ ጥንቃቄ መሆኑ ነው። ጨለማ የወረሰውን ደረጃ ወጥቼ ሙዚቃ ታፍኖ የሚሰማኝ ክፍል ጋር ስደርስ በሩ የትኛው መሆኑ ግራ ገባኝ። አገኘሁት። ወደ ውስጥ ገባሁ።

በዘመናዊና ባህላዊ መካከል የሚገኝ ጥቁር አጭር ጉርድ ቀሚስ መሀሉን ጥንታዊው የጥበብ መስቀል የተጋደመበትን ልብስ የለበሱ የሚያማምሩ ሴት አስተናጋጆች ውር ውር ሲሉ ሳይ የት ነው እንዴ ያለሁት?… አልኩኝ። ጀግናው አትሌት ቀነኒሳ ሆቴል። የተነገረኝን “ሀሜት” እውነትነት ለማረጋገጥ አሁን ካለሁበት ሰወር ወዳለው ክፍል መዝለቅ ነበረብኝ። በደመ ነድሴ እና ልምድ ባካበተው አፍንጫዬ ተመርቼ ገባሁ። እውነትም ሺሻ ቤት ውስጥ ገብቻለሁ። እያንዳንዱ የቡድን መስተናገጃ ክፍልፋይ በብራማ ክር መሳይ የጌጥ ገመዶች በስሱ ተጋርዶ፤ በውስጡ በርካታ ተስተናጋጆች በሙዚቃ ታጅበው ሺሻውን ያንዶቆዱቁታል። የሰማሁት ነገር እውነት መሆኑን ባይኔ በብረቱ፤ ባፍንጫዬ ባነፍናፊው፤ በጆሮዬ በቅስሩ፤ አረጋገጥኩ። “ስራ የተፈጠረላቸው ወጣቶች” ከሰል ሲያቀጣጥሉ፤ ባለ አጭር ቀሚሶቹ ደግሞ በፈገግታ ያስተናግዳሉ።

በመጠኑም ቢሆን ለትዝብት ያህል ተቀምጬ፤ እዚህም እዚያም የሚብሎቀለቀው ሺሻ ጠረኑ ስላልተስማማኝ በፍጥነት “ቀነኒሳ ሺሻ ቤት”ን ለቅቄ ወጣው። ቀነኒሳ ግን በሀገራችን ከሱ ውጪ ሳንባ ያለው ሰው እንዲኖር አይፈልግም እንዴ?…እንደው ድህነቱ ቢቀር ሽሻውን በሩጫ ለማምለጥ ወደሊፈቱ መሮጥ አማረኝ !! ወደኋላየ ገልመጥ እያልኩና ‹‹አልሆንልህ አለኝ ማመን ›› እያለኩ… መቸስ ይህን ስራ ባለቤቱ ሳያውቀው ይከናወናል ማለት ይከብዳል ቢሆንም ግን … በየጉዳንጉዱ በሰሌንና ችፕውድ ተከልለው ሽሻ ከሚጨስባቸው ቤቶች የተሰበሰበ እቃ ፖሊስ ‹‹አቃጠልኩ›› እያለ እኛም ‹‹አበጀህ ›› እያልን የኖርን ህዝቦች …ይሄ ትውልድን ገዳይ ቆሻሻ ሱስ የሰው አናት ላይ መውጣቱ ሲገርመን እንዲህ ህንፃው አናት ላይ ያውም ከነፍሳችን የምናደንቀው ብርቅየ አትሌታችን የከፈተው ሆቴል ህንፃ ላይ መውጣቱ አሳዝኖናል !! 

ለአትሌታችን ያለን አክብሮት እንዳለ ሁኖ ይህን ድርጊት ግን ‹‹አይጠበቅም›› እንላለን !!
እንዲህ በስራቸው በአለም ፊት ያስጠሩን ታላላቅ ሰዎቻችን ለትውልዱ አርአያ ካልሆኑ …እሽ ማነው ለዚህ ህዝብ ከልቡ የሚያዝነው የሚቆረቆረው ?? እንኳን ጓዳቸው ውስጥ ሲፈፀም በዝምታ ማለፍ በምድራችን ላይም ይህ ነገር ድራሹ እንዲጠፋ በገንዘብ በዝናቸውና በሃሳብ ሊፋለሙት ይገባ ነበርኮ ! በድርጊቱ አዝኛለሁ እንደሚስተካከልም አምናለሁ ! 
ፀያፍ ነገርን የሚፈፀምበት ቦታ ታላቅነት ንፁህ ሊያደርገው አይችልም !! ጨረስኩ !

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 9 years ago on May 1, 2015
  • By:
  • Last Modified: May 1, 2015 @ 11:45 am
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar