www.maledatimes.com አምባሳደር ዘውዴ ረታ አረፉ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

አምባሳደር ዘውዴ ረታ አረፉ

By   /   October 9, 2015  /   Comments Off on አምባሳደር ዘውዴ ረታ አረፉ

    Print       Email
0 0
Read Time:4 Minute, 38 Second
አቻምየለህ ታምሩ
ታዋቂው ዲፕሎማትና የታሪክ ተመራማሪ አምባሳደር ዘውዴ ረታ አረፉ!
የሀያኛውን መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ በአራት ተከታታይ የታሪክ
ትውልዶች በመክፈል፤ የየትውልዱን ታሪክ ሰሪዎች የህይወት ታሪክና
ትሩፋቶቻቸውን በሚገባ በማሳየትና በመተንተንድ በይዘታቸውም ሆነ በቅርጻቸው
ትላልቅ ሊባሉ በሚችሉ ሶስት [አራተኛው በቅርቡ ገበያ ላይ ይውላል ተብሎ
እየተጠበቀ ነበር] ሰፊ ተቀባይነትን ያገኙ መጽሀፍት በመጻፍ በግራ ፖለቲካ
ልክፍት ተተብትቦ ሲዛባ የኖረውን ታሪካችንን ከምንጩና ትክክለኛ የታሪክ
ሠነዶችን በመያዝ እውነተኛውን የኢትዮጵያ ታሪክ ለትውልድ ካስተላለፉት
የኢትዮጵያ ታሪክ ጸሀፊዎችና ተመራማሪዎች መካከል ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው
አምባሳደር ዘውዴ ረታ በተወለዱ በ81 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለዩ።
አምባሳደር ዘውዴ ረታ ከታሪክ ጸሀፊነታቸውና ተመራማሪነታቸው ሌላ የትልቅ
ታሪክ ባለቤት አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ነበሩ። ባጠቃላይ አምባሳደር ዘውዴ ረታ
ለሀገራቸው በሙያቸው ብዙ ተግባራትን ያበረከቱ ታላቅ ሰው ነበሩ።
በመጽሐፍቶቻቸው ውስጥ የአምባሳደር ዘውዴ ረታ አጭር የሕይወት ታሪክ
እንደሚያሳየው፣ አምባሳደር ዘውዴ ረታ ነሐሴ 7 ቀን 1927 ዓ.ም አዲስ አበባ
ውስጥ ተወልደው ከ1933 ዓ.ም እስከ 1945 ዓ.ም ድረስም ቀድሞ
ደጅአዝማች ገብረማርያም ይባል በነበረውና ኋላ “ሊሴ ገብረማርያም” ተብሎ
በተሰየመው የፈረንሳይ ት/ቤት የመጀመሪያውንና የሁለተኛ ደረጃ
ትምህርታቸውን አከናውነዋል።
ከዚያም ከ1945 ዓ.ም እስከ 1948 ዓ.ም በጋዜጣና ማስታወቂያ መሥሪያ
ቤት፣ የቤተ-መንግሥት ዜና ጋዜጠኛና በራዲዮ ዜና አቅራቢነት ሠርተዋል።
ቀጥሎም ከ1948 ዓ.ም እስከ 1952 ዓ.ም ድረስ በፓሪስ የጋዜጠኝነት
ትምህርት በማጥናት በዲፕሎማ ተመርቀዋል። ከትምህርታቸው መጠናቀቂያ
በኋላ ከ1952 ዓ.ም እስከ 1954 ዓ.ም የኢትዮጵያ ድምጽ ጋዜጣና የመነን
መጽሔት ዳይሬክተር ሆነው ሰርተዋል። በኋላም ከ1954 እስከ 1955 ዓ.ም
ለአንድ ዓመት የኢትዮጵያ ራዲዮ ብሔራዊ አገልግሎት ዳይሬክተር ሆነው
ሰርተዋል። ከ1955 ዓ.ም እስከ 1958 ዓ.ም ደግሞ የኢትዮጵያ ወሬ ምንጭ
ዋና ዳይሬክተር ነበሩ። ከ1958 ዓ.ም እስከ 1960 ዓ.ም የማስታወቂያ
ሚኒስቴር ረዳት ሚኒስትር ሆነው ሰርተዋል። ከዚህ በመቀጠል ከ1960 ዓ.ም
እስከ 1962 ዓ.ም ድረስ ደግሞ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ
አስኪያጅ በመሆን አገልግለዋል። ከ1956 ዓ.ም እስከ 1962 ዓ.ም የፓን
አፍሪካ ኒውስ ኤጀንሲ ማኅበር ፕሬዝደንት ሆነውም ሰርተዋል። ከ1962 ዓ.ም
እስከ 1967 ዓ.ም ድረስ ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተዘዋውረው በሦስት
ዘርፎች አገራቸውን አገልግለዋል። እነዚህም የሚከተሉት ናቸው፡-
1ኛ. በፓሪስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሚኒስትር ካውንስለር
2ኛ. የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ም/ሚኒስትር
3ኛ. በሮም እና በቱኒዚያ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አምባሳደር ሆነው
ሰርተዋል።
በጠቅላላው በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የሀያ ሁለት ዓመታት
አገልግሎት። ካበረከተ በኋላ በደርግ ዘመን ከ1967 ዓ.ም ጀምሮ ስደተኛ ሆኖ
በአውሮፓ በቆየበት ዘመን በሮም የኢንተርናሽናል ድርጅት ውስጥ [IFAD]
ለአሥራ ሦስት ዓመታት በፕሮቶኮልና በመንግሥታት ግንኙነት ጉዳይ ኃላፊ ሆኖ
ሠርቷል።
አምባሳደር ዘውዴ በ1959 ዓ.ም ጋብቻውን መሥርቶ ከሕግ ባለቤታቸው
ከወይዘሮ ገሊላ ተፈራ ጋር ሦስት ልጆች አፍርተዋል። ከንጉሠ ነገሥቱ
መንግሥት የምኒልክ የመኮንን ደረጃና የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ አዛዥ መኮንን
ኒሻን ተሸልመዋል። እንዲሁም ከአፍሪካ ፣ ከእስያና ከአውሮፓ በድምሩ ከሀያ
ሁለት አገሮች የታላቅ መኮንን ደረጃ ኒሻኖች ተሸልመዋል። ከዚህ ቀደም
በ1945 እና በ1946 ዓ.ም ካዘጋጇቸው አራት ቲያትሮች ሌላ ፤ በ1992 ዓ.ም
የኤርትራ ጉዳይ፤ በ1997 ዓ.ም ተፈሪ መኮንን ረጅሙ የስልጣን ጉዞና በ2004
ዓ.ም ደግሞ የቀድሞ ኃይለሥላሴ መንግሥት የተሰኙትን መጻሕፍቶች ጽፈዋል።
የአምባሳደር ዘውዴ ረታ «የኤርትራ ጉዳይ» ብለው በጻፉት መጽሀፋቸው ውስጥ
ተጽፎ የቀረበው ታሪክ በሶስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ የተመረኮዘ ነው፡-
1ኛ. አብዛኛው የኤርትራ ሕዝብ ፣ ከባዕድ አገዛዝ ለመላቀቅና ወደ መሠረት
አገሩ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ኢትዮጵያ ወይ ሞት ብሎ በመታገል ምን ያህል
መከራና ፈተና እንደተቀበለ፤
2ኛ. የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር ለማዋኃድ
በአራቱ ኃያላን መንግሥታት ዳኝነትና ቀጥሎም በተባበሩት መንግሥታት ሸንጎ
ላይ ለብዙ ዓመታት ያደረገው ፋታ የሌለው ሙግት ምን ውጤት እንደሰጠ፤
3ኛ. በተባበሩ መንግሥታት ሸንጎ ላይ ኤርትራ በፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ጋር
እንድትቀላቀል፣ ፍርዱ እንዴት እንደተወሰነና፣ ከዚያም ለአሥር ዓመታት
የተካሄደው የፌዴሬሽን አስተዳደር በምን መልክ ይሠራበት እንደነበረና በኃላም
በምን አኳኋን እንደፈረሰ እውነተኛውን ታሪክ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች
እንዲያውቁት በዝርዝር በማዘጋጀት ረገድ ከፍ ያለ ጥረት አድርገዋል።
«ተፈሪ መኰንን ረዥሙ የሥልጣን ጉዞ» የሚለው ሁለተኛ የታሪክ መጽሀፋቸው
ደግሞ በሐምሌ 1997 ዓ.ም ለአንባቢዎች የቀረበ ሲሆን መጽሐፉ ቀዳማዊ
ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ-ነገሥት ሆነው ኢትዮጵያን መምራት ከመጀመራቸው በፊት
ደጃዝማች ተፈራ መኰነን ከሐረር ጠቅላይ ገዥነት ተነስተው በምን አኳኋን
ባለሙሉ ሥልጣን አልጋወራሽ ለመሆን እንደበቁና ዘውድ እስከጫኑበት ጊዜ
ድረስ የኢትዮጵያን መንግሥት እንዴት ሲመሩ እንደቆዩ የሚያስረዳ ነው።
ከአፄ ምኒልክ ሕይወት ፍጻሜ በኋላ በአገራችን በያለበት እየተቀመመ ይሰራጭ
በነበረው ወሬ መሰረት ተፈሪ መኮንን የኢትዮጵያ መሪ ለመሆን የበቁት ልጅ
ኢያሱን በኩዴታ ጥለው ንግሥት ዘውዲቱን በሐኪም መርፌ አስገድለው ነው
የሚል ነበር።
ደራሲው ግን በዚያን ዘመን የተካሄደውን የኢትዮጵያን ታሪክ ለረዥም ጊዜ
ምርምርና ጥናት በማካሄድ፡-
1ኛ. ልጅ ኢያሱ ከሥልጣን እንዴት እንደወረዱ ፣ ወይዘሮ ዘውዲቱ ምኒልክ
ንግሥተ ነገሥታት ተብለው ዘውድ ለመጫን እንደበቁ፤
2ኛ. ለመንግሥቱ ሥራ አመራር የራስ መኰንን ልጅ ተፈሪ መኰነን ባለሙሉ
ሥልጣን እንደራሴና አልጋ ወራሽ እንዴት ሆነው እንደተመረጡ፤
3ኛ. ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ ከዚህ ዓለም በሞት እንዴት እንደተለዩ
ትክክለኛውን ታሪክ ለአንባቢዎች በማቅረብ ብርቱ ጥረት አድርገዋል።
በመጨረሻም አምባሳደር ዘውዴ ረታ «የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት»
በሚል ርዕስ በጻፉት ባለ811 ገጽ መጽሀፍ ኢትዮጵያን ለአርባ አምስት ዓመታት
ያህል በንጉሠ ነገሥትነት ሲያስተዳድሯት የኖሩት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ
የመጀመሪያዎቹ ሃያ አምስት ዓመታት የመንግሥታቸው አመራር ታሪክ ምን
ይመስል እንደነበር ተንትነው አቅርበዋል።
መጽሀፉ ውስጥ ከተካተቱት የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ሃያ አምስት ዓመታት ዘመነ
መንግሥት ውስጥ ታሪኮች ውስጥ፡-
1ኛ . የፋሽስት ጣሊያን ወረራ አመጣጥ፤
2ኛ. የኢትዮጵያን ነጻነት ለማዳን ንጉሠ ነገሥቱ በዤኔቭ የመንግሥታት ማህበር
ሸንጎ ላይ ያደረጉት ሙግትና በመጨረሻም ሊግ ኦፍ ኔሽን ያደረገው አሳዛኝ
ውሳኔ፤
3ኛ. ሙሶሊኒ ከሂትለር ጋር ተሰልፎ የአውሮፓን መንግሥት በጦር ሲወጋ ፣
እንግሊዞች የኢትዮጵያን ነፃነት ለማስመለስ አገራችንን ከያዙ በኋላ የጫኑብን
የሞግዚት አስተዳደር እንዴት እንደነበር፤
4ኛ. ነፃነታችን ከፋሽስት እጅ ከተመለሰ በኋላ ከእንግሊዞች የሞግዚት አስተዳደር
ለመላቀቅ ምን ያህል ድካም እደጠየቀ፤
5ኛ. ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በምሥጢር ወደ ስዌዝ ካናል ተጉዘው ከአሜሪካው
መሪ ከፕሬዚዳንት ሩዝቬልት ጋር ያደረጉት ንግግር ይዘት፤
6ኛ. ኢትዮጵያ ከእንግሊዞች የሞግዚት አስተዳደር ከተላቀቀች በኋላ በአገር
ውስጥ የሁለት ሰዎች [መኮንን ሀብተወልድና ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ]
የሥልጣን አነሳስና ትብብር ንጉሠ ነገሥቱን ምን ያህል እንደአሳሰባቸው፤
7ኛ. ከእነዚህ ከሁለቱ ሰዎች መካከል የሥልጣን ኃይላቸው አስጊ ሆኖ
የተገመተውን ጸሐፊ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስን በሽረት ከካቢኒያቸው ለማራቅ
ንጉሠ ነገሥቱ የወሰዱትን እርምጃ አምባሳደር ዘውዴ በዝርዝር በመግለጽ
ለኢትዮጵያ ሕዝብ እውነተኛ ታሪክ አቅርበዋል።
አምባሳደር ዘውዴ የኢትዮጵያን ታሪክ በሚመለከት ሊጽፉ ቃል ከገቧቸው አራት
መጽሀፍት መካከል አራተኛውንና የመጨረሻውን መፍሀፋቸውን በመጻፍ ላይ
እንዳሉ ሞት ቀደማቸው። በሰው ላይ ሞትን የሚያህል እዳ አለና አምባሳደር
ዘውዴም ያሰቡትን ሁሉ ለመፈጸም ባለመቻላቸው እጅግ ያሳዝናል።
እግዚአብሔር ነፍሳቸውን በገነት ያኑረው። ለወዳጆቻቸውና ለቤተሰባቸው በሙሉ
ጽናትንና ብርታትን እግዚያብሄር እንዲሰጣቸው ከልብ እመኛለሁ።

Melkam-selam Molla's photo.

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 9 years ago on October 9, 2015
  • By:
  • Last Modified: October 9, 2015 @ 11:04 am
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar