www.maledatimes.com እውነት እንነጋገር! - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

እውነት እንነጋገር!

By   /   January 31, 2015  /   Comments Off on እውነት እንነጋገር!

    Print       Email
0 0
Read Time:5 Minute, 2 Second

 

በአገራችን ከሚካሄዱ ማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች( ትርምሶች) ገለል ብሎ ከዳር መቃኘት ለሞከረ ብዙ ነገሮችን መታዘብ ይቻለዋል፡፡ ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ችግሮች ተባብሰው መቀጠል፤ የተቃዋሚ ድርጅቶች(ሓይሎች) የውስጥ ችግር፤ አንዳንድ ድርጅቶች(ሃይሎች) የመረጡት ቅጡ ያልታወቀ መደዴ የትግል መንገድ፤ የአንዳንዶቹ በተለይም የዲያስፖራው መለያ እየሆነ የማጣው ዓላማው ግልፅ ያልሆነ ጭፍን ግብግብ፤ በቀደምት እንስቃሴያቸው አንቱ የተባሉ አንዳንድ ግለሰቦች ባልተጠበቁበት ቦታ መገኘት፤ ግለሰቦችና ድርጅቶች ውስጥ ያለ ፅንፈኝነት፤ ጥላቻ፤ መፈራረጅ፤ ተጠራጣሪነት፤ አለመደማመጥ፤ ፍፁም ዘረኝነት፤ ወ.ዘ.ተ የወቅቱ ፖለቲካ ባህላችን ልዩ ባህሪያቶች ናቸው፡፡ ከላይ ለመጥቀስ የሞከርኳቸውና ሌሎች ምክንያቶች ተዳምረው ሲታዩ አንዲት የተሸለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር የሚደረግ ትግል ሳይሆን በዝና የምናውቀውን የባቢሎን ታሪክ ለመድገም የሚደረግ ግብግብን መልክ የያዘ ነው፡፡
ልብ ብለን ከሆነ በየግዜው እንደ አዲስ የሚጀመሩና ብዙ የተባለላቸው እንቅስቃስዎችም ቢሆኑ ለውጥ ያመጣሉ ተብለው ሲጠበቁ ብዙም ሳይራመዱ ቆመው አሊያም የዚያ የእብድ ሰፈራችን ፖለቲካ ማድመቂያ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ቀደም ብለው የነበሩ ትልልቅ ችግሮችን እንደ ችግር ቆጥሮ ለእርሱ መፍተሄ ለማምጣት መስራት ለእኛ አገር ፖለቲካ ባዳ ነው፡፡ የተሞከሩ ቢኖሩም ትርምስንና ለእንዲህ አይነት ነገር የሚሰጠውን ስምና ዘለፋ መቛቛም አቅቷቸው ብዙ ያልተጓዙ ናቸው፡፡ ለጥራዝ ነጠቅ የፖለቲካ ባህላችን መፍትሄ ከመሻት ይልቅ ልምድና እውቀት የማይጠይቀው ግርግር ውስጥ ገብቶ የችግሩ ተዋናይ መሆን የወቅቱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፋሽን ነው፡፡ ችግር ፈቺ ናቸው ተብለው የተጀመሩ የፖለቲካ ትግሎች የተነሱበትን ዓላማ ትተውና ይባስ ብለው ችግር ሆነው ሲመጡ እያየን ነው፡፡
አብዛኞች የተቃዋሚ ድርጅቶች(ሃይሎች) የመጨረሻ ግባቸው ወያኔን መጣል ብቻ ሆኖ እናየዋለን፡፡ ይህ አካሄድ ራሱን የቻለ ትልቅ ችግር ነው፤ በምንም መመዘኛ ስልጣን ላይ ያለን አምባገነን ለመጣል ብቻ መስራት ያለብንን ችግር የሚፈታ ስርዐትን ይዞ ይመጣል ማለት አይደለም፡፡ምክንያቱም አሁን እኛ አለብን የምለው ችግር አምባገነን መንግስትን ከመጣልና አዲስ መንግስት ስልጣን ላይ ከመተካት ያለፈ ነውና፡፡ በየቦታው በተበታተነ መልኩ የሚካሄድ የተቃውሞ እንስቃሴ የራሱን ችግሮች ሳይፈታ የመንግስት ስልጣንን በሌላ ተክቶ ሰላምና ዲሞክራሲን ያመጣል ብሎ ማሰቡ ፌዝ ነው የሚሆነው፡፡
የዚህ ውጤት አልባ የተቃውሞ ፖለቲካችን በተለያዩ ችግሮቹ የምንመኘውን ፍትህ እና ዲሞክራሲ ሲያቀዳጀን ካለመቻሉ ባለፈ ብዙ ዋጋ እያስከፈለን መሆኑንም ልብ ልንለውይገባል፡፡ የኔም የዚህ ሁሉ መንደርደሪያዬ ማሰሪያው ይሄነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በገዢው ፓርቲ ዕይታ አብዛኞቹ በሃገርም ውስጥም ሆነ በውጪ ያሉ ድርጅቶች(ሃይሎች) እንደፖለቲካ ድርጅት መቆጠራቸው ካበቃ የቆዩ ይመስላል፡፡ ከዚህ የፖለቲካ ምህዳር መጥበብ ጋር ተያይዞ የተቃዋሚ ድርጅቶች አመራሮች፤ ደጋፊዎቻቸው፤አክቲቪስቶች፤ ጋዜጠኞችና በሌሎች ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን መታሰር፤ መዋከብ፤ሃገርን ጥሎ መሸሽና ሌሎች ጫናዎች በተደጋጋሚ መፈፀማቸው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡
ይህንን ተከትለው ሰላማዊ ትግልን ትተው በሌላ አማራጭ የትግል መንገድ እንታገላለን ያሉ ድርጅቶች( ሃይሎች) የተፈጠሩበት ሁኔታ የቅርብ ግዜ ትዝታችን ነው፡፡ አንዳንዶቹ ከምርጫ 97 በኋላ የመጣውን የመንግስት ጫናና እርምጃ ለዚህ ውሳኔ ያበቃቸው ቢሆንም ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ያለየናቸው አንዳንድ ሃይሎች ከዚያ ቀድመው በትጥቅ ትግል ስም እንስቃሴ ላይ መሆናቸው የሚታወቅ ነው፡፡
በሃገራችን በፖለቲካው ሜዳ የብዙ ነገሮች መቀየርና መፈጠር ምክንያት የሆነው ከ97 ምርጫ በኋላ ሰላማዊ ትግልን ትቶ ሁለገብ የትጥቅ ትግል አማራጭ የሌለው ነው ብሎ የጀመረው ግንቦት ሰባትም ከ97 በኋላ ተፈጠሩ ለሚባሉ ነገሮች የአንበሳውን ድርሻ የሚይዝ ነው፡፡ ከሌሎች በተለየ ግንቦት7ን ላለንበት ፖለቲካ ማሳያና እንደምሳሌ ማንሳቴም ያለምክንያት አይደለም፡፡
በዚህ ፅሁፌ የሃሳቤን መሃከል ግንቦት7ን ያደረግሁበትን ተያያዥ ጉዳዮች ለመጥቀስ እሞክራለሁ፤
በመጀመሪያ የብዙ ሰዎች ተስፋ የነበረው የቅንጅትን ወራሽነት ይዞና በመንግስት የተገታውን ትግል በሌላ መንገድ አስቀጥለዋለሁ ብሎ በመነሳቱና ከዚያ ጋር ተያይዞ በሚመጡ ነገሮች ስሙ ስለማይጠፋ፤
ሁለተኛው በዚህ የግንቦት7 ስብስብ ውስጥ ህዝቡ ከሚያውቀው እውነታ ጋር ፍፁም ተቃራኒ የሆኑ እውነታዎችን በቅርበት ለመመልከት በመቻሌና ይህም ዛሬ ላለንበት ችግር ሰበብም ነው ብዬ ስለማምን እንዲሁም ከዚህ ስብስብ የመነጩ ናቸው በተባሉ ጉዳዮች በተለያዩ ግለሰቦች፤ ድርጅቶችና በአጠቃላይ በተቃውሞ ፖለቲካ እንቅስቃሴያችን ላይ እየደረሰ ያለው አሉታዊ ጫና እየተባባሰ መምጣቱ ዋነኘ ምክንያቶቼ ናቸው፡፡
ግንቦት7 ሁለገብ የሚለውን የትግል መንገድ ይዤ እታገላለሁ ባለ ጥቂት ግዜ ውስጥ ነገሮችን ለመዘጋጋትና እርምጃ ለመውሰድ ወደኋላ የማይለው የኢህአዴግ መንግስት ይህን ይመክትልኛል ያለውንና አስደንጋጭ የሆነውን የፀረ ሽብር ህግ ይዞ ከተፍ አለ፡፡ ይህን አፋኝ ህግ ለማስፈፀም ይረዱኛል ያላቸውን ነገሮች ተንትኖ አስቀመጠ በዚህም አላበቃም አሸባሪ ያላቸውን ድርጅቶችና ስብስቦችን ስም ዝርዝር ይፋ አወጣ፡፡ በዚህም ዝርዝር ውስጥ ዋና ተጠቃሽ የነበረው ግንቦት7ም የቻለውን ያህል በተለያዩ የአለም ክፍሎች ያሉትን አባለትና ደጋፊዎች ሊያሰባስብ የሚችልባቸውን መዋቅሮች ፈጥሮ መንቀሳቀስ ጀመረ፤ ቀድሞም ህዝብ ጋር የነበረው የ97 ምርጫ ቁጭት ለግንቦት7 ቶሎ መታወቅና የአባላትና የደጋፊውን ቁጥር ለማብዛት እጅጉን ረዳው፡፡ በዚያው ሰሞን ከሃገር ውስጥም ከሶማሌ ክልል ውጪ በተቀሩት ሁሉም ክልሎች የተደረጃ መዋቅር እንዳለው የድርጅቱ ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ደጋሞ ሲናገር ተሰማ፡፡ ይህን የሰጋው የወያኔ መንግስት በግንቦት7ና በሌሎች ሃይሎች ይመጣብኛል ያለውን ኪሳራ አስልቶ የሚከላከልባቸውን የተለያዩ መንገዶች ሲያበጃጅ ተመልክተናል፡፡
በዚህ አይነት ሂደት ውስጥ ስንጓዝ ስድስትና ሰባት አመታት አለፈ፡፡ ግንቦት7ም ሆነ ሌሎች  ሃይሎች እዚህ ግባ የሚባል ስራ ሰርተው ሳያሳዩን እንሱ የነኩትም እዲሁም የማያውቁትም የዚህ ፀረ-ሽብር ህግ ሰለባ መሆን ችለዋል፡፡ መንግስትም ለስርአቱ ስጋት የመሰሉትን በሙሉ በሽብርተኝነት መነፅር በመመልከት ብዙ ግለሰቦችን፤ ፖለቲከኞችን፤ ጋዜጠኞችንና በሃገሬ ጉዳይ ያገባኛል ያሉ ዜጎች ወደ እስር ቤት ሲወረወሩ ቆይቷል፡፡ ከዚህም ባለፈ በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማህበራት በተለያየ መንገድ ሲያሸመደምድ አስተውለናል፡፡
ይህ ሲባል ግን ገና ከመነሻው ከሃገር ውስጥና ከሃገር ውጪ ብዙ ወቀሳዎች የበዙበት የፀረ- ሽብር ህጉ ሰለባ የሆኑት ግለሰቦችና ተቛማት በሙሉ ከግንቦት7ና ከሌሎች በሽብር የተፈረጁ ሃይሎች ጋር ግንኙነት አልነበራቸውም ማለት አይቻልም፡፡ ግንቦት7 በዘረጋላቸው ዝርክርክ መስመር ሄደው የማዕከላዊና የቂሊንጦ ሲሳይ የሆኑትን ግለሰቦች ቤቱ ይቁጠረው፡፡
ከግንቦት7 ጋር ንክኪ አላቸው ተብለው ለእስራት፤ለእንግልትና ከሃገር መሰደድ የበቁ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ጉዳይ ስንመለከት አንዲት ነገር ሳይፈጠር ሁልግዜ ግንቦት7 በጠራቸው ቦታዎች በሙሉ ገንዘብና ግዜውን የሚለግስ ዲያስፖራ ባየን ቁጥር “ምንም አልሰራችሁም ” የሚለውን የአባላትና ደጋፊዎች ወቀሳ ብቻ በመፍራት ያልተጠናና ጭራሽ አዋጭ ያልሆነ የኤርትራ ውስጥ ትግል ተቀላቅለው የሻእቢያን ድብቅ አጀንዳ ማስፈፀሚያና መቀለጃ የሆኑ ወጣቶችን ባሰብን ቁጥር፤ የተቃውሞ ሜዳን የብቻ ለማድረግ በሚደረግ ግብግብ ውስጥ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶችንና ሲቪክ ማህበራትን ለማፍረስ አልያም ለመቆጠር የሚካሄደውን የፖለቲካ ብልግና ልብ ባልን ቁጥር፤ ያላደረጉትን አደረግን፤ ያልደረሱበትን ደረስንበት ተብሎ የሚነገር የውሸት ፕሮፓጋንዳቸውን ዘወትር በሰማን ቁጥር “ጎመን በጤና” ከማለት ባለፈ በግንቦት7 ላይ ተስፋ ማድረግ ካቆምን ሰንበት ብለናል፡፡
አሁንም ቢሆን  ሃገርቤት ውስጥ ያለው ከግንት7 ጋር በተያያዘ በወገን ላይ የሚደርሰው እስራትና እንግልት እየበዛ የመጣበትን ሁኔታ እያየን ነው፡፡ ብዙ ወጣት ፖለቲከኞች፤ አመራሮ፤ አክቲቪስቶች፤ ጋዜጠኞችና ብሎገሮች ለእስራትና ለስደት ተዳርገዋል፡፡ የብዙዎቹ ጉዳይ ከመንግስት ስጋት የመነጨ ተራ ክስ ቢሆንም ሙሉ ለሙሉ በግንት7 መዋቅር ስር ወድቀው የተገኙ እንዳሉም ነው፡፡ ለዚህ ጉዳት ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም በተጠያቂነት የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው ግንቦት7 በዚህ ጉዳይ ላይ አንዳች ነገር ሲል አልተስተዋለም፡፡
ከግንቦት7 ጋር ንክኪ አላችሁ ተብለው በስህተት የተከሰሱ ግለሰቦችን በተመለከተ አንዳች ነገር ለማለት ፍቃደኛ ሆኖ አያውቅም፤ በየግዜው ከዲያስፖራው ከሚሰበሰበው ገንዘብ ለእስራት በመዳረጋቸው ለከፍተኛ ችግር የተዳረጉ ቤተሰቦቻቸውን ሲረዳ አላየንም፤ የሚረዱበትን መንገድ ፈልጎም አያውቅም፤ ሌላው ቢቀር ሃገር ጥለው የወጡትን እንኳን ባሉበት ቦታ ለማገዝ ሲሞክሩ አልታዩም፡፡
ይህን እውነት ብዙዎች የሚያውቁትንና የሚረዱት ቢሆንም የሚያውቁትን ያህል ግንቦት7ን በተመለከተ ጨከን ብለው ለመናገር ብዙ አልደፈሩም፡፡ የግንቦት7ን  በአደባባይ መናገር ትግልን የሚጎዳና ዞሮዞሮ ጥቅሙ ለኢህአዴግ ነው ብለው የሚያስቡም ይኖራሉ “ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ” የሚለው የትግርኛ ብሂል ለዚህ አይሰራም፡፡ ተስፋ የማይጣልበት ተስፋ ማድረግ ነው ትግል የሚጎዳ፤ ከወያኔ ብቻ ሳይሆን የብዙዎች እስራትና እንግልት ከመሆን ባለፈ ፋይዳ ከሌላቸው ግንቦት7ና መሰሎቹ ይሰውረን አሜን፡፡
በማስረሻ ባዴጋ
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 9 years ago on January 31, 2015
  • By:
  • Last Modified: January 31, 2015 @ 8:44 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar