www.maledatimes.com ከአረብ ሀገር እስከ ደቡብ አፍሪካ የስደተኛው ሮሮና የመንግስት ቸልተኝነት ! ይድረስ ለክቡር ዶር ቴዎድሮስ አድሃኖም - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ከአረብ ሀገር እስከ ደቡብ አፍሪካ የስደተኛው ሮሮና የመንግስት ቸልተኝነት ! ይድረስ ለክቡር ዶር ቴዎድሮስ አድሃኖም

By   /   April 21, 2015  /   Comments Off on ከአረብ ሀገር እስከ ደቡብ አፍሪካ የስደተኛው ሮሮና የመንግስት ቸልተኝነት ! ይድረስ ለክቡር ዶር ቴዎድሮስ አድሃኖም

    Print       Email
0 0
Read Time:6 Minute, 38 Second

የማለዳ ወግ… ሀዘን የወለደው ደካማ ስሜት ፍርሃት !
* በጨለመው ሚያዝያ ፣ የጨነቀ እለት …
=========== =========== ===========

በማለዳው አነሳሴ እንደለመድኩት በስደቱ ዙሪያ ገብ የሆነውንና እየሆነ ስላለው ልሞነጫጭር ፣ ልብተከተክ አልነበረም … ከትናንት ከትናንት በስቲያ ጠዋት ፣ረፋድና ተሲያት ፣ ምሽት ፣ በደረቁ ሌሊት እያቅበጠበጠኝ ስልኬን አንስቸ ወደ ሊቢያ ዋና ከተማ ትሪፒሊ ወደ ማትረጋው ቢንጋዚና ሚስራታ የደዋወልኳቸውን ስልኮች ተመለከትኩ ። ከወዳጆቸ የደረሱኝን ሁለት ሶስት አድራሻዎችና እዚህ ጅዳ ያለ ሊቢያዊ ጓኛየ አድራሻቸውን አፈላልጎ የሰጠኝን ሌሎች ሰብሰብ ያሉ ወንድሞችን አግኝቻለሁና ደጋግሜ ቁጥሮችን አየኋቸው …

የሰበሰብኳቸው ስልኮችን ደጋግሜ የደወልኩባቸው ስለሆኑ መፈላለጉ ጊዜ አይወስድብኝም ፣ ከስልኬ ፊት ለፊት ተደርድረዋልና እየመራረጥኩ … እደውላለሁ … እንቅልፍ ለአመል ያህል ተኝቸ ብንን ብንን ማለቱ ቢያስቸግረኝ ይለይለት ብየ እንደ ቀደመው የማለዳ ወግ ለመጻፍ ሳይሆን ባለፉት መራራ ሁለት የሃዘን ቀናት ያነጋገርኳቸው ሊቢያ የሚገኙ እህት ወንድሞቸን ሳነጋግራቸው በመቅርጸ ድምጼ ያስቀረኋቸውን ድምጾች መልሸ መላልሸ ማደመጥ ይዣለሁ …

“ቤንጋዚ ውስጥ ነን !” ያሉኝ ሌሎች ወንድሞች ጋር ቃለ ምልልስ እያደረግኩ ከሊቢያ አውጡን የሚለውን የድረሱልን እተሰማሁ እያለ ይቆራረጥ የነበረው የስልክ መስመር እራሹን ተቋርጦብኝ ስብተከተክ ፣ ሌሎች በሊቢያ የሚገኙ እህቶችን በሌላ መስመር አገኘሁ ! የአድራሻቸውን መስመር ያገኘሁት የሆነው ያንገበገበው ከእኔ ቢጤ ቅምጥል ኩዌት ከሚገኝ ስደተኛ ወዳጀ ነው ። እንዲህ ይላል ” ሃይ ነብይ እንዴት ነህ በካይሮ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አድራሻ ማግኝት የሚቻለው በምንድነው ልጆች ይፈልጋሉ ሊቢያ ያሉ …ካንፖኒ ውስጥ ነው የሚሰሩ ፣ ወደ 14 ልጆች መንቀሳቀስ መውጣት አልቻሉም ፣ ችግር በተፈጠረበር ቦታ ላይ ነው ያሉት ፣ ወደ ሀገር መግባት ይፈልጋሉ ” ከመልዕክቱ በኋላ አድራሻቸውን ላከልኝ … ሁሉንም የሰበሰብኳውን አድራሻዎች ደዋወልኩ … አንዳንዴ ስልኩ ይነሳል ፣ አንዳንዴ አይነሳም ፣ አንዳንዴ እያወራን በመካከል ይቋረጣል ፣ አንዳንዴ ከአጠገቤ ያሉትን ያህል የቀረበ ድምጽ ይሰማኛል …

ጥርት ያለው ድምጽና መልዕክቱ …
===================

ንጹህ ድምጹ ከአመታት በፊት በስራ ኮንትራት መጥተው በስራ ላይ ካሉት እህቶቸ እንደሆነ አላጣሁትም ፣ ” እባክህ ከሊቢያ ወደ ሀገራችን የሚያወጣን አካል አፈላልግልን ? ለሚዲያ ሽፋን ሳይሆን ከጭንቅ እንድንወጣ እርዳን ? ምንም ቢሆን ሀገራችን መግባት ነው የምንፈልገውና እርዳን ? የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዜናውን ሲናገር በዚህ ቁጥር ደውላችው ተረዱ አላለም ፣ ያሳዝናል ፣ ለማን አቤት እንበል? የምትችል ከሆነ እርዳን ? ” በሚለው ተማጽኖ ድምጻቸውና አልፎ አልፎ እኔኑ አላምነን እያሉ በምናደርገው ያልተናበብንበት ውይይት እኒሱ መሆናቸውን እለየዋለሁ !

ተቆራራጩ ድምጽና የተቆራረጠው ተስፋ …
==========================

ተቆራራጩ ድምጽ ደግሞ በሱዳን አድርገው የሰሃራን በርሃ በስቃይ ቆርጠው መጥተው ፣ ባንዷ ሁከት በማይለያት ከተማ የተኮለኮሉ ወንድሞች ናቸው ። በማይገኘው መስመር አልፊ ሳገኛቸው ስሜቴን ይፈታተኑታል ፣ የሆነውን በተባራሪ ወሬ እንጅ እንደ ትርፖሊ ነዋሪ እህቶቸ ክፉ ደጉን አላዩትም ፣ ያ መሆኑ በጀ ! …ብቻ ወደ እንሱ ተስፋ ምድር አውሮፖ ሊሄዱ አስበው ፣ በ28 ( ሰላሳ ናቸውም ይባላል) በጽነፈኛው ደዕሽ ISIS ጨካኝ አራጆች ተፈጸመ የተባለውን ግድያ ሰምተው ተደናግጠው ባንድ አሳቻ ቦታ ተደበወቀዋል ” ወደ ሰላሳ እንጠጋለን ” ብለውኛል ! የሚቀመስ ምግቡ ቀርቶ በረሃ ቆርጠው ቀዝቃዛ ውሃ ጠግበው ያልጠጡ ችግረኞች ናቸው ። የእኒህ ችግረኛ ወንድሞች ስልክ ደከም ያለች ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ይመስለኛል ውይይታችን ብዙም አይሰማም ፣ ችግሩን መገመት አያዳግትም … ብቻ ” የት እንሒድ ? ” ብለው ከሀገር ያስለቀቃቸውን ችግር ፣ ቸነፈርና ድህነት ሳይሆን የአስተዳደር በደልና ስራ አጥነት ለዚህች ቀን አደንዳደረሳቸው የቆመው ጀሮየ ሰምቷል … እኒህኞቹ ወደ ሀገር መግባት አይፈልጉም ፣ እዚያው መቆየት ደግሞ አይፈልጉም … ብቻ ምርጫቸው አለም ችግራችን ሰምቶ ወደ ሶስተኛ ሀገር ያውጣን ባዮች ናቸው ! የተቆራረጠው ተስፋ መልዕክትና ተስፋ … ሲናገሩት ያማል …

ሰማሁት … ሰማሁት ፣ ተስፋየ በተነው !
===========================

ከሞቱት ሰማዕት በላይ ውስጤን ያወከውና ልብን የሚሰብር ሆነው ካገኘኋቸው መካከል በትሪፖሊ ውስጥ በአንድ ሆስፒታል በስጋት ላይም ሆነው ስራቸውን በመስራት ላይ ያሉ 14 የሚደርሱ እህቶች ይገኙበታል ። ከመካከላቸው ያነጋገርኳቸው ከሶስት ባይበልጡም ፣ የሶስቱ ጭንቀት ገላጭ ደረቅ አስተያየት የሁሉንም ይገልጸዋል ፣ በሚወጡበት ጉዳይና ባሉበት ሁኔታ ስንወያይ አልፎ አልፎ ባንግባባም ፣ ስንለያይ ፍላጎቴን አስረድቸ ተግባብተን ነው … ” አየህ ወንድም እኛ ስለታረዱት ወንድሞቻችን የሰማነው በሚዲያ ነው ፣ ከሁለት አመት በፊት ወደ ሊቢያ ትሪፖሊ መጥተን ስራችን እየሰራን ነው ፣ ስራ ላይም ሆነ ቤት ውስጥ ሆነን ሁሌም የጥይት ድምጽ ከከተማ ውጭ ፣ በርቀት እንሰማለን … አሰሪዎቻችንን ወደ ሀገራችን ስደዱን ስንላቸው ከተማ ውስጥ ችግር የለም እያሉ ያጽናኑናል ፣ በእርግጥም እስካሁን ከስራ ቦታ ወጥተን በቅርብ ርቀት ባለው በተዘጋጀልን ቤት እናርፋለን ፣ እስካሁን ችግር የለብንም ፣ አሁን ግን የወንድሞቻችን መታረድ መሪርና አስደንጋጭ ዜና ስንሰማ ሰግተናል ፣ ተሸብረን ጨንቆናል …አንተ ምን ትረዳናለህ ? ለሚዲያ ሽፋን ብቻ ከሆነ አይጠቅመንም ፣ እኛ የምንፈልገው በሰላም ከሊቢያ መውጣት ነው ፣ ጭንቅ ላይ ነን ፣ የሚረዱንን ሰዎች አገናኘን ፣ እባክህ እርዳን ? ” ያሉበትንና የገለጹበትን ድምጽ ደጋግሜ እያዳመጥኩ ተጨናንቄያለሁ ! ” ከሊቢያ እንድንወጣ ብቻ እርዳን !” ብለው ከፍቷቸው አዝነው እየተማጸኑኝ ነበርና እኔም የቻልኩትን ለማድረግ እሞክራለሁ በሚል ቃል ገብቸ ላበረታታቸው ስሞክር አልተቻለኝም …አንዳንዴማ የጨነቀ እለት ይከፋ የል …ከፍቷቸው የሚሰጡት ጥርጣሬ የሞላበት አስተያየት ውስጤን ያውከው ያስቸግረኝ ይዟል … ግን ቻል አደርገዋለሁ ! … ማድረግ መሆን አለመቻል በተስፋ ተሞልቸ ስኖር ተስፋየ በተነው …

የግብጽ ኢንባሲና እህቶች …
===================

ጨለማው ሚያዝያ 12 ቀን 2007 ዓም ሰኞ ማለዳ እኩለ ቀን ገደማ ነው ፣ ከማለዳው እስከ እኩለ ቀን የብዙ ወገኖች ትጋት የታከለበት ጥረት ተሳክቶ ሊቢያ ያሉት ወገኖቻችን ይረዳሉ የተባሉ ኃላፊዎች አድራሻ ተገኘ ፣ በአድራሻው ወደ ሃገረ ግብጽ ካይሮ ደወልኩ ፣ ኃላፊውን አግኝቸ ሀገር ቤት መግባት ለሚፈልጉት እያደረጉ ስላለው ጥረት ጠየቅኳቸው ” ጉዳዩ ገና እየተጣራ በመሆኑ መረጃ ልሰጠህ አልችልም ፣ ነገር ግን በተለያዩ የሊቢያ ክፍል ያሉ ወገኖቻችን እየተደዋወልን ነው! ” የሚል ድፍን ያለ መልስ ሰጡኝ ። ያገኘሁትን አድራሻ ለመለጠፍ ባስፈቅድም ፈቃደኛ አይደሉም ! በኢንባሲው መደበኛ ስልክ መስጠት እንደምችል ግን መከረውኛል ። አዎ አለቆቻቸውን ማነጋገር አለባቸው ! አለቆቻቸው ደግሞ የተቸገሩት የሚደውሉና እርዳታ የሚያገኙበት እስካሁን ግልጽ ያለ አድራሻ አላስተላለፉም … ያነጋገርኳቸው ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉት የግብጽ ኢንባሲ ትሁቱን ዲፕሎማት በተለይም ወደ ሀገር ቤት ለመግባት ፍላጎት ያላቸውን ትሪፖሊ የሚገኙ እህቶች አድራሻ ሰጠኋቸውና አደራ ብያቸው ተለያየን !

አመሻሹ ላይ ወደ ትሪፖሊ ደወልኩ ፣ ስልኩ ተነሳ ! ከሰላምታ በኋላ አድራሻቸውን እንደሰጠሁ ተናግሬ ሳልጨርስ ” አዎ ደውለውልን ነበር ፣ ትሪፖሊ ያሉ አቶ … የሚባሉ ኢትዮጵያዊ አድራሻ ሰጠውናል ፣ ግን የትም አይጥሉንም ? እንዴት ታምናቸዋለህ ? ሁላችንም ተነጋገርንበት ግን ፈራን !” አለችኝ ስልኩን ያነሳችው እህት ከትሪፖሊ …

ያልደረሰንላቸው በሽዎች የሚቆጠሩ በሱዳን አድርገው በርሃውን ቆርጠው ሊቢያ የገቡት የሚያጠቃ፣ ኢትዮጵያውን ክርስትያኖችን ለይቶ የሚያድን የሰው አውሬ በሊቢያ መሽጓል ። አሸባሪው ISIS ይባላል ፣ እንዳሻው አንገት እየቀላ የንጹሃንን ደም በማፍሰስ የሚፎክር ፣ የሚኩራራ እኩይ አውሬ ! አሸባሪው ትናንት በግብጽ ክርስትያኖች ጀምሮ ዛሬ በኢትዮጵያ ክርስትያኖች ደም ማፍሰሱን ቀጥሎ ማን ይነካኛል ብሎ እየፏለለ ይገኛል ። ኃያላኑ አሜሪካና ምዕራባውያን ዝም ጭጭ ብለዋል ! አሸባሪው ISIS የሚደፍረው ጠፍቷል ፣ አለያም ሆን ተብሎ እንዳበደ ውሻ ተለቆ ሰው መፍጀት ይዟል !

ተስፋ መቁረጥ ፣ ስጋትና ፍርሃት …
=====================

የሰሃራ በርሃን ቆርጠው ሊቢያ የተኮለኮሉትን ኢትዮጵያውያን ቁጥር ማንም አያውቀውም ፣ መሸሻ መሸሸጊያ ቢጠባቸው ፣ ችግራቸው ችግር ቢሆንም በሃገር ቤት የመሳደድ መታሰር ፍርሃቻ ሃገር መግባት እንዳላስቻላቸው አጫውተውኛል ፣ የተመዘዘው ስል ጩቤ አላስፈራቸውም .. ! ” ሶስተኛ ሀገር እንጅ ወደ ሃገር አንገባም !” እያሉ ነው ! አደጋውን በተጨባጭ መረጃ ስታስረዳቸው ” በራሴ ወገን ፣ በራሴ ሀገር በእስር ከምሰቃይ ፣ በርሃው ይብላኝ … ” ይሉሃል …ከበርሃው በላይ ያለውን ጨካኝ አሸባሪ ስራ ቢያውቁትም የሀገር ቤቱ የፖለቲካ ትኩሳት ወደ ሀገር የመመለስ ተስፋቸውን አጨልሞታል ! ሀገር ቤት መግባቱ እንኳን ለእነሱ በራሴ ላይ ምን ይፈጠርብኝ እንደሁ የማላውቀው ጎልማሳ የፈለገው ቢያደርጉም ፣ በሰው ሃገር በጨካኞች እጅ ከመውደቅ በሀገር መከራን መቀበል ይሻለል ! ስላቸው ወያኔያዊ መንፈስ የተጠናወተኝ እየመሰላቸው ” እሱ ያንተ ምርጫ ነው ፣ ብቻ ስማችንና ድምጻችን እንዳታወጣው አደራ ! ” ይሉኛል መልሰው ይጠራጠሩና … ፈርተው ! እናም ፖለቲካው የፈጠረው ስጋትና ፍርሃት ታየኝ …

ክህደት ፣ ሸፍጥ ፣ አምነት ማጣት … የወለደው ፍርሃት …
===================================

“ወደ ሃገር እንግባ ” ያሉት ሞልተው ተርፈዋል ፣ ያም ሆኖ እስካሁም በግላጭ የሚታወቅ ለሁሉም ተደራሽ አድራሻ አልተላለፈም ! … የተደረሰላቸው ጭንቀት ፍርሃቱ የራሳቸውን ወገን እስከ መጠራጠር አድርሷቸዋል አይተናል ፣ ለመረዳት ” ፈራን !” እያሉ ነው ! … ክህደት ፣ ሸፍጥ ፣ አምነት ማጣት … የወለደው ፍርሃት ፈሪ አድርጓቸዋል !

ወደ አውሮፖ በጣሊያንና ማልታ በኩል ለመድረስ በአሳር በመከራ እዚህ ጫፍ የደረሰ የሀበሻ ልጅ ደምም ረክሷል ፣ ሃበሻ የሌለበት ፣ የሀበሻ ነፍስ ረክሶ ፣ ነፍሱ የማይጠፋበት ቦታ አይሰማም ። ይህ የባህር አደጋ ብዙ ባይነገርለትም ፣ ተደጋግሞ የእኛን ሰው ነፈወስ ነጥቆታል ፣ አጥፍቶናል ። ቢደደጋገምም ሀዘን ቁጭቱ አልለመድ ብሏል ። እነሆ በሃዘን ላይ ሃዘን ሰምተናል ! የወንድሞቻችን አንገት በተቀላበት የሜዲትራንያን ውቅያኖስ በተሰናከለች የአሻጋጋሪዎች መርከብ / ጀልባ “የሞቱት የተረፉት እነማን ናቸው ? ” ተብሎ ወደ የማይመረመርበትን ትራጀዲ ተፈጽሟል ! ይህን የሰማነው ትናንት ነው ፣ በሀዘን ላይ ሆነን !

ካለሁበት ሳውዲ ኩታ ገጠሟ የመን የሀበሻ ልጅ የድረሱልኝ ድምጽ አባርቶ ባያውቅም ፣ የመን ሰማይ ስር በጦርነት እየታመሰ በመሆኑ የከፋ ዋይታ ድምጽ ይሰማል ፣ ጭካኔያቸውም አይተን የአፍሪካዊ ISIS ያልናቸው ደቡብ አፍሪካውያን ውለታችን ረስተው አመድ አፋሽ አድርገውን ብቻ አልቀሩም ፣ የለየለት የንቀት ግፍ ተፈጽሞብናል ! ይህም ያም ሁሉም ያስፈራል !

ሁለት አስርት አመታት በኩራትና ፍጹም በነጻነት የኖርኩባት ሳውዲ አረቢያ አሁንም እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ ከሀገሬ ባልተናነሰ ከከተማ እስከ ገጠር ከተሞቿ በነጻነት ብንቀሳቀስባትም ዛሬ የነጻነቱን ግርማ ከላየ ላይ የለም ! … ቤቱ ፣ ስራ ፣ ቦታው ፣ መንገዱ … ሁሉም ያስፈራል ! ” ፈራን !” ብለው አስፈሩኝ …

ትናንት ማምሻውን ከልጆቸ ጋር ስንጨዋወት የወትሮው አባታቸው አለመሆኔን ተረድተዋልና ” አቤ ምን ሆነሃል ፣ ፊትህ ደስ አይልም! ” እያሉ ጠየቁኝ ፣ ወደ ውስጥ ሳልገባ ” ከእናንተ የሚጠበቀው ጥናት ነው አጥኑ! ” አልኳቸው ፣ መልሴ ያልጣመው የ13 ዓመቱ የበኸር ልጀ ” አቤ እስኪ ላንድ ሰሞን ይህንን የምትጽፈውን ተወውና ዘና በል ፣ ባህር መጫወቻ ቦታ ሁሉም አካባቢ ጥሩ ጥሩ ወዳጆች እያሉህ እዚያም ወስደህንኮ ትጽፋለህ ? ለምን ለራስህ እረፍት አትሰጠውም !” ሲል እህቱ ማሂን እንዳቀፈ ክችም ብሎ አፍጥጦ ጠየቀኝ እዮብ ፣ የመጻፊን ጥቅም ባስረዳውም ” እኛም እኮ አንተ ስትረባበሽ እንረበሻለን ” ሲል ሞገተኝ ፣ መልስ የለኝም ” ልጀ ምን ታይቶት ይሆን ? ” አልኩ ራሴ ለራሴ በውስጤ … ከነጎድኩበት እሳቤ ራሴን በተሎ ሰብስቤ ” አዎ ትክክል ነህ ፣ እስኪ አረፍ እላለሁ ! ” አልኩትና ቃል ገባሁለት …ለአባቱ የፈራ ልጅ !

ፍርሃቱ ባያሸሸኝ ፣ ለልጀ የገባሁትን ቃል ለማክበር ላፍታ ያህል ከማህበራዊ መገናኛ መስመሩ ዘወር ልል አስቤያለሁ ፣ አብራችሁኝ ለተጓዛችሁ ፣ ለደገፋችሁኝ ፣ ለተረዳችሁኝ ፣ ” ራስክን አትቆልል! ” ስትሉ የድርሻችሁን ስታደርጉ የማላያችሁ ወቃሾቸ ጭምር ሁላችሁንም አመሰግናለሁ ! የሰማሁት ሰሞነኛ ልብም ሰባሪ እማኝነት እንዳይቀር አንድተነፍስና ለእረፍት የመሰናበቻ መልዕክቴን በተሰበረ ልብ ካስተላለፍኩ ምንም አልሻም ! የጨለቀ እለት … እንዲህ ነው !

ብቻ ከመግፋት መገፋት ፣ መልካም ነገር ነው ፣ ለሚቀረው አለም ለሚያምኑበት መሞት ደግሞ ሰማዕትነት ነው ! ነፍስ የሚያስምር !

ነቢዩ ሲራክ
የጨለመው ሚያዝያ 13 ቀን 2007 ዓም

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 9 years ago on April 21, 2015
  • By:
  • Last Modified: April 21, 2015 @ 5:06 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar