www.maledatimes.com የጃፓን መንግስት ISISን ለመከላከል እንቅስቃሴ ከኢትዮጵያ ጋር ሲነፃፀር - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የጃፓን መንግስት ISISን ለመከላከል እንቅስቃሴ ከኢትዮጵያ ጋር ሲነፃፀር

By   /   April 30, 2015  /   Comments Off on የጃፓን መንግስት ISISን ለመከላከል እንቅስቃሴ ከኢትዮጵያ ጋር ሲነፃፀር

    Print       Email
0 0
Read Time:2 Minute, 37 Second

Abenezer B. Yisihak

ISIS ሁለት የጃፓን ዜጎችን ማገቱን፤ ቀጥሎም ማረዱን ተከትሎ ጃፓኖች ከፍተኛ መደናገጥ ውስጥ ገብተው ነበር። ያንንም ተከትሎ ሚድያዎቻቸው በሙሉ ስለድርጊቱ የተለያዩ አይነት ዘገባዎችን፣ ውይይቶችን ያቀርቡ ነበር። መጀመሪያ ላይ ያነሱት ጥያቄ ISIS እንዴት ጃፓንን ኢላማ ሊያደርግ ቻለ? የጃፓን መንግስት በውጪ ጉዳይ ፖሊሲው ላይ የሰራው ስህተት አለ ወይ? ወደፊት ተመሳሳይ ጥቃት ጃፓናውያን ላይ እንዳይደርስ ምን ማድረግ አለብን? በሚል በጣም ሰፊና ተከታታ ውይይትና ክርክር ሲያደርጉ ነበር። ተቃዋሚ ፓርቲዎቹም ለሚያነሷቸው ከፍተኛ ትችቶች ጠ/ር አቤ ሺንዞና መንግስት ተከታታይ ምላሽና ማብራሪያ ይሰጡ ነበር። 

የጃፓን መንግስት ISISን ለመከላከል እንቅስቃሴ ለሚያደርጉ ሀገሮች ዕርዳታ ለማድረግ ተናግሮ ነበር። ይህም ዕርዳታ የሰው ሀይል ግንባታን፣ የመሰረት ልማት ግንባታንና የመሰሳሰሉትን የሚያጠቃልል ሲሆን መጠኑም 200 ሚሊዮን ዶርላ የሚሆን ነበር። ጃፓን በሕገ መንግስቷ መሰረት ምንም አይነት ወታደራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባት አትችልም። ስለዚህ ድጋፍ የምታደርገው በገንዘብ ወይም በችግሩ የተጠቁ ሀገሮችን በትምህርትና በስልጠና፣ በመሰረት ልማት ግንባታና ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ በማድረግ ነው። ወይም የገንዘብ ድጋፍ ነው የምታደርገው። ይሄም 200 ሚሊዮን ዶላር ለዚያ አላማ የተመደ ነው። ነገር ግን ISIS ሁለት የጃፓን ጋዜጠኞችን አግቶ ከወሰደ በኋላ ይሄንን 200 ሚሊዮን ዶላር የጃፓን መንግስት ለISIS የማይሰጥ ከሆነ ሁለቱንም ጋዜጠኞች እንደሚያርዳቸው አስታወቀ።

በገዢው በሊበራል ዶሞክራቲክ ፓርቲና በተቃዋሚዎች መካከል ከፍተኛ ክርክር አስነስቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጥ የተጠየቀው በዚህ ጉዳይ ላይ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዕርዳታው ISIS ለመዋጋት ሳይሆን የሰጠነው የመካከለኛው ምስራቅ መረጋጋት አስፈላጊ ነውና ISIS ለማስቆም ለሚሰሩ ሀገሮች ወታደራዊ ያልሆነ ድጋፍ ነው ያደረግነው የሚል ምላሽ ሰጠ። ተቃዋሚዎችና የተለያዩ ሰዎችም በዚህ ወቅት ግብጽ ድረስ ሄዶ ጠቅላይ ሚኒትሩ በይፋ የገንዘብ ዕርዳታ እንደሚያደርግ መናገሩ ነው ለጥቃት ያጋለጠን። መርዳትም ከነበረብን ከዚህ በፊት እናደርግ በነበረው መልኩ ማድረግ እየተቻለ ጠ/ር አቤ ነገሩን ለማስቆም ከሚቻልበት ጉዳይ ጋር አያይዞ ማቅረቡ ተገቢ አልነበረም የሚል ትችንና ተቃውሞ ቀርቦበት ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ፓርቲው በተለመደው መልኩ በሥርዓትና በጨዋ ደንብ ነበር ለተነሳው ተቃውሞ ሁሉ ምላሽ ሲሰጡ የነበረው።

በመጨረሻም የተነሳው ክርክር ሁለቱን ዜጎች ለማትረፍ ምን ይደረግ? የሚል ነበር። መንግስት ISIS በጠይቀው መሰረት ገንዘቡን እንደማይሰጥ በግልጽ አስቀምጦ በሌላ መንገድ ዜጎቹን ለማዳን ነው ድርድር የጀመረው። ገዢው ፓርቲ ከታቃዋሚዎች ከፍተኛ ትችት ቢቀርብበትም ስሜታዊ ሆኖ የሰጠው ምላሽ አልነበረም። በሕዝቡ በኩል ግማሹ የተጠየቀው ገንዘብ ይከፈልና ነጻ ይደረጉ ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ መከፍል የለበትም የባሰ አደጋ በራሳችን ላይ እናመጣለን የሚል ሀሳብ ያንጸባርቁ ነበር። በመጨረሻም የተባለው ገንዘብ አልተከፈለም ያው ከዚያ በኋላ ISIS ያደረገውን አይተናል።

እነሱ የሚሰደድ ዜጋ የላቸውም። ለሽብርተኛ ጥቃት የሚጋለጡት ለስራ ወይም ለጉብኝት ሲንቀሳቀሱ ነው። ያም ቢሆን ግን በዚህ ደረጃ ሁለት ዜጎቻቸው ሲገደሉባቸው የችግሩ ምንጭ ምንድነው? ብለው መፍትሄ ለመስጠት ገዢው ፓርቲ ሀላፊነቱን ወስዶ ተንቀሳቀሰ እንጂ ተቃዋሚዎችን ሲኮንን ውሎ አላደረም። በውጪ ጉዳይ ፖሊሲያቸውም በኩል ክፍተት ካለ ለመፈተሽ ቃል ገባ እንጂ ፍጹም ነኝ ብሎ አልተመጻደቀም። ሚዲያዎቻቸው በጉዳዩ ላይ ሁሉም ሰው የሚሰማውን በግልጽ እየተናገረ ውይይት አካሄዱ እንጂ የተፈጠረውን አጋጣሚ ለገዢው ፓርቲ የፕሮፓጋንዳ መዋያ እንዲሆን አላደረጉም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለቀረቡለት ጥያቄዎችና ትችቶች በሙሉ በተገቢው መልኩ ምላሽ ሲሰጥ ነበር።

እንደ ሀገር ጃፓን የደረሰችበት ደረጃ አልደረስንም። ማነጻጸርም አይቻልም። ኢህአዴግም እንደ ጃፓን ገዢ ፓርቲ ዲሞክራት እንዲሆን አልጠብቀውም። ባሕሪውና የመጣበት መንገድ እንደዚህ አይነት አመለካከትንና አሰራርን እንዲያዳብር አላደረገውም። ነገር ግን ከሕዝብም ሆነ ከተቃዋሚዎች የሚቀርበውን ቅሬታ ሰምቶ ተገቢውን ምላሽ መሰጠት አለመፈለጉና አለመቻሉ ሳያንስ አልፎ ሄዶ እጅግ በዘቀጠ ሁኔታ የዜጎችን ሞት ለራሱ ፖለቲካዊ ትርፍ ለማዋል መንቀሳቀሱ፣ ሰማያዊ ፓርቲን የISIS ወኪል ነው ማለቱ የሚያሳፍር ነው። የሕዝቡን ንዴትና ቁጭት ተረድቶ እንደ ዜጋ የሁሉንም ስሜት ተጋርቶ በፍጥነት አለመንቀሳቀሱ ብሎም የችግሩን ትክክለኛ ምንጭ ትቶ በሌሎች ወገኖች ላይ ፕሮፓጋንዳ ለመስራት መሞከሩ ኢህአዴግ ምን ያህል ከዜጎችና ከሀገር ክብር በላይ ለሥልጣኑ የሚሳሳ ፓርቲ መሆኑን ድጋሚ ያረጋገጠበት ነው።

 

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 9 years ago on April 30, 2015
  • By:
  • Last Modified: April 30, 2015 @ 12:08 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar