www.maledatimes.com ጥቂት ስለ አማረ አረጋዊ ተስፋዬ ገብረአብ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ጥቂት ስለ አማረ አረጋዊ ተስፋዬ ገብረአብ

By   /   March 21, 2013  /   Comments Off on ጥቂት ስለ አማረ አረጋዊ ተስፋዬ ገብረአብ

    Print       Email
0 0
Read Time:11 Minute, 3 Second

             ሰሞኑን ዘሃበሻ ድረገፅ ላይ አንዲት፣ “እየሩሳሌም” የተባለች ሴት አማረ አረጋዊ እና ሪፖርተር ጋዜጣን የተመለከተ ተከታታይ ፅሁፍ አውጥታ አነበብኩ። እየሩሳሌም ከፃፈችው ፅሁፍ እንደተረዳሁት ከአማረ ጋር የሆነ አንጀት ውስጥ የገባ ቂም ያላት ነው የምትመስለው። በተለይም ስለ አማረ ስነምግባር ስትገልፅ፣ “አማረ ቢሮ ውስጥ ሴት ጋዜጠኞችን እንትን ያስቸግር ነበር” ምናምን ብላ ተናግራለች። ምናልባት እሷ የደረሰባት ነገር ካለ ግልፅ ብታደርገው ጥሩ ነበር። ሴት ጋዜጠኞችን ሁሉ ወክላ መናገሯ ግን ተገቢ አይደለም። አማረ አረጋዊን ለአስር አመታት ያህል አውቀዋለሁ። በዋናነት ሊታማ የሚችለው ለህወሃት ያለው ስስ ስሜቱ ነው። በተረፈ እሷ እንደገለፀችው የደከመ ሰብእና ያለው ሰው አይደለም።

እስከማውቀው አማረ ስልጣን ላይ በነበረበት ዘመን በማስታወቂያ ሚኒስቴር ሰራተኞች ተወዳጅ ነበር። እንደ ወያኔ ካድሬዎች አክራሪና ጡሩንባ አልነበረም። ዲማ ነገዎን እንኳ ጓደኛው አድርጎት ነበር። በግልባጩ አማረ ከኢህአዴግ ጠላቶች ጋር በመወዳጀት በተደጋጋሚ ይወነጀል ነበር። በርግጥ ሴቶች ይቀርቡታል። ስለሚቀልድ ይመስለኛል። አማረ ከቴሌቪዥን ወደ ኢዜአ ሲዘዋወር የቴሌቪዥን ሰራተኞች ገንዘብ አዋጥተው ወርቅ እንደሸለሙት አውቃለሁ። እነዚህ ሸላሚዎቹ የኢህአዴግ ደጋፊዎች አልነበሩም። በደርግ ዘመን የተቀጠሩ ነበሩ። አማረ ወርቅ በመሸለሙ በህወሃት ተወቅሶበታል። “ከሰራተኞቹ ጋር ያለህ ግንኙነት የኢህአዴግን አላማ መሰረት ያደረገ አይደለም” ተብሎ ነበር የተወቀሰው። እዚህ ላይ እውነት ነበር። የኢትዮጵያ ሬድዮ የፕሮግራም ሃላፊ? የነበረው ታደሰ ሙሉነህ ከአማረ ጋር ቅርርብ ነበረው። አንድ ቀን እንዲህ ሲለው ሰምቼያለሁ፣
“ታዴ! ባክህ አንድ ቀን እንገናኝና ቢራ ይዘን ኢህአዴግን እንማ?”
ታደሰ በጣም ሳቀ። እና እንዲህ አለ፣
“እንዲህ ተለሳልሰህ ልባችንን ለማግኘት ነው? አታገኘንም። አንተን ወደኛ እናመጣሃለን!”
ሰለሞን አባተ ከአማረ ጋር ከሚቀራረቡት አንዱ ነበር። 120 የተባለውን ፕሮግራም የነደፉት እነ ሰለሞን ነበሩ በአማረ ስር ሆነው። ቴሌቪዥኑን በተሻለ ሁኔታ ለቆላቸው ነበር። “ሰዎች ምን ይላሉ?” የሚለውን ፕሮግራም አማረ ራሱ ነበር የጀመረው። ኢህዴግን የሚቃወሙ አሳቦች እንደልብ ይቀርቡበት ነበር። እውነት ለመናገር አማረ ሰው ማሰራት እና ሰው መያዝ ይችልበታል። ይቺ እየሩሳሌም የተባለች ሴት የፃፈችው አልተዋጠልኝም። ከፅሁፏ እንዳየሁት በሆነ ነገር ጨጓራዋ ተልጦአል። “አማረ ሴት ይወድ ነበር” የሚለውን በተለይ በጣም ደጋገመችው። ነገሩን በክስ መልክ ማቅረቧ ካልቀረ መረጃው ተጨባጭ ቢሆን ባልከፋ።
የሆነ ሆኖ አማረ ጋዜጠኛ ነው። ለህወሃት የሚያደላ ቢሆንም ብዙ መረጃ እየሰጠን ነው። ህወሃትን ሲደግፍ በአሳብ መሞገት እንጂ፣ አማረን እንደ ጠላት ደርቦ ማየት ሚዛናዊ አይመስለኝም። የህወሃት ሰዎችም ሲቀጠቅጡት እያየን ነው። ብዙ በደልም አድርሰውበታል። ከሚኖርበት የኪራይ ቤት ጭምር አስወጥተውታል። የአላሙዲ ሰዎች ከዚህ ቀደም ምን እንዳደረጉትም ሰምተናል። ብዙ ጠላት አለው። በዚህ ሁሉ ጠላት መካከል ግን እየሰራ ነው። በርግጥ እንዲህም ሆኖ ህወሃትን እስካሁን አልከዳም። አላማው ነው። መቸም ዋናው ግብ ስርአቱን መለወጥ ወይም ማስወገድ ከሆነ አማረ አረጋዊን ኢላማ በማድረግ ተጠቃሚ የሚሆነው ህወሃት ይመስለኛል። ታደሰ ሙሉነህ እንዳለው እንደ አማረ አረጋዊ ያሉ የሾለ ብእር ያላቸው ጋዜጠኞች ዴሞክራሲን እንዲያገለግሉ ጫና መፍጠር ይበልጥ በጎ መንገድ ይመስለኛል።
ሪፖርተር ጋዜጣ ሲጀመር መለስ ዜናዊ ለአማረ አረጋዊ አንድ ሚሊዮን ብር እንደሰጠው እየሩሳሌም ፅፋለች። ይሄ ነጭ ውሸት ነው። ሪፖርተር ጋዜጣ የተጀመረው በአበበ ባልቻ ገንዘብ ነው። አማረም ከዚህም ከዚያም ለቃቅሞ 25 ሺህ ብር ማግኘት መቻሉን አውቃለሁ። አማረ ስራውን ከለቀቀ በሁዋላ፣ ደበቅ እያልንም ቢሆን እንገናኝ ነበር። ጋዜጣው ሲጀመርም አማክሮኛል። አንድ ጊዜ ጋዜጣውን ከማተሚያ ቤት የሚያወጣበት ገንዘብ ቸግሮት፣ ሚልኪያስ ከተባለ በወቅቱ ጓደኛዬ ከነበረ የስቴሽነሪ ነጋዴ 6000 ብር ተበድሬ ለአማረ ሰጥቼው ጋዜጣውን አውጥቶ ሸጦአል። ሸጦ ሲያበቃም ገንዘቡን መልሶልኛል። ያንን ስድስት ሺህ ብር ለማግኘት በጣም ተቸግሮ እንደነበር አስታውሳለሁ። ከዚያ በሁዋላ ማስታወቂያ እየፈላለገ ቀስበቀስ እየተጠናከረ ሄደ። በእርግጠኛነት ህወሃት ለአማረ ገንዘብ አልሰጠውም። ክንፈ ግን በግል መረጃ ይሰጠው ነበር። ያልተነገሩ መረጃዎችን ማተም ሲጀምር የጋዜጣው ሽያጭ እያደገለት ሄደ። ከዚህ ይልቅ አማረ አረጋዊ ከሙያው ስነምግባር ባፈነገጠ መልኩ አንዳንድ ህገወጥ ድርጊቶችን የፈፀመው ኤርትራውያን በሚባረሩበት ወቅት ነው። ይህ ከአጀንዳችን ውጭ ስለሆነ ብዙ አልገፋበትም።
እየሩሳሌም ስትፅፍ ትቸኩላለች። ያነበቡ ሰዎች እንደነገሩኝ፣ የወያኔ ፖሊሶች ዘጠኝ ሜትር ርቀት ካለው ድልድይ ላይ ቁልቁል ወርውረዋት፣ ድንጋይ ላይ ከወደቀች በሁዋላ ምንም ሳትሆን መትረፏን ፅፋለች አሉ። ጀምስ ቦንድ ናት። ሌላ ጊዜ ደግሞ ወዲ መድህን የተባለው ጄኔራል ሰምሃል የተባለችውን የመለስ ልጅ ክርስትና ማንሳቱን ተናገረች ወይም ፃፈች አሉ። ክርስትና የሚነሳው ሴት ለሴት፣ ወንድ ለወንድ መሆኑን ልብ አላለችም። በርግጥ ሰዎች ሲቸኩሉ ማዳለጥ የተለመደ ነው። እና ረጋ ማለት ይሻላል።

ttgebreab@gmail.com

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on March 21, 2013
  • By:
  • Last Modified: March 21, 2013 @ 10:13 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar