www.maledatimes.com ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ – “ፓርቲዎች የሚመሩት የድሮ አገር ወዳድና የእናት አገር ፍቅር አቃጠለን በሚሉ ሽማግሌዎች ነው” - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ – “ፓርቲዎች የሚመሩት የድሮ አገር ወዳድና የእናት አገር ፍቅር አቃጠለን በሚሉ ሽማግሌዎች ነው”

By   /   November 27, 2014  /   Comments Off on ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ – “ፓርቲዎች የሚመሩት የድሮ አገር ወዳድና የእናት አገር ፍቅር አቃጠለን በሚሉ ሽማግሌዎች ነው”

    Print       Email
0 0
Read Time:24 Minute, 39 Second

* የምርጫ ጉዳይ የሁላችንም የጋራ ጉዳይ ነው ለምን በዚህ ጉዳይ ላይ እንኳን አንስማማም ? ስንል መጀመሪያ ላይ የሚስማሙ ይመስሉና ኋላ ግን ማን ነው አመራሩን የሚይዘው? ማነው ዋናው ?ወዘተ የሚሉ ጉዳዮች ቀስ እያሉ ይመጣሉ፡፡

* የፖለቲካ ፓርቲ አቋቁመናል ከሚሉ ወገኖች ጋር ለመነጋገር ሞክሬአለሁ፤ ከነ ደጃዝማች ፣ ከነራስ ወዘተ ጋር፡፡ ሁሉም ከራሳቸው ካላቸው ግንዛቤ ተነስተው ነው ፓርቲ የሚያቋቁሙት፡፡ የእናት አገራችን ነገር ዕረፍት ነሳን ይላሉ፡፡ እንግዲህ የኢትዮጵያ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ ብቃት ባለውና የዘመኑ ፖለቲካ በገባው ሰው መመራት ይገባው ነበር ፡፡

* ጠንካራ ማለት እንደ ግንቦት 7 ጦርነት ማወጅ ከሆነ ይሄ አይገባኝም ፡፡ በሰላማዊ መንገድ ተደራጅቶ በመንቀሳቀስ ረገድ የእኛም ፓርቲዎች ጠንካራ ናቸው፡፡

* ዲያስፖራው ከእኛ ጋር ቁጭ ብሎ ማውራትም አይፈልግም፡፡ በየነ መጣ ስብሰባ ይደረግና ጥያቄ ካላችሁ ጠይቁ ሲባል የለም ፡፡ እኔ ንግግር እንዳደርግ የተሰበሰበውን ስብሰባ እኮ ነው የበተኑት ፡፡ ሰልፍ ነው ያደረጉት፤ ዋሽንግተን ላይ፡፡

(ሰለሞን በቀለ)

በመጪው ግንቦት ወር በአገራችን አገራዊ ምርጫ ይካሄዳል፡፡ ለምርጫው ከወዲሁ ዝግጅት በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡ሁሉም በተለይም የፖለቲካ ፓርቲዎች በየፊናቸው በምርጫው ላይ ለመሳተፍ ሽር ጉድ ማለት ጀምረዋል፡፡ ስለቀጣዩ ምርጫና እስከ ዛሬ ስለነበረው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግላቸው እንዲያወጉን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲውን ምሁርና የመድረክ ፓርቲ አመራር የሆኑትን ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስን ለቃለ መጠይቅ ስንጋብዛቸው ምላሻቸውን በደስታ ገለጹልን፡፡ከሰፊው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ልምዳቸው ትንሿን ቀንጭበን አቅርበንላችኋል፡፡እነሆ ታነቡት ዘንድ ጋብዘናል፡፡

ዘመን፡- ፕሮፌሰር ለቃለ መጠይቁ ስንጋብዝዎ ወዲያውኑ ፈቃደኛ መሆንዎትን ነው የገለጹልን እና በአንባቢያን ስም አመሰግ ናለሁ፡፡

ፕሮፌሰር በየነ፡- እኛ እንግዲህ ይሄ ኃላፊነ ታችን ነው፡፡ ከህዝቡ ጋር የሚያገናኝ፤ ትችታችንንም፣ እሴታችንንም ሆነ ሌላውንም ለማቅረብ ዕድል ሲኖር የምንጠቀምበት ነው፡፡ እና እናንተም ይሄንን ጊዜ ወስዳችሁ ስለመጣችሁ አመሰግናለሁ፡፡

ዘመን፡- ፕሮፌሰር ጠፉ ፡፡

ፕሮፌሰር በየነ፡- እኔ እንግዲህ ከምኑ እንደጠፋሁ አላውቅም፡፡ በኢትዮጵያ በትንሹም በትልቁም ጉዳይ ላይ አደባባይ ወጥቼ አስተያየት እየሰጠሁ ሁኔታዎችን ለማስተካከል የማደርገውን ትግል እንደቀጠልኩ ነው፡፡ ምናልባት ከግል ጋዜጦች ቁጥር መቀነስ ጋር የእኛንም ፎቶግራፎች አደባባይ ይዘው የመውጣቱ ነገር ቀንሶ ሊሆን ይችላል፡፡ እና ጠፋህ የሚያስብለው ይሄ ከሆነ አዎ በዚያ መልክ ጠፍቻለሁ ፡፡ በነገራችን ላይ ለአንድ ዓመት አሜሪካን አገር ሳስተምር ቆይቼ አሁን መስከረም ሲገባ አካባቢ ነው ወደ አገሬ የተመለስኩት ፡፡

ዘመን ፡- ለአንድ ዓመት ውጭ ሲያስተምሩ ነው የቆዩት?

ፕሮፌሰር በየነ፡- አዎ! ቺካጎ አካባቢ ( government state university) የሚባለው ውስጥ ለአንድ ዓመት ሳስተምር ነው የቆየሁት ፡፡

ዘመን፡- ስለዚህ ዘመን መጽሔት ከአንድ ዓመት የውጭ ቆይታዎ በኋላ እንኳን ወደ አገርዎ በሰላም ተመለሱ ትላለች፡፡

ፕሮፌሰር በየነ – አመሰግናለሁ፡፡

ዘመን ፡- እንግዲህ እርስዎ ባለፉት ጊዜአት በተቃዋሚ ፓርቲ ውስጥ በተለይም በህብረት ፓርቲ ውስጥ ትልቅና ከፍተኛ ተሳትፎ እንደነበረዎት ይታወሳል፡፡ አሁን እንዳሉኝም በሰላማዊ ትግሉ ሂደት ውስጥ እንደቀጠሉ ነው እና ትግሉ እንዴት እየሄደ ነው?Proff Beyene Petros

ፕሮፌሰር በየነ፡- እንግዲህ እኛ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ድርጅቶች አደረጃጀት ብቃት እንዲያገኝ ባለፉት 20 ዓመታት በከፍተኛ ደረጃ ጥረት ስናደርግ ነው የቆየነው፡፡ በተለይም በተቃዋሚነት የተሰለፉት እነኚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተናጠል ብቻቸውን ምንም ለውጥ ሊያመጡ አይችሉም ብለን በተለይም ኢህአዴግ ለዘመናት የተደራጀና አቅም ያጎለበተ ስልጣን ላይም ያለ ፓርቲ እንደመሆኑ ኢህአዴግ ከሚለው የተሻለ አማራጭ አለን የሚሉቱ ተሰባስበው፣ ግንባርና ቅንጅት እንዲሁም ውህደት ፈጥረው ለአንድ አላማ ቢንቀሳቀሱና ቢሰባሰቡ ተገቢ ነው ከሚልና ይሄ የህዝቡም ጥያቄ ስለነበር ይሄን ለማስተባበር ስናደርግ ከነበረው ጥረት የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ህብረት ተወለደ፡፡ በዚህም አማካኝነት ነው ወደ 1997 ምርጫ የገባነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ ህብረትም ሆነ ከህብረት ወጥቶ በራሱ ተደራጅቶ ሲንቀሳቀስ የነበረው ቅንጅትም አካባቢ መፍረክረክ ደረሰ፡፡ እንግዲህ ብዙ ተስፋ ከማድረግ በመነሳት የፈለጉት ነገር ሳይሳካ ሲቀር ተስፋ መቁረጥ አለ፡፡ ስለዚህ የ1997 ምርጫና ከዚያ በኋላ በተከሰተው ሁኔታ በነዚህ ሁለት ትላልቅ ግንባሮች ውስጥ ችግሮች ተፈጠሩና ተፍረከረኩ፡፡ ከዚህም የተነሳ የህዝባችን መታገያ መሳሪያ የመሆኛ ጊዜአቸው አበቃለት፡፡ ይሄንን ሁኔታ ካየን በኋላ ደግሞ ሌላ ስብስብ መፍጠር የግድ ነው፡፡ እንግዲህ በአገራችን ጉዳይ ላይ አማራጭ አጀንዳና ሃሳብ አለን እስካን ድረስ ቁጭ ማለት ከእኛ አይጠበቅም በማለት ወደ ስምንት የምንሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሰባስበን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ የሚባለውን ፓርቲ ፈጠርን፡፡ በአሁኑ ጊዜ እየተንቀሳቀስን ያለነው በዚሁ መድረክ አማካኝነት ነው፡፡ በነገራችን ላይ በዚሁ መድረክ አማካኝነት ነው የ2002 ምርጫ ላይ ልንሳተፍ የቻልነው፡፡ እንግዲህ አብዛኞቻችን የቀድሞው ህብረት ውስጥ የነበርን ነን፡፡ በአሁኑ ጊዜ መድረክን አቀናጅተን በዚያ ስር እየተንቀሳቀስን ነው ያለነው ፡፡

ዘመን ፡- መድረክ አሁን በምን አይነት ሁኔታ ላይ ነው የሚገኘው? እርስዎስ በፓርቲው ውስጥ ያለዎት ተሳርፎ ምን ይመስላል? ከፊታችሁም ምርጫ አለ ፡፡

ፕሮፌሰር በየነ ፡- እኔ መድረክ ውስጥ ያለሁት በኢትዮጵያ ማህበራዊ ዴሞክራሲ ደቡብ ህብረት አንድነት ፓርቲ አማካኝነት ነው፡፡ እኔ የፓርቲው ሊቀመንበር ነኝ ፡፡ በዚህም ፓርቲያችን የመድረክ አባል ነው፡፡ የመድረክ አመራሩ ተዘዋዋሪ ነው ፡፡ በፊት በየስድስት ወሩ አሁን ደግሞ በየዓመቱ ጠቅላላ ጉባኤ እየተጠራ አመራር ይሰየማል፡፡ እኔ ላለፈው አንድ ዓመት ስላልነበርኩ የበላይ አመራር ላይ ሆኖ እንቅስቃሴ ይበደል ይሆናል በሚል ሌላ የሚተካኝ ሰው ከፓርቲው ውስጥ ተመድቦ ነው እየሠራ ያለው፡፡ አሁን የማዕከላዊ ምክር ቤቱ አባል ነኝ፡፡በፊት መድረክን ስናቁዋቁም እኔ አመራሩን ይዤ ተንቀሳቅሼአለሁ፡፡ በተለይ 2002 ወደ ምርጫ በተገባበት ጊዜ መድረክን በሰብሳቢነት እመራ የነበርኩት እኔ ነኝ፡፡ በኋላም የህዝብ ግንኙነት ጉዳይን ለዓመታት ስመራ ቆይቻለሁ፡፡ የአሁን ጊዜው የሽግግር ጊዜ ነው፡፡እኔም ከውጭ ገና መመለሴ ስለሆነ የመድረክን ጉዳይ እየተከታተልኩ ነው፡፡

ዘመን ፡- እንደሚታወቀው እርስዎም እንዳሉት በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አለመግባባቶችና መፍረክረኮች አሉ ፡፡ ተጠናክረው ጠንካራ ፓርቲ ሆነው ገዢውንም ፓርቲ መወዳደር የሚችሉበት ሁኔታ ለምን አልተፈጠረም ? ችግራቸውስ ምንድን ነው ይላሉ? እርስዎ በትግሉ ሂደት ውስጥ የረጅም ጊዜ ልምድም አለዎትና፤

ፕሮፌሰር በየነ ፡- እዚህ አገር ውስጥ ያለው የፖለቲካ ሂደት ውስብስብ ነው፡፡ እንደ ብዝሀነታችን ሁሉ የፍላጎት ልዩነቶችም አሉ፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ያለው የፖለቲካ አስተላለፍ ፅንፍና ነፃ ልውጣ የሚል አጀንዳ ይዞ ከሚንቀሳቀስ እስከ ሉአላዊት ኢትዮጵያ ስር ለውጥ በሰላማዊ አግባብ እናመጣን እስከምንለው እኛ ድረስ ሰፊ ነው ፡፡ ህገ መንግስቱን በራሱ እስካለመቀበል ድረስ የሚደርስና ከአገሪቱ የተወሰነውን ወገን ይዤ ነፃ እወጣለሁ የሚል፤ ሌላው ደግሞ በስልጣን ላይ ያለው ኃይል በሰላማዊ አግባብ ስልጣን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ስለማይሆን በጉልበት ማስወገድ አለብን የሚል አካል ሁሉ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ በተለይም በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች መሀከል የዚህ አይነት ልዩነት አለ፡፡ እናም በጥቅሉ የዚህ አይነት ፅንፍ ያለውን አካል ሁሉ ተቃዋሚ ብሎ ሁሉንም በአንድ ስም ለመፈረጅ ይሞከራል ፡፡ ይህ በራሱ ትክክል አይደለም፡፡ ተቃዋሚ ሲባል ለምንድን ነው የምቃወመው? ማንን ነው የምቃወመው? የሚል መኖር አለበት፡፡እንግዲህ ለምሳሌ ይሄንን አካባቢ ነፃ እናወጣለን እኛም ነፃ እንወጣለን የሚሉት ኢህአዴግን ብቻ ሳይሆን የቀረነውን በኢትዮጵያዊነት ከምናምነው ኢትዮጵያን ወደ ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ለመውሰድ ከምንሞክረውም ጋር ፀብ አላቸው ማለት ነው ፡፡ ሌላው ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ሊመጣ የሚገባው ለውጥ በሰላማዊ አግባብ በሂደት ነው የሚመጣውና ትዕግስት ማጣት የለብንም ከምንለውም ጋር ደግሞ ከፍተኛ ጥል ያላቸው አሉ ፡፡ ይሄ መንግሥት በጉልበት ነው ከስልጣን መወገድ ያለበት ይላሉ፡፡ እና እነዚህን ሁሉ አንድ ላይ አድርጎ እንዲያው ለንግግር እንዲያመች ብቻ ተብሎ ተቃዋሚዎች ተበታተኑ የሚባል አባባል ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፤ ፅንፉ ብዙ ነውና፡፡

እንግዲህ በሰላማዊ መንገድ ለውጥ እናመጣለን ብለው በምርጫ ቦርድ ፕሮግራማቸው ተገምግሞና ተመዝግበው ያሉት ቁጭራቸው ከፍና ዝቅ ይላል፤ አሁን ግን ወደ ሰባዎቹ ቤት ነው መሰለኝ ያሉት፡፡ እና ከጥያቄህ እንደምረዳው በእነዚህ መካከል ለምን መሰባሰብ ጠፋ? ለማለት የፈለግህ ይመስለኛል እና እነኚህ አባላት አጀንዳቸው የተለያየ ነው ፡፡ ግማሹ የፌዴራል ስርዓቱን በሰላማዊ ትግልም ቢሆን አሸንፌ አፈርሰዋለሁ የሚል አለ ፡፡ ሌላው ደግሞ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰብ የሚባል ነገር ኢህአዴግ ያመጣው ጣጣ ስለሆነ ያንንም እናጠፋዋለን፤ ኢትዮጵያ ማለት አንድ ህዝብ፣ አንድ ሰንደቅ ዓላማ፣ አንድ አገር፣አንድ ቋንቋ የሚሉና ይሄ የሚቀናቸው አሉ፡፡ እና ይሄ በሰላማዊ መንገድም እንንቀሳቀሳለን በሚሉት መካከል ፅንፉ ብዙ ነው ፡፡ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ነው የሚያዋጣው የሚሉት ደግሞ በአንድ የጋራ ጉዳይ ላይ ይስማማሉ፡፡ ይህም ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ታአማኒነት ያለው ምርጫ ማካሄድ፡፡ ይሄንን እውን ለማድረግ ለምን አንተባበርም የሚል ነው የእኛ ሃሳብ፡፡

እና በዚህ የተነሳ የፖለቲካ ድርጅቶችን ለማስተባበር ስንለፋ ኖረናል፡፡ እነዚህን በማስተባበርም ብዙ ጊዜ ተሳካልን ያልንባቸው ጊዜያትም ነበሩ፡፡ አንዱ ውጤት ያስመዘገብንበትም የደቡብን የፖለቲካ ፓርቲዎችና ብሄር ብሄረሰቦች ሰብስበን የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ህብረት የሚል አቋቁመን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በዚሁ ስንንቀሳቀስ ነበር ፡፡ በዚህም አማካኝነት የ2002 ምርጫ በደቡብ ክልል ተንቀሳቅሰን በአንድ ዞን ኢህአዴግን ሙሉ ለሙሉ አሸንፈን ነበር ለማለት ይቻላል፤ በተለይም በሀዲያ ዞን በከንባታና ጠንባሮ የተወሰኑ ወረዳዎች፡፡ ይሄ ነው እንግዲህ ምክንያት ሆኖ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ህብረት ፖለቲካ ፓርቲዎች ማሰባሰብ የቻለውና የ1997 ምርጫ እንቅስቃሴን የፈጠረው፡፡ለዚህ ሁሉ መነሻው ቀደም ብለን በደቡብ ህብረት ያስመዘገብነው ድል ነው፡፡ ለቅንጅትም መፈጠር ይሄው ነው ምክንያት የሆነው ፡፡ እኛ ከደቡብ ህብረት ቀጥሎ ሰፋ ያለው ስብስብና የኢትዮጵያ አማራጭ ኃይሎች ምክር ቤት ብለን ያቋቋምነውና ወደ50 የሚሆኑ የፖለቲካና ሲቪክ ማህበራት ተሰባስበው ያቋቋሙት ሁሉ የእኛ ልፋትና ሥራ ውጤት ነው፡፡ እንግዲህ በዚህ ሁሉ ህዝቡን ያሳተፈ እንቅስቃሴ አድርገናል ፡፡ ሆኖም ግን ይሄ ሁሉ እየታየ ፈረሰ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አንዳንድ አብረውን የነበሩ ፓርቲዎች ጥቅማችን በደንብ አልተጠበቀልንም ፣ አንዳንዶች ብቻ ጎልተው ታዩ ወዘተ የሚል ነገርም ያነሱ ነበር ፡፡ ከዚያ አማራጭ ኃይሎች ተልፈስፍሶ ሲቀር ህብረትንና ቅንጅትን ወደ ማቋቋሙ ተሄደ ፡፡

እና አንድ ላይ አብሮ ለመሄድ ምንድን ነው ችግሩ? ላልከው እኛ መቼም ከፍተኛውን ጥረት አድርገናል፤ እውነቱን ለመናገር በነፃ ምርጫ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብሎ የተንቀሳቀሰውን ኃይል ማለትም ውጭም አገር ውስጥ ያለውም ሁሉ ሳይቀር አስተባብረን የኢትዮጵያ ህዝብ ተስፋ እስከሚሰ ንቅበት ደረጃ ድረስ አድርሰናል፡፡ ግን ያ ሁሉ አሁን የለም፡፡ ምንድን ነው ችግሩ? የጥቅም ሽኩቻ ነው ፡፡ ጥቅም ስል የፖለቲካ መስመር ጉዳይ ነው፡፡ ቅድም እንዳልኩት የፅንፉ አይነት ነው፡፡ ፌዴራሊዝም ኢትዮጵያን የሚበትን ነው፣ ይሄ የጎሳ ፌዴራሊዝም ነው፣ ክልል ምናምን የሚሉትንም ጭምር እኮ ነው ያየነው ፡፡ አይ በምርጫ ብታሸንፉ እኮ ይሄንን አጀንዳችሁን ተግባር ላይ ማዋል ትችላላችሁ ብለን ሁሉ ለማሳመን ሞክረናል ፡፡

የዚህ የምርጫ ጉዳይ የሁላችንም የጋራ ጉዳይ ነው ለምን በዚህ ጉዳይ ላይ እንኳን አንስማማም ? ስንል መጀመሪያ ላይ የሚስማሙ ይመስሉና ኋላ ግን ማን ነው አመራሩን የሚይዘው? ማነው ዋናው ?ወዘተ የሚሉ ጉዳዮች ቀስ እያሉ ይመጣሉ፡፡ እና እኔ ሳጠቃልለው በዚህ በሰላማዊ አግባብና በምርጫ ለውጥ እናምጣ የሚሉቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንድ የሚፈፅሙት ትልቅ ስህተት አለ ፡፡ ተንቀሳቅሶ አንድ ውጤት ካስመዝገቡ በኋላ ታሪካዊ የሆኑ ጉዳዮችንና መለስተኛ ፕሮግራሞችን እንዴት ሥራ ላይ እናውላለን በሚሉ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ልዩነት አለ፡፡

ለምሳሌ መድረክ ምንድን ነው የሚለው? ተሳክቶልን ኢህአዴግን በምርጫ አሸንፈን መንግሥት ብናቋቁም የምናቋቁመው መንግሥት የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ነው ብለን አስቀምጠናል ፡፡ ይሄ የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ይዘቱ የሚሆነው ሌሎችንም ያሳትፋል፡፡ ለብቻው የራሱን መንግሥት አያቋቁምም፡፡ ምክንያቱም መድረክ አንድ አይነት ርዕዮተ ዓለም የለውም፡፡ አራትና አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ፤ በውስጡ፡፡ እናም የሚለያዩባቸው ጉዳዮች አሉ ማለት ነው፡፡ግን በመለስተኛ ፕሮግራሞች የተገናኘን ነን ፡፡ አንድ፣ ሁለት ፣ሶስት ፣አራት ተብሎ እነዚህ ልዩነቶች መጀመሪያ ይፈቱ፡፡ ከዚያ የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ሲቋቋም እያንዳንዱ ፓርቲ ወደ ዝርዝር ፕሮግራሙ ሊሄድ ይችላል የሚል ነገር እናነሳለን፡፡ ነገር ግን እነኚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዝርዝር የፖለቲካ አጀንዳችን ጎልቶ አልታየም ፣ መሬት ይሸጥ ይለወጥ ፣ ይሄ የጎሳ ምናምን ይፍረስ የሚል ዝርዝር ፕሮግራሞችን ለማጉላት የመሞከር አይነት ነገር አለ ፡፡ኧረ አይደለም! እነዚህ ጉዳዮች አሁን ይቀመጡ፡፡ ሁኔታዎች ሲመቻቹ ያኔ በእነዚህ በራሳችሁ የፖለቲካ ፕሮግራሞች ተወዳድራችሁ ስልጣን ለመያዝ ትሞክራላችሁ ፡፡ አሁን ግን የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ማቋቋም ነው፣ እርቀ ሰላም ማውረድ ነው እና እስከዚያ መታገስ ነው ሲባሉ አይሰሙም ፡፡ እና ይሄ መንስኤው ያው የዲያስፖራ ፖለቲካ ነው፡፡ ምንም የተደበቀ ነገር የለውም ብዙው ድጋፍ የሚገኘው ከዲያስፖራ አባላትና ደጋፊዎች ነው ፡፡ ያ እዚያ ያለው ወገን ደግሞ አገር መግባት አቅቶት በቁጭት የሚኖር ነው፡፡ ለውጡ አንድ እሱ በሚያልመው መልክ እንዲመጣም ይፈልጋል ፡፡ እነዚህን ዝርዝር የፖለቲካ አጀንዳ ይዛችሁ ካልወጣችሁ በስተቀር ገንዘብ አንሰጣችሁም የሚባል ነገር አለ ፡፡

አሁን ለምሳሌ መድረክ በአንድ አባሉ ከሆነ ፓርቲ ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብቶ ያንን ፓርቲ ለጊዜው አግዶታል ፡፡ ከዚህ ፓርቲ ጋር የነበረን ችግር መድረክ ያስቀመጠው መለስተኛ ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደንብ አለ፡፡ ሥራ ላይ የሚያውለው መርሀ ግብርና እንቅስቃሴ አለ፡፡ እሱን ይተውና በጎን ሰላማዊ ሰልፍ ጠራሁ ይላል ፡፡ በዚያ በኩል ደግሞ ስብሰባ ጠራሁ ይላል ፡፡ ሌላም ሌላም፡፡ እዚያ ውጭ ባለው ሬዲዮናቸው ደግሞ ይሄንኑ ያስተጋበሉ ፡፡ ከዚያ ሰባት ስምንት ሆነን የሰበሰብነው መድረክ ይቀርና አንድ አባል የሆነው ፓርቲ ስሙን አግንኖ ለማውጣት ይፈልጋል ፡፡እነዚህ ፓርቲዎች መጀመሪያ መድረክ ውስጥ የገቡት ኢህአዴግን ለብቻዬ ተፎካክሬ መለወጥ አልችልም በሚል ግንዛቤ ነው ፡፡ ግን ደግሞ ለብቻው ታዋቂ ለመሆን ያምረዋል፡፡

ይሄ እንግዲህ እዚያ ውጭ ያሉ የካዝናውን ቁልፍ የያዙት ድጋፍ ሰጪዎች ተፅእኖ ነው፡፡ በእርግጥ እነዚህ ፓርቲዎች ይሄንን ተፅዕኖ መስበር አይችሉም ፡፡ምክንያቱም ጥገኞች ናቸው ፡፡ የቢሮው ኪራይስ በምን ይከፈላል ? ወጪው ከየት ይመጣል ? ሰልፍ ቢጠራስ በምን ገንዘብ ይወጣል ? ወዘተ ወጪው ብዙ ነው ፡፡ እና ከዚህ ሁሉ የተነሳ አገራዊ የሆነ በቂ ድጋፍ የለም ፡፡ ድህነቱ አለ፡፡ ከዚህ ሌላ ደግሞ ኢህአዴግ ማነው ከተቀዋሚ ጋር የሚውለው ? ይላል ፡፡ በየነ ከማን ጋር ነው የተጨባበጠውና ምሳ የበላው? በሚባልበት አገር ማነው ለፖለቲካ ፓርቲ ድጋፍ የሚሰጠው? ሌላ አገር እያንዳንዱ ሀብታም ከየትኛው ፓርቲ ጋር አግባብነት እንዳለው ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ አሜሪካ አገር ዴሞክራቶችን የሚደግፉ ከበርቴዎች ይታወቃሉ፡፡ በሚሊዮኖች ይሰጣሉ፡፡ይሄ ዴሞክራሲ በሰፈነባቸው አገሮች የታወቀ ነው ፡፡

እዚህ ግን ጋብቻ ሁሉ ክልክል አይነት ነው የሚመስለው፡፡ ደግነቱ ቀደም ብለን አግብተናል ፡፡ ልክ ቆሻሻ እንደነካው ጨርቅ ስብሰባ ላይ እንኳ ስንገናኝ ሰላም ለማለት የሚፈሩ ባለሀብቶች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ እና በዚህ በትልቅና ብዙ ሚሊዮን ህዝብ ባለበት አገር በዚህ አይነት ሁኔታ ለመንቀሳቀስ ያስቸግራል፡፡ ይሄንን ለመተግበር ብዙ ድጋፍ ያስፈልጋል ፡፡ እናም ብዙዎቻችን ውጭ ያሉ ደጋፊዎቻችንና አባሎቻችን ጋ ነው የምንሄደው ፡፡ ይሄ በእርግጥ የኢትዮጵያን ህግ እስካልጣሰ ድረስ ነውር የለውም፡፡ ስለዚህ ብዙ ፓርቲዎች ነፃ አይደሉም፡፡ ይሄንን ነው የማምንበት ፣ በዚህ ነው የተቀላቀልኩትና የተስማማሁት፣ በዚህ መንገድ እሄዳለሁ ለማለት ነፃነት የለም፡፡ እና እንዲያው ዝም ብሎ ሰው እንደቀላል ነገር አድርጎ ይተቻል ፡፡ እነዚህ ሰዎች ተበታተኑ ይላል፡፡ ግን እኛ ውስጥ ሆነን ስንት እንደምንለፋ የሚያውቅ የለም፡፡ ስንት ለፍተን ያሰባሰብነው ተመልሶ ይበታተናል ፡፡ ይሄ ነው ዋናው ችግር፡፡

ዘመን ፡- ይሄንን ልዩነት በመፍታትና የአገርንና የሕዝብን ጥቅም በማስቀደም የማይሰራው ለምንድን ነው? ከወቅቱ የዓለም አቀፍና የአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ አንፃር ስምምነት ፈጥሮና ልዩነቶችን አቻችሎ መሄድና መታገል አይቻልም ?

ፕሮፌሰር በየነ ፡- የአገር ጥቅም ከተባለው ብነሳ እኔ የአገራችንን ጥቅም የሚፃረር ነገር ውስጥ የገባ፤ በሰላማዊ መንገድ የሚታገል የፖለቲካ ፓርቲ አላየሁም፡፡ በአካሄድ ላይ ልዩነት ካለ መተቸትና አማራጭ መስጠት ያለ ነው፡፡ ለምሳሌ የህዳሴውን ግድብ ብናነሳ እሱ የሁላችንም አጀንዳ ነው ፡፡ ግን የተመረጠው ጊዜና አቅም ለዚህ ይፈቅዳል ወይ? ብለን አስተያየት የሰጠንበት ጊዜ አለ ፡፡ ፕሮጀክቱን ግን የምንኮንነው አይደለም ፡፡ በሌላውም ጉዳይ እንዲሁ ገዢው ፓርቲ የኢትዮጵያን ጥቅም በብቃት እያስከበረ አይደለም ፡፡ አንዳንድ በማይገባንና ብዥ በሚል ሁኔታ የአገሪቱን ጥቅም አሳልፎ የሰጠባቸው ሁኔታዎች አሉ ብለን አቋም የያዝንባቸው አሉ ፡፡ ይሄ እኔም ፓርላማ በነበርኩባቸው ጊዜያት የተከራከር ኩባቸው ጉዳዮች ናቸው ፡፡ ይህ የተቃዋሚ ፓርቲ ፀባይም ነው፡፡ መተቸት ያለ ነው ፡፡ ግን በሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ የአገር ጥቅም ተላልፎ እንዳይሰጥ ነው ማሳየት ያለብህ፡፡ ያንን ሚና ሳትጫወት ስትቀር ነው ችግሩ፡፡ እና ፓርቲዎች ሚናቸውና ፋይዳቸው የአገርን ጥቅም ማስጠበቅ ነው ፡፡ ስለዚህ ፓርቲዎች የኢትዮጵያን ጥቅም አደጋ ላይ የጣሉበት ሁኔታ እኔ አይታየኝም ፡፡ገዢው ፓርቲ አካሄዱ ታሪካዊ አይደለም ፣ የግምት ስህተት አድርጓል ፣ የአገራችን ጥቅም ላይ ይደራደራል ወዘተ የሚል ትችት እናቀርባለን ፡፡ ይሄ ማለት ያለብን ነው ፡፡ ይሄንንም ስንል መረጃዎች እንዲኖረን ጥረት እናደርጋለን እንጂ ዝም ብለን ከአሉባልታና ከጥላቻ ተነስተን አይደለም ፡፡ ይሄ ለእኛም ክብር አይሰጥም ፡፡ ምክንያቱም ነገ ጉዳዩ ይፋ ሲሆን የምናፍርበት ነገር ውስጥ መግባት አንፈልግም፡፡ እና እንዳልኩት የፍላጎቶች መጣረስና አንድ ላይ የመሆን ጉዳይ ላይ መስማማትና መለስተኛ አጀንዳ ላይ ተግባብቶ መሄድን እንደ መርህ ለመውሰድ ፓርቲዎች ብቃት ያላቸው መሆን አለባቸው፡፡ እኔ እውነቱን ለመናገር ይሄ ብቃት የሌላቸው ሆነው ነው ያገኘኋቸው ፡፡ ሰባ ድረስ የደረሱት ሰላማዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች በታሪካዊ ጉዳዮች ላይ መሰባሰብና ምርጫ ላይ ትኩረት አድርገው ኢህአዴግን በህብረት መፎካከር የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር ሲችሉ ወደ ዝርዝር ጉዳይ ይገቡና የተፈጠረውን ህብረት ወደ መበተን ይሄዳሉ፡፡ ችግሩ ይሄ ነው ፡፡

ነገር ግን በሌላ የዳበረ ዴሞክራሲ ባላቸው አገሮች ውስጥ የሚታየው አይነት በእኛ አገር የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የመቻቻል ፖለቲካን ለመፍጠር ዕድሉ አለ ወይ? ለተባለው ጥያቄ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ በራሳቸው በኩል ያለውን ድክመት ማረም አለባቸው ነው የምለው ፡፡ ይኼን ማረም የሚችሉት ደግሞ ምን ሲሆን ነው? እነዚህ ፓርቲዎች ብቃት ባላቸው ሰዎች መመራት አለባቸው፡፡አገሪቱ ያስተማረቻቸው ምሁራንና በፖለቲካውም ዓለም ክህሎት ያላቸው ሰዎች ወደ አደባባይ ወጥተው በፖለቲካው መሳተፍ አለባቸው፡፡ እስከ አሁን እንደምንሰማው ትልልቆቹ ሰዎች የምንላቸው ሳይቀሩ ከፖለቲካና ከኮሬንቲ መራቅ ነው የሚል ብሂል አላቸው ፡፡ የእዚህ ምንጩ በደርግ ጊዜ ሰው ላይ የደረሰው ከፍተኛ ጭፍጨፋ ነው ፡፡ ግማሹ ከቁስሉ ያልሻረ ነው፡፡ አስርና አስራ አምስት ዓመት ታስሮ የወጣ ነው ፡፡ ከዚያ ወጥቶ እንደገና ትምህርት ቤት ገብቶ እንጀራ ቆርሶ ቤተሰቡን ሰብስቦ መኖር የሞከረ ቁስለኛ ነው የሞላው ፡፡ እና ይሄ ደግሞ የፖለቲካው መድረክ ላይ ተገኝቶ አመራር እየሰጠም እየተሳተፈም አይደለም፡፡ ፓርቲዎች የሚመሩት የድሮ አገር ወዳድና የእናት አገር ፍቅር አቃጠለን በሚሉ ሽማግሌዎች ነው፡፡(ሳቅ) እኔ ባለፉት ሃያ አካባቢ ዓመታት በተለያየ ደረጃ የፖለቲካ ፓርቲ አቋቁመናል ከሚሉ ወገኖች ጋር ለመነጋገር ሞክሬአለሁ፤ ከነ ደጃዝማች ፣ ከነራስ ወዘተ ጋር፡፡ ሁሉም ከራሳቸው ካላቸው ግንዛቤ ተነስተው ነው ፓርቲ የሚያቋቁሙት፡፡

የእናት አገራችን ነገር ዕረፍት ነሳን ይላሉ፡፡ እንግዲህ የኢትዮጵያ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ ብቃት ባለውና የዘመኑ ፖለቲካ በገባው ሰው መመራት ይገባው ነበር ፡፡ አንዳንዴም ኢህአዴግ መተካካት እንደሚለው ይሄ ፋሽን ተደርጎ ወጣት ወጣት እየተባለ እኛም ጋ ወጣት መሆን አለበት ይባላል፡፡ ይሄ ደግሞ ትግሉ የሚጠይቀውን መስፈርት ግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ ሁኔታን ነው የሚያሳየው፡፡አንዳንዴ የአገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ በአግባቡ ያልተረዱ ወጣቶችን ዝም ብሎ ብቻ ወጣት ትኩስ ኃይል ነው ይደፍራል፣ ያለፍቃድም ሰላማዊ ሰልፍ ይወጣል፣ ዱላም ቢያርፍበት ይችላል የምትለዋን ይዘው ይሄንን ለማስተጋባት ይሞክራሉ፡፡ ይሄም የሰከነ አመራር አይደለም፡፡ ኢህአዴግ የሆነ ነገር ሲል ምን ለማለት ፈልጎ ነው? ከየት አቅጣጫ ነው የመጣው? የኃይል አሰላለፉን ከአገር አቀፍም ከዓለም አቀፍም አይቶ ያለው ሁኔታ ምንድን ነው? የሚለውን አይቶ በዚያ ግንዛቤ መድረክ ላይ ወጥተው አንድን ፓርቲ ለመምራት ብቃት ያላቸው ሰዎች አለመታየታቸው አንዱ ትልቁ ችግር ነው፡፡

ወጣት ወጣት ይባላል ፡፡ አንዳንዶቹ የሚመጡት ወይ ሥራ አጥተው ወይ ዩኒቨርሲቲ ጨርሰው እዚህና እዚያ ብለው በብሶት የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ በብሶት መንቀሳቀስና ይሄ አላማዬ ነው ብሎ ወደ ትግል መግባት የተለያየ ነገር ነው፡፡ ተቃውሟችን የብሶትና የጥላቻ መሆን የለበትም ፡፡ የመርህ ነው መሆን ያለበት፡፡ ይሄን መርሀችንን በዘላቂነት ይዘነው የምንቆየው ነው ወይስ አንዳንድ እርማቶች ሲደረጉ ትተነው ወደ ቤት የምንገባበት ነው? ስለዚህ የፖለቲካ ፕሮግራሜ ኢህአዴግ ከሚለው በርዕዮተ ዓለማዊ ነው ወይስ በፍልስፍናዊ ነው ልዩነቱ? በሚል ደረጃ የሚያስቡና የሚሰሩ መሪዎች ያስፈልጋሉ ፡፡ ይሄ ብቃት የለም ፡፡ ሃሳብን ወደ ክርክርና ፍጭት የሚያስገቡ ሰዎችን አናይም፡፡ ጥቂት ደፈርን የሚሉ ልጆችን ደግሞ ኢህአዴግ ያወጣውን ህግ ጣሱ እየተባለ ይታሰራሉ ፡፡ ይሄ ደግሞ ለፓርቲያቸው አስታዋፅኦ እንዳያደርጉ ያደርጋል ፡፡ እና ይሄ አገሪቱ ያፈራቻቸው የተማሩ የሚባሉትም ማኪያቶ እየጠጡ ብሶት ከማውራት አልፎ በዚህ በፖለቲካው ጉዳይ ላይ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ሁሉ ከፍለው አደባባይ ወጥተው ለትግሉ አመራር መስጠት እስካልጀመሩ ድረስ እየተምቦራጨቅን እንኖራለን፡፡ ኢህአዴግም ያው ውሾቹ ይጮሀሉ ግመሎቹ ይቀጥላሉ ይላል፡፡ እና በዚህ አይነት ሁኔታ ከዚህ አዙሪት ውስጥ የሚያስወጣን አይኖርም፡፡ ስለዚህ ብዙ ይቀርናል ፡፡

ዘመን ፡- መንግሥትስ በአገሪቱ ውስጥ ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲኖሩ የሚወጣው ኃላፊነት የለም ? የዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ እንዲጎለብት መንግሥት ማመቻቸትና ማድረግ ያለበት የቤት ሥራ የለም ይላሉ ?

ፕሮፌሰር በየነ፡- እንግዲህ ሁሉም መደማመጥ መጀመር አለበት፡፡ ገዥው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቆም ብለው መነጋገር መቻል አለባቸው፡፡ ፈረንጆች pick in choose ይላሉ፡፡ አንድ አካል የፈለገውን ነገር ብቻ ወስዶ ሌላውን በማይሆን ነገር መፈረጅ አይነት ማለት ነው፡፡ አሁን ኢህአዴግን ብትጠይቀው ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የጋራ የፖለቲካ ምክር ቤት አቋቁመን አብረን እየሠራን ነው ይላል ፡፡ ማናቸው የእዚያ ምክር ቤት አባላት? ቢባል ያ pick in choose ያልነው አይነት ነው የሚሆነው፡፡ እነዚያ ተፈላጊዎቹ ታማኝ ተቃዋሚዎቹ ናቸው፡፡ ከእኛ ከቀረነውና ከዚህ በፊት በምርጫና በፖለቲካው መድረክ ተወዳድረን ኢህአዴግን አሸንፈንና እንቅስቃሴዎችን መርተን ብቃት ያለው ውድድር ካደረግነው ጋር ደግሞ መነጋገር አይፈልግም፡፡ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ካረፉ ጊዜ ጀምሮ ይሄን አገር ከሚመራው አካል ጋር ተገናኝተን አናውቅም፡፡ ውይይት መኖር አለበት፡፡ ከልዩነት ጋር አብሮ መኖር ይቻላል፡፡ የሃሳብ ልዩነት ነው እንጂ ከእያንዳንዱ ግለሰብ ጋር ምን አገናኝቶኝ ነው የምጣላው? የመስመርና የሃሳብ ልዩነት ላይ ተመርኩዘን ነው የምንከራከረው እንጂ እኔ ግለሰቦች ላይ ጥላቻ የለኝም፡፡ ምንም አያገናኘንም፡፡ እና ይሄንን የሃሳብ ልዩነት አክብሮ መሥራት ነው ለህዝቡም ለአገሪቱም የሚበጀው፡፡ እና በመነጋገር መፍትሔ ፈልጎና ያለመግባባት እንዳይኖር ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ገዥው ፓርቲም እየተወጣ አይደለም፡፡

ያው አሻፈረኝ እንዳለ ነው ያለው፡፡ መንግሥትና ገዥው ፓርቲ አንድ የሆኑበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ገዥው ፓርቲ አጋር ከሚላቸው ውጭ ለመድኃኒት ቢፈለግ እንኳ ሌላ ሰው በውስጡ አይገኝም፡፡ በመንግሥት መዋቅሩ ውስጥ ኢህአዴግ ከሆነው ውጪ ብቸኛ የሚባል ማን ሰው አለ? አንድ ሰው አሉ መሰለኝ ያኔ በሽግግሩ ጊዜ አብረን የነበርን፡፡ እና ሁሉም አንድ ናቸው፡፡ በአንድ ጉዳይ ላይ በእኔ አስተያየት እንዲህ ቢሆን ያሻላል ብሎ የተለየ ሃሳብ የሚያቀርብ ሰው አይኖርም፡፡እንዲህ አይነት ነገርም አይታሰብም፡፡ ፖሊሲው ፣ አሰራሩ ሁሉም ነገር አንድ ነው፡፡ ሁሉም ነገር ልዩነት የለውም፡፡ ደቡብ ብትሄድ ሌላውም ጋ አንድ ነው ይዘቱ ሁሉ፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ ከእዚህ አይነት አሰራር ለመውጣት ከራሱ ጋር ቢታገል ጥሩ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ በራስ የመተማመን ጉዳይ ነው፡፡ ፡፡ ነገሮችን ሁሉ በራሱ ብቻ የመቆጣጠር ነገር አለ፡፡ ተኝቶ አያድርም፡፡ እነዚህ ሰዎች ፓርቲ የሚያቋቁሙት ሊበቀሉኝና ሊያጠፉኝ ነው የሚል ስጋት አለበት፡፡ ይሄን ደግሞ አድርጎ ያውቃል፡፡ ከ1997 ምርጫ ማግስት ለምንድን ነው አዲስ አበባ ውስጥ ምስኪንና ጠግበው ያላደሩ ልጆችን መንገድ ላይ ጎማ አቃጠላችሁ፣ ድንጋይ ወረወራችሁ ብላችሁ እርምጃ የምትወስዱት? ስንል ፡፡ እንዴ ሊያጠፋን ነው ፡፡ አንተ የፀጥታ መረጃ የለህም ሁሉ ተብያለሁ ፡፡ እኛ የፀጥታ መረጃ ስላለን ይሄን አደጋ ቶሎ መቀልበስ አለብን ነው ሲሉ የነበሩት፡፡

ዘመን ፡- ግን ፕሮፌሰር የእዚያን ጊዜ ህገ መንግሥቱን በኃይል ለመናድና በጉልበት መንግሥት ገልብጦ ሥርዓት ለመለወጥ የተነሱ ኃይሎች ወጣቱን ተጠቅመው ወደ አልተገባ ብጥብጥ ውስጥ ተገብቷል የሚል ነበር፡፡

ፕሮፌሰር በየነ ፡- ብሶት አለኝ የሚል ህዝብ ተደራጅቶም ሳይደራጅም በአንድ ከተማ ውስጥ ወጥቶ እሳት የሚያቀጣጥልበት ሁኔታ ሞልቶ የለም እንዴ? አሜሪካም ቢሆን ስንቴ ነው እሳት የሚነሳውና ንብረት የሚወድመው? ህዝቡ መሣሪያ አንስቶ ጦርነት ውስጥ እስካልገባ ድረስ ስሜቱን የሚገልጽበት ሁኔታ አለ፡፡ ህዝቡ ምርጫው ተጭበርብሯል ብሎ ቢወጣ መንግሥትን በምን ዓይነት ሁኔታ ነው የሚገለብጠው ? መንግሥት እኮ የጦር ኃይሉን ሁሉ ተቆጠጣሮ ነው ያለው፡፡ የተለያየ የተደራጀ ኃይል እያለ፡፡ እኔ በዚያን ጊዜ በግል ባለሥልጣናትን ጉዳቱን አንስቼ ወቅሻአቸዋለሁ፡፡ እና መንግሥትና ገዢው ፓርቲ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ አድርገን በአገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፎ እናደርጋለን፡፡ ቢቻለንም ለውጥ እናመጣለን የሚሉትን ወገኖች ማደፋፈር አለበት፡፡ እነዚህ ብቃትና ጥራት የሌላቸውን ፓርቲዎች ብቻ ሰብስቦ ሳይሆን በእውነት ተወዳድረው ማሸነፍ ከሚችሉት ጋር መነጋገር አለበት፡፡

ዘመን ፡- ለአገራችን የዴሞክራሲ ሥርዓት ማበብ የሚጠቅመው ይሄ ነው የሚሉት ?

ፕሮፌሰር በየነ፡- አዎ! ይሄ ነው የሚጠቅመው፡፡ ይሄ ካልሆነ ይሄንን ሥርዓት በጉልበት እንደመስሳለን፡፡ በእሱ አመድ ላይ አዲስ ሥርዓት እናቋቁማለን ለሚሉት ወገኖች መንገድ መስጠት ነው፡፡ ምክንያቱም እኛ ዋጋ ቢስ ናቸው ተብለን ነው የምንታሰበው፡፡ ዝም ብለው በምርጫው ይገባሉ፡፡ ግማሹ ይታሰራልና በቃ ዋጋ የላቸውም፡፡ ከጅብ የማያስጥል የአህያ ባል እየተባልንም ነው፡፡ ዲያስፖራውም ችግር አለበት ፡፡

ዘመን ፡- ልክ ነው ፕሮፌሰር እዚህ ጉዳይ ላይ ጥያቄ ላነሳ ነበር ፡፡ እርስዎ ለአንድ ዓመትም ቢሆን ውጪ ስለነበሩ እስኪ እዚያ ያለውን የዲያስፖራ ሁኔታ ይንገሩን ?

ፕሮፌሰር በየነ፡- እንግዲህ ዲያሰፖራው በእያንዳንዱ ዲሽ ባለበት ቤት በር እያንኳኳ ማለት የሚፈልገውን እያለ ነው ፡፡ ይሄ እኮ ምስክር አያስፈልገውም፡፡ አንዴ ኢሳት ይላል አንዴ ሌላ ይላል ፡፡ በዚያ መልክ ተደራጅቶ በሥርዓቱ ላይ ያለውን ተቃውሞ ለመግለፅና ፕሮፖጋንዳ ለመንዛት ብቃት ያዳበረ ነው፡፡ በአንድ የዲፕሎማቲክ ግቢ ውስጥ ገብቶ የማይፈልገውን ሰንደቅ ዓላማ አውርዶ የሚፈልገውን ለመስቀል የሚያስችል ድፍረት ያለውና እስከዚያም ድረስ የሚያምንበትን መስዋዕትነት በቆራጥነት ለመክፈል የደረሰ ነው ፡፡ ዲያስፖራ ስልህ ግን አብዛኛው ዝም ያለ ነው ፡፡ የተወሰነው ጥቂቱ ገንዘብ ያዋጣል ፣ የሚያስፈልገውን እንቅስቃሴ ሁሉ አማጦ ይጠቀማል ፡፡ በዚህም ባለው አቅም ሁሉ ይሄንን መንግሥት ለማሳጣት፣ ለማጋለጥና ለማዋረድ ጥረት የሚያደርግ ነው ፡፡ እንግዲህ እኔ ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ ለፖለቲካ ተልዕኮ ወደ ውጭ ስመላለስ የነበረው ዲያስፖራና የአሁኑን ሳወዳድር በዚያን ጊዜ ሁሉም ኢህአዴግን ማውገዝ ብቻ ነበር ሥራው ፡፡ አሁን ግን ኢህአዴግ ለዓመታት ባደረገው ጥረት ዋጋ ከፍሏል፡፡የራሱንም ደጋፊዎች ፈጥሯል ፡፡ ድረ ገፅ ከፍቶም ሆነ በሌላ ሁኔታ፤ ባያስፈልግም ሰልፍ የሚወጣ ደጋፊ አበጅቷል፡፡ በቀደም እንኳን ሰንደቅ ዓላማ አወረዱ የተባሉትን እንቃወማለን የሚሉ ወዲያው ሰላማዊ ሰልፍ እንዲወጡ ማድረግ የቻለበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ይሄን አይቻለሁ፡፡ እኔ መቼም ኢህአዴግን በዚህ ሥራው ሁልጊዜ የወፍጮ ቤት በግ ወይም ሙክት ነው የምለው። (በሳቅ ወደቅን)

ዘመን ፡- እንዴት ፕሮፌሰር ?

ፕሮፌሰር በየነ፡- ልብ ብለህ ከሆነ የወፍጮ ቤት በግ ጭንቅላቱንም እየተቀጠቀጠና ከወዲያና ከወዲህ እየተወገረና እየተወረወረበት የፈለገውን ነገር ሳይወስድ አይመለስም ፡፡

ዘመን ፡- ተቃውሞ ቢኖርም የፈለገውን ግብ ሳያሳካ አይመለስም ነው ?

ፕሮፌሰር በየነ ፡-ኢህአዴግ አንድ ነገር ካነሳ የፈለገበት ሳይደርስ ስሙን ብታጠፋ፣ የፈለከውን ብትወረውር፣ ምን ብትል አይመለስም ፡፡ዛሬ ባይሳካለት ነገ ይመለስበታል እንጂ ይሄ አያዋጣም ብሎ አይተውም ፡፡ እና ኢህአዴግ በዚህ ሙያው ተሳክቶለታል ፡፡ የራሱም ደጋፊ አለው ፡፡ በእሱም ስም የሚናገሩ አሉ፡፡ እኔ ስንቀሳቀስበት ከነበረው ካለፈው ሃያ ዓመታት ይለያል ፡፡ በየትላልቅ ከተሞች ዓመታዊ በዓላት ይከበራሉ ወዘተ ። እና ይሄንን አፍርቷል፡፡ በዚህ አይነት ሁኔታ እንግዲህ እዚያ ውጭ አገር በእግር ኳስ ቡድኑም ሳይቀር ደጋፊም ተቃዋሚም አለ፡፡ በቤተክርስቲያኑም አካባቢ የተከፋፈለ ነገር አለ ፡፡ ከዚህ በፊት የተሰደዱትን ጳጳስ የሚከተል ወገን ስለነበር እዚያ የነበረው ኦርቶዶክስ ኢህአዴግን አውጋዥ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ኢህአዴግ የራሱን ተከታዮች አፍርቷል ፡፡ እና እሱም በበኩሉ እየሠራ ነው፡፡ በተለይ ከ1997 ምርጫ ወዲህ እላይ ተሰቅሎ የነበረው ተስፋ ወድቆ ሲንኮታኮት ከዚያ መዳን አልተቻለም ፡፡ ማገገም አልተቻለም ፡፡ በቃ አለቀ ፡፡ ያኔ ከፍተኛውን ጥረትና ሙከራ አድርገናል፡፡ ያ ተኮላሽቷል ፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ ሰላማዊ የፖለቲካ ለውጥና ምርጫ የሚባለው ነገር የሞተና ያለቀ ጉዳይ ስለሆነ እንደነ በየነ ጴጥሮስ የመሳሰሉት ያለው ሥርዓት አጫፋሪዎች ናቸው ይላሉ፡፡ መጠቀሚያ ናቸውም ይላሉ፡፡ስለሆነም የኢትዮጵያ ህዝቦች የለውጥ ምኞት እየከሸፈና ተስፋው እየጨለመ ነው፡፡ እናም በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለውጥ አላመጣም ብሎ ምሎ ከተገዘተው ኢህአዴግ ጋር ምርጫ ምርጫ እያላችሁ ህዝቡን ከፍተኛ መስዋዕትነት እያስከፈላችሁ ነው ብለው ይከሱናል፡፡በእርግጥ ለእኛ ኢትዮጵያዊነታችንን ማንም የሚሰጠንና የሚነሳን የለም፡፡ነገር ግን እነርሱ ጋ (ዲያስፖራው) ብዙ የመመፃደቂያ ነገር እናያለን ፡፡ ፖለቲካው በእነማን እጅ ቢመራና ቢንቀሳቀስ ነው ትክክለኛው ኢትዮጵያዊ የሆነ ለውጥ የሚመጣው? የሚለውም ላይ ብዙ ልዩነት አለ፡፡ አሁን ኢትዮጵያዊነት የሚባለው እንቅስቃሴ ውስጥ ድሮ አብረውን ላለፉት ሃያ ዓመታት ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ይሄ የምርጫ ፖለቲካ በሚባለው ነገር ላይ ተስፋ ቆርጠው ብዙ ጊዜአቸውንና ሀብታቸውንም በዚህ በተቃውሞ ጉዳይ ላይ ሲያውሉ አይቼ ነው የመጣሁት፡፡ ለቀረነው በኢትዮጵያዊነት ክልል ውስጥ ነው የምንንቀሳቀሰው ለምንለው ደግሞ ጆሮ እየሰጡ አይደለም ፡፡

ዘመን ፡- እንደሚታወቀው በቀጣይ ከፊታችን ምርጫ አለ ፡፡ በእዚህ ምርጫ ላይ ተሳትፌ ወደ ፓርላማ እገባለሁ የሚል ሃሳብ አለዎት ?

ፕሮፌሰር በየነ ፡- ይሄ ታሳቢ የሚሆነው ኢህአዴግ በ2002 ዓ.ም አሸንፍኩ የሚለውን ቲያትር የማይደግም ከሆነ ነው፡፡ ያንን ከደገመ ያው የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት የመገንባቱ ተስፋ ላይ የመጨረሻ በረዶ ውሃ መቸለስ ነው የሚሆነው፡፡ይህንን እያደረገ እስከ መቼ እንደሚቆይ ይቸግረኛል ። በባለፈውና ከዚያ በፊትም በተወዳደርንባቸው ምርጫዎች ላይ ማን ማሸነፍ እንደሚችልና የት ማሸነፍ እንደሚቻል ይታወቃል ፡፡ ባለፈው ምርጫም እኔን ካልገባህ ተብዬ በዚህም ሰውን ለማደፋፈርና ሌሎች ታጋዮች ተሳትፎ እንዲያደርጉ በማሰብ ነው ራሴ እዚያ ምርጫ ውስጥ የተሳተፍኩት እንጂ እዚያ ተመርጦ ቁም ነገር መሥራት እንደማይቻል አውቃለሁ። እኔ መጀመሪያ ፓርላማ በገባሁበትና በመካከሉ በ1997 ምርጫ በገባሁበት ጊዜ መካከል እንኳ ልዩነት አለ፡፡ ቀደም በነበረው ፓርላማ የፈለግሁትን ያህል መናገር የምችልበት ሁኔታ ነበር፡፡ በቀጣዩ ደግሞ ያም ስጋት ፈጠረባቸውና አንድ ፣ሁለት ፣ ሶስት ደቂቃ ወደ ማለት ተሸጋገሩ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ባልጠፋ ጊዜ፡፡ በዚህም ልዩነታችንን የምናብራራበትን ዕድል እንዳናገኝ የተደረገበት ስልታዊ ሁኔታ ነበር የተፈጠረው፡፡

ዘመን ፡- ያ ምናልባት የውጭ አገራት ልምድ ነው ተብሎ ነበር በፓርላማ ተግባራዊ የሆነው፡፡

ፕሮፌሰር በየነ ፡- በዳበረ የዴሞክራሲ ሥርዓት በሚያራምዱና በታዳጊ አገሮች መካከል አፈፃፀሙ ይለያያል ፡፡ አሁን ለምሳሌ በእንግሊዝ ፓርላማ ሁሉም ቢጯጯሁ ያው ናቸው፡፡ የእኛ ያሸነፈ በሙሉ ጠቅልሎ ይወስዳል የሚለው የመድብለ ፓርቲ ስርዓት በዚህ አገር ዴሞክራሲን ለመገንባት በር የሚከፍት አይደለም ፡፡ ተስፋ አስቆራጭ ነው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስንት ለፍተውና ተጎሳቁለው ፣ ታስረውና ፣ ተፈትተው፣ ተወንጅለውና ስንት ፍዳ አይተው ነው ፓርላማ የሚገቡት፡፡ ሌላው አገር ግን ዘና ብሎ ስሙን ሰጥቶ ነው የሚወዳደረው፡፡ ከዚህ አገር ቀዳን የሚባለው ውስጥ ሀቅ መኖር አለበት፡፡ እንግሊዝ አገር የሚጠቀሙበትን እዚህ እንጠቀም ብንል የክፋት ነው የሚሆነው ፡፡ እና ለሚመጣው ምርጫ ኢህአዴግ በ2002 እንዳደረገው አሁንም የአውራ ፓርቲ ይህቺን አገር በብቸኝነት የማስተዳደር አጀንዳ አለው ከዚህ ወይ ፍንክች የሚል ከሆነ የሞተ ነገር ነው፡፡ እና እዚህ ላይ መሳተፉ የሞኝ ለቅሶ ነው የሚሆነው ፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ተቀይረው የተሻለ ተፎካካሪነት የሚመጣበት ሁኔታ ለማምጣት ነው አሁን እየታገልን ያለነው ፡፡

ይሄም መነሻው ኢህአዴግ ከእኛ ጋር ይነጋገር ነው ፡፡ ለምሳሌ የ1997 ምርጫ የድርድር ውጤት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ህብረት ከኢህአዴግ ጋር በምርጫው ህግ ላይ ተደራድሯል ፡፡ የምርጫ ክርክሩ በሚዲያ በቀጥታ መተላለፉ ፣ታዛቢዎች ከአገር ውስጥ ሲቪክ ማህበራት ከውጭም ሁሉ እንዲሳተፉ መደረጉ በድርድር ያገኘነው ነው፡፡ ይሄ ከምርጫ 97 በኋላ ለግብር ይውጣ ነው ወደሚለው ተሸጋግሯል ። ስለዚህ የሚቀጥለው ምርጫ ቢያንስ በ 1997 ምርጫ ወደ ተወዳደርንበት ሁኔታ የሚመለስ ከሆነ አዎ እወዳደራለሁ፡፡ በዚያ አይነት ከሆነ መሸነፍንም በፀጋ እንቀበላለን ፡፡ አሁን ግን 99ና መቶ በመቶ አውራ ፓርቲ ነው ይህን አገር የሚገዛውና ወይ ፍንክች ሞቼ እገኛለሁ በሚልበት ሁኔታ ግን ምን ፋይዳ አለው ? ኳሱ በኢህአዴግ ካምፕ ውስጥ ነው ያለው ፡፡ ፓርቲዎች መወዳደር የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር አለበት ። በቀደም ከአንድ የውጭ ዲፕሎማት ጋር ስናወራ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምርጫው ሁሉንም ሁኔታ ልናመቻች ነው ብለዋል አለኝ።

ዘመን ፡- ምን አሉ ነው ያሉት ዲፕሎማቱ?

ፕሮፌሰር በየነ ፡- አሁን በፊታችን ያለው ምርጫ ሙሉ ለሙሉ ሰላማዊ፣ አሳታፊና ነፃ እንዲሆን መንግሥት ዝግጅት ጨርሷል አይነት ነው አባባሉ፡፡ ምርጫ ቦርድም የዛሬ ሳምንት በጠራው ስብሰባ ላይ ተገኝቼ ይሄንኑ ነው የደገመው፡፡ የሚገርመው ነገር አዳማ ላይ በተደረገው ስብሰባ ላይ እኛ ያልነውን አስተያየት ለህዝቡ ሳያሰሙ የሌለውን ነገር በጎን ሲናገሩ ነበር፡፡ ያኔ እኔ የተናገርኩትን ነገር ህዝቡ ቢሰማ ኖሮ በዚህ ምርጫ ጉዳይ ላይ ያለንን ስጋት ይረዳ ነበር ፡፡ ነገር ግን እንዲሰማ አልፈለጉም ምርጫ ቦርዶች ፡፡ የጊዜ ሰሌዳ ላይ እንነጋገር ከማለት በፊት ዋናው አስቸጋሪና ደንቃራው ጉዳይ ላይ እንነጋገር ብሎ ነው ያኔ የፖለቲካ ፓርቲ ተጠሪው ሁሉ የሄደው፡፡አዳማ ላይ ግን ሁሉም ተስማምተዋል ነው የተባለው ፡፡ ምርጫው አሳታፊ ነው ካሉ በተግባር ማሳየት አለባቸው፡፡ ካለፈው ጊዜ የተለየ ምን አዲስ ነገር ይኖራል? ምርጫ አስፈፃሚዎቹ እንደሆኑ የፓርቲ መታወቂያ የያዙ ካድሬዎች ናቸው ፡፡ ሹመኞች ናቸው ስንል ነበር ፡፡ አሁንም ሁሉንም በሬዲዮ ጠርተው በየቢሮው እንድትከቱና እንድትገኙ ብለዋል፡፡እና ምን ልዩነት አለው ? እኛ የምንለው ይሄ በኮንትራት በየስድስት ወሩ የሚሰራ ስራ ነው ስለዚህ ማስታወቂያ አውጡና ችሎታ ያላቸው ያመልክቱ ፡፡ አንድ ኮሚቴ እናቋቁምና እንመልምላቸው ነው የምንለው። ይህ ሲሆን በችሎታና በብቃት ይሆናል የሚሰራው፡፡ አሁን ግን በካድሬ መስመር ነው እየተሰራ ያለው፡፡ ስለዚህ አሁንም በተግባር የሚታይ ነገር እያየን አይደለም፡፡

ዘመን፡- ስለዚህ መንግሥት ለመጪው ምርጫ ቁርጠኛ ሆኖ ለዴሞክራሲያዊነቱ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ከወዲሁ መደረግ አለባቸው ነው እያሉ ያሉት ?

ፕሮፌሰር በየነ ፡-ካለፈው ምርጫ አሁን ልዩ ምርጫ ሊካሄድ ስለመሆኑ የሚያሳይ ምን እንቅስቃሴ አለ? ባለፈው ምርጫ ስህተቶች ናቸው ብለን ያስቀመጥናቸው ነገሮች በዝርዝር አሉ። እነዚህን ለማረም የተወሰዱ እርምጃዎች አሉ? ይህንን በዚህ አርመናል። ይሄ በዚሀ አይደገምም ቢሉ ምርጫውን ለማመን ይቻል ነበር፡፡

ዘመን ፡- አሉ ያላችኋቸውን ስህተቶች ምርጫ ቦርዱ በእርግጥ ስህተቶች ናቸው ብሎ ካመነ ስህተቶቹን የማረም አቅም የለውም ብለው ያስባሉ ?

ፕሮፌሰር በየነ -ምርጫ ቦርድ አቅም ሊኖረው ይገባል፡፡ ግን የለውም፡፡ የሙያ ብቃትም የላቸውም፡፡ እኛ ከዚህ በፊት የምርጫ ቦርድ ኃላፊ ከነበሩት ክቡር አቶ አሰፋ ብሩ ጋርም አብረን ሰርተናል ፡፡ እሳቸው የህግ ባለሙያም ነበሩ፡፡ ለራሳቸው የሙያ ስነምግባር ግዴታ እንዳለባቸው ያስቡ እንደነበር አይ ነበር ። ብዙ ጊዜም ተከራክረናል፡፡ በወቅቱ የሚስተዋሉ ስህተቶችንም ለማረም ጥረት ያደርጉ ነበር።እኛ ማስረጃ ስናቀርብ ምርጫው ሁሉ ይደገም ነበር ። በዚህም ሰራተኞችን ሁሉ ቀይረዋል ፡፡ እገሌ እኮ ካድሬ ነው ስንል መረጃ ይምጣ ይላሉ፡፡መረጃ ስናቀርብ ይቀይራሉ፡፡ አሁን ግን የዚህ አይነት ነገር የለም፡፡ መስክ ላይ ችግር አለ ሲባል ቢሮ ውስጥ አይቀመጡም፡፡ መኪናቸውን አስነስተው ይሄዳሉ ፡፡ የምርጫ ውጥረት አለ ከተባለ ችግሩ ባለበት የምርጫ ጣቢያ ነው ጊዜአቸውን የሚያሳልፉት፡፡ አስታውሳለሁ እኔ በተወዳደርኩበት ወረዳ ላይ ሄደው አይተው ከስነ ስርዓት ውጪ መሆኑን አረጋግጠው ምርጫው እንዲደገም አድርገዋል ፡፡ አሁን ግን እንዲህ ያለ ለሙያው ክብርና ጥንቃቄ የማድረግ ሁኔታ አይደለም ያለው፡፡

ዘመን ፡- ስለዚህ ቦርዱ አካባቢም የአሰራር ማሻሻያ ያስፈልጋል ማለት ነው ?

ፕሮፌሰር በየነ – መሻሻል አለበት፡፡ ሙያና ሙያተኛ መገናኘት አለበት፡፡ እንግዲህ በዚህ ዓለም ውስጥ አንድ ጊዜ ነው የምንኖረው፡፡ እንጀራውም ምግቡም አንድ ነው፤ የሚበላው ፡፡ ይሄ ሲጠሩት አቤት ሲልኩት ወዴት የሚሉት አይነት ነገር ነው እኔ የምታዘበው፡፡፡

ዘመን ፡- እንግዲህ ፕሮፌሰር በአገራችን ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያስፈልጋሉ ፤ ኢህአዴግን በብቃት ሊፎካከሩ የሚችሉ ፡፡ እና ፓርቲዎች ጠንካራና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ምን መደረግ አለበት? እርስዎ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ትልቅና ረጅም ልምድ ስላለዎት በዚህ ላይ ምን ይመክራሉ ?

ፕሮፌሰር በየነ – ይሄ ጥያቄ የአገሪቱን ሁኔታ በብቃት ያገናዘበ አይደለም፡፡ ጠንካራ ማለት እንደ ግንቦት 7 ጦርነት ማወጅ ከሆነ ይሄ አይገባኝም ፡፡ በሰላማዊ መንገድ ተደራጅቶ በመንቀሳቀስ ረገድ የእኛም ፓርቲዎች ጠንካራ ናቸው፡፡አሸንፈን እናውቃለን እኮ ፡፡ አንድን ፓርቲ ጠንካራና ደካማ የሚያሰኙት ሁኔታዎች ናቸው ፡፡ ሁኔታዎች ቢፈቅዱ ተወዳድሮ ማሸነፍ ይቻላል፡፡ ምርጫ ከዚህ ሌላ መስፈርት የለውም ፡፡ ሁኔታዎች ለመንቀሳቀስ ፋታ የሚሰጡ ሆነው ከተገኙ በሂደት ለስልጣን መብቃት ይቻላል፡፡ ነገር ግን አንድ ፓርቲ በምርጫ አሸንፎ ስልጣን ይዞ ካልተገኘ ደካማ ነው ከተባለ ይሄ ትክክለኛ አገላለፅ አይደለም ፡፡ አንድን ፓርቲ ጠንካራ ወይም ደካማ ነው የሚያሰኘው ምንድን ነው ? የሚንቀሳቀስበት ከባቢያዊ ሁኔታ ወይም ምህዳሩ ነው የሚወስነው ፡፡ ከዚህ አልፎ አሁን አንተ የጠየከኝ ጥያቄ ምን ያረገዘ ነው መሰለህ ለምንድን ነው ወጥታችሁ ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቃችሁ፣ ደም አቃብታችሁ፣ ሞታችሁና ታስራችሁ የማትታዩት ?ልክ እንደ አረቡ አብዮት አይነት ውስጥ ለምንድን ነው የኢትዮጵያ ፓርቲዎች የማይገቡት? ወደሚለው ይወስዳል፡፡ እኔ በግሌ ህዝባችንን መስዋዕትነት ለመክፈል ወደማይፈራበት ደረጃ አድርሰን አታግለናል። በተለያዩ አካባቢዎች የተደረጉት ትግሎች ጠንካራ ነበሩ ፡፡ በዚህም አባሎቻችን ታስረዋል ተሰደዋል ፡፡

ይሄ አሁን የደቡብ አፍሪካን አጥለቀለቀ የተባለው የደቡብ ወጣት መነሻው እኮ ያኔ ነው፡፡ በ1992 ምርጫ ለክልልና ለፓርላማ አሸንፈን እንዳንገባ በተደረገው ዘመቻ የተፈናቀለ ነው፡፡ እንግዲህ በሰላማዊ ትግል ከዚህ በላይ አልፈህ ወዴት ትሄዳለህ ? የትም እኮ አትሄድም፡፡ እንግዲህ ተጨባጩ ሁኔታ ይህ ሆኖ እያለ ነው እንግዲህ ደካማና ጠንካራ ፓርቲ ምናምን የሚባለው ፡፡ አንተ መጠንከር ቀርቶ እንደብረት ብትጠነክርም ኢህአዴግ ባስቀመጠው ከባቢያዊ ሁኔታ ምንም ማድረግ አትችልም ፡፡ ከዚህ አልፈህ ከሄድክ ደም መፋሰስ ነው የሚሆነው ፡፡ ይሄን ያህል አታግለናል ፡፡ ኢህአዴግ ከፈቀደው የእንቅስቃሴ ምህዳር ውጪ መሆን አይቻልም፡፡ ከዚህ ውጪ እንግዲህ እኛም ወደ ዲያስፖራው ሄደን ነጋ ጣባ ደረስኩ ደረስኩ ማለት አለብን? ከዚህ ውጪ የፈለከውን ያህል አለት ሆነህ ብትገኝ አስቸጋሪ ነው ፡፡ መንቀሳቀስ ካልቻልክ ምን ሆነህ ጠንካራ ትሆናለህ ? ይሄንን ጥያቄ በጥንቃቄ ነው መጠየቅ የሚያስፈልገው፡፡ እኛ ዝም ብለን በደካማነት የምንኮነንም አይደለንም ፡፡ ተወዳድረን ማሸነፍ እንደምንችልና ህዝቡንም ማደራጀት እንደምንችል እስከ ታች ድረስ ወርደን አሳይተናል ፡፡ ኢህአዴግ ለምንድን ነው ሀዲያ ዞን ላይ ከአስራ አንድ ወረዳዎች አንዱ ብቻ ሲቀር በሌላው የተሸነፈው ? እና መሸነፍ ያለ ነው ፡፡

ዘመን ፡- ዲያስፖራውንስ እንዴት ይገልፁታል ? የትግል ስልቱስ ምን አይነት መሆን አለበት? እስኪ ምክር ይስጧቸው፡፡

ፕሮፌሰር በየነ ፡- ዲያስፖራውን እንግዲህ ለመምከር እንሞክራለን፡፡ ቅድም እንዳልኩት ዲያስፖራው ከእኛ ጋር ቁጭ ብሎ ማውራትም አይፈልግም፡፡ በየነ መጣ ስብሰባ ይደረግና ጥያቄ ካላችሁ ጠይቁ ሲባል የለም ፡፡ እኔ ንግግር እንዳደርግ የተሰበሰበውን ስብሰባ እኮ ነው የበተኑት ፡፡ ሰልፍ ነው ያደረጉት፤ ዋሽንግተን ላይ፡፡

ዘመን ፡- እርስዎ እንዳይናገሩ ተፈልጎ ነው ?

ፕሮፌሰር በየነ – አዎ

ዘመን ፡- ለምንድን ነው ?

ፕሮፌሰር በየነ – እኔ እውነቱን አወጣለኋ፡፡ 1997 ምርጫን ተከተሎ ለምን ፓርላማ ገባችሁ? የሚል ዘመቻ ተካሄደብን ፡፡ በኋላ የእኛ ደጋፊ የነቡሩት በተለያዩ ሚዲያዎች ስብሰባ ጠሩ ፡፡ በኋላ ዲያስፖራው በየነ መጣ፣ ይሄ የወያኔ አንጋች ምናምን ብለው ስብሰባውን እንበትናለን አሉ ፡፡ ህዝቡ አዳራሽ እንዳይገባ በሩን ዘግተው ቆሙ ፡፡ በፈረንጅ አገር ደግሞ ሄደህ አንዱን ሰው ካልነካህ በስተቀር ፖሊስም መጥቶ መች ነካህ ምናምን ይላል ፡፡ እስከዚህ ድረስ ተሰልፈውብናል እኮ፡፡ እኛ አሁን የተቸገርነው ኢህአዴግ በአንድ በኩል እኛን ትክክል ባልሆነ ምስል ያስቀምጠናል፡፡ ዲያስፖራው ደግሞ በባሰ ይሄው እንዲህ ያደርጋል፡፡ እና እኛ ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ለመንቀሳቀስ በምንጥርበት ጊዜ ትልቅ ችግር ላይ ነው ያለነው ፡፡ ኢህአዴግ የእኛን እንቅስቃሴ ዋጋ በማሳጣት ምን እንደሚጠቀም አላውቅም ? ይሄ አገሪቱን ለበለጠ ውጥረትና ለፅንፈኛ ፖለቲካ ኃይሎች አሳልፎ መስጠት ነው የሚሆነው፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለብቻቸው ስልጣን ይዘው ይኸው ስሞኑን በሚደረገው ሦልጠና ላይ እንኳን አርባ ዓመት ቆይተን ነው አገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ የምናደርሳት እያሉ ነው፡፡ እኛ የመንግሥት ተቀጣሪ ነን ነገር ግን ስለ ምርጫ ዘመቻ ነው አስር ቀን ሙሉ ከተማሪ እስከ መንግሥት ሠራተኛ እያስተጋቡ ያሉት፡፡ ይኼ በራሱ ህገ ወጥ ነው ፡፡ በመንግሥት መዋቅር ተጠቅሞ ይኼንን ማድረግ ትክክል አይደለም ብለን ለምርጫ ቦርድ ተቃውሞአችንን አስታውቀናል ፡፡ እኛ አሁን ወጥተን አደባባይ ህዝቡን ጠርተን መቀስቀስ እንችላለን ? አይፈቅዱም፤ ጊዜው ገና ነዋ ፡፡

ዘመን፡- በጣም እግዚአብሔር ይስጥልን ፕሮፌሰር እናመሰግናለን።

ፕሮፌሰር በየነ ፡- ይሁን እኔም አመሰግናለሁ።

***********************

ምንጭ፡-  አዲስ ዘመን፣ ሕዳር 2007

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar