www.maledatimes.com የስቅለቱ እና የትንሣኤው አብነት! (ከሆሳዕና እስከ ማዕዶት) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የስቅለቱ እና የትንሣኤው አብነት! (ከሆሳዕና እስከ ማዕዶት)

By   /   April 18, 2014  /   Comments Off on የስቅለቱ እና የትንሣኤው አብነት! (ከሆሳዕና እስከ ማዕዶት)

    Print       Email
0 0
Read Time:33 Minute, 18 Second
በሰሎሞን ተሰማ ጂ.  
በየዓመቱ የትንሣኤ በዓል ተከብሮ የሚውለው፣ በዕለተ እሑድ ነው፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ የተነሳው በዕለተ እሑድ-መጋቢት 29 ቀን ነው፡፡ የግዕዝ ቋንቋ ሊቃውንት እንደሚተረጉሙት ከሆነ፣ “ትንሣኤ ማለት-መነሳት ማለት ነው፡፡” ሞትን ድል አድርጎ፣ ከሙታን ተለይቶ መነሳት ማለት ነው፡፡ “ሕይወት ማግኘት፣ ነፍስ መዝራት፣ ሕልው መሆን” ማለት ነው፡፡ በዓሉ ጌታችን የተሰቀለበትን ዕለት (መጋቢት 27ን እና ሞትን ድል አድርጎ “ለይኩን ትንሣኤ ለሙታን!” ብሎ የተነሳበትን መጋቢት 29ን ቀን) ጠብቆ እንዳይከበር ያደረገው ትልቅ ምክንያት አለ፡፡ እርሱም፣ በየዓመቱ መጋቢት 29 ቀን እሑድ-እሑድ አለዋሉ ነው፡፡ ስለሆነም፣ ከዘመናት በኋላ መጋቢት 29ን እየጠበቁ፣ አንዴ ሰኞ፣ ሌላም ጊዜ ማክሰኞ ወይም ረቡዕና ኀሙስ፣..ወዘተርፈ ይከበር የነበረውን የጌታ ትንሣኤ በዕለተ-እሑድ ለማክበር የሚያስችለውን ድንጋጌ፣ በ13ኛው ክፍለ ዘመን ላይ-አቡሻህር ኢብን ቡትሩስ ራሒብ (ወይም ዮሐንስ) የተባለው የእስከንደሪያ ካህን ገለጠው፡፡ በዚህም ድንጋጌ መሠረት የትንሣኤ በዓል ከመጋቢት 26 እስከ ሚያዚያ 30 ባሉት እሑዶች ውስጥ እየተዘዋወረ ይከበር ጀመር፡፡ በመሆኑም፣ የጾመ ነነዌና የዐብይ ጾም የሚጀርባቸው ዕለታት ሰኞ-ሰኞ እንዲሆኑ ተደነገገ፡፡ የሆሳዕና እና የትንሣኤም ዕለቶች ከእሑድ ውጪ እንዳይሆኑ ደንብ ተሠራ፡፡ የጸሎተ ኀሙስም-በዕለተ ኀሙስ፤ የስቅለት ዕለትም በያመቱ አርብ-አርብ እንዲሆን ተደረገ፡፡ የቅዳሜ ሥዑርም-ከቅዳሜ ውጪ እንዳይሆን ተደረገ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችንም የሞትን ቅኝ-ግዛት ድል የተቀዳጀበት ዕለት እሑድ ስለነበረ፣ የትንሣኤ በዓል ከእሑድ ውጪ እንዳይሆን ተደረገ፡፡

“ለመሆኑ ሆሳዕና ማለት ምንድን ነው? ጸሎተ ኀሙስስ ማለት ምንድን ይሆን? ስቅለትስ ሲል ምን ማለት ነው? የቅዳሜ ሥዑርስ ሲባል ትርጓሜው ምንድን ነው?” ብሎ የሚወዛገብ አንባቢ ሊኖር እንደሚችል እንገምታለን፡፡ ስለሆነም ወደ ዋናው ጽሑፋችን ስንገባ፣ እግረ-መንገዳችንንም የነዚህን ቃላትና ሃረጋት ፍቺም እያስተነተንን እንቀጥላለን፡፡ (በመሆኑም፣ የተወሰኑ አንባቢያን ያንዳንድ ቃላትን ትርጓሜ ለማላመጥና ለመዋጥ እንዳያንገራግሩ አደራ እንላለን፡፡) ከላይ እንደገለጽነው፣ “ሆሳዕና” ማለት “ከትንሣኤ በፊት ባለው እሑድ የሚከበር በዓል ሲሆን፣ ጌታችን ኢየሱስ በአህያ ውርንጭላ ተቀምጦ ወደ እየሩሳሌም የገባበት ቀን ነው፡፡ ወደ ቤተ-መቅደስም ሲገባ፣ ሕዝበ-አዳም ሰሌን አንጥፎ፣ የወይራ ዝንጣፊ ጎዝጉዞ፣ “ሆሳዕና” እያሉ ጌታንና ደቀመዛሙርቱን የተቀበሉበት ዕለት ነው፡፡ የመዝሙሩም ትርጓሜ፣ “ጌታችን ሆይ፣ አድነን!” ማለት ነው፡፡ ስለሆነም፣ የሕዝቡን የአድነን ጥሪ ለመመለስ ሲል ኢየሱስ ሰሙነ-ሕማማቱን በዕለተ-ሰኑይ (ሰኞ) ጀመረ፡፡ እያስተማረና አያዘጋጀ ከሰኞ እስከ ኀሙስ ድረስ በእየሩሳሌም ከተማ በአካባቢዋ ሲዘዋወር ሰነበተ፡፡

በዕለተ ኀሙስ ግን ሁለት የማይታለፉ ተግባራትን አከናወነ፡፡ የመጀመሪያው ወደ ተራራው ጫፍ ወጥቶ ያደረገው ጸሎት ነው፡፡ ደም እንደላብ እየወረደው በተመስጦ ሲጸልይና ሲተጋ ሳለ፣ ሦስቱ ነብያት (ነብዩ ሄኖክ፣ ነብዩ ሙሴ፣ እና ነብዩ ኤልያስ) የሰማየ-ሰማያትን አድማስ ጥሰው ከተፍ አሉ፡፡ እንዲጸናም አዘዙት፡፡ የእግዚአብሔርም ድምጽ እያስገመገመ መጣ፡፡ ፈጣሪያችን መጽናናትንም ለዓለም ላከ፡፡ ከተራራው ከወረዱ በኋላ የመጨረሻውን ራት ለመብላት ሄዱ፡፡ በዚህም ምሽት ወቅት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው፡፡ “ነገ በመልዕልተ መስቀል ላይ የሚፈተተው ሥጋዬ እና የሚፈሰውም ደሜ ይህ ነው!” ስለዚህም፣ በምሴተ-ኀሙስ ሥጋውን-በስንዴ፣ ደሙንም-በወይን አምሳል አድርጎ ለደቀ መዛሙርቱ የሠጠበት ምሽት ነው፡፡ ከዚህም ሌላ የደቀ መዛሙርቱን እግር ዝቅ ብሎ በትህትና ያጠበበትም ሰዓት ነው፡፡ እናንተም ለባልንጀሮቻችሁ እንደዚህ አድርጉላቸው! ብሎም ያዘዘው በዚሁ ጊዜ ነበር፡፡ የጌታንም አርዓያነት በመከተል የኢትዮጵያ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ምእመናን ዕለተ-ኀሙስን ጸሎት በማድረግና የጌታንም ራት ለማሰብ ተብሎ የሚዘጋጀውን ጉልባን በመመገብ ታከብረዋለች፡፡ ከዚህም የመጨረሳ ራጽ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ እስከሚነሳበት (ለእሑድ አጥቢያ) ከሌሊቱ 9፡00 ሰዓት ድረስ ምእመናን ምንም ነገር ከመመገብ ይታቀባሉ፤ (ይጾማሉ)፡፡

ከጸሎተ ኀሙስ ቀጥሎ ያለው አርብ፣ “ዕለተ-ስቅለት” ይባላል፡፡ በዚህ ዕለትም፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አሥራ አራቱ(14)ን ግብረ-ሕማማት በግፍ እየተፈጸመበት ከሊዮስጥራ (የሔሮዱስ የፍርድ አደባባይ) እስከ ቀራኒዮ ድረስ ጉንደ-መስቀሉን ተሸክሞ ተጉዟል፡፡ (14ቱ ግብረ ሕማማትም የሚቀጥሉት ናቸው፡- መያዝ፣ የኋሊት መታሰር፣ በጥፊ መመታት፣ መገረፍ፣ መራቆት፣ አክሊል ስክ፣ ኩርዐተ-ርእስ፣ መስቀል መሸከም፣ ድካም፣ መውደቅ፣ ከሐሞት ጋር መፃፃ መጠጣት፣ ስቅለት፣ ውሃ መጠማት፣ እና መሞት ናቸው፡፡ አንድ ሰው በዚህ ዓለም ላይ ሲኖር ከነዚህ የመስቀል መከራዎች የበለጠ አይደርስበትም፡፡) ኀሙስ ለአርብ አጥቢያ እጁ ከተያዘበት ሰዓት ጀምሮ፣ ኮምጣጤ ጠጥቶ ሕማማቱን እስከፈጸመበት እስከ አርብ 9፡00 ሰዓት ድረስ ከፍተኛ በደል ተፈጽሞበታል፡፡ ይህንንም ዕለት ለማሰብ፣ በኢትዮጵያ ተዋሕዶ አብያተ-ክርስቲያናት ሥርዓት መሠረት የክርስቶስ ስቅለት ይከበራል፡፡

ምዕመናንም በየአጥቢያ ቤተ-ክርስቲያኖቻቸው እየተሰበሰቡ ክርስቶስ ራሱን አሳልፎ የሰጠበትን ዕለት ያከብራሉ፡፡ የሠሩትንም ኃጢያት በመናዘዝ ሲጾሙ፣ ሲጸልዩና ሲሰግዱ ይውላሉ፡፡ ንስሐም ይገባሉ፡፡ በክርስቶስ አስተምህሮት መሠረት፣ “ንስሐ መልካም ነው፤ ያለንስሐ ይቅርታ አይገኝምና፡፡” ሆኖም፣ ንስሐ መግባቱ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ክርስቶስ አርዓያነቱንም እንድንከተል አስተምሯል፡፡ አስተምሮም ብቻ አላቆመም፤ በተግባርም ፈጽሞታል፡፡ ለሰው ልጆች ሲል ራሱን አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ እያንዳንዳችንም ግማደ-መስቀላችንን ተሸክመን እንድንከተለው ጠይቋል፡፡ ግማዱም ራሱ የተሸከመው ዓይነት ነው፡፡ “ራስን፣ ለሌሎች አሳልፎ የመስጠት ‘ግማደ-መስቀል’ ይባላል፡፡” ክርስቶስ የመጨረሻውንና የሰው ልጆች ከቶም ሊሸከሙት የማይችሉትን መስቀል ተሸክሞ ለሌሎች መድኅንነቱን አሳይቷል፡፡ እኛ ደግሞ ከዚህ ቀለል ያለውን ግማደ-መስቀል መሸከም እንችላለን፡፡ ለወገኖቻችን በማሰብ- ጉልበታችንን፣ ዕውቀታችንን ከመሰጠን፣ ለእውነትና ለመርህ በሀቅ ከመቆምን፣ ከዘረኝነትና ከጎሰኝነት ከራቅን-ያን ጊዜ የስቅለቱን አርዓያነት ተከትለን፣ የመስቀል ድርሻችንን ተወጣን ማለት ነው፡፡

ከኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ በፊት ያለውም ዕለት፣ “ቅዳሜ ሥዑር” ይባላል፡፡ በዚህ ዕለትም ጳጳሳቱ፣ ካህናቱ፣ የየአድባራቱ ሊቃውንት እና መዘምራንም በሊቶስጥራ አደባባይ ወደ እምትመሰለው የነገሥታቱ ቤተ-መንግሥት መጥተው ከተዘገጃጁ በኋላ፣ ንጉሠ ነገሥቱ (አፄው) የክብር ስፍራቸውን ይይዛሉ፡፡ በሰልፍ የተደራጁት መዘምራንም፣ “ገብረ ሰላም በመስቀሉ፣ ትንሣኤሁ አግሃደ!” እያሉ ለክርስቶስ ትንሣኤ ማብሠሪያ የሆነውን ግሥ በጸናጽልና በከበሮ ያሰማሉ፡፡ (ግዕዝ ለማያውቁ አንባቢያን “ገብረ ሰላም በመስቀሉ” ማለት፣ “መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ሰላምን መሠረተልን፣ ትንሣኤውንም ገለጸልን” ማለት ሲሆን፤ ይህም የተገለጸው ሰላምና ትንሣኤ ለመላው ዓለም እንዲሆን ቤተ-ክርስቲያኒቱ በነገሥታቱ ፊት ጸሎትና ምልጃዋን ታሰማለች፡፡) ከብዙ ዘመናትም ጀምሮ፣ የቅዳሜ ሥዑር ዕለት፣ ካህናቱ ለምለም ቄጠማ ለምእመናን ያድላሉ፡፡ ለዚህም እደላ ዋናው ምክንያት፣ ኖኅ በመርከቡ ውስጥ ከነበሩት አሞሮች መካከል ቁራን፣ “ሄደህ የጥፋት ውኃ መጉደሉን የሚያወሳ ምልክት ይዘህ ና!” ሲል አዘዘው፡፡ ነገር ግን፣ ቁራው-ሆዱ አታሎት፣ ውድቅዳቂ (ጥንብ) ሲዘነችር ሳይመለስ ቀረ፡፡ (በአማርኛ-የቁራ መልዕክተኛ!- የሚባለውም ፈሊጥም ይህንን ኩነት ለመዘከር ያለመ ነው፡፡) ከቁራው እንደወጣ ሲቀር፣ ርግብን ቢልካት ለምልም የወይራ ዝንጣፊ ይዛ ተመልሳ የጥፋቱን ውኃ መጉደል አበሠረችው፡፡ ይህንንም የእርግቧን አብነት በማድረግ፣ ክርስቲያኖች ለምለም ቄጠማ በእጆቻቸው ይዘው፣ “ገብረ ሰላም በመስቀሉ” በማለት የጌታችንን ከሙታን ተለይቶ የመነሣቱን ተዓምር/ትንሣኤ በጭምጭምታ ይወያዩ ነበር፡፡ ስለሆነም፣ “ቅዳሜ ሥዑር” የሚለው ስያሜ፣ “ሽረት፣” ወይም ደግሞ “የተስፋ መለምለም ቀን” የሚል ትርጓሜ ያዘ፡፡

በቅዳሜ ሥዑር ዕለት ከየደብሩ የመጡት ሊቃውንት የሚከውኑት ሌላም ተግባር አላቸው፡፡ የኢትዮጵያ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን የትንሣኤውን ምሳሌ ምክንያት በማድረግ፣ በጨለማና በሲዖል የነበሩት ነፍሳት ወደብርሃንና ወደገነት የወጡ መሆናቸውን ለማብሠር-በነገሥታቱ አደባባይ (በሊቶስጥራ) ዝማሬ ማሰማትና ቄጠማም ማደል ብቻ አይደለም ተግባሯ፡፡ ባለቅኔዎችም በንጉሠ ነገሥቱ ዙፋን ፊትለፊት ቆመው ክርስቶስ ሞትን ድል እንዳደረገውና የአዳምን ወገን ሁሉ ከመከራ፣ ከችግር፣ ከጽልመት፣ ከባርነት፣ ከጠላትና ከድንቁርና እንዳዳነው ሁሉ፣ የኢትዮጵያም ነገሥታት በዘመናቸው የተደቀነባቸውን መከራ፣ ችግር፣ ጽልመት፣ ባርነት፣ እንዲሁም አደገኛ ጠላት ድል አድርገው ለወገኖቻቸውን የፖለቲካና የማኅበራዊ ፍትሕ እንዲያሰፍኑ ያመሰጥራሉ፡፡ ነገሥታቱ ክርስቶስ በመስቀሉ ላይ ተሰውቶ የመሠረተውንም ዘላለማዊ ሰላም እንዲጸና ተግተውና ነቅተው እንዲጠብቁት መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ፡፡ (ይህ ሁሉ  የቅዳሜ ሥዑር አከባበር፣ ከዛጉዌ ሥርወ-መንግሥታት ጀምሮ እስከ አፄ መራ-ተክለሃይማኖት ይዘልቅና፣ በመኃል በአፄ ሱስንዮስ ዘመን ተስተጓጉሎ፣ እንደገና በአፄ ፋሲለደስ ዘመን ተጀምሮ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ እስከ 1965ዓ.ም ድረስ ይከናወንም ነበር፡፡ ከ1966ዓ.ም ጀምሮ ግን፣ ገዢዎቹ ለቅዳሜ ሥዑሩ የምሥራች “ጆሮ-ዳባ ልበስ” ብለዋል፡፡ ይባስ ብለውም፣ የኢትዮጵያን ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን እንደክፉ ባላንጣቸው ቆጥረው ሕዝበ-ምእመኑን ያተራምሱታል፡፡)

እነሆ ጌታችንና መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነስቷል፡፡ ቅዳሜ ለእሑድ አጥቢያ (ከሌሊቱ በ9፡00 ሰዓት ላይ) ክርስቶስ መቃብር ፈንቅሎ ገቢረ-ተዓምራቱን ፈጽሟል፡፡ ይህ ዕለት እስከሚደርስም ድረስ፣ በኢትዮጵያ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ምእመናን ዘንድ የሃምሳ-አምስት(55) ቀናት ጾም ይደረጋል፡፡ ስያሜውም “ዓብይ ጾም” ወይም “ሑዳዴ” ይባላል፡፡ “ሑዳዴ” የተባለበትንም ምክንያት ማወቅ የተገባ ነው፡፡ ዱሮ ብዙ ገበሬዎች ጥማዳቸውን እየያዙ ለአረም፣ ለአጨዳና ለውቂያ ጊዜ በእዝ እየተሰበሰቡ ከዓመት ውስጥ የተወሰኑትን የአዝመራ ወራት ሥራ የሚያከናውኑበት ሰፊ ማሳ “የንጉሥ ሑዳዴ” ይባላል፡፡ “ዓብይ ጾም”ም “ሑዳዴ” መባሉ፣ ንጉሠ ሰማያት ወምድር፣ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ስለጾመውና ክርስቲያኖች ሁሉ እንዲጾሙት የታዘዘ ሕግ ስለሆነ ነው፡፡ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ፣ “የሞቴን መስቀል ያልተሸከመ ሊከተለኝ አይችልም፤ የእኔንም ደቀ መዝሙር ሊባል አይገባውም” ብሏል፡፡ መስቀሉንም ለመሸከም ደግሞ በመንፈስ መንጻት ያስፈልጋል፡፡ “መስቀል” ማለት “በቅዱሳን ወንጌሎች የተጻፉትና እየሱስ ራሱ የሠራው ተግባር ሁሉ ማለት አይደለምን?” ነው፡፡ ከጥምቀቱ ጀምሮ በመልዕልተ መስቀል ላይ ተቸንክሮ፣ “ሊሆን ያለው ሁሉ-ተፈጸመ” እስከተባለበት የመጨረሳ ቃል ድረስ ያለው መለኮታዊ ድምጽ ሁሉ፣ “መስቀል” ይባላል፡፡ ከእንጨት ግንድም ተጠርቦ የተሠራው አማናዊው መስቀል ደግሞ፣ “እፀ-መስቀል” ይባላል፡፡

የሆነው ሁሉ ሆኖ፣ ክርስቶስ አዳምንና የልጅ ልጆቹን ሁሉ፣ ሞትን ድል አድርጎ፣  ከሞት ወደ ሕይወት አሻግሯቸዋል፡፡ በመሆኑም፣ ከትንሣኤ ቀጥሎ ያለው (ሰኞ) ዕለት “ማዕዶት” ይባላል፡፡ ከሞት ማዶ መሻገር ማለት ነው፡፡ ከሞት ወደ ሕይወት በእየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት መሸጋገር ማለት ነው፡፡ የጽልመትና የመከራው ዘመን ድልድይ ሆኖ የሚያሸጋግረን ብቸኛ ቤዛ-ለኩሉ ክርስቶስ፣ ከሞት ወዲያ ማዶ ያለውን ዓለም የተቀላቀለበት ዕለት ነው፡፡ ሕያው ሆኖ የተገለጠበትም ዕለት ነው፡፡ ስለዚህም፣ “ማዕዶት” ተባለ፡፡ አዳምና ሄዋን ከነልጆቻቸው ከሲኦል ፍዳና መከራ ነጻ ወጥተው፣ የሳጥናኤል የባርነት አገዛዝ አክትሞ፣ ሕዝበ-አዳም ወደ ነጻይቱ ሀገረ-ገነት የገቡበት ዕለት ሰኞ ነው፡፡ ይህም ቀን፣ “ማዕዶት” ይባለል፡፡

 

ማጠቃለያ፤
በአካለ ሥጋ መንቀሳቀስ ብቻውን “ሕይወት” አይደለም፡፡ በአካለ ሥጋ መቀበርም ብቻውን “ሞት” አይደለም፡፡ በአካለ ሥጋም እያሉ፣ ሞት እንዳለው ሁሉ፤ በአካለ ሥጋም ሞተው ሕይወት አለ፡፡ በአካለ ሥጋ ሞተው ሕይወትን ማስቀጠል እንደሚቻል ከአዝርዕት ቅንጣቶች ማስተዋል እንችላለን፡፡ ሕማማቱ፣ ሥቃዩ፣ ስቅለቱም ሲከበር የኖረው፣ ትንሣኤውንም በየዓመቱ የምናከብረው የእየሱስ ክርስቶስ ከሃሊነት ያስረዳናል፡፡ በሕክምና ባለሙያዎች አገላለጽ፣ “ሞት” ማለት-የልብ ትርታ መቆም፣ የሳንባ ሥራውን ማቋረጥ፣ የደም በሰውነታችን ውስጥ መርጋት፣ የአእምሮም የነርቭ ሥርዓትን ማስተባበር ተግባሩን ማቋረጥ ነው፡፡  በሃይማኖት መሪዎችና በፈላስፎች አስተያየት ደግሞ፣ “ሕይወት ከአካል እንቅስቃሴ የላቀ፣ ሞትም በአካል እንቅስቃሴ ከመቆም የከበደና የከፋ ነው፡፡” አንዱ ባለቅኔ፣ “መሞት፣ መሞት፣ አሁንም ደጋግሞ ዕልፍ ጊዜ መሞት፤ ከዚህ የበለጠ ነውና-ታላቅ ሰውነት!” ሲል ገልጾታል፡፡ ሆኖም፣ እየኖሩ መሞት ደግሞ ከባድና መራርም ነው፡፡ በቁም መሞትን የሚያህል የቁም ሲኦል ስለመኖሩም ያጠራጥራል፡፡

ሺህ ጊዜ ለመሞት ቆርጦ የመጣው ክርስቶስ፣ “ፍጹም ሰውና ፍጹም አምላክ”ም መሆኑን ቤተ-ክርስቲያን ትሰብካለች፡፡ እርሱ ዓለምን ለማዳን  የመጣ መሲህ ብቻም አይደለም፡፡ ትልቅ ፈላስፋም ነው፡፡ ትምህርቱና አድራጎቱም፣ ክርስትናን በሚያምኑትም ሆነ በማያምኑትን ዘንድ ግንባር-ቀደም ፈላስፋ ያደርገዋል፡፡ ላስተማረው “እውነት” ራሱን ሰውቷልና፡፡ ክርስቶስ ሌላውን ሞት፣ “ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ፣ ራሱን ግን ካጣው ምን ይጠቅመዋል?!” ሲል ገልፆታል፡፡ የክርስቶስ ትምህርት፣ ሰው በጥቃቅን የግል ጥቅም ተደልሎ፣ በለስላሳ ድሎትና ምቾት ተቀማጥሎ፣ ራሱን አጥቶ መኖር እንደሌለበት ያሳስባል፡፡ ክርስቶስ ሞትን ናቀና፣ ሞትንም ድል አደረገው፡፡ ይህንን የበለጠ በሚያጎላ አስተምህሮት የገለጹት አንድ ካህን አጋጥመውኛል፡፡ እንዲህ አሉ፤ “ሁላችንም ስቅለት አለብን፡፡ ግና፣ የሁላችንም ስቅለት እንደክርስቶስ የኋሊት ታስረን፣ ደም እያፈሰስን፣ አካላቶቻችን በሚስማርና በችንካር እየተቸነከሩ፣ መራር መጠጥ ከሐሞት ጋር እየተጎነጨን አይደለም፡፡ እንደዚያ ዓይነቱ የመስቀል መከራንም እንድንቀበል አይጠበቅብንም፡፡….ከእኛ የሚጠበቀው መስዋዕትነት የሰብዓዊነት መስዋዕት ነው፡፡ ንብረታችንን ለተቸገሩት ከለገስን፣ ወገኖቻችንንም በሙያና በዕውቀታችን ከረዳን፣ ጉልበታችንን ለአካለ-ስንኩላን ካጋራን – የእኛ ስቅለት እርሱ ነው፡፡”

እውነታቸውን ነው፡፡ ሁላችንንም ትንሣኤ ይጠብቀናል፡፡ ግና፣ እንትክክለኛው የክርስቶስ ስቅለት፣ በአካለ ሥጋ መሞትና መቃብርም መውረድ፣ ሬሳ ሳጥንም ውስጥ ተገንዘን መመቀበር፤ ከዚያም ቋጥኝ ፈንቅለን ለመውጣት አያስፈልገንም፡፡ ጉልህ ታሪከዊ ሥራን ሠርተን በታሪክ ጉባኤ ላይ መነሳትና መወሳት መቻልም “ትንሣኤ” ነው፡፡ ከአጓጉል ሱስና ከክፉ ባሕሪም ርቆ፣ በባሕሪ መታደስም “ትንሣኤ” ነው፡፡ ዝንባሌን አውቆና መርምሮ ራስን መግዛትና ራስንም ፈልጎ ማግኘት-ሰብዓዊ “ትንሣኤ” ነው፡፡ ለሀገርና ለወገን የሚፈይድ የፈጠራ ሥራ ሠርቶ ለወገን አገልግሎት መስጠትም “ትንሣኤ” ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሲታሰብ የክርስቶስ ትምህርት ለሰማያዊ ጽድቅ ብቻ የሚውል መንፈሳዊ እሴት ብቻ አይደለም፡፡ የሰብዓዊነትን ምርምር የሚያስረዳ፣ የኅብረተሰብንም ሥርዓት የሚገልጥ፣ ዘላለማዊ ፍልስፍናም ጭምር ነው፡፡ ከክርስቶስ ትምህርት-እውነትን፣ ሰብዓዊነትን፣ ክብርን፣ ለኅብረተሰብና ለሰው ልጆች የሚበጀውንና የሚያስፈልገውን ፍቅር፣ ሰላም፣ ታጋይነትን፣ ቆራጥነትን፣ በጎ ማድረግንም ሁሉ እንገነዘብበታለን፡፡ ፍልስፍናዊ አስተምህሮት ብቻም ሳይሆን፣ አርዓያዊ ተግባርም ነው፡፡ ይሄንን አስተምህሮትም መፈጸሙ ራሱ “ትንሣኤ” ነው፡፡ የመንፈስ ትንሣኤንም ያቀዳጃል፡፡ ጎበዝ ምን እንጠብቃለን! (የተባረከና የተቀደሰ የትንሣኤ በዓል ያድርግልን!)       http://semnaworeq.blogspot.com   Email: solomontessemag@gmail.com
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 10 years ago on April 18, 2014
  • By:
  • Last Modified: April 18, 2014 @ 4:25 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar