www.maledatimes.com ይድረስ በኢትዮጵያ ለአሜሪካ አምባሳደር ጉዳዩ – ቪዛ ስለመከልከል Letter to American Ambassador in Ethiopia about my denied visa application - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ይድረስ በኢትዮጵያ ለአሜሪካ አምባሳደር ጉዳዩ – ቪዛ ስለመከልከል Letter to American Ambassador in Ethiopia about my denied visa application

By   /   July 28, 2014  /   Comments Off on ይድረስ በኢትዮጵያ ለአሜሪካ አምባሳደር ጉዳዩ – ቪዛ ስለመከልከል Letter to American Ambassador in Ethiopia about my denied visa application

    Print       Email
0 0
Read Time:4 Minute, 16 Second

Letter to American Ambassador in Ethiopia about my denied visa application
ይድረስ በኢትዮጵያ ለአሜሪካ አምባሳደር ጉዳዩ – ቪዛ ስለመከልከል
ክብርት አምባሳደር፣ ለጤናዎ እንዴት ነዎት? ይህንን ግልጽ ደብዳቤ ጋዜጣ ላይ እንዳወጣ ያስገደደኝ፣ ከወር በፊት ደብዳቤዬን ቢሮዎ ድረስ በመምጣት ሰጥቼ ብሄድም እስካሁን መልስ ባለማግኘቴና ምናልባትም እርስዎ አላገኙት ይሆናል በሚል ጥርጣሬ ነው።
ክብርት አምሳደር፣ ተስፋዬ እሸቱ ሀብቱ እባላለሁ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት መምህርና የትምህርት ቤቱ ኃላፊም ነኝ። በተጨማሪም በአገሬ ባለ የጥበባት እንቅስቃሴ ውስጥ በጸሐፌ ተውኔትነት፣ በአዘጋጅነትና በተዋናይነት ጉልህ ሚና እየተጫወትኩ እገኛለሁ።
ክብርት አምባሳደር፣ ለእርስዎ ቅሬታዬን እንድጽፍ ያስገደደኝ ምክንያት እንደሚከተለው ነው። ባለፈው ዓመት “ሰን ዳንስ ኢንስቲትዩት” የተባለ ታዋቂ የአገርዎ ድርጅት ለሦስት ሳምንት የሚቆይ የቴአትር ዳይሬክተሮች ሥልጠና ሙሉ ወጪውን ሸፍኖልኝ እንድሳተፍ ቢጋብዘኝም፣ “ወጣት ነህ? አላገባህም? ባንክህ ውስጥ ገንዘብ የለም? ከዚህ በፊት የትም አገር ሄደህ አታውቅም?’’ ተብዬ ቪዛ በመከልከሌ ከተጋበዙ ስምንት ወጣት የምሥራቅ አፍሪካ ዳይሬክተሮች እኔ ብቻ መካፈል አልቻልኩም። በድጋሚ አመለከትኩ፣ እንደገና ተከለከልኩ። የጋበዘኝም ድርጅት እኔን ወክሎ ለኮንግረሱ ቢያመለክትም አልሆነም።
ክብርት አምባሳደር፣ የቆንስላዎ ቪዛ የመከልከል ምክንያት አሳማኝ ብቻ ሳይሆን ነጥብ ያለው ሆኖ
አላገኘሁትም ነበር። እንደሚገባኝ እርስዎ አገር ያለውን እምቅ እውቀት መማር ያለብኝ በወጣትነት ዘመኔ ይመስለኛል። እኔ እርስዎ አገር ለመሄድ እርጅናዬን መጠበቅ ይኖርብኝ ይሆን?
ትዳርስ መመሥረት ያለብኝ አሜሪካ ለመሄድ ብቻ መሆን ነበረበት? ትዳር ላለመያዝ የራሴ የግል ምክንያቶች መታየት አልነበረባቸውም? አገርዎ ተምሮ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ባለትዳር መሆን መሥፈርት መሆን ነበረበት?
ክብርት አምባሳደር፣ እኔ የዩኒቨርሲቲ መምህር እንጂ ነጋዴ አይደለሁም። እርስዎ በግልጽ እንደሚያውቁት የዩኒቨርሲቲ ምሁራን የሕይወት ግባቸው በዘመናቸው ጥናትና ምርምር በማካሄድ አገራቸውን በእውቀት ማነፅ ነው።
እንደሚገባኝ ገንዘብ ለማፍራት ዩኒቨርሲቲ ትክክለኛ ምርጫ አይመስለኝም። ወይስ ኮንሳላሩ ፊት ከመቅረቤ በፊት ከወዳጅ ጓደኞች ገንዘብ ሰብስቤ ማሳየት ነበረብኝ ይሆን? ከዚያስ በኋላ በራሴ ውሸት ከራሴ ጋር በቀላሉ የምታረቅ ይመስልዎታል?
ታዲያ አንድን የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የባንክ ደብተር መጠየቅ ክብረ ነክ አይሆንም? ከዚህ ቀደም ሌላ አገር አለመሄዴ ቪዛ ከመከልከያ መሥፈርቶች መካከል አንዱ መሆንስ ነበረበት?
የእኔ ምርጫ እርስዎ አገር ካሉ አርቲስቶች እውቀት መካፈል ቢሆንና ለመጀመሪያ ጊዜ ሳመለክት የእርስዎ አገር ድርጅቶች ቢቀበሉኝ፣ ቪዛ ለማግኘት ከእኔ ፍላጐት ውጪ አውሮፓ ወይም ላቲን አሜሪካ መሄዴ ግዴታ መሆን አለበት? የምርጫ ጉዳይ ሥፍራ ሊኖረው አይገባም! በምርጫ ማመን የእርስዎ አገር የዘመናዊነት አስተሳሰብ መገለጫ ይመስለኝም ነበር።
ክብርት አምባሳደር፣ በእነዚህና መሰል ምክንያቶች ያለፈው ዓመት ሥልጠናዬ ሳይሆን ቀረ። ምክንያቶቹ ባያሳምኑኝም ምናልባትም እኔ ያላየሁት፣ ያልገባኝ ነገር ሊኖር ይችል ይሆናል በሚል እምነት ቪዛ መከልከሌን በፀጋ ተቀበልኩት።
ክብርት አምባሳደር፣ በዓመቱ በሊንከን የቴአትር ማዕከል አማካይነት እ.ኤ.አ ከሐምሌ 6 እስከ 27 የሚቆይ ወጣት የቴአትር ዳይሬክተሮች ሥልጠና ከነሙሉ ወጪው ጋር ብጋበዝም፣ የእርስዎ ቆንስላ ለሦስተኛ ጊዜ ቪዛ ከለከለኝ።
ይቅርታ ያድርጉልኝና ይኼ ለእኔ ስድብ ነው። ምክንያቱም ኮንስላሩ ጥያቄ ከጠየቀኝ በኋላ ቪዛ ለመስጠት ፈቃደኛ እንደሆነ ነገረኝ። እኔም አመሠገንኩት። ከአፍታ ቆይታ በኋላ ግን ቪዛ እንደማይሰጠኝ አረጋገጠልኝ። የተከለከልኩበትን ምክንያት ስጠይቅ እንደ ሥራ ፈት ሰው “ወረቀቶችህን ጠቅልለህ ውጣ!’’ ነበር መልሱ።
ክብርት አምባሳደር፣ በአገረ አሜሪካ በእኔ ዕድሜ አካባቢ ለሚገኝ የዩኒቨርሲቲ መምህርና የአንድ ታዋቂ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ስለሚደረግለት እገዛና ድጋፍ፣ ስለሚያገኘው ሙገሳ ጠንቅቄ አውቃለሁ። ታዲያ በጣም ሠለጠኑ ከሚባሉ ቀዳሚ አገሮች መካከል የእርስዎ አገር ለወጣት ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮች የሚሰጠው ምላሽ አግባብ ነው ይላሉ?
በምክንያት ማሰብና መኖር የእርስዎ አገር መገለጫስ አይደለምን? ወይስ የቆንስላው የቪዛ ፈቃድ እንዲፀድቅልኝ “ቪዛው ተፈቅዶልሃል” ስባል እንደ ሕፃን ልጅ መቦረቅ ነበረብኝ? ይህ ዓይነቱ ኢምክንያታዊነት እኔን ብቻ ሳይሆን በኃላፊነት የማስተዳደረውን ትምህርት ቤት፣ ሲቀጥልም በአገሬ የኩራት መገለጫ ከሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች ቀዳሚ ሥፍራ ያለውን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን መሳደብና ቦታ 
አለመስጠት  ከዚህ የዘለለ ትርጉም ማግኘት አልቻልኩም:: 
ቅሬታዬንም ለእርስዎ የገለጽኩልዎ የምኮራበት፣ ቀን በቀን ራሴን በእውቀት የማንፅበት፣ ተማሪዎች ከዚያም በላይ አገሬ 
ብዙ የምትጠብቅበት ዩኒቨርሲቲዬ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚገባውን ክብር በማጣቱ ነው::
ክብርት አምባሳደር፣ ካልተሳሳትኩ የእርስዎ አገር ሥልጣኔና የታወቁ ዩኒቨርሲቲዎቻችሁ የጥንካሬ ምንጭና 
የጀርባ አጥንት ከሚገለጽባቸው ባህሪያት አንዱ፣ አገርዎ ለዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮች የምትሰጠው ክብር ነው:: በተለይም 
እኛ የታዳጊ አገር ወጣቶች ይህ ከእናንተ መማር የምንፈልገው ነው:: ታዲያ ገና ለገና የደሃዋ ኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ መምህርመሆኔ፣ አሜሪካ ሄዶ አይመለስም ተብሎ ታስቦ ከሆነ ስህተት ነው:: ስድብም ይመስለኛል:: ምናልባት አገርዎ ሄደው የቀሩካሉ ስህተት ብቻ ሳይሆን አገርን መክዳት ነውና አገሩን ለከዳ ደግሞ ይችን ታህል ቦታ የለኝም:: ሁሉም ያደርጉታል ማለት ግን አይደለም:: በመሆኑም የእኔም፣ የዩኒቨርሲቲዬም ክብር ሲጓደል፣ በምክንያት ለሚያምኑት ለእርስዎ ቅሬታዬን ማቅረብ አግባብ ነው እላለሁ::
ክብርት አምባሳደር፣ እኔ እጅግ በጣም ኃላፊነት የሚሰማኝ ሰው ነኝ:: ለዚህም ነው ዩኒቨርሲቲው ትልቅ ኃላፊነት 
የሰጠኝ:: ከዚያም በላይ ፕሮፌሽናል አርቲስት ነኝ:: እርስዎም እንደሚያውቁት አርቲስት ከአገሩ ወጥቶ መኖር አይችልም:: 
ከሆነ ግን ከውኃ የወጣ ዓሣ በመጀመሪያ የማይጠቅመው ራሱን ነው:: እኔም በእርስዎ አገር ሸፍቼ መኖር አልችልም:: 
የቴአትር ጥበብ ከልጅነት እስከ እውቀት ያስተማረኝ አገርን መውደድና መውደድ ብቻ ነው:: የምተነፍሰውም ይህንን ሀቅብቻ ነው:: የምጽፈውም፣ የማዘጋጀውም፣ የምገልጸውም፣ ጠንቅቄ የማውቀውን፤ የተወለድኩበትን፣ ያደግኩበትን፣ 
ከሕይወት እስትንፋስ እስከ ሞት ወድቄ የምነሳበትንና የምኮራበትን አገሬን፣ ኢትዮጵያን ነው:: ይቅርታዎትን 
አይንፈጉኝና አሜሪካ ሄዶ አይመለስም ብሎ ያሰበው ቆንስላዎ እንዳዋረደኝ ነው የሚሰማኝ:: ምናልባት ይኼ ዓይነቱ ስድብእርስዎ አገር በሚገኝ አንድ የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ላይ ቢከሰት ክብረ ነክ አይሆን ይሆን? 
ክብርት አምባሳደር፣ እንደሚሰማኝ ይህ ዓይነቱ ውሳኔ ለአገርዎ እውቀት ያለኝን ከፍ ያለ ከበሬታ እንድጠይቅ ነው 
ያስገደደኝ::፡ በተለይም እንደኔ ዩኒቨርሲቲ ለሚያስተምር ወጣት ምሁር ቪዛ መከልከል ከሠለጠነ አገርዎ መምጣቱ፣ 
እኛ ወጣቶች ለአገርዎ ያለንን በጐ አመለካከት የሚንድ ነው:: 
የእርስዎንም ዋና ተግባር፣ የሁለቱን አገሮች በጎ ግንኙነት መመሥረት የሚያደናቅፍና ጥቁር ነጥብ የሚያስቀምጥም 
ይመስለኛል::
ክብርት አምባሳደር፣ ጉዳዬን የመጻፌ ዓላማም ከእርስዎ አገር መጻሕፍት በቀሰምኩት እውቀት መሠረት ተግባራዊ 
መፍትሔ ለሚሻ ጉዳይ አመክንዮን መሠረት ያደረገ ግብረ ምላሽ የመስጠት ሥርዓትን መተግበሬ ቅሬታዬንም በዚሁ 
አግባብ መግለጽና መግለጽ ብቻ መሆኑን እንዲያጤኑልኝ እሻለሁ:: ምናልባት የአንድ አገር አምባሳደር በቆንስላ የውሳኔ 
አሰጣጥ ውስጥ ጣልቃ የመግባት ሥልጣን የለውም ብለው የሚያስቡም ከሆነ፣ ቆንስላዎ ሰው ነውና ህፀፅ እንደማያጣው 
ልብ ሊሉ ይገባል:: በተለይም ከላይ ከጠቀስኩልዎ ማሳያ አንፃር ‹‹አጥፍቷል›› ብዬ ብናገር የምሳሳት አይመስለኝም::
ክብርት አምባሳደር፣ በመጨረሻም ቅሬታዬን አንብበው ሐሳቤን በውል እንደሚያጤኑልኝና የቅሬታዬንም አግባብነት 
ተረድተው በኤምባሲዎ ቀጣይ የተግባር አፈጻጸም ሥርዓት ውስጥ በግብዓትነት እንደሚጠቀሙበት ያለኝን ፅኑ እምነት 
ስገልጽልዎት በአክብሮት ነው::
(ተስፋዬ እሸቱ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት 
ትምህርት ቤት ኃላፊና መምህር)

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 10 years ago on July 28, 2014
  • By:
  • Last Modified: July 28, 2014 @ 7:53 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar