www.maledatimes.com (“Maede ESAT” ይሻላል ወይንስ “ማዕደ ኢሳት”?) …አጭር መልእክት ለልባም ኢትዮጵያውያን! - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

(“Maede ESAT” ይሻላል ወይንስ “ማዕደ ኢሳት”?) …አጭር መልእክት ለልባም ኢትዮጵያውያን!

By   /   November 18, 2015  /   Comments Off on (“Maede ESAT” ይሻላል ወይንስ “ማዕደ ኢሳት”?) …አጭር መልእክት ለልባም ኢትዮጵያውያን!

    Print       Email
0 0
Read Time:15 Minute, 29 Second

ይሄይስ አእምሮ

ስለአሁኑም ሆነ ስለመጪው የሀገራችን ዕጣ ፋንታ ያገባናል የምንል ወገኖች ካለአንዳች መሳቀቅና ይሉኝታ የሚሰማንን መናገርና መጻፍ ይዘናል፤ በግዴለሽነት አባዜ ካልተለከፍን በስተቀር ደግሞ ይህ ጉዳይ የግዴታም ያህል ሊሆን ይገባል፡፡ ተደመጥንም አልተደመጥንም፣ መድረክ አገኘንም አላገኘንም እውነት የሆነንና እውነት መስሎ የታየንን እንናገራለን፤ እትብታችን ስለተቀበረባት የወል ሀገራችን ስንል ጩኸታችን ከአድማስ አድማስ ይናኛል፡፡ ለተቀየደ ወይም በቅድመ ሁኔታ ለታጠረ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትም ልናጎበድድ አንሻም፤ ለዚህ አልደኸየንም፤ ለዚህ ከሌላ ሰውና ከጓደኛም በታች አልሆንም፡፡ በምንናገረው  ወይ በምንጽፈው ነገር ውስጥ እንከን ቢኖርብን ሰው የመሆናችን ተፈጥሯዊ ጠባይ የሚያስከትልብን ሁሉን ማወቅ ያለመቻል ሰብኣዊ ውሱንነት እንጂ ሆን ብለን አንዱን ለማስከፋትና ለመጉዳት ወይም ሌላውን ለማስደሰትና ለመጥቀም እንዳልሆነ ሁሉም ሊረዳው ያስፈልጋል፡፡ በምንም ምክንያት ይሁን እውነትን መሸፈን ባህላችን እንደሆነ ሊቀጥል አይገባምና ሰሚ ባይኖር እንኳን ለአፈሩና ለዛፍ ቅጠሉ እንናገራለን፡፡ ስለግለሰቦችና ስለድርጅቶች ስሜትና የግል ፍላጎት ሣይሆን ስለሀገራችን ብቻ የሚሰማንንና የሚታየንን በመናገራችን ከያቅጣጫው የሚደርስብንን ሥነ ልቦናዊ ጦርነት ችለን በሚዲያው በኩል የአቅማችንን የምንውተረተር ብዙ ዜጎች አለን፡፡ አንዳንዶቻችን ጫናውና የምንታገለው የተግዳሮት ብዛት ሲበዛብን በጎመን በጤና አፋችንን ዘግተን ሊሆን ያለውን በአርምሞ የምንጠባበቅ አለን – ጥቂቶቻችን ደግሞ ባገኘናት ቀዳዳ ሁሉ መተንፈሳችንን ቀጥለናል – ዴሞክራሲ ወደ  ሀገራችን ተሳስቶም ቢሆን ይመጣ ይሆናል በሚል ምኞትና ተስፋ፡፡ ለማንኛውም አሁን አድማጭ ባይኖር መጪው ትውልድ ፍርዱን ይሰጣል፤ በተመሳሳይ አረንቋ ገብቶ እንዳይዳክርም ትምህርት ይቀስምበታል፡፡ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ እንደተናገረው ሐዋርያቱ ሲያስተምሩ የሚሰማቸው ሰው ጠፍቶ ሕዝቡ በእምቢተኝነቱ  የድንቁርና ልምሻ ተቀፍድዶ አልቀበላቸው ቢል የእግራቸውን አቧራ ሣይቀር አራግፈው ከዚያ ምድር እንዲወጡ አዟቸዋል፡፡ የነሱ አንደበትም አልተለጎመም፡፡  …

ባለፈው ሰሞን ስለኢሳት ዝግጅት አንድ መጣጥፍ ጻፍኩና እንደወትሮው ለምልክላቸው ድረገፆች ሁሉ – ለኢሳትም ጭምር – ላክሁ፡፡ በሚገርም ሁኔታ ከሞላ ጎደል ሁሉም “የዘወትር ደምበኞቼ” ያን ጽሑፍ የቅርጫት ሲሳይ አደረጉት – “እኔውም ዕብድ ነኝ ከወፍ የገበየሁ፤ መቀመጧን እንጂ መብረሯን የት አየሁ” ብዬ ልተርት አሰኘኝና ትርፉ ትዝብት ይሆናል ብዬ ከምላሴ ጫፍ ላይ መለስኩት፡፡ በባህላችን “የወለዱትን ሲስሙለት፣ ያቀረቡለትን ሲበሉለት ደስ ይላል” ይባላልና አለምንም ተጨባጭ ምክንያት ድግሴ መና ሆኖ ሲቀር በጣም ከፋኝ፡፡ መከፋቴ ስለኔ ስለራሴ አልነበረም፤ አይደለምም፡፡ የሀገሬ መፃኢ ዕድል ከአሁኑም የከፋ ሊሆን እንደሚችል በሚገባ ታየኝ፡፡ የእውነተኛው መሰደጃ ጊዜየም ኢትዮጵያ አሁን ከተቀፈደደችበት የአፓርታይድ ሥርዓት ነፃ ስትወጣ እንደሚሆን ተረዳሁ፡፡ በወቅቱ በንዴት ልጽፍ ፈለግሁና ስናደድ የምጽፈው ነገር እኔንም ቆይቶ ስለሚያናድደኝ እስኪበርድልኝ ድረስ አቆየሁት፡፡ አሁን ግን ልጽፍ ነው – ጀመርኩ፡፡

በነገራችን ላይ ያን ጽሑፌን ያወጡልኝን maledatimes.com እና mahidereandinet.comን ከልብ አመሰግናለሁ፡፡ ሌሎች ያወጡት ካሉ ማረጋገጥ አልቻልኩምና ባለማመስገኔ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ ለነገሩ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሀገራችን ማበብ የሁሉም ዜጎች ኃላፊነትና ግዴታ በመሆኑ አመስጋኝና ተመስጋኝ መኖር አለበት ብዬ እንደማላምንም መግለጽ እፈልጋለሁ – ለወጉና ለባህሉ ያህል ግን አሁንም በድጋሚ  ከልቤ ላመሰግን እወዳለሁ፡፡ የተቀረው ተከድኖ ይብሰል ከማለት ውጪ ብዙም መናገር አልችልም፡፡ (ለወትሮው የተለያዩ ተቃራኒ ሃሳቦችን በማስተናገድ የምትታወቀው የዘሀበሻ ድረገፅ እንኳን ምን እንደነካት ሳላውቅ ፊቷን ማጥቆሯ በጣም የገረመኝ መሆኔን ሳልጠቅስ ባልፍ ከራማዋ ይወቅሰኛልና አላስፈላጊ መሆኑን ብረዳም ይሄውና ከራሴ አወረድኩ፡፡ ግን “በባዳ ቢቆጡ በጨለማ ቢያፈጡ” ምን ዋጋ አለው?)

አንድ ሰው እንኳንስ የፈጠጠንና በግልጽ የሚታይን እውነተኛ ነገር ጠቁሞ ይቅርና ተሳስቶ እውነት የመሰለውን አንድ ነገር ቢናገር ኪላ ኪላ ሊባልና ሊወገዝ፣ ጀርባም ሊሰጠው አይገባም – ዛሬ ዓለም በደረሰችበት የሥልጣኔ ደረጃ ሊናገር የሚፈልግን አንድ ዜጋ ማፈን ዴሞክራሲያዊ ነውር ነው፤ ሃሳብን በሃሳብ ማሸነፍና ለአንባቢ ፍርድ መተው ሲገባ የሳንሱር ኅልውና ብርዥ ጥርዥ በሚልበት ዘመን በጸሐፊና በአንባቢ መካከል ያለውን ድልድይ መስበር ከ’babysitter”ነት ተለይቶ የማይታይ አንባቢን እንደሕጻን የመቁጠር ደርጋዊ የአእምሮ ህመም ነው – ለዚህ ደግሞ “ሁሉን ነገር እኔ አውቅልሃለሁ” የሚለው ወያኔ በቂያችን ሊሆን በተገባ ነበር፡፡ ይሄ ለጆሮ የሚጥምን ሙዚቃ ብቻ እየመረጡ የማዳመጥ ነገር ደግሞ በሙዚቃው ኢንዱስትሪ እንጂ ሃሳብን በነፃነት በመግለጹ የዴሞክራሲ ይትበሃል ውስጥ ሊሠራ አይገባም – ነገሩ እንዲያ ከሆነ አንዳርጋቸው ጽጌ እንዳለው “ነፃነትን የማያውቅ ነፃ አውጪ” በሚል ያስተቻል፡፡

መድሓኒት ይመራል ተብሎ ሳይወሰድ ከቀረ በሽታ ይነግሣል፤ ህልም የሚፈራ ሰው አልተኛም ቢል ጤንነቴ ይቃወስና ለአደጋ ይጋለጣል፡፡ ስለኔ ብጫቂ ወረቀት ወደ ቅርጫት መጣል ሣይሆን ስለሀገሬ የወደፊት ዕጣ መጨነቄና በብርቱው ማዘኔ እንግዲህ ከዚህ በሼክስፒር አገላለጽ “የመሆንና ያለመሆን” መሠረታዊ ነጥብ አንጻር ነው፡፡ ሌላው ይቅርና የሁልጊዜ ተፍጨርጫሪ እንደኔ ያለ ድኩም ዜጋ ጽፎ ሲልክ “ይቅርታ ወንደማችን፤ ይህ ጽሑፍህ እንደዚህ ያለ ጉድለትና ሕፀፅ ስላለበት ልናወጣው አልቻልንም፡፡ በሌሎች ጉዳዮች ግን እንደቀድሞው በርታልን፡፡” ቢሉኝ ደስ ባለኝ፡፡ ግን ግን ያ ኢትዮጵያን እግር ከወርች ጠፍንጎ የያዛት የትዕቢትና የዕብሪት ዐመል መች በቀላሉ ይሰበርና! የሚገርመው ይህ ትምክህት የትም ቦታ ሆነን፣ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ሆነን፣ በየትኛውም ጊዜ ውስጥ ሆነን ትንሽ እንኳን ለዘብ ሊልልን አለመቻሉ ነው፡፡ ገደል እየከተተን ያለው ባህርያችንም ይሄው ነው፡፡ “ለካንስ እነእንቶኔ እንደፌንጣ ዘልለው ወደወያኔው ጎራ የሚገቡት ወደው አይደለም?”ብዬም አዝኜላቸዋለሁ፡፡ አዎ፣ “የጨነቀው እርጉዝ ያገባል” እንዲሉ ነውና ግራ የገባው ሰው የአእምሮው ሚዛን በሁኔታዎች መጨናጎል ቢዛነፍና ወዳልጠበቀው አቅጣጫ ቢነጉድ አይፈረድበትም፡፡ አሃ! ለካንስ የባሰበትም እመጫት ያገባል፡፡ ከዚህ ይሠውር!

መናናቅና በከንቱ መነቃቀፍ የትግሥትና የግንዛቤ ዕጥረት  ውጤቶች ይመስሉኛል፤ መናናቅና በከንቱ መነቃቀፍ የተጣመመ ሥነ ልቦናዊ አቋም መገለጫ ናቸው ብዬም አምናለሁ፤ መናናቅና አለመከባበር የጨለማው ንጉሥ የሆነው ዲያቢሎስ ሞራላዊ ዕሤቶች ናቸው፡፡ ክርስቶስ የሐዋርያትን እግር አጥቦ መከባበርን የባሕርይ ልብሳችን እንድናደርግ በተግባራዊ ምሳሌ ያሳየን በምንም ዓይነት አመክንዮና በምንም ዓይነት መሠረት እኛን መሰሉን ሰብኣዊ ፍጡር እንዳንንቅ ብቻ ሳይሆን እንድናከብርም ለማጠየቅ ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ግን እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ አቅለቢሶች ሆንና የምንሠራውንም እስካለማወቅ የደረስን እንመስላለን – በወያኔ ምክንያት በከንቱ እየተቃጠለ ያለው ዕድሜያችን እያበሳጨንና እያሳዘነን ቀልብ አሳጥቶንም ሊሆን ይችላል – የተስፋይቱ ምድር ሀገረ ማርያም ኢትዮጵያ እየናፈቀችን በቀንም በሌትም የማያቋርጥ ስይት ውስጥ ስለምንገኝም ሊሆን ይችላል – ግን በዚያም በሉት በዚህ ከፍተኛ ጥድፊያ ላይ የምንገኝ ይመስለኛል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ስንዋትት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የቅርብ ወዳጃችንንና የአካላችንን ክፋይ ሳይቀር በካልቾ እየጠለዝን ከኛ እናርቀዋለን – አንዳንዱን ለጊዜው ስናስኮርፈው አንዳንዱን ደግሞ እጁን ጠምዝዘን በግድ ጎራ እንዲቀይር እናስገድደዋለን፡፡ ከኛ በላይ የሚያሳዝን አለ ታዲያ?  እናሳ እንዲህ እንዳሁኑ መበታተንና ወያኔን ለመሰለ ጭራቅ መዳረግ ይነሰን? ወያኔን ጥምብ እርኩሱን ስናወጣ የምንወደስ፣ ራሳችንን ስንተች ግን የምንወቀስና የምንወገዝ ከሆነ ከወያኔ በምን ተሻልን? የአምባገነንነት ግርድና አመሳሶ አለው እንዴ? “የበዛብህ ጴጥሮስን ዝናና ሙያ ለወንድሙ ለበየነ ጴጥሮስ አትስጡ፤ ስህተት ይታረም፤ ስህተትን ሳናውቅ በድንገት እንሳሳተው እንጂ እንደባህል የሙጥኝ ብሎ መያዝ ይቅርብን…” ብሎ መጻፍ ከአሁኑ አፈናና እመቃ ካስከተለ ነገ ደግሞ “የአዲሱ ‹ዴሞክራሲያዊ› መንግሥታችን ጠ/ሚኒስትር አንገት አጭር ነው” ተብሎ ቢጻፍ በስቅላት የሚያስቀጣ ወንጀል ሊሆን ነው ማለት ነው? በዴምራሲ ሥርዓ ሃሳብን በነፃነት መግለጽ የመጨረሻው ትንሽ መብት ነው፡፡ ይህን ማክበር የማይችል የዴሞክራሲ ፋኖ ካለ እንደዘረኛው ወያኔ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አቀንቃኝ እንጂ የእውነተኛ ዴሞክራሲ ጠበቃ ሊሆን አይችልም፡፡ በዴሞክራሲ ሥርዓት የግል ፍላጎትና እምነት ለግል ፍጆታ የሚውል ከመሆኑ ባሻገር በመተማመን ከሰው ወደ ሰው የሚያዛምቱት ወይ የሚያስተላልፉት እንጂ በሰዎች ላይ በግድ የሚጭኑት ሸቀጥ ሊሆን አይችልም፡፡ በአግባቡ የተያዘ  የሃሳብ ፍጭት እንጂ ለውጥን የሚያመጣ የሰሙትን ብቻ እንደሚደጋግሙት በቀቀኖች  አንድ ዓይነት ቃል እየተናገሩ የትም አይደረስም፡፡ “ዚአከ ለዚአየ” የቤተ ክህነት ይትበሃል እንጂ የዴሞክራሲ ባህል ገጽታ አይደለምና ከቁጡው ፊውዳላዊ የቂም በቀልና በከንቱ የመኮፈስ እሥረኝነት ባፋጣኝ መላቀቅ ያስፈለገናል፡፡ ይህንንም የምናደርገው ለኛ ብቻ ሣይሆን ለልጆቻችንና አሁኑኑም ሊሆን ይገባል – ጊዜ የለንም፡፡ እንዲሁ ስንጃጃል ከረምንና ዘመኑ  በጣም መሸብን፤ ጀምበሯም ልትገባ በእጅጉ አዘቅዝቃለች፡፡ ታዲያ ለቀረችን ትንሽ ጊዜ እንኳን እንደምንም ብለን ሰው አንሆንም?

እየፈጩ ጥሬነታችንን በጥልቀት ከመገንዘብ አንጻር ነው እንግዲህ “የኔ ስደት ኢትዮጵያ ነፃ ስትወጣ ነው” እንድል ያደረገኝ፡፡ አሁን ያለንበት ዘመን የባርነትና የዘረኝነት ነው፡፡ በኔ ውስን ግንዛቤ ነፃነት ፍቺው ብዙ ይመስለኛል፡፡ ዐማርኛው አንድ ቃል ብቻ ሆኖ አስቸገረኝ እንጂ በእንግሊዝኛው ቢሆን freedom, independence, liberty, salvation, emancipation, deliverance, ወዘተ. የሚሉ በርካታ ቃላት ስላሉና በመንፈስ፣ በአእምሮና በሥጋ መካከልም የሚንሸራሸር የፍቺ መጠነኛ ልዩነት ሊኖራቸው ስለሚችል ከዐማርኛው እንግሊዝኛው የበለጠ ገላጭ እንደሚሆን እገምታለሁ፡፡ እናም በአጭሩ ሀገራችን ሁለት ነፃነቶች እንደሚያስፈልጓት ልጠቁምና በዚያ ረገድ የሚታየኝን በመጠኑ ገልጬ ወደሌላው የተነሳሁበት ጉዳይ ላምራ፡፡

ኢትዮጵያ ከወያኔዎች ናቡከደነፆራዊ የእፉኝቶች አገዛዝ ነፃ መውጣት አለባት፤ ይህ በየግድ መሆን ያለበትና የሚጠበቅም ነው፡፡ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በቃሉ መሠረት በቅርቡ ነፃ ትወጣለች ብለንም ተስፋ እናደርጋለን – ምክንያቱም የዚህ ዓይነት ታሪካዊ አጣብቂኞች እየገጠሟት ብዙ ጊዜ ፈጣሪዋ ደርሶላታልና፡፡ ስሆነም ወያኔዎች በሠፈሩት ቁና ሊሠፈሩ የሚቀራቸው ጊዜ የተፈረመን ደብዳቤ ከአንድ ቢሮ ወደሌላ ቢሮ የሚደርስበትን ጊዜ ቢያህል እንጂ እምብዝም ዕድሜ ያላቸው አይመስልም፡፡ እንኳንስ የገዳዮች የሟቾችም ዘመን አልቋል፡፡

ይህ ነፃነት ሀገራዊ ነፃነት ነው – ከገዛ ልጆቻችን ቅኝ አገዛዝ ነፃ የምንወጣበትና ቢያንስ እንደ ኢትዮጵያውያን እንድንታይ ወደሚያደርገን የጋራ ቤት የሚያስገባን ነፃነት ነው፡፡ ከተናጠል እርግጫ ነፃ አውጥቶ ወደጋርዮሽ እርግጫ መግባት በራሱ ትልቅ ነገር ነው – ይህንንስ ማን አይቶበት፡፡ ይህ ነፃነት ትልቅ ነፃነት ነው፡፡ ይህ ነፃነት አሁን ካለንበት የአፓርታይድ አገዛዝ ሃራ የሚያወጣንና የጋራ ሀገር ባለቤት እንድንሆን የሚያስችለን ቢሆንም በብዙ መስዋዕትነት የሚገኝ ነፃነት ነው፡፡ ሲመጣ ደግሞ ዳፋው ቀላል አለመሆኑን ሁሉም ሊገነዘብ ይገባል፡፡

ሁለተኛው ነፃነት ከዴሞክራሲ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ነው፡፡ ይህ ግን ለኛ ለኢትዮጵያውያን የሚፈቀድ አይደለም – በሃያዎቹ ጣቶቼ እፈርማለሁ፡፡ ተፈጥሯችን ከዴሞክራሲያዊ ባህል ጋር ዐይንና ናጫ ነው፡፡ ቁርጡን እንወቅ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ወደኢትዮጵያ ከሚገባ ይልቅ ጂቡቲ ላይ በገመድ ራሱን ቢያንቅ እንደሚሻለው የሚመርጥ ይመስለኛል – አንመቸውም፡፡ ብዙዎቻችን ቀናነት የለንም፡፡ ሥልጣን እንወዳለን፡፡ ገንዘብን (የሚጠላ ሰው ባይኖርም) የኛው የተለዬ ነው፡፡ ለጦር መሣሪያ ያለን ፍቅር ገደብ የለውም – ለአንዲት ስንዝር መሬትና አንድ ቀን ለተኛናት ውሽማ ስንል የምንገዳደል “ጀግኖች” ነን፡፡ መከራን እንጂ ጥጋብን አንችልም፡፡ አንቀጥቅጦ የሚገዛንን ክፉ መንግሥትን እንጂ በፍቅር የሚያስተዳድረንን ደግ መንግሥት ስለመውደዳችን ማረጋገጫ ማግኘት አይቻለንም፡፡ የትግስታችን ድካ አፍንጫችን ሥር ነው፡፡ አንድን ነገር በውይይት ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ በጉልበትና በኃይል፣ በዛቻና በማስፈራራት፣ በጉቦና በዘመድ አዝማድ፣ በትውውቅና በአበልጅነት፣ በጎጥና በወንዝ ልጅነት … ባቋራጭ ወደችግራችን መፍትሔ መድረስ ይቀናናል፡፡ ሕግን በማክበር ከምናገኘው የኅሊና እርካታና ቁሣዊ ጠቀሜታ ይልቅ ሕግን በመጣስ የምናገኘው ጀብዳዊ ራስን የማታለል ተግባር ይበልጥ የሚያስደስተን ብዙዎች ነን፡፡ ሰውን በማማት፣ በምቀኝነት ዜጎችን ጠልፎ ባጭር በማስቀረት፣ አደራን በመብላት፣ በሰው ላይ በማሤር፣የሃይማኖታችን ትዕዛዛት በመጣስ፣ የባህልና የሞራል ዕሤቶችን በመረምረም፣ ወዘተ.  … ብዙዎቻችንን የሚስተካከለን የለም፡፡  ስለዚህ የዴሞክራሲን ጽንሰ ሃሳብ መረዳት አንችልም፤ ብንችልም እንኳን አንደበታችንና ተግባራችን አራምባና ቆቦ እየሆነ ጅምራችን ሁሉ ከዳዴነት ሳያልፍ ሾተላይ ይቀጥፈዋል፡፡ የተፈጥሮ ዝንባሌያችንን ዐይቶ ዴሞክራሲ ራሱም አይወደንም፡፡ ለንግግርማ ወያኔስ ይህችን “ዴሞክራሲ” የምትል ቃል ከሚሊዮን ጊዜ በላይ ሳይጠራት ይቀራል?

አስተዳደጋችን – የብዙዎቻችን ማለት ይቻላል – የተንሻፈፈ ነው፡፡ ብዙዎች ተረቶቻችንም ይህንን ይጠቁማሉ፡፡ ልጅና ሴት ወደጓዳ – ለልጅ አትሳቅለት ለውሻ አትሩጥለት – የማይቀጡት ልጅ ሲቆጡት ያለቅሳል – ልጅ ያቦካው ለራት አይበቃም  – ልጅ አትሁን – ቆማጣን ቆማጣ ካላሉት ገብቶ ይፈተፍታል – የልጅ ነገር አንዱ ጥሬ አንዱ ብስል – ንጉሥ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ –  ዝምታ ወርቅ ነው – በለፈለፉ በአፍ ይጠፉ – የአፍ ወለምታ በቅቤ አይታሽም – ነገር ካፍ ሲያመልጥ ፀጉር ሲመለጥ አይታወቅም – አቅምን አያውቁ – የእርጎ ዝምብ – ከደመኛው ጋር አብሮ የሚበላ – ደም የማይመልስ ልጅ አይወለድ – ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል – ዘመድ ከዘመዱ አህያም ካመዱ  …. እነኚህንና ሌሎችንም አጢኗቸው፡፡ ሰውን ለማፈንና በይሉኝታ ገመድ ሸብበው ወንጀል ለማሠራት የተፈጠሩ ተረቶች ናቸው – የበሰበሱና የገለሙ፡፡

በዚህን ዓይነት አፋኝና ጨቋኝ ባህል ያደገ ሰው ዐርባ ዓመት አይደለም አራት መቶ ዓመት አውሮፓና አሜሪካን ሀገር ቢጎለት የዴሞክራሲን ሀሁ ሊያውቅ፣ ቢያውቅ ሊተገብር አይችልም – ሥነ ልቦናው ውስጥ የሚያቃጭለው አምባገነንነቱና በልጅነቱ የተቀረፀበት የዝቅተኝነት ስሜቱ ነው – እናቱን በርግጫና በጡጫ ሲደልቅና በየፍርድ ቤቱ ሲያንከራትታት ያየውን የአባቱን “አኩሪ ታሪክ” ለመድገም አፄ በጉልበቱ ሆኖ ሰውን ማስጨነቅና ማስለቀስ ነው ምኞቱ፡፡ ይህ ዓይነት ሰው የዲግሪ ዓይነትና ብዛትም አይለውጠውም፡፡ ሁልጊዜ ጥሬ እንደሆነ ያረጃል እንጂ በሕይወቱ አወንታዊ ለውጥ አያመጣም፡፡ እንግዲያው ሀገራችን ምሁር አጥታ ነውን? በልምድና በዕውቀት የዳበረ ዜጋስ ጠፍቶ ነውን? መስተፃልዕ እንደተደገመበት ሰው በዘርና በጎሣ፣ በሃይማኖትና በቋንቋ እየተቧደንን የዓለም መሣቂያና መሣለቂያ ሆነን የቀረነው በወያኔ ትብታብ ብቻ ሣይሆን በኛም የባሕርይ መዛነፍ ሳቢያ ነው፡፡ በንግዱና በፖለቲካው ዘርፍ የተሰገሰገውን ሕዝበ አዳም ብታየው ኅሊናውን ስቶ ገንዘብ በማግበስበስ ላይ የሚገኘው ለሀገርና ለወገን ቅንጣት ባለማሰብ ነው – የነጋዴው  ትርፍ የሚሰላው በመቶኛ ሣይሆን በመቶዎች በሚገመት የዕጥፍ ስሌት ነው፤ የፖለቲከኛው ሙሰኝነት ቆብ ሸጣችሁም ቢሆን አምጡ የሚል አጥንትና መቅኒን የሚመጥ ነው፡፡ ዛሬ በሀገራችን ኢትዮጵያዊነት ይቅርና ሰው የመሆን ጥያቄ ራሱ በጥያቄ ውስጥ ከገባ ቆይቷል፡፡ እውነት ብትመርም በስኳርም ቢሆን እናወራርዳት፡፡ ሀበሾች ደግ ናቸው የመባላችንን ያህልና ከዚያም በባሰ ክፉዎች ሆነናል፡፡ አንዳችን የአንዳችንን ውድቀት እንጂ ዕድገት አንወድም፤ እንዲያውም ሌላው እንዳያድግ ያለ የሌለ ሀብት ንብረታችንን ለጠንቋይና ለደብተራ ገብረን ወዳጅ ዘመዶቻችንን የምናደኸይና የምናሳብድ ብዙዎች ነን – በየጠበሉ ሂዱና ምድረ የአጋንንት መንፈስ የሚለፈልፈውን ስሙ፡፡ ስለዚህም እኛ ወያኔ ሲያንሰን ነው!!!!! የወያኔን ዕድሜ ለማኞች እኛ እንጂ ወያኔዎችስ ቅንጦቱና የደም ባሕር ዋናው፣ የአጥንቱ ቁልል ድልዳሉ ሰልችቷቸው የቀያሪ ያለህ ማለት ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡ የኛ ኃጢኣት በዝቶ ግን የነሱን ዕድሜ እያረዘመ የማቱሳላንም ዕድሜ ሊያስከነዳው ተቃርቧል፡፡ ውሸት ነው ካልህ በዳኛ ፊት ሞግተኝና እርታኝ፡፡ ከ6 ሚሊዮን ሕዝብ መሀል ተመራርጠው ከትግራይ የመጡ ጥቂት የከተማ ወንበዴዎች 90 ሚሊዮኑን ሕዝብ እንዲህ ሊጫወቱበት የቻሉት በነሱና በላኪዎቻቸው የምሥጢራዊ ድርጅቶች(Cabals) ጥበብና ዕውቀት እንዲሁም ጥንካሬ ብቻ ሣይሆን በኛም የጠባይና የምግባር ብልሹነት ነው፡፡

ለአገዛዝ እንዲያመቻቸው መንግሥቶቻችን ሆን ብለው የሚጭኑብን የማይምነት ቀምበር ደግሞ ከየትኛውም ችግራችን ባልተናነሰ እንዲያውም በበለጠ ኮድኩዶ ያስቀረን ትልቅ የመከራ ሸክም ነው፡፡ የአሁኑ ማይምነትማ ተማረ በሚባለው የኅረተሰብ ክፍልም ተዛምቶ ሁላችንንም በገፍ እያደነቆረን ይገኛል፡፡ ማይምነት ሰጥ ለጥ ብለህ ለሆድህና ለወንበዴዎች አኮርባጅ እንድትገዛ የሚያደርግ ትልቅ የዕድገት ማነቆ ነው፡፡ ባገር ቤት ያለነው ዜጎችማ አቤት ስናሳዝን! ከከብት እኮ አንሻልም፡፡ ለካንስ ሰውን ወደከብትነት መለወጥም ይቻላል?

ለገረረው ጠባያችንና ድውዩ አስተሳሰባችን አንዱና ሌላው መንስኤ ሃይማኖታችን እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡ “አትመራመር – ትቀሰፋለህ!” እየተባለ በእመቃ የሚያድግ ዜጋ የነፃና ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ባለቤት ይሆናል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡ ሁለንተናዊ እሥር ቤት ውስጥ ነው የምንገኘው ወንድሞቼ፡፡ በቀላሉ የማይገላገሉት ማኅበረሰብኣዊ የተወሳሰበ ግንኙነት ውስጥ የሚገኝ ሕዝብ አሁን ተቀስፎበት እንደሚገኘው ያለ ውጥንቅጥ ችግር ውስጥ ቢገኝ አይደንቅም፡፡ ይህ ችግር ደግሞ በአሥራ ሰባት ወይ በሃያ አምስት ዓመታት ውስጥ የተፈጠረ ሣይሆን ለሺዎች ዓመታት ሲንከባለል የመጣ ነው፡፡ የሚያሳዝነው በየዘመናቱ እየጨመርን ሣይሆን እየቀነስን መጥተን አሁን የለየልን ውልየለሾች መሆናችን ነው – እነአክሱምና ላሊበላ የሚያንጓጥጡን የታሪክ ተወቃሾች ሆነናል፡፡ በቁጥር 96 ሚሊዮን ደረስን ብንባልም በአስተሳሰብና በአመለካከት ግን ከዓለም ሕዝብ የመጨረሻዎቹ ለመባል እንኳን የማንበቃ ሌላው ቀርቶ “የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራችን” – “ከ96 ሚሊዮን ሕዝብ መካከል ስምንት ሚሊዮኑ ለድርቅና ለርሀብ ቢጋለጥና ቢሞት it is OK. (ምንም ማለት አይደለም)፤ ከዚህም በላይ ወጪ ልናደርግ የምንችለው የሕዝብ ብዛት ስላለን ይህ ቁጥር ኢምንት ነው” በሚል ወራዳ ንግግር ከሰውነት በታች መውረዳችንን በቅርቡ በታሪክ መዝገብ ያሰፈርን ድንቅ ሕዝብና የድንቅ ሀገር ሕዝብ ነን፡፡ ከወረዱ አይቀር ደግሞ እንዲህ ነው፡፡ ሠለጠነ በሚባለው ሀገር አንድን ሕይወት ያለውን ዜጋ ቀርቶ በባዕዳን እጅ የሚገኝን አንድ በድን ሬሣ ለማስለቀቅ በሺዎች የሚቆጠሩ እሥረኞችን የሚፈቱ አገሮች መኖራቸውን ስንገነዘብ በኛ ሀገር እንዴት ያለ ከባድ መቅሰፍት እንደወረደ ለመረዳት አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ ያልዘራነውን አይደለም እያጨድን ያለነው፡፡ የምንገደለውም ሆነ የምንገድለው፤ የምንናቀውም ሆነ የምንንቀው እኛው ነን፡፡ የምንሰደደውም ሆነ የምናሰድደው፣ የምናከብረውም ሆነ የምናደኸየው እኛው እኛኑ ነው፡፡ ወያኔ ምን አደረገን? ወያኔ የልብሳችንን ልኬት የሚያሳየን፣ የቁመታችን መጠን የሚያመላክተን፣ የዕድገታችን ደረጃ የሚጠቁመን፣ … የኛነታችን ነፀብራቅ ክፉ ጽልመታዊው ጥላችን (silhouette) ነው፡፡ ይልቁንስ ውስጣችንን እንመርምር፡፡ እንደገናም ራሳችንን ራሳችን እንፍጠር፡፡ አሁን የለንምና፡፡

ፈጣሪ ሲፈጥረን ደግሞ ስህተታችንን ማመን አናውቅበትም፡፡ ስህተታችንን የሚነግረን ሰው ትልቁ ጠላታችን ነው – ቀድመን ስለምንንቀው፤ ሂስን እንደአቃቂርና መጥፎ ትችት በመቁጠር አስቀድመን ስለምንፈራ ፡፡ አቋማችን – “ሀበሻ ስህተት መሥራት አያውቅም፡፡” “ሀበሻ ፍጹምነትን የተላበሰ ምሉዕ በኩልሄ ነው” የሚል ይመስላል፡፡  ስለሆነም ብዙው ሰው ይቅርታ መጠየቅንና ስህተቱን ማመንን አያውቅበትም፡፡ አንዳች ስህተት መሥራቱን እየፈራህ እየቸርህ በትህትና ልትጠቁመው ብትሞክር ሽንጡን ገትሮ የሚከራከርህ የርሱን ፍጹምነት በማስረዳትና ያንተን ስም አጥፊነት በመግለጽ ነው፡፡ ትልቅ አለመታደል፡፡ ራስን ወደ ውስጥ ዞሮ ካለማየት የሚመነጭ ትልቅ ተፈጥሯዊ ጉድለት፡፡

በዚህ ረገድ ፈረንጆች ያስቀናሉ፡፡ “ይቅርታ፣ አመሰግናለሁ፣ መልካም፣ እሺ…” የመሳሰሉ ወርቃማ ቃላት አሏቸው፤ እኛ ዘንድ ግን እነዚህ ቃላት ምናልባት በመዝገበ ቃላት እንጂ በተግባር የዕንቁ ያህል ውድ ናቸው – በቀላሉና ተዘውትረው የማይደመጡ ቁጥብ ቃላት፡፡ እዚህም ትዕቢት እዚያም ትዕቢት … ቤትም ውስጥ ትዕቢት … በአደባባይም ትዕቢት… በችሎትም ትዕቢት… በቤተ አምልኮትም ትዕቢት፡፡ ከሞላ ጎደል ሁሉም በዕብሪትና በትዕቢት በመወጠሩ  ጥቂት ርቀቶችን ተራምዶ መሀል ላይ ለመገናኘት የሚሞክር ጠፋ፡፡ የዛሬ 50 ዓመት እንዲህ ነበርን፤ የዛሬ ሃያ አምስት ዓመትም እንዲሁ ነበርን፡፡ በዚሁ ከቀጠልን ደግሞ የዛሬ 100 ዓመትም እንዲሁ እንሆናለን፡፡ መጥኔ ለቀሪው፡፡ አንዳንዴ ሳስበው ዳርዊናዊ የሰውነት የዕድገት ደረጃችንን የጨረስን ስለመሆናችን እጠራጠራለሁ፡፡ ፈረንጆቹ የሚንቁን ለዚህ ይሆን እንዴ? እውነታቸውን ነው!

በማሰመሰሉ ሸንጎ ብዙዎቻችን አፋችን ጤፍ ይቆላል፡፡ ሃሳብን በነፃነት ስለመግለጽ ሃያ አራት ሰዓት አውርተን የማንጠግብ ብዙ ነን፡፡ ስለዴሞክራሲ መርሆዎችና አላባውያን ስንደሰኩር ለጉድ ነው – አፍ እናስከፍታለን፡፡ በተግባር ግን ድኩማን ነን – “ሲሉ ሰምታ ዶሮ ሞተች እጪስ ገብታ” እንደተባለው ነው፡፡ የእስራኤልና አሜሪካ ፓርላማ ከመሰዳደብ አልፈው የሸሚዛቸውን እጅጌ ሲሰበስቡና ሲደባደቡ በኋላ ግን ምንም እንዳልተፈጠረ ሆነው ሲስማሙና አብረው ሲበሉ ሲጠጡ እያየን እኛ ግን በአንዲት ቃል ተኮራርፈን በዚያችም የማትረባ ቃል ጦስ ለመገዳደል የአጭርና የረጂም ጊዜ ዕቅድ ነድፈን ወጥመድ ስንዘረጋና በከንቱ ስንጠፋፋ እንስተዋላለን፡፡ የብቀላችን አድማስ ደግሞ ሰፊና ዘመድ አዝማድን ሁሉ ሳይቀር የሚያካትት ነው፡፡ ስለዚህ ባጭሩ እኛ እንደገና ካልተፈጠርን ዴሞክራሲን አናገኘውም፡፡ ቡና አልጠሩንም ብሎ አፍንጫውን በሚነፋ ማኅበረሰብ ውስጥ፣ ተዘንግቶ ባልተጠራበት ሠርግ ምክንያት ወዳጁን  አኩርፎ በ15 ቁጥር ምስማር በሚጠረቅም ሕዝብ ውስጥ፣ ከሁለት ዐረፍተ ነገሮች የከረረ ንግግር በኋላ ወደጩቤና ጎራዴ የሚያመራው ቆሽተ ቀላል ዜጋ ጥቂት ባልሆነበት ኅብረተሰብ ውስጥ፣ የሥልጣን አራራው የአፋሩ የደንከል እሳተ ገሞራ ውስጥ እስኪጨምረው ድረስ የሚንጠራራው ዜጋ ጥቂት በማይባልበት ሀገር ውስጥ ዴሞክራሲ እንዲህ በቀላሉ ተገንብቶ አያለሁ ማለት በትንሹ ሞኝነት ነው፡፡ የሚወጣ እንጀራ እኮ እኮ ከምጣዱ ያስታውቃል – የመንጌ ዐማርኛ ትዝ አለችኝ፡፡ “ኢትዮጵያውያን በየጭንቅላታቸው ትንንሽ ዘውዶችን ተሸክመው ይዞራሉ” ብሎ የተናገረው ሰው ዘር ይውጣለት፡፡ እናም በዚህ ረገድ ተስፋ አይኑርሽ እህቴ፡፡ ትልቁን ነፃነት ግን ፈጣሪ በቶሎ ያምጣልን፡፡ ሌላው እዬዬም ሲደላ ነው፡፡ …

በርዕሴ ላይ ስለጠቆምኩት አንድ ነጥብ ጥቂት ልበል፡፡ ኢሳት “ማዕደ ኢሳት” የሚሰኝ ጥሩ ዝግጅት አለው፡፡ ማንም ባያዳምጠኝም ስለዚህ ግሩም ዝግጅት የታዘብኩትን አንድ አስተያየት ግን ልስጥ፡፡ በአዘጋጆቹ ጀርባ የሚታየው ጽሑፍ ዐማርኛው በእንግሊዝኛ ፊደላት ተጽፎ መታየቱ ለምን ይሆን? የምን “ሳይቸግር ጤፍ ብድር” ነው? ካስፈለገ “ማዕደ ኢሳት” ለሚለው በእንግሊዝኛው የሆነ ሐረግ ተፈልጎለት በዚያው ቋንቋ ቢጻፍ መልካም ነው፡፡ ዝግጅቱ በዐማርኛ ሆኖ፣ የዝግጅቱ ስያሜ በዐማርኛ ሆኖ፣ ተከታታዮቹ ዐማርኛ ተናጋሪዎች ሆነው(ዐማሮች አላልኩም!)፣ በአቅራቢዎቹ ጀርባ እንግሊዝኛ መታየቱ ጉራማይሌና በራስ ያለመተማመንን ሥነ ልቦናዊ ቀውስ በተዛዋሪ የሚጠቁም ነውና ይስተካከል፡፡ ይህን መናገር ደግሞ ሊያስከፋ አይገባም፡፡ ግንጥል ጌጡን በማስቀረት ባማርኛ “ማዕደ ኢሳት” ተብሎ ቢስተካከል ነውር የለበትም፡፡ ዐማርኛን ለማንኳሰስ ወያኔ በቂ ነው – በኢሳት ደግሞ አያምርም፡፡ በኢትዮጵያ ሀብት እያፈርን ስለኢትዮጵያ ዋስ ጠበቃ መሆን አንችልም፡፡

በሀገራችን የከፋ ርሀብ እንደገባ በስፋት እየተነገረ ነው፡፡ ረሀብን በሚገባ አውቀዋለሁ፡፡ እኔም የርሀብ ትራፊ ነኝ፡፡ ፈጣሪ ይህን የተጨመላቀ ዘመን ሊያሳየኝ ፈቅዶ በሕይወት አስቀረኝ እንጂ የዛሬ 45 ዓመታት ገደማ በርሀብ ልሞት እል ነበር፡፡ በአካባቢያችን ገብቶ በነበረ ጠኔ ሌሎች ወገኖቼ ሲረፈረፉ እኔና መሰሎቼ በዕድል ተርፈን ከነዚያም ውስጥ እስካሁን በሕይወት ካሉት አንደኛው ልሆን የበቃሁት በዕድል ነው፡፡ ስለዚህም ርሀብን ከፈረንሳይዋ ልዕልት በበለጠ አውቀዋለሁ፡፡ አደገኛ ጊዜ እየመጣብን ነው፡፡ ከፕሮፓጋንዳና ከመካሰስ እንዲሁም አንዱ የሌላኛውን ገመና ከማጋለጥ የዘወትር ድርጊት ባለፈ ተጨባጭ መፍትሔ ያሻዋል፡፡ ለንትርኩ ይደረስታል፤ ሕዝብን ማዳን ይቅደም፡፡

ይህን የርሀብ ወቅት ወያኔ በስለት የማያገኘው ሰይጣናዊ በረከት ነው፡፡ ዐማራን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት ያልፈነቀለው ድንጋይ የሌለው የትግሬው ገዢ መደብ ሕወሓት ይህችን ጊዜ በሚገባ በመጠቀም ብዙ ኢትዮጵያውያንን በተለይም ዐማራ የሚባሉትን ምሥኪን ወገኖቻችንን እንደሚጨርስበት መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ከፍ ሲል ለመጠቆም እንደሞከርኩት ይህን የርሀብ ወቅት ማንም ወገን ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ባለመጠቀምና ወያኔውን በተቻለ መጠን ከፊጋነት በማውጣት በልዩ ሥልት ወገንን መርዳት ይገባል፡፡ ፕሮፓጋንዳው ቀን ይሰጣል – ርሀቡ ግን ጊዜ አይሰጥም፡፡ አሁን ልዩ ሥልት ቀይሶና ወያኔን አባብሎም ቢሆን አንዳች ዘዴ ፈጥሮ ወገንን ማትረፍ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ለምሳሌ ደጋግ ትግሬዎች ወዳማራው አካባቢ ዕርዳታ ይዘው እየሄዱ ወገናቸውን እንዲረዱ ቢደረግ፣ ዐማሮች የሚባሉትም በተመሳሳይ ሁኔታ ወደትግሬዎችና ሌሎች አካባቢዎች እየሄዱ ዕርዳታ እንዲያደርሱ ቢደረግ ጥሩ ነው፡፡ ዐማራ የሆነ ሰው ወዳማራው አካባቢ ልሂድና ልርዳ ቢል ትግሬ ወያኔዎችና የተጋቦት ወያኔዎቹ ብአዴኖች ላይፈቅዱ ይችላሉ፡፡ ወያኔ እንዲያልቅለት የሚፈልገውን ሕዝብ ከርሀብ ዕልቂት ላድን ብሎ መነሣት ከመነሻው ዕብደት መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፤ ለዚህም ነው ብልህነትና ልዩ ሥልት አስፈላጊ ነው የምለው፡፡ ዓለም አቀፍ ተሰሚነት ባላቸው ሰዎችና መንግሥታት በኩል መሞከርም ያስፈልጋል፡፡ በሃይማኖት አባቶች በኩልም ጭራቆቹ የተወሰነ የማርያም በር ከፍተው ሕዝብ እንዲረዳ የሚደረግበት ብልኃት ቢመቻች ጥሩ ነው፡፡ ወያኔ ቀላል ቡድን አይደለም፤ የራሴ የሚለውን ሕዝብ ሣይቀር በወባ ክኒን ሰበብ ሽማግሎችን በመርዝ ጨርሶ የትግሬያዊ ኢትዮጵያዊነትን ደብዛ ለማጥፋት የሞከረ የማፊያ ቡድን ዐማራን በግላጭ አግኝቶ በርሀብ ሰበብ ከመጨረስ ወደኋላ አይልምና በቶሎ መረባረብ ይገባል፡፡ የትጥቅ ትግል እያደረጉ እንደሆነ ያወጁ አካላትም ጊዜው ሳይመሽና ብዙ ሕዝብ ሳያልቅ አንድ ነገር ማድረግ ይችሉ እንደሆነ መምከር ይገባቸዋል፡፡ ጨለማ ጊዜ እየመጣ መሆኑን ጡት ያልጣለ ሕጻንም ይረዳዋልና የምትችሉ ፍጠኑ፡፡

እንደኔ ትልቁ  መፍትሔ ወደፈጣሪ መጮህ ነው – በንጹሕ ልብ፡፡ በሀገር ውስጥ ጸሎትና ምህላ ማድረግ አይሞከርም፡፡ የየሃይማኖቶቹ አመራር አካላትና አባላት በወያኔዎች ስለተያዘ ይህ የጸሎት ጉዳይ በሀገራችን ውስጥ የሚታሰብ አይደለም፡፡ የፈጠጠ ርሀብ ባለበት በአሁኑ ወቅት እንኳን እግዚኦ እንበል ቢባል “ምን ተፈጠረ?” ከሚል ወያኔያዊ እሳቤ በመነሳት መንግሥት ተብየው የወያኔ የአጋንንት መንጋ ብቻ ሣይሆን እነ አቡነ ዘሊባኖስና እነኤጲስ ቆጶስ ዘኪሮስ ጸሎትና ምህላን በጭራሽ አይፈቅዱም፤ ቂልነታቸው ግን ይገርመኛል – እግዚአብሔርም እንደሰው የሚታለል ሳይመስላቸው አይቀርም መሰለኝ፡፡

ለማንኛውም የገባንበት አዘቅት እንዲህ ቀላል እንዳልሆነ መገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡ ጭቃ ስትረግጥ ምጧ የመጣባት ሴት እዚያው ላይ እንድትወልደውና ጭቃውን እንዲያጠነክረው ልጇን ከነደሙ በእግሯ እንድትረግጠው የተደረገበት  የጥንት እስራኤላውን በግብጽ ፈርዖናውያን የደረሰባቸው መከራና ስቃይ እኛ በወያኔ ከደረሰብንና ከሚደርስብን መከራና ስቃይ ሲነፃፀር ልዩነቱ የሰማይና የምድር ያህል ነው – በኛ ላይ የሚደርሰው በደልና እንግልት በእጅጉ ይበልጣል፡፡ … ቢሆንም ዴሞክራሲው ሲያምረን የሚቀር ሆኖ ቢያንስ ሀገራዊ ነፃነቱ እንኳን ይምጣልን፡፡ ያኔ እኔም ሊቀበለኝ ወደሚችል ሌላ ሀገር ተሰድጄ ቀሪዋን ሕይወቴን በሌላ ነፃነት እኖራለሁ – ቃል ነው፤ ቃሌን የሚያስለውጥ መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት አይኖርም ብዬ ግን ላምን አልፈልግም፡፡ ሁሉም ነገር ሲሞት ተስፋ ግን አይሞትም – የሞት መጨረሻ የተስፋ መሞት ነውና፡፡

ይህችን የኑዛዜ ደብዳቤ ለዘወትር ደምበኞቼ ላለመላክ ወስኜ ነበር፡፡ ግን ራሴን ራሴው ታዘበውና እኔው በኔው አንሼ የመታየት አዝማሚያ በራሴው ውስጥ ውልብ አለብኝ፡፡ እናም እየመረረኝም ቢሆን እንዲያውቁት ያህል ብቻ በግልባጭ  ልልክላቸው ወደድኩ፡፡ እንጂ ክልቤ ደስ ብሎኝ የላክሁት ቀድመው ላከበሩኝና ዴሞክራሲያዊ የመተንፈስ መብቴን ላከበሩልኝ ለmaledatimes.comና ለmahidereandinet.com ድረገፆች ነው፡፡ ሰው ያድርገን፡፡ ከሰው በታች እንደሆንን አያስቀረን፡፡ እኛም እኮ ዘጠኝ ወር ነው የምንረገዘው!

ሟርቴ ሀሰት ይሁንና በኢትዮጵያ ውስጥ እውነተኛ ዴሞክራሲ ሠፍኖ ቃላባይ ለመባል ያብቃኝ፡፡ ከአንድ ቃል ይልቅ የ96 ሚሊዮን ነፍሳት ክብደት ሰማይንና ምድር ያናውጣልና በተናገርኩበት ምላሴ ይሄውና አሁኑኑ ሣር ነከስኩ፡፡

ለመማርና ራሴን ለማረም ሁሌም  ዝግጁ ነኝ፡-  yiheyisaemro@gmail.com

 

 

 

… አለች  አሉ የጎንደር ወፍ

እዛፍ ላይ ብሠራ አሞራው መከራ፤

እካብ ላይ ብሠራ እባቡ መከራ፤

እየት ውዬ እየት ልደር፡፡

 

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 8 years ago on November 18, 2015
  • By:
  • Last Modified: November 18, 2015 @ 6:29 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar