www.maledatimes.com ሲያልቅ አያምር - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ሲያልቅ አያምር

By   /   February 28, 2017  /   Comments Off on ሲያልቅ አያምር

    Print       Email
0 0
Read Time:5 Minute, 38 Second

ተሻለ መንግሥቱ (teshalem1@gmail.com)

እንዳጀማመራቸው አምሮባቸው የሚያልቁ ነገሮች ቢኖሩ በጣም ጥቂት መሆን አለባቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ እንጂ ድል ባለ ድግስ የተዳሩ ጥንዶች በፍቺ ወይ በሞት እንደሚለያዩ፣ ብን ባለ ፍቅርና ወዳጅነት ውስጥ የነበሩ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች አንዳች ነገር በመሃላቸው ገብቶ እንደሚመነቃቀሩና “ዐይንህ/ሽ ላፈር” እንደሚባባሉ… ፀሐይ የሞቀው ማኅበረሰብኣዊ እውነታ ነው፡፡ እናም እውነትም እንዳማረ አይገድልም – ማለቂያም ሁሉ እንደጅማሮ አያምርም፡፡

ትናንት የካቲት 20 ቀን 2009ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ ትልቅ ድግስ ነበር፡፡ የድግሱ ባለቤቶች የመንግሥት ኮሙኒኬሽንና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴሮች ናቸው (በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ‹መንግሥት አለ› ብዬ እንደማላምን ሁሉም አንባቢ እንዲገነዘብልኝ እማጠናለሁ – ሲሉ ስለምሰማና ከሰው ላለመለየት ስል ነው ‹መንግሥት፣ መንግሥት› የምለው፡፡) የሁለቱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ቁንጮ ኃላፊዎች በድግሱ ቦታ የተገኙት ከጧቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ ነው፡፡ ድግሱ የሚጀመረው ደግሞ በ2፡30፡፡ ቀጠሮን ያለማክበርን ሀበሻዊ ባህል ሰብረው ቀድመው በመገኘታቸው “ባለሥልጣናቱ” ሊመሰገኑ ይገባቸል፡፡ይቺን ችግር ብንቀርፋት ትልቅ ሸክም እንዳራገፍን ይቆጠራል – እየጎተተን ነው፡፡ (ሰዓት የምናከብረው – አስቀድመንም የምንገኘው ቀብር ላይ ብቻ ነው – ቶሎ ለማዳፈን! ለነገሩ በመቀባበር ረገድ ሀበሻን የሚስተካከለው የለም ይባላል፡፡ ሠርግ ላይ ግን ቀርፋፋ ነን፡፡ ሰውን በማጉላላት መደሰት፡፡)

ዶክተሮች ነገሪ ሌንጮና ሂሩት ወ/ማርያም በጧት የተገኙበት ድግስ የዘንድሮን የዐድዋ በዓል በማስመልከት ወያኔ ያዘጋጀውን ዲስኩር ለማሰማት ነው፡፡ የተጋባዥ እንግዶች ቁጥር ከ3000 በላይ መሆኑ በቦታው ተገልጾኣል፡፡ ከሦስት ሺዎቹ እንግዶች ሦስተኛው ሰው ብቅ ያለው ከጧቱ ሦስት ሰዓት ገደማ ነው፡፡ አዘጋጆቹና የክብር እንግዶቹ ተደናግጠዋል፡፡ መድረኩን ይዘው ዐይኖቻቸውን ከበሩ ወደ ግድግዳው እያቁለጨለጩ ቢመለከቱ አዳራሹን የሰው ድርቅ እንደመታው አራት ሰዓት ያልፋል፤ አምስት ሰዓትም ሰዓቱን ጠብቆ መምጣቱ አልቀረም – ግን ሰው የለም፤ ውር ውር ብቻ፡፡ አምስት ተኩል ገደማ ሲሆን ባለው ሰው ይጀመር ተባለ፤ ያኔ ከ3000 የተጋበዘ የአዲስ አበባ ሕዝብ መካከል 120 ብቻ ተገኝቶ ነበር – የደርግ አባላትን ያህል፡፡ ንቀት ነው!

መቼስ ማል ጎደኔ፡፡ ስብሰባው መጀመር ነበረበት፡፡ ተጀመረ፡፡ ወጉ አይቀርምና “እንኳንስ ለዚህኛውን ያህል የዐድዋ በዓል አደረሳችሁ!” ተባለና በምሥራች መልክ ዲስኩሩ ከመድረክ ይሰራጭ ጀመር፡፡ በመንግሥት ተኳኩለው እንዲገኙ የተደረጉ “አርበኞች”ም ቦታ ቦታቸውን ይዘዋል፡፡

እውነቱን ለመናገር የቀረው ቀርቶ የተገኘውም ሰው ስሜት አልባ ነበር፡፡ የመጣውም ሙሉ አካልና ግማሽ ልቦናው ብቻ ነው – ከታሪክ ጠልነቱና ከአፍራሽነቱ አንጻር ወያኔን ጠንቅቆ የሚያውቀው ተሰብሳቢ በልቡ “ለማያቃችሁ ታጠኑ” እያለ ነው – “ሰይጣን ለዘዴው ከመጽሐፍ ቅዱስ ይጠቅሳል” ይባላልና ወያኔም ለዘዴው ሲል ፍጹም የሚያንቋሽሸውንና ሊያወድመው ቆርጦ የተነሣውን የኢትዮጵያ ታሪክ እንዳሁኑ ከፍተኛ የችግር አጣብቂኝ ውስጥ ሲገባ አንዳንድ ታሪኮችን አቧራቸውን እያራገፈ ካሉበት ያነሳና ላይታመን በከንቱ ሕዝብን ለማነሁለል ይሞክራል – ሕዝቡማ “ያልወለድኩት ልጅ ቢለኝ አባባ አለኝ አፌን ዳባ ደባ” እያለ መተረት ከጀመረ 25 ዓመታት ነጎዱ፡፡ ሕዝብና ወያኔ ዘይትና ውኃ – ዐይንና ናጫም ናቸው፡፡ ለማንኛውም ይህ የዛሬው ጥረቱ ሕዝብንና የፈረደበትን “ዓለማቀፉን ማኅበረሰብ” የማጭበርበር ተፈጥሮው አካል ነው፡፡ ግን ሞኝ አትበሉኝና ይሄ “ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ” የሚሉት ነገር የት ይሆን ያለው? እኛን ያውቀናል ለመሆኑ? እንዴት እንደምንኖርስ ትንሽ ግንዛቤ አለው? እንደምገምተው ከሆነ ረቂቅ ማለትም  ጽንሰ ሃሳባዊ  ፍጡር ይመስለኛል፡፡ አለበለዚያ እንዴት እንደምንኖር ያውቅና አንዳች መፍትሔም ፈልጎ ያገኝልን ነበር፡፡ የተዘፈቅንበት የሲዖል ኑሮ ለማንም ግልጽ ነውና፡፡…

ከተሰበሰበው ተጋባዥ እንግዳ መካከል አንዳንዱ ለሽንት እያለ ገና ጉባኤው ከመጀመሩ ውልቅ ማለት ጀምሯል፡፡ ለ3000 ሰው የተዘጋጀ ምሣ በመቶ ሰው አካባቢ ተበላ፡፡ ጉድ ተባለ፡፡ መንግሥትና ሕዝብ ተለያይተዋልም ተብሎ ሃሜት ተስተጋባ፡፡ ወያኔ ከሚያምናቸውም መቆራረጡ በለኆሳስ ይወራ ገባ፡፡

በጉባኤው ወቅት የሕዝብ አስተያየት ተጠይቆ መድረከኞቹ እያወናገሩና በሀፍረት እየተሸማቀቁ፣ እያምታቱና አራምባና ቆቦ እየዘለሉ የመለሷቸው ጥያቄዎች ብዙ ናቸው፡፡ ሲያልቅ አያምር – ለካንስ ጅል አስተላለቅ ሰውንም ያጃጅላል፡፡ የተከበሩ ዶክተሮች በተገጠመላቸው የወያኔ ሲዲና ዲቪዲ ምክንያት ሲቃትቱና ቋንቋና ወኔ እየከዳቸው እንዲያ ሲዘለባብዱ የታዘቡ ስለነሱ አፈሩ፡፡ “መማር ከንቱ” ብለውም አዘኑላቸው፡፡ ይቺ አንዲት እንጀራ – የወጧ ጉዳይ በይደር ይቀመጥና – እንዴት ከሰውነት ተራ እንደምታወጣ በወያኔያዊ አገላለጽ ግንዛቤ ተወሰደባት፡፡

 

ይህ ክስተት ብዙ ነገር ያሳያል – ጥቂቶቹን በወፍ በረር ለመቃኘት ያህል፡-

 

  1. የወያኔው መንግሥት የዐድዋን በዓል ተንተርሶ ምንም ነገር መሸጥ እንደማይችል ተጋባዥ እንግዶች በዋናነት በጉባኤው ባለመገኘት ጭምር በግልጽና ያለ አንዳች ፍራቻ ነግረውታል፡፡ ይህ አጋጣሚ ለመንግሥት ተብዬው የወያኔ ቡድን(ጉጅሌ) ትልቅ ውርደት ነው፡፡ ወያኔ አንበሣ ሆኖ የሚያውቅ ከሆነ እዚህ ላይ “አንበሣ ሲያረጅ የዝምብ መጫወቻ ይሆናል” ተብሎ ቢተረት ህፀፁ ለክፉ የሚሰጥ አይመስለኝም፡፡ በቃ፤ ሕዝብ  ወያኔን መጥላቱን፤ ወያኔ ለሚጠራው ሀገራዊ ስብሰባም ሆነ ጉባኤ ማር ቢዘንብ እንኳን መገኘት የማይፈልግ መሆኑን አሳይቶበታል፡፡ ለብልኅ ሰው ትልቅ መልእክት ነው፡፡ ሰማይ ይጠቋቁራል፤ ነጎድጓድ ይከተላል፤ መብረቅ ይሰልሳል፤ ከዚያስ? ከዚያማ ምኑ ይወራል፡፡ ሲደርስ ለማየት ዕድሜና ጤና መለመን ብቻ ነው፡፡ ግን ግን “ለኃጥኣን የመጣ ለጻድቃን ይተርፋል” እንደሚባለው ጥንቸል ዝኆን አለመሆኗ እስኪጣራ ከሚደርስባት ዓይነት ስቃይና እንግልት ለመዳን ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ መሆኑን መገንዘብ ይጠቅማል፡፡
  2. ወያኔ አንዳች ችግር ቢገጥመው እንደቀድሞ እየታዘዘ ሕዝብን የሚጨርስለት ኃይል እያጣ መሆኑንም በተዛዋሪ መረዳት ይቻላል፡፡ ስብሰባን እንዲህ መርገጥ ከተቻለ አንዳች አቅም ቢፈጠር ወያኔ ማለት በህዝባዊ ጎርፍ በደቂቃዎች ውስጥ ተጠራርጎ ወደ ቆሼ ተራ የሚጣል – በመጥፎ ገናና ስሙ ብቻ ኅልውናውን አስጠብቆ አየር ላይ የሚኖር ባዶ ቀፎ መሆኑን መገንዘብ አያቅትም፡፡ ችግሩ፣ ችግር እስኪፈጠር ችግርን ለማወቅ የማንችል ልበ-ሥውራን ፖለቲከኞች መብዛታችን ነው እንጂ የኢትዮጵያ መሬትና ሰማይ ያረገዙትን ብንረዳ ቢያንስ ራሳችንን – የትራጂክ ትያትሩን ደራሲያንና ተዋንያንን – ከማይቀርልን የዕልቂት አደጋ ማውጣት በተቻለን ነበር፡፡ እስኪ የዓይነ ኅሊናችሁን መቅረዝ ለኩሱትና ለአፍታ ይህን አስቡ – ከሶቪየት ኅብረት ካልተማርን፣ ከሦርያ ካልተማርን፣ ከሶማሊያ ካልተማርን፣ ከየመን ካልተማርን፣ ከአፍጋኒስታን ካልተማርን፣ ከሊቢያ ካልተማርን፣ ከማዕከላዊ አፍሪቃ ካልተማርን፣ ከናይጄሪያ ካልተማርን፣ ከቱኒዝያ ካልተማርን፣ ከሱዳኖች ካልተማርን፣ ከኮሪያዎች ካልተማርን፣ ከጀርመኖች ካልተማርን፣… ከማንና ማንስ ከሰማይ ወደ መሬት ወርዶ እንዲያስተምረን እንጠብቃለን? የኛ አላዋቂነትና ከንቱነት እኮ ወደር የለውም፡፡ የእሳትን አቃጣይነት ለማወቅ በግድ እጃችንን እቶን ውስጥ መክተትና ቆራጣ መሆን አለብን ማለት ነው? “አንገት የተፈጠረው አዙሮ ለማየት ነው” እንላለን፡፡ አንገታችን የት ገባ ታዲያ?
  3. ይህን ጉባኤ ውስጥ ዐዋቂዎች በዚህ መልክ እንዳየነው ባዶ ነበር፡፡ ወያኔው በሚቆጣጠራቸው ሚዲያዎች ግን – ትግስቱ ኖሮት ለሚከታተል- በነበረ ፊልም ወይም ያው የተሰብሳቢ ቁጥር እየተባዘተ(በ ‹dubbing› system) አራትና አምስት ሺህ ተሣታፊ እንደተገኘ ተደርጎ ዜናው ሲራገብ የሚታዘብ ሰው ኢቲቪ የተጣባውን ባሕርያዊ የሀሰት ዜና አሰራጭነት በጉልኅና በተጨባጭ ይረዳል – ምንም እንኳን ይህ እውነታ የአደባባይ መሥጢር ቢሆንም፡፡

 

ስለዚህ “ታሪካዊ” ስብሰባ የምላችሁ ሁሉ እውነት ነው፡፡ ከሁሉም የማይረሳው ግን በዚሁ ስብሰባ አንድ ካህንና አንድ ጨዋ የተናገሩት ነው፡፡ ካህኑ ምን አሉ – “ዛሬ ዐወደ ምሕረቶች ባዶ ናቸው፡፡ ይሄ ቃና የሚባል ቲቪ ሕዝቡን ከቤተ ክርስቲያንም እየለየው ባዶኣችንን እየቀረን ነው፡፡….” እውነታቸውን ነው – ይህ ደግሞ የወያኔ ሥውር ሤራም ይመስላል፤ ሽማግሌዎችና አሮጊቶች ሣይቀሩ “ሀገር ለምኔ!” ብለው ቲቪያቸው ሥር እንደባልዲ በመደቀን 24 ሰዓት የሚከታተሉት ይህን ሀሽሽ ቲቪ – ቃናን – ነው፡፡ በስንት ዓይነት አሜሪካዊና አውሮጳዊ ማደንዘዣ ኢትዮጵያ እየጠፋች እንደሆነ ስታስቡት ይህች ምሥኪን ሀገር አንጀታችሁን ነው የምትበላው፡፡ እኔ ራሴ ኢሳትን ከማየት የተከለከልኩት በዚሁ ጣቢያ ጦስ ነው – እግዜር ይይለት፡፡ የዚህን ጣቢያ ትናጋ የሚዘጋልኝ ባገኝ የአንድ ወር ደሞዜን ባመት ብሰጥ ቅር አይለኝም፡፡ ልጆች አያጠኑም፤ ሠራተኞች አይሠሩም፤ ብዙ ሰዎች አቅላቸውን እያጡ ወሬያቸው ሁሉ የቃና ገጸ ባሕርያት ሆኗል፡፡ … ኧረ በቅጡ የፈላ ሽሮ ማግኘት ራሱ ብርቅ እየሆነብን ነው፡፡

ጨዋው ደግሞ “እናንተ የጣላችሁትን ታሪክ የአሁኑ ትውልድ እንዴት ይወቀው? ‹ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ…› ይባላል፡፡ ወጣቱን ከሀገሩ ታሪክ ለይታችሁ ራቁቱን አስቀራችሁት፡፡ ዐድዋን ቀርቶ አሁን ራሱንም አያውቅም፡፡ የታሪክን ትምህርት ከየዩንቨርስቲው ሥርዓተ ትምህርት አወጣችሁት፡፡ የሀገር ፍቅርን በጎሣና በብሔር ሸንሽናችሁ ትውልዱ አየር ላይ ተንሳፍፎ ቀረ፡፡ አሁን እኮ ‹የዐድዋ ጦርነት ምንድን ነው?› ተብሎ ቢጠየቅ ‹በእንግሊዝና በጣሊያን መካከል የተደረገ ጦርነት ነው› ብሎ የሚመልስ ትውልድ መሀል ነው የምንገኘው፡፡…” ግሩም ታዛቢ ነው፡፡ ሌሎችም የመሰላቸውን ተናግረዋል፡፡ በአንጻራዊ ሁኔታ ጥቂት ዴሞክራሲያዊነት የታየበት መድረክ ነበር፡፡ የፈራው ብዙ ቢሆንም በመጣው ይምጣ ተናግረው የወጣላቸው ነበሩ፡፡ ያ የኮማንድ ፖስት የሚሉት የጅብ ውኃ ጠጪ ዓይነት ጭራቃዊ ፍጡር አንደበታቸውን የሸበበባቸው ተሣታፊዎች እንደነበሩም መገመት አይከብድም፡፡ እርሱ እላይ ሆኖ እየጠጣ ሳለ እታች ሆና የርሱን ትራፊና እርጋጭ የወንዝ ውኃ እየጠጣች የነበረችዋን ምሥኪን አህያ “ውኃውን አታደፍርሽብኝ!” ብሎ የተቆጣው ወያኔ-ጅብ ትዝ አላችሁ? አዎ፣ ከወያኔ መገላገል ማለት ከጅብ መገላገል ማለት ነው – ሊያውም ከቀን ጅብ፡፡

ዋናው ነገር የጣር ጉዳይ ለመተንበይ አስቸጋሪ በመሆኑ መቼ ነፍሱ እንደምትወጣ መናገር ይከብዳል እንጂ ወያኔ “በአልጋ ቁራኛ በደዌ ዳኛ” መመታቱን በዚህች ትንሽ ግን የትልቅ ትልቅ በምትሆን አጋጣሚ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ለሥርዓተ ቀብሩ እንዲያደርሰኝ ለራሴ እየጸለይኩ ልለያችሁ፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 7 years ago on February 28, 2017
  • By:
  • Last Modified: February 28, 2017 @ 4:11 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar