www.maledatimes.com መቶ አለቃ እሸቱ አለሙ እድሜልክ እስራት ስተፈረዳባቸው - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Addis Admas  >  Current Article

መቶ አለቃ እሸቱ አለሙ እድሜልክ እስራት ስተፈረዳባቸው

By   /   December 15, 2017  /   Comments Off on መቶ አለቃ እሸቱ አለሙ እድሜልክ እስራት ስተፈረዳባቸው

    Print       Email
0 0
Read Time:4 Minute, 9 Second

ዘሄግ (14 dec. 17) ዛሬ ዲሴምበር 15 ቀን 2017 ከቀትር በኋላ በሆላንድ ዘሄግ ከተማ የዋለው ችሎት በመቶ አለቃ በእሸቱ አለሙ አቃቤ ህግ ባቀረበባቸው የጦር ወንጀል ክስ እድሜልክ እስራት በይኖባቸዋል። በተጠቀሳባቸው ክስ በሙሉ ጥፋተኛ ተብለዋል። ከሁለተኛው አለም ጦርነት በህዋላ እንዲህ አይነት ፍርድ በሆላንድ ሃገር ሲሰጥ የመጀመርያው መሆኑን አቃቤ ህግ ተናግረዋል። በሃገሪቱ ህግ የእድሜ ልክ እስራት አመክሮ የለውም።

አቶ እሸቱ አለሙ በውሳኔው ሰዓት ችሎቱ ላይ መገኘት አልፈለጉም።

በአራት ዳኞች በተሰየመው በዚህ International Crime Chamber የተሰኘ ችሎት የመሃል ዳኛዋ ማርየት ሬከንስ የፍርድ ውሳኔውን ባሰሙበት ወቅት አቃቢያን ህጎቹ እና የተበዳይ ጠበቆች በውሳኔው የደስታ ስሜት ታይቶባቸዋል።

ከ29 ኦክቶበር 2017 ጀምሮ ሲታይ የነበረው ይህ የፍርድ ሂደት የከሳሽ አቃቤ ህግንና የተከሳሽ ጠበቆችን ክርክክር ለወር ያህል ሲያዳምጥ ቆይቶ ፣ ውሳኔ ለመስጠት ከ3 ሳምንት በኋላ ቀጠሮ ይዞ እንደነበር የሚታወስ ነው።

ከሁለት አመት በላይ የፈጀው ይህ በአይነቱ ለየት የሚለው፣ የአቶ እሸቱ አለሙ የምርመራ እና የክስ ሂደት አለም አቀፍ ትኩረትን ስቦ ነበር። ፍርዱ በተሰጠበት በዛሬው እለትም በርካታ የሃገር ውስጥ እና የውጭ ሃገራት ጋዜጠኞች ወደ ችሎቱ ታድመዋል።

የ63 ዓመቱ እሸቱ አለሙ ከ 120 የደርግ አባላት አንዱ ሲሆኑ፣ በ1970ዎቹ ቀይ ሽብር ዘመን ደርግን ወክለው የጎጃም ክፍለ ሃገር አስተዳዳሪ እንደነበሩ በችሎቱ ፊት ቢመሰክሩም የተመሰረተባቸውን የጦር ወንጀል ክስ ግን ሲቃወሙ ነበር።

አስራ ሁለት ዓመት ፈጅቶ የነበረው የኢትዮጵያው የቀይ ሽብር ወንጀል ችሎት እ.ኤ.አ 2006 አቶ እሸቱ አለሙ ላይ በሌሉበት የሞት ፍርድ መወሰኑ አይዘነጋም።

በ1991 ኢህአዴግ ሃገሪቱን ሲቆጣጠር አቶ እሸቱ አለሙ ከነበሩበት ከቡልጋርያ ወደ ሆላንድ በመምጣት የፖለቲካ ጥገኝነት በመጠየቅ በ1992 የሆላንድ መኖርያ ወረቀት ያገኙ ሲሆን ከ5 አመት በኋላም የሃገሪቱ ዜጋ ሆነዋል። ግለሰቡ በ 2015 ክመኖርያ ቤታቸው ባላሰቡበት መንገድ ተይዘው ታሰሩ። ኦክቶበር 29, 2017 – በታሰሩ ከ 2 ዓመት በኋላ – ጉዳዩ በሄግ ችሎት መታየት ጀመረ።

በሆላንድ አቃቤ ህግ የቀረበባቸው ክስ በነሃሴ ወር 1978 ፣ በ75 ወጣቶች ግድያ (በቅዱስ ሚካኤል ቤተ-ክርስትያን ውስጥ ተገድለው በጅምላ የተቀበሩ) በዘጠኝ ዜጎች ላይ የተደረገ ድብደባ እና የማሰቃየት ወንጀል እና በ 321 ሰዎች ላይ በደረሰ ህገ-ወጥ እስራት የሚል ነው።

ለክሶቹ ክ3000 ገጽ ያላነሰ የጽሁፍ ማስረጃዎች ፣ ፎቶ እና ተንቀሳቃሽ ምስልሎች፣ ከኢትዮጵያ፣ ከአሜሪካ፣ ከካናዳ እና ከእንግሊዝ የተገኙ ከ30 በላይ የአይን ምስክሮች ( ከነዚህ ውስት ስምንቱ ምስክሮች ከካናዳ እና ከአሜሪካ ተጉዘው በሄግ ችሎት በመገኘት ምስክርነታቸውን የሰጡ ሲሆን፣ በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉ ሶስት ባለሙያዎች (ፕ/ር ጃን አቢንክ ፣ ዶ/ር ካሳ እና ክፉሉ ታደሰ) በማስረጃነት ቀርበዋል።

የሆላንድ ፍትህ ሚንስትር በአቶ እሸቱ ላይ ክሱን ለመመስረት መነሻ የሆነው፤ እ.ኤ.አ. በ1998 ‘ፍራይ ኔደርላንድ’ (ነጻ ኔዜርላንድ) በሚል መጽሄት ስለ ተከሳሹ የወጣ ወንጀል ነክ ጽሁፍ ነው። የሆላንድ አለም ዓቀፍ የወንጀል ምርመራ ቡድን ይህንን ጽሁፍ እንደተመለከተ ከ2009 ጀምሮ የአቶ እሸቱን ስልክ በመጥለፍ መከታተል እንደጀመረ አቃቤ ህግዋ ሚስ ኒኮል ፎገለንዛግ ተናግረዋል።

ይህ ቡድን በ2012 ወደ ኢትዮጵያ በመጓዝ የኢዮጵያን መንግስት መረጃ ቢጠይቅም ከመንግስት በኩል ትብብር እንደተነፈገውም አቃቤ ህግዋ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ መንግስት በጉዳዩ አልተባበርም ለማለቱ የሰጠው ምክንያት ጉዳዩ በሃገር ውስጥ በቀይ ሽብር የወንጀል ችሎት ስላለቀ መቶ አለቃ እሸቱን አሳልፋችሁ ስጡን በሚል ሰበብ ነው። በሆላንድ እና በኢትዮጵያ መካከል የወንጀለኛ ልውውጥ ስምምነት ባለመኖሩ እና በኢትዮጵያ የሞት ፍርድ መሰጠቱ ተጠርጣሪውን የማስረከቡ ጥያቄ ውድቅ ሊሆን ችሏል።

አቶ እሸቱ አለሙ ፍርድ ቤት ቀርበው ክሱ በተደመጠበት ወቅት “የተሳሳተ ሰው ነው የያዛችሁት” ብለው ነበር። ማስረጃዎች ሲቀርቡና የምስክሮች ቃል መሰማት ሲጀምር በወቅቱ አስከፊ ነገር እንደተፈጸመ ተናግረው ፣ ለተፈጠረው ነገር ሁሉ ይቅርታ ጠይቀዋል። ይሁን እንጂ እሳቸው በወቅቱ በፕሮፓጋንዳ ስራ እንደተሰማሩና አንድም ሰው እንዳልገደሉ፣ ሰው እንዲገደልም ሆነ እንዲታሰር ትዕዛዝ እንዳልሰጡም ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።

“ይህን አጋጣሚ ተጠቅሜ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንዳደርግ ፍርድ ቤቱ እድል ስለሰጠኝ አመሰግናለሁ። 120 የደርግ አባላት ውስጥ አንዱ ሆኜ ስለተሰራው ወንጀል አዝናለሁ። ግን የቀረቡብኝ ክሶች በሙሉ አልቀበልም።” ብለዋል።

“የ4 ሺህ አመት ታሪክ ያላት ሃገራችን እንዳትፈራርስ አሜሪካንን እርዳታ ብንጠይቅ እንቢ ስላሉን ነው ወደ ሶቭየት ለመሄድ የተገደድነው። በወቅቱ የተደራጀው ሃይል ደርግ ብቻ ነው። ኢህአፓ ሃገሪቱን ሊያፈርስ በእብደት የተነሳ ሃይል ነበር። አቶ ክፍሉ ታደሰ የኢህአፓ አመራር የነበሩ በመሆናቸው ሃሳባቸው ነጻና ገለልተኛ ሊሆን አይችልም።” ሲሉም ኢህአፓን በፍርድ ቤት ውሎ ኮንነዋል።

ሚ/ር ሳንደር አርት፤ የአቶ እሸቱ ጠበቃ የስም መደባለቅን እንደ ለመከራከርያ አቅርበው ነበር። ወንጀሉን የፈጸሙት ተከሳሹ እሸቱ አለሙ ሳይሆኑ ሌላ እሸቱ ናቸው ሲሉ ተከራክረዋል።

“የግድያውን ትዕዛዝ የያዙ ፊርማዎች የሱ ሳይሆኑ የሌላ እሸቱ ናቸው። ምስክሮቹም የተናገሩት የሚያሳምን አይደለም። የፍርዱ ሂደት ፍትሃዊ አይደለም። አቶ እሸቱ አለሙ በ2015 ከቤታቸው ተወስደው ሲታሰሩ ወንጀለኝነታቸው አስቀድሞ እንደተረጋገጠ ይተቁማል።” የሚል ነበር የመከራከርያቸው ጭብጥ።

ሌላው የጠበውቃው መከራከርያ ነጥብ ደግሞ “በ1978 ጎጃም ውስጥ የርስበርስ ውግያ ባለመካሄዱ ጉዳዩ የጦር ወንጀል ሊሆን አይችልም። ተራ ወንጀል ደግሞ በዚህ ችሎት መታየት አይችልም።” የሚል ሲሆን፣ ቀደም ሲል አቶ እሸቱ አለሙ በጎጃም ኢህአፓ በተደራጀ መልክ ጦርነት ከፍቶ እንደነበር ለፍርድ ቤቱ የተናገሩት ቃል ይህንን መከራከርያ ነጥብ አፍርሶታል።

የተበዳዮች ጠበቃ የሆኑት ሚስ ባርባራ ፋን ስትራተን – ለእያንዳንዱ ተበዳይ 200 ካሳ ኤሮ እንዲከፈል ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል። ይህ ካሳ ምንም እንኳን መጠኑ ዝቅተኛ ቢሆንም ጥፋቱን ለማስረገጥ የተደረግ ተምሳሌታዊ (ሲምቦሊክ) ነው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ሁለት የሩዋንዳ እና አንድ የኢራቅ ተወላጆች ላይ ተመሳሳይ ክስ ተመስርቶ እንዳንዳቸው በ 16 17 አመት እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል።

በሆላንድ የእድሜ ልክ እስራት የሚበየነው እጅግ አስከፊ ለሆነ ወንጀል ስለሆነ የተመክሮ መብትም የለውም። በሃገሪቱ እድሜልክ የተፈረደባቸው ሰዎች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው።

አቶ እሸቱ አለሙ ባለትዳር እና የሁለት ልጆች የነበሩ ሲሆን ባለቤታቸው እና ልጆቻቸው በውል በማይታወቅ ምክንያት ከአመታት በፊት ጥለዋቸው ወደ አሜሪካ በመሄድ ኑሯቸውን እዚያ አድርገዋል። በ2015 ከመታሰራቸው በፊት ሆላንዳዊት የትዳር ጓደኛቸው ጋር ይኖሩ ነበር።

የአቶ እሸቱ መያዝ እና መታሰር የዚህን ትውልድ ትኩረት ባይስብም አሁን በሃገሪቱ እየተፈጸመ ላለው ተመሳሳይ ወንጀል አይን ከፋች ነው። በሰብአዊነት ላይ ወንጀል ሰርቶ ከሃገር መውጣት እና መደበቅ እንደማይቻል ትምህርት ይሆናል። የሆላንድ ፍትህ ሚኒስቴር ያሉትም ይህንኑ ነው። “ሃገራችን ዜጋቸውን ጨፍጭፈው ለሚመጡ ወንጀለኞች የመደበቅያ ገነት መሆን የለባትም!”

“እሸቱን ያየህ ተቀጣ!”

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

♦ “ ትክክለኛ ፍትሕ አይሰጡም” የተባሉት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ከችሎት እንዲነሱ ተጠየቀ !

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar