www.maledatimes.com Ethiopia: የቀይ ለባሾቹ ውሎና አዳር - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

Ethiopia: የቀይ ለባሾቹ ውሎና አዳር

By   /   March 19, 2013  /   Comments Off on Ethiopia: የቀይ ለባሾቹ ውሎና አዳር

    Print       Email
0 0
Read Time:21 Minute, 39 Second

በበፍቃዱ ኃይሉ

ወጣቷ ዓለምን የቀን አጋጣሚ ስድስት ኪሎ አካባቢ፣ በዕለተ እሁድ (መጋቢት 8/2005) አንቀዥቅዦ አመጣት፡፡ በዕለቱ የለበሰችው የአዘቦት ቀይ ቲ-ሸርት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ለመዋል ምክንያት ይሆነኛል ብላ አልተገመተችም ነበር፡፡ በሰዓቱ የባለራዕይ ወጣቶች ማኅበር እና የሰማያዊ ፓርቲ አባላት የኢትዮጵያውያን ጠላት የነበረው የፋሺስት ጣሊያን ጄኔራል ግራዚያኒን ኃውልት (በጣሊያን አገር፣ የትውልድ መንደሩ አካባቢ) መቆም በመቃወም የሰልፍ ጉዞ ከስድስት ኪሎ (የካቲት 12 ሰማዕታት መታሰቢያ ኀውልት) እስከ ጣሊያን ኤምባሲ ድረስ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ ነበር፡፡ የሰልፉ ተሳታፊዎች ከጀርባው ላይ ‹‹ለግራዚያኒ ኀውልት ማሠራት አባቶቻችን የከፈሉትን መስዋዕትነት ማራከስ ነው›› የሚል ጽሑፍ የታተመበት ቀይ ቲ-ሸርት ለብሰው ነበር፡፡ የኢሕአዴግ ካድሬዎች ደግሞ ‹‹ይቺ ባቄላ…›› በሚል ምክንያት ነው መሰለኝ ‹‹የተቃውሞ ሰልፍ…›› የሚባለውን ነገር ለማስቆም ራሱ ግብግብ ፈጥሮ፣ ራሱ ቀይ ለባሾቹን ማፈስ ሲጀምር ዓለምንም አብሮ አፍሶ አጋዛት፡፡

(ፎቶ፡- ከታሳሪዎቹ ሞባይል)

በተመሳሳይ ሰዓት ለሥራ ጉዳይ ጓዙን ጠቅልሎ ወደአፋር ለመጓዝ እየጠበቁት ያሉ ባልደረቦቹን ለማግኘት በታክሲ ውስጥ ይጓዝ የነበረ አንድ ሰው ከስድስት ኪሎ ተነስቶ አምስት ኪሎ እስኪደርስ የተመለከተውን ሁካታ ዓይቶ ላለማለፍ ከታክሲ ይወርዳል፡፡ ፖሊሶች ከሰልፈኞቹ ውስጥ አሳደው የያዙትን እያፈሱ መኪና ውስጥ ሲያጉሩ፣ ከፖሊሶች ዕይታ እየተሰወረ በሞባይሉ ፎቶ ለማንሳት ሲሞክር፣ አንድም የረባ ፎቶ ሳያነሳ በሦስተኛው ፎቶ ላይ ከፖሊሶች ጋር ዓይን ለዓይን ተጋጠመ፡፡ እሱም ተይዞ ተከተላቸው፡፡ ይህ ድንገተኛ እስረኛ የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ ሆነ፡፡

 

 

የታፈሱት ሰልፈኞች ሁሉ የታጎሩት በአራዳ ፖሊስ መምሪያ ጊቢ ውስጥ ነበር፡፡ ጊቢው ውስጥ እንደደረስኩ ከፊት ለፊቴ ደረጃው ላይ የተኮለኮሉትን ሰልፈኞች ተመለከትኩ፡፡ ወጣቶቹ ታፍሰው የገቡ ሳይሆን ወደው የተሰበሰቡ ይመስሉ ነበር፡፡ እንዲያውም በገባሁ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ጮክ ብለው ይዘፍኑ ጀመር፡-

 

‹‹… ተከብረሽ የኖርሽው ባባቶቻችን ደም፣ ባባቶቻችን ደም

እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውደም…››

 

በዚህ ጊዜ ከፖሊሶቹ አንዱ አብሮ ሲዘምር ይታይ ነበር፡፡ ፖሊሶቹ የተሻለ ትሁቶች ቢሆኑም፣ ሲቪል ለባሾቹ ግን ማመናጨቅ እና ማዋከብ ዋነኛ ሥራቸው ነበር፡፡ እኔን በመኪና ይዘውኝ ከመጡት ውስጥ አንዱ ‹‹ዴሞክራሲ በዛ…›› የሚለውን ቃል እየደጋገመ በቁጭት ይናገራል፡፡ ብዙዎቹ የመምሪያው ፖሊሶች ከየት እንደመጣ የማያውቁት ኮማንደር ግን የተቆጨው በመዘግየቱ ነው፤ ‹‹ይሄን ያክል እስኪሰባሰቡ መቆየት አልነበረብንም›› አለ – እኔው ጎን ቁጭ ብለው ሲነጋገሩ፡፡ በሬዲዮናቸው ሲለዋወጡ ከነበረው ውስጥም ‹‹ሱማሌ ተራ የተጎዳውን ሰውዬ የት ወሰዳችሁት?… ተክለሃይማኖት ሆስፒታል?…›› ይባባሉ ነበር፡፡ በዚሁ ጉዳይ ይሁን አይሁን ግን ‹‹መረጃም (ማስረጃም)›› አልነበረኝም፡፡

 

ጊቢው ውስጥ ከሌሎቹ እንዳልቀላቀልና ብቻዬን እንድቆይ አድርገውኛል፡፡ ባንድ በኩል ስልኬ ላይ ያሉትን ፎቶዎች አጥፍተው ይፈቱኛል፣ ጉዞዬም ይቀጥላል በሚል ደስ ብሎኛል፡፡ በሌላ በኩል በዓይን የማውቃቸውን እነዚያን ልጆች ቀረብ ብዬ አለማነጋገሬ ቆጭቶኛል፡፡ በዚህ መሐል ግን ሁሉም እየሄዱ ቃል ሲሰጡ ቆዩ (ቃል ሲባል ቃል እንዳይመስላችሁ፤ ከስም አንስቶ የኔ የምትሉትን ነገር በሙሉ ይጠይቋችኋል)፤ ከዚያም የኔም ተራ ደረሰና ቃል ሰጥቼ ሳበቃ እኔም በቀላሉ እንደማልሰናበት ሲያረዱኝ የጓዝ ኮተቴን ሁሉ አስመዝግቤ እዚያው ተጠቃለልኩ፡፡

 

ከዚያም ቃል የመስጠቱ ሥነ ስርዓት ቀጠለ፤ የመጣው ሁሉ በራሱ መንገድ ያንኑ ጥያቄ መልሶ፣ መላልሶ እያንዳንዱን ታሳሪ (ተጠርጣሪ ልበል ይሆን?) ይጠይቃል፤ እያንዳንዱም ተጠርጣሪ ይመልሳል፡፡ ሆኖም ብዙዎቹን መርማሪዎች የብስጭት መንስኤ የሚሆን ነገር ባለራዕዮቹ ወጣቶች ሳይናገሩ አይወጡም ነበር፡፡ ብሔር ሲባሉ ‹‹ኢትዮጵያዊ›› ይላሉ፡፡ ይህንን የሚሉት ‹‹ብሔር›› የሚለው ቃል ከግዕዝ የተወሰደ ሲሆን፣ ትርጉሙም ‹‹አገር›› መሆኑን እያጣቀሱ ነው፡፡ ታዲያ ይህ አባባል ለመርማሪዎቹ የሚያበሳጭ ድፍረት ነበር፡፡

 

ፖሊሶቹ የሆነችውን ሁሉ እየደወሉ፣ ለአለቆቻቸው ይናገራሉ፡፡ ከዚህ መሐል ከሰልፈኞቹ አንዱ ለብሶት የነበረው ባንዲራ ላይ በእስክርቢቶ የጻፈውን ደብዳቤ ከስልኩ ወዲያ ላለ ሰው በንባብ ሲያጽፉት ሰምቻለሁ፡፡ ጽሑፉ ባብዛኛው መንፈሳዊ ነው ቢባል ይቀላል፡፡ ‹‹ለእመቤታችን በአስራትነት የተሰጠችው አገራችን ኢትዮጵያ…›› ብሎ ነው የሚጀምረው፡፡

 

ምርመራው/ጥያቄው ቀጥሏል፤ ከጠያቂዎቹ መካከል የደኅንነት እና የኢንሳ ሰዎችም ነበሩበት፡፡ ከጥያቄዎቻቸውም ውስጥ የኢሜይል አድራሻ እና የይለፍ ቃል፣ የፌስቡክ አድራሻ እና የይለፍ ቃልም ይጠይቁ ነበር፡፡ እያንዳንዱ ታሳሪ (ተጠርጣሪ አልልም) ስሙን በቪድዮ ካሜራ ፊት እንዲናገር ይገደድ ነበር፡፡ እንግዲህ ይህንኛው መጀመሪያ ላይ እያንዳንዱ ሰው ከተነሳው ፎቶ በተጨማሪ መሆኑ ነው፡፡ በዚህ የጅምላ እስር ውስጥ ካስተዋልኳቸው ጉዳዮች ውስጥ የሴቶቻችንን ጀግንነት ነበር፡፡ ለምሳሌ፣ እኔ ያለምንም ማንገራገር ምስሌን አስቀርጬ ወደቃለመጠይቁ ሳልፍ የሰማያዊ ፓርቲዋ አመራር አባል ሐና ዋለልኝ ‹‹አልቀረጽም፣ አሻፈረኝ›› ብላ ስትሟገት ድምፅዋ ይሰማኝ ነበር፡፡

 

ሲመሽ ይፈቱን ይሆን? እዚሁ ያሳድሩን ይሆን? ሌላ ቦታ ይወስዱን ይሆን? ምን ብለው ይከሱን ይሆን? እየተባባልን የተሰባሰብንባት አንዲት በረንዳ መሳይ ክፍል ውስጥ፣ ኢቴቪ በቀጥታ የሚያስተላልፋቸውን የአዳማ እና የመቐለ የኦሕዴድ እና የሕወሓት ስብሰባዎች መኮምኮም ጀመርን፡፡ አሳሪዎቻችንም በስልክ አለቆቻቸውን እያነጋገሩ ሽር ጉዳቸውን አጧጡፈውታል፡፡ ኢቴቪም ብቻውን በዓሉን ማክበር አልቻለም፡፡ መብራቱ ብልጭ ድርግም አበዛ፡፡ ብልጭ ድርግም አልኩ እንጂ ያበዛውስ ድርግም ማለት ነው፤ አልፎ፣ አልፎ ግን ላፍታ ብልጭ እያለ ነበር፡፡ በጨለማው ውስጥ ራታችንን በጨለማ ተቋደስን፡፡ ሁላችንም ምሳ ያልበላን ቢሆንም አንዳንዶች ግን ቁርሳቸውንም አልበሉም፡፡

 

የመታሰራችን ዜና በማኅበራዊ አውታሮች በመጠኑ ቢስተገባም የብዙዎቻችን ቤተሰቦች ግን አልሰሙም፤ ደውሎ የማሳወቅ ዕድሉም አልተሰጠንም፡፡ እዚያው ጨለማ ውስጥ ከቆየን በኋላ ወደ 3፡00 ሰዓት ገደማ ወደ ጃንሜዳ አካባቢ የሚገኝ ማረሚያ (እስር ቤት) በሁለት ዙር ተወሰድን ከ30 በላይ እስረኞች አንድ ላስቲክ ብቻ ወለሉ ላይ የተነጠፈበት ክፍል ውስጥ ብንታጎርም በእርስ በርሳችን ጫወታ ተጠምደን ነበር፡፡ (በነገራችን ላይ እኛ ወደዚህ እስር ቤት ስንዛወር ቀይ ለባሽዋ ዓለም ተለቅቃ ወደቤቷ ሄዳለች፡፡) የሄድንበት በሰልፉ ዋዜማ ሲቀሰቅሱ ከታሰሩ ሌሎች ጋር ተቀላቅለናል፡፡ የጅምላ እስሩ ጉዳይ በዋዜማው እንደተጀመረ ያወቅኩትም ያኔ ነው፡፡ ቀድመው ከታሰሩት ውስጥ ሁለቱ ክፉኛ ቡጢ እና ካልቾ ቀምሰው እንደሆነ ለማወቅ እስኪናገሩ መጠበቅ አያስፈልገንም ነበር፤ የአንደኛው ጃኬት የደረቀ ደም ከፊትለፊት ይታይበታል፡፡

 

ለአምስት ሰዓት ዐሥራ አምስት ደቂቃዎች ሲቀሩት ግን እንደገና እንድንንቀሳቀስ ተነገረን፡፡ ከኛ ቀደም ብለው ሴቶቹም ወደቀጨኔ (ችሎት መድኃኔዓለም ኮንዴሚኒዬም አጠገበ ያለ) ወረዳ 9 ማረሚያ ቤት እንደተወሰዱ እና ከኛም ውስጥ 12ቶቻችን መከተል እንዳለብን ተነገረን፡፡ እዚያ እንደደረስን ግን ምነው እዚያው በቀረን የሚያስብል ትዕይንት ገጠመን፡፡ እያንዳንዱ ክፍል እላይ በላይ ተደራርበው በተኙ እስረኞች ተጨናንቋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ጫማ ማስቀመጫ ቦታ እንኳን በክፍሉ ውስጥ ስለሌለ ጫማዎቻችንን ውጪ እያስቀመጥን እንድንገባ ተገደድን፡፡ ሦስቱ (አራት ሜትር በአራት ሜትር የሚገመቱ) ክፍሎች ውስጥ አንዱ 37፣ አንዱ 34 እና ሌላኛው ውስጥ 30 እስረኞችን ይዟል፡፡

 

እንዳጋጣሚ 30 ሰዎች የያዘው ውስጥ ነበር እኔ የደረሰኝ፡፡ የኛ ክፍል ይሻላል ተብሎ ዶ/ር ያዕቆብንም አመጧቸው፡፡ ጉዳዩ በጣም አሳዛኝ ነበር፡፡ እኛስ ባልደከመ ጉልበታችን እንችለዋለን፤ ለርሳቸው ግን በጣም ፈታኝ እንደሚሆን መገመት ቀላል ነው፡፡ ክፍሉ በጣም ጥቅጥቅ ብሎ ከመሞላቱ የተነሳ ለኛ ቦታ ለማግኘት የቤቱ ካቦ ተነስቶ እያንዳንዱን እስረኛ እየቀሰቀሰ ማጠጋጋት ነበረበት፡፡ በቦታ ጥበት ምክንያት ደረቁ ወለል ላይ በአንድ ጎናችን እንድንተኛ ከመገደዳችን የተነሳ እኔ ይህን ጽሑፍ እስከምጽፍበት ሰዓት ድረስ ቁርቋሬው የፈጠረው ሕመም ጎኔን አያስነካኝም፡፡ ካቦው አጠጋግቶልን ሲጨርስ ሁላችንንም የገቢ ገንዘብ ተቀበለን እና ተኛን፡፡ እዚያ ክፍል ውስጥ መተኛት ማለት፣ መተኛት ማለት አይደለም፡፡ የክፍሉ መታፈን እና አስቀያሚ ጠረን፣ ሙቀት፣ በዚያ ላይ እየተቀባበሉ የሚያጨሱት ሲጃራ ጢስ፣ ከዚያ እና ከዚህ የሚተኮስ የፈስ ሽታ… ብቻ የአበሳ ናሙና ነበር፡፡ ሌሊቱን ሲዘንብ ማደሩ ግን በከፊልም ቢሆን የክፍሉን አየር አቀዝቅዞታል፤ ችግሩ ዝናቡ ውጪ ያስቀመጥነው ጫማ ውስጥ ውኃ መሙላቱ ብቻ ነበር፡፡

 

እንደምንም ነጋልንና ወደፍርድ ቤት እንደምንሄድ ተነግሮን ጥንድ ጥንድ እየተደረግ በካቴና ተቆላለፍን፡፡ ከመሐከላችን አንዱ የማኅበሩ አባል፣ ፀጉሩን አጎፍሮ ስለነበር (ለፍርድ ቤቱ ውበት አይመጥንም ብለው ይሆናል) ይቆረጥ አሉና መቀስ አንስተው ይከመክሙት ጀመር፡፡ ፀጉሩን ቆርጠው ሲጨርሱ አሰለፉንና ካቴናችንን ፈቱት፡፡ ‹‹ፍርድ ቤት መወሰዳችሁ ቀርቷል፣ ምናልባት ፖሊስ ጉዳዩን ይፈታዋል›› ተባልንና ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ወደጃንሜዳ ማረሚያ ቤት መልሰው ወሰዱን፡፡ እዚያ ስንደርስ ለፖሊስ ዋስ እያቀረብን እንድንፈታ ተፈቀደልን፡፡ ቀድሞውንም የታሰርነው ያለወንጀል በመሆኑ አስገራሚ ውለታ አልነበረም፡፡

 

የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ የሚያስፈልገው ቅድመ ሁኔታ ለመስተዳድሩ ማሳወቅ ሲሆን፣ መስተዳድሩ ደግሞ በ24 ሰዓት ውስጥ ‹‹አይሆንም›› የሚል ደብዳቤ ካልጻፈ እንደተፈቀደ ይቆጠራል፡፡ ስለዚህ ሰልፍ ማድረጉ ሕጋዊ ስህተት የለበትም፣ ጉዳዩ ባንድ ጀምበር የተወለደ ሳይሆን ጋዜጦች ዜና የሰሩለት፣ ቁጥቦቹ ሬድዮዎች ሳይቀሩ ያወሩለት ጉዳይ ስለሆነ ወንጀል ነው ፍርድ ቤት ሊያቀርቡት አይችሉም/አይገባቸውምም፡፡ ነገር ግን ‹‹…ካፈርኩ አይመልሰኝ…›› ይመስላል በዋስትና እንድንፈታ ፈቅደው ያገቱብንን ንብረቶቻችንን እየመለሱ መጋቢት 9/2005 እኩለ ቀን ላይ አሰናበቱን፡፡

—-

የዚህ ጽሑፍ ዋና ቅጂ በኢትዮጵያ እንዳይነበብ በታገደው በዞን ዘጠኝ ጦማር ላይ ይገኛል፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on March 19, 2013
  • By:
  • Last Modified: March 19, 2013 @ 8:50 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar