www.maledatimes.com የማለዳ ወግ … የተዘጋውን የአረብ ሀገራት የኮንትራት ሰራተኛ አቅርቦትን ለመክፈት የወጣው ረቂቅ ! - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የማለዳ ወግ … የተዘጋውን የአረብ ሀገራት የኮንትራት ሰራተኛ አቅርቦትን ለመክፈት የወጣው ረቂቅ !

By   /   December 2, 2014  /   Comments Off on የማለዳ ወግ … የተዘጋውን የአረብ ሀገራት የኮንትራት ሰራተኛ አቅርቦትን ለመክፈት የወጣው ረቂቅ !

    Print       Email
0 0
Read Time:5 Minute, 18 Second

* ስለ ሰራተኞች መብት ጥበቃ መነሳቱ አልተዘገበም
* በተወያይ ኤጀንሲዎች በኩል ግን ቂቁን ውዝግብ አስነስቷል
* ከዚህ ቀደም ያለ በኮንትራት ለተበተኑትስ ዜጎችስ ምን ታስቧል ?

አዲሱን መረጃ ያገኘሁት ሃገር ቤት ከሚታተው ከአድማስ ጋዜጣ ላይ ነው ፣ እንዲህ ይላል ” ወደ አረብ አገራት የሚሄዱ ሰራተኞች ላይ የሚደርሰውን ችግርና እንግልት ለማስቀረት በሚል ከአንድ ዓመት በላይ ተቋርጦ የቆየውን አሰራር ለማስጀመርና ለመቆጣጠር የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ውዝግብ አስነሳ፡፡ ” ይላል … ወረድ ብለን ዝርዝር መረጃውን ስንቃኝ በዋናነት መታየት ያለበት አንኳሩ የሰራተኞች ይዞታና የመብት ጥበቃ ጉዳይ በዘገባው ላይ አልተካተተም። ይሁን ብለን ዝርዝሩን ስንቃኝ ለዚህ ቀደም በነጻ ያገኙትን ቪዛ በደላላ በየገጠር ከረሞች ሰብስበው የላኳቸው እህቶቻችንን ከመላካቸው አስቀድሞ ፈቃድ ሲያወጡ ለመንግስት ያቀረቡት የገንዘብ መያዣ በደል ደርሶባቸው ለሚመለሱ ዜጎች ካሳ ሲከፈል አላየንም አላሰማንም ። ከሁሉም የሚያመው ሰራተኞች ሲላኩ ለሚደርስባቸው አደጋ ኢንሹራን ሳይቀር ገንዘብ የላኳቸው ቢሆንም በተበደሉበት ሃገር እያሉም ሆነ በደል ተፈጽባቸው ሃገር ቤት ሲገቡ በከፈሉት ኢንሹራን ተጠቃሚ አይደረጉም። የሰራተኞችን መብት አሟልተው ስራ ለማሰማራት እንግዲህ ውል ገብተው በወሰዱት ፈቃድ ልክ ውል ሲያፈርሱ ህግ አስፈጻሚ አካላት በኩል በዝምታ የታለሀፉት የእኛ ስራና ሰራተኛ አገናኝ ደላላ “ኤጀንሲዎች ” በአዲሱ ረቂቅ ያነሱት ተቃውሞ ቅድመ ሁኔታዎች አያሰሩንም የሚል መሆኑን እያመመኝ አነበብኩት! እንቀጥል …

በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ሰራተኞችን የሚልኩ ኤጀንሲዎች ያሰሙት የኤጀንሲዎች ቅሬታ የስራ ፈቃዱን ለማግኘት ከአንድ ሚሊዮን እስከ አምስት ሚሊዮን ብር ካፒታል ሊኖረው ይገባል መባሉና ለሰራተኛው መብትና ደህንነት ዋስትና ማስከበሪያ የሚውል 100 ሺህ ዶላር (ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ) በዝግ ሂሳብ የማስቀመጥ ግዴታ አለበት መባሉ ነው ። ጋዜጣው ኤጀንሲዎች ለስራ ወደ ውጭ አገር የላኳቸውን ሰራተኞች ለኢትዮጵያ ኤምባሲ በ15 ቀን ውስጥ ማስመዝገብና የስራ ፈቃድ ማግኘታቸውን የሚያረጋግጥ መረጃ ለሚኒስቴሩ ማቅረብ እንዳለባቸውምና ለስራ የሰደዷቸውን ሰራተኞች በሚሔዱባቸው ሃገራት ላሉ ኢንባሲና ቆንስል መስሪያ ቤቶች በ15 ቀናት እንደሚያስታውቁ ይጠቁማል ።

የኤጀንሲዎች የአዞ እንባ …

ኤጀንሲዎች ” ይህ መሰሉ ረቂቅ ህግ እንደማያሰራቸው እንዲያውም በውጭ ሃገር ስራ ለማሰማራት የሚፈልጉትን ዜጎች እድል ያጠባል ፣ ህገ ወጥነትን የሚያባብስ ነው ” ሲሉ ህመሙን ወደ የመከረኞቹ ህመም ሊያደርጉት የአዞ እንባ የማንባት አትነት ቅሬታ መሰማታቸውን በአድማስ ጋዜጣ ዘገባ ተጠቅሷል ። እንደ ጋዜጣው ዘገባ ኤጀንሲዎች ረቂቁን ህግ በወይይቱ የተቃወሙበትና ያልደገፉበት ዋንኛ ምክንያታቸው የተደነገገውን ቅድመ ሁኔታ ለማሟላት እንደሚከብድ መሆኑንም ያስረዳል ።

ዳግም እንዳናነባ …!

ከወራት በፊት ጀምሮ “ወደ አረብ ሃገራት የተዘጋው የኮንትራት ቪዛ ይከፈታል !” የሚል መረጃ በሰፊው በመሰራጨት ላይ የሚለውን የሹክሹክታ ከሰማን ወዲህ ረቂቁ ለውይይት መቅረቡን ይህው ሰማን ። ከዚሁ ጋር ባያያዝኩት EBC TV ዘገባ እንደ ምትመለከቱት የዜና ዘገባ ከወራት በፊት የተባበሩት ኢምሬትን የጎበኙት ፕሬዘደንት ዶር ሙላትና የኢምሬት አምባሳድር አቶ አብድልቃድር የተዘጋውን የአረብ መንገድ መቸ እንደሚከፈት ተጠይቀው ሲመልሱ ” ህግ ሆነ መመሪያ እየወጣ መሆኑን ጠቁመው ነበር ። ከዚህ ጋር በማያያዝ በሰጡት መግለጫም ከአሁን ቀደም ከአረብ ሃገራት ጋር ያልነበረው የሁለትዮሽ ስምምነት በቀጣይ መከወን እንዳለበት ገልጸውም ነበር ። ይህ መግለጫ በተነገረ ማግስት በቪዛው ንግድ ተሰማርተው ከገጠር እስከ ከተማ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ እህቶቻችን ለሳውዲ ” ገበያ” ያቀረቡት ባለ ኤጀንሲ ደላሎች ጅዳና ሪያድ መምጣት መጀመራቸው መረጃ ቢጤ አቅርቤም ነበር ። አሁን በውስጥ አዋቂዎች የሰማነው ተባለው ሁሉ እውን እየሆነ ፣ እውነቱ እየጠራ የሄደ ይመስላል !

ከዚህ ቀደም በሁለት ሃገራት መካከል ስምምነትና በቂ ዝግጅት ሳይደረግ በሳውዲ ብቻ ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጥ ዜጋ የህግ ሽፋን ህጋዊ ፈቃድ ባላቸው ኤጀንሲዎች በየገጠር ከተሞች ሳይቀር ተበትነዋል። ዛሬ በኮንትራት የመጡት ” ያሉበትን ይዞታ እንዲህ ነው” ብሎ መረጃ መስጠት ቀርቶ ፣ የትና በምን ሁኔታ እንደሚገኙ የሚያውቅ ኤጀንሲም ሆነ የመንግስት ተወካዮች የሉንም የምለው በእርግጠኝነት ነው ። በተደጋጋሚ ከሚደርሱኝ መረጃዎች መረዳት እንደ ቻልኩት በአሁኑ ሰዓት መግቢያ መውጫው ጠፍቶባቸው ፣ በደልን እያስረናገዱ የሚንገላቱት በርካታ እህቶች በየቤቱ እንዳሉ አውቃለሁ። በዚህ መሰሉ የተወሳሰበ ችግር ዜጎች እየተሰቃዩ ፣ መብታቸው የሚያስጠበቅ ስራ እየተሰራ በሌለበት ሁኔታ ሌላ እንባ ልናነባ የተቃረብን ይመስላል ! የኮንትራት ሰራተኞችን አበሳ ብዙ ነው፣ የሚሰራው ታስቦና ተጠንቶ ስላልሆነ ፣ መብታችን የሚያስጠበቅልን ስለጠፋ ተዋርደናል ። አሁን ድረስ በዚህ ዙሪያ ያገባናል ብለን ስንጽፍ ፣ ስንናገረው እንደ ተቃዋሚ እየታየንም ቢሆን ግፍ ሰቆቃና ስቃዩን ሊያሰለች በሚችል ስፋትና ጥልቀት ጽፈነዋል ፣ ተናግረናል! ሰሚ ግን የለም !

በህግ መመሪያ የተቀመጠው የመንግስት ዲፕላማቶች ቀዳሚ ስራ ባሉበት ሃገር የሚገኙ ህጋዊም ሆኑ ህገ ወጥ ዜጎችን ሰብአዊ መብት ረገጣ እንዳይደርስበቸው መከላከል ሰብዕናችን መርከስ ይዟልና ግፍ እየተፈጸብን ነው ፣ ላከል ነበር። የህገ ወጦችን ቀርቶ በከንትራት በሰራተኛና አሰሪ ስምምነት የመጡ ዜጎችን መብት ማስከበር አልቻሉም ! የቪዛ ውል ማስፈጸሚያ ገንዘብ እየሰበሰቡ ባጸደቁት የኮንትራት የስራ ውል ላይ የተጻፉት ስምምነቶች የዜጎች ይዞታ የመከታተልና የማስፈጸም ሃላፊነትን ሲወጡ አላየንም ! በዚህ ሁኔታ ረቂቁ ጸድቆና በተግባር ውሎ ዳግም እንዳናነባ ያሰጋል !

ግልድ መሆን ያለበት ነባራዊው እውነታ …

የረቂቁ ጉዳይ እንዳለ ይህም ከኢትዮጵያ መንግስት አስቀድሞ ከኢትዮጵየ የኮንትራት ሰራተኞች እንዳይመጡ ያገደው የሳውዲ መንግስት እገዳውን እስካሁን አላነሳም። በዚህ ላይ መንግስት ከአረብ ሃገራት በኩል እግዱ ተነስቶ ሰራተኞች እንዲያቀርብ ጥያቄ እየቀረበለት መሆኑን ደጋግመን ሰምተናል ። ከአረቦች በኩል ግን የምንሰማው ለየቅል ነው !

ይህ በእንዲህ እንዳለ ብዙዎቻችን የሚያሳስበን በማህበራዊና ሰራተኛ ሚኒስትር ለኤጀንሲዊች ውይይት የቀረበው ረቂቅ ህግ በሰራተኞች ይዞታና መብት ጥበቃ ዙሪያ የተነሳ ጉዳይ አለመኖሩ ነው ። በአድማስ ጋዜጣ ጋዜጣ ዘገባ በማህበራዊና ሰራተኛ ሚኒስትር በቀረበው ረቂቅ ኤጀንሲዎች መወያየታቸውን ሲያስረዳ ፍቃድ ለመውሰድ የተጣለባቸውን ከፍተኛ ገንዘብ የማስያዝ ፣ ሰለሰራተኞች እድሜ የትምህርት ደረጃ ገደበወ እና ሰራተኞችን በሚሄዱበት ሃገር ኢንባሲና ቆንሰል መ/ቤትበ 15 ቀን ውስጥ ከማሰመዝገብ ቅድመ ሁኔታ ያለፈ አለመወያየታቸውን የቀረበው ዘገባ ያስረዳል ።

በረቂቁ ላይ ሰራተኞች ቢያንስ እስከ ስምንተኛ ክፍል በላይ የሆኑት ብቻ እንደሚያካትት ከመጠቆሙ ባለፈ ሰራተኞች ማግኘት ስላለባቸው በቂ ስልጠናና ተዛማጅ ቅድመ ዝግጅት በቀረበው ረቂቅ ቀርቦ ለውይይት አለመደረጉ ያሳስባል። ከዚህ ቀደም ድህነትና የኑሮ ውድነቱን ተከትሎ በልጆቻቸው ህይወታቸውን ለመለወጥ የቋመጡ ወላጆች በደላሎች ቀቢጸ ተስፋ ተታልለውና የተሳሳተ የእድሜና የትምህርት መረጃና የመጓጓዣ ሰነድ አቅርበው ከሃገር እንዳይወጡ የተሰራውን ስራ የሚከላከል ዘዴ በረቂቁ አልቀረበም። አለም አቀፍ የሰራተኛ ህግንና ሰብአዊ መብት ማስከበሪያ ድንጋጌዎችን ባገናዘበ መልኩ ሰራተኞች ስለሚከፈላቸው ክፍያ ፣ ስለጤና ፣ ስለ እረፍት ሰአታቸው እና ስለመሳሰሉት መሰረታዊ የኮንትራት ሰራተኞች አንገብጋቢ ጥያቄዎች ስራ ውይይት ሳይደረግበት ስለኤጀንሲዎች ፈቃድ ማግኘት ቅድመ ሁኔታ ውይይት መቅረቡ ያሳስባል። በረቂቁ ውይይት ከ።ደረጉ አስቀድሞ ኤጀንሲዎች ከዚህ በፊት ስላቨጋገሯቸው ዜጎች ነባራዊ ሁኔታ ፣ አድራሻና ያሉበትን ሁኔታ በዝርዝር መረጃ ፣ በላኳቸው ሰራተኞች ላይ ለተፈመውና እየተፈጸመ ላለው በደል ተጠያቂው ሳይታወቅ ስለመጭው ፈቃድ አወጣጥ ከኤጀንሲዎች ጋር በረቂቁ ዙሪያና መስፈርት ዙሪያ መወያየቱ ጠቃሚ ነው አይመስለኝም።

በየኮንትራት ሰራተኞች ጉዳይ ሲነሳ በየአረብ ሃገራት ያሉትን ኢንባሲና ቆንስል መስሪያ ቤቶች ለዜጎች በሚሰጡት ያልተሟላ ግልጋሎትና ያልሰመረ የመብት ማስጠበቅ ይጠቀሳል። ይህ ለምን ሆነ ሲባሉ የሰራተኛና በበጀት እጥረት እንዳለባቸው አዘውትረው ይናገራሉ። በዚህ አሁን ድረስ ስለሚንከላወሱት የኢንባሲና የቆንስል መ/ቤቶች ረቂቁ ምን ይላል ? የሚለው እንዳለ ሆኖ በሃገር ቤት ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ዝግጅት ፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት በረቂቁ ውይይት አልተነሳም።

…እልፍ አእላፍ የኮንትራት ሰራተኞች አሁን ያሉበት ይዞታ በውል ሳይመረመርና ሳይታወቅ እየተንገዋለለ ባለበት ሁኔታ የተዘጋውን ለመክፈት ሂደት ግልጥልጥ አለማለት ያስፈራል። ከዚህ በፊት በኮንትራት የገቡት ጉዳይ ገለል አድርጎ ስለ አዲሱ ህግና መመሪያ እንነጋገር መባል ችግሩን ያገዝፈዋል እንጅ አይቀርፈውም ። ይፋ መውጣት የጀመረው ረቂቁ ህግና በዚህ ጫፍ ያለው ዝግጅት የተዳከመ አለያም የለም የሚባል አይነት መሆኑ አሁንም የዜጎችን አበሳ በቅርብ ለምንመለከተ ውን ዜጎች አሁንም ጉዳዩ ያሳስበናል። መፍትሄው በአረብ ሃገራት ያሉትን ዜጎች ጨምሮ የሁሉም ባለድርሻ አካላት በረቂቁ ህግ ተሳትፎ ሊያደርጉበት ይገባል። በፈለገው መንገድም ይሁን በረቂቁ ህግና መመሪያ ዙሪያ ግልጽና ጥልቅ ውይይት ካልተደረገ አሁንም ዳግም እንደምናነባ ልብ ያለው ልብ ይበል !

ጄሮ ያለው ይስማ !

ቸር ያሰማል !

ነቢዩ ሲራክ
ህዳር 24 ቀን 2007 ዓም

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 9 years ago on December 2, 2014
  • By:
  • Last Modified: December 2, 2014 @ 11:47 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar