www.maledatimes.com በከፍተኛ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት የሜቴክ ከፍተኛ ኃላፊዎች ተሳትፈውበታል የተባለው ድርጊት ተለይቶ ቀረበ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Addis Admas  >  Current Article

በከፍተኛ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት የሜቴክ ከፍተኛ ኃላፊዎች ተሳትፈውበታል የተባለው ድርጊት ተለይቶ ቀረበ

By   /   December 2, 2018  /   Comments Off on በከፍተኛ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት የሜቴክ ከፍተኛ ኃላፊዎች ተሳትፈውበታል የተባለው ድርጊት ተለይቶ ቀረበ

    Print       Email
0 0
Read Time:3 Minute, 51 Second

ታምሩ ጽጌ

‹‹በቀጥታ የሚመለከተንና የሚያስጠረጥረን ማስረጃ አልቀረበብንም››

ተጠርጣሪዎች

‹‹ለመጠርጠር የሚያስችሉ መረጃዎች እንዳሉ ችሎቱ ተመልክቷል››

ፍርድ ቤት

ላለፉት 24 ቀናት ታስረው የሚገኙትና በከፍተኛ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ ተሳትፈውበታል የተባለው የሙስና ወንጀል ድርጊት ተለይቶ ቀረበ፡፡

በብርጋዴር ጄኔራል ጠና ቁሩንዲ የምርመራ መዝገብ የተካተቱት 26 ግለሰቦች፣ የተጠረጠሩበትን የሙስና ወንጀል የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን የጊዜ ቀጠሮውን እያየው ለሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አሥረኛ ወንጀል ችሎት እንዳስረዳው፣ ተጠርጣሪዎቹ በ14 የወንጀል ድርጊቶች ተሳትፈዋል፡፡ በመንግሥት ላይ ከፍተኛ የሆነ ጉዳትም አድርሰዋል ብሏል፡፡

ብርጋዴር ጄኔራል ጠናን ጨምሮ ስምንት ተጠርጣሪዎች ከመርከብ ግዥ ጋር በተገናኘ፣ ኮሎኔል ዙፋን በርሔ ከልብስ ንፅህና አገልግሎት መስጫ ማሽን ግዥ ጋር በተገናኘ፣ እንዲሁም ሻለቃ ይርጋ አብርሃ ያላግባብ ብድር እንዲሰጥና ስፖንሰር በመፍቀድ መሳተፋቸውን ገልጿል፡፡ ከሃያ ባለሁለት ጋቢና ፒክአፕ ተሽከርካሪዎችና ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ቁርጥራጭ ብረቶች በከፍተኛ ዋጋ እንዲገዙ በማድረግ ሙስና በመፈጸም የተጠረጠሩት ደግሞ ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውና ኮሎኔል ግርማይ ታረቀኝ መሆናቸውንም መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡ ከሪቬራ ሆቴልና ፕላስቲክ ፋብሪካ፣ እንዲሁም ከኢምፔሪያል ሆቴል ግዥ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩት ደግሞ ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው፣ ኮሎኔል በርሔ በየነ፣ ሌተና ኮሎኔል ሸጋው ሙሉጌታና አቶ ዓለም ፍፁም ናቸው፡፡

ሌሎቹም ተጠርጣሪዎች ከአዳዲስና ያገለገሉ ክሬኖች ግዥ ጋር በተገናኘ፣ ከኮንስትራክሽን ማሽኖች ግዥ፣ ከአውሮፕላኖች ግዥ፣ ከኃይል ማመንጫ ግዥ፣ ከያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ፣ ከነዳጅ ማጣሪያ ማሽን ግዥና ከተለያዩ ተሽከርካሪዎች ግዥ ጋር በተገናኘ፣ የእያንዳንዳቸው ተሳትፎ ስለነበረበት መጠርጠራቸውን መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ከላይ ተከፋፍሎ የቀረበውን ግዥ፣ ከግዥ መመርያ ውጪ ዓለም አቀፍ የጨረታ ውድድር ሳይደረግ በመፈጸም መንግሥት ከጨረታ ውድድር ሊያገኝ የሚገባውን ጥቅም እንዲያጣ ማድረጋቸውን መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ መንግሥትና ሕዝብ የሰጣቸውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው፣ ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም ለትልልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ የሚውለውን የሕዝብ ገንዘብ ከዓላማ ውጪ በማዋል፣ 37 ቢሊዮን ብር እንዲመዘበር ማድረጋቸውን መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን በተሰጠው 14 ቀናት ውስጥ የአገር ውስጥና የውጭ ግዥዎች ያለ ጨረታ መፈጸማቸውን የሚያስረዱ ሰነዶች፣ ከግዥ ጋር በተገናኘ ከከፍተኛ ኃላፊዎቹ የተላለፈ የውሳኔ ሰነድ፣ የተለያዩ ሰነዶችን በቢሮአቸው፣ እንዲሁም በብርበራ ከመኖሪያ ቤታቸው የተገኙ ሰነዶችን መሰብሰቡን፣ የ31 ምስክሮችን ቃል መቀበሉንና በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 27(2) መሠረት የሦስት ተጠርጣሪዎች ቃል መቀበሉን አስረድቷል፡፡

መርማሪ ቡድኑ የኦዲት ሪፖርት መሰብሰብ፣ በመንግሥትና በሕዝብ ላይ የደረሰውን ጉዳት መጠን በልዩ ባለሙያ ማስገመት፣ ለብልሽት የተዳረጉ በሜቴክ መጋዘን ተከማችተው የሚገኙ ንብረቶችን በባለሙያ ማስቆጠርና የደረሰውን ጉዳት ማስላት፣ ከተለያዩ ተቋማት የጠየቀውን ማስረጃ መሰብሰብ፣ ለፎረንሲክ ምርመራ መስጠት፣ በተለያዩ ቋንቋዎች የተጻፉ ሰነዶችን ማስተርጎምና የቀሪ ተጠርጣሪዎችን ቃል መቀበል እንደሚቀረው ገልጿል፡፡ በመሆኑም ለተጨማሪ የምርመራ ሥራ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

በቀጥታ እነሱን የሚመለከትና ሊያስጠረጥራቸው የሚችል ማስረጃ እንዳልቀረበባቸው በመናገር ክርክራቸውን የጀመሩት ተጠርጣሪዎቹ፣ በመንግሥትም ላይም ሆነ በሕዝብ ላይ ያደረሱት ጉዳት እንደሌለ አስረድተዋል፡፡ ከሦስት ተጠርጣሪዎች በስተቀር ሁሉም ተጠርጣሪዎች በምን እንደተጠረጠሩ ከአሥር ቀናት በላይ ታስረው ሲቆዩ አለማወቃቸውንና ገና መስማታቸው መሆኑን ኅዳር 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል፡፡ ቃላቸውንም መርማሪ ቡድኑ እንዳልተቀበላቸው ተናግረው፣ ይኼ የሚያሳየው ደግሞ ምንም ዓይነት የወንጀል ተሳትፎም ሆነ የሙስና ጥርጣሬ ስላልተገኘባቸው በመሆኑ፣ መዝገቡ ተዘግቶ ወይም የዋስ መብታቸው ተጠብቆ ከእስር እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡

አንዳንዶቹ ልጆቻቸውን የሚንከባከቡትና የሚያስተዳድሩት እነሱ መሆናቸውን፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ሕመምተኛ በመሆናቸው ሐኪም እየተከታተላቸው የሚኖሩ ከመሆናቸው አንፃር፣ ፍርድ ቤቱ ዋስትናቸውን እንዲጠብቅላቸው ደጋግመው ጠይቀዋል፡፡ አንዳንዶቹ ተጠርጣሪዎች ደግሞ ተቋሙን ከለቀቁ ከአምስት ዓመታት በላይ እንደሆናቸውና እንኳን ሌላ ነገር ሊጀምሩ ቀርቶ አብረዋቸው ይሠሩ የነበሩት ጓደኞቻቸውንም ካገኟቸው ዓመታት እንዳለፋቸው አስረድተዋል፡፡ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ጠበቃ አቁመው የተከራከሩ ሲሆን፣ የተወሰኑት ደግሞ የወር ደመወዝተኛና በጡረታ የሚተዳደሩ መሆናቸውን በማስረዳት መንግሥት ጠበቃ እንዲያቆምላቸው ጠይቀዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ባቀረቡት መከራከሪያ ነጥብና ዋስትናን በሚመለከት ምላሽ የሰጠው መርማሪ ቡድኑ፣ ተጠርጣሪዎቹ ዋስትና ቢፈቀድላቸው ያላቸውን ተሰሚነት በመጠቀም ሰነድ ሊያሸሹ፣ ምስክር ሊያባብሉ፣ ሊያስፈራሩና ከአገር ሊወጡ ስለሚችሉ እንደሚቃወም በመግለጽ ውድቅ እንዲደረግለት ጠይቋል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር ሲሳማ የቆየው ፍርድ ቤቱ እንደገለጸው፣ ተጠርጣሪዎች ሊጠረጠሩበት የሚያስችል ማስረጃ በመርማሪ ቡድኑ እንዳልቀረበባቸው ቢናገሩም፣ የምርመራ መዝገቡ ግን ሊያስጠረጥራቸው የሚችል መረጃ መያዙን ገልጿል፡፡

ፍርድ ቤቱ 17 የምርመራ መዝገቦችን አስቀርቦ ማየቱን ጠቁሞ፣ እያንዳንዱ መዝገብ ከ50 ገጽ በላይ እንዳለውና ምርመራውም የተጀመረው ተጠርጣሪዎች ከመያዛቸው አስቀድሞ ከሐምሌ 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ይኼ የሚያሳየው ምርመራው ሕጋዊ ሒደትን ተከትሎ እየተከናወነ መሆኑን እንጂ፣ ምርመራው መጠናቀቁን እንዳልሆነም አክሏል፡፡ ጠበቃ ለማቆም አቅም እንደሌላቸው የገለጹት ተጠርጣሪዎች ቃለ መሃላ ፈጽመው በማረጋገጣቸው፣ የተከላካይ ጠበቃ ጽሕፈት ቤት ተከላካይ ጠበቃ እንዲመደብላቸው ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ መርማሪ ቡድኑ በቀጣይ የምርመራ ጊዜያት በእያንዳንዱ ተጠርጣሪ ላይ የሠራውን ምርመራ በዝርዝር እንዲያቀርብ በመንገር፣ የጠየቀውን 14 ቀናት መፍቀዱን በመግለጽና የተጠርጣሪዎቹን ክርክር ውድቅ አድርጎ ለታኅሳስ 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ለፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ሌላው ፍርድ ቤቱ ሰጥቶት የነበረው፣ ትዕዛዝ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሐሺም ቶፊቅ (ዶ/ር)  በማሸሽና የጦር መሣሪያ በመደበቅ ተጠርጥረው የታሰሩትን ባለቤታቸውን ወ/ሮ ዊዳን መሐመድና አቶ ሰሚር መህመድን በሚመለከት ማብራሪያ እንዲሰጥ ነበር፡፡ መርማሪ ቡድኑ ቀደም ብሎ ካብራራው በተጨማሪ፣ በአቶ ሰሚር ላይ በተጨማሪ ሊያብራራ ባለመቻሉ በ30 ሺሕ ብር ዋስ እንዲለቀቁ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ወ/ሮ ዊዳንን በሚመለከት በስማቸው ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ማከማቸታቸውን፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ 10 ሺሕ ብር የሚከራይ ቤት መኖሩንና በሐሺም ቶፊቅ (ዶ/ር) ስም አንድ አውቶሞቢል መገኘቱን ጠቁሞ፣ ተጨማሪ ሀብት መኖሩን የሚያጠና ቡድን መቋቋሙን ተናግሯል፡፡ በዋስ ቢለቀቁ ሰነዶች ሊያበላሹበትና ከአገርም ሊወጡ እንደሚችሉ በማስረዳት ዋስትናውን ተቃውሟል፡፡ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር አዳምጦ ከተጠየቀው 14 ቀናት ውስጥ ሰባት ቀናት በመፍቀድ፣ ለኅዳር 26 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

♦ “ ትክክለኛ ፍትሕ አይሰጡም” የተባሉት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ከችሎት እንዲነሱ ተጠየቀ !

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar