www.maledatimes.com “የሠራዊቱ ሁኔታ ከፍተኛ የህሊና መረበሽ ውስጥ ከቶኛል” - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Addis Admas  >  Current Article

“የሠራዊቱ ሁኔታ ከፍተኛ የህሊና መረበሽ ውስጥ ከቶኛል”

By   /   March 20, 2019  /   Comments Off on “የሠራዊቱ ሁኔታ ከፍተኛ የህሊና መረበሽ ውስጥ ከቶኛል”

    Print       Email
0 0
Read Time:6 Minute, 54 Second

አቶ ነአምን ዘለቀ ለቢቢሲ

ላለፉት 26 ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ ሲያደርጉ የቆዩት የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ከፍተኛ አመራርና ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ነአምን ዘለቀ ከፓርቲ መልቀቃቸውን ተከትሎ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ቢቢሲ፡ የአርበኞች ግንቦት 7 የሠራዊ አባላት አሁን ያሉበት ሁኔታ ትንሽ ያስጨነቀዎት ይመስላል። ግን ደግሞ ለመልቀቅ ከወሰኑ ቆይተዋል፤ እርስዎም በጽሑፍዎ እንደጠቀሱት። እና ዝም ብሎ ከመውጣት፣ መልቀቅዎን ከአንድ ጉዳይ ጋ ሆን ብለው ለማያያዝ የሞከሩ ይመስላል።

አቶ ነአምን፡ (ዘለግ ካለ ሳቅ በኋላ ) ምን እላለሁ እንግዲህ። አንተ የመሰልህን (ማሰብ ትችላለህ). . .። መጀመሪያ (ከጽሑፌ) አንተ ይሄን ብቻ ነጥለህ ለምን እንዳወጣኽው አላወቅኩም። እዚያ ላይ ሠራዊቱን በሚመለከት የተደረገው ጥረት በዝርዝር ተቀምጧል። እስካሁን ድረስ እነኚህ የሠራዊት አባላት በከፍተኛ ችግር ላይ ነው ያሉት፤ ላለፉት ሰባት ወራት።

መንግሥት የእነርሱን ጉዳይ በተደረገው ስምምነት መሠረት (ማለትም) ቶሎ በሁለትና በሦስት ወር ውስጥ መልሰው ይቋቋማሉ፣ ድጎማ ይሰጣቸዋል አለ፤ የጀርመን መንግሥት ገንዘብ ለመስጠት ቃል ገባ፤ ነገር ግን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት የተቋቋመው ቢሮ ምንም አቅም ስላልነበረው እስካሁን ድረስ ሲጓተት ቆይቶ አሁን ገና ወደ ኮሚሽን ጉዳዩ ተመርቶ ያው ኮሚሽኑ ኃላፊነት ተሰጥቶት በብሔራዊ አደጋ መከላከል ኮሚሽን በኩል የእነርሱ ጉዳይ እንዲካሄድ ነው እየተደረገ ያለው።

ቢቢሲ፡ ለመሆኑ የሠራዊቱን አባላት በአካል አግኝተዋቸዋል?

አቶ ነአምን፡ የዛሬ ሁለት ወር ወረታ ካምፕ ሄጄ አይቻቸው፤ ችግራቸውን መርምሬ ለሥራ አስፈጻሚውም ሪፖርት ያደረግኩበት ሁኔታ ነው ያለው።

ቢቢሲ፡ሁሉም ወረታ ካምፕ ነው ያሉት?

አቶ ነአምን፡ ሁሉም አይደሉም። ግማሾቹ እዚያ ናቸው፤ ግማሾቹ የመልሶ ማቋቋሚያ እርዳታ ታገኛላችሁ ተብለው ከካምፑ ውጪ ናቸው። ከካምፑ ውጪ ያሉት በሺህ የሚቆጠሩ ናቸው። በተለይ ደግሞ በጣም የተቸገሩት ከኤርትራ በረሃ የመጡት ናቸው። በመቶዎች የሚቆጠሩ ናቸው፤ ካምፕ ውስጥ ያሉት ደግሞ ወደ 150 የሚጠጉ ናቸው።

ቢቢሲ፡ እና ለመልቀቅ ያበቃዎ ምኑ ነው?

አቶ ነአምን፡ እነዚህ ልጆች፤ እነዚህ የሠራዊት አባላት፤ የአርበኞች ግንቦት 7 ሠራዊት አባላት፤ ከኤርትራ የተመለሱትን ወሮታ ሄጄ አነጋግሬያለው። ችግራቸውን ተገንዝቤያለሁ። በአፋጣኝ መፍትሄ እንደሚያገኙ በሁለት ወር ውስጥ ቃል ገብቼ ነው ጥር ላይ የተመለስኩት። አቶ አንዳርጋቸውም ይህንኑ አድርጓል። ያ ሁለት ወር አለቀ።

እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት እርዳታ አላገኙም። እንዳልኩት ገና የዛሬ ሳምንት ኃላፊነት የተሰጠው ኮሚሽን አለ፤ በዚያ ኮሚሽን በኩል ይሄ በመንግሥት በኩል ቃል የተገባው የመልሶ የማቋቋም እርዳታ ተግባራዊ ይሆናል የሚል ግምት አለን። ግን ጉዳዩ ካልተፋጠነ ደግሞ ትልቅ አደጋ አለው።

እነሱ እራሳቸው በሁለት በሦስት ሳምንት ውስጥ እርዳታ ካላገኙ ወደ ሚዲያ እንደሚሄዱ፤ ሌላም እርምጃ እንደሚወስዱ የተናገሩበት ሁኔታ ነው ያለው።

በአንጻሩ የሌላ ድርጅቶች፤ የብሔር ድርጅቶች፤ በአማራ በኦሮሞ የተደራጁ ደግሞ በየክልላዊ መንግሥቱና ጸጥታ ኃይል ውስጥ እንዲካተቱ ተደርገዋል።…ይሄን እያዩ…

ቢቢሲ፡ ላቋርጥዎት አቶ ነአምን፤ እሱን እንመለስበታል። አሁን የእርስዎ መልቀቅ እንዴት ነው ይህን ነገር ወደፊት የሚያራምደው? የጀርመን እርዳታ የእርስዎን መልቀቅ ተከትሎ አይመጣ? የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት እርስዎ ስለለቀቁ ተደናግጦ እርዳታውን አይቀጥል? በእርስዎ መልቀቅ የሚመጣ ለውጥ ይኖራል ብለው ነው?

አቶ ነአምን፡ የእነሱ መቸገር፣ የእነሱ ለከባድ ማኅበራዊ ችግር መዳረግ፣ በቀን ሥራ ከዚያም ውጪ በረሃብና በጉስቁልና ሕይወታቸውን እንዲገፉ መደረግ፤ የእኔ መልቀቅ የበለጠ አሁን የተወሰነውን ውሳኔ እንዲያፋጥነውና ትኩረት እንዲያገኝ ያደርጋል ብዬ እገምታለው።

ቢቢሲ፡ ውስጥ ሆነው ቢታገሉ አይቀልም ነበር ግን?

አቶ ነአምን፡ ይሄ እኮ የትግል ጉዳይ አይደለም። እኔ ጽሑፌ ላይ እንደገለጽኩት የንቅናቄው አመራር፤ ዶክተር ብርሃኑ፤ ዋና ጸሐፊው ጥረት አድርገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩንም በተለያየ ደረጃ ያሉት ሰዎችንም አነጋግረዋል፤ ግፊት አድርገዋል። አንዴ አይደለም ብዙ ጊዜ።

ጉዳዩ ከሚገባው በላይ ተጓቶ አንድ ውሳኔ የመስጠት አቅም ያለው ጽህፈት ቤት ማቋቋም ስላልተቻለ፤ ጀርመኖቹም ቃል ከገቡ በኋላ ድጋፉን ያልሰጡበት ምክንያት አምባሳደሩን ስናነጋግር ይሄ የተቋቋመው ጽሕፈት ቤት አቅም የለውም። ፕሮጀክትና ፕሮግራሞችን ቀርጾ ማሠራት የሚችል የሰው ኃይል የለውም ብለው እኮ በግልጽ ነግረውናል።

ምንድነው ለማድረግ የሞከርነው? ይሄ ጽሕፈት ቤት አቅም ከሌለው ወይ ለሌላ ስጡት። ወይ ደግሞ ይሄንንን የመልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት በአግባቡ ፕሮግራምና ፕሮጀክት የሚቀርጹ ባለሙያዎች ይመደቡ። አንድ ግለሰብና አንድ ጸሐፊ ብቻ ነው እዚያ ያሉት ብለን እኮ ብዙ ጊዜ ተናግረናል።

ይሄ ጉዳይ ስላልተፈጸመና ስለተጓተተ ነው እዚህ ደረጃ የደረስኩት። ነገሩ ገና የዛሬ ሳምንት ውሳኔ አግኝቷል። ያ ደግሞ ምን ያክል ተግባራዊ እንደሚሆን እናያለን።

በዚህ ሁሉ ሂደት እኛ (ለሠራዊታችን) ቃል የገባነው ጊዜ አልቋል። ያ ሁለት ወር ከማብቃቱ በፊት ለሠራዊቱ ቃል የገባነው፤ እንደውም ሁለት ወይም ሦስት ወር ነው ከኤርትራ ከገቡ በኋላ፤ አሁን ስምንተኛ ወር ሊመጣ ነው። ያ ከሆነ በኋላ ነው በዚህ ጉዳይ ላይ ጫና ለመፍጠር፣ ትኩረት እንዲያገኝ ለማድረግ ብዬ የለቀቅኩት።

ቢቢሲ፡ እርስዎ በመልቀቅዎ የሠራዊቱ አባላት የተሻለ ድምጽ የተሻለ መሰማት ያገኛሉ ብለው የምር ያምናሉ ማለት ነው?

አቶ ነአምን፡ እኔ መጀመሪያውኑም እለቃለሁ ብዬ ደብዳቤው ላይ በዝርዝር አስቀምጫለሁ። እኔ በፖለቲካ ድርጅት አባልነት አልቀጥልም። የእኔ ኃላፊነት ከፖለቲካ ድርጅት አመራርነት ወይም አባልነት ነው የሚያበቃው፤ በኢትዮጵያና በሃገር በሕዝብ ጉዳይ ላይ ተሳትፎዬ በተለያየ መንገድ ይቀጥላል።

እስካሁን ድረስ 26 ዓመት ያልተቋረጠ ትግል አድርጌያለው፤ ብዙ አስተዋጽኦ አድርጌያለው፤ ከሚጠበቅብኝ በላይ። ለኢትዮጵያ ሕዝብ አሁንም የሚጠቅሙ፣ የሚበጁ፣ ለሀገር ደኅንነት፣ ለሰላም፣ ለዴሞክራሲ፣ ለፍትህ ለሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ እንደግለሰብ፣ እንደዜጋ አስተዋጸኦ አደርጋለሁ።

ግን በኃላፊነት ላይ ተቀምጬ እንዲህ ዓይነት በጣም ህሊና የሚቆጠቁጥና እንቅልፍ የሚነሳ ሁኔታ ውስጥ እራሴን ማግኘት አልፈልግም። አንተ በእኔ ቦታ ብትሆን ከዚያ ከሚመጣው ጭንቀት፣ መከራና ስቃይ፤ ልመናና ተማጽኖ ብትሰማ ታዝናለህ።

ቢቢሲ፡ አሁንም ያልተመለሰልኝ ጥያቄ፣ አልታይህ ያለኝ ነገር ሠራዊቱን ከእርስዎ መልቀቅ ጋ ያያዙበት ገመድ ነው?

አቶ ነአምን፡ ምክንያቱንና ውጤቱን አታመሰቃቅለው። እኔ ያልኩት መጀመሪያ ቀደም ሲል ለውጡ ከመጣ በኋላ ተናግሬያለሁ፤ እኔ አልቀጥልም። የቆየሁበት ምክንያት አቶ አንዳርጋቸውም ሌሎቹም እንድቆይ ስለጠየቁኝ ነው።

በዚህ በቆየሁበት ጊዜ ዋናው ማሳካት የፈለግኩት የሠራዊቱ ሰላማዊ ሕይወት እንዲቋቋም ያንን መስመር ማስያዝ ነው። በዚያም መሠረት ብዙ እንቅስቃሴ ተደርጓል። አቶ አንዳርጋቸውም አድርጓል፤ ዶክተር ብርሃኑም አድርጓል፟፤ እኔም አድርጌያለሁ።

ግን በፈለግነው ፍጥነት አልሄደም። በዚህ መካከል ሠራዊቱ ከፍተኛ የማኅበራዊ ችግር ውስጥ ነው ገባ። ከካምፕ ውጪ ያሉትም፤ ካምፕ ውስጥ ያሉትም ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ናቸው። እኛ ደግሞ ቃል ገብተናል፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ብለን። ያ ጊዜ ደግሞ አለቀ።

አሁንም ሥራው ገና አልተጀመረም፤ በዚህ መካከል ከፍተኛ ችግር አለ። በየቀኑ አዲስ አበባ ሆኜ ስልኮች ይመጣሉ፣ ሰዎች ይመጣሉ፤ ብዙ ነገር ነው የምሰማው። ይሄ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የህሊና መረበሽ ነው በእኔ ላይ ያመጣው።

ቢቢሲ፡ ከእንግዲህ በፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ ምንም ተሳትፎ ማድረግ አይፈልጉም። የመጨረሻዎ ነው ይሄ?

አቶ ነአምን፡ አዎ! እኔ ለዚህ ትግል ሁሉ ነገሬን ሰጥቼ ስለነበር የቤተሰቤንም፣ የራሴንም የድርጅቴንም ሁሉ ነገሬን ነበር የሰጠሁት። አሁን ራሴ ላይ ማተኮሪያ ጊዜ ነው።

ግን የኢትዯጵያ ጉዳይ፣ የዲሞክራሲ ጉዳይ፣ እኔ የማምንባቸው መርሆች፣ አገሬ ውስጥ እንዲኖሩ የምፈልጋቸው በጎ ነገሮች ውስጥ አስተዋጽኦዬን እንደ አንድ ዜጋ እቀጥላለሁ። ነገር ግን ፓርቲ ውስጥ ወደፊት እሳተፋለሁ አልሳተፍም የሚለውን አሁን የምናገረው አይደለም።

ቢቢሲ፡ ችግር ውስጥ ናቸው የሚሏቸው የሠራዊቱ አባላት እርስዎ ጥለዋቸው ወደ ግል ሕይወትዎ ሊያተኩሩ እንደወሰኑ ሲሰሙ የሚያዝኑብዎ አይመስልዎትም?

አቶ ነአምን፡ እነሱም እኮ ብዙዎቹ ወደ ግል ኑሯቸው (እንዲመለሱ)፣ ሕይወታቸው እንዲስተካከል ነው ጥረቱ። አሁን እኮ የትጥቅ ትግሉ አልቋል። አሁን የሚደረው ትግል ፖለቲካዊ ትግል ነው። በተለያዩ መንገዶች ለውጡን የማስቀጠል ነው ትግሉ። ይህ ደግሞ በአንድ ድርጅት የሚሳካ አይደለም።

ቢቢሲ፡ ለሠራዊቱ ቃል የተገቡ ነገሮች ምን ምን ነበሩ?

አቶ ነአምን፡ በቅድሚያ ኤርትራ ጉባኤ ተደረገ። ሠራዊቱ አገር ወስጥ እንደሚገባ፣ ከዚያ ደግሞ በሁለት በሦስት ወራት ወስጥ መልሶ እንደሚቋቋም፣ ድጎማ፣ ድጋፍና ስልጠና ተሰጥቶት ሁሉም ሰላማዊ ኑሮ የሚገፋበትን ሁኔታ እንደምናመቻች ነበር ቃል የተግባባነው። ይህን ደግሞ ከጠቅላይ ሚኒሰትሩ ጋር ዋሺንግተን ውስጥ ተነጋግረንበት ነበር። እኛም አስተዋጽኦ እንድናደርግ ተስማምተን ነበር።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ብዙ የተደረገ ጥረት ነበር፤ ይህ የሚካድ አይደለም። ነገር ግን ሄዶ ሄዶ ሁለት ሦስት ወር ወስጥ ትቋቋማላችሁ የተባለው ቃል ሊከበር አልቻለም። ከዚያም አልፎ የዛሬ ሁለት ወር ገደማ እኔ ራሴ ካምፕ ሄጄ አነጋግሪያቸው ሁለት ወር ጊዜ ስጡን ነው ያልናቸው። ያ ሁለት ወር አለፈ።

ቢቢሲ፡ ሠራዊታችሁን በቁጥር ማስቀመጥ ይቻል ይሆን?

Image may contain: 1 person, suit

አቶ ነአምን፡ ቁርጥ ያለ አኀዝ ባልሰጥህም አሁን አገር ውስጥ ካሉ ከተለያዩ በረሃዎች የገቡት ከ2ሺህ በላይ ናቸው። ከኤርትራ በረሃ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ናቸው።

ቢቢሲ፡ ስለዚህ እያወራን ያለነው ከ3ሺ ስለማይበልጥ ሠራዊት ነው?

አቶ ነአምን፡ አዎ።

ቢቢሲ፡ መልቀቂያዎ ተቀባይነት አግኝቷል?

አቶ ነአምን፡ ቀደም ብዬ ለሥራ አስፈጻሚው መልቀቂያዬን አቅርቢያለሁ፤ ከዚያ ለሕዝብ ይፋ አድርጊያለሁ።

ቢቢሲ፡ ተቀባይነት አግኝቷል ግን?

አቶ ነአምን፡ በርግጥ ይሄ የእኔ ውሳኔ ነው። ነገር ግን ሊቀመንበሩ እስከ ጉባኤ እንድቆይ ጠይቆኛል። የራሴን ምክንያት ሰጥቻለሁ። ይሄ ጉዳይ ጉባኤም ለማድረግ የማንችልበት ደረጃ ይደርሳል። ስለዚህ ይህ ጉዳይ ወደ ሕዝብ መሄድ አለበት። አንዳርጋቸውም ብርሃኑም በዚህ ላይ ብዙ ሠርተዋል፤ ግን በተጨባጭ እስካሁን የተወሰደ እርምጃ የለም።

ይሄ ጉዳይ የሚያስፈልገውን ትኩረት አግኝቶ በሁለት ሦስት ሳምንት ውስጥ ሠራዊቱ መረዳት ካልተጀመረ የሚፈጠረውን ለፓርቲም ሆነ ለጉባኤው አስቸጋሪ ይሆናል። እንዲውም ታገሱን እያልን ነው እንጂ ወደ ሚዲያም መውጣት ይፈልጋሉ።

ቢቢሲ፡ ቅድም አቋረጥኮት እንጂ “ሌሎች ከትጥቅ ትግል የተመለሱ ብሔር ተኮር ድርጅቶች ቃል የተገባላቸው ሲፈጸምላቸው፣ የእኛ ተዘነጉ” ሲሉኝ ነበር ልበል?

አቶ ነአምን፡ ሆን ተብሎ ይሁን ሳይታወቅ፤ ብቻ ምንድነው ስሜቱ፣ ወሮታ ካሉ የሠራዊት አባላት ጋር ባደረግነው ውይይት የተረዳነው፤ በብሔር የተደራጁ ኃይሎች በአማራም በኦሮሞም ከኤርትራም የገቡትም አገር ውስጥም የነበሩት በጸጥታም በአስተዳደርም ከአመራር እስከ አባላት ተገቢ በሆነ ሁኔታ እንዲካተቱ አድርገዋል።

እኛ ግን ለኢትዮጵያ ብለው የታገሉ፣ ኅብረ ብሔር የፖለቲካ ዓላማን አንግበው የታገሉ፣ ለአንድ ብሔር ሳይሆን በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ብለው የታገሉ፣ ልክ አባት እናት እንደሌለው (ኦርፋን እንደመሆን) ነው የተሰማቸው። ይሄ ደሞ ጥሩ አይደለም።

አሁን ባለው አክራሪ ብሔርተኝነት ለኢትዮጵያ መቆም እንደ ነውር እንዲታይ የሚያደርግ ነው። ያኔ ሳናግራቸው እንደዚህ ዓይነት ድርጅቶች፣ የብሔር ድርጅቶች (ስም መጥቀስ አልፈልግም) የእነሱ ታጋዮችም አመራሮችም እንደዚህ ሆነዋል። ‘እኛ ለኢትዮጵያ ብለን ሕይወታችንን ለመስጠት በረሃ በወረድን ለምን ተጣልን’ የሚል ስሜት ነው ያላቸው፣ የሠራዊቱ አባላት።

ቢቢሲ፡ አቶ ነአምን፣ ከአመራሩ ጋር መጠነኛም ቢሆን ቁርሾ ወይ መቃቃር ውስጥ ገብተዋል እንዴ?

አቶ ነአምን፡ አንዳንዶች የእኔን መልቀቅ በሌላ እየተረጎሙ እየጻፉ ነው። እኛ በጣም ወፍራም መተማመን ያለን ነን። ብንጋጭም ለዓላማችን ለዓመታት አብረን በጋራ ሠርተናል።

ሁልጊዜ በድርጅት ውስጥ ችግር ይኖራል። ነገር ግን በዋናው በኢትዯጵያ ጉዳይ ላይ ተማምነን ተከባብረን ነው የሠራነው። ዛሬ ለምሳሌ ከአንዳርጋቸውም ከብርሃኑም ጋር በጽሑፍ ተነጋግረናል። ምንም ዓይነት ቅራኔ የለም፤ ይህን ላረጋግጠልህ እወዳለሁ።

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

♦ “ ትክክለኛ ፍትሕ አይሰጡም” የተባሉት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ከችሎት እንዲነሱ ተጠየቀ !

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar