www.maledatimes.com ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ከአውሮፓ ህብረት የ13ሚ. ብር ድጋፍ አገኙ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ከአውሮፓ ህብረት የ13ሚ. ብር ድጋፍ አገኙ

By   /   March 20, 2014  /   Comments Off on ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ከአውሮፓ ህብረት የ13ሚ. ብር ድጋፍ አገኙ

    Print       Email
0 0
Read Time:10 Minute, 42 Second

ያሬድ ዘለቀ Lamb ለሚለው ፊልሙ 12ሚ. ብር አግኝቷል
የኃይሌ ገሪማ “የጡት ልጅ” ቀረፃ  በሰኔ ወር ይጀመራል
የሁለቱም ፊልሞች ቀረፃ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ  ከአውሮፓ ህብረት የ13ሚ. ብር ድጋፍ አገኙ

ታዋቂው ኢትዮጵያዊ የፊልም ፕሮዱዩሰርና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ሃይሌ ገሪማ፤ “የጡት ልጅ” በሚል ርዕስ ለሚሰሩት አዲሱ ፊልማቸው የሚውል የ500 ሺህ ዩሮ (13ሚ. ብር ገደማ)  ድጋፍ ከአውሮፓ ህብረት አፍሪካን ካረቢያን ፓሲፊክ ፈንድ ያገኙ ሲሆን በፈረንሳይ የሚኖረው የፊልም ባለሙያ ያሬድ ዘለቀም Lamb ለሚለው ፊልሙ  መሥሪያ የ495 ዩሮ (12ሚ. ብር ገደማ) ድጋፍ አግኝቷል፡፡
ሳንኮፋ፣ አድዋ እና ጤዛ በተሰኙት ፊልሞቻቸው በአለማቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተደናቂነትን የተጎናፀፉትና በርካታ ሽልማቶችን የወሰዱት ፕሮፌሰር ሃይሌ ገሪማ፤ በቀደምት ኢትዮጵያውያን አኗኗር ላይ የሚያተኩረውን “የጡት ልጅ” የተሰኘ አዲስ ፊቸር ፊልማቸውን ለመስራት የሚያስፈልጋቸውን የገንዘብ ድጋፍ የአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ፣ የካሪቢያንና የፓስፊክ ሀገራትን የፊልም ኢንዱስትሪ ለማሳደግ ከምደባው ገንዘብ ማግኘታቸውን የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ደልጌሽን የፕሬስና ኢንፎርሜሽን ኦፊሰር አቶ ሰለሞን ከበደ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡
በለጋ ዕድሜዋ በፊውዳል ባላባቶች ቤት በባርነት ማገልገል በጀመረች አንዲት ልጃገረድ ታሪክ ዙሪያ የሚያጠነጥነውና ቀረጻው በመጪው ሰኔ ወር  በባህር ዳር እና በጎንደር ከተሞች የሚጀመረውን ፊልም ሰርቶ ለማጠናቀቅ፣አንድ ዓመት ከስምንት ወር  እንደሚፈጅ ታውቋል፡፡
ተቀማጭነቱን በጀርመን ያደረገውና “ፊልም ፎርም ኮሎኝ ጂኤምቢኤች” የተባለው የፕሮፌሰር ሃይሌ ገሪማ የፊልም ኩባንያ፤ ከአውሮፓ ህብረት ያገኘውን የ500 ሺህ ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ በኢትዮጵያ ከሚገኘው “ነጎድጓድ” የተሰኘ የፊልም ድርጅትና ከሃይቲው ቬልቬት ፊልም ግሩፕ ጋር በአጋርነት ለሚሰራው ለዚህ የፊልም ፕሮጀክት እንደሚያውለው ተጠቁሟል፡፡
ከአቶ ሰለሞን ከበደ ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው፤ ይሄን ፊልም  በማዘጋጀት፣ በመቅረጽና በማከፋፈል ሥራ ላይ  ለሚሳተፉ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችና የፊልም ባለሙያዎች ስልጠና የሚያገኙበት አውደጥናቶች ይዘጋጃሉ፡፡
በፕሮፌሰር ሃይሌ ገሪማ ከሚሰራው “የጡት ልጅ” በተጨማሪ፣ የዘንድሮውን የአውሮፓ ህብረት የገንዘብ ድጋፍ ያገኘው ሌላው ኢትዮጵያዊ የፊልም ዳይሬክተር ነዋሪነቱን በፈረንሳይ ያደረገው ያሬድ ዘለቀ ሲሆን “ላምብ” በሚል ርዕስ ለሚሰራው ፊቸር ፊልሙ የ495 ሺህ ዩሮ (12ሚ. ብር ገደማ) ድጋፍ ተደርጎለታል፡፡
ተቀማጭነቱን በፈረንሳይ ያደረገው የያሬድ “ግሎሪያ ፊልምስ ፕሮዳክሽን”፤ ከኢትዮጵያው “ስለም ኪድ ፊልምስ” እና ከአይቮሪ ኮስቱ “ዋሳካራ ፕሮዳክሽንስ” ጋር በአጋርነት የሚሰራ ሲሆን  ለዚህ የፊቸር ፊልም ፕሮጀክት፣ የ495 ሺህ ዩሮ ድጋፍ ተደርጎለታል፡፡
እናቱን በልጅነቱ በሞት ከተነጠቀ በኋላ፣ ከአንዲት የበግ ግልገል ጋር ጥብቅ ወዳጅነት በፈጠረ አንድ ኢትዮጵያዊ ብላቴና ታሪክ ዙሪያ የሚያጠነጥነው “ላምብ” ፊልም፤በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ተሰርቶ የሚጠናቀቅ ሲሆን  ቀረጻው ሙሉ ለሙሉ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚከናወን ተጠቁሟል፡፡
አጠቃላይ ስራው ከኢትዮጵያና ከአይቬሪኮስት በተውጣጡ የባለሙያዎች ቡድን በሚመራው በዚህ ፊልም ላይ የሚሳተፉት ኢትዮጵያውያን ተዋንያን ሲሆኑ የገንዘብ ድጋፉ የተደረገውም የኢትዮጵያን የፊልም ኢንዱስትሪ ለማጠናከርና በዘርፉ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን ክህሎት ለማሳደግ በሚል እሳቤ መሆኑን ከአውሮፓ ህብረት የኤትዮጵያ ደልጌሽነ የፕሬስና ኢንፎርሜሽን ኦፊሰር ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡
ከተለያዩ የአፍሪካ የካሪቢያንና የፓስፊክ አገራት ከሚገኙ አመልካቾች የሚቀርብለትን ፊልምና የተለያዩ የመዝናኛ ኢንዱስትሪ የፕሮጀክት ፕሮፖዛል በመገምገም፣ ለተመረጡ ፕሮጀክቶች በየአመቱ ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርገው የአውሮፓ ህብረት፤ ዘንድሮም በተለያዩ ምድቦችና ዘርፎች ለመረጣቸው 37 የተለያዩ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡
በመጀመሪያው ምድብ “የጡት ልጅ” እና “ላምብ’ን ጨምሮ ለዘጠኝ የተለያዩ የአፍሪካና የካረቢያን አገራት ፊቸር ፊልሞች እንዲሁም በሞዛምቢክ ለሚሰራ “ፍሮም ዎር ኤንድ ፒስ” የተሰኘ ተከታታይ የቴሌቪዥን ዶክመንታሪ ፊልም የገንዘብ ድጋፍ ተሰጥቷል፡፡
በዚሁ ምድብ ውስጥ ለተካተቱ ስምንት የተለያዩ አገራት የሲኒማና ኦዲዮ ቪዥዋል፣ የኔትወርኪንግና የፌስቲቫል ዘርፍ ፕሮጀክቶች፤ የማከፋፈልና የፕሮሞሽን ስራ ለማከናወን የሚውል የገንዘብ ድጋፍ ተበርክቷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በባለሙያዎች ስልጠናና በሙያ ክህሎት ግንባታ መስክ ከቤልጂየም፣ ከኡጋንዳ፣ ከጣሊያን፣ ከታንዛኒያና ከፈረንሳይ ለቀረቡ አምስት የሲኒማና ኦዲዮ ቪዥዋል ዘርፍ ፕሮጀክቶች ጠቀም ያለ ገንዘብ ተሰጥቷል፡፡
በሁለተኛው ምድብ በክዋኔ ጥበባት፣ በፌስቲቫል ዝግጅት፣ በኔትወርኪንግ፣ በባህል አስተዳደርና በቅርስ ጥበቃ ዘርፎች ለቀረቡ ስድስት ፕሮጀክቶች የማከፋፈልና የፕሮሞሽን ወጪ የሚውል ገንዘብ የተሰጠ ሲሆን፣ በክዋኔ ጥበባት፣ በባህል ልማት፣ በሙዚቃ ኢንዱስትሪና በቅርስ ጥበቃ ዘርፎች ለቀረቡ ሰባት ፕሮጀክቶችም የስልጠናና የሙያ ክህሎት ግንባታ ገንዘብ ተለግሷቸዋል፡፡ በፓሲፊክ አገራት የባህል እድገት ለመፍጠር ለተቀረፀ አንድ ፕሮጀክትም የገንዘብ ድጋፍ መደረጉን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 10 years ago on March 20, 2014
  • By:
  • Last Modified: March 20, 2014 @ 7:01 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar