www.maledatimes.com የፍትህ መጓደል እና የቴዲ አፍሮ የሰቆቃ ጉዞ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የፍትህ መጓደል እና የቴዲ አፍሮ የሰቆቃ ጉዞ

By   /   October 14, 2014  /   Comments Off on የፍትህ መጓደል እና የቴዲ አፍሮ የሰቆቃ ጉዞ

    Print       Email
0 0
Read Time:15 Minute, 2 Second

በዘላለም ገብሬ

1524949_712295792122084_1859708246_n

ዛሬ ምንም ባልታሰበ እና ባልተጠበቀ ጊዜ ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ በቀረጥ ክፍያ በማጭበርበር ተከሰሰ የሚል አደናጋሪ ወሬ ሰማን እና ምን አለብቶት የሚል ሆኖብን ታዲያ ይህ የክስ መዝገብ እንዴት ዛሬ ሊታይ ቻለ የሚለውን ዙሪያ ጥምጥም ለማየት ለመዳሰስ ሞክረን ቀደም ካሉት አንዳንድ መጣጥፎች እና የቴዲን መዝገብ አስመልክቶ ምን ተካሂደው ነበር የሚለውን የመኪና አደጋውን ሂደት ምን ይመስል ሁኔታውም ሆነ የክስ ሂደቱ እንዴት አለፈ ?የሚለውንነና ሌሎቹንም ለመዳሰስ ያስችለን ዘንድ አንዳንድ ነጥቦች እናንሳ ።በ1999 አመተ ምህረት ጥቅምት ሃያ ሁለት ቀን በተፈጸመ የመኪና አደጋ ክስ በተጭበረበረ የክስ መዝገብ ሲከናወን እንደነበረ ይታወሳል።

ሆኖም ዛሬ ደግሞ ከስድስት አመታት ቆይታ በኋላ እንደገና አዲስ ክስ ተቀስቅሶ ይሄው አቤቱታውን ሊያሰሙን የቅድሚያ ምርመራ እንዲደረግ እና ክሱን በውጭ ሆኖ እንዲከላከል ሲሉ ዳኛው በመወሰናቸው የ30.000 ብር ዋስትና ተፈቅዶለት ከእስር መለቀቁ ሁሉንም አስደንግጦአል ።

የቴዲ አፍሮ ክስ መመስረት በአመክሮ ከተመለከትነው በትክክል የፍርድ ሂደትን እና የህግ ረቂቅ አዋጅን ተከትሎ የመጣ ሳይሆን የግላዊ ጥላቻን ለማንጸባረቅ ከሚጀመረው የሂደት ጉዞ ሲሆን ካለው የፖለቲካ ልዩነት አንጻር የግለሰቡን የፖለቲካ አመለካከት ካለመቀበል እና ልክ እንደ ጣኦት እኛን ካላመለከን አንተም አትመለክም የሚለውን አመጸኛ አመለካከታቸውን በጊዜያዊው ስልጣናቸው ፣የስልጣን በትራቸውን ለመቃጣት የሞከሩት የኢሃዴግ አጎብዳጆች መሆናቸው ይታወቃል ።ለዚህም እንደምክንያት ሊቀርቡ የሚችሉ የተለያዩ ዳሰሳዎችን ማቅረብ እችላለሁ ።

በመጀመሪያ ደረጃ ክሱ ከመጀመሩ በፊት መኪናዋ እንዴት ቴዲ አፍሮ ሊገዛት ቻለ ?የሚል ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል በዚህ ጥያቄ ላይ ብዙ ነገሮችን ሊያሳየን የሚችለው ጠቋሚ መንገድ ይኖራል አንደናው ያለ ቀረጥ ካስገባ ሰው ላይ ገዝቶ ከሆነ ፣ያለቀረጥ ያስገባው ሰው ያልከፈለበትን ቀረጥ የመክፈል ግዴታው እንደሆነ ግልጽ ነው ፣ሆኖም ግን በዚህም ሆነ በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ቴዲ አፍሮ ቀረጥም ሆነ የግብር ገቢ ታክስ ሊከፍልበት የሚችልበት ብዙ አማራጭ መንገዶች እንዳሉ ይታወቃል ከእነዚህም መካከል በኢንቨስትመንትም መልኩ መኪናዋን አስገብቶ ከሆነ ቦሎ እና የሰሌዳ ቁጥር ለማውጣት ሲያስመዘግብ የሚጠየቀውን ነገሮች ሁሉ በማሟላት ወደ ህጋዊ የሆነው የፈቃድ አገልግሎት ማግኘት የሚችልበት መንገድ የተዘረጋበት አስራር እንዳለው የሚታወቀው የትራንስፖርት እና መገናኛ ባለስልጣን ሁሉንም መረጃዎች አጣርቶ ፈቃዱን እንደሰጠው ግልጽ ነው ። በሌላም በኩል ቢሆን በግዥ አገር ውስጥ የተፈጸመ ከሆነ ደግሞ በውል እና ማስረጃ በኩል የሚከናወኑትን የስም ማዛወር ስራዎች በሙሉ ከነ ሙሉ መብቱ ክፍያውን ሊያጠናቅቅ እንደሚችል እና የባለቤትነቱን ሰርተፊኬት እንደሚያገኝ የሚታወቅ ነው ። ይህ አሰራር በወቅቱ የነበረውን ክፍለ ከተማ ስብጥር በሚል በተጀመረው አሰራር ሂደት የሚከተል እንደሆነ ይታወቃል ።

በቴዲ አፍሮ ጉዳይ ላይ ብዙ ነገሮችን እናንሳ ካልን የዚህች የቢ ኤም ደብሊው ጦስ እና መከራ ብዙ ነገሮችን ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ይታወቃል ።ምክንያቱም መንግስት ከመሰረተው ክስ ጀምሮ መጣረስ እና ምስክር ነን ባዮች የሰጡት ቃል አለመገጣጠም ፣የቴዲ የመኪና አደጋ እና ሟች ደጉ ይበልጣል የተባሉት ግለሰብ ሞቱ የተባሉበት ቀን እና ቴዲ አፍሮ ወደ ሃገር ቤት የገባበት ቀን አለመገጣጠም ፣የፖሊሶች የይግባኝ ጥያቄ ጠይቀው እንደገና ክሱን በመከለስ ቴዲ በገባበት ቀን የክስ መዝገቡን ቀን እና እለቱን በመቀየር ክሱ በአዲስ መልኩ እንዲታይ ማስደረጋቸው ይሄ ሁሉ በተጨባጭ ንጹህ የሆነን ሰው ለመኮነን ከሚደረጉት ጥቂት የሆኑ ግን ጉልህ ስህተቶቻቸው እራሳቸውን ተወቃሽ ሲያደርጋቸው የሚኖር ሲሆን ዛሬም ለመሰረቱት ክስ የዚሁ አይነት እጣ ፈንታ እንዳለው ከመገመት አያዳግትም ።

ይህንን ለመን መገመት አስፈለገ ተብሎ ለሚጠየቀው ጥያቄ ከላይ ያለው መንደርደሪያ ሃሳብ መልሱን ሲሰጥ ለአሁኑ ክስም ሆነ ለቀድሞው ክስ መመስረት ምክንያት የሆኑት ዋነኛ ነገሮች

ጃ ያስተሰርያል …. አዲስ ንጉስ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ የሚለው እና እንዲሁም ባንዲራ ከሚለው ከ 9 አመታት በፊት በአውሮጳ የተዘፈነው ዘፈን ቀስተዳመናው ላይ አንበሳው ከሌለ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ትርጉሙ የታለ ! የሚሉት ሁለት ዜማዎች አስቆጥቶአቸው ክሱን ለመፈጸም ደፋ ቀና ሲሉ የከረሙት የወያኔ አዛውንቶች ዛሬ ሊሳካላቸው አገረቤት ሲገባ ጉሮሮውን ይዘው እስርቤት በማስገባት በጥያቄዎቻቸው ሊሞሉት ሞክረዋል።

ታዲያ ነገሩ እንዲህ ከሆነ ለምን የሚለው ጥያቄ ያስነሳል እስከዛሬስ የት ነበሩ ? ለሰባት እና ለስምንት አመታት ምርመራ እያደረጉ ነበርን ወይንስ የሚከሱበትን መንገድ እያውጠነጠኑ ?

ይህ በእንዲህ እንዳለ ለምን ከዛሬ 6 ወይንም 7 አመታት በፊት የመኪና አደጋ ክሱ በነበረበት ወቅት ሊታይ አልቻለም ?

ለምንስ የጉሙሩክ ስራ አስፈጻሚ አካላቶች ይህንን መኪና ያስገባውን ሰው በዋነኛነት ሊጠይቁ አልቻሉም ?

ቴዎድሮስ ካሳሁን በሚል ስም የገባ ከነበረስ እንዴት እስከዛሬ ድረስ ሳይከፍል መረጃዎቹ ተጠናቀው ተሰጡት ፣ካልከፈለምየጉሙሩክ ቱባ ባለስልጣናት ለዚህ ስራቸው በከፍተኛ ደረጃ ተጠያቂ ሊያደርጋቸው ለምንስ አልቻለም?

ይህ በሙስና የተደራጀ ድርጅት እንደሆነ እና ከፍተኛውን ድርሻ የያዙት የትግራይ ተወላጆች እና በህወሃት ጥላ ስር ያሉ ልጆች ብቻ እንደሆኑ የሚታወቅ ሲሆን በቴዎድሮስ  ላይ ያረፈው አለንጋ በእነርሱ ላይ ማረፍ ሲገባው ለምን ለሶስተኛ እና አራተኛ ወገን ላይ ህጉ ሊፈጸም ይችላል ?

በሃገራችን እየተዛባ ያለው የፍትህ ስርአት  ግንባር ቀደም ተጠያቂ ሊሆኑ የሚገባው በእራሳቸው አስተዳደር ላይ ያሉት ሰዎች የተሰጣቸውን ስራ፣ ስነ ምግባር በጎደለው መንፈስ  ፣በቅንነት በሌለው ጎዳና እና በስነ ምግባር ካለማገልገላቸው የተነሳ የህብረተሰብንም ሆነ የሃገርን ገንዘብ በመዝረፍ ለከፍተኛ ኪሳራ እየዳረጉ ዛሬ ምንም ባለተጠበቀበት ወቅት የንጹሃንን ገንዘብ ለማጋበስ ያመቻቸው ዘንድ የሚጠቀሙበት አቋራጭ መንገድ ሆኖ ተገኝቶአል ።

ምናልባትስ የከፈለበትን ፋይል ከግምሩክ ውስጥ ደብዛውን አጥፍተውትስ ከሆነ እና ዛሬ ደግሞ በሌላ ሁኔታ ለማሰቃየት እና መቀጣጫ እናድርገው ብለው በሙስና የጎለበተውን ጉልበታቸውን ሊያሳዩት ይሆን ?

አለበለዚያም ከእስር ቤት በነበረበት ወቅ ላይ በሲ ኤም ሲ የነበረው መኖሪያ ቤቱ ሲፈተሽ አስፈላጊ ያሉአቸውን መረጃዎች ሰብስበው ሄደው እሱ በማያገኛቸው መልኩ ከናካቴው አጥፍተው እንደገና ፊታቸውን እና ጣታቸውን ወደ እሱ ቀስረውስ ቢሆን ማን ያውቃል ?

ለማንኛውም ቀድሞ የነበረውን የክስ ሂደት ምን ይመስላል የሚለውን ለመዳሰስ ያህል ከስር አስቀምጠነዋል ለመረጃ ያህል የተቀመጠ ሲሆን የምርመራው ሂደት ምን ይመስል እንደነበር እና ክሱንም አስመልክቶ የቀረቡትን ሁኔታውች የሚያሳይ ስለሆነ ትኩረት ቢሰጡበት መልካም ነው እንላለን ።

ለፍትህ ሚንስትርም ቢሆን አሁንም ልብ ይስጠን እያልን የተጀመረው የክስ ሂደት ክሱ ከመቅረቡ በፊት ጥናት ቢደረግበት መልካም ነው የሚለውን ሃሳባችንን እየሰጠን በዚሁ አጋጣሚ በጉምሩክም ሆነ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ የሚሰሩ የደህንነት አባላት በትራዋይነታቸው ብቻ አትንኩኝ አትናገሩኝ እኛ ብቻ የንነግራችሁን ትፈጽሙ ዘንድ ቃላችን ነው ይህንን ካላደረጋችሁ ግን አገር ትቃጠላለች የሚሉትን በስርአቱ ብታስተነፍሷቸው የሚቀል ይሆናል እንጂ በዘር ተለይቶ የምትከፋፈል አገር ልትኖረን እንደማይገባ እና የነገውን ትውልድ ሌላ ጠባሳ ጥላችሁበት የምታልፉበት እንዳይሆን ጊዜው ዛሬ ነው እና ትውልዶቻችንን የማዳኑን ስራ በትክክለኛ የፍትህ ስራ በመታገዝ እናሳይ ። ከላይ የተጻፈው አጭር ጽሁፍ የሚያሳየው በሃገራቸን ያለውን የፍትህ መጓደል እና የቴዲ አፍሮ የሰቆቃ ኑሮ ሲሆን የእርሱ ኑሮ የሌሎችንም በየቤታችን የሚያሳይ ድብቅ ሚስጥር ቅንጨብ አድርጎ ሊያቀብ የተሞከረ እንጂ በጥናታዊ ጽሁፍ የተደገፈ ባለመሆኑ ብዙም ከረር ያሉ ሰነ ጽሁፋዊ አጀንዳዎችን ይዞ አልተነሳም ዋናው ነገር ሊያስገነዝብ የሞከረው በቴዲ ክስ ላይ የተመሰረተው አልባሌ የሆነ ክስ ለምን ዛሬ ሊመሰረት ቻለ በሚለው ዋነኛ ሃይለ ቃል እስከዛሬ ለምን እንደጠበቁት ማብራሪያ ሊያሰጥ የሚችል ሃሳብ ካላቸው በሰነዙሩ በሚል አንደምታ የተተየበ ነው ።

 

የክሱ አመጣጥና ሂደት

ቴዲ አፍሮ ረቡዕ ጥቅምት 22 ቀን 1999 ዓ.ም. ከካናዳ ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል። ዓርብ ጥቅምት 24 ቀን 1999 ዓ.ም. በሲ.ኤም.ሲ. ይኖርበት ከነበረው መኖሪያ ቤቱ “ሰው ገጭተህ አምልጠሃል” በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ እስር ቤት ይገባል። ሜክሲኮ በሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ ነክ ፍርድ ቤት የሰባት ቀን የጊዜ ቀጠሮም ተጠይቆበት ወደ ታሰረበት ጣቢያ ይመለሳል።

 ቅዳሜ ጥቅምት 25 ቀን 1999 ዓ.ም. ከታሰረበት ጣቢያ የ50 ሺህ ብር ዋስትና አስይዞ ይለቀቃል። በቀጠሮው መሰረትም ፍርድ ቤት ሲቀርብ፤ ፖሊስ የምርመራ መዝገቡን አጠናቆ ለሚመለከተው አካል ያስተላለፈ መሆኑን በመግለጽ የቀጠሮ መዝገቡ እንዲዘጋለት ጠይቆ መዝገቡ ተዘግቷል።

 ጉዳዩን የያዘው ፖሊስም ኅዳር 7 ቀን 1999 ዓ.ም. በፖሊስ መዝገብ ቁጥር 2749/99 ቁጥር 8206/ወ/መ18 በተጻፈ መሸኛ ደብዳቤ “ቴዎድሮስ ካሣሁን ገርማሞ ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ከአስር ደቂቃ ሲሆን በአራዳ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 17 ክልል በቤተ መንግሥት አካባቢ ንብረትነቱ የግላቸው በሆነው ኮድ 2-59868 አዲስ አበባ BMW አውቶሞቢል መኪናቸው ደጉ ይበልጣል የተባለ እግረኛ ገጭተው ገድለው ካመለጡ በኋላ፣ በፍለጋ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ የተደረገባቸው ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓት የምርመራ መዝገቡ ተጠናቆ ከዚህ ሸኚ ደብዳቤ ጋር ተልኳል።” የሚል ደብዳቤ ጽፎና ምርመራውን ማጠናቀቁን ገልጾ መዝገቡን ለአዲስ አበባ ፍትህ ሚኒስቴር ተጠሪ ጽሕፈት ቤት አስተላለፈ።

 ስለ ሟች “ፎርቹን” ጋዜጣ አውጥቶት የነበረው የሕይወት ታሪክ

ቴዲ አፍሮ በመኪና ገጭቶ ገድሎታል በሚል የተጠረጠረበትን የሟች ደጉ ይበልጣል የሕይወት ታሪክ “ፎርቹን” የተባለ የእንግሊዘኛ ጋዜጣ የሟች አባት አቶ ታምሩ ተፈሪን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ሟች ከጎጃም መጥቶ ሽሮ ሜዳ አካባቢ ከአጎቱ ጋር ይኖር የነበረ የ18 ዓመት ወጣት ነው። ደጉ መጠጥ ከሚጠጡ ልጆች ጋር በመግጠሙ ቤቱን ጥሎ ለጎዳና ሕይወት ይዳረጋል። ነገር ግን በሣምንት አንዴ ወይም ሁለቴ ወደ ቤተሰቦቹ በመምጣት ይጠይቃቸው እንደነበር ነው። ዓርብ ጥቅምት 24 ቀን 1999 ዓ.ም. ደጉ በመኪና አደጋ መሞቱ ተነግሯቸው አስከሬኑን ከምኒልክ ሆስፒታል ወስደው በእንጦጦ ቁስቋም ማርያም ቤተክርስቲያን መቅበራቸውን ጋዜጣው ዘግቦ ነበር።

 

ቴዲ በወቅቱ ለአዲስ አድማስና ሪፖርተር ጋዜጣ የሰጠው መልስ

“ሰውን የሚያህል ክቡር ነገር ገጭቼ ላመልጥ አልችልም፣ እኔ ድርጊቱ ተፈጸመ በተባለበት ቦታ አልነበርኩም፣ ‘ሰው ገጭቶ አምልጧል’ የተባለው ወሬ ሐሰትና ጉዳዩም ክብሬን የሚነካ ነው” ነበር ያለው።

 

ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር በኋላ የተቀሰቀሰው የቴዲ ክስና የፍርድ ሂደት

ረቡዕ ሚያዝያ 8 ቀን 2000 ዓ.ም.

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስምንተኛ ወንጀል ችሎት፤ (ለሁለት ዓመታት የዘለቀውንና የቅንጅት አመራሮች … የተከሰሱበትን የሁለተኛ ወንጀል ችሎት በቀኝ ዳኝነት ሲያስችሉ በነበሩት) ዳኛ አቶ ልዑል ገብረማርያም ከጠዋቱ 3 ሰዓት ከ30 ደቂቃ የተሰየመው ችሎት ከጠዋቱ 5 ሰዓት አካባቢ ሲሆን በወንጀል መዝገብ ቁጥር 06226 የተከሰሰው ተከሳሽ እንዲቀርብ ጥሪ አስተላለፉ።

 

ችሎቱ መደበኛ በመሆኑና በዕለቱ በህዝብ ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፈው የታዋቂው ዘፋኝ የአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን መዝገብ መሆኑን በችሎት ታዳሚው የሚታወቅ ባለመሆኑ፤ ቴዲ አፍሮ ከጠበቃው ጋር ወደ ተከሳሽ ሳጥን ገብቶ ሲቆም የችሎት ተከታታይ ዓይን ወደ ሣጥኑ ተወረወረ።

 

ዳኛው፤ መዝገቡ በችሎት ተከፍቶ ሊቀርብ የቻለበትን ምክንያት ማሰማት ጀመሩ፣ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በቴዎድሮስ ካሳሁን ያቀረበው ክስ “መጠጥ ጠጥቶ ካለመንጃ ፈቃድ በማሽከርከር ሰው ገጭቶ ከገደለ በኋላ ምንም እርዳታ ሳያደርግ አምልጧል” የሚል ነው። ዓቃቤ ሕግ በክሱ ላይ የጠቀሰው አንቀጽ በ1997 ዓ.ም. በወጣው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የወንጀል ሕግ፤ በቸልተኝነት ሰው መግደል የሚለውን አንቀጽ 543 ንዑስ ቁጥር 3 መተላለፍ የሚል ነው።

 

የቴዲ አፍሮ ጠበቃ አቶ ሚሊዮን አሰፋ ደንበኛቸው ቴዎድሮስ ካሳሁን በዋስ እንዲፈታና ጉዳዩን በውጭ ሆኖ እንዲከታተል ያቀረቡት አቤቱታ በዓቃቤ ሕግ ተቃውሞ ስለገጠመው በዋስትናው ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ።

 

ሰኞ ሚያዝያ 13 ቀን 2000 ዓ.ም.

ፍርድ ቤቱ በዋስትናው ጥያቄ ላይ ትዕዛዝ ይሰጣል ተብሎ ሲጠበቅ፣ ዓቃቤ ሕግ ክሱን እንዲያሻሻል ትዕዛዝ አስተላለፈ።

 

ረቡዕ ሚያዝያ 15 ቀን 2000 ዓ.ም.

በዚህ ዕለት ዓቃቤ ሕግ ክሱን አሻሽሎ አቀረበ። ”ቴዲ አፍሮ መንጃ ፍቃድ ሳይኖረው ጥቅምት 23 ቀን ከለሊቱ በ7 ሰዓት ከአራት ኪሎ ወደ ካሳንችስ በሚወስደው መንገድ ሲያሽከረክር ለእግረኛ ቅድሚያ መስጠት ሲገባው ቅድሚያ በመከልከል ሙዋች ደጉ ይበልጣል የተባለን የ18 ዓመት ወጣት ገጭቶ ገድሏል። ከዚያም መርዳት ሲገባው ምንም እርዳታ ሳያደርግ አምልጧል” የሚል ሲሆን፣ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘም ከአምስት ዓመት እስከ 15 ዓመት በሚደርስ እስራት እንዲቀጣ የሚጠይቅ ነበር።

 

ቴዲ አፍሮ የእምነት ክህደት ቃሉን ሲጠየቅ ”ድርጊቱን አልፈፀምኩም ጥፋተኛም አይደለሁም” ሲል የእምነት ክህደት ቃሉን ሰጥቷል። ዋስትናውን በሚመለከት ጠበቃውና ዓቃቤ ሕግ ክርክር ቢያደርጉም ማክሰኞ ሚያዚያ 21 ቀን 2000 ዓ.ም. ጠዋት የተሰየመው ችሎት ዋስትናውን ከልክሎታል።

 

ኀሙስ ግንቦት 14 ቀን 2000 ዓ.ም. የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች

ዓቃቤ ሕግ አሉኝ ካላቸው አራቱ ውስጥ ሦስቱን አቅርቦ አስመስክሩዋል። ሦስቱም የቀረቡት ምስክሮች ፖሊሶች ነበሩ።

 

የመጀመሪያው ምስክር ኮንስታብል ከበደ ወየሳ ሲሆን፣ ከዓቃቤ ሕግ፣ ከቴዲ ጠበቃ እና ከዳኛው ከተሰነዘሩለት ዋና፣ መስቀለኛ እና ማጣሪያ ጥያቄዎች ምስክርነቱን አስረድቷል። እንደዓቃቤ ሕግ የመጀመሪያ ምስክር አገላለጽ ከሆነ ጥቀምት 23 ቀን 2000 ዓ.ም.፣ ከሌሊቱ 7 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ላይ፣ በተለምዶ “ፊት በር” እየተባለ በሚጠራው አካባቢ፣ የጥበቃ ሥራ እየሠራ ባለበት ወቅት፣ አንድ አረንጓዴ የቤት መኪና፣ ግራና ቀኝ በሁለት ላዳ ታክሲ ታጅቦ በፍጥነት እየበረረች ትመጣለች፣ ምስክሩ በ20 ሜትር ርቀት ላይ ሆነው ይመለከታል። አንድ ሰው ደግሞ፣ ከቀበሌው አካባቢ (ከቀኝ ወደ ግራ) አስፋልቱን ወደ ቤተ መንግሥት ሲያቋርጥ፣ መሃል አስፋልት ላይ ይወድቃል። ያች ስትበር የነበረችው አረንጓዴ መኪና፣ የተኛውን ሰው ገጭታው ትሄዳለች። መኪናውን ሮጦ ይከተልና ታርጋ ቁጥሩን ይመዘግባል።

 

በአራት ኪሎ ግንብ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ፣ በሥራ ላይ የሚገኘውን የሥራ ባልደረባውን ጠርቶ፣ ወደ ወደቀው ልጅ ሲሄድ፣ የመጠጥ መንፈስ እንዳለውና ሕይወቱ እንደነበረች ተመልክቷል። ከዛም ከ5 ደቂቃ በኋላ ሕይወቱ አልፏል። ስልክ ደውሎም ጉዳዩን ለፖሊስ ማሳወቁን ገልጿል። በማግስቱም ትራፊክ ጽ/ቤት ሄዶ ቃሉን መስጠቱን፣ መኪናዋን እዚያ ሲያያት እንዳወቃት ገልጾ፣ ተከሳሹን ቴዲ አፍሮን ግን አላውቀውም ብሏል።

 

የሁለተኛው ምስክር ኮንስታብል ታምራት ዱላ ቃልም ተመሳሳይ ነበር። አማርኛ ቋንቋ አጥርቶ መናገር ባለመቻሉ የሚለው አይሰማም፣ በጣም እየፈጠነ የሚናገር በመሆኑም፣ ዳኛው “እንደው አስተርጓሚ የሚፈልግ ዓይነት ነገር እኮ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል። ጠበቃውና ዓቃቤ ሕጉም ሲጠይቁ ዳኛው በመካከል እየገቡ ይጠይቁ፣ እንዲብራራም ያደርጉ ነበር። ይሄ ምስክር በተጠቀሰው ቀንና ሰዓት፣ ግንብ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የጥበቃ ሥራ እየሠራ እያለ፣ አንድ አረንጓዴ መኪና በሁለት ላዳ ታክሲዎች መካከል በከፍተኛ ፍጥነት እየበረረች ስትመጣ፣ ፊሽካ ነፍቶ ፍጥነቱን እንዲቀንስ ለማድረግ እንደሞከረ ገልጾ፤ ትንሽ ቆይቶ ጓደኛው ከሼራተን አካባቢ፣ በእጁ “ና! ና!” ብሎ እንደጠራውና፣ ስለተፈጸመው እንደነገረው፣ ከዛም ወደ ልጁ ሲሄዱ የልጁ ሕይወት እንደነበር፣ ከአምስት ደቂቃ በኋላ ደግሞ መጥፋቱን ገልጾ፣ ለፖሊስ ደውሎ እንደተናገረ መስክሯል። ስለሟች የአለባበሱንና የኑሮውን ሁኔታ እንዲናገር ሲጠየቅ፣ እዛ አካባቢ ለረጅም ጊዜ መሥራቱንና፣ ልጁ የጎዳና ተዳዳሪ መሆኑን ገልጾ፣ መጠጥ እየጠጣ ሲወድቅ እንደሚያውቀው ተናግሯል።

 

ሦስተኛ ምስክር ሆነው የቀረቡት የፕላን ምስክር ሲሆኑ፣ አደጋው ከደረሰ በኋላ በቦታው ተገኝተው ፕላን ማንሳታቸውን ተናግረዋል፣ ስለ ፕላኑም አስረድተዋል። ባነሱት ፕላን ላይ ስለተፃፈው ነገር፣ ከጠበቃው መስቀለኛ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል። የታርጋ ቁጥሩን መዝግቤያለሁ ያሉት አንደኛው ምስክር፣ ፕላኑ ሲነሳ በቦታው መኖራቸውን አረጋግጠው ፈርመው እያለ፣ በዚሁ ፕላን ላይ ፕላን አንሺው ደግሞ “ፕላኑን ተመልከቼዋለሁ የሰሌዳ ቁጥሩ ያልታወቀ ተሽከርካሪ ሰው ገጭቶና ገድሎ ያመለጠ ስለሆነ፣ በማስረጃ ጭምር በአስቸኳይ ይጣራ” ብለው ጽፈዋል። በወቅቱም የሰሌዳ ቁጥር የያዘ የዓይን ምስክር ካለ፣ ለምን ይሄ ተፃፈ? በሚል ጥያቄ አቅርቧል። እንደ አሠራር የታርጋ ቁጥር የሚያሠፍሩት ገጭቶ ያላመለጠና ሹፌሩ እዛው ኖሮ በፕላኑ ላይ ሲፈርም እንደሆነ ገልጸዋል።

 

ጠበቃው ከእኝህ ምስክር ጋር ስለሟች አወዳደቅ፣ ስለ መኪናው አገጫጭ፣ በርካታ መስቀለኛ ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን ስለ ግጭቱም ከኮንስታብሎቹ ጠይቄ የተረዳሁት ነው ያሉትን ፕላን አንሺው ሲገልጹ “ሟች ከጓደኛው ጋር እየተጓተተ አስፋልቱን በማቋረጥ ላይ እያለ ይወድቃል። በወደቀበት በዚያው ፍጥነት በመኪናው ተገጭቷል። ገጪው መኪናም ልጆቹ ሲያቋርጡ አይቷቸዋል” የሚል ነበር።

 

የምስክሮቹ ቃል፣ ከተሰማ በኋላ፣ ዓቃቤ ሕግ አንዱን ምስክር በአድራሻው ስላላገኘው ምስክሩ ለፖሊስ የሰጠው ቃል ከመዝገቡ ጋር እንዲያያዝለት ጠይቆ ተፈቅዶለታል።

 

ዓቃቤ ሕግ ያለው ማስረጃ፣ ምን እንደሚያስረዳለት አጠቃሎ እንዲያቀርብ ዳኛው ትዕዛዝ ሲሰጡ፣ ጠበቃው ከጊዜ አንፃር ምላሻቸውን እዛው ለመስጠት ተዘጋጅተው መምጣታቸውን በመግለጽ የተከራከሩ ቢሆንም፣ ጥያቄያቸው ተቀባይነት ባለማግኘቱ ዓቃቤ ሕግ በጽሑፍ አጠቃሎ የሚያቀርበውን የማስረጃ ዝርዝር ሂደት ለመጠባበቅ ለግንቦት 27 ቀን 2000 ዓ.ም. ተቀጥሯል።

 

ሦስቱም የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች የመረበሽ፣ የመደናገጥ፣ የመርበትበትና የመንተባተብ ሁኔታ ይታይባቸው የነበረ ሲሆን፣ አንዳንዴም ይሰጡት የነበረው ምስክርነት እርስ በእርሱ ይጋጭ ነበር። በተለይ ደግሞ ፖሊሶች ከመሆናቸው አንጻር ሁኔታቸው በችሎት የነበረው ተመልካች የምስክሮች ቃል በሚሰማበት ወቅት፣ ምስክሮች ለሚቀርብላቸው ጥያቄ የሚሰጡት ምላሽ በሚፈጥርባቸው ስሜት፣ የማጉረምረም ድምፅ ሲያሰሙ የነበረ ሲሆን ከዳኛም፣ ከፖሊስም ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።

 

ረቡዕ ግንቦት 27 ቀን 2000 ዓ.ም.

ዓቃቤ ሕግ በታዘዘው መሰረት ያቀረባቸው ስድስት የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ለችሎቱ ምን እንደሚያስረዱለት ያቀረበ ሲሆን፣ አንደኛ የአደጋ ቦታ ፕላን ሲሆን፣ ተከሳሽ የሚያሽከረክረው መኪና በቤተ መንግሥት አካባቢ ከላይ ሲመጣ ሟች ደጉ ይበልጣልን ከሩቁ ማየት ስለሚችል ከአደጋው ማትረፍ ይቻለው የነበረ ቢሆንም ሳያተርፈው መቅረቱን ያስረዳልኛል በማለት ያቀረበ ሲሆን፤ የተቀሩት አምስቱ ደግሞ መኪናውን የሚያሳይ ፎቶግራፍ (በትራፊክ ቢሮ አካባቢ)፤ ከምንሊክ ሆስፒታል የአስከሬን ምርመራ የም/ወረቀት (ኦሪጅናል ያልሆነና የመርማሪው ስም ኢሳያስ ብቻ ተብሎ በእጅ የተጻፈበትና የዶክተር ፊርማ ያላረፈበት)፤ አስከሬኑ ቀና ተደርጎ የተነሳ ፎቶግራፍ፤ መኪናው አደጋ ከማድረሱ በፊት ምንም አይነት የቴክኒክ ብልሽት ያልነበረው መሆኑን አስረድቷል።

 

የቴዲ አፍሮ ጠበቃም በተራው ዓቃቤ ሕግ ያቀረባቸው የማስረጃ ዝርዝር መግለጫዎች ተቃውሟል። ጠበቃው፤ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው ማስረጃ ተከሳሽ በጎማ ሄዶበታል የሚል ሲሆን፣ የሟች አስከሬን የተገኘው ሰውነቱ ተቀጥቅጦና ተሰባብሮ ነው በማለት ተቃውሞውን ያቀረበ ሲሆን፣ እስከዛሬ በፍርድ ቤቶች ሕግ መሰረት የአስከሬን ምርመራ በሁለት ዶክተሮች ተመርምሮና ተፈርሞበት መቅረብ የሚገባው ኦሪጅናል የአስከሬን ምርመራ ውጤት በአንድ ኢሳያስ ተብሎ በቀረበ ኦሪጅናል ባልሆነ የምስክር ወረቀት መቅረቡ አግባብ አለመሆኑን አመላክቷል።

 

በተጨማሪም የቀረበው የፕላን ማስረጃ ያልታወቀ መኪና ገጭቶ ማምለጡን ከመግለጹ ውጭ የተከሳሽ መኪና ወይንም ተከሳሹ ገጭቶ ማምለጡን የማይገልጽ ሲሆን፣ የመኪናውን አይነትና ታርጋ ቁጥር ያልታወቀ መሆኑን ከማስረዳት ያለፈ የተከሳሽ መኪና ስለመግጨቱ የቀረበ የፕላን ማስረጃ ባለመኖሩ ደንበኛዬን ጥርጣሬ ውስጥ የሚከት ነገር ስለሌለ በነፃ ይሰናበትልኝ በማለት ጠይቋል።

 

ዳኛውም “ኦሪጅናል የአስከሬን ምርመራ ወረቀት ይቅረብ” ሲሉ፣ የተከሳሽ ጠበቃ “ዓቃቤ ሕግ የለኝም ብሏል ባለው ውሳኔ ይሰጥ” ብሎ ሊያስረዳ ቢሞክርም፤ ዳኛ ልዑል “ጠበቃ ስነሥርዓት! አንዴ ትዕዛዝ ተሰጥቷል” በማለት ከገሰጹ በኋላ፤ “አሰራር ነው” በማለት ተከሳሽ ቴዲ አፍሮ መከላከል ሳያስፈልገው በነፃ እንዲሰናበት ወይንም ደግሞ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው ማስረጃ ጥርጣሬ ውስጥ የሚጥለው ከሆነ ይከላከል የሚል ብይን ለመስጠት ለሰኔ 27 ቀን 2000 ዓ.ም. በመቅጠር ችሎቱን በትነዋል።

 

ዓርብ ሰኔ 27 ቀን 2000 ዓ.ም.

ዓቃቤ ሕግ ኦሪጅናሉ ነው በማለት ያቀረበው የሰነድ ማስረጃ ሟች ደጉ ይበልጣል በ22/2/9 ዓ.ም. ሞቶ በ23/2/99 ዓ.ም. አስከሬኑ ተመርምሯል የሚል ሲሆን፣ ቴዎድሮስ የተከሰሰው በ23/2/99 ከሌሊቱ 8 ሰዓት ሟቹን ገድሎ አምልጧል የሚል ነው በመሆኑ ጠበቃው ደንበኛቸው በነፃ እንዲሰናበት ይጠይቃል። ዓቃቤ ሕግ የምኒልክ ሆስፒታል ስህተት እንጂ የእኔ ስህተት አይደለም፤ ማስተካከያ አመጣለሁ በማለቱ ማስረጃው ማስተካከያ ተደርጎበት ይቀርባል።

 

ለሁለተኛ ጊዜ ማስተካከያ ተደርጎበት የመጣው የሰነድ ማስረጃ ከዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ መቆጣጠሪያ እና ምርመራ መምሪያ በሸኚ ደብዳቤ የተላከ ሲሆን፣ ደብዳቤው “በ12/10/2000 ዓ.ም. በደብዳቤ ቁጥር 20307/ወ/መ/42 ሟች ደጉ ይበልጣል በ22/02/99 ዓ.ም. ሕወታቸው አልፎ በ23/02/99 ዓ.ም. የአስክሬን ምርመራ የተደረገላቸው መሆኑን የሚገልፅ በቁጥር 856/44/99 በ04/03/99 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ የላክንላችሁ የአስክሬን ምርመራ ውጤት ማስተካከያ ተደርጎ እንዲላክላችሁ መጠየቃችሁ ይታወቃል።

 

“በመሆኑም ሟች ደጉ ይበልጣል በ23/02/99 ዓ.ም. ሕወታቸው አልፎ በዕለቱ አስክሬናቸው ወደ አስክሬን ክፍል ገብቶ የአስክሬን ምርመራው በ24/02/99 ዓ.ም. የተደረገላቸው መሆኑን እያረጋገጥን፣ ስህተቱ የተከሰተው በወቅቱ የነበሩት የአስክሬን መርማሪ ባለሙያ ወደ ዋናው መዝገብ በሚያሰፍሩበት ወቅት በተከሰተ ግድፈት መሆኑን እየገለጽን ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ እንጠይቃለን።” የሚል ነው።

 

ከዚህ ሸኚ ደብዳቤ ጋር ተያይዞ የተላከው የአስከሬን ምርመራ የምስክር ወረቀት ሟች ደጉ ይበልጣል በ23/2/99 ዓ.ም. አስከሬኑ ወደ ምርመራ ክፍሉ ገብቶ በ24/2/99 ዓ.ም. ተመርምሮ ወጥቷል የሚል ነው።

 

የቴዲ ጠበቃም ደንበኛው የተከሰሰበት ቀንና ሟች የሞተበት ቀን ተመሳሳይ ባለመሆኑ ክሱ ውድቅ እንዲደረግና ደንበኛው እንዲለቀቅለት ቢጠይቅም፤ ዳኛው “መመርመር አለበት” በማለት ለሣምንት ቀጠሮ ሰጥተው ችሎቱን ከበተኑ በኋላ በጽ/ቤት በኩል የምኒልክ ሆስፒታል ባለሙያ ችሎት ተገኝተው ጉዳዩን እንዲያስረዱ ያዛሉ።

 

ዓርብ ሐምሌ 4 ቀን 2000 ዓ.ም.

ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) በቀረበበት ክስ ላይ ሁለት ዓይነት ቀን ያለው የሰነድ ማስረጃ ሰጥቷል የተባለው የዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ባለሙያ ፍርድ ቤት ቀርቦ እንዲያስረዳ በታዘዘው መሰረት የኩባ ዜግነት ያላቸው የአስክሬን መርማሪ ፍ/ቤት ቀርበው የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ ከውጭ በመጣ አስተርጓሚ ሥራውን የሠራው ፍርድ ቤቱ፣ ባለሙያውን ስለ ሟች አስክሬን ጠይቀዋል። አስክሬኑን የመረመሩት ሐኪም ሴት መሆናቸውንና አሁን አገር ውስጥ እንደሌሉ ገልጸው፣ አሁን በቦታው ላይ ያሉት ራሳቸው እንደመሆናቸው ጉዳዩን ማጣራታቸውን አስረድተዋል። የመጀመሪያዋ ሐኪም አስክሬኑን ሲመረምሩ ሟች ደጉ ይበልጣል በ23/02/99 ዓ.ም. ሕወታቸው አልፎ በዕለቱ አስክሬናቸው ወደ አስክሬን ክፍል ገብቶ የአስክሬን ምርመራው በ24/02/99 ዓ.ም. ተደርጎላቸዋል የሚል ማስረጃ መጻፋቸውንና ይኸው ማስረጃ ወደ መዝገብ ሲገለበጥ ሟች ደጉ ይበልጣል በ22/2/99 ዓ.ም. አስከሬኑ ገብቶ በ23/2/99 ዓ.ም. ተመርምሮ ወጥቶአል ተብሎ መጻፉን መስክረዋል።

 

ማስረጃው ከመዝገቡ ላይ ተገልብጦ ለፖሊስ መሰጠቱን ከተናገሩ በኋላ ፖሊስ ይህንኑ ማስረጃ እንዲስተካከልለት ሲጠይቅ ከመጀመሪያዋ ሐኪም የእጅ ጽሑፍ ላይ አይተው ሟች ደጉ ይበልጣል በ23/02/99 ዓ.ም. ሕወታቸው አልፎ በዕለቱ አስክሬናቸው ወደ አስክሬን ክፍል ገብቶ የአስክሬን ምርመራው በ24/02/99 ዓ.ም. ተደርጎላቸዋል የሚል ማስተካከያ እንደሰጡ ተናግረዋል።

 

ቴዲ አፍሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ችሎት የተናገረ ሲሆን፣ “የተከበረው ፍርድ ቤት ስለተሰጠኝ ዕድል በጣም አመሰግናለሁ! እኔ የማምነው ይህን ሁሉ ሰው በሚያይ እግዚያብሔር ነው። ግን አንድ ነገር መናገር እፈልጋለሁ። እኔ አንድም ሰው አልገደልኩም ሰውም አልገጨሁም። ነገር ግን በማላውቀው ነገር ሰብዓዊ መብቴ ተገፍፎ ቅማል እየበላኝ ሦስት ወር ታስሬያለሁ። ፍርድ ቤቱንም ሆነ የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት የምጠይቀው ጉዳዩን በሚገባ ተረድተው በነፃ እንዲሰናብቱኝ ነው።” ሲል ተደምጧል። በዚህን ሰዓት ወላጅ እናቱን ጨምሮ በርካታ ሰው ድምፁን አውጥቶ ሲያለቅስ ተሰምቷል። ዳኛው ጉዳዩን ገለልተኛ ሆነው በማየት ላይ መሆናቸውን አስረድተው የግራ ቀኙን ክርክር መርምረው ለሰኞ ሐምሌ 14 ቀን 2000 ዓ.ም. በነፃ ይሰናበት ወይም ደግሞ ይከላከል የሚለውን ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ሰጥቶ ተበትኖ ነበር።

 

ያልተለመዱ ሁነቶች – በቴዲ ችሎት

– የቴዲ አፍሮ ጉዳይ ፖለቲካዊ መምሰሉና ጠበቃው አቶ ሚሊዮን አሰፋ የኢህአዴግ ደጋፊና የምርጫ ቦርድ ጠበቃ ሆኖ፣ የቅንጀት አመራሮች እስር ቤት በነበሩበት ወቅት እስሩን ደግፎ ሞት ሊፈረድባቸው ይገባል እያለ በመንግሥት ራዲዮና በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በየቀኑ መግለጫ ሲሰጥ የነበረ ጠበቃ መሆኑ፤

 

– ሁለተኛ ወንጀል ችሎት የነበሩትና ለሁለት ዓመታት የዘለቀውንና የቅንጅት አመራሮች … የተከሰሱበትን ችሎት በቀኝ ዳኝነት ሲያስችሉ የነበሩት አቶ ልዑል ወ/ማርያም በድንገት 8ኛ ወንጀል ችሎት መገኘት፤

 

– ምኒልክ ሆስፒታል በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ኦርጅናል የአስከሬን የምርመራ ውጤትን ‘ተሳስቷል’ በሚል መቀየሩ፤

 

– ችሎት በሚኖርበት ጊዜ በርካታ ቁጥር ያላቸው ደህንነቶች ችሎቱን ማጨናነቃቸውና ችሎት ተከታታዩን ሰው ማስጨነቃቸው፤

 

– የቅንጅት አመራሮችን ሲጠብቁ የነበሩ የፌደራል እና የአዲስ አበባ ፖሊሶች ሳይታክቱ በችሎት በመገኘት ጥብቅ ቁጥጥር ማድረጋቸው፤

 

– ቃሊቲ ከገባ በኋላ ለብቻው መታሰሩ፤

 

– ከተወሰኑ ሰዎች በስተቀር ማንም እንዳይጠይቀው መከልከሉ፤ በመኪና ሰው ገጭተሃል በሚል ተጠርጥሮ ለታሰረ ሰው ያልተለመዱ ድርጊቶች ናቸው።

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 10 years ago on October 14, 2014
  • By:
  • Last Modified: October 14, 2014 @ 9:53 am
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar