www.maledatimes.com ብርቱካን በሊባኖስ ተረፈች ፣ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ብርቱካን በሊባኖስ ተረፈች ፣

By   /   November 16, 2014  /   Comments Off on ብርቱካን በሊባኖስ ተረፈች ፣

    Print       Email
0 0
Read Time:4 Minute, 31 Second

የማለዳ ወግ …
ብርቱካን በሊባኖስ ተረፈች ፣
አልማዝ በኦማን የአካል ጉዳተኛ ሆና ቀረች !

የተረፈችው የእህት ብርቱካን ጉዳይ …
በሃገረ ሊባኖሰ ቤሩት  ከ4ኛ ፎቅ ወድቃ የተረፈችው እህት ብርቱካን  ጤንነት የተስተካከለና ከድካም ህመሟ ሙሉ በሙሉ እያገገመች መሆኑን መረጃዎች ማምሻውን ደርሰውኛል ። የቆንስል ሃላፊዎች አልማዝን ሲያነጋግሯት በሊባኖስ ቆይታ ስራ መስራት እንጅ ወደ ሀገር ቤት መመለስ እንደማትፈልግ እንደገለጸችላቸው አምባሳደር ሐሊማ ሙሃመድ አጫውተውኛል። በቀጣይ ቀናትም ህክምና እየወሰደች ያለችበትን መካስድ ሆስፒታልን ለቃ እንደምትወጣ ፣ በቤሩት የቆንስል መጠለያ ሆና ህክምናና ጉዳይዋን እንደምትከታተል ተረድቻለሁ !

ተስፋ የቆረጡት ኢትዮጵያውያን አስተያየት …

    በብርቱካን ጉዳይ ዙሪያ ያነጋገርኳቸው ብዙ ነዋሪዎች የቆንስል ተዋካዮች ላይ እምነት እንደሌላቸው ይገልጻሉ ። እንደ አማራጭም የብርቱካንን ጉዳይ በጠበቃ አስይዘው ለመከራከር የሚቻልበትን ንገድ ለማፈላለግ ስራ መሰራት አለበት ሲሉ  ” የቆንስል ሃላፊዎችን ዲስኩር ማመን ትቶ የተለመደው የነዋሪውን ትብብር ማስተባበር ያሻል ” ይላሉ።  ለምን በመንግስት ተወካዮቻችን እምነት አጣችሁ?  ማለቴ አልቀረም ፣ ምላሻቸው ዘርዘር ያለ መረጃና ማስረጃ ያለው እውነት ይመስላል። አንድ ያሉኝን ብቻ ላንሳው  … በሃገራ ባንዴራ ስር ፣ በቆንስሏ በር በጥጋበኛ “ጀብራሬ” አረብ  እየተጎተተች ስትደበደብ የቆንስል ሀላፊዎች ምንም አለማድረጋቸው ፣  ከዚያም  ሃኪም ቤት በገባች በቀናት ልዩነት ” ራሷን በራሷ ገደለች !” መርዶ ነጋሪና ሬሳ ተቀባይና ላኪ ከመሆን ያለፈ ስራ የመብት ማስጠበቅ ስራ በቆንስል መስሪያ ቤቱ አለመሰራቱን ያጣቅሳሉ።  ከዚሁ ጋር በተዛማጅ ከአንድ ወር በፊት እዚያው ሊባኖስ “የአሰሪዋን ህጻን ልጅ አፍና ገድላለች! ” በሚል በፍርድ ውሳኔ ያልተሰጠው ጉዳይ በመገናኛ ብዙሃን ቀርቦ ነበር። በቀረበው መረጃ ስማችን ጎደፈ ። ዳሩ ግን የቀረበው መረጃ ኢትዮጵያዊቷ ወንጀለኛ አለመሆኗ ፍንጭ ሰጠ ፣ የራሳቸው ዜጎች ከሳሽ ባቀረበው መረጃና ማስረጃ ተመርኩዘው የተገላቢጦሹን አሳዩት ። ይህ ሁሉ ሲሆን የመንግስት ተወካዮቻችን ከሳሽን ወደ ተከሳሽነት የሚያሸጋግረውን መረጃ እንኳ ይዘው ታሳሪዋ ኢትዮጵያዊት እህት በዋስ መብቷ  ተጠብቆ በውጭ ሆና  እንድትከራከር አለማድረጋቸው በቆንስሉ የብርቱካን ክትትል ላይ የረባ ውጤት የማምጣት አቅም እንደሌላቸው ማሳያ ነው በማለት የሰላ ሂስና ወቀሳ ያቀርባሉ ።

የተስፈኞቹ ኢትዮጵያውያን አስተያየት …

    ” በቤሩት የቆንስል መ/ቤት ከበፊቱ የተሻለ ለውጥ ይታያል! ”  ያሉኝ ወገኖች ፣ ለውጥ ለመምጣቱና ለመታየቱ የሚያቀርቧቸው ጥቃቅን የቆንስል ግልጋሎት አሰጣጥ መረጃዎች ናቸው ።  ያም ሆኖ የመስራት አቅሙ የላቸውም ያሉኝ  የሚያነሱትን ” …የከዚህ በፊቱን የአለም ደቻሳና ሌላው ሌላው አሳዛኝ የመብት ጥበቃ ጉድለት “ያለፈው አለፈ ፣ ይሁን !”  ቢባል አሁን ድረስ እንዳልተሻሻሉ ብዙ ማሳያ አለ። ከወር በፊት  በነፍስ ግድያ ወንጀል ያለ ተጨባጭ መረጃ የታሰረችውን እህት ቆንስሉ አያማክሯትም ። ለዋስ መብቷን አላስጠበቁላትም።  ” በማለት “የቀረበውን የሰላ ሂስ ” ለውጥ አለ! ” ባዮች በተጨበጠ መከራከሪያ መላሽ ለመስጠት አልተቻላቸውም ።  ብቻ የቀረበውን ወቀሳ ሳያስተባብሉ ” በለውጥ ተስፋ ከማድረግ የተሻለ ነገር የለም! ”  በማለት የቆንሰል መ/ቤቱ የብርቱካንን ጉዳይ በቅርብ ተካታትሎ ውል እንደሚያስይዘው ያላቸውን ተስፋ አጋርተውኛል  !  …ቀጣዩ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ቢቸግርም ዛሬ የእህት ብርቱካንን በአሰቃቂ ሁኔታ መውደቅና ከከፋ አደጋ መትረፏ በሊባኖስ ቤሩት ካሉት ባለፈ በአለም ዙሪያ ሆነን ጉዳዩን በቅርብ ለተከታተልን ሁሉ እፎይታ ሆኗል  … ተመስገን ነው !  እናም ” ያገባናል ” ባዮች በእህት ብርቱካን ሰናይ ዜና ተደስተን ፊታችን ወደ ሌላዋ ግፉዕ ማዞር ግድ ብሎን  ወደ አልማዝን እንርዳ ” ዘመቻችን ፊታችን መዞራችን እውነት ነው!

የአካል ጉዳተኛዋ የአልማዝ ጉዳይ  …

   ህዳር 2 ቀን 2007 ምሽት በሊባኖስ  የብርቱካንን ከፎቅ መውደቅ አሳዛኝ ዜና ስሰማ በሌላኛው አረብ ሀገር በኦማን የመኪና አደጋ ደርሶባት የአካል ጉዳተኛ በሆነችው በእህት አልማዝ ጉዳይ ተወጥሬ ነበር።  ከተለያዩ አረብ ሃገራት እና በሃገር ቤት በማህበራዊ መገናኛዎች ተገናኝተን የተውጣጣን ወደ ስድስት የምንደርስ ወንድምና እህቶች  ባንድ እየመከርን ነው። አላማችን ከመረጃ ልውውጡ ባለፈ የወገናችን እንባ በተግባር መጥረጉም “ያገባናል !” ብለን ነው። የእህት አልማዝን እርዳታ ለማሳካት ማድረግ ስላለብን ጉዳይ እየመከርን ባለበት ወቅት ከቤሩት የብርቱካን አደጋና  “አትተርፍም!” የተባለ መረጃ ደረሰኝ … ሌላዋን የአረብ ሃገር ኦማን ጉስቁል እህት አልማዝን አሰብኳት …

    እህት አልማዝ የአረብ ሃገሩ ስደት ሲነሳ ከመንግስት ጀምሮ እስከ ግለሰብ የእኛ ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ ድጋፍ እህቶቻችን አደጋ ላይ ጥሏቸዋል።በህግ ሽፋን ተሰጥቷቸው በሚንቀሳቀሱ ወሮበላ ህግ ይጣሳል ፣  ለህዝብ ቆመናል በሚሉ የመንግስት ተቋማት ህግ ይጣሳል ፣  በመልካም አስተዳደር እጦት ፣ በሙስና  ህይወታችን ከፍቷል ፣ በተለያያየ መንገድ በአረበወ ሃገራት ለገነነው “ዘመናዊ ባርነት ” ድጋፍ እያደረግን እያበረታታን ነው ። ይህን ማለቴ ያለነገር አይደለም ፣ በአረቡ ሃገር በኦማን አካሏ ተሰናክሎ  የእኛን እርዳታ ጠባቂ የሆነችውን እህት አልማዝ አበሳ አስታውሼ ብዙውን አውጥቸ አወረድኩት …

    …አልማዝ አንድ ፍሬ ጉብል ሳለች ካላቻ ጋብቻ   ትዳርን ሳታውቀው መስርታ ልጅ ወልዳ ነበር ፣ ብዙም ሳይቆይ ጉብሏ እናት ሆነች ፣  ኑሮ አልሞላ አልሳካ ብሏት ወደ አረብ ሀገር ወደ ኦማን ተሰደደች … ሙሉ አካሏን ይዛ ለስራ ብላ በራ ከሄደችበት ኦማን ሞስካት ብዙም ሳትቆይ ለመኪና አደጋ ተጋለጠች ፣  ሆስፒታል ገባች ፣ ለወራት በህክምና ስትረዳ ብትቆይም አዕምሮዋ ፣ እግሯና እጇ ብሎም መላ አካሏ የከፋ ጉዳት ደረሰባቸው ፣ አይሆኑ ሆነች: (  ከሃገር ቤት ጀምሮ በአረብ ሀገራት ብርቱ መረብ ያላቸው ደላሎች እህት አልማዝ ሆስፒታል ከገባች በኋላም በጉዳቷ ለመጠቀም መስገብገባቸውን ጠልቆ መረጃ መሰብሰብ አሞኛል ፣ ዛሬ ወደ ክፉዎች ባለ ጊዜ ደላላ ባለጸጎች መሰሪ ምግባር ዳሰሳ አልገባም !  … እህት አልማዝ በተስፋ አቢሲኒያ በጎ አድራጊ ቡድን  አባላት ፣ በተለይም በመስራቹ ብርቱ ወንድም በወዳጀ በመሳይ አክሊሉ ( በኑቢያ ኩሽ ቀዳማዊ  ) እና በወዳጆቹ ብርታት  በአሳር በመከራ ሃገር ቤት ገብታለች ። መቄዶንያ የአረጋውያን ደጋፊ በጎ አድራጊ ቡድን ትብብርም መጠለያም ተሰጥቷታል ።  … እህት አልማዝ እዚህ ላይ ደርሳለች …  ይህም ተመስገን ነው!

   ይህም ሁሉ ሆኖ የአልጋ ቁራኛ የሆነችው አልማዝ ” ከህመም ጉዳቷ የምታገግምበት ተስፋ አለ ” በመባሉ የእርዳታ ስራ ተጀምሯል ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በተጀመረው እርዳታ እዚህ ሳውዲ አረቢያ ውስጥ ያለውን እርዳታ ለማስተባበር ሃላፊነት ከወሰድኩ ቀናት ወዲህ ወገኖች አልማዝን ለመርዳት ያሳዪት መነቃቃት እጅግ በጣም አበረታች ሆኖ ቀጥሏል። በኮንትራት ስራ በየአረቡ ቤት የሚሰሩ እህቶቸ የ “ነግ በኔ ” ብለው በሰብአዊነት እያደረጉት ያለው መተባበር ውስጥን ስሜት የሚያረካ ለመሆኑ እማኝ ለመሆን ታድያለሁ  !  የቤት ቆሻሻ ለመጣል መውጫ ቀዳዳውን ፈልገው ያላቸውን ለአልማዝ ለማካፈል ያሳዩት ቅንነት ፍጹም በቃላት ልገለጽ የማይቻለኝን ኩራት፣ በእህቶቼ እንድጎናጸፈው ዘንድ  ምክንያት ሆኖኛል  ! ድምጻዊ  ጆሲ እንደ ሀውስ ያን ሰሞን እርዳታ ለማሰባሰብ ሲሞክር በገጠመውና በሆነው በግኖ ይመስለኛል   ” ለመስጠት መሰጠት ያስፈልጋል! ”  ማለቱ በእኔም ላይ ደርሶ  እውነት ነው ብያለሁ  ! ለእኔ እርዳታ ማድረግ ትርጉሙ ገንዘብ መስጠት ብቻ አይደለም ፣ ቀና ማሰብ ፣ መረጃ መለዋወጥ ፣ ሌላ ተዛማች ተጎጅውን የሚደግፍ ስራ መስራት ፣ የሚረዳን አለመቃወም ፣ ገንዘብ  ከመስጠት ባለፈ ለተጎጅው ወገን ወገናዊ አብሮነት  ፍቅር መግለጫ ነው… ባይ ነኝ  !

    ለማንኛውም ብርቱካን በሊባኖስ ተረፈች ፣ እሰየው ነው!   እህት አልማዝ በኦማን ተሰናክላ እንዳትቀር ወገናዊ ትብብራችን ትሻለችና እናስብበት !  በዚህ የበጎነት መንገድ በመጓዝ በጠና የተጎዱ ወገኖቻችን  በመደገፍ ልንታደጋቸው ካልቻልን ከንፈር መምጠጡ ብቻ እንዳላዋጣን ከእኛ በላይ የሚያውቀው የለም ! እናም የዜጎቹን መብት እንዲያስከብር መንግስትን ስንወተውት የዝሆን ጀሮ ሰጥቶ አልሰማን ቢልም ጩኸት በደላችን እስኪሰማ እየጮህንም ቢሆን በመደጋገፉ የተጎዱትን እየነቀስን በማውጣት የቻልነውን መስራት የዜግነት ውዴታ ግዴታ ነው ባይ ነኝ  !

ሁሉም ለበጎ ነው  !

ነቢዩ ሲራክ
ህዳር 5 ቀን 2007 ዓም

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 9 years ago on November 16, 2014
  • By:
  • Last Modified: November 16, 2014 @ 11:35 am
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar