www.maledatimes.com ግፍና አፈና ዐመጽን ይወልዳሉ! - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ግፍና አፈና ዐመጽን ይወልዳሉ!

By   /   December 24, 2014  /   Comments Off on ግፍና አፈና ዐመጽን ይወልዳሉ!

    Print       Email
0 0
Read Time:9 Minute, 57 Second

ግፍና አፈና ዐመጽን ይወልዳሉ!

የዐመጸኛ አፍ ጥልቅ ጉድጓድ ነው (መ. ምሳሌ ም. 22፣ ቁ. 14)

 

ከያሬድ ኃይለማርያም

 

ብራስልስ፣ ቤልጂየም ታኅሣሥ 10፣ 2007

 

ሰብአዊ መበቶችን በመጣስ፣ ግፍ በመፈጸምና አፈናን በማጠናከር እደሜ የሚሸምት የአገዛዝ ሥርዓት የእያንዳንዱን ሰው መንፈሳዊና አካላዉ ጥንካሬ የማዳከም፣ ቅስምን የመስበርና ፍርሃትን የማንገስ ከፍተኛ አቅም እንዳለው ሁሉ በብሶት የሚወለዱ፣ እምቢኝ ለግፈኞች፣ እምቢኝ ለአንባገነኖች፣ እምቢኝ ለነጻነቴ የሚሉ መንፈሰ ጠንካራ ጀግኖችንና ታጋዮችንም ይወልዳል:: የአለማችን ስመ ጥርና ዘመን የማይረሳቸው የነጻነት ታጋዮች እነ ማህተመ ጋንዲ፣ ማርቲን ሉተር ኪነግ፣ ማንዴላ፣ ኡንግ ሳን ሱ ኪ እና ሌሎችም ብዙዎች የፈለቁት በብሶት ከተሞላ፣ ጭቆና ካንገሸገሸውና በአፋኝ ሥርዓት ከታመቀ ማኅበረሰቡ ጉያ ነው:: አንድን ማኅበረሰብ በአፈሙዝ፣ በሕግና በገንዘብ ኃይል ጭፍሎቆና አፍኖ ማቆየት የሚቻለውም ለተወሰነ ጊዜ ብቻ መሆኑን የእነዚህ ታጋዮች ገድልና የአለም ታሪክም ይመሰክራል:: አንድ ሕዝብ በላዩ ላይ ገዢዎች እየተፈራረቁበት ረዘም ላለ ጊዜ በአገዛዝ ሥርዓት ሥር ሊቆይ ይችል:: ይሁንና እድሜ ልክ የገዛ አፋኛ ሥርዓት ግን የለም:: ሥርዓቱም እንደ ድርጅት፣ ሹማምንቱም እንደ ሰው የጉብዝና እድሜያቸው የተወሰነ ነው:: የአፈናን ስልት በመለዋወጥና ሸምቀቆውን በማጥበቅም እድሜን ማራዘም የሚቻል ቢመስልም በተቃራኒዉ ውድቀትንም ያፋጥናል:: ግፉ እየበረታና የመብት ጥሰቱም መረን እየለቀቀ በሄደ ቁጥር የሕዝብ ትእግስት ይሟጠጣል:: ሕዝብ መቆጣት ከጀመረና ቁጣውም ወደ አደባባይ አመጽ በተቀየረ ጊዜ የግፍ አገዛዝ ወደ መቃብር፣ ግፈኞቹም ወደ ዘብጥያ እንደሚወርዱ እርቀን ሳንሄድ ባለፉት አምስትና አሥርት አመታት ውስጥ በአለም የታዩ ሕዝባዊ ነውጦችንና ያስከተሉትን መዘዝ ማጤን በቂ ነው::

ትልቁ ጥያቄ በግፍ አገዛዝ ውስጥ ያለ ሕዝብ መቼ እና ብሶቱስ ምን ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው የሚቆጣው? መቼ ነው ቁጣውንስ በየመንደሩ ከማጉረምረም አልፎ ባደባባይ የሚገልጸው? ቁጣውስ ወደ አመጽ ሊያመራው የሚችለው በምን ሁኔታ ነው? የሚለው ነው:: የሕዝብ ቁጣ ወደ አመጽ የሚለወጥበት ጊዜና ደረጃው የሚለካው በተለየ ሳይንሳዊ ቀመር ስላልሆነ መቼና በምን ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችል እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቸግራል:: ይህ አይነቱ ሁኔታ በእያንዳንዱ ማኅበረሰቡ ባህላዊ፣ ኃይማኖታዊና ማኅበራዊ አመለካከቶችና የፖለቲካ ንቃተ ህሊና ላይ ይወሰናል:: በትንሽ በትልቁ አደባባ እየወጣና በሚሊዮን የሚገመት የመንግሥትና የሕዝብ ንብረትን እያወደመ ተቃውሞውን የሚገልጽ ሕዝብ አለ:: በሌላ መልኩም አገሩን ቢሸጡበት፣ መሬቱን ቢነጥቁት፣ ሚስቱን ቢያስጥሉት፣ ልጆቹን ቢደፍሩበት፣ ቢገድሉበት፣ ቢያስሩበትና ቢያፍኑበት፣ ቤቱን በላዩ ላይ ቢያፈርሱበት፣ ቀየውን ለቱጃሮች ሰጥተው ቢያፈናቅሉት፣ ግብር እየከፈለ ያስተማራቸውን ልጆቹንና አመራቹን ኃይል እያዋከቡ ከአገር ቢያሰድዱበትና ለባርነት ቢዳርጉት፣ ከሰው ተራ አውርደው በየጎዳናው ቢጥሉትም ‘አዬ ጉድ፣ አዬ ጉድ’ ከማለት ባለፈ ቁጣውን የማያሳይም ሕዝብ አለ:: በከፋ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ታዋቂ የነበሩት ሟቹ ጠ/ሚ መለስ ያረፉ ወቅት አስከሬናቸውን ይሳለሙ ከነበሩ ሰዎች በኑሮው እጅግ የተጎዳና የተጎሳቆለ አንድ የጎዳና ተዳዳሪ በመንግሥት የቴሌቪዥን ማሰራጫ ሃዘኑን የገለጸበት መንገድ ጥሩ ማሳያ ሊሆን ይችላል:: የአዞ እንባውን እያነባ “እኔ እኮ እሳቸውን ተማምኜ ነው ጎዳና ላይ የማድረው” ነበር ያለው::

በሳንቲም ደረጃ የዋጋ ጭማሪ ተደረገብኝ ብሎ ወደ አደባባይ እየደጋገመ የሚወጣውን የኬኒያን ሕዝብ ቁጣ ለማየት በሚያዚያ ወር 2011 (እ.ኤ.አ) የነዳጅ ዋጋ ማሻቀብን ተከትሎ የተከሰተውን የኑሮ ውድነት በመቃወም በናይኖቢ የተካሄደውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ማየት ይቻላል:: እኛ ዘንድ የነዳጅ ዋጋ ስንት ጊዜ አሻቀበ? በእያንዳንዱ የእለት ተዕለት መገልገያ ቁሳቁሶች ላይ በምን ያህል መጠንና ስንት ጊዜ የዋጋ ንረት ታየ? የቤት ኪራይ፣ የትራንስፖርት፣ የጤና አገልግሎት፣ የመድሃኒቶች እና ሌሎች መሰረታዊ አቅርቦቶች ዋጋስ በስንት እጥፍ ናረ? እኛስ ስንት ጊዜ ቁጣችንን ገለጽን? በኑሮ መማረራችንንስ በምን መልኩ ለገዢዎቻችን አሳየን? ከኑሮ ዋስትና ማጣት ባሻግር የሹመኞች ከሕግ በላይ መሆን የዜጎችን በሕገ-መንግሥቱ የተደነገጉ መሰረታዊ የፖለቲካና የሲቪል መብቶችንና ነጻነቶችንም ትርጉም አልባ ሲያደርጋቸው እያየን ምን አደረግን? ለዚህም ነው የሕዝብ ብሶትና ምሬት የት ደረጃ ላይ ሲደርስ ቁጣ ወደተቀላቀለበት ተቃውሞ ሊያመራ እንደሚችል ሳይንሳዊ በሆነ ቀመር ማረጋገጥ ወይም መገመት የማይቻለው:: ምክንያቱም ግፍና በደሉን የተሸከመው ሕዝብ ያለው የታጋሽነት ልክ፣ ሆደ ሰፊነቱ፣ አርቆ አሰተዋይነቱ፣ የተዋጠበት የፍርሃት ጥልቀት ወይም ሌሎች ስነ-ልቦናዊ ሁኔታዎች ናቸው ይህን የሚወስኑት:: በዛሬዎቹም ሆነ በትላንት ገዢዎቹ ጭካኔና የማስተዳደር ብቃት ማነስ የተነሳ ለከፋ ድህነት የተጋለጠውና በልቶ ማደር ፈተና የሆነበት የኢትዮጵያ ሕዝብ ምሬቱንም ሆነ ተማጽኖውን የሚያሰማው ለፈጣሪው ብቻ ነው:: ሲመረውም ‘ምነው ዝም አልክ? ወይ ፍረድ ወይ ውረደ’ እያለ ካምላኩ ጋር መሟገት ይቀለዋል:: ትንሽ ሲደሰትም ‘ተመስጌን ይችን አትንሳኝ’ እያለ የነገን እጣፈንታውን እያሰላሰለ ፈጣሪውን ያመሰግናል:: ስለዚህ መንግሥት በሕዝብ ላይ ያሻውን ቢያደርግም ሕዝብ የልቡን የሚወያየውም ሆነ ይግባኝ የሚለውም ከመንግስት ዘንድ ሳይሆን ከፈጣሪው ጋር ነው:: ይህ አይነቱ የኅብረተሰብ ምላሽ ገዢዎችን ያማግጣል፣ ያሻቸውን እንዲያደርጉም ያበረታታል፣ ሕዝብን እንዲንቁና እራሳቸውንም ከሕግ በላይ አድርገው እንዲያስቡ ያደርጋል::

በዚህ አይነት ማኅበረሰብ ውስጥ ትልቁ ቀውስና ፖለቲካዊ ነውጥ የሚጀምረው የገዢዎቹ መረን መልቀቅ እየበረታ፣ የሕዝቡም ክፌት እየገነፈለ ሕዝብ የሚጠብቀው የፈጣሪው ምላሽ ግን የዘገየ ዕለት ነው:: ያኔ የሕዝብ ትግስት ይሟጠጣል፣ ሰፊውም ሆድም በቂም፣ በክፌትና በጥላቻ ይሞላል፣ አርቆ አሰተዋይነቱም ወደ ግብታዊነትና ንዴት ይለወጣል፣ ፍርሃቱም ተስፋ መቁረጥ ወደሚያሰከትለው ጨለምተኝነትና ጀብደኝነት ይቀየራል:: እዛ ደረጃ ከተደረሰ በኋላ የሚሆነውን መገመት አይከብድም:: በቅርቡ በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች በተለይም በቱኒዚያ፣ በግበጽ፣ በሊቢያ፣ በዩክሬንና ሌሎች አገሮች የተከሰቱት የሕዝብ ቁጣዎች ለዚህ ጥሩ ማሳያዎች ናቸው:: ባለፉት አራት አመታት ውስጥ በሕዝብ ቁጣና አመጽ ሲናወጡ የከረሙትን፣ በንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመቶችን ያሰተናገዱትንና የመንግሥታትም ለዉጥ የታየባቸውን የአረብ አገራት መለስ ብለን የተመለከትን እንደሆነ አብዛኛዎቹ በቡዙ መልኩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሚገኝበት ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ሁኔታዎች እጅግ በተሻለ ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው:: ጥሩ የነፍስ ወከፍ ገቢ ያላቸው፣ ሕዝብ በምግብ አጦት የተነሳ በርሃብ የማይሰቃየባቸውና የማይሞትባቸው፣ እጅግ የተሻለ የእሌክትሪክ፣ የውሃ፣ የነዳጅ፣ የጤና፣ የትምህርት፣ የኢንተርኔትና ልሎችም መሰረታዊ አቀርቦቶች የተሟሉባቸው አገሮች ናቸው:: ከፖለቲካ ነጻነቱም አንጻር ብዙዎቹ ከኢትዮጵያ በተሻለ ሃሳብን የመግለጽ፣ የመደራጀት፣ ባደባባይ የመሰብሰብና ተቃውሞንም የመግለጽ ነጻነትም የሚታይባቸው ናቸው:: ይሁንና በእነዚህ አገራት ውስጥ ሕዝብ ሙሉ በሙሉ የሥልጣን ባለቤት ባለመሆኑና ብለሹ በሆኑት የፖለቲካ ሥርዓቶች እጅግ ተከፍቶ የቆየ ስለነበር በቀላሉ ወደ አመጽ ሊያመራ ችሏል:: አንዳንዶቹም ዘላቂ ለሆነ ቀውስ መዳረጋቸው ይታወቃል::

በእነዚህ አገራት የሕዝብ የነጻነትና የመብት ጥያቄ የሥርዓት ለውጥን ለማምጣት ወደሚችልበት ሕዝባዊ አመጽና ኃይል ወደታከለበት ግጭት እንዲያመራ የውጪው አለም ከፍተኛ ሚና እንደተጫወተ አይካድም:: ቢሆንም ዋነኛው ምክንያት ግን የተጠራቀመው የሕዝብ ክፌትና ብሶት ነው:: በእነዚህ አገሮች በተነሱት የሕዝብ አመጾችና በተከሰቱት የፖለቲካ ቀውሶች ማን አተረፈ የሚለው እራሱን የቻለ ሰፊ የመወያያ ርዕስ ነው:: ነገር ግን በግልጽ እንደሚስተዋለው የመጀመሪያዎቹ ተጠቂዎች ሕዝብን ሲያሰቃዩ፣ ሲያፍኑ፣ ሲገደሉና ሲያስገደሉ፣ ሚሊዮኖችን እያደኸዩ ሃብት ሲያካብቱ የነበሩ ሹማምንትና ዙሪያቸውን የከበቡዋቸው ባለሃብቶች ለመሆናቸው በጋዳፊና በሙባረክ እንዲሁም በዙሪያቸው የነበሩ ሰዎችን እጣ ፈንታ ማየት በቂ ነው:: ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሕዝብ ክፌትና ብሶት፣ የአፈናው ደረጃ፣ የኑሮ ውድነት፣ የመሰረታዊ አቅርቦቶች መጓደል፣ የባለሥልጣናቱ ሙሰኝነትና ከሕግ በላይ መሆን፣ የሥራ አጡ ቁጥር፣ የድኅነቱ ደረጃ፣ ተሰፋ ማጣትና ጨለምተኝነት በምንም መልኩ ቢሆን ከሌሎች በአገዛዝ ሥርዓት ውስጥ ከሚገኙ አገሮች ጋር የሚወዳደር አይደለም:: የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ ከገጠሙት ክፉና አንባገነናዊ ሥርአቶች ውስጥ የወያኔን አገዛዝ የተለየና የከፋ የሚያደርገው የዘረኝነት ፖሊሲው ብቻ ሳይሆን በአገር ሃብትና ንብረት የከበሩ የንግድ ድርጀቶች ባለቤትና ከታጋይነት ወደ ሚሊየነርነት የተቀየሩ ቱጃር ባለሥልጣናትንና የጦረ አዛዦችን የያዘ ድርጅት መሆኑ ነው:: ብሶት የወለዳቸው የወያኔ ባለሥልጣናት ዛሬ በተራቸው ሕዝብን ሆድ ከማስባስ አልፈው ማቆሚያ ወደማይኖረው የእርስ በርስ ግጭት፣ አመጽ፣ ቀውስና የዘር ቁርሾ ውስጥ እንዲገባ እየጋበዙት ነው::

የኢትዮጵያ ሕዝብ የወያኔ ሥርዓት አራሱን እንዲያርቅና አገሪቱንም ከተንጠለጠለችበት የገደል አፋፍ እንዲታደግ ከሃያ ዓመታት በላይ እድል ሰጥቶታል:: ፍጹም ሰላማዊና ስልጡን በሆነ መልኩም በ1997ቱ ምርጫ የማስጠንቀቂያ ደውሉን አቃጭሏል:: ይሁንና ይህን ማስጠንቀቂያ የወያኔ ባለሥልጣናት የተረጎሙበት መንገድ ሕዝብ ማስተላለፍ ከፈለገው መልዕክት እጅቅ የራቀና በተሳሳተ መልኩ መሆኑን ለመረዳት ምርጫውን ተከትሎ የወሰዱትን የኃይል እርምጃና ከዛም ወዲህ ያሳዩትን አፈናውን በሕጎች አጠናክሮ የመቀጠል ፍላጎት ማጤን በቂ ነው:: ለሕዝብ ያላቸውን ንቀትና እብሪትም በደንብ ያመላክታል:: ከዚህ በመነሳት ከፊታችን የሚጠብቀን ምርጫ ሊኖሩት የሚችሉትን ሁለት ገጽታች መገመት ይቻላል::

  • የመጀመሪያው ወያኔ ከዚህ ቀደም እንደነበሩት ምርጫዎች ብቻውን ተወዳደሮ ወይም አጃቢ ተቃዋሚዎችን አስከትሎ ያለምንም ችግር 99% ወይም ተቀራራቢ በሆን አሃዝ ጠቅልሎ ይቀጥላል:: አለያም የተወሰኑ ግጭቶችን ባስከተሉ ተቃዉሞዎች ውስጥ አልፎ ከ 10% እስከ 20% መቀመጫን ለተወሰኑ ተቃዋሚዎች ለቆ የፖለቲካ መዘውሩን እንደያዘ ተደላድሎ ይቀጥላል::
  • ሁለተኛው ግምት ደግሞ በተቃዋሚዎች አበሮ መስራት ላይ በተመሰረት ጥንካሬና ከሕዝብ በሚገኝ ድጋፍ ምርጫው ለምክር ቤት ወንበር ሽሚያ ሳይሆን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ከአንባገነናዊ ሥርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማላቀቅ፣ ሕዝብንም የሥልጣን ባለቤት ለማድረግና እና አገሪቱንም ካንዣበበባት አደጋ ለመታደግ የሚደረግ የነጻነት ወይም ሞት ትግል ይሆናል::ይህ አይነቱ በምርጫ ስም የሚደረግ ማደናገሪያ ከቀዝቃዛው የአለም ጦርነት ማብቂያ ወዲህ በበርካታ የሦስተኛው አለም አገሮች ተደጋግሞ የሚታይ ክስተት ሆኗል:: ባለፉት አስርት አመታት እንደተስተዋለው ምርጫ አንድ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባትና የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት ለማረጋገጥ የሚረዳ መንገድ የመሆኑን ያህል ድሃ ሕዝብን አፍኖ ለመግዛትና የአንባገነኖችንም እድሜ ለማራዘም እያገለገለ መሆኑን ነው:: በዚህ ሂደት ውስጥ ዋነኛ ተዋናዮቹ የአገዛዝ ሥርዓቶቹ ብቻ ሳይሆኑ የምዕራቡ አለም እና የአለም ከበርቴዎችም ናቸው:: የቅኝ ግዛት ታሪክ ካከተመ በርካታ አመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም አገሮችን በቅኝ ለመግዛት የምዕራቡ አለም ቆርጦ የተነሳባቸው ዋነኛ የኢኮኖሚና የፖለቲካ መንስዔዎች ዛርም እጅግ በከፋና ባፈጠጠ መልኩ ይታያሉ::ሁለተኛው ሂደት ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ማካሄድ የሚቻለው ነጻ የፖለቲካ መድረክ፣ ነጻነት የሚሰማውና የሌሎችንም ነጻነት የሚያከብር መንግሥት፣ በነጻነት ማሰብና ሃሳቡንም በነጻነት መግለጽ የሚችል ሕዝብ፣ በነጻነት መደራጀትና መንቀሳቀስ የሚችሉ ጠንካራና ተፎካካሪ የፖለቲካ ኃይሎች እና ነጻ ተቋማት በተለይም ገለልተኛ የሆኑ ምርጫ አስፈጻሚዎችና የፍትሕ ተቋማት ሲኖሩ ብቻ ነው ከሚል እምነት ይመነጫል:: ይህ ደግሞ በወያኔ ዘመን እስካሁን ያልታየና ወደፊትም እነዚህ ነገሮች በሂደት ሊሟሉ ስለመቻላቸው ምንም አይነት የሚታዩ ምልክቶች፣ ዋስትና ወይም መተማመኛ ሊሆን የሚችል ነገር የለም:: እንዚህ ፖለቲካዊና ተቋማዊ አደረጃጀቶችና መሰረታዊ ነጻነቶች ጭርሱኑ በሌሉበት ሁኔታ ነጻ ምርጫ ሊካሄድ አይችልም:: ያለፉት አይነት ምርጫዎች ቢካሄዱም ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ መገመት ቀላል ነው:: ሰለዚህ ምርጫው ሊሆን የሚገባው በቅድሚያ የሕዝብን ነጻነት ማረጋገጥ ወይም በግዞት ውስጥ ሆነን ወያኔ የመረጠልንን ሕይወት መቀጠል ነው:: የእነሱን ቋንቋ ልጠቀምና ባጭሩ “ሃርነት ወይስ ባርነት”::ከወያኔ የአገዛዝ ሥርዓት ለመላቀቅ በ1997ቱ ምርጫ ወቅት ታይቶ የነበረው የሕዝብ ተነሳሽነትና የተጀመረው ሰላማዊ ትግል ሥርዓቱ በወሰደው የጭቃኔ እርምጃ ቢቀለበስም በአገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ትቶት ያለፋቸው በርካታ ነገሮች አሉ:: ከዚህ ሂደት ትምህርት በመውሰድ የተጀመረውን ሰላማዊ ትግል ለመቀጠል በአገር ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ባርቲዎች እየከፈሉት ያሉት መስዋትነት ሊበረታታና ሊደገፍ የሚገባው ነው:: በተለይም የሰማያዊ ፓርቲ አባላት፣ ደጋፊዎችና አመራሮች እንዲሁም የዘጠኙ ፓርቲዎች ጥምረት በመባል የሚጠሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችና አባላት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያሳዩ ያሉት እንቅስቃሴና ከሥርዓቱ ጋር የገጠሙት የእምቢተኝነት ግብግብ ሰላማዊ ትግልን በኢትዮጵያ ውስጥ ማካሄድ እንደሚቻል ብቻ ሳይሆን መጀመሩንም ያረጋግጣል:: ሕግን ማክበርና በሕግ የበላይነት ማመን ከእያንዳንዱ ዜጋ ይጠበቃል:: ግድታም ነው:: ይሁንና ዜጎች በዚህ ግዴታ የሚወሰኑት እያንዳንዱ ሕግ የሕገመንግሥቱን የበላይነት እስካልጣሰና በውስጡም የተደነገጉትን መሰረታዊ መብቶችና ነጻነቶች ባረጋገጠ መልኩ እስከ ተደነገገና በአግባቡም እስከ ተተገበረ ድረስ ብቻ ነው:: ልክ እንደ ደቡብ አፍሪቃው አፓርታይድ ሕግን የማፈኛ መሳሪያ አድርጎ በሚጠቀም ሥርዓት ውስጥ የሚደረግ ሰላማዊ ትግልና ሕዝባዊ እምቢተኝነት የዜጎችን መሰረታዊ ነጻነቶችን ለሚያጠቡ ወይም ጭርሱኑ ለሚያግዱ ሕጎች፣ ደንቦችንና መመሪያውችን አለመገዛትንም ይጨምራል:: በአገር ውስጥ ያለውም ሆነ ከአገር ውጭ ያለውና የአገሩ ጉዳይ የሚያሳስበው ኢትዮጵያዊ ለእነዚህ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ብዙ መከራዎችን እየተቀበሉ አንባገነናዊ ሥርዓትን ታሪክ አድርጎ ለማስቀረት ከሚታገሉ መንፈሰ ጠንካራ ኢትዮጰያዊያን ጎን በመቆም ትግሉ እንዳይደናቀፍና አገሪቱም አስከፊ ወደ ሆነ ደም አፋሳሽ ሁኔታ እንዳታመራ ድጋፍ ሊያደርግላቸው ይገባል::ያሬድ ኃይለማርያም
  • አንባገነናዊ ሥርዓትን ታሪክ አድርገን ለማስቀረት ከሰላማዊ ታጋዮቹ ጎን እንቁም! በቸር እንሰንብት!
  • ይህ የሁለተኛው ሂደት በሕዝብ እምቢተኝነት ላይ የተመሰረተና ፍጹም ሰላማዊ በሆነ የትግል ሂደት ሊመጣ የሚችል ስኬት ነው:: ብዙዎች በሕዝብ እምቢተኝነት ላይ የተመሰረተን ሰላማዊ ትግል ከምርጫ ውድድር ጋር ሲያምታቱት ይሰታዋል:: በአገሪቱ ውስጥ ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች አለመሟላት ወይም በነጻነት የመደራጀት፣ የመሰብሰብ፣ ሃሳብን የመግለጽና ተቃውሞ የማድረግ መብቶችና ነጻነቶች አለመኖርን ለሰላማዊው ትግል ማክተም እንደ አስረጂነት ያቀርቡታል:: ይህ እጅግ የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው:: የእነዚህ ሁኔታዎች አለመሟላት የሚያሳየው በምርጫ ሂደት ተወዳድሮ ሥልጣን መያዝ የሚቻልበት እድል አለመኖሩን በቻ ነው:: እነዚህ ነጻነቶች በተከበሩበትና ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችሉ የተወሰኑ ነገሮች እንኳን ከተሟሉ ሂደቱ ሰላማዊ ትግል መሆኑ ቀርቶ በፓርቲዎች መካከል የሚደረግ ውድድር ነው የሚሆነው:: በአሜሪካም ሆነ በሌሎች ዲሞከራሲያዊ ሥርዓት በጎለበተባቸው አገሮች ፓርቲዎች ለሥልጣን ይወዳደራሉ እንጂ ሰላማዊ ትግል ውጥስ አይደለም ያሉት:: ብዙዎቹ ይህን የትግል ምዕራፍ ከዘጉ ዘመናቶች ተቆጥረዋል:: ሰላማዊ ትግል የሚካሄደው እነዚህ ነጻነቶች ፈጽሞ በሌሉበት፣ አፈና እና ጭቆና በተንሰራፋበት የአገዛዝ ሥርዓት ውስጥ ነው:: ትግሉም ጠመንጃ ያነገበና በኃይል ሕዝብን በሚደፈጥጥ አካል እና በልበ ሙሉነትና ከፍ ባለ የመንፈስ ልዕልና ተሰባስበው ሕዝብንና አገራዊ ዕራእያቸውን ጋሻ በማድረግ ያለ ነፍጥ ሥርዓቱን በሚያርበደቡዱ የሰላም መልዕክተኞች መካከል ነው:: አንደኛው ወገን ይገድላል፣ ያስራል፣ ያሰቃያል:: ሌላኛው ወገን እየሞተ፣ እየታሰረ፣ እየተደበደበና እየተዋከበም ስለ ነጻነት፣ ስለ ፍትሕ፣ ስለ እኩልነት፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ ሰላምና ስለ ሕግ የበላይነት በአደባባይ ይዘምራል፣ ይሰብካል፣ ሕዝብን ያደራጃል፣ ይታገላል::
  • የምዕራቡ አለምና ከበርቴዎቹ የቅኝ ግዛት ፖሊሲዎቻቸውን ለማስቀጠልና ጥቅሞቻቸውንም በእነዚህ ድሃ አገሮች ላይ፣ በተለይም በአፍሪቃ አገሮች ውስጥ እንደተጠበቀ ለማቆየት እንደ አማራጭ ከወሰዱት መንገድ አንዱ ከትቢያ እያነሱ ወደ ስልጣን እንዲመጡ የረዷቸውን የጫካ ሽፍቶች በስልጣን ለማቆየት በገንዘብና በጦር መሳሪያ ከሚያደርጉላቸው ድጋፍ ባሻገር አንጻራዊ የሆነ የፖለቲካ መረጋጋትም እንዲኖር የእነዚህን አፋኝ ቡድኖች እድሜ በይስሙላ ምርጫ እንዲታጀብ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ማድረግ ነው:: ይህ አካሄድ ሁለት ግቦች አሉት:: አንዱ እነዚህ አንባገነኖች ሙሉ በሙሉ በምዕራቡ አለም ድጋፍ ነው የቆሙት ወደሚል ድምዳሜ ከተደረሰ የዳግም ቅኝ ግዛት እቅዳቸውን ከማጋለጡም በላይ የምዕራቡ አለም ከአንባገነኖችና የሰብአዊ መብቶችን በገፍ ከሚጥሱ ቡድኖች ጎን አብሮ በመቆም የደሃ አገር ሕዝቦችን በማሰቃየትና ሃብታቸውንም በመዝረፍ ተግባር ውስጥ መጠመዳቸው ፈጦ እንዳይታይ ይጋርዳል:: ሌላው ምርጫው የተጭበረበረ ቢሆንም የሕዝብ ተሳትፎ እስከታየበት ድረስ ገዢዎቹ እራሳቸውን ትክክለኛና ተቀባይነት (legitimate) ያላቸው አድርገው እንዲቆጥሩና ሕዝብም ይህን አምኖ እንዲቀበል ለማስገደድ ይረዳል:: በምርጫ ወቅት የሚታዩ ግድፈቶችም ሆኑ ያፈጠቱ ውንብድናዎች በእነዚህ ድሃ አገሮች ውስጥ እስከሆነ ድረስ የተከሰቱትና በሥልጣን ላይ ያሉት ቡድኖችም የምዕራቡ አለም ወዳጆች እስከሆኑ ድረስ ችግሮቹ የዲሞክራሲያዊ ግንባታው ሂደት አካል ተደርገው እንዲወሰዱ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጥረትና የሚዲያዎች ቅስቀሳም ይደረግበታል::
  • በመጀመሪያው ሂደት ውስጥ የሚከሰቱት ነገሮች መሰረታዊ ለውጦችን ለማምጣት የታለሙ ሳይሆን የአገዛዝ ሥርዓቱ ያስቀመጠውን የጨዋታ ሕግ በማክበር ተቃዋሚ የሆነው የፖለቲካ ኃይልም ሆነ ሕዝቡ ሥርዓቱን በረዥም ጊዜ ሂደት እንለውጠዋለን ወይም በራሱ ጊዜ ይከስማል ወይም አራሱን በሂደት ያርቃል የሚል ተስፋ ሰንቀው እድሜውን እንዲያራዝም የሚፈቅዱበት ሁኔታ ነው:: ባጭሩ “ያለ ምንም ደም ወያኔ ይቅደም” ነው:: በዚህ አካሄድ አትራፊዎቹ ወያኔ እና በወያኔ መቆየታ ላይ ተማምነው በኢኮኖሚም፣ በጸጥታ ዘርፍም እና ሆነ በአካባቢው የፖለቲካ መረጋጋት ለማትረፍ ከሥርዓቱ ቃር የተወዳጁ የውጪ ኃይሎችና የዘመኑ ባለሃብቶች ብቻ ናቸው:: ሰፊውና ድሃው የኢትዮጵያ ሕዝብ አገሩን ለቀማኞች አስረክቦ የስቃይ ዘመኑን በየአምስት አመቱ በሚደረጉ የማደናገሪያ ምርጫውዎች እያደሰ የግፍ እንቆቆውን መጋቱን ይቀጥላል::
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 9 years ago on December 24, 2014
  • By:
  • Last Modified: December 24, 2014 @ 1:30 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar