www.maledatimes.com የአጥር መፍረስ የሚያስከትለው ጦስ ማስተዋል በለጠ (አዲስ አበባ) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የአጥር መፍረስ የሚያስከትለው ጦስ                                                             ማስተዋል በለጠ (አዲስ አበባ)

By   /   June 23, 2016  /   Comments Off on የአጥር መፍረስ የሚያስከትለው ጦስ                                                             ማስተዋል በለጠ (አዲስ አበባ)

    Print       Email
0 0
Read Time:12 Minute, 3 Second

 

 

“ቤት ያለ አጥር፣ ጥርስ ያለ ከንፈር (አያምሩም)” ይላል – ቱባው ኢትዮጵያዊ የሥነ ቃል ትውፊታችን፡፡ ግሩም አባባል ነው፡፡ በተለይ ሁለንተናዊ ዕድገታችን እየጫጫ በሚሄድበት የኛይቷን በመሰሉ ሀገራት ከአንድም ባለፈ ሁለትና ሦስት አጥርም ቢኖር ለደኅንነታችን ዋስትና አስተማማኝ ነው፡፡ ቢያንስ ቢያንስ መንግሥት ከሚባለው ህግ አልባ ወምበዴ ውጪ የሚያጠቁንን ተራ ሌቦች ይከላከልልናል፡፡ አጥርን በፊት ለፊት ትርጉሙ ካየነው ማለቴ ነው፡፡

ጥርስንም ካለ ከንፈር ማሰብ አንችልም፡፡ የገጠጡ፣ የወላለቁና የተሰባበሩ ጥርሶች ገመናቸውን የሚከትላቸው ከንፈር ነው፡፡ እናንተም እንደምታውቁት የከንፈር ጥቅም ከዚህም ያልፋል፡፡…

አነሳሴ ስለአጥርና ከንፈር መግለጫ ለመስጠት አይደለም፡፡ ምሣሌያዊ ንግግሩን ተመርኩዤ ግን አንዳንድ ሀገራዊ ጠቃሚ ነጥቦችን ማስታወስ እፈልጋለሁ፡፡ ጊዜ ያለው ለ5 ደቂቃ ያህል አብሮኝ ቢጓዝ  በምድርም ባይሆን በሰማይ ዋጋውን አያጣም፡፡

አንድ ማኅበረሰብ እንደማኅበረሰብ እንዲኖር ብዙ አጥሮች ያስፈልጉታል፡፡ ከተራው ግለሰብ ጀምሮ ሀገር ምድሩን እስከሚሞላው ሕዝብ የሚባል የአንዲት ሀገር ዋና ሀብት ድረስ አንዱ ከሌላው ሳይደርስ፣ ባልተገባ ጠብና ግጭት ምክንያት የመኖሪያ ቀዬና አካባቢ ሳይደፈርስ ሁሉም በሰላም እንዲኖር የተለያዩ አጥሮች አሉ ወይም ሊኖሩ ይገባል፡፡ እነዚያ አጥሮች ከፈረሱ ወይም በቅጡ ካልተበጁ የሚያስከትሉት ጦስ ሀገርን እስከመበተን ሊያደርስ ይችላል፤ ይህም ትንሹ ጦስ ነው፡፡ ከዚያም ባለፈ በሦርያና ከቅርባችንም በሶማሊያ እንደምናየው ያለ ዘላቂ ጭፍጨፋና ዕልቂት የባህል ያህል ተተክሎ ዜጎች ሲንከራተቱ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡

አጥሮቹ ምን ምን ናቸው? እንዴትና በማንስ ይገነባሉ? ለምንና በማን ሊፈርሱ ይችላሉ?

አጥሮች በመልክም በይዘትም ይለያያሉ፤ ግንባታቸውም የዘመናት ማኅበረሰባዊ ተራክቦዎችን የሚጠይቅ ሲሆን አስፈላጊነታቸውም አብሮነትን ማስተሳሰር የሚያስችል መጣብቅ መፍጠር ነው፡ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ኖሯቸው ከተገነቡ በአብዛኛው በቀላሉ የመደርመስ ዕድላቸው አነስተኛ ነው፡፡ ነገር ግን አጥሮች ተገንብተው ሲያበቁ እኩል መጠን ያላቸውን ፍጡራን በእኩል ደረጃ የማያስገቡ ወይ የማያስወጡ ከሆኑና ይህ አሠራራቸው በተገልጋዮች ዘንድ ከታወቀ አድሎኣዊ እንደሆኑ ይቆጠርና ህገወጥነት ህጋዊነት ይሆናል፤ አጥሮቹም ምንም እንኳ ተገትረው ቢታዩ ማንም የሚጥሳቸው ውሽልሽል አጥር ይሆናሉ፡፡የሚያከብራቸውም ሆነ የሚፈራቸው አይኖርም፡፡ ኑሯቸው የላንቲካ ዓይነት ይሆንና ‹ከጅ አይሻል ዶማ‹ ወይም ‹የአህያ ባል ከጅብ አያስጥል› እየተባሉ በማኅበረሰቡ ዘንድ ይተቻሉ፡፡ ቀስ እያለም አጥርነታቸው ይቀርና በ“እነማን ነበሩ” መዝገብ ተዛውረው ወደመረሳቱም ሊያዘነብሉ ይችላሉ፡፡ እንዲህ ያለ ሁኔታ ሠለጠነ በሚባለው ዓለም በስፋት ይስተዋላል፡፡ እኛ ሀገር ጥርዥ ብርዥ የሚሉ ሃይማኖትን መሰል ትውፊቶች በአንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት ወደታሪክነት የመቀየራቸው አዝማሚያ የዚህ ነባራዊ ሁኔታ ውጤት ነው፡፡ …

በሀገራችንም ሆነ በሌላው ዓለም ዜጎች ተከባብረው እንዲኖሩ ለማስቻል ሃይማኖት እንደ አንድ ዋና አጥር ሆኖ ለዘመናት ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ ፈሪሃ እግዚአብሔርን ወይም ፈሪሃ አላህን እያነገሠ ዜጎች ለክራቸው ወይም ለአንድ የሚያምኑበት ልዕለ-ሰብዕ የሆነ ኃይል እንዲገዙና ከሞት በኋላ ሕይወት እንደሚኖር በዚያም ሕይወት ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚወስደው በዚህ ምድር የሚከናወነው የጽድቅ ወይም የኩነኔ ተግባር እንደሆነ በማሳመን ሰዎች ተጠንቅቀው እንዲኖሩ ሃይማኖታዊ መጻሕፍቱና ቀሣውስትና ሼሆቹ እምነቶቹን በየምዕመኖቻቸው አእምሮ ያሠርጻሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት አካሄድ ሣይንስን መሰል ምድራዊ የምርምር ተቋማትና ኢ-አማንያን ባይቀበሉትም ሕዝቦችን በፍቅርና በመተዛዘን አስተሳስሮ በማኖር ረገድ ያለው ጉልህ ድርሻ ግን ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ አጥር ፈረሰ ማለት ደግሞ አንድ ልጓም ተበጠሰ ማለት ነውና ሰዎች የለዬላቸው ዐውሬዎች በመሆን አሁን በሀገራችን እያስተዋልነው እንደምንገኘው ያለ ችግር ይፈጠራል፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥም የቀን ጅብነት የዘመኑ ፋሽንና ያልተጻፈ ህግ ይሆናል፡፡ ለሆድ ማደር እንደ መልካም ባህል ይቆጠራል፤ ሞራላዊ ፍጡር መሆን በፋራነት እያስፈረጀ ጅልና ቂል ያሰኛል፡፡ ከተለመደው ብልሹ አካሄድ ውጪ አድርጎም ለጉዳት ይዳርጋል፡፡

ዱሮ በኔ የልጅነት ዘመን ሃይማኖት ትልቅ ዋጋ ነበረው፡፡ ለአብነት ያህል ማዕድ ላይ ቀርቦ የጠገበ ሰው ወዳጆቹ ሊያጎርሱት ብለው የልጅ ምሣ የሚያህል ጉርሻ በጃቸው ይዘው ሲንጠራሩ “ገብርኤልን” ብሎ ከማለ አንዲት ግራም የምትመዝን እንጀራ እንኳን አይቀምስም፡፡ ማላ ማላ ነበር፡፡ አሁን ግን አንድ ክርስቲያን ነጋዴ በአንድ መቶ ብር የገዛውን ዕቃ ሊሸጥ ሲያስማማ “ቅዱስ ገብርኤልን በአንድ ሺ ብር ነው ያስገባሁት፣ ሊያውም ላንተ ለደንበኛየ ስል ከአንድ ሺህ አንድ መቶ ብር ሣንቲም አልቀንስም፡፡” ሲል ቅንጣት አያፍርም፡፡ ምክንያቱም አንድ ዋና አጥር ተደርምሷል፤ ለእህል ውኃ ሲባል አንድ ጠንካራ ማተብ ተበጠሰ፤ አንገትም ዞሮ ማየቱን ረሳ፡፡ ይህን አጥር ማን ቀድሞ ደረመሰው? አናውቅም፡፡ ምናልባት አገልጋዮቹ፣ ምናልባት የቅዱስ መንፈስ ተፃራሪ የሆነው የአጋንንት ኃይል፣ ምናልባት በሕይወት ተስፋ የቆረጡ ሰዎች፣ ምናልባት በፈጣሪ ፍርድ ምድራዊ “ቀርፋፋነት” ወይም የዘገዬ መምሰል የተበሳጩ ሰዎች፣ … ብቻ ማንም ቀድሞ ይደርምሰው ዋናው ነገር ግን አጥሩ ፈራርሶ ማኅበረሰባችን በኅሊና ቀውስ እየተሰቃየና በመንፈሣዊ ኪሣራ ተዘፍቆ እምነቱ እየተሸረሸረ ይገኛል፡፡ የሃይማኖት ልጓሙ የተበጠሰበት ማኅበረሰብ ደግሞ ዐይን የለውም፤ እርስ በርስ እንደጅብ ሲበላላ ለጭካኔው ወደር አይገኝለትም፡፡

በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ቤተ አምልኮዎች ለታይታና ለባህል እንጂ ከእውነት እግዚአብሔርን ስለማምለካቸው አላውቅም – ደግሞም ሃይማኖትና ባህል ተዛንቀው ምኑንም ከምኑ ለመለየት አዳጋች ሆኗል፡፡ ባጭሩ ሁሉ ነገር ተደበላለቋል፡፡ እግዜር ተረስቷል፤ የሥጋ ገበያ ደምቋል፡፡ ገንዘብ ተመልኮ ሰብኣዊነት ረክሶ፣ ዘረኝነት ደርቶ፣ ሆዳምነት ፋፍቶ፣ ያለው ከሌለው ተለይቶ የሚከበር፣ የሌለው ካለው ተለይቶ የሚዋረድ… ሁሉ ነገር ግራ የሚያጋባና የተዘበራረቀ ሁኔታ ጎልቶ የሚታይበት ሀገራዊ ድባብ ነው የሚታየው፡፡ አጥር ሲፈርስ እንዲህ ነው፡፡ ይሉኝታ ይጠፋል፤ የመተሳሰብና የመተዛዘን ምንጭ ይደርቅና በቦሌም ይሁን በባሌ የግል ጥቅምን ማሳደድ ብቻ ቅድሚያ የሚሰጠው ይሆናል፡፡ ተያይቶ ማደግ፣ በጋራ መበልጸግ በመጽሐፍ የክት ቃልነት እንጂ በእውን አይታሰብም፡፡ በበኩሌ በኔ ዕድሜ መጨረሻችን እንዲህ ይሆናል ብዬ አስቤ አላውቅም፡፡

ቀደም ሲል አንድ ነጋዴ የሚከብረው በዓመታት ልፋት ነበር፡፡ ላቡን ጠብ አድርጎ በአንዲት ዕቃ ላይ ጥቂት ሣንቲሞችን ብቻ በማትረፍ በከፍተኛ ድካም ያሰበው ጫፍ ይደርሳል፡፡ በዚያም ምክንያት ሳይሆን አይቀርም ከንግድ ይልቅ መምህርነትና ሌላው የመንግሥት የቢሮ ሥራ ይመረጥ የነበረው፡፡ ዛሬ ግን ሁሉ ነገር ተገለባብጦና ተመሰቃቅሎ ይታያል፡፡ መምህሩ በደመወዙ ከልደታ እስከባታ እንኳን መኖር አቅቶት በቀዳዳ ጫማና በነተበ ሸሚዝ ለመኖር ያህል ሲንጠራወዝ ትናንት ማታ ወደንግድ ዓለም የገባው የ20 ዓመቱ ታዳጊ ወጣት በአንድ አዳር የአየር ባየር ንግድ(ዘረፋ ማለት ነው የሚቀለው) የሚያምር ቪላ ሠርቶ በቪ8 እና በሀመር መኪኖች ሲንደላቀቅ ስናይ አጥሮቻችን ሁሉ ፈራርሰው ሀገር የወንበዴዎችና የወሮበሎች መፈንጪያ መሆኗን እንረዳለን፡፡

የዱሮ ነጋዴ ሃይማኖት ስለነበረው በዚያ ላይ የሀገርና የወገን ፍቅርም ተፈጥሯዊ የፀጋ ሀብቱ ስለነበሩ ይሉኝታና ሀፍረት ያውቅ ነበር፡፡ የአሁኑ ግን ኅሊናውን ለገንዘብ የሸጠና ጫፍ ላይ የሚታየው ገንዘብ ብቻ በመሆኑ እዚያ የሚያጓጓ ጫፍ ለመድረስ የማይፈነቅለው ድንጋይም ይሁን ቋጥኝ የሌለው የለዬለት ጅብ ነው፡፡ ከትምህርት ትምህርት የለውም፤ ከዕውቀት ዕውቀት የለውም፤ ከሃይማኖት ሃይማኖት የለውም፤ ከተሞክሮ ተሞክሮ የለውም፤ ከመንግሥት ሃይ የሚለው መንግሥት ወይም የህግ የበላይነትን የሚያስጠብቅ አካል የለውም፡፡ ምን ይዳኘው? ማን ይውቀሰው? ማን ይክሰሰው? ማን ሥርዓት ያሲዘው? በጥቅምና በዘር ሐረግ ከላይ እስከታች ተያይዞ  ሀብት ማማ ላይ ፊጥ ብሎ የሚታየው አብዛኛው ዜጋ ደንቆሮና ሆዳም ብቻ ነው – አእምሮውን የተነጠቀ፡፡

ከሃይማኖት አጥር ሌላ የባህል፣ የሰብኣዊነት፣ የግብረገብ (ሞራል)፣ የይሉኝታ፣ የወገንተኝነት፣ የዕውቀትና ትምህርት፣ የግንዛቤ ዕድገት፣የጓደኝነትና የወዳጅነት፣ የቤተሰብነት፣ የአብሮ አደግነትና የመሳሰሉ አጥሮችም ነበሩ – የዛሬን አያድርገውና፡፡ ዱሮ ሀገራዊ ስሜት ነበር፤ የባንዴራ ፍቅር ነበር፤ የአንድነት ስሜት ነበር፤ ያለመጨካከን የጋራ መግባባትና መተዛዘን ስሜት ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት እነዚህ አጥሮች ተሰባብረው በዘረኝነትና በተናጠላዊ የሀብት ክምችት አባዜ ብቻ ተለውጠው አዳሜ የግል ሩጫውን ሽምጥ እየጋለበ ይገኛል፤ በዚህ ሩጫውም የሚሊኖችን ኢኮኖሚያዊ ነፍስ እየደፈጠጠ በመኖርና ባለመኖር መካከል ያንጠራውዛቸዋል፡፡ ተቆጣጣሪ የሚባል መንግሥታዊም ሆነ የግል ተቋም ባለመኖሩ አለ ቢባልም የይስሙላ በመሆኑና ሀገር ምድሩ በሙስና በመብከቱ ማንም ማንንም ቆም ብሎ የሚያዳምጥበት ትግስትና ፍላጎት የለውም፡፡ ያለን መንግሥታዊ ቅርጽም ለዚህ ዓይነቱ ቅጥ አምባሩ የጠፋ ሥርዓት-አልበኝነት(አናርኪዝም) የተመቸ ነው፡፡ ሆድ በነገሠበት አእምሮ ወደሆድ ወርዶ ይሸጎጣልና በኩኑ ከማሆሙ የሆድአምላኪዎች መርህ አንድም በዘረፋው ትካተታለህ አለዚያም የኢኮኖሚያዊ ሞትህን ተቀብለህ በድህነት አሣርህን እየበላህ ለመኖር ያህል ብቻ ትኖራለህ፡፡ ና እስቲልህ – ባገሬ ጅልን ሰው “ አንተ ‹ና እስቲለው› አንዴ ናማ ልላክህ” ይባላል –  እኛም እንደዚያው ሆነናል፡፡ ምርጫህ በመኖርና ባለመኖር መካከል ነው፡፡ ምርጫህ የሚንጠለጠለው ለኅሊናህ አድረህ የሚመጣብህን ፍዳ በመቀበል ወይም በተቃራኒው ከነሱ ጋር ወግነህ የልብህን በመሥራት እንደፈለግህ በመሆን መካከል ነው – እየኖርክ መሞት ወይም እየሞትክ መኖር፡፡ ሌላው ምርጫ ጠባብ ነው – ምናልባት ከሀገርህ ወጥተህ መሰደድ፡፡ እሱም የሞት ሞት ነው – ኢትዮጵያህ እንዲህ ናት፡፡ ደናቁርት ወደ ሥልጣን ሲመጡ፣ ከደናቁርትም የሚገዙትን ሕዝብና አገር እንደራስ ሕዝብና አገር የማይቆጥሩ፣ ራሳቸውንም እንደአድሮ ሂያጅ የባዕዳን ቅኝ ገዢዎች የሚያዩ የዕድሜ ልክ ሽፍቶች ባዶ ቤተ መንግሥት ሲገቡ ነገረ ሥራቸው ሁሉ የዝንጀሮና የጃርት ዓይነት ነው የሚሆን – እስኪያንገሸግሸን አየነው፡፡

ማኅበረሰብኣዊ ወግና ባህል መልካም አጥሮች ነበሩ፡፡ ዱሮ ለኅሊናህ ብለህ የምትሠራቸው ብዙ ነገሮች ነበሩ፡፡ ልጆች ሆነን ትልቅ ሰው የተሸከመውን ዕቃ ተቀብለን እናግዛለን – አጉል ቦታ የቆመ መኪናን ገፍተን ዳር እናሲዛለን ወይም ሞተሩ እንዲነሳ እስከመጨረሻው እንገፋለን፤ አቅመ ደካማን በሸክም ወይም ዐይነ ሥውር ከሆነ እየመራን መንገድ እናሻግራለን ፤ ቤትና ሠፈር የጠፋውን ሰው እናመላክታለን – … ይህን ሁሉ ስናደርግ ግን ገንዘብ መስጠትም ሆነ መቀበል አይታሰብም፤ ነውር ነበር፡፡ ዛሬ ግን አይደለም ሠፈር ጠቁመህ መስቀል ተሳልመህና “በጥፊ ምቱኝ፤ ይጠቅመኛል” ብለህም ገንዘብ ትጠየቃለህ – ብዙ ገንዘብ ሊያውም፡፡ በዛሬው ዘመን የኔ ቢጤ (ለማኝ) ባቅሙ ከብርና ከሃምሣ ሣንቲም በታች ብትሰጠው አንዳንዱ ይወረውርልሃል፡፡ የልመና ‹ኤቲክስ›ም ተለውጧል፡፡ ለምን ብትል ብዙ አጥሮች ፈራርሰዋልና፤ ምን ይሉኝ የለም፡፡ “በቃኝ” ወይም “ጠግቤያለሁ” ማለት ዱሮ ቀረ፡፡

በሥልጣን ረገድ ካየነው አብዛኛው ሰው በተቃውሞው ጎራ ሣይቀር አንዴ አመራር ላይ ፊጥ ካለ ሀኪም ይንቀለኝ ባይ ነው፤ ወያኔ ከገባ ጀምሮ ላፉት 25 ዓመታት የድርጅት አመራር ላይ ቁጭ እንዳሉ የሚገኙ ጎምቱ ዶክተሮችና ፕሮፌሰሮች መኖራቸው የሚጠቁመን ዋና ነገር ዴሞክራሲና እኛ መቼም ቢሆን ልንተዋወቅ እንደማንችል ነው፡፡ እነኚህን መሰል ማፈሪያ ገብጋባ ዜጎች ቤተ መንግሥት ቢገቡ የሚያስወጣቸው ክሬን ወይም ግሬደር እንጂ በሕዝብ ድምጽ የሚሞከሩ አይሆኑም፡፡ አዎ፣ ብዙ ነገር ከቁጥጥር በላይ ሆኖብናል፡፡ የይሉኝታ አጥር ከፈረሰና የኅሊና ዳኝነት በጥቅምና በግል ዝና ከተለወጠ አእምሮ ማሰብ ያቆማል፤ ያኔ አንዱ አንዱን ሲያማ ጀምር ትጠልቃለች እንጂ ማንም ከማንም የሚሻል አይሆንም፡፡ በትንሹ ያልታመነ በትልቁም አይታመንምና በየጎራው አሉን የምንላቸው ሰዎች ዓሣማና ጅብ ናቸው፡፡ የማያፍሩና “ሕዝብ ምን ይለናል?” ብለው ራሳቸውን የማያስተካክሉ ደናቁርት ናቸው –  ፊደል መቁጠር ብቻው ደግሞ ዋጋ የለውም፡፡ …. እነዚህን የፈራረሱ አጥሮች ይዘን ኢትዮጵያን እንደ አዲስ መገንባት ይከብዳል፡፡ ብዙ ሥራ መሠራት ይኖርበታል፡፡ አለበለዚያ ጉዟችን ህልማዊ እንጂ እውናዊ አይሆንም፡፡

ዜጎች የማኅበረሰብ ሸክላና ጡቦች ናቸው፡፡ በሥርዓት ታንጸው ካደጉና በመልካም ግብረ ገባዊ ሰበዞች ተሰፍተው ለወግ ለማዕረግ ከበቁ ሀገርም ትታደላለች፡፡ ወንጀልና ክፋት ይቀንሳሉ፡፡ ጥሩ መንግሥትም ይኖራል – ምክንያቱም መንግሥት ከሰማይ የሚወርድ ሣይሆን ከሕዝቡ የሚወጣ የማኅበረሰቡ ሁለንተናዊ ዕድገት ነፀብራቅ ነውና፤ ጥሩ ሕዝብ ጥሩ መንግሥት ይኖረዋል፤ መጥፎ ሕዝብም መጥፎ መንግሥት ይኖረዋል – ባብዛኛው፡፡ እንደኛ እንዳሁኑ ከሆነ ግን ከሥር መሠረታቸው በቂም በቀልና በጥላቻ ተኮትኩተው፣ ከራስጌያቸው እስከግርጌያቸው በዘረኝነት የመርዝ በርሜል ተዘፍዝፈው ወደ ሥልጣን የሚመጡ ዜጎች ከተፈጠሩ አዲዮስ ሀገርና ሕዝብ፡፡ ለምን ቢባል የመልካም አስተዳደር ባህልና ወግ አጥር ፈርሷልና፡፡ እነመለስና አቦይ ስብሃት ያደጉበት ከባቢያዊ ሁኔታ በፀረ-ኢትዮጵያ አስተሳሰብ በእጅጉ የተበከለ ስለነበር እነዚህ ሰዎች በለስ ቀንቷቸው ከደደቢት እስከ አራት ኪሎ ሲጓዙና ከዚያም በኋላ በነበራቸው ሰፊ ጊዜ ብዙ የወል አጥሮችን አፈራርሰው ባዶ ያገኙትን አልጋ ተደላድለው ተኙበት፡፡ ይህንን ባዶውን ያገኙትን አልጋ ትኋንና ቁንጫ አወረሱትና ሌላ ከነሱ የተሻለ ደህና ዜጋ እንኳን መጥቶ እንዳይተኛበት አጓጉል አደረጉት፡፡ ደህና ሰውም እንዳይፈጠር በጠላቶቻችን ምክር ደህና ደህናውን ከመካከላችን እያወጡ ለመቀጣጫነት ለጭዳ ዳረጉት፡፡ ለጭካኔያቸው ወደር ማጣት ትልቁ ሰበብ ትውልድ ሁሉ ሀገር አለኝ ብሎ እንዳያስብ ጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ እንዲገባና እንዲደብተው ማድረግ ነው፡፡ የአጥር መፍረስ ጦሱ ብዙ ነው፡፡

የማያልቅ ነገር ነው የያዝኩት፡፡ አውሎ የሚያሳድር ብቻ ሳይሆን የሚያከርም ነው፡፡ ስለዚህ ለምን ሰዎች ዐረመኔ ይሆናሉ? በሚል ድረ-ገፃዊ መዛግብትን ሳገላብጥ ያገኘሁትን አንድ ጥሩ አንቀጽ ላካፍላችሁና ለአሁኑ ልሰናበት፡፡ ማንበብንም ዕርም ብለው የተው እጅግ ብዙ ዜጎች ስላሉ መጻፍንም ዕርም ብለን ልንተው የደረስን መኖራችንን ግን በዚህ አጋጣሚ ሳልጠቅስ ማለፍ አልፈለግም፡፡ አጥር አፍራሹ የወያኔው ጭፍራ ያዞረብን ሁለንተናዊ አፍዝ አደንግዝ ከሀገራችን የጋራ ጉዳይ  እንድንወጣ ሳያስገድደን አልቀረም፡፡ ከፍ ሲል በጨረፍታ ለመጠቆም እንደሞከርኩት ብዙዎቻችን ጥልቅ እንቅልፍ ላይ ነን፡፡ መድኅናችን ከሰማይ እንዲወርድ የምንጠብቅ ብዙ ተላላዎች አለን፡፡ እንደውነቱ ተመቸኝ ብሎ ሀገርንና ሕዝብን እርግፍ አድርጎ መተው የጤናማነት ምልክት አይመስለኝም፡፡ “ሲሞቅ በማንኪያ ሲቀዘቅዝ በእጅ”ም ደግ አይደለም፡፡ ሀገርን በደስታዋ ጊዜ ብቻ ሣይሆን በመከራዋ ዘመንም አለሁልሽ ማለት ይገባል፡፡ ይህ የትኋንና የመዥገር ግሪሣ ሲራገፍ – መራገፉ አይቀርምና – ያኔ አደባባይ ወጥቶ የሌለን ነገር በመናገር የድል አጥቢያ አርበኛ ከመሆን ከአሁኑ የተቻለንን ማድረግ ይሻለናል፤ ይገባናልም፡፡ ሀገር አንደበት ስለሌላት አትወቅሰኝም፣ አትከሰኝም አይባልም፡፡ ዋናው ወቃሽና ከሳሽ ደግሞ ኅሊና ነው፡፡ እነዚህ ክፉዎችና ጊንጦች በአሁኑ ሰዓት ምን እየሠሩ እንደሆነ ማወቅና ማሣወቅ አለብን፡፡ ምንም እንኳን ዓለም አቀፉን የክፋት ኃይል በአጠገባቸው ቢያሰልፉም ቀን ማለፉ አይቀርምና ፈጣሪ ፊቱን ሲያዞርልን ልንከሳቸውና ልንወቅሳቸው ከፈለግን አሁን መተኛት የለብንም፤ ለመክሰስና ለመውቀስ ደግሞ አንዳች ማስረጃ በእጃችን መያዝ ይኖርብናል፡፡ የሚሠሩትን ክፋት መዝግበን እናስቀምጥ፡፡ “ምንም ደግ ሥራ ሣይኖራችሁ ጌታ ሆይ የተራቡትን በስምህ መግበናል፤ የታረዙትን በስምህ አልብሰናል፤ የታመሙትን በስምህ ጎብኝተናል… ብትሉ ያኔ አላውቃችሁምና ባባቴ ፊት ‹ዘወር በሉ› እላችኋለሁ” ሲል ክርስቶስ የተናገረውን መልካም ምክር እናስብ፡፡ ኢትዮጵያና ሕዝቧም በዚህ የነናቡከደነፆር ግፈኛ አገዛዝ ሲሰቃዩ ቢያንስ ልንጮኻላቸው ካልቻልን በቁማችን እንደሞትን ያህል ነው፡፡ እስኪ የድረ ገፆቻችንን ልፋትና ድካም እንኳን ቆም ብለን እናስብ፡፡ እኔማ ኑሯቸውን የተው እስኪመስለኝ ድረስ ሲፈጉ መዋል ማደራቸውን ስረዳ “እንዴ፣ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ለነዚህ ጥቂት የቁርጥ ቀን ልጆች ብቻ ተትታ ቀረች ማለት ነው?” እስከማለት እደርሳለሁ፡፡ እግዜር  ይባርካቸው ልበል በዚህ አጋጣሚ፡፡ ስም መጥራት ብጀምር ስለማልጨርሰው ይቅርብኝ፡፡ በነፃነት ቀን ዋጋቸው  ትልቅ መሆኑን ብመሰክር ግን ደስ ይለኛል፡፡አዎ፣ ብዙዎች እርግፍ አድርገው የተዋትን ሀገር ለማገልገል ቀን ከሌት የሚደክም ዜጋ ቢመሰገን ሲያንሰው እንጂ አይበዛበትም፡፡ ብዙዎች ለሀገራቸው ነፃነት ብዙ ነገር ማድረግ እየቻሉ ነገር ግን ተደብቀው ራሳቸውን ብቻ ማዳንን መርጠዋል፤ ያስተዛዝባል፡፡ ለሀገርና ለወገን ያልዋለ ሀብትና ዕውቀት ደግሞ ከንቱ ነው፡፡

ዛሬ ስለ ሕወሓት የጭካኔ ተግባር በኢሜል አድራሻየ ኪሩቤል በቀለ የተባለ ታጋያችን የላከልኝን ነገር ሳነብ በኅሊና አልቅሻለሁ፡፡ ወያኔ በአንደበት እንኳን በማይነገር የማሰቃያ ዘዴው ዜጎችን እንዴት አድርጎ እንደሚያሸማቅቅና አንገታቸውን ደፍተው ተደብቀው እንዲኖሩ እንደሚያደርግ ስንሰማ የመከራችን ክብደት ግዘፍ ነስቶ ይታየናል፡፡ የሞቱስ ሞቱ – ተገላገሉ፡፡ ነገር ግን እንደነ እንትና ያሉ የክፉ ቀን ልጆቻችን ከእሥር ቤት እንደወጡ በስማም የተባለበት ሰይጣን ይመስል አፋቸውን ለጉመው የሚኖሩበት ምክንያት እነዚህ የአጋንንት ውላጆች ምን ቢያደርጓቸው እንደሆነ እናውቃለን፤ ሰምተነዋልም፡፡ ይህን የመሰለ ሰይጣናዊ ኃይል ቤተ መንግሥት አስቀምጦ ሌላው ይቅርና ዘፈን ማዳመጡ ራሱ ነውር ሊሆንብን በተገባ ነበር፡፡ ብሔራዊ ሀዘን መታወጅ ነበረበት፤ እስከነጻነት ድረስ የሚዘልቅ ጥቁር ልብስ መልበስ ነበረብን፤ እነዚህ ወያኔዎች የሚሠሩብን ግፍ ወደር የሌለው ነው፡፡… ብድራታቸውን መከፈላቸው ባይቀርም እያደረሱብን ያለው አእምሯዊ፣ ኅሊናዊና አካላዊ ስብራት ግን መቼም የሚጠገን አይደለም፡፡ (የውሻን ደም በከንቱ የማታስቀር የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ ኢትዮጵያን  ከነዚህ የዲያብሎስ ሽንቶች ፈጥነህ ገላግላት፤ እባክህ ምሕረትህን በቶሎ ላክልን፡፡ አሜን)

ቀጥሎ ያለው ጽሑፍ የሚያወራው ሰዎችን በጠላትነት ስለመፈረጅና ከሰው ተራ ስለማውጣት ነው፡፡ አንድ የሰዎች ቡድን አንድን የማኅበረሰብ ክፍል በአንድ ነገር ፈርጆ ዐይንህ ላፈር ካለው በዚያ የማኅበረሰብ ክፍል ላይ የሚፈጽምበትን በደልና ግፍ ሁሉ በሰው ላይ ሳይሆን በዐውሬ ወይም በእንስሳ ላይ እንደሚፈጽመው ይቆጥራል፡፡ ለምሣሌ አይሁዶች በተለይም የጽዮናዊነትን መርህ አቀንቃኝ የሆኑት ይሁዳዎች ሌላውን የዓለም ሕዝብ “ጎይ” ይሉታል – ሥርዓት ባለው አጠራር ሲሆን ደግሞ “ጀንታይል”ይላሉ፡፡ ይህን ትልቅ ቁጥር ያለውን የዓለም ሕዝብ እንደበሬ ጠምደው ቢያርሱት፣ እንፊሪዳ አርደው ቢበሉት፣ እንደ ታዳኝ ዐውሬ ተኩሰው እየገደሉ ቢዝናኑበት፣ እንደባሪያ ቢሸጡትና ቢለውጡት፣ ሴቶቹን እየቀሙ (እንዳይወልዱ በመጠንቀቅ!) ቢዝናኑባቸው፣ ወዘተ. ለነሱ የተፈቀደና በመጽሐፈ ቶራ ወታልሙዳቸው የጸደቀ የአበው ውርስ ነው፡፡ ወንድሞቼና እህቶቸቼ – አንጎልን የመሰለ አስቸጋሪ ነገር የለም፤ እምነትን የመሰለ ክፉ አባዜ የለም፡፡ አንድን መጥፎ ነገር በሚሊዮኖች አእምሮ ውስጥ እንደጽድቅ ነገር መትከል ይቻላል፡፡ ከዚያም የሰነቀርከው ነገር ፍሬ ሲያፈራ በጭካኔ ተግባራት እየተደሰትክ መኖር ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሰይጣን አዝመራ ነው፤ የአዝመራው ተጠቃሚዎች ደግሞ በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡

ወያኔዎች  ፍጹም ምሥኪንና ከትግሬ ቀርቶ ከማንም የባዕድ ወገን ጋር ጠብ የሌለውን የዐማራን ሕዝብ በሆነ ነገር ፈርጀው እንዲህ የሚያስጨርሱት ተራው ጀሌ በገባው ነገር ሣይሆን ብልጣብልጦቹና አስተዳደግ የበደላቸው እንደነመለስ ዓይነቶቹ የሰንበት ፍሬዎች በዘሩት የዐመፃ ዘር ነው፡፡ ይህን የዐመፃ ዘርና ቡቃያ ለመንቀል ሌላ ከዚህ አስተሳሰብ የተሻለ መላ መምታት ይገባል፤ የዳግም መምጣቱ ብሥራት በአሁኑ ወቅት በአድማሳት ውስጥ የሚታየው ክርስቶስ ብቻ ሣይሆን አልበርት አነስታይንም የሚለው ይህንኑ ነው፡፡ ክርስቶስ “ክፉን በክፉ አትቃውሙ” ሲል አነስታይን ደግሞ “አንድን ክፉ ተግባር ለማክሸፍ ያ ክፉ ሥራ በተቃኘበት የአስተሳሰብ መንገድ መጓዝ ሳይሆን ከርሱ በተቃራኒ ማሰብ ያስፈልጋል” ይላል፡፡ በተመሳሳይ መንገድ መጓዙ የመጠፋፋትን ቀጣይነት እንደማረጋገጥ ነውና እንደሕዝብ ስናስብ ከዚህ የአነጋገር ትውፊት ትምህርት ብንቅስም ብዙ እንጠቀማለን፡፡ እንደ ጦር ሠራዊት ስናስብ ግን መጽሐፉም “ደም ትነጽሕ በደም” ይላልና በምንም ዓይነት መንገድ ማሸነፍ የማትችለውን የሰይጣን ኃይል ባለ በሌለ ጉልበትህ ብትደመስሰው ጽድቅ እንጂ ኃጢኣት የሌለበት መሆኑን የነሣምሶን ተሞክሮ በጉልኅ ያስረዳል፡፡ ሣምሶን በመቶዎች የሚቆጠሩ ጠላቶቹን በአንዴ በአንድ የአህያ መንጋጋ ይረፈርፋቸው እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡ ቢበቃኝስ …

THE SPIRIT OF ABSTRACTION

It’s called the spirit of abstraction, a term originally coined by Gabriel Marcel in his essay “The Spirit of Abstraction as a Factor Making for War,” and is defined as the practice of conceiving of people as functions rather than as human beings. In early American history a large segment of the population labeled African Americans as “slaves,” reducing their identity as human beings into an abstract idea only, freeing slave owners to consider slaves their property. Hitler convinced a majority of Germans to conceive of a segment of their population as “Jews,” abstracting their identity as human beings into something he convinced the German people was so inferior he was able to wipe out 6 million of them (not to mention half a million gypsies as well). Americans, in turn, abstracted the Japanese people into “Japs,” a derogatory term that reduced them from human beings with hopes, loves, families, and fears into the “enemy” on whom it was therefore eventually permissible to drop two atomic bombs.

 

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 8 years ago on June 23, 2016
  • By:
  • Last Modified: July 22, 2016 @ 11:53 am
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar