www.maledatimes.com ፌዴራሊዝምና የብሄር ጥያቄ በኢትዮጵያ ሲሚናር - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ፌዴራሊዝምና የብሄር ጥያቄ በኢትዮጵያ ሲሚናር

By   /   August 3, 2016  /   Comments Off on ፌዴራሊዝምና የብሄር ጥያቄ በኢትዮጵያ ሲሚናር

    Print       Email
0 0
Read Time:9 Minute, 51 Second

Ethiopians Forum in Europe  Den Haag, July 2016

የማንነት ፖለቲካ ጠንቆችና የአብሮነት አኗኗሪ መፍትሔ ፍለጋ ዩሱፍ ያሲን(ደንሓግ) (It is NOT our differences that divide us. Rather it is our INABILITY to recognize, accept and celebrate those DIFFERENCES. ) Audre Lorde ልዩነቶቻችን ውበታችን የሚሆኑት ስናስተናግዳቸው ብቻ ነው፤ አለበለዚያ ያወዛግቡናል። ዩሱፍ ያሲን (አርቲክል 2012) 1. የማንነት ጥያቄዎች በየፈርጁና በየመልኩ እገሌ የሚባል ስብስብ ለመንግሥት ምክር ቤት የማንነት ጥያቄ አቀረበ።እገሌ የሚባለው ደግሞ በዚህ ክልል ሳይሆን በዚኛው ክልል ልካለል አለ። ሌላው እኛ መታወቂያ መለያ አጠራሬ ይህ ነው እንጂ ይህኛው አይደለም። አንደኛው ብሔረሰብ ልዩ ዞን (ኮንሶ) ሌለኛው ክልል (ሲዳማ) ይሰጠኝ የሚል ጥያቄ አቀረበ።ስብስቦች የማንነት ጥያቄያቸው በሕገ መንግሥት መሠረት ለመንግሥት ምክር ቤት አቀረቡ ሲባል እንሰማለን።ይህንን ጥያቄ ያቀረቡ የቅማነት፣ የቁጫ፣ የወልቃይት፣ የዱቤ ብሔረሰብ አባላት ተገደሉ፣ ታሠሩ፣ተቀጡ፣ ወዘተ ሲባል እንሰማለን።ገሚሱ የማነት ጥያቄ ቀላል መልስ አለው።ገሚሱ ቀላል መልስ የለውም።ማንነትን ማጠንጠኛ ያደረጉ ጥያቄዎች መልስና መፍትሔ የሚጠበቀው አንዳንዴ ጊዜ ከመንግሥት አካል (የመንግሥት ምክር ቤት፣ ክልል) ነው።

በሌላ ጊዜ በባለጉዳዩ ስብስብ እንዲወሰን ይፈለጋል፣ይደረጋልም።አንዳንድ ጊዜ ችግሩ ማኅበራዊ በስብስቦች መካከል ነው።ሌላ ጊዜ በመንግሥት አካልና ስብስቦች መሃል ነው። የዛሬ 8 ወር ጀምሮ በኦሮሞ ክልል፣ ሰሞኑን ደግሞ በጎንደር መሳሳቦች መንስኤቸው ማንነት ነው ተብሏል። ማንነት በአገሪቷ ባሉት ባለድርሻ ስብስቦች ቀጣይ አብሮነት ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ሕልውናዋም ጭምር ከሁሉም ችግሮች በላይ ተፈታታኙ በታኝ ተግዳሮት የጋረጠ ጉዳይ የሆነ ነው።ይህም ከቀርብ ጊዜው ወዲህ እኛ ብቻ ሳንሆነ የገዢው ፓርቲ ወገን የነበሩ የቀድሞ ጀኔራሎችም ጭምር እያሳሳባቸው መጥቷል። ሁሉም የማንነት ነክ ጥያቄዎች ተመሳሳይ ይዘትም ሆነ ቅርጽ የላቸውም። በመዛኙ በማንነት ዙርያና ሳቢያ የተነሱ ጥያቄዎችና ያስከተሉ ውዝግብ ዥንጉርጉር ቢሆንም ቅሉ አብዛኛዎቹ ያነታርካሉ።አልፎ ተርፎ ያወዛግባሉ። አንዳንድ ጊዜም ጦር ያማዝዛሉ።።ለምን? 2 ዛሬም ማንነትን ማጠንጠኛ ያደረጉ ጥያቄዎች ለምን ያነታርኩናል? የዛሬ ስንት ዓመት ያውም መልስ ያላገኘ የማንነት ጥያቄ የለም ከተባለ ጊዜ በኋላ። 50 ዓመት ዋልልኝ መኮነን የተባለ የፖለቲካል ሳይንስ ተማሪ ሰመ ጥሪው አርቲክል ከጻፈ በኋላ። 23 ዓመት አገሪቱ ብሔር፣ ብሔረሰቦች ጥያቄ መልስ የሰጠ ሕገ መንግሥት ከተረቀቀ በኋላ። ታዲያ ስብስቦች ለምን ይወዛገባሉ? ስብስቦች እርስ በርስ ይጋጫሉ፣ ከመንግሥት ጋር ያጋጫሉ። ድሮ አፋርና ኢሣ በውኃና ግጦሽ ይጋጫሉ ይባል ነበር።ያሁኑ ጥያቄዎች የመሬት ይገበኛል ጥያቄዎች ብቻ አይደሉም።

የሥልጣን፣ የሃብትና የተጽእኖ ማሳረፍ ዙሪያ የሚደረጉ ናቸው። ያሁኑ ጥያቄዎች የመሬት ይገባኛል ጥያቄዎች ብቻ አይደሉም። ዛሬም ማንነትን ማጠንጠኛ ያደረጉ ጥያቄዎች ለምን ያነታርኩናል? ጥያቄን ከመመለሳችን በፊት በቅድሚያ ማንነት ምንድነው የሚትለዋን ጥያቄ ባጭሩ ለመቃኘት ቢንሞክርስ! 3 ለመሆኑ፣ ማንነት ምንድነው? በቀላሉ አማርኛ በልዩነት ላይ የተመሠረተ ወገንተኛነት መገለጫ ነው። መለያ ነው፣ካንድ ስብስብ አባለት ጋር የምገለጸው ልዩነት፣ ከሌላው ስብስብ አባለት ጋር አለን የሚንለው አንድነትና ወገንተኛነት መሠረት ያደረገ ወገንተኛነት ነው።ማንነት፣ ባጭሩ አንድ ስብስብ እሱን ከሌሎቹ ስብስቦች የሚለዩትን መታዋቂያ መለያዎቼ ናቸው በሚላቸው ተጋሪዮሾች (COMMONNESS) ላይ ተሞርኩዞ ወገንተኛነት የመፍጠር ክንዋኔ ነው።ሥልጤ ፣ ሥልጤ እንጂ ፣ጉራጌ አይደለም።ወልቃይት ጠገዴ አማራ እንጂ ትግራዊ አይደለም። የለም ወልቃይት ትግራዊ ስለሆነ በትግራይ ክልል ውስጥ መካለል አለበት። ቁጫ፣ ቁጫ እንጂ ጋሙም፣ጎፋም፣ወላይታም አይደለም።ኦሮሞ ሃገሩ ኦሮሚያ እንጂ፣ ኢትዮጵያ አይደለም።ማንነት (identity) በቀላሉ አማርኛ የመለያ መታወቂያ ሊባል ይችላል። “እነሱ” እና “እኛ” ተባብለው “እኛን» “ከእነሱ» በሚለያቸው ተጋርዮሾች መግለጫዎች ፈልገውና ላንዱ ወገን ወገንተኛት መፍጠር ነው።

በሌላ በኩል “ የሌላኛውን” ( The other) ዝምድና መካድ ብቻ ሳይሆን ከእሱ ጋር መፋጠጥ ነው።ገሚሱ ማንነቴ ይታወቅ (እውቂያ ይሰጠው?) ነው ጥያቄው፣ገሚሱ ደግሞ በዚህ እውቂያ መሠረት ራሴን በራሴ የማስተዳድርበት የራሴ ወረዳ፣ዞን፣ክልል ይሰጠኝ ይላል። ሌላው በኢትዮጵያ ውስጥ ባንድነት እንኑር ወይስ ለእየብቻቻን የራሴ ጎጆ እንቀልስ ባዮች ደግሞ አሉ።ሌላው በተለያዩ ምክንያቶች አብረን መኖር ስለማንችል የራሳችን መንግሥት እንመሥረት ብሎ ይነሳል፣ ይቀሰቅሳል።ይህ ስሜት ወደ ኢዶሎጂ ብሎም ወደ እንቅስቃሴ ያድጋል።ባንድ ላይ ብሔረተኛነት የሚሰኘው ይህው ስሜት፣ ኢድዮሎጂና እንቅስቃሴ ቢባል ያስኬዳል እንደዚህ ናቸው ማለት ይቻላል። እነዚህና እነዚህ የመሳሰሉ ርእሰ ጉዳዮች ስብስቦችን ያነታርካሉ፣ ያነታርኩናል፣ያወዛግቡናል።አልፎ ተርፎ አቧድነው፣ ጎራ አስለይተው፣ ጦር ያማዝዙናል።ዛሬ በጎንደር የምንመለከተው አተረማማሽ ሆኔታ መንስኤቸው ማንነትና ማንነትን ማጠንጠኛ ያደረጉ ጥያቄዎች ናቸው። የሰው ልጅ ስብስቦች እንጋራለን የሚሉትን የማንነት መገለጫዎች መሠረት አድርገው የሚፈጥሩት የወገንተኛነት መገለጫዎች በርካታ ናቸው።እዚህ ለመዘርዘር ያስቸግራል።ሁሉ ግን ባንድ ሚዛን የሚመዘኑም አይደሉም።ሚዛን የሚደፉ አሉ።ሚዛን የማደይፉ ተጋሪዮሾች ይኖራሉ።

የሰው ልጆች ስብስቦችን መቧደን መነሻ በማድረግ በመካከላቸው የሚፈጠረው አለመግባባት ፈረጀ ብዙ።በተለያዩ ርእስ ግዳዮች ይጋጫሉ። አንዳንዱ ተጋሪዮሾቹ ከሌሎቹ ይበልጥ ወሳኝ ናቸው።ይበልጥኑም ያወዛግባሉ። የዘር ወይም ያንድ ቋንቋ ስብስብ ወይም ያንድ እምነት ወገንተኛት ላይ የተመሰረተው “እኛ» እና “እነሱ» ተሰናኝተው መቧደን ነው እንግዲህ የዓለማችንን ሕዝቦች የሚያነታርከው ፤የሚራኩተውና አልፎ ተርፎ ጦር እያማዘዘ የሚያገዳድለው።ገና ዓላማችን ያወዛግባሉ የተባሉትም እነዚሁ ሁለቱ አናቋሪ የማንነት መግለጫዎች ናቸው። 4 መቧደንና ውዝግብ  ማንነት በልዩነቶቻን ላይ የተመሠረት ወገንነተኛነት ነው እስከተባለ ድረስ፣ ልዩነቶቻችን ማስተናገድና ማስተዳደር እስካልቻልን ድረስ ያወዛግቡናል። ይህ ውዝግብ ነው ለቁሩቁሱ ምክንያት።

ሰለዚህ ማህበራዊ ስብስቦች በቡደን ቡደን መቧደናቸው አይደለም ወደ ግጭት የሚያመራቸው ተፃራሪ ወይም በጊዜው ተፃራሪ የሚመስላቸው ግቦችን በየፊናቸው ለመምታት ወይም ለማሳካት ማለማቸው እንጂ።ይህ ድርጊት ነው እንግዲህ ውዝግብ የሚሰኘው። የ Conflict (ውዝግብ) አጥኚዎች፣ ውዝግብ ”ሁለት ወይም ከዚያ በለይ የሆኑት ወገኖች ተፃራሪ ሆነው የሚታያቸውን ዓላማዎች አንግበው አንዱ የሌላው ዓላማ ግብ መምታት እንዳይይሳካ የማድረግ ክንዋኔ ነው” ይሉናል። በግለሰቦች መካከል በነጠላ ማንነታቸው የሚነሱትን አለመግባባቶች ለጊዜው ከዚህ ውጭ እናድርጋቸውና ሌላውን እንመልከት። ሰዎች ሕወታቸውን ሲመሩ የተለያዩ ግቦች አንገበው እንደሚንቀሳቀሱ ይታወቃል። በዚያኑ መጠን ተፃራሪ የሚመስሉ ፍላጎት ፤ ዓላማ ፤ ጥቅምና አመለካከቶችን ያራምዳሉ።

እነዚሁ ሌሎቹ ካነገቡትና ከሚያራምዱት ሳይጣጣሙና የተቃረኑ ሲመስሏቸው ይሻኮታሉ፤ይሯኮታሉ፤ይቆራቆሳሉ።ባጭሩ ጠብ ይፈጥራሉ።ባንድ ዓላማና ፍላጎት ተፃርረው ጎራ ላይተው ሁለቱም የራሳቸውን ዓላማ ለማሳካትና በዚያኑ መጠን የሌለኛውን ዓለማ ስኬት ለማደናቀፍ አልፎ ተርፎ ወድቅ ለማድረግ በየፊናቸው ይፍጨረጨራሉ።

በዚያኑ ወቅት ዓላማዎቹ ተፃራሪ ሰለሆኑ ወይም ለግቡ አንጋቢዎች ተፃራሪ ዓላማዎቻቸን ማጣጣም የማይቻል ሆነው ሰለሚታዩዋቸው የግድ ጎራ ይለያሉ።ይፋጠጣሉ።ደረጃው ይለያያል እንጂ ለውዝግብ ተመራማሪዎቹ ከቤተሰብ አለመግባባት እስከ ሶማሊያው ዓይነቱ አመሰቃቃይ እርስ በእርስ ጦርነት የመሳሰሉት ቁሩቁሶች ሁላ በውዝግብ ውስጥ ነው የሚጠቃለሉት።ሰለዚህ በቡድን ቡድን መቧደኑ አይደለም ወደ ግጭት የሚያመራቸው ተፃራሪ ወይም ተፃራሪ የሚመስላቸው ግቦችን ለመምታት ማለማቸው እንጂ። በመካከላቸው “ውዝግብ” ተፈጠረ የምንለው ይህው አለመግባባትና አለመጣጣም ሲከር ነው።  የማንነት ፖለቲካ መሠረቱ እነዚህን ልዩነቶቻችንን መሠረት አድርጎ ወገን ለይቶ መደራጀትና አንዱ ከእነሱ የተለየውንና ” ሌላው» ከተሰኘው ጋር ተፃርሮ መፋጠጥ ነው።

አንዳንድ ጊዜም በጦር ሜዳ መግጠም ነው።ያን ጊዜ ልዩነቶቻችን ጌጦቶቻችን ሳይሆኑ የጠብ መነሾ ሆነው ቁጭ ይሉና ያነታርኩናል፣ ያወዛግቡናል።አልፎ ተርፎም አቧድነው፣ ጎራ አስለይተው፣ ጦር ያማዝዙናል።  ልዩነቶቻችን ጌጦቻችን ናቸው ከሚለው መፈክር አሸጋግረን ልዩነቶቻችንን ማስተናገድና ማስተዳደር አልቻልንበትም፣ በረዥሙ ታሪካችን። እስካሁን አላወቅንበትም ማለት ሳይሻል አይቀርም። እነሱን ከማስተናገድና ማኔጅ ከማድረግ ይልቅ ልዩነቶቻችን ከእነጭራሹ መካዱ ይቀናናል። እኛ አንድ ነን፤ የምን ልዩነት አመጣችሁብን ደግሞ ማለቱን የምናዘወትርም አልጣፋንም።በእኛ መካከል ልዩነት የሚፈጥሩት የውጭ ጠላቶቻችን ናቸው በማለት በሌላው ላይ ማላከኩን የምንመርጥበት ጊዜም አለ ።ጉራማይሌነታችን ከእነአካቴው ሽምጥጥ አድርጎ መካድም ብቻ ሳይሆን በጉልበት እንዲወገዱ መጣሩ ሌለኛው አደገኛ አካሄድ ነው። በርካታ አብነቶችን መጠቀስ ይቻላል።

ከረዥሙ ታሪክችን በግድ አንድ የማድረግ ሙከራዎች ውስጥ ሁለት አብነቶች ብቻ እንመልከት። በመንግሥታዊ ሥልጣን የተደረጉ እምነትን በጉልበት አንድ የማድረግ ሙከራዎች።መላው የሃገሪቷ ሕዝብ በሃይማኖት አንድ ማድረጉ በኢማም አሕመድ ግራኝ በ 1529/1543 ተሞክሮዋል።የዛሬ 480 ገደማ። ብዙ ጥፋት አደረሰ እንጂ የሃገሪቷን ሕዝብ ማስለም ወይም በግድ ሙስሊም እንዲሆን የተደረገው ሙከራ አልተሳካም። በ1877 በቦሩ ሜዳ አፄ ዮሃንስ ሙስሊሞችን በሙሉ ክርስቲያን ሁኑ ወይም “ክስትኑ” ብለው በንጉሣዊ አዋጅ ለማጥመቅ የተደረገው ሙካራም እንዲሁ አልተሳካም።ዛሬ በግድ አንድ እንድርግ ብሎ የሚነሳ ወገን ባይኖርም ማስተናገድ ተሳክቶልናል ማለትም በፍጹም አይቻልም።

ባንድ መንግሥት ሥር ለመተዳደር ከወሰኑ በኋላም ቢሆን መንግሥቱን በምን መልክ እናደራጅ ጥያቄ ብሔረሰቦችን ያነጋግራል። ባንድ ሃገር አብርን ለመኖር ብንወሰን አሁንም የወደፊቱ አብሮነታችን በምን መልኩ ይደረጅ በሚለው ሓሳብ ላይም የሁሉም ስምምነት ያስፈልጋል ።የተወሰነው ክፍል የራሴ እድል በራሴ ልወስን ካለ አስቸጋሪ ሆኔታ ይፈጠራል። ያለፉ የታሪክ ስህተቶቻችን የወደፊቱ አብሮነታችን አይታሰቤ አድርጎታል ከተባለም ለዚህ ችግር መፍትሔ እንደሚያስፈልግ ከሃገራችን ተሞክሮ መገነዘብ አይገድም። አስቸጋሪ ነው አልኩኝ እንጂ መፍትሔ የለውም ማለቴ አይደለም።ጉዳዩ አስቸጋሪና የተወሳሰበ የሚሆነው ግን አንዳንድ ስብስቦች በአብሮነት መኖሩን አሻፈረን ብለው የራስ መንግሥት መመሥረት አመለካከትና እቅድ መንደፍ ሲጀመሩ ብሔረተኛነት ሥር እየሰደደ መጣ እንላለን። ለመሆኑ ብሔረተኛነት ምንድነው? 5 ለመሆኑ ብሔረተኛነት ምንድነው? አንድ ስብስብ የራሴ ናቸው የሚላቸውን አባላት ባንድ መንግሥት አሃድ ወይም ትድድር ሥር እንዲጠቃለሉት ምኞቱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያደረገው እንቅስቃሴ መግላጫ ተደረጎ እስከ ተወሰደ ድረስ ከፖለቲካዊ ክውን ወይም አሃድ ውጭ ከቶ ሊታሰብ አይችልም። ብሔርተኛነት ከመንግሥት ውጭ ሊታይ አይችልም። በዚህ ጽሑፍ በዚህ አግባብ ነው እየተጠቀምኩበት ያለሁት።

ከመንግሥት ወይም ከብሔር ማዕቀፍ ውጭ ብሄርተኛትን ማሰቡ አስቸጋሪ የሚያደረገው ይህ ይመስልኛል።በሌላ በኩል፣ በማንነቱ ወገንተኛት የተደራጀ ሃይል ሁሉ የራሱን መንግሥት ወደ መመሥረቱ አያመራም። ከላይ በሥልጤ ብሔረሰብ ምሳሌነት የተመለከትነው ወገንተኛነት ዓላማውና ግቡ ሥልጤን ከኢትዮጵያ ገንጥሎ የራሱን መንግሥት ወይም ፖለቲካዊ አሃድ የመስረት ግብና ዓላማ አልነበረውም።የለውምም።የተወሰኑ ብሔረሰቦች ከራሳቸው ጋር ለተያያዙ የአስተዳደር ጥያቄዎችና ችግሮች እልባት እንዲያገኙላቸው መፈለጋቸው እንደተጠበቀ ሆኖ። ብሔርተኝነት እንደ ማንነት ማደራጃ፤ ብሔርተኛነት እንደ ስሜት ፤ብሔርተኛነት እንደ እንቅስቃሴና ብሔርተኛት እንደ ኢድዮሎጂ በብዙ ትርጉም፤ፊቺና ደርዝ ያለው ማስገንዘቢያ ንባበ ቃል ነው። ወደዚያ ዝርዝር እዚህ ላይ አንገባም። 6. የአብሮነት መፍትሔ ፍለጋ  ማንነት በልዩነት ላይ የተመሠረተ ወገንተኛነት ነው ከተባለ፣ ልዩነቶቻችን ማስተናገድ ካልቻን ያለጥርጥር ያወዛግቡናል።የግድ የአብሮነታችን መሠረት በመሆኑ የመንግሥት አደረጃጀት አማኻኝነት አኗኗሪ ቀመር እንሻለን የምንለው ለዚህ ነው። ያልተማከለ ፌዴራላዊ ሥርዓትም የተመረጠውም ለዚሁ ነው። ከላይ የተመለከትናቸው በማንነት ዙሪያ ያጠነጠኑ ጥያቄዎች መልስ ማገኘት ይኖርባቸዋል፣ ከማንነት እውቂያ ጀምሮ፣አከላለል፣ራሳቸው በራሳቸው የሚያስተዳድሩበት አሃድ ደረጃ፣በራሳቸው ጉዳዮች ላይ የመወሰን ሥልጣንና ተግባራዊነቱን ይመለከተል። በተለይም ባልተማከለ የመንግሥት አወቃቀር።

የተዘረጋው ፌዴራላዊ ስርአት በተለያዩ ምክንያቶች የተተለመለትን ግብ ማሳካት አልቻለም።  የተወሰኑትን ለመጠቃቀስ፣ o የገዢው ፓርቲና መንግሥት የማንነት ጥያቄን እንድ አንደ ማተረማመሻና የሥልጣን እድሜ ማራዘሚያ አድርጎ መጠቀሙ፣ o በዚህና በሌሎች ተዛማጅ ምክንያቶች ፌዴራልዊ ሥርዓትን በቅጡ ተግባራዊ ማድረግ አለመቻል፣ o የአከላለል ችግሮች o የመልካም አስተዳደር ችግሮች  እነዚህን ችግሮች መፍታት በራሱ በቂ ሊሆን አይችልም። ባጭሩ፣ ለነዚህ ያልተማከለ ፈዴራላዊ አወቃቀርን ለተበተቡ ችግሮች መፍትሔ መፈለጉ ነው የሚያዋጣው። እንደገና ወደ ተማከለ አሠራር አስወግዶ ከማዕከል ለመተዳደር ተቀባይነት በብዙዎቹ ዘንድ በግምት መግባት አለበት ። ስለዚህ ኢማዕከላዊነት ወይም ያልተማከለ አውቃቀር እንጂ ወደ አሃዳዊ አሰራር መመለሱ ከምንፈታው ችግር ይልቅ የሚያወሳሰባቸው ችግሮች ያሳስባሉ። እነዚህን ልዩነቶች ማስተናገድ ነው በተለይም በመንግሥት መንግሥታዊ አወቃቀር አማካኝነት አኗኗሪ መፍትሔና ፎርሙላ መፈለጉ የግድ ነው ።በአጠቃልይ ሁሉም ራሱን የሚመለከቱ ጉዳዮችን በራሱና በዚያው በአካባቢው በራሱ በተመረጡ ወኪሎች እንዲወሰኑለት ፍላጎት ይስተወላል። ይህ ደግሞ ያልተማከለ አሰራር ነው።ኢማዕከላዊነት ወይም ያልተማከለ አወቃቀር አንዱ ቅርጽ ደግሞ ፌዴሬሸን ነው። በዓለም ከ25 ሃገራት በላይ ፌዴራላዊ አደረጃጀት አላቸው።

በሕዝብ ብዛት ሲሰላ ግን ከዓለማችን ሕዝብ አብዛኛው ክፍል የያዙ ናቸው። በሃገራችን ላለፉት 24 ዓመታት የተሞከረው ፌዴራል ሥርዓት ዝርጋታ ግን ካላይ ከተመለከትነው ጉድለቶች በተጨማሪ በበርካታ የአከላለል መፋለሶች የተተበተበ ሆኖ ተገኝቷል። ስለዚህ ፌዴራል ሥርዓቱን ማወጅ በራሱ በቂ አይደልም። 7 ከማነቶች መራኮት እስከ አኗኗሪ ቀመር አብሮ መንደፍ ¨ልዩነቶቻችን ውበቶቻችን ናቸው” የተሰኘው ውብ መፈክር ተግባራዊ ለማድረግ ብቻ ሳይሆን ዲሞክራሲን በቅጡ ለመማማር በቅድሚያ ልዩነቶችን መቀበል ይኖርብናል።»ሌላኛው መቀበል” የዲሞክራሲ “ሀ፣ ሁ” ነው ይላሉ ጠበብቶቹ። ምክንያቱም የሌላውን ግለሰብ ወይም ስብስብ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ አመለካከት መቀበል አብሮ መኖር የግድ የሚለው ግዴታችን ነው ለማለት ያስደፍራል።በሌላ በኩል፣ ሌላኛው አለመቀበልና አመለካከቶችን ማስተናገድ አለመቻል ራሱ ልዩነቶች ካለመቀበል ጋር በቅርብ የተቆራኘ አካሄድና አመለካከት ነው።ከታሪክም ከዛሬው ተጨባጭ እውነታ።እንዲያውም አብዛኛው ችግሮቻችንም የሚመነጩት ከዚህ ጉድለት ነው ማለቱ የቀላል። ዲሞክራሲ በመሠረቱ ከእኛ የተለየውን “የሌለኛውን» አመለካከት መቀበል ወይም ማስተናገድ የመቻል አካሄድና አግባብ ነው እስከ ተባለ ድረስ። የራስን ጉዳዩ በየደረጃው በራስ በተመረጡ አካላትና ግለሰቦች ማከናወንንም ይጨምራል።

የዲሞክራሲያዊ አግባብነቱ መሠረትም ይህ ምርጫና ተጠያቂነት ነው። 8 ማጠቃሊያ በቅድሚያ ልዩነቶቻችንን አስተናግደን ማስተዳደር ስንችል ብቻ ነው ለዜግነታዊ መንግሥት መሰረት የምንጥለው።እሱም ተግባራዊ የሚሆነው ገባር ወይም ቅርንጫፍ ማንነቶችን በአስባሳቢ ማንነት ማቀናጀት ስንችል ነው።የዜግነት መብት ማዕከል ያደረገ አሰባሳቢ ማንነት ብቻ ነው እነዚያ የተመለክትናቸው አነታራኪ የሆኑትን የቅርንጫፍ ማንነቶቻችንም ሁላ አዋህዶ ልያስተሳስረን ብቃት ያለው። ኢትዮጵያ እንደ ሃገር፣ የኢትዮጵያውያን እንደ ሕዝብ ባንድነት የሚያኗኑረን ቀመር ካለም እሱ ነው። እጣ ፋንታችንም እሱ ነው። ባጭሩ ተቻችሎ መኖር መሠረቱ ፤ማገሩና ግርግዳው እሱ ነው።ላለፉት 25 ዓመታት በኢትዮጵያ የምንመለከታቸው የብሔረሰብና የሃይማኖት አለመግባባቶች የገዢው ፓርቲ የራሱን የሥልጣን እድሜ ማራዘሚያ አድርጎ የተከተላቸውን ፖሊሲ ውጤቶች ናቸው መባሉ የተወሰነ እውነተኛነት ያለው አባል ነው። በከፊል ገዢው ፓርቲ የተከተለው አግላይ ፖሊሲ ውጤቶች ናቸው።በሥልጣን ያለው መንግሥት ሆን ብሎ ልዩነቶቻችን እንዲሰፉ ሲያደርግ ተመልከተናል።የሚያለያዩን ጉዳዮች እንጂ የሚያስተሳስሩን ችላ ሲባሉ አይተናል። ማንነት በመሠረቱ ልዩነት ነው ካልን ይህ ልዩነት የሚገለጽባትውን ፖለቲካዊና አመለካከታዊ አብዛሕነት(DIVERSITY) መቀበልና ማክበር ነው ቀዳሚው።ስለዚህ በልዩነት ላይ የተመሠረተ ወገንተኛነት መኖሩን እስተቀበልን ድረስ መፍትሔው ይህንን ልዩነት መቀበልና ማስተናገድ ነው።በተለይ በመንግሥት መዋቅር ላይ ያለን ግንኙነት ማስተዳደር መቻል ነው።ስለዚህ ¨It is NOT our differences that divide us. It is our INABILITY to recognize, accept and celebrate those DIFFERENCES የምትለው አባባል የተለየ ትኩረትን የምትሻ ናት።

ከሁሉም በላይ እነዚህት ልዩነቶች ማስተናገድና ማስተዳደር ሊኖርብን ነው፣በተለይም በመንግሥት አደረጃጀትና በምንዘረጋው አኗኗሪ ፎርሙላ አማኻኝነት። መሠረቱ በየደረጃው ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት የአብላጫው ይሁንታ በምርጫ የታከለበት ዲሞክራሲያዊ አግባብት ነው። የማንነት እውቂያ የሚያቀርቡ ስብስቦች ፣ እውቂያን ከተቀዳጁ በኋላ በደረጃዎ ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበት አሃድ (ክልል፣ ዞን፣ ልዩ ወረዳ … ወዘተ) ይጠይቃሉ። ለነዚህ መልስ መስጠቱ ለብቻው ግን በቂ አይደለም። እነዚያ ከላይ የተመለክትናቸው አነታራኪ የሆኑ ቅርንጫፍ ማንነቶችን ሁሉ አዋህዶ ሊያስተሳስረን ብቃት ያለው የዜግነትን መብት ማዕከል ያደረገ አሰባሳቢ ማንነት ነው። የሚያለያይ ሳይሆን የሚያስተሳስርና የሚያሰባሰብ እንሻለን ማንም ይግዛ ማንም ገዢው የዜጋውን መብት ሊጥስ የማይችልበት ሕጋዊና ተቋማዊ ዋስትናዎች የሚያረጋግጥ አዲስ መንግሥት፣ በአዲስ መሠረቶች መገንባቱ ነው ቅድሚያችን መሆን ያለበት።

ዜግነታዊ መንግሥት የምንለው እነዚህ ሁሉ አጣምሮ የያዘ አግባብና ሥርዓት ነው በማለት ንግግሬን እዚሁ ልቋጭ። ከላይ የውይይት መንደርደሪያ ማጠንጠኛ ያደርግኳቸው ማንነት፤ ውዝግብ፤ ብሔረተኛነትና የመሳሰሉ ፅነሰ ሓሳቦችና ማስገንዘቢያ ንባበ ቃሎች ባለ ብዙ ፊቺ፤ትርጉምና ፈረጅ እንደ ሆኑ አልሳትኩም። በአጭር ደቂቃዎች ንግግር እነዚህ ጽንሰ ሓሳቦች ተዛምዶ፤ ተያያዥነትና መወሳሰብ በሚገባ አብራራለሁ የሚል የተሳሳተ ግምት የለኝም። በጥያቄና ውይይት ጊዜ ልንዳብራቸው እንሞክር !! አመሰግናለሁ።

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 8 years ago on August 3, 2016
  • By:
  • Last Modified: August 3, 2016 @ 6:37 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar