አንድ ሚሊዮን ስንት ነው?                                                                    ነፃነት ዘለቀ

                          

ይሄ የቁጥር ነገር አልገባኝ እያለ መቸገሬን የምገልጥላችሁ ሀገሬ ውስጥ በምታዘበው የሙስና ግዝፈት እያፈርኩና እያረርኩም ነው፡፡ ትሹም ትልቁም ከመሬት እየተነሣ “አንድ መቶ ሚሊዮን ከባንክ ተበድሬ…፣ አምስት መቶ ሚሊዮን ብር ከባንክ ተበድረን ስናበቃ …፣ ለእገሊት 30 ሚሊዮን አበድሬያት …” እያለ ሲያወራ አንደበቱን ያዝ እንኳን አያደርገውም፡፡ ስለዚህ ቁጥር እኔ ማይም ነኝ ወይም እነሱ የጣሱት አኃዛዊ ሕግና ሥርዓት መኖር አለበት፡፡ እንጂ የ18 ዓመትና የ20 ዓመት ታዳጊ ወያኔ የ5 ሚሊዮን ብር መኪና ሲነዳ ማየት ባልተቻለ ነበር፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዩ ብዙ ነገሮች አውሮፓና አሜሪካ ቢሆን ኖሮ ዕድሜ ልክ ዘብጥያ ያስወርዳሉ፡፡ “ከየት አመጣኸው?” ብሎ የሚጠይቅ እኮ የለም፡፡ ካጠገብህ ተነስቶ ላጥ ይልና በአንዲት ቀን አዳር ሚሊዮኔር ሲሆን ታየዋለህ፡፡ በትብታብ ይሁን በጥንቆላ ወይም ሰርቶ ይሁን ሰርቆ የሚታወቅ ነገር የለም – ተሰርቶ ደግሞ በቅጽበት ጠሀብ ጫፍ አይደረስም፤ ህግና ሥርዓት ከሌለ በስተቀር፡፡ ንግድ ዱሮም ነበር – ያኔ ተያይቶ ነበር ሰው የሚናገደው እንጂ እንዳኑ በደረቅ ምላጭ – በባልጩት – አይለጫጭም ነበር፡፡ ብቻ አነዳዱን እንኳን ላያውቅበት፣ አበላሉንና አጠጣጡን ሳይቀር ላያውቅበት በአንዴ የከበርቴዎችን ቡድን ሲቀላቀል ትታዘባለህ – ከዘሩ ውጪ ደግሞ የምታውቅለት የተለዬ ሥራም ይሁን የንግድ ተሰጥዖ የለውም፡፡ አጥፍቶ ጠፊ የኢኮኖሚ አልቃኢዳዎችና አይሲሶች ወርረውን እንደትኋን እያንገበገቡን ናቸው፡፡

ሚሊዮንን ዱሮ የማውቀው በሰው ስምነቱ ነበር፡፡ አሁን ግን በተለይ ወያኔዎች ጢባጢቤ የሚጫወቱበት የብር መጠን መግለጫ ሆኖኣል፡፡ ባለፈው ሰሞን የጎላጉል ሕንፃ ባለቤት ለአንድ ጨረታ ይቀርባል አሉ፡፡ ከዚያም ባንክ የመሠከረለት ቢያንስ ሦስት ሚሊዮን ብር የሚደርስ ተቀማጭ ገንዘብ እንዳለው የሚያሳይ ማስረጃ እንዲያቀርብ ይጠየቃል፡፡ ያ ወያኔ – እንዳትደነግጡ – ከአንድ ባንክ ብቻ ያመጣው የባንክ ደብተር 350 ሚሊዮን ብር ይነበብበታል፡፡ ይህቺ እንግዲህ ጥቂቷ ናት፡፡ ወያኔዎች ወሬያቸው ሚሊዮንንም አልፎ ቢሊዮን ከገባ ቆይተዋል፡፡ እኛ ለምደነዋል፡፡ የኔን ኪስ ሸረሪት ያደራበታል፤ የነሱን የባንክ ደብተር ዶላርና ብር ይዝመነመንበታል፡፡ ሆዳም ማይም ሲገን እንዲህ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ጉዷ ፈላ፡፡ ኢትዮጵያውያን ጉዳችን ተንተከተከ፡፡ ወያኔዎች መሬቱንም፣ የመንግሥትን የገቢ ምንጭም፣ የሀብት መገኛ የኢኮኖሚ አውታሮችንም ጥርግርግ አድርገው ለራሳቸው ወስደው ሌላውን ሙልጭ አውጥተውታል፡፡ አዲስ አበባ የትም ግባ ሕንፃና ቪላው በአብዛኛው የትግሬ ወያኔዎች ነው፡፡ ከጠቅላላው የሀገሪቱ የሕዝብ ቁጥር ስድስት መቶኛ የሚሆነው ማኅበረሰብ በምን ምትሃትና ተዓምር ይህን ሁሉ የሀገርና የሕዝብ ሀብት በ25 ዓመታት ውስጥ ሊቆጣጠር እንደቻለ ሲያስቡት ያስደነግጣል፡፡ ሆቴሉ፣ ሱፐርማርኬቱ፣ ነዳጅ ማደያው፣ ባንኩና ኢንሹንሱ፣ ኮንዶምኒየሙ፣ ሪል ኢስቴቱ፣ መስጂዱ፣ ቤተስኪያኑ፣ የመንግሥት ሥልጣንና የጥቅም ቦታዎች ሁሉ… ምን አለፋችሁ … ኢትዮጵያ እንዳለች በወያኔ ተይዛ ሌላው መለመላውን ቀርቶላችኋል – መለመላውን፡፡ ምን ዓይነት ጉድ ነው? እነዚህ ሰዎች ሌላው ቢቀር ፈጣሪን ረሱት ማለት ይሆን? ይህ የአሁን አልጠግብ ባይነት ወደፊት ሲያስታውካቸው/ ሲያስመልሳቸው እንደሚያድር ጠፍቷቸው ነው ልበል? የዶሮን የሚያህል አንጎል ያለው አንድ ትንሽ ሰው እንኳ የዚህን አፀያፊ ተግባራቸውን የዞረ ድምር ማሰብ አያቅተውም፡፡ ምን ዓይነት ጥርሱን ያገጠጠ ገብጋባነትና ስስታምነት ነው? እንዴ? ወያኔን ያጀበ ትግሬ በልቶ ሲያድር ሌላው በርሀብ ይለቅ ብሎ ያወጀው የየትኛው ሰማይ አዛዥ ነው? ኧረ እየተስተዋለ ይሁን! ኧረ አሁንና ዛሬ በ11ኛው ሰዓት ላይም ቢሆን እናንት ወያኔዎች ሶበር በሉ – በሆድ እያሰባችሁ ዘመነ መንግሥታችሁን ትጨርሱት? አንጎላችሁ እንዲሠራ በቻይና አኩምፓንክቸርም ቢሆን ወጋ ወጋ አድርጉት፤ አኩፕሬዠርንም ጨምሩበትና ዓይነ ኅሊናችሁን አሸት አድርጉ – ምናልባት የምትሠሩት ግፍ የሚያስከትልባችሁ የኋላ ጠንቅ ቢገለጥላችሁ፡፡ አሁን በተዘረፈ ሀብት ስለጠገባችሁና አእምሯችሁን የጥጋብ ሞራ ስለሸፈነባችሁ ያላችሁ ይመስላችኋል እንጂ ሞታችኋል እኮ፡፡ “ከገዳይና ከሟች ማንኛቸው ናቸው የሞቱ?” የሚለውን ፍልስፍና ነክ ጥያቄ ደግሞ ለጥቂት ጊዜ አመንዥኳት፡፡ ያኔ እኛን ገደልን ብላችሁ በባዶ ሜዳ ከምትፎክሩት ከእናንተና በእናንተ “ከተገደልነው” ከኛ ማንኛችን እንደሞትን ታውቃላችሁ፡፡ ከዚህ ቂልነታችሁ አሁኑኑ ካልባነናችሁና ወደሰውነት ደረጃ ካተመለሳች የምትሰምጡበት አዘቅት ከቬርሙዳም የጠለቀ ነው፡፡ ይህን አውነት መናገር ነቢይነትን አይጠይቅም – ሦስተኛዋን ዐይን ገርበብ ማድረግ ብቻ በቂ ነው፤ ያ ዐይን ደግሞ ጨፍናቸሁት ወይም አፍርጣችሁ ጥላችሁት ይሆናል እንጂ እናንተም ጋ አለ፡፡ ከሰው ማሕጸን ነዋ የተገኛችሁት!

ሙስና፡፡ ይህችን ሀገር – ኢትዮጵያን – መቀመቅ እየከተታት ያለው ሌላው ነገር – ከዘረኝነቱ ቀጥሎ – ሙስና ነው፡፡ ሙስና ብሎ መጥራቱም ያንሰዋል፡፡ ለሀገራችን የሙስና ደረጃ ይህ የሦስት ፊደላት ቅምር – ሙስና – የሚል ቃል አይመጥነውም፡፡ ሙስና እግር አውጥቶ ሲሄድ የሚታየው በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ሙስና ግም ነው፤ ግማቱ ደግሞ አይል ነው፡፡ ሰውን ወደ ጅብነት የሚለውጥ ክርፋት፡፡ እንዴት እንደምንጸዳ እግዜር ይወቅ፡፡

አንድም ሥራ – በተለይ የመንግሥት ሥራ – ካለሙስና አይሠራም፡፡ ሙስና ውስጥ የማይገባ ሰው በመንግሥት መሥሪያ ቤት ሥርፋ የለውም – ሥርዓቱ ይተፋዋል፡፡ ለምን ቢባል – ሙሰኞችን ያደናቅፋልና፡፡ አብረህ ካልበላህ ያጠፉሃል- እንዲያውም ብሶ በሙስና ሲከሱህ አያፍሩም፡፡

የዱሮው ሙስና ይሉኝታ ነበረው፡፡ የዱሮው ሙስና በሀገር ፍቅር ስሜት የታሸ ነበር – ብዙም አይጨክንም፡፡ ለምሣሌ መቶ ብር ቢወጣ አምስቷ ወይ ስድስቷ ብር ነበረች በአዩኝ አላዩኝና በልመና በሚገኝ ሰነድ የምትሰረቀው፡፡ አሁን ግን ያ ዓይነቱ ሙስና የፋራ ነው፡፡ እውነት ነው የምላችሁ – በዚህ ዘመን ሙስናው ከ60 እና ከ70 በመቶ በላይ ነው፡፡ በገንዘባዊ ምሣሌ ቢገለጽ – አንድ የመንግሥት ፕሮጀክት በመቶ ሚሊዮን ሊሠራ ነው  እንበል፡፡ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ 60 እና 70 ሚሊዮኑ ብር ከላይ እስከታች ያሉ ባለሥልጣናት እንደየደረጃቸው ይቃረጡትና ቀሪው 40 ወይ 30 ሚሊዮን እንደነገሩ ለዚያ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያነት ይውላል – ያውም ከተሠራ ነው –  ገንዘቡ ተበልቶ ከናካቴው ላይሠራም ይችላል፡፡ ጠያቂ የለም፤ ተጠያቂም የለም፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ሌባና ሙሰኛ ነውና፡፡

በዚያ ላይ የጥራት ነገር አይነሳ፡፡ ማን ስለሀገር ይጨነቃል? ማን ስለነገው ትውልድ ያስባል? የጨረባ ተዝካር፡፡ ያባትህ አገር ሲወረር አብረህ ውረር፡፡ የሚታየው ዛሬ መክበር እንጂ የነገ የሀገሪቱ ዕጣ ፋንታ እንጦርጦስ መውረድ መሆኑ ለማንም ደንታ አይደለም፡፡ የምንገርም ዜጎች ፈልቀናል፡፡ መንገዱ ከመመረቁ ይቦዳደሳል፤ ሕንፃው ከመመረቁ ይሰነጣጠቃል፤ ማሽኑ ከመተከሉ ኃይሉ ይዝላል፤ “ምሁሩ” ከመመረቁ “ሀሁ”ን ከ”ለሉ”ና ትንሹዋን “a,b,c,d” ከትልቁ  “A,B,C.D” መለየት ያቅተዋል፤ የህክምና ዶክተሩ ከመመረቁ የህክምና መርፌን ከልበስ መስፊያ መርፌ መለየት ይሳነዋል፤ ወይ ጉዳችን – ጉዳችን እኮ ተዘርዝሮ አያልቅም፡፡ ምን ይዋጠን? “What swallow us?” ብዬ በ‹ቆንጆ› እንግሊዝኛ ባስፈግጋችሁስ ምን ይለኛል?

ሙስና ባህል ሆኖኣል፡፡ የማይሞስን የድህነቱ ጎርፍ አጥለቅልቆት እንደሚሞት ይታመናል፡፡ ስለሆነም አለመሞሰን የሚያስመሰግን ሳይሆን የሚያሰድብ እየሆነ ነው፡፡ አዲስ ማኅበራዊ “ኖርም” እያዳበርን ነው፡፡ የምሥራች!

ሙስና በዓለማዊ ብቻም ሣይሆን በእምነት ቦታዎችም የእስትንፋስ ያህል ነው፡፡ ከአንድ አነስተኛ ደብር ወደ ትልቅ ደብር ለመዛወር ለሀገረ ስብከቱ ባለሥልጣናት እስከ 80 ሺህ ብር ጉቦ እንደሚከፈል ሰምቻለሁ፡፡ አለበለዚያ በዚያው አነስተኛ ደብር እያከኩ መኖር ነው፡፡ ብዙ የሙስና ሥራ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲካሄድ እግዜሩም ታዝቦ ቁጭ እንጂ አንዳችም የሚፈጠርቅ መቅሰፍት አይልክም – ዱሮ ግን ቀልድ የለም፤ ቤቱን የሚደፍርን ባለጌ ካህን በመብረቅ ይሰነጥቀው ነበር – ዛሬ ግን ስንቱን ፈጥርቄ እዘልቀዋለሁ ብሎ ሳይን አይቀርም ትቶታል – ሒሣባቸውን ባንዴ እንዲያወራርዱ ፈቃዱ የሆነ ይመስለኛል፡፡ ምን ያለ ዘመን ውስጥ ገባን ግን ጎበዝ! (መሴሰኑን፣ መዋሸቱን፣ ሙዳየ ምጽዋት መገልበጡን፣ የሰው ሚስት ማባለጉን… ይህን ይህን “ተራ ወንጀል”ና ኃጢኣትማ ተውት – ሆድ ይፍጀው)፡፡ እንደሀገርም እንደማኅበረሰብም በቁም ሞተናል፡፡

እግዚአብሔር ካልተፈራ፣ የሀገር ፍቅር ስሜት ከጠፋ፣ ሰብኣዊነት ተንጠፍጥፎ ካለቀ፣ የሞራልና የባህል ክሮች ከተበጣጠሱ ሰው ዐውሬ ነው – ከዐውሬም የባሰ እንዲያውም፡፡ ዕውቀት ደግሞ ብቻውን ምንም አይሠራም፡፡ ማወቅማ ከፓትርያርካችን የበለጠ ዐዋቂ አለ እንዴ? የእግዚአብሔርን ቤት የሚደፍር እኮ የሚያውቃት ነው – ሊቀ ሣጥናኤል እኮ ከቤተኛነትም አልፎ የመላእክት አለቃ ነበር፡፡ ግን ማወቅ ብቻውንና በራሱ ዋጋ ስለሌለው ይህ መልአክ ከመረገምና የጨለማውን መንግሥት ከመውረስ – ወርሶም ርዕሰ-መስተዳድሩ ከመሆን – አላመለጠም፡፡

እኛም መሀገር ውስጥ ብዙ መኳንንትና መሣፍንት እንዲሁም በሃይማኖቱም ረገድ በርካታ ካህናትና ሊቃነ ጳጳሣት የዚሁ የጨለማው መንግሥት አጋፋሪዎች ናቸው – በጊዜው ንስሃ ካልገቡ፡፡ ወዮ ለቀኑ በሉ! ቀኑ ደርሷል፡፡ ምርትና ግርድ ሊለይ፣ ንፋሹ በሲዖላዊ የዘላለም እሳት ሊቃጠል ጊዜዋ ቀርባለች፡፡ ያወቀ ዳነ፤ ያላወቀ አልዳነም፡፡ ይብላኝ አእምሯቸው ለደነበሸ ትግሬ ወያኔዎችና አጫፋሪዎቻቸው፡፡ … ሰላም እጆቿን ወደፈጣሪዋ ለዘረጋችው ኢትዮጵያ፡፡

ለአስተምህሯዊ አስተያየት – nzeleke35@gmail.com

 

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar