ዶ/ር ብርሃኑና ጀዋር መሐመድ ነጋ በጋዜጣ ይፈለጋል ጥሪ ሊቀርብላቸው ነው

  ዶ/ር መረራ ጉዲና የቀረበባቸው ክስ በችሎት ተነበበላቸው | ለፍርድ ቤት ያቀረቡትን አቤቱታ ይዘናል

ምንጭ ዘሃበሻ

(የካቲት 24/2009) ዶ/ር መረራ ለሶስት ወር በማእከላዊ ሲመረመሩ ከቆዩ በኋላ በባለፈው ሳምንት ክስ እንደተመሰረተባቸው ይታወሳል። ክሱ የደረሳቸው ቢሆንም በችሎት እንዲነበብላቸው ለዛሬ የካቲት 24, 2009 ቀጠሮ ተይዞ ነበር። በዶ/ር መረራ ጉዲና ስም የተከፈተው መዝገብ፤ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ እና አቶ ጃዋር መሃመድን ጨምሮ፤ ኦኤምኤን እና ኢሳት የቴሌቭዥን ጣቢያዎችንም አካቷል። በመዝገቡ በአጠቃላይ አራት ክሶች የቀረቡ ሲሆን ከቀረቡት ክሶች ሁለቱ ዶ/ር መረራ ጉዲና ላይ ብቻ የቀረቡ ሲሆን አንድ ክስ ሶስቱም (በዶ/ር መረራ ፣ ፕ/ር ብርሃኑ እና አቶ ጃዋር) እንዲሁም ቀሪው ክስ (የሽብር ክስ) ኢሳት እና ኦኤምኤን ላይ የቀረበ ነው።

1ኛ ክስ በዶ/ር መረራ፣ ፕ/ር ብርሃኑ እና ጃዋር መሃመድ ላይ የቀረበ ክስ ነው
የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀፅ 32 (1) ሀ እና ለ 27 (1) 38 (1) እና 238 (1) እና (2)ን በመተላለፍ የቀረበ ክስ ሲሆን፤ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል ህብረተሰቡ ለሁከት እንዲነሳ በማድረግ፣ በኢሳት እና ኦኤምኤን የሃሰት ወሬ መንዛት ፣ ንብረቶች እንዲወድሙ እና ለሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት ናቸው ሲል ክሱ ያስረዳል።
2ኛ ክስ በኢሳት ሳተላይት ቴሌቭዥን እና የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ላይ የቀረበ ክስ ነው
ክሱ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀፅ 32 (1) ሀ እና ለ፣ 34 (1)፣ 38 እና የፀረ ሽብር ህጉን 652/01 አንቀፅ 5(1)ለ ስር የተመለከተውን በመተላለፍ የተመሰረተ ህግ ሲሆን፤ የሽብር ድርጅት ለሆኑት የአርበኞች ግንቦት ሰባት (አግ7) እና ለኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦነግ) ልሳን መሆናቸው በክሱ ላይተጠቀሷል።

3ኛ ክስ በዶ/ር መረራ ጉዲና ላይ የቀረበ ክስ
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ 01/2009 አንቀፅ 12/1 ስር የተመለከተውን እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንስ ፓስት ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃ አፈፃፀም መመሪያ አንቀፅ 2/1 ስር የተመለከተውን በመተላለፍ የቀረበ ክስ ሲሆን፤ ዶ/ር መረራ ከሽብርተኛ ድርጅት መሪ ከሆነው እና በመዝገቡ ሁለተኛ ተከሳሽ ከሆነው ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር መገናኘታቸው እና ኦኤምኤን ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ መገኘታቸውን ክሱ ይገልፃል።
4ኛ ክስ በዶ/ር መረራ ጉዲና ላይ የቀረበ ክስ
የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀፅ 486 (ለ) ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ የቀረበ ክስ ሲሆን፤ በጥቅምት ወር 2006 ( ከሶስት አመት ከአራት ወር በፊት) የኢትዮጵያ እና የናይጄሪያ ብሄራዊ ቡድን በሚያደርጉት ጨዋታ ላይ መንግስት የሽብርተኛ ቡድን አባላት ጥቃት ሊፈፅሙ እንደነበር ከመግለፁ ጋር በተያያዘ ዶ/ር መረራ ለአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ጣቢያ የሀሰት ወሬዎችን ማውራታቸው ይገልፃል ክሱ።

ዛሬ የካቲት 24, 2009 በዋለው ችሎት ዶ/ር መረራን ብቻ የሚመለከቱት 3ቱ ክሶች በችሎት ተነቦላቸዋል። አቃቤ ህግ በመዝገቡ ተካተው ያልቀረቡ ተከሳሾችን በተመለከተ ያለውን አስተያያት ዳኞች ጠይቀውታል። 2ኛ ተከሳሽ (ፕ/ር ብርሃኑ ) እና 3ኛ ተከሳሽ (ጃዋር መሀመድ) እንዲሁም ሁለቱ የቴሌቭዢን ጣቢያዎችም በውጪ ሃገር እንደሚገኙ ገልፆ በጋዜጣ የጥሪ ማስታወቂያ እንዲወጣ ጠይቋል። በተጨማሪም 2ኛ ተከሳሽ ፕ/ር ብርሃኑን በተመለከተ አቃቤ ህግ የፅሁፍ ማመልከቻ አቅርቧል። በማመልከቻው ተከሳሹ ከዚህ ቀደም በነ ብ/ጄ ተፈራ ማሞ እና አንዷለም አራጌ መዝገብ በሌሉበት ተከሰው የቅጣት ውሳኔ እንደተላለፈባቸው ጠቅሶ በታሳቢነት እንዲያዝልን ሲል አመልክቷል።

በእለቱ ዶ/ር መረራን ወክለው የቀረቡት ጠበቃ ወንድሙ ኢብሳም አስተያየታቸውን አቅርበዋል። በመዝገቡ ላይ ዶ/ር መረራ ከተቀሩት ተከሳሾች ጋር በአንድነት የሚከሰሱበት ምንም አግባብ እንደሌለ እና በክሱ ላይ ማስተር ማይንድ አለመኖሩን ጠቅሰው የደንበኛቸው የዶ/ር መረራ ጉዳይ ተለይቶ ለብቻ እንዲታይላቸው ጠይቀዋል። በተጨማሪም ዶ/ር መረራ የተከሰሱት በወንጀል ህጉ ስለሆነ የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ጥያቄ አቅርበዋል። ተከሳሹ ከዚህ ቀደም በሃገሪቱ እና የነበራቸው የፓለቲካ ታሪክ፣ የተከሰሱበት አንቀፅ የሚያስቀጣው ቀላል እስራት መሆኑ፣ ለዋስትና የሚሆን የንብረትም ሆነ የሰው ዋስትና ያላቸው መሆኑ፣ ከቤልጂየም ሲመጡ እንደሚታሰሩ ተነግሯቸው መምጣታቸው እና ከዚህ ቀደም በነበረው መንግስትም ለረጅም አመት ቢታሰሩም እንደሌሎቹ መሰሎቻቸው ከሃገር ለመውጣት ፍላጎት የሌላቸው መሆኑን ስለሚያሳይ፣ የስኳር ህመምተኛ መሆናቸው እና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን በፍሬ ነገርነት በማንሳት ዋስትና ሊሰጣቸው እንደሚገባ አቶ ወንድሙ በችሎት ተናግረዋል። በፅሁፍም ለዳኞች እና አቃቤ ህግ ሰጥተዋል። ዋስትና ቢከለከሉ እንኳን የስኳር ህመምተኛ በመሆናቸው እስሩ በቤታቸው ውስጥ እንዲሆንላቸው ወይም አሁን ባሉበት ማእከላዊ ወይም ደግሞ በቃሊቲ የአዛውንቶች ቤት (ክፍል) እንዲሆንላቸው ሲሉ አቶ ወንድሙ ተናግረዋል።
ዳኞችም የሚከተለውን ውሳኔ አስተላልፈዋል።

1 አቃቤ ህግ በዋስትና ጥያቄው ላይ ያለውን አስተያየት ለየካቲት 30, 2009 እንዲያቀርብ። ተከሳሽም በክሱ ላይ ያላቸውን መቃወሚያ ከደረሰላቸው በዚሁ ቀን እንዲያቀርቡ፤ ካልደረሰላቸው ሌላ ቀጠሮ የካቲት 30 በሚኖረው ችሎት እንደሚሰጥ።
2 ያልተገኙ ተከሳሾችን በተመለከተ ቀርበው ክሳቸውን እንዲከታተሉ ካልሆነ በሌሉበት ጉዳያቸው እንደሚታይ የሚገልፅ ማስታወቂያ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዲወጣ እና በጋዜጣው የወጣውን ማስታወቂያ መጋቢት 29, 2009 እንዲቀርብ።
3 ዶ/ር መረራ ጉዲና ለጊዜው ያሉበት ቦታ (ማእከላዊ) እንዲቆዩ እና በቀጠሯቸው ቀን እንዲቀርቡ።
*ዶ/ር መረራ ጉዲና ተጠርተው ወደ ችሎት በሚገቡበት ወቅት በችሎቱ ጉዳያቸውን የሚከታተሉ ሌሎች ተከሳሾች በሙሉ ቆመው ተቀብለዋቸዋል።
*የኦፌኮ የአመራር እና አባላት፣ የኤምባሲ ተወካዮች፣ ጋዜጠኞች፣ የሰመጉ ተወካዮች፣ ጓደኞቻቸው እና አድናቂዎቻቸው ችሎቱን ተከታትለውታል።
*በችሎቱ ቦታ በመጥፋቱ ምክንያት በርካቶች ችሎቱን ለመከታተል አልቻሉም ነበር። *የእነ ዶ/ር መረራን ክስ የሚያየው 19ኛ ችሎት ነው።

*ዶ/ር መረራ በጠበቃቸው በአቶ ወንድሙ በኩል የዋስትና ጥያቄ ያቀረቡበት ማመልከቻን ለማየት እዚህ ይጫኑ PDF

ዘገባው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ፕሮጀክት ነው::

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar