www.maledatimes.com “እውቁ ፖለቲከኛ አሰፋ ጫቦ አረፉ!” በአክሱማዊት ተሠማ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

“እውቁ ፖለቲከኛ አሰፋ ጫቦ አረፉ!” በአክሱማዊት ተሠማ

By   /   April 24, 2017  /   Comments Off on “እውቁ ፖለቲከኛ አሰፋ ጫቦ አረፉ!” በአክሱማዊት ተሠማ

    Print       Email
0 0
Read Time:3 Minute, 21 Second

“እውቁ ፖለቲከኛ አሰፋ ጫቦ አረፉ!”

አንጋፋ ጸሓፊ፤ ማራኪ ተናጋሪ እና አንደበተ ርቱእ የፖለቲከኛና የሕግ ምሁር የነበሩት አቶ አሰፋ ዳላስ ቴክሳስ ሆስፒታል ውስጥ ሲታከሙ ቆይተው በዛሬው እለት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
:
አቶ አሰፋ በሕይወት በነበሩበት ወቅት ባሳሰቡት መሰረት አስከሬናቸው ወደ ሃገር ቤት ተልኮ የሃገራቸውን አፈር እንደሚቀምስ ተገልጿል::
:
አቶ አሰፋ ማን ናቸው? የሚለውን በጥቂቱ ላስቃኛችሁ!
:
➊.”የትምህርትና ሌሎች ሁኔታቸው!”
:
አንጋፋው ፀሐፊና ፖለቲከኛ የአንደኛና ደረጃ ትምህርቱን በደቡብ ክልል በጋሞ ጎፋ ዞን በምትገኘው በጨንቻና ሻሸመኔ የተማረ ሲሆን የሁለኛ ደረጃ ትምህርቱን በአዲስ አበባ ኮከበ ጽባህ ተከታትሏል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ህግ ካጠና በኋላም በህግ አማካሪነት፣ በሲቪልአቪዬሽን አስተዳደር፣ በአገር አስተዳደር ሚኒስቴርና በምድር ባቡር ኩባንያ ሠርቷል፡፡
:
አሰፋ ጫቦ ደቡብ ኢትዮጵያ ካፈራቸው ሶስት ስመ-ጥር ፖለቲከኞች አንዱ ነው (ሌሎቹ የሲዳማው ወልደአማኑኤል ዱባለ እና የሐዲያው ዶ/ር በየነ ጴጥሮስ ናቸው)፡፡አሰፋ ጫቦ ግን ፖለቲከኛ ብቻ አይደለም፡፡
:
አንጋፋ የህግ ባለሙያ፣
:
ዳኛ፣
:
ጠበቃ፣
:
የሀገር አስተዳዳሪ፣
:
አንደበተ ርቱዕ ተናጋሪ፣
:
የስነ-ቃልና የባህል አዋቂ፣
:
የታሪክ ምሁር፣
:
ደራሲ፣
:
ጸሐፊ፣ ይህንን ሁሉ ነው፡፡
:
➋.”በኢትዮጵያ ፖለቲካ የነበራቸው ሚና!”
:
አሰፋ ጫቦ በኢትዮጽያ ፓለቲካ ውስጥ ረጅም ጉዞ በማድረግ ብዙ መስዋእነት ከፍሏል።

በተለይ በደርግ ዘመንና ከዚያ በኋላ ጉልህ የፖለቲካ ተሣትፎ የነበረው ሲሆን ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በማደራጀትም ይታወቃል፡፡የኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት ምክር ቤት አባልም ነበር፡፡

በኢትዬጵያ ምስቅልቅል ታሪክ ውስጥ በጃንሆይ ግዜም፣በደርግ ግዜም ከመታሰሩ በፊትም ሆነ ኢህአዴግ ከገባ በሁዋላ ለተወሰኑ ወራትም ቢሆን ወደ አሜሪካ ከመሰደዱ በፊት ቀላል የማይባል ፖለቲካዊ ሚና በተለይ ከደቡብ ኢትዮጵያ አቅጣጫ ትውልዱ የነበረው ግለሰብ ነው።

አሰፋ ጫቦ በአጼ ኃይለ ሥላሤ ዘመን የፓርላማ አባልም ነበረ፡፡ በፓርላማው ውስጥ ሆነው ታሪካዊውን የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ይደግፉ ከነበሩት ጥቂት ተራማጅ ግለሰቦች መካከል አንዱ እርሱ ነው፡፡
:
የሃይለ ሥላሤ መንግሥት ከስልጣን ሲባረር ደግሞ ከባሮ ቱምሳ፣ ዘገዬ አስፋው፣ ኢብሳ ጉተማ፣ አብዩ ገለታ እና ከሌሎችም ጋር ኢጭአት (የኢትዮጵያ ጭቁኖች አብዮታዊ ትግል) የተባለ ድርጅት በመመስረት ከደርግ መንግሥት ጋር ለመስራት ሞከሩ (አሰፋ ጫቦ፣ ባሮ ቱምሳና ዘገየ አስፋው ኢጭአትን በመወከል “የህዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት” የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ሆነው ነበር)፡፡
:
ከዓመት በኋላ ግን የደርግ አብዮት ልጆቹን መብላት ጀመረና እነ ኃይሌ ፊዳንና መስፍን ካሡን እንክት አድርጎ ዋጣቸው፡፡ የአሰፋን ነፍስ ግን እግዚአብሔር በተአምሩ አተረፋት፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን የአብዮቱ የቅጣት ጠበል ለርሱም አልቀረለትም፡፡ ለአስር ዓመታት በስመ-መጥፎው የማዕከላዊ እስር ቤት የግፍን ጽዋ ሲጠጣት ከረመና በ1981 ተለቀቀ (አሰፋ ጫቦ የማዕከላዊ ቆይታው ምን ይመስል እንደነበረ “እንዲህ መለስ ብለው ሲያዩት” የሚል ርዕስ በሰጠው ውብ መጣጥፍ አስነብቦን ነበረ)፡፡
:
አሰፋ ጫቦ በብዙዎች ቀልብ ውስጥ የገባው በ1983 መጨረሻ ላይ “የኦሞቲክ ነጻነት ግንባርን መስርቶ እንደገና ወደ ፖለቲካው ውስጥ በገባበት ጊዜ ነው፡፡በዚያ ዘመን 87 ወንበሮች በነበሩት የተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ልበ ሙሉእ ሆነው የተሰማቸውን ከሚናገሩት ጥቂት ሰዎች መካከል አንዱ እርሱ ነበረ፡፡
:
አሰፋ ጫቦ በ1985 አጋማሽ ላይ ከቪኦኤው ጌታሁን ታምራት ጋር ያደረገው ቃለ- ምልልስ በሀገር አቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ አድርጎት ነበረ፡፡ አልፎ ተርፎም ቃለ- ምልልሱ አሰፋንና የያኔውን የሽግግር መንግሥት ያፋታ ሰበብ ሆኗል፡፡ አሰፋም ከዚያች ቃለ ምልልስ በኋላ ወደ ምክር ቤቱ አልተመለሰም፡፡ እርሱ ምክር ቤቱን ጥሎ ሲኮበልልም የምክር ቤቱ ግርማ ሞገስ መገፈፍ ጀመረ፡፡ ቀስ በቀስም ምክር ቤቱ አንደበት አልባ ሆነና ቁጭ አለ፡፡ በ1987 መጨረሻ ላይ ደግሞ ያኛው ምክር ቤት ተበትኖ አሁን የምናየው ፓርላማ መጣ፡፡
:
➌.”በስነ-ጽሑፍ ስራ ያላቸው ሚና!”
:
በ1984 ዓ.ም ከኢትዮጵያ በመውጣት ቋሚ መኖሪያውን አሜሪካ ሀገር ያደረገው አሠፋ ጫቦ፤ ኮብልሎም አላረፈም፡፡ በአሜሪካን ሀገር በተደረጉ ሁለት የህግ ውድድሮች ላይ አሸናፊ ሆኖ ለመሸለም በቅቷል። ታዲያ አሰፋ ወደ ውጪ ገና ሀገረ አሜሪካ ከመግባቱ ብዕሩን ጨበጠና “አጃዒብ” የሚያስብሉ መጣጥፎችን ያዥጎደጉድ ጀመር፡፡

አንጋፋው ፖለቲከኛና ፀሐፊ አሠፋ ጫቦ፤ የአፃፃፍ ስልቱ የተለየ ከመሆኑ የተነሣ “አሠፋ እስታይል” በመባል ይታወቃል፡፡

በአዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ በጦቢያ መጽሔት፣ በኢትኦጵ መጽሔት እና በሌሎችም የፕሬስ ውጤቶች ላይ ሲጽፋቸው በነበሩት መጣጥፎች ብዙ አድናቂዎችን አፈራ፡፡ከዚህም አልፎ የርሱን አጻጻፍ የሚከተሉ ብዕረኞችም ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ፡፡
:
የመጽሐፍ ችሎታው የተመሰከረለት አንጋፋው ፖለቲከኛና ፀሐፊ አሠፋ ጫቦ “የትዝታ ፈለግ” በሚል ርዕስ በአሜሪካን ሃገር ያሳተመው የመጀመሪያ መጽሐፉ እንደገና እሱን እያስታወሰ ብሎም ለአዲሱ ትውልድ እንደ አዲስ እያስተዋወቀው ይገኛል።

አሰፋ – ለመጀመሪያ ጊዜ በጋዜጣ ላይ መፃፍ የጀመረው በ1956 ዓ.ም ከባህርዳር ለ“ፖሊስና እርምጃው” ጋዜጣ ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 52ዓመታት በጽሑፎቹ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን ችሏል፡፡
:
በ1980ዎቹ እና በ1990ዎቹ ይታተሙ የነበሩ መፅሄቶች እና ጋዜጦች ላነበበ ሰው አሰፋ ጫቦ የሚባል ቅኔ እና ቤተክህነት አፃፃፍ የነካው የፖለቲካ አምደኛ ያስታውሰናል።

ግና በዛሬዋ ዕለት ልብ የሚሰብር ዜና የኚህን አንጋፋ ምሁር ህልፈተ ህይወት ከወደ አሜሪካ ሰማን ፡፡ዳግም የእሱን እነዚያ ማራኪ ጹሑፎች ከእንግዲህ እንዳናይ ተገደናል።

ዳሩ ግን በድንቅ ስራዎቹ ዘወትር እናስታውሰዋለን!” እንወደዋለን..እናከብረዋለን!
:
አፈሩን ገለባ ያድርግልህ!!…
:
“በቸር ያቆየን”

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 7 years ago on April 24, 2017
  • By:
  • Last Modified: April 24, 2017 @ 12:47 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar