የህወሓት ባለስልጣናት በንግድ ስም ገንዘብ ለማጭበርበር ያቋቋሙት የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ)፣ ላልሰራው ስራ 3 ነጥብ 4 ቢሊዬን ብር ክፍያ እንዲፈጸምለት መጠየቁ ተነገረ፡፡ በህወሓት ወታደራዊ አዛዦች የሚመራው ይኸው የንግድ ተቋም፣ በሀገሪቱ የሚገኙ የፋብሪካ እና መሰል ፕሮጀክቶችን ያለ ተቀናቃኝ በመውሰድ የሚታወቅ ሲሆን፣ በዚህም የተነሳ የግል ባለሀብቱን ከገበያ ውጪ በማድረግ ብዙዎችን አማርሯል፡፡ ሜቴክ ለስም በመከላከያ ሚኒስቴር ስር ይቋቋም እንጂ፣ የሚዘውሩትም ሆነ ገንዘቡን የሚረጩት የህወሓት ባለስልጣናት ናቸው፡፡
ከዚህ ቀደም ያዩ የተባለውን እና በኦሮሚያ ክልል የሚገኘውን የማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ኮንትራቱን የወሰደው ሜቴክ፣ ግንባታውን እጅግ ከማዘግየቱም በላይ ገና ስራውን ሳይጨርስ ተጨማሪ ክፍያ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ ከተጨማሪ ክፍያው በላይ ደግሞ፣ 40 በመቶ ብቻ ላጠናቀቀው የፋሪካው ስራ 60 በመቶ የሚሆነውን ከፍያ መውሰዱም ተነግሯል፡፡ በአንድ የቻይና ድርጅት በተደረገው ጥናት መሰረት፣ የስኳር ፋበሪካውን ገንብቶ ለመጨረስ አራት ዓመት ብቻ እንደሚፈጅ ተነግሮ ነበር፡፡ ሆኖም ሜቴክ በፋብሪካው ላይ የተደረገውን ጥናት በድጋሚ በመከለስ፣ የፋብሪካውን ግንባታ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ አጠናቅቀዋለሁ ብሎ ዝቶ ነበር፡፡ በዚህም መሰረት ኮንትራቱ የተሰጠው ሜቴክ፣ ግንባታውን በ2004 ጀምሮ በ2006 እንደሚያተናቅቀው ገልጾ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ የፋብሪካው ስራ የተጠናቀቀው ግን 40 በመቶዉ ብቻ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
የፋብሪካው ስራ ገና አርባ በመቶ ላይ በሚገኝበት ሁኔታ በህወሓት የሚመራው ሜቴክ ግን ከአጠቃላይ የፕሮጀክቱ የውል ዋጋ ብር 11,084,850,000.00 (አስራ አንድ ቢሊየን ሰማንያ አራት ሚሊየን አምስት መቶ ሺ ብር) ውስጥ ብር 5,653,273,500.00 (አምስት ቢሊየን 653 ሚሊየን 273 ሺ 500 ብር) ወይም የውሉ 60 በመቶ ከፍያ ተፈጽሞለታል፡፡ ድርጅቱ ፋብሪካውን ገንብቶ ለማጠናቀቅ የገባውን ቃል ከማጠፉም በላይ፣ ያልሰራበትን ክፍያ ጭምር መውሰዱ፣ ህወሓት በስርዓቱ ውስጥ ያለውን የበላይነት እንደሚያረጋግጥ ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡ የህወሓት ባለስልጣናት በቀጥታ ከሚዘርፉት የሀገር ሀብት በተጨማሪ፣ በንግድ ስም ደግሞ በሜቴክ በኩል ከፍተኛ ገንዘብ በማሸሽ ላይ መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
Average Rating