www.maledatimes.com ጠቅላይ ቤተ ክህነት: የ”ሰንደቅ” ዋና አዘጋጅን ኪሳራና ወጪ እንዲከፍል ፍ/ቤት አዘዘ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ጠቅላይ ቤተ ክህነት: የ”ሰንደቅ” ዋና አዘጋጅን ኪሳራና ወጪ እንዲከፍል ፍ/ቤት አዘዘ

By   /   June 17, 2017  /   Comments Off on ጠቅላይ ቤተ ክህነት: የ”ሰንደቅ” ዋና አዘጋጅን ኪሳራና ወጪ እንዲከፍል ፍ/ቤት አዘዘ

    Print       Email
0 0
Read Time:30 Minute, 21 Second

ጠቅላይ ቤተ ክህነት: የ”ሰንደቅ” ዋና አዘጋጅን ኪሳራና ወጪ እንዲከፍል ፍ/ቤት አዘዘ፤ የክሡን ሒደትና የፍርድ ሐተታውን ሰነዶች ይመልከቱ

“ከሣሾች፤ ፕሬሱን ያለአግባብ በስም ማጥፋት ሲከሡ፣ ላንገላቱበት ተጠያቂዎች እንደሚኾኑ ለማሳየት ነው፤” /ጋዜጠኛ ፍሬው አበበ/

(አዲስ አድማስ፤ ዓለማየሁ አንበሴ፤ ቅዳሜ፣ ሰኔ ፲ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም.)

“ስሜን አጥፍቷል” በሚል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ የ100 ሺሕ ብር የካሳ ጥያቄ ያዘለ የፍትሐ ብሔር ክሥ ተመሥርቶበት፣ ከክሡ በነጻ የተሰናበተው የ“ሰንደቅ” ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ፍሬው አበበ፤ በፍርድ ሒደቱ የደረሰበትን ኪሳራ እና ወጪ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ እንዲከፍለው ፍ/ቤቱ አዘዘ፡፡

ጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ “የፓትርያርኩን ስም አጥፍተሃል” በሚል በዋና አዘጋጁ ላይ የመሠረተው የ100 ሺሕ ብር ክሥ ላይ ተከሣሹ ባቀረበው መቃወሚያ፣ ፍ/ቤቱ፤ “ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ፓትርያርኩን ወክሎ መክሠሥ አይችልም፤” የሚል ብይን መስጠቱን ተከትሎ፣ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በራሱ ስም ክሡን መመሥረቱ የሚታወቅ ሲኾን፣ ፍ/ቤቱ የግራ ቀኙን ማስረጃዎች ከመረመረ በኋላ “የጠፋ ስም የለም” ሲል ተከሣሹን በነጻ አሰናብቶታል፡፡

ተከሣሽም፤ “ያለአግባብ ክሥ ቀርቦብኝ ለወጪ እና ኪሳራ ተዳርጌያለኹ” በማለት ወጪ እና ኪሳራውን አስልቶ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ እንዲከፍለው አቤቱታ ያቀረበ ሲኾን፣ ፍ/ቤቱም፤ “ተገቢ ጥያቄ ነው፤ ይከፈለው” ሲል መወሰኑን፣ የተከሣሽ ጠበቃ አቶ ነብዩ ምክሩ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡

የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት፤ በዋና አዘጋጁ ላይ ያቀረበው ክሥ፣ በዲያቆን ዳንኤል ክብረት ተጽፎ በብሎጉ ላይ ከወጣ በኋላ፣ በጋዜጣው ላይ ባተመው ጽሑፍ፣ የፓትርያርኩንና የቤተ ክህነትን ስም አጥፍቷል፤ የሚል የወንጀል እና የፍትሐ ብሔር ክሥ የነበረ ሲኾን፣ ጋዜጠኛው ከኹለቱም ክሥ በነጻ መሰናበቱ ይታወሳል፡፡

በጉዳዩ ላይ አስተያየቱን ለአዲስ አድማስ የሰጠው ዋና አዘጋጁ ፍሬው አበበ፤ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እንዲከፈለው የጠየቀውን የገንዘብ መጠን ከመግለጽ ተቆጥቦ፣ ወጪ እና ኪሳራ ይከፈለኝ፤ የሚለውን አቤቱታ ያቀረበበትን ምክንያት ሲገለጽ፤ “ከሣሾች፤ ፕሬሱን ያለአግባብ በስም ማጥፋት ሲከሡ፣ ላንገላቱበት ተጠያቂዎች እንደሚኾኑ ለማሳየት ነው፤” ብሏል፡፡

************************************************
የፍርድ ሐተታውን ከዚኽ በታች ይመልከቱ፤

በቀረበው የስም ማጥፋት ወንጀል ክሥ፣ ዋና አዘጋጁን ነጻ ያደረገው የፍርድ ሐተታ፤

መ/ቁጥር 32710

ጥር 17 ቀን 2009 ዓ.ም.

ዳኛ፡- መሐመድ ሀጂ አቡበከር

ከሣሽ፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት – ነገረ ፈጅ አባ ገብረ ሥላሴ – ቀረቡ

ተከሣሽ፡- ፍሬው አበበ – ቀረቡ

መዝገቡ የተቀጠረው ፍርድ ለመስጠት ነው፤ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል

ፍርድ

መዝገቡ ሊቀርብ የቻለው፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት፣ በ18/08/08 በተጻፈ ክሥ በ2000 ዓ.ም. በወጣው የመገናኛ ብዙኃን ነጻነት ዐዋጅ ቁጥር 590/200 አቀንጽ 43/7/ እና የወ/ሕ/አ43/1/ሀ/ እና 613/3/ ሥር የተመለከተውን በመተላለፍ ተከሣሹ ዋና አዘጋጅ ኾኖ በሚሠራበት ጋዜጣ፣ በገጽ 20 ላይ፣ “ፓትርያርኩ፤ ለኢትዮጵያ የደኅንነት፣ለምእመናን የድህነት ሥጋት፤ የክርስቶስ አንዲት በግ መከራን ስትቀበል ከማይ እኔ የበጉ እረኛ መከራ መቀበል እመርጣለኹ” በሚል ርእስ በዳንኤል ክብረት ፀሐፊነት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተቋማዊ አሠራርን ጥላሸት የሚቀባና የቤተ ክርስቲያኒቱን ፓትርያርክ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያን ስም የሚያጠፋ፣ እንዲኹም በመልካም ስምና ዝናቸው ላይ ከባድ ጉዳት በማድረስ ሕዝበ ክርስቲያኑ የቤተ ክህነቱን ተቋማዊ አሠራር እንዳይቀበል ለማድረግ ማሰብ በተጻፈው ዓምድ ሥር የጽሑፉ ይዘትም በአንደኛ ዓምድ ላይ፣ “ምእመናንን የሚያጸና ጉባኤ ሊዘጋጅ ነው ሲሏቸው፤ ሕዝቡ ወደ ቤተ ክርስቲያን እየመጣ ነው ሲሏቸው፣ ወጣቱ ትውልድ ቤተ ክርስቲያኑን ለማገልገል እየተጋ ነው ሲሏቸው፤ ብዕራቸውን ይዘው ለማገድና ለመክሠሥ ይነቃሉ በማለት በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ግፍና በደል እንደተፈጸመ በማስቆጠር፣ የፓትርያርኩ ብዕር ምእመናንን የሚያጽናና ጦማር ለመጻፍ ወይም ድንግልን የሚያመሰግን ድርሳን ለመድረስ የሚጨበጥ አይደለም፤ እንደ ጠንቋይ ብዕር ለማፍዘዝና ለማደንዘዝ እንጂ” በማለት በተቋማቱ የሚጻፉ ደብዳቤዎች ተቀባይነት እንዳይኖራቸው በመቀስቀስ፤ ኹለተኛ ዓምድ ላይ፣ “የመንግሥት ባለሥልጣናት ሳይቀሩ የገዛ ልጆችዎን ያወያዩ ሲሏቸው፣ በራቸውን ጠርቅመው የሚዘጉ ፓትርያርኩ የመጀመሪያ ናቸው፡፡ በሱራፊ ነበልባል የተዘጋች ገነት ስትከፈት በፓትርያርክ የተዘጋች የቤተ ክህነት በር ልትከፍት አልቻለችም፤” በማለት የቤተ ክርስቲያኑ ተቋማዊ አስተዳደር እንደተዘጋና ህልውና እንደሌላት በመቁጠር፤ በሦስተኛው ዓምድ ላይ ዐውደ ርእዩ የማይደረግበት በቂ ምክንያት ከነበረ ቢያንስ ከሳምንት በፊት መግለጥ ይቻል ነበር በማለት በመንግሥታዊ አሠራር የታገደን ዐውደ ርእይ በቤተ ክህነቱ እንደ ታገደ አስመስሎ በማቅረብ ሕዝበ ክርስቲያኑ ለዐመፅ እንዲነሣሣ ለመቀስቀስ በማሰብ ኾን ብሎ፤ ዓላማው ግን ማበሳጨት፣ ዐመፅ ማነሣሣት፣ ተስፋ ማስቆረጥና ምእመናንን ወደማይፈለግ መስመር መውሰድ ነው በማለት ስውር ቅስቀሳ በማድረግ፡፡ እንዲኹም የዚች ሀገር ሰላም አይፈለገም? እና ሀገሪቱ ያለባት ችግር አይበቃትም? ተጨማሪ ችግር ማምረት ይፈልጋል? በማለት ሀገሪቱን ሰላም አልባ አድርጎ ከመቁጠሩም በላይ ቤተ ክርስቲያኒቱን የሀገር ደኅንነት ስጋት አድርጎ በመሣል፡፡ በአራተኛ ዓምድ ላይ፣ “ቤተ ክህነቱ የሚያመጣው ዳፋ አለ፤ በማለት አጠቃላይ የቤተ ክህነቱን መልካም ስምና ዝና ላይ ጥላሸት በመቀባት እንዲኹም የገዛ ፓትርያርካችን ለእኛ ለምእመናን ድኅነትን እንዳናገኝ ስጋት ኾነውብናል፤ የታገሡትን ኹሉ ለክፋት በማነሣሣት ደግ ለሀገሪቱ የደኅንነት ሥጋት እየኾነነው፤” በሚል ይዘት ያለው ጽሑፍ እንዲታተም በመፍቀድ እንዲታተም ያደረገ በመኾኑ የስም ማጥፋት ወንጀል ፈጽሟል በማለት ክሥ መሥርቷል፡፡

ለተከሳሽ ክሡና ማስረጃው ደርሷቸው በችሎት ከተነበበላቸውና እንዲረዱት ከተደረገ በኋላ፣ በክሡ ላይ ተቃውሞ እንዳላቸው ተጠይቆ ተቃውሞ አቅርበው በመቃወሚያው ላይ ብይን ተሰጥቶ የእምነት ክሕደት ቃል ሲጠየቁ፣ ድርጊቱን በተመለከተ አልፈጸምኩም፤ ጥፋተኛ አይደለኹም በማለታቸው ከሣሽ ማስረጃውን አሰምቷል፡፡

በከሣሽ በኩል የቀረበው፣ ሰንደቅ ጋዜጣ 11ኛ ዓመት ቁጥር 551 ረቡዕ መጋቢት 21 ቀን 2008 ዓ.ም. እትም፣ በከሣሽ በኩል የፓትርያርኩ እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ስም አጠፋ ብሎ የቀረቡት በክሡ ላይ የተጠቀሱት ስም የሚያጠፉ ሐሳቦች በጋዜጣው ገጽ 20 ላይ፣ በዳንኤል ክብረት ተጻፈ በሚል ታትሞ የወጣ ስለመኾኑና የዚህም ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ተከሣሽ መኾኑ በጋዜጣው ገጽ ኹለት የተገለጸ በመኾኑ በጋዜጣው ላይ የሰፈሩት ሐሳቦች የስም ማጥፋትን ወንጀል የሚያቋቁሙ በመኾናቸው ተከሣሽ በተከሠሡበት ወንጀል እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቷል፡፡

ተከሣሽ ቃሌን ልስጥ፣ በማለት በክሥ የቀረበውን ጽሑፍ “የኔ ሐሳብ” በሚል ነጻ አስተያየት ዓምድ ላይ ከማተማችን በፊት፣ በጸሐፊው/ዲያቆን ዳንኤል ክብረት/ ድረ ገጽ ላይ ወጥቶ አስተያየት ተሰጥቶበት እና ተተችቶ የነበረ እና እሳቸው ከአምስት ቀን በኋላ ለኅትመት ያበቁት መኾኑን ጉዳዩ ቀድሞ የተነገረ የሚያደርገው መኾኑን፤ ድርጊቱን የፈጸሙት፣ የፓትርያርኩ አመራር የሕዝብ ጉዳይ በመኾኑ ውይይት ይፈጥራል፣ እንዲኹም የቀረበውን ትችት ምላሽ ያገኛል በሚል ቅን ልቦና የፈጸሙት መኾኑን የምስክርነት ቃላቸውን ሲሰጡ፤ 2ኛ የተ/መ/ምስክር በጋዜጣ ላይ የወጣውን ጽሑፍ፣ እርሳቸው እንደጻፉት በመግለጽ ቅዱስ ፓትርያርኩ የቤተ ክህነት የበላይ ርእስ በመኾናቸው ተፈጸመ ያልኩትን የተለያዩ አስተዳደራዊ ችግሮች እንደተፈጸሙ ሒስ ነው የሰጠኹት፣ ያልኾነውን ኾነ ያልተደረገውን ተደረገ ከተባለ ምላሽ ሊሰጥበት እንደሚችልና ሊታረም እንደሚችል ገልጸው ሥራውን የሚሠራው ተቋም ሥራውን በበቂ ሠርቷል አልሠራም በሚል የሚቀርቡ ሐሳቦች ሒስ ናቸው አስተያየት የሚሰጥበት ክፍተትን ለመሙላት ነው በማለት የጻፉበትን ምክንያት በመዘርዘር የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡

በተከሣሽ ጠያቂነት የፌዴራል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሐምሌ 6 ቀን 2008 ዓ.ም. በተጻፈ ምላሽ፣ ጽሑፉ የችግሩ ምንጭ አስተዳደሩን በተለይም ፓትርያርኩ ችግሩ እንዲፈታ ከማድረግ ይልቅ ችግሩ እንዳይወጣ አፍነው ይዘዋል፤ በማለት የሚተችና መድረክ ይከፈትልን፣ በግልጽ እንነጋገር በማለት የመፍትሔ አቅጣጫ ጭምር የሚጠቁም ጽሑፍ ነው፡፡ በመኾኑም ጽሑፉ ስም ከማጥፋት ይልቅ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ውስጥ ያለውን የአስተዳደር ችግር የሚተች የግለሰብ አስተያየትና ሒስ /Opinion/ነው የሚል አስተያየት አለን በማለት የተሰጠ ምላሽ፤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሐምሌ 6 ቀን 2008 ዓ.ም በተጻፈ ምላሽ አራት የባለሞያዎችን ኮሚቴ በማቋቋም በጥልቀት የመረመረው መኾኑን በመግለጽ የታተመውን ጽሑፍ ውሸትነቱን ወይም እውነትነቱን ማረጋገጥ ያልተቻለ እና ጽሑፉ ግን ትችት ነው በማለት ምላሻቸውን የሰጡ ሲኾን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጋዜጠኞች ኅብረት ሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. በተጻፈ ምላሽ ከፍተኛ የትምህርት ዝግጅትና ልምድ ያላቸውን ሦስት አባላቱን በመምረጥ የመገምገሚያ ነጥቦችን በመለየት መመልከታቸውን ምክንያታቸውን ገልጸው የቀረበው ጽሑፍ የስም ማጥፋት መንፈስ/ይዘት/ የሌለው፣ በተቋሙ አሠራር ላይ በማተኮር የቀረበትችት/ሒስ/ መኾኑን ሞያዊ አስተያየታቸውን በመግለጽ የተላከው ምላሽ ከመዝገቡ ጋር ተያይዟል፡፡

የግራ ቀኙ ማስረጃ ከላይ በአጭሩ የተገለጸው ሲኾን፣ ተከሣሽ ባቀረቧቸው ምስክሮች የቀረበባቸውን ክሥና ማስረጃ አስተባብለዋል አላስተባበሉም የሚለውን ጭብጥ በመያዝ አግባብ ካለው ሕግ ጋራ በማገናዘብ መርምሯል፡፡

ተከሣሽ በሰጡት የምስክርነት ቃል፣ ጽሑፉ ቀደም ሲል በድኅረ ገጽ ላይ የወጣና እርሳቸውም ያቀረቡት ስምን ለማጥፋት ሳይኾን ለውይይት በር ይከፍታል በሚል ሐሳብ መኾኑን የገለጸ ሲኾን፤ በመከላከያ ምስክርነት የቀረቡት ምስክር ጽሑፉን ያዘጋጁት መኾኑንና ያዘጋጁበትም ምክንያት ስም ለማጥፋት ሳይኾን፣ ለውይይት መነሻ ለማድረግ ነው፤ በማለት የምስክርነት ቃል የሰጡ ሲኾን፣ ይህን የተከሣሽ እና የምስክሩን ቃል በሚያጠናክር ኹኔታ በተከሣሽ አስተያየት እንዲሰጡ የተጠየቁት ተቋማት በሰጡት ምላሽ በፀሐፊው የቀረበው ጽሑፍ፣ የስም ማጥፋት ሳይኾን የትችት ይዘት እንዳለው መግለጻቸው ተቋማቱም ሦስት ተቋማት በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን አማካይነት በእንደዚህ ዓይነት የሚሰጡ አስተያየቶች ላይ ቀጥተኛና የሚመለከታቸው ተቋማት መኾናቸውና በከፍተኛ ባለሞያዎች ታይቶ መቅረቡ ሲታይ ተከሣሽ ለቀረበባቸው ክሥና ማስረጃ የሚያስተባብልበ መኾኑ የተከሠሡበትን ወንጀል በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ149/2/ መሠረት በነጻ እንዲሰናበቱ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

ትእዛዝ

የተከሣሽ ዋስትና እንዲመለስ ታዟል፤
ይግባኝ መብት ነው፤ ተገልጿል፤
መዝገቡ ተዘግቷል፡፡
+++++++++++

የ100ሺሕ ብር የኅሊና ጉዳት ካሳ በቀረበበት ክሥ ተከሣሽ በነጻ የተሰናበት የፍርድ ሐተታ፤

የኮ/መ/ቁ 32717

ቀን፡-17/08/09

ቂርቆስ ምድብ 2ኛ ፍትሐብሔር ችሎት

ዳኛ፡- ዮሲያድ አበጀ

ከሣሽ፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት

ነገረ ፈጅ አባ ገብረ ሥላሴ ጌትነት፦ ቀረቡ

ተከሣሽ፡- አቶ ፍሬው አበበ፦ ቀረቡ

መዝገቡ ለዛሬ የተቀጠረው መርምሮ ለመወሰን ነው፡፡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

ፍርድ፡-

ለዚህ ፍርድመነሻ የኾነው፣ ከሣሽ ኅዳር 14 ቀን 2009 ዓ.ምአሻሽሎ ያቀረበው በኅትመትና ሚዲያ የተፈጸመ የስም ማጥፋት ጉዳይክሥ ጥያቄ መሠረት ያደረገ ክርክር ነው፡፡

የተሻሻለ የክሥ ይዘት፣ ተከሣሽ ከመገናኛ ብዙኃን የዘገባ ሥነ ምግባር አንጻር፣ ማንኛውም ዘገባ አስቀድሞ ለሕዝብ ከመሠራጨቱ በፊት፣ በማስረጃ አስቀድሞ የባላንሲንግ ምዘና ሥራ መሠራት ሲገባው፣ ከዚህ ሚዛናዊ አሠራር ውጪ በኾነ መንገድ፣ ራሱን ተከሣሽ ዋና አዘጋጅ ኾኖ በሚሠራበት የሰንደቅ ጋዜጣ 11ኛ ዓመት ቁጥር 551፤ ረቡዕ፣ መጋቢት 21 ቀን 2008 ዓ.ም በወጣው ዕትሙ ገጽ 20 ላይ፦

1ኛ. በአንደኛ ዓምድ ላይ፣ የቤተ ክርስቲያኑ ዋና የበላይ መዋቅርና አስፈጻሚ የኾነውን ቤተክህነቱን፣የኑፋቄ ማኅደር ኾኗል፤ በማለት ምእመናን ቤተክህነቱን እንዲጠሉ የሚያደርግ ዘገባ በማውጣት እና ያለምንም በቂ ማስረጃ ከእንጦጦ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ግማሽ ሚሊዮን ብር በአንድ ሙሰኛ ተዘረፈ በማለት ሐሰተኛ ወሬ በመንዛት፣

2ኛ. በዘገባው 2ኛ ዓምድ ላይ፣በሱራፊ ነበልባል የተዘጋች ገነት ስትከፈት በፓትርያርክ የተዘጋች የቤተክህነት በር ልትከፈት አልቻለችም፤በማለት ከሀገር አቀፍም አልፎ ዓለም አቀፍ አገልግሎት በመስጠት ላይ ያለውን የቤተክህነት መዋቅር እንደተዘጋ በማስመሰል የቤተ ክርስቲያኒቱን ተቋም ዋና አስተዳደር ጽ/ቤት እንደተዘጋ እና ህልውና እንደሌለው አስመስሎ ሐሰተኛ ወሬ በመንዛት፤

3ኛ. በሦስተኛ ዓምድ ላይ፣ዐውደ ርእይ የማይደረግበት በቂ ምክንያት ከነበረ ቢያንስ ከሳምንት በፊት መግለጽ ይችል ነበር፤ በማለት በመንግሥት ተቋማዊ አሠራር የታገደን የማኅበረ ቅዱሳንን ዐውደ ርእይ በቤተክህነቱ እንደታገደ አስመስሎ በማቅረብ ሕዝበ ክርስቲያኑ ለዐመፅ እንዲነሣሣ ለመቀስቀስ በማሰብ ኾነ ብሎ በጽሑፍ ላይ ቃል በቃል ዓላማው ግን ማበሳጨትዐመፅማሥነሳት ተስፋ ማስቆረጥ እና ምእመናንን ወደማይፈልጉት መስመር መውሰድ ነው፤ በማለት ስውር ቅስቀሳ በማድረግ፤እንዲኹም፣የዚኽች ሀገር ሰላም አይፈለግም? ሀገሪቱ ያለባት ችግር አይበቃትም? ተጨማሪ ችግር ማምረት ይፈልጋል? በማለት ሀገሪቱን ሰላም አልባ አድርጐ ከመቁጠሩም በላይ ቤተ ክርስቲያኒቱ የሀገር ደኅንነት ስጋት አድርጐ በመሳል፤

4ኛ. በአራተኛ ዓምዱ ላይ፣ቤተክህነቱ በሚያመጣው ዳፋ መንግሥት መከራ ለመቀበል ዝግጁ ነው፤በማለት ወደ ፊት በሀገሪቱ ላይ ቤተክህነቱ የሚያመጣው ዳፋ አለ፤ ዓይነት በሚመስል አገላለጽ አጠቃላይ የቤተክህነቱ መልካም ስምና ዝና ላይ ጥላሸት በመቀባት በጥንታዊና ታሪካዊ እንዲኹም የሀገር ባለውለታ በኾነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር ላይ የስም ማጥፋትና ክብረነክ ስድብ የተፈጸመ በመኾኑ፣በዐዋጅ ቁጥር 590/2000 አንቀጽ 41 ንኡስ ቁጥር 1 እና 2 መሠረት፣ 100,000 (አንድ መቶ ሺሕ) ብር የኅሊና ጉዳት ካሳ እንዲከፈለን ከወጪና ኪሣራ ጋር ይወሰንልን፤ የሚል ነው፡፡

ከሣሽ ለክሡ አስረጅነት የማስረጃ ዝርዝር መግለጫ በማዘጋጀት፣ የሰው ምስክሮች ስም ዝርዝር የሰነድ ማስረጃ ዝርዝር ጠቅሶ ከክሡ ጋራ የሰነድ ማስረጃ ግልባጩን በማያያዝ አቅርቧል፡፡

የተከሣሽ መልስ፣ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ እና የፍሬ ነገር መልስ የያዘ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ ብይን ተሰጥቶ የታለፈ በመኾኑ ድጋሚ በዚኽ ፍርድ ላይ አልተመዘገበም፡፡

የተከሣሽ የፍሬ ነገር መልስ ይዘት፣ በ5 (አምስት) ንኡስ ዝርዝሮች ተከፍሎ የቀረበ ነው፡፡ እንደ መልሱ አቀማመጥ አንድ በአንድ ስንመለከተው፡-

1ኛ. ለክሡ ምክንያት የኾነው ጽሑፍ ሚዛናዊነቱን ጠብቆ የታተመ ጽሑፍ ነው፡፡ በጋዜጠኝነት ሞያ ሚዛናዊነትን መጠበቅ ዋነኛ መርሕ ቢኾንም፣ ለክሥ ምክንያት የኾነው ጽሑፍ የተካተተው መደበኛ የሕዝብ አስተያየት በሚስተናገድበት “የእኔ ሐሳብ”በሚለው የጋዜጣው ዓምድ ሥር ነው፡፡በዚህዓምድ ሥር የሚነሡት ሐሳቦች፣የጸሐፊው ወይም የዓምደኛው ሐሳብ እንጂ የኤዲቶሪያል አቋም እንደማያንፀባርቅ በግርጌው ላይ በግልጽ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ የዚህ ዓይነት ዓምድ መፈጠር ዋነኛው ዓላማ፣ ዜጐች በሀገራዊ ጉዳይ እና የሕዝብ ጥቅሞች በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሐሳባቸውን እንዲያንሸራሽሩ ለማበረታታት እና የውይይት ባህል ለማዳበር፣በዚህም ተቋማት እና ሕዝብ መሃል መተማመንን መፍጠር፣ ችግሮች ሲኖሩም በውይይት እንዲፈቱ እገዛ እንዲያደርግ ነው፡፡ እንዲኽ ዓይነት ተግባር ደግሞ የሕግ ጥበቃ ያለው እንጂ የስም ማጥፋት ድርጊት አይደለም፡፡

2ኛ. ከሣሽ ያልተሻሻለ ክሥ ሲያቀርብ፣ ፓትርያርኩን የሚመለከቱ ፍሬ ነገሮች ላይ የመክሠስ መብት የለውም፤ ተብሎ ብይን ተሰጥቷል፡፡ ከሣሽ ከዚህ ተቃራኒ የቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ መዋቅርና ሥራ አስፈጻሚ የኾነው፣ ቤተክህነቱ የኑፋቄ ማኅደር ኾኗል፤ በሱራፊ ነበልባል የተዘጋች ገነት ስትከፈት በፓትርያርክ የተዘጋች የቤተ ክርስቲያን በር ልትከፈት አልቻለችም፤ በሚል የቀረበው ጽሑፍ፣ ፓትርያርኩን የሚተች እንጂ የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደር አይደለም፡፡ በጽሑፉ ላይ በግልጽእንደሰፈረው፣ቤተክህነቱ የኑፋቄ ማኅደር ሲኾን ፓትርያርኩ ይተኛሉ፤ በሚል ስም ተጠቅሶ የተጻፈ በመኾኑ፣ ግለሰቡ ፓትርያርኩን እንጂ ቤተክህነቱን አይመለከትም፡፡

3ኛ.ለክሥ ምክንያት የኾነው ጽሑፍ የቀረበው፣ በበቂ ማስረጃ ላይ ተመሥርቶ እንጂ ያለማስረጃ የቀረበ አይደለም፡፡ጠቅላይ ቤተክህነቱ ከላይ እስከታች ባለ መዋቅር፥ ውስጠ ብልሹ አሠራር፣ የመልካም አስተዳደር ችግር መኖሩ ቤተክህነቱ የኑፋቄ ስውር እንቅስቃሴ ችግር ውስጥ ስለ መግባቱም ኾነ ከእንጦጦ ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ግማሽ ሚሊዮን ብር በአንድ ሙሰኛ መዘረፍ ሐሰተኛ ወሬና ስም ማጥፋት ሳይኾን በራሷ በቤተክርስቲያኒቱ ተደጋጋሚ መግለጫ የተሰጠበት የታመነ ጉዳይ ከመኾን አልፎ፣ በሰነድ ማስረጃ የተደገፈ፤ ለማሻሻል ቃል የተገባበት ጉዳይ በመኾኑ ስም ማጥፋት ሊኾንአይችልም፡፡

4ኛ. ከሣሽአንዳንድየጽሑፉን ይዘቶች ከሙሉ ይዘቱ በመነጠል ቃላትን በመምዘዝ በራሱ አረዳድ ስም ማጥፋት ነው ሲል ፈርጆ ክሥ ማቅረቡ በአግባቡ አይደለም፡፡“በሱራፊ ነበልባል የተዘጋች የገነት በር ስትከፈት በፓትርያርክ የተዘጋች የቤተክህነት በር ልትከፈት አልቻለችም፤”የሚለው ሐሳብ፣ ፓትርያርኩ ለውይይት በራቸውን አልከፈቱም፤በሥራቸው ላይ ግልጽ የውይይት መድረክ የለም፤ የሚለውን እንጂ የቤተክህነት በር ተዘግቶ አገልግሎት ስለማቆም የሚገልጽ አይደለም፡፡ማኅበረ ቅዱሳን ያዘጋጀው ዐውደ ርእይ ቤተክህነቱ ያገደው ስለ መኾኑ በጋዜጣው የትኛውም ገጽ ላይ አልሰፈረም፡፡ በግልፅ በጋዜጣው ላይ በሰፈረው ጽሑፍ፣ በስውር ምእመኑን ለዐመፅ እንዲነሣሣ ሊያደርግ የሚችል ቅስቀሳ የለም፡፡ይህ ባልኾነበት ስም ማጥፋት የለም፡፡

5ኛ. ለክሥ ምክንያት የኾነው ጽሑፍይዘቱ፣ ትችት ወይም ሒስ እንጂ የስም ማጥፋት ተግባር አይደለም፡፡የጽሑፉ አጠቃላይ ይዘት፣ ቤተክህነቱ በየደረጃው ባለው አስተዳደር የሙስና እና ብልሹ አሠራር፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና የመናፍቃን እንቅስቃሴ መኖራቸውን፤በጊዜ እልባት ያልተሰጠው መኾኑ፣ በወቅቱ ችግሩ ካልተቀረፈ ደግሞ ዳፋው ለሀገር እና ለመንግሥት ሊተርፍ እንደሚችል በመግለጽ የተሰጠ ትችት ወይም ሒስ እንጂ የስም ማጥፋት ተግባር አይደለም፡፡

ስለኾነምፍ/ቤቱ ክሡን ውድቅ በማድረግ ተከሣሽ ከወጪና ኪሣራ ጋራ እንድንሰናበት ይወሰንልንየሚል ነው፡፡

ተከሣሽለመልሱ አስረጅነት የማስረጃ ዝርዝር መግለጫ አቅርቧል፡፡ በዝርዝር መግለጫው ላይ፥ የሰው ምስክሮች ስም በማስፈር የሰነድ ማስረጃ ዝርዝር ጠቅሶ ግልባጩን በማያያዝ አቅርቧል፡፡

የግራ ቀኙ የጽሑፍ ክሥና መልስ ከላይ የተገለጸው ሲኾን፣ ፍ/ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር በችሎት ለመስማት ቀጠሮ ይዞ የክርክሩን ጭብጥ በመለየት ክርክር ሰምቷል፡፡

ከሣሽ በቀረበው የሙግት ክርክር፣ ከሣሽ የሃይማኖት ተቋም በመኾኑ፣ ሰው ሃይማኖትን የሚወስነው በተረዳውና ባመነው ልክ በኅሊናው በመኾኑተከሣሽ ጽሑፉን በጋዜጣ ከማተሙ በፊት የ3ኛወገን ጥቅም የሚነካ ስለ መኾኑማጣራት አለበት፡፡ ኾኖም ተከሣሽ ቤተ ክርስቲያን ተዘጋች ሲል ዘግቧል፡፡

ይህ ቤተ ክርስቲያኗ አገልግሎት አቆመች፤ ወደሚል ድምዳሜ የሚያመጣ ነው፡፡ ይህም የተቋሙን ክብር ይነካል፡፡

ተከሣሽ በሌሎች የጽሑፍ ይዘት፣ ቤተ ክርስቲያን በሚጐዳ መልኩ ዘግቧል፡፡ቤተ ክርስቲያን ለበጐርዳታ ያደረገችውን በሐሰት ስም በሚያጠፋ መልኩ ዘግቦታል፡፡ድጋፍ ይደረግ ተብሎ ተወስኖ የነበረ ቢኾንም፣ ገንዘቡ እንዳይወጣ በፓትርያርኩ ታግዷል፡፡ ኾኖም ይህን ተከሣሽ ዘረፋ አድርጐ ዘግቦታል፡፡

ቤተ ክርስቲያን የራሷየኾነ አደረጃጀት አላት፡፡ ከዚህ ውስጥ በመምሪያ ሥር የተደራጀውማኅበረ ቅዱሳን አንዱ ነው፡፡ማኅበረ ቅዱሳን የተለያዩ እንቅስቃሴዎች አሉት፡፡ዐውደ ርእይ ያዘጋጃል፡፡ ዐውደ ርእይ ሲያዘጋጅ እንዲፈቀድ ደብዳቤ የጻፈው ከሣሽ ነው፡፡ ዐውደ ርእይ ከተፈቀደ በኋላ ኤግዚብሽን ማዕከሉፈቃደኛ ሳይኾን ቀረ፡፡ኤግዚቢሽን ማዕከሉ ፈቃደኛ ያልኾነው ፖሊስ፥ ከተማ አስተዳደሩ ይፍቀድ፤ ብሏል፣ በሚል ነው፡፡እውነታው ይህ ኾኖ እያለ ተከሣሽ ዐውደ ርእዩን ቤተክህነት እንዳገደ በማስመሰል ጽፏል፤ ዓላማው ሌላ ነው፤ ብሏል፤ ቤተክህነቱ ላይ የሰላም ችግር እንዲፈጠር ቀስቅሷል፤ በዚህም ስማችንን አጥፍቷል፡፡ ቤተክህነቱ የበርካታ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ኾኖ እያለ፣ ቤተ ክርስቲያንን ከሐዲ ይመራታል፤ በማለት ዘግቧል፡፡

ስለዚህ ጉዳይ ቅዱስ ሲኖዶስ መክሯል፤ የመከረው ስለ መንፈሳዊ ኮሌጆች ነው እንጂ ስለቤተክህነቱ አይደለም፡፡ቤተ ክርስቲያኗም ብትኾንርምጃ ወስዳለች፤ እየወሰደች ነው፤ እየተጣራም ነው፤ ቤተክህነት በዚህ ረገድ ጥፋት የለበትም፡፡የጋዜጠኞች ማኅበር እና አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጽሑፉን ገምግመው የሰጡት አስተያየት፣ በተከሣሽ መከላከያ ማስረጃ ቀርቧል፡፡ ይኹን እንጂ የጋዜጠኞች ማኅበር፣ ተከሣሽ አባል የኾነበት ማኅበር በመኾኑ ገለልተኛ ኾኖ አስተያየት ለመስጠት አይችልም፡፡አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አስተያየት እንዲሰጥ ሲጠየቅ የተሰጠው ምርጫ፣ ጽሑፉ ሒስ ነው ትችት የሚል ነው፡፡ በዚህ ምርጫ የተሰጠ አስተያየት፣ ገዥ ሊኾን አይገባም፤ በማለት የክሥ አቤቱታውን በማጠናከር ተከራክሯል፡፡

ተከሣሽ በችሎት በቀረበው ክርክር ስም ማጥፋት እና አስተያየት መስጠት መሃል ሰፊ ልዩነት አለ፤የሐሳብ ነጻነት በሕገ መንግሥት ተፈቅዷል፡፡ በሐሳብ ነጻነት አንድ ልዩ ኹኔታ ስም ማጥፋት ነው፡፡ስም ማጥፋት፣የሐሳብ ነጻነት ልዩ ኹኔታ እንደመኾኑበጠባቡ መተርጐም እንዳለበት የሕግ መርሕ ነው፡፡ የተከሠሠበትን ጽሑፍ “የእኔ ሐሳብ” በሚል ዓምድ ሥር በመጻፉ፥ ይህ ዓምድ የጸሐፊውን እንጂ የጋዜጣውን ሐሳብ አያንፀባርቅም፤ የዜጐችን ሐሳብ ነው፡፡ ይህ የሚኾነው ለውይይት ነው፡፡ ጋዜጣው ይህን በማድረጉ ስም አጥፍቷል ሊባል አይገባም፤ የጽሑፉ ዋና ይዘት ፓትርያርኩን የሚተች ነው፡፡ ፓትርያርኩ በበዓለ ሢመታቸው ላይ ሙስና እና ኑፋቄ መሮናል፤ በማለት ተናግረው ችግሩን ለመፍታትአልሠሩም በሚል የቀረበ ነው፡፡

ለክሡ ምክንያት የኾነውም፣ከዚሁ ጽሑፍ የተቀነጨበ ነው፡፡ተቋምን የሚመለከት ሒስ እንኳን አላቀረብንም፡፡ ጽሑፉ ውስጥ የተዘረዘሩ ይዘቶች በሙሉ ማስረጃ የቀረበባቸው ናቸው፡፡ቤተ ክርስቲያን፥ በውስጤ ሙስና አለ፤ በማለት ኮሚቴ አቋቁማለች፤ ከዚህ ውስጥ ተከሣሽ ሙስና መኖሩን ጠቅሶ ቢዘግብ ስሕተት አይኾንም፡፡ ከሣሽ አንዳንድ የጽሑፉ ይዘት በራሱ መንገድ ተርጉሞ አቅርቧል እንጂ ተከሣሽ ጋዜጣ ላይ ያወጣው እንደ ከሣሽ አገላለጽ አይደለም፡፡ተከሣሽ፣ ቤተ ክርስቲያን ተዘጋ አላለም፡፡ስም ማጥፋት ማለት፣ያልኾነን ኾኗል ብሎ መዘገብ ነው፡፡ተከሣሽ ያተመው ጽሑፍ፣ ፓትርያርኩ በተሰጣቸው ሥልጣን አልሠሩም በሚል የመፍትሔ አካል ኾነን ነው፡፡

ጽሑፉ ስም ማጥፋት አለመኾኑንየመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤት ገልጿል፡፡ይህ ጽ/ቤት፣ ዐዋጅ ቁጥር 590 በበላይነት እንዲጠበቅና እንዲያስፈጽም የተቋቋመ ነው፡፡ አስተያየቱ ገዥ ነው፡፡ የጋዜጠኝነት ማኅበር ተቋም ነው፤ አስተያየት የሰጠው ኮሚቴ መርምሮ ነው፤ ተከሣሽ የኮሚቴው አባል አልነበረም፡፡ ስለኾነም አስተያየቱ አግባብ ነው፡፡

የአዲስአበባ ዩኒቨርስቲ ኮሚቴ አቋቁሞ፣ ጽሑፉን መርምሮ ምሁራዊ አስተያየት ሰጥቷል፡፡

በአጠቃላይ የከሣሽ ክሥ፣ የፍሬ ነገር እና ማስረጃ ድጋፍ የሌለው በመኾኑ ክሡ ተዘግቶ ከክርክሩ እንሰናበት በማለት ተከራክረዋል፡፡

ከሣሽ በማጠቃለያ ክርክር፣ ስም ማጥፋት፣ሐሳብን በነጻ የመግለጽ ሽፋንን በመጠቀም ሊፈጸም አይገባም፤ ተከሣሽ ልዩ ኹኔታ ብሎ መተርጐም አለበት፤ በማለት የገለጸው መርሕየሕግ ድጋፍ የለም፤ በ“የእኔ አስተያየት” በቀረበ ጽሑፍ ተከሣሽ አልጠየቅም ሊል አይችልም፡፡ሕጋዊ ግዴታ አለበት፤ ሙስና መኖሩን ከሣሽ አልካደም፤ ኾኖም ክሥ የቀረበው፣ የግለሰብ ስም ተጠቅሶ ያልኾነው ኾኗል በማለት በማጻፍ ነው፤ የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ራሱን የቻለ ሲኾን ከሣሽ ራሱን የቻለ ነው፡፡ፓትርያርኩ በር ቢዘጉ የልዩ ጽ/ቤታቸውን እንጂ የከሣሽን አይደለም፡፡ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ዐዋጅ የመጠበቅ የተለየ ሥልጣን አልተሰጠውም፤ አስተያየቱም ገዥ አይደለም፤ ለተቋማት ትእዛዝ የተሰጠው ሒስ ነው ወይስ ትችት በሚል ነው፡፡ በዚህ መነሻ የሚሰጡት አስተያየት ገዥ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ለድምዳሜው መመዘኛ ያላስቀመጠ ሲኾን፤አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ እውነት መኾኑን አልደረስኩበትም፤ ብሏል፡፡ ይህ የተሟላ ማስረጃ ሳይደርሰው የሰጠው አስተያየት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማኅበር፣ ገለልተኛ አይደለም፤ አልን እንጂ አስተያየቱ ሕገወጥ ነው አላልንም በማለት ተከራክሯል፡፡

ግራ ቀኙ በተያዘው ጭብጥ አግባብ ምስክር አቅርበው እንዲያሰሙ ታዘው ከሣሽ 2 (ኹለት) ምስክሮች አቅርቦ አንዱን ብቻ አሰምቷል፡፡

የከሣሽ ምስክር የኾኑት መምህር ሙሴ ኃይሉአስገዶም፣ ሥራቸው የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ፕሮቶኮል መኾናቸውን ገልጸው፣ሰንደቅ ጋዜጣ ላይ የወጣውን ጽሑፍ በጸሐፊው የግል ብሎግላይ ወጥቶ አውቀው ነበር፤በጋዜጣ ወጥቶ አንብቤዋለኹ፤ ጽሑፉ የቤተ ክርስቲያን ስም የሚያጠፋ ነው፤ ቤተክህነት ከሲኖዶስ ቀጥሎ ከፍተኛ የቤተ ክርስቲያን አመራር ነው፤ አርኣያ አመራሮች ያሉበት ነው፤ኾኖም ጽሑፉ ሠራተኞች የኑፋቄ ማኅደር ናቸው፤ ሲል ጽፏል፡፡ ከእንጦጦ ማርያም ግማሽ ሚሊዮን ተዘረፈ፤ ይላል፤ኾኖም ይህ ገንዘብ ሊወጣ የነበረ ቢኾንም ታግዷል፡፡ የዐውደ ርእይ ሐተታ ይዟል፡፡ ኾኖም ቅዱስ ፓትርያርኩ ዐውደ ርእይ ሲፈቀድም ሲታገድም አያውቁም፤ መነሻ ሳይኖረው ነው የጻፈው፤ ከፓትርያርኩ የወጣ መረጃም ደብዳቤም የለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን በየትኛውም ወቅት ተዘግቶ አያውቅም ፓትርያርኩ ቤተ ክርስቲያን ለመዝጋትና ለመክፈት አይችሉም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለሀገር አዎንታዊ አስተዋፅኦ ከማድረግ በዘለለ ለሀገር ዳፋና ስጋትኾና አታውቅም፡፡በሥነ ጽሑፍ እና ሥነልሳን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ 2ኛ ዲግሪ አለኝ፤የተከሣሽን ጽሑፍ ለመገምገምና ድምዳሜ ላይ ለማድረስ ዕውቀቱ የለኝም፡፡ ከእንጦጦ ኪዳነ ምሕረት ሊወጣ የነበረው በሒሳብ ክፍል ጥቆማ መነሻ ታግዷል፡፡ በጽሑፍ ምክንያት የሚደረስ ጉዳት አለ፤ አማኙ በቤተ ክርስቲያን ላይ ጥርጣሬ እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ ፓትርያርኩ ዐውደ ርእይ እንዲዘጋ አድርጓል፤ ሲባል ሰው ይጠራጠራል፡፡ የፓትርያርኩ የፕሮቶኮል ሓላፊ ነኝ፤ ለ3 ዓመት ሠርቻለኹ፤ አጠቃላይ እንቅስቃሴያቸውን አውቃለኹ፤ ፓትርያርኩ ምእመናንን የሚያስተናግዱበትን ኹኔታ አውቃለኹ፤ ፓትርያርኩ ያላስተናገደው ባለጉዳይ/ምእመናን ስለመኖሩ አላውቅም፤ኾኖም በማኅበረ ቅዱሳን በኩል፣ ፓትርያርኩ አልሰሙንም፤ አላናገሩንም፤ በማለት ቅሬታ እንደሚያቀርቡ እሰማለኹ፤ ማኅበሩ በርካታ አባላት አሉት፤የጽሑፉ ጸሐፊ የማኅበሩ አባል እንደነበር አውቃለኹ፡፡ የአ.አ ሀገረ ስብከት ሓላፊ የነበሩ አመራር፣ ከእንጦጦ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ገንዘብ የተነሳ ከሓላፊነት መነሣታቸውን አውቃለኹ፤ ገንዘቡ አልጠፋም፤ ተዘረፈ የሚለው ቃል አግባብ አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የሌላ ሃይማኖት ተከታይ ሰዎች እንቅስቃሴ መኖሩ ይነገራል፤ በቤተ ክርስቲያን ደረጃና በኮሌጆች ሊኖር ይችላል፡፡ በአብያተ ክርስቲያን ሊኖር ይችላል፤ ይህ ተጠቅሶ ማኅደር ነው ለማለት ግን አይቻልም፤ በማለት መስክረው ተመልሰዋል፡፡

ከሣሽ ቀሪ ምስክር የተለየ አያስረዳም፤ በሚል እንዲሰናበት ጠይቆ የምስክርነት ቃል ሳይሰጥ ተሰናብቷል፡፡ የተከሣሽ ምስክሮች በተመለከተ፣ አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የምስክርነት ቃላቸውን በጽሑፍ እንዲሰጡ ብይን ተሰጥቶ፣ የካቲት 21 ቀን 2009 ዓ.ም.በተጻፈ ጽሑፍ ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡

ይዘቱምየቤተ ክርስቲያኑ ሲኖዶስ ያቋቋማቸው ኮሚቴዎች ማለትም፦የሙስና ዐብይ ኮሚቴ፤ የአስተዳደር መሻሻል ዐብይ ኮሚቴ እና የገንዘብ አያያዝ ሥርዓት ማሻሻያ ዐብይ ኮሚቴማቋቋም ያስፈለገው፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ዘመኑን የዋጀ ይኾን ዘንድ እና የተሻሻለ የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት ይቻል ዘንድ ነው፡፡ በዚኽም የሒሳብ አሠራር ከሲንግል ኢንትሪ ወደ ደብል ኢንትሪ ተቀይሯል፡፡ ሕገ ቤተ ክርስቲያን እና ቃለ ዐዋዲው በ2007 ዓ.ም. ተሻሽሎ የተሻለ ውጤትተመዝግቧል፡፡

የመልካም አስተዳደር ዕጦት እና የሙስና ጉዳይ አጥንቶ የችግሩን መነሻና መፍትሔ የሚያጠና ኮሚቴ ተቋቁሟል፤ ችግሩ በአንድ ጀንበር መፈታት አይቻልም፤ለዚኽም አስፈላጊ በኾነ ጊዜ በቅዱስ ሲኖዶሱ ሲታመንበት ኮሚቴ ይቋቋማል፤የሚለውም ለኮሚቴው በሚሰጠው ዝርዝር ተግባሩ ነው፤ ጥራቱም ገና ተጠናቆ ለሲኖዶሱ አልቀረበም፤ ውጤቱ በቀጣይ ውሳኔ ሲሰናበት የሚታይ ይኾናል፡፡ መናፍቅ ማለት በቤተ ክርስቲያኒቱ ዶግማና ቀኖና የማያምነውን መናፍቃን በቤተ ክርስቲያኒቱ ተስፋፍቷል የሚለው ጥያቄ ችግር አለበት፤ የተከሣሽ ጋዜጣ ጽሑፍ ቤተ ክርስቲያኑ የኑፋቄ ማኅደር ኾኗል የሚል ነው፡፡ ይህ ከቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ ውጪ የቤተ ክርስቲያኒቱን ስም ለማጥፋት የተጻፈ ነው፡፡ከእንጦጦ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ግማሽ ሚሊዮን ብር ሊወጣ የነበረው ለስጦታ ሳይሆን በከፍተኛ ደረጃ በሕመም በመሠቃየት ላይ ላለ በሽተኛ ሕክምናው በሀገር ውስጥ አይቻልም፤የሚል ድምዳሜ ላይ በመድረሱ የውጪ ሀገር ለማሳከም ይቻል ዘንድ ኮሚቴ ተዋቅሮ ገቢ ለማሰባሰብ በቀረበው ጥያቄ መነሻነት ለማሳከሚያ በርዳታ መልክ እንዲሰጥ በገዳሙ አስተዳደር ኮሚቴ የተወሰነ ቢኾንም፣ውሳኔው ከመፈጸሙ በፊት አመራር በመስጠት እንዳይከፈል አድርጌያለኹ፤ በጋዜጣው ላይ ግን የተጻፈው ግማሽ ሚሊዮን ብር ተዘረፈ የሚል ነው፡፡ያልወጣ ገንዘብ ወጣ ብሎ መዘገብ አግባብ አይደለም፡፡ ገና ገንዘቡ ሳይወጣ እንዲቀር የተደረገ በመኾኑ፣ለሕዝብ የሚነገርበት አግባብ ባለመኖሩርምጃው ለሕዝብ አልተነገረም፡፡የመልካም አስተዳደር ጉድለት እና የሙስና ችግር ለመቅረፍ ቤተ ክርስቲያኒቱ በበርካታ መድረክአስተምራለች፡፡ የፀረ ሙስና ተቋም ጋር የኮሚቴ አባል በመኾን ሠርታለች፡፡ ቤተክህነት ምእመናንን ለማወያየት ምን ጥረት ተደርጓል? ለተባለው ቤተክህነት በፌዴራል ደረጃ ያለ ነው፤ በመቀጠል የዞን ሀገረ ስብከት ቀጥሎ ወረዳ ቤተክህነት የመጨረሻው አጥቢያ ሰበካ ጉባኤ ያለው አደረጃጀት አለ፡፡ ምእመን ተሰባስበው የሚወያዩበትናራሳቸውን ጠቅላላ ጉባኤ አባልነት የሚሳተፉበት በአጥቢያ ሰበካ ጉባኤ ነው፤ ቅሬታ ሲኖር በየደረጃው ይስተናገዳሉ፡፡ በቤተክህነት የታገደ ዐውደ ርእይ የለም፤ የታገደው በኤግዚብሽን ማዕከሉ በራሱ አሠራር ነው፡፡ ቤተክህነት ሀገር ላይ ዳፋ ታመጣለች፤ በማለት በጋዜጣው የተጻፈው ከዐውደ ርእይ መታገድ ጋር በተያያዘ የጽሑፍ ክፍል ነው እንጂ ጸሐፊው ዳፋ የሚመጣው በሌላ መልካም አስተዳደር ችግር መኾኑን ጸሐፊው ባልገለጸበት፣ በፍ/ቤት የቀረበ ጥያቄ ግልጽነት የጐደለውና ሀገር አቀፋዊ የመልካም አስተዳደር አጀንዳ ተላብሶ የቀረበ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሀገር ላይ ዳፋ አምጥታ አታውቅም፤ ወደፊትም አታመጣም፡፡ የቤተ ክርስቲያን አመራሮች ሥራቸው ለምእመናን ክፍት ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ የሌላ ሃይማኖት ተቋም እንቅስቃሴ የለም፡፡ በጋዜጣ የታተመው ጽሑፍ የተጻፈው ስም ለማጥፋት ነው፤ ለዚህም በሐሰት የተጻፈ የጽሑፍ ይዘቶች ማሳያ ናቸው፡፡የጸሐፊው እና አሳታሚው የመለየት ሐሳብ በራሳቸው ኅሊና ውሳኔ በመኾኑ የቤተ ክርስቲያኑን ስም ለምን እንደሚጠፋ የሚያውቁት ራሳቸው ናቸው፤ ጽሑፉ የተጻፈው ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመጉዳት ነው፤ ሃይማኖታዊ ተቋምን መናፍቅ ማለትና ለሀገር ሉአላዊነት መከበር ታሪክ የማይረሳ ውለታ የዋለውን ቤተ ክርስቲያን ሀገር ላይ ዳፋ ያመጣል ከማለት በዘለለ ለመጉዳት ማሰብ ማሳያ ሊኖር አይችልም በማለት ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡

ቀሪ የተከሣሽ ምስክሮች በወንጀል ችሎት በመ/ቁጥር 32710 የተሰጠ ቃል በማስረጃ እንዲያዝ ተጠይቆ ተይዟል፡፡ ተከሣሽ በወንጀል ችሎት በሰጠው የተከሣሽነት ቃል፣ ጽሑፉ “የእኔ ሐሳብ” በሚል ዓምድ የወጣ ነው፤ ጽሑፉ በጋዜጣው ከመታተሙ ቀደም ብሎ መጋቢት 16/2008 ዓ.ም በጸሐፊው ድረ ገጽ ታትሟል፤ ድረ ገጹ ከ20,000 ሰዎች በላይ ተከታይ አለው፤ አስተያየትተሰጥቶበታል፤ በጋዜጣ ላይ የወጣው ከአምስት ቀን በኋላ ነው፤ የተነገረን ነገር ደግመን አትመን የታተመበት ዋነኛ ምክንያት፣ የቤተክህነት እና የፓትርያርኩ አመራር ጉዳይ የሕዝብ ጉዳይ በመኾኑነው፡፡ውይይት ይፈጥራል በሚል ቀና ልቦና ነው፤ ቤተክህነት በአሠራር ላይ ላቀረቡትትችት መልስ ሰጥታ ነገሩ እልባት ያገኛል በሚል ቀና ልቦና ነው፤ ቅሬታ ካደረባቸው መልስ መስጠት ይችሉ ነበር፤ መልስ ለመስጠት አልተጠየቅንም፤ እምቢ አላልንም፤ በማለት መስክረዋል፡፡

2ኛ. ምስክር ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ጽሑፉን አውቀዋለኹ፤ የጻፍኩት እኔ ነኝ፤ ፓትርያርኩ የቤተ ክርስቲያን የበላይ ርእስ ናቸው፤ በሳቸው አመራር ሥር ተፈጸመ ያልኩትን የተለያዩ የአስተዳደር ችግሮች እንዲታረሙ ሒስ ነው የሰጠኹት፤ በዚያ ውሳኔ ያላሰጣቸው ሙስናን አልታገሉም፤ መልካም አስተዳደር አላሰፈኑም፤ ችግሮች በወቅቱ ከመፍታት ይልቅ በራቸው ዝግ ነው፤ የሳቸው አመራር ውሳኔ በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ላይ ፈጣን ውሳኔ እና አመራር አይሰጡም፤ ሙስና እንዲባባስ በመኾኑ ለሀገሪቱ ደኅንነት ስጋት ነው፤ ችግሩን ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያወጣው መግለጫዎች፣ ራሳቸው ቅዱስ ፓትርያርኩ ወደ መንበሩ ሲመጡ ለቤተ ክርስቲያኒቱ እሠራለሁ ያሏቸው ሥራዎች ሙስናና መልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ ነው፡፡ እኔ በቤተ ክርስቲያን አካባቢ እሠራለሁ፤ ቅዱስ ፓትርያርኩ ላይ ሒስ መስጠት ነው፤ ይሄ በቤተክህነቱ የተለመደ ነው፡፡ እንኳን ፓትርያርክ እግዚአብሔርን እስከመውቀስ ይደርሳል፡፡በምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት አንድ ፓትርያርክ ምን ማድረግ እንዳለበት በጽሑፍ ውስጥ ተካቷል፡፡ ይሄ ገንቢ ሒስ መኾኑን ያሳያል፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ ያለኝ ሞያ በዲቁና ነው፡፡ ጥናት አጠናለኹ፤ 24 መጻሕፍት አሳትሜያለኹ፤በጽሑፌ፣ ቤተክህነት ተዘግቷል ያልኩት፣ ፓትርያርኩ ለውይይት በራቸው ዝግ ነው፤ ማኅበረ ቅዱሳን ከፓትርያርኩ ጋራ በተፈጠረው ችግር ለመወያየት ፈቃደኛ ስላልኾኑ ነው፡፡ቤተ ክርስቲያን የኑፋቄ ማኅደር ሲኾን ማለት ኑፋቄ ተጠራጣሪ ማለት ነው፤ ሲኖዶሱ፣መናፍቃን አስቸገሩኝ በማለት ኮማቴ አቋቁሟል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ዳፋ ታመጣለች፤ ያልኩት ይሄ ሳይስተካከል ቀርቶ ችግር ቢመጣ ዝግጁ ነው ለማለት ነው በማለት መስክረዋል፡፡

ጥበቡ በለጠ የተባለው የሞያ ምስክር፣ በጋዜጠኝነት ትምህርት በሀገር ውስጥና በወጪ ሀገር ትምህርት እንደወሰደ በመግለጽ፣ ላለፉት 20 ዓመታት በኅትመት እና በጋዜጠኝነት ሥራ ላይ ተሰማርቶ እንደሚገኝ ለዚህ ክሥ መነሻ የኾነ ጽሑፍ ማንበቡን ገልፆ መስክሯል፡፡ ጽሑፉ የወጣበት ዓምድ ነጻ አስተሳሰብበሚለው ሥር መኾኑን፤ ዓምዱም የኅብረተሰቡ የተለያዩ ሐሳቦች ተጽፈው የሚቀርቡበት እንደኾነ ገልጿል፡፡አኹን አከራካሪ የኾነው ጽሑፍ፣ ከዲያቆን ዳንኤል ክብረት ጽሑፍ እንደተወሰደ፣ ዲያቆኑ በኢትዮጵያ ውስጥ በሃይማኖት፣ በታሪክ ዙሪያ በርካታ መጽሐፎች እንዳሏቸው፤ ሃይማኖታዊ ሰባኪ መኾናቸውንና ጽሑፎቻቸውን በርካታ ሰዎች የሚያነቡ በመኾኑ የኅብረተሰቡ ትኩረት እንደሚስቡ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ከዲ/ን ዳንኤል ክብረት ብሎግ ላይ ተወስዶ በጋዜጣው ላይ እንደታተመ፤ ዓምዱ ሐሳቦች በነጻ የሚንጸባረቁበት በመኾኑ ከዚህ በፊት እንደሚደረገው ቅሬታ መጻፍ እንደሚቻል አስረድቷል፡፡ የሀገር መሪዎች፣ የልዩ ልዩ ተቋማት መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣በሥራቸው የሚመሩት በርካታ ሚሊዮን ሰው አለ፡፡ በዚህ ምክንያት የጋዜጠኝነት ሞያ የትኩረት አቅጣጫ ናቸው፡፡ ለጋዜጠኞች ዜናዎችን ለመጻፍ ሲፈልጉ፣ እነዚህ ዓይነት ሰዎች ላይ ያተኩራሉ፤ በጋዜጠኝነት ሞያ እነዚህ አካላት የሚመጣባቸውን ቅሬታ የመቋቋም ኃይል አላቸው ተብሎ የሚታሰቡ ናቸው፡፡

የተሰጠው አስተያየት፣ ከዚህ ሐሳብ ጋራ የተያያዘ ነው፡፡ የወጣውን ጽሑፍ ጋዜጣው ማስተናገዱ ከዚኽ አንጻር ሀሳብን በነጻነት ከመስጠት አንጻር እንዲስተናገድ ነው በሞያው የማየው፡፡ እንደ ባለሞያ እና እንደ አንባቢ ሳየው፣ ጽሑፉ የተጻፈው በአመራር እና ተቋም ላይ የተጻፈ እንደ መኾኑ ጽሑፉ የስም ማጥፋት ሳይኾን አመራር ላይ የተሰጠ ትችት ነው፡፡ ጽሑፉ ያለያቸው ብሎ ምላሽ ይሰጥባቸዋል የሚል አስተያየት ነው ያለኝ፤ ያልተደረገ ነገር ተደርጓል ከተባለ አስተያየት እና ምላሽ ይሰጥበታል፤ ማብራሪያ ቢሰጥ ይታረማል፡፡ ዓምዱ ነጻ አስተሳሰብ ነው፤ ጋዜጠኛውን የሚመለከት አይደለም፤የሚለው ቃል በጋዜጣው ለሚወጣ ማንኛውም ኅትመት ሓላፊ ነው ከሚለው የፕሬስ ሕግ አንጻር ያሟላል? የተለያዩ ጽሑፎች የሚስተናገድበት ነው ስህተት ቢሰራም ይቅርታ የመጠየቅ እድል አለ የሚታረመው ስህተት መስራቱን ሲያምን ወይም ሲጠየቅ ነው፡፡

ሥራን የሚሠራ ተቋም ሥራውን በአግባቡ ሠርቷል ወይስ አልሠራም በሚል የሚቀርብ ጽሑፍ ሂስ ነው፤ ስም ማጥፋት ማለት አንድ ሰው ባልዋለበት ቦታ ያላደረገውን ድርጊት አድርጓል፤ ማለት ነው፤ በማለት ምስክርነቱን አጠናቋል፡፡ ፍ/ቤቱም መዝገቡን ለመመርመሩ፦

ተከሣሽ በጋዜጣው ያተመው ጽሑፍ፣ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት በመጠቀም የተሰጠ ሒስና ትችት ነው ወይስ ስም የሚያጠፋ ይዘት ያለው ጽሑፍ ነው?በጽሑፉ የከሣሽ ስም ጠፍቷል?
በጽሑፉ የከሣሽ ስም ጠፍቶ ከኾነ ለከሣሽ ሊከፍል የሚገባው የኅሊና ጉዳት አለ? ምን ያህል ካሳ ሊከፍል ይገባል? የሚሉ ጭብጦች በመለየት ከሣሽ ክሥ ያቀረበባቸው ጽሑፍ ይዘቶች የከሣሽና ተከሣሽ ክርክር እና ማስረጃ ከሕጐች ጋራ ተጣምረው ተመርምሯል፡፡
በዚህ መዝገብ ክርክር ያሥነሳው ጽሑፍ፣ በሰንደቅ ጋዜጣ 11ኛ ዓመት ቁጥር 551፣ ረቡዕ መጋቢት 21 ቀን 2008 ዓ.ም. በወጣው ዕትም ገጽ 20 ላይ ታትሞ የወጣ ነው፡፡ የጽሑፉ ዋነኛ ይዘት አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣የቤተ ክርስቲያን አመራራቸው ላይ፣ በጸሐፊው እይታ መፈጸም ሲገባቸው ያልፈጸሙትንና ፈጽመው ስሕተት የኾነውን በመዘርዘር የተጻፈ ነው፡፡በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የአኹኑ ከሣሽ ስም እና ተግባር ተጠቅሶ የተጻፈ የሚገኝበት በመኾኑ ከሣሽ ስሜን አጥፍቷል ያላቸውን ይዘቶች ነቅሶ ምክንያት ጠቅሶ ስሙን እንደጠፋ ዘርዝሮ ክሥአቅርቧል፡፡

በከሣሽ ቀርበው በተከሣሽ ተክደው ክርክር የቀረበባቸው የጽሑፍ ይዘቶች ስም የሚያጠፉ ስለመኾን ያለመኾናቸው ለመመርመር በፕሬስ ስም ማጥፋት በኢትዮጰያ ሕጐች ካለው ከለላ ጀምረን ማየት ይገባናል፡፡ ከዚያም ከጽሑፍ ይዘቶች እና ክርክሮች በመነሣት ከሕጐች ጋራ አጣምሮ መመርመር ይገባል፡፡

ሐሳብን የመያዝና የመግለጽ መብቶች ተፈጥሮ ለሰውልጅ የሰጣቸው ሰብአዊ መብቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29 እና ኢትየጵያ የተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሰነዶች እውቅና አግኝቶ ተደንግጓል፡፡

ይኹን እንጂ ሐሳብን የመግለጽ መብት ፈጽሞ ሊገደብ የማይችል መብት አይደለም፡፡ የሀገርን፣ የሕዝብን፣ የመንግሥት እና ግለሰቦች ተነጻጻሪ መብት ጥቅም እና ደኅንነት መሠረት በማድረግ መብቱ ሊገደብ የሚችልበት አስገዳጅ ኹኔታዎች ይኖራሉ፡፡ የሐሳብን በነጻ የመያዝና መግለጽ መብት ገደብን የሚመለከቱ ኹኔታዎች በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29/ንዑስ 6 ሥር ተመልክቷል፡፡ አንቀጹሲነበብም፦

“እነዚህ መብቶች ገደብ ሊጣልባቸው የሚችለው የሐሳብና መረጃ ማግኘት ነጻነት በአስተሳሰባዊ ይዘቱና ሊያስከትል በሚችለው አስተሳሰባዊ ውጤት ሊገታ አይገባውም፤ በሚል መርሕ ላይ ተመሥርተው በሚወጡ ሕጐች ብቻ ይኾናል፡፡ የውጤቶች ደኅንነት የወሰነ ክብርና መልካም ስም ለመጠበቅ ሲባል ሕጋዊ ገደቦች በነዚህ መብቶች ላይ ሊደነገጉ ይችላሉ….” ይላል፡፡

በዚህ መዝገብ የተያዘው ክርክር፣ የከሣሽ ስም የማጥፋት ይዘት ያለው ጽሑፍ ይዘት ስለመኖርም ያለመኖርም በመኾኑ ሕገ መንግሥቱ ዐረፍተ ነገር ውስጥ “ያለውን ክብርና መልካም ስም ለመጠበቅ” የሚለው ሐረግ አግባብነት ያለው ይኾናል፡፡ይህን የሕገ መንግሥት አንቀጽ ተከትለው የስሙን መልካም ስምና ክብር ስለመጠበቅ የተደነገጉ ገደብን የያዙ ሕጐች ስንመረምር፣ የመገናኛ ብዙኃን የመረጃ ነጻነት ዐዋጅ ቁጥር 590/2000 የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ ዐዋጅ ቁጥር 414/1996 እና የፍትሐ ብሔር ሕግ ውስጥ የተደነገጉ የተለያዩ አንቀጾችንና ፅንሰ ሐሳቦችን እናገኛለን፡፡

የመገናኛ ብዙኃን የመረጃ ነጻነት ዐዋጅ ቁጥር 590/2000 አንቀጽ 40 ሥር፣ በመገናኛ ብዙኃን በቀረበ የፍሬ ነገር ዘገባ መልካም ስሙ እና ክብሩ የተነካበት ማንኛውም ሰው መልስ የመስጠት መብት እንዳለው ተደንግጓል፡፡ በዐዋጅ አንቀጽ 41 ሥር ደግሞ ሊጠይቀው የሚችለው የህሊና ጉዳት ካሣ ተደንግጓል፡፡ የስሙን መልካም ስምና ዝና የሚያጐድፍ የሐሳብ መግለጽ ድርጊት ተፈጽሞ የሚገኝ በሚኾንበት ጊዜ የመኖር የወንጀል ተጠያቂነት በተመለከተ፣ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 607 እስከ 619 ተደንግጐ የሚገኝ ሲኾን ስለፍትሐብሔር ተጠያቂነት የፍትሐ ብሔር ሕግ ከቁጥር 2044 እስከ 2048 ተመልክቷል፡፡

አኹን በያዝነው ጉዳይ ተከሣሽ ላይ የወንጀል ክሥ ቀርቦ ተከሣሽ በነጻ የተሰናበተ በመኾኑ የወንጀል ተጠያቂነት ተከትሎ ስለሚመጣ ተጠያቂነት በዝርዝር አልተመረመረም፡፡

በቀጥታስለ ስሙ ማጥፋት የፍትሐ ብሔር ተጠያቂነት በፍትሐ ብሔር ሕጉ ስለተደነገገው ስንመረምር፣ ከቁጥር 2044 እስከ 2048 የተመለከቱ የሕጉ ቀሪዎች ሊመረመሩ ይገባል፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2044 ስለ ስም ማጥፋት የተደነገገ ሲኾን የሕጉ አነጋገር፦

“አንድ ሰው በንግግሮቹ በጽሐፎቹ ወይም በሌላ ዓይነት አድራጐቶቹ የሰውን ስም በማጥፋት ይህ ሰው እንዲጣላ እንዲዋረድ እንዲሣቅበት እና እርሱ ላይ ያለውን እምነትና መልካም ዝናው ወይም የወደፊት ዕድሉ እንዲበላሽ ያደረገ እንደኾነ ጥፋተኛ ነው፤” የሚል ነው፡፡

የዚህ ሕግ አነጋገር የስም ማጥፋት ተግባር ውጤቶችን ከመዘርዘር አልፎ ስም ማጥፋት ማለት ምን ማለት እንደኾነ አልተተረጐመም፡፡ይኹን እንጂ የሕጉ ቁጥር 2047 ስም ማጥፋት ማለት ርግጠኛ ያልኾነ ጉዳይ/ነገር አንድ ሰው አድርጓል በማለት በመናገር የሰውን ስም ማጥፋት ወይም እውነት የኾነርግጠኛ የሆነ ጉዳይ እንኳ ቢኾን ስሙን በተለየ ኹኔታ ለመጉዳት በማሰብ ተናግሮ ሰው እንዲጠላው፣ ተቀባይነት እንዲያጣና ዕጣ ፈንታው እንዲበላሽ ማድረግእንደኾነ ያመለክታል፡፡

ስም ማጥፋት ተግባር ተደርጓል ሊባል ቢችል እንኳ የተነገረው ጉዳይ የሕዝብን ጥቅም የሚነካ ጉዳይ በሚኾንበት ጊዜ የተለየ መመዘኛ በሕጉ ተመልክቷል፡፡ ይኸውም ተናጋሪው ወይም ጸሐፊው የተናገረው ነገር ሐሰት መኾኑን ፍጹም ዕውቀት ኖሮት እያወቀ የሰውን ስም እና ዝና ለመጉዳት እያወቀ ንግግር ማድረግ ወይም መጻፍ እንደሚገባ ያመለክታል፡፡ ይህ መመዘኛ የተቀመጠው ሕዝቦች በጉዳያቸው ላይ የመሰላቸውን እንዲናገሩ ለማበረታታት ኾኖ ሐሰት መኾኑን እያወቁ የሚናገሩትን ጥፋተኛ አድርጐ ለጥፋታቸው ለማስከፈል ነው፡፡

በመኾኑምበሕጉ፣ስም ማጥፋት ማለት፣ሐሰት የኾነ ነገርን በመግለጽ ወይም በመጻፍ የሰውን ስም ማጥፋት ሲኾን፤ የንግግሩ ጉዳይ የሕዝብ ጥቅምን የሚነኩ ጉዳዮች ላይ የተደረገ ከኾነ ጸሐፊ ወይም ንግግሩ በርግጥም ሐሰት መኾኑን ድምዳሜ ደርሰው እያወቁ በመናገር የሰውን ስም እና ዝና ለመጉዳት መናገር ነው፡፡በዚህ መመዘኛ አከራካሪው ጽሑፍና ማስረጃ እንደሚከተለው ተመርምሯል፡፡

የመጀመሪያው የክሡ ይዘትየተካተተ ጽሑፍ፣ቤተ ክህነቱ የኑፋቄ ማኅደር ኾኗል፤ በማለት የተጻፈው ጽሑፍ ቤተክህነቱን እንዲጠላ የሚያደርግ ዘገባ ነው፤ የሚል ነው፡፡ ይህ አነጋገር እውነት ስለመኾን ያለመኾኑይህ ችሎት ድምዳሜ ላይ ሊደርስ የሚችለው ጉዳይ አይደለም፤ ምክንያቱም ስሙ የተጠቀሰው ተቋምሃይማኖታዊ ተቋም በመኾኑ፣ ምን ያህል የቤተ ክርስቲያኒቱን ዶግማና ቀኖና የማይከተሉ ሰዎች በውስጥዋ ገብተው ይኹን የሚለውን ማረጋገጥ በችሎት ከሚሰማው ምስክርነት እና ማስረጃ በላይ ዝርዝር ሰፊ ጥናት የሚፈልግ ጉዳይ የመሆን ፍሬ ነገር ነው፡፡ ሰፊ ጥናት ከማስፈለጉም በዘለለ ለአንድ መንግሥታዊ ፍ/ቤት በአንድ ሃይማኖት ተቋም ውስጥ ያለን የአማኝ ኹኔታ እና እምነቱ ላይ ምን ያህል ጥርጣሬ እንዳደረበት ለይቶ ድምዳሜ መድረስ የሀገራችን ሕገ መንግሥት የሚፈቅድ አይደለም፡፡

በመኾኑም ይህ ችሎት፣ ከሣሽና ተከሣሽ በቤተክህነቱ ታይቷል ወይም አልታየም በማለት የተከራከሩበት የቤተክርስቲያኒቱ ዶግማና ቀኖና ያመለክታል ጉዳይ ላይ ድምዳሜአልደረሰም፡፡ ይኹንእንጂ እንደዚኽ ዓይነት ምልክቶችቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዳለ ተከሣሽ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተጉባኤ ስብሰባ ጥቅምት 24 ቀን 2007 ዓ.ም.የተያዘ በማቅረብ ለማስረዳት ሞክሯል፡፡

ከሣሽ በዚህ ቃለ ጉባኤ የተመለከተው ስለመንፈሳዊ ኮሌጆች ነው፤ ሲል ተከራክሯል፡፡ ኾኖም የቃለ ጉባኤው ሙሉ ሲነበብ፣ ስለኮሌጆች የተመለከተው ምንጭ እና መፍትሔው እንጂ ችግሩ የተፈጠረው እና ለውይይት ምላሽ የኾነው በኮሌጆች ብቻ እንደኾነ አይመለከትም፡፡በተመሳሳይ የከሣሽ ምስክር ችሎትቀርበው ችግሩ በቤተ ክርስቲያኖች ሊኖር እንደሚችል መስክረዋል፡፡ ከዚኽ አንጻር ጸሐፊው ለጽሑፉ ፈጽሞ መነሻ አልነበረውም ለማለት አልተቻለም፡፡ ቤተ ክርስቲያኒትዋ የሕዝበ ክርስቲያኑ ተቋም የሀገር ሀብት እንደ መኾኗ መጠን ጉዳዩ ሕዝባዊ ጉዳይ ነው፡፡ በጸሐፊው አመለካከት፣ ቤተክህነት በቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖና እና ዶግማ የማያምኑ መኾኑን መጻፍ ሐሳቡን መግለጽ ነው፡፡ ሐሳቡን ሲገልጽም ድርጊቱ ፈጽሞ ሐሰት ላይ የተመሠረተ ስለመኾኑ ከሣሽ አላስረዳም፤ ችሎትም እውነት ስለመኾኑ አለመኾኑ ድምዳሜ ላይ ሊደርሱ አልቻሉም፡፡ ከዚያ በተቃራኒ ተከሣሽ የቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ቃለ ጉባኤ በማቅረብ መነሻ እንዳለው ስላሳየ፣ የዚህ ጸሐፊ ክፍል ስም ለማጥፋት የተጻፈ ነው ለማለት አይቻልም፡፡

ኹለተኛው አከራካሪ የጸሐፊ ይዘት፣ ከእንጦጦ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ግማሽ ሚሊዮን ብር በአንድ ሙሰኛ ተዘርፏል፤ በማለት የተጻፈ የጽሑፍ ይዘትን የሚመለከት ነው፡፡ በጋዜጣው የታተመው ጽሑፍ መሉ ይዘት፦

“ፓትርያርኩ ዕንጨት የሚሸጡ እናቶች ካዋጡት የእንጦጦ ኪዳነምህረት ገንዘብ ግማሽ ሚሊዮን ብር እንደዋዛ በአንድ ሙሰኛ ሲነጠቅ ተኝተዋል፤” የሚል ነው፡፡ ተከሣሽ ይህ እውነት መኾኑን ተከራክረው የእንጦጦ ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ገዳም አስተዳደር ኮሚቴ የካቲት 25 ቀን 2008 ዓ.ም በወቅቱ የአ.አ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩ ሰውልጅ በመታመሙለመታከሚያርዳታ ብር ግማሽ ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎ እንዲሰጥ የወሰነበትን ቃለ ጉባኤ አቅርበዋል፡፡ቃለ ጉባኤው ተንተርሰው፣ የገዳሙ ጽ/ቤት ለገዳሙ ሒሳብ ክፍል ገንዘቡ ወጪ ተደርጐ እንዲከፍል ማዘዙን የሚያሳይ ደብዳቤ ግልባጭም አቅርበዋል፡፡ ማንም ምክንያታዊ ሰው እነዚህን ደብዳቤዎች እና ሰነዶች ከተመለከተ በኋላ ገንዘቡ ከቤተ ክርስቲያኑ ውጪ አልተደረገም የሚል ድምዳሜ ላይ ላለመድረስ አይቻለውም፡፡ ፓትርያርኩ በሰጡት ምስክርነት፣ ገንዘቡ እንዳይከፈል ትእዛዝ ሰጥተው ሳይከፈል እንደቀረ ገልጸዋል፡፡ገንዘቡ ወጪ እንደኾነ መታዘዙ ለሕዝብ ጆሮ ደርሶ ጸሐፊው ጭምር ያወቀ በመኾኑ እንዳይከፈል የተሰጠው ትእዛዝ ለሕዝቡ ደርሶ/ግልጽ ተደርጐ እንደኾነ ፓትርያርኩ ተጠይቀው መልስ ሰጥተዋል፡፡ መልሳቸውም ሳይወጣ እንዲቀር ለተደረገ ጉዳይ ለሕዝብ የሚነገርበት አግባብ ባለመኖሩ አልተነገረም የሚል ነው፡፡ተከሣሽ ያተመውን ጽሑፍ የጻፈው፣ ጽሑፉንም ኾነ ተከሣሽ ገንዘቡን እንዲወጣ ለሒሳብ ክፍል ጭምር መታዘዙን ካወቁ ለጻፉትና ለታተሙት ጽሑፍ መነሻ የላቸውም፤ የጻፉት ሐሰት ነው፤ ለማለት አይቻልም፡፡ጽሑፉ፣ በአንድ ሙሰኛ ገንዘብ ሲነጠቅ ማለታቸውን በተመለከተ የገንዘቡ አወጣጥ ንጥቂያ ነው፤ የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሳቸው ላይ አገላለጹ ያልተገራ አጻጻፍ ነው፤ ከመባል በቀር ሐሰት ነው ለማለት አይቻልም፡፡ ከሣሽ ገንዘቡ ለርዳታ ለሕይወት ማዳን ለበጐ ተግባር የተደረገ ነው፤ ቢልም በገንዘብ መሰጠቱ ራሱ ያላመነ ገንዘቡም እንዳይከፍል ያደረገ በመኾኑ ክርክሩ አሳማኝ አይደለም፡፡አመራሩን ሙሰኛ ብሎ መግለጽ ማስረጃ ያልቀረበበት ወንጀል ቢመስልም አነጋገሩ ግላዊ በመኾኑ አላግባብ የተገለጸው ሰው ቀርቦ ያልተከራከረ በመኾኑ ከከሣሽ ጋር አገናኝቶ ስም ማጥፋት ነው ለማለት አይቻልም፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሕዝብ ተቋም እንደመኾኑ ገንዘቡም ከሕዝብ የሚሰበሰብ በመኾኑ ጉዳዩ ሕዝብን የሚመለከት ጉዳይ ነው፤ ሕዝበ ክርስቲያን በሚመለከት ጉዳይ ላይ በምክንያታዊ ሰው መመዘኛ ገንዘብ ወጪ መኾኑን በቂ ማስረጃ በመያዝ የተሰጠ አስተያየት የስም ማጥፋት ተግባር ነውማለትአይቻልም፡፡

ሦስተኛው፣ ከሣሽ ስሜ ጠፍቷልብሎ አመልክቶበት በተከሣሽ የታገደው ጉዳይ፣ “በሱራፊ ነበልባልየተዘጋች ገነት ስትከፈት በፓትርያርክ የተዘጋች የቤተክህነት በር ልትከፈት አልቻለችም፤”በሚል አገልግሎትበመስጠት ላይ ያለች ቤተ ክርስቲያን የተዘጋችና ህልውና የሌላት በማድረግ ተጽፏል፤ የሚለው ሐረግ ነው፡፡ ይህ ዓረፍተ ነገር በጋዜጣው ላይ ከተጻፈ ሙሉ ዓምድ የተወሰደ ነው፤ሙሉው ሲነበብ፦

“ባለሞያ ሴት የሰፋችው … ጅልትተረትረዋለች” እንደተባለው፣በደኅና ጊዜ ትጉሃን አበው የሰበሰቧቸውን ውጤቶች ካልበተንኩ ብሎ እንዴት አንድ ፓትርያርክ ይነሣል፡፡ ወጣቶቹ ሊሳሳቱ ሊያጠፉም ይችላሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ግን ለዚህም መንገድ ያላት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሳይቀሩ፣ የገዛ ልጆችዎን ለምን አያወያዩምሲሏቸው በራቸውን ጠርቅመው የሚዘጉ ፓትርያርክ በታሪክ የመጀመሪያ መኾን አለባቸው፡፡

በሱራፌ ነበልባል የተዘጋች የገነት በር ስትከፈት በፓትርያርክ የተዘጋች የቤተክህነት በር ልትከፈት አልቻለችም፡፡ ሰይጣንን ከእግዚአብሔር ጋር ለማነጋገር የደከሙ እነ ክርስቶስ ሠምራን የመሰሉ ቅዱሳን ባሉበት ቤተ ክርስቲያን እረኛውን ከመንጋው ጋራ መነጋገር አቃተው፤ ኢየሱሳውያንን በዐደባባይ ሳናነጋግራቸው መሔድ የለባቸውም ብለው የተሟገቱ እነ እጨጌ በትረጊዮርጊስ በነበሩባት ቤተ ክርስቲያን የገዛ ልጆቿን ለማነጋገር በር የምትዘጋ እጨጌ ተፈጠረ የሚል ነው፡፡

በዚኽ ጽሑፍ ያለ ነገር በሙሉ የሚገልጸው፣ ጸሐፊው የቤተ ክርስቲያኑ ወጣቶች ያሏቸው ቡድኖች ለማነጋገር ፓትርያርኩ ፈቃደኛ ያለመኾናቸው በራሳቸው ስለመዝጋታቸው የሚገልጽ ነው፡፡

የጽሑፉ ይዘት መነበብ ያለበት በሙሉ እንጂ፣ ዓረፍተ ነገሮች ለብቻቸው ተነጥለው አይደለም፡፡ ዓረፍተ ነገሩ ከሙሉ ጽሑፉ ይዘት ጋራ ሲነበብ የቤተ ክርስቲያኒቱ ህልውና ላይ የቀረበ ጽሑፍ አይደለም፡፡ ስለኾነም ከሣሽ አንድ ዓረፍተ ነገር ከጸሐፊ መዝዞ በማውጣት ጸሐፊው ያላሰበውን ጽሑፍ ሲታተም ያልሰጠኹ መልእክት ለጸሐፊ ሰጥቶ ስም ማጥፋት ተፈጽሟል ማለቱ አግባብ ኾኖ አላገኘንም፡፡

አራተኛው አከራካሪ የጽሑፍ ይዘት፣ ዐውደ ርእይ በሚደረግበት በቂ ምክንያት ከነበረ ቢያንስ ከሳምንት በፊት መግለጽ ይቻል ነበር፤ በማለት በመንግሥት ተቋማት አሠራር የታገደና የማኅበረ ቅዱሳን ዐውደ ርእይ በቤተ ክርስቲያኒቱ አስመስሎ ጽፏል፤ ሕዝበ ክርስቲያኑ ለዐመፅእንዲነሣሣ ለመቀስቀስ ኾን ብሎ በጽሑፍ ይዘት ዓላማው ግን ማበሳጨት ዐመፅማሥነሳት ተስፋ ማስቆረጥና ምእመናንን ወደማይፈልጉ መስመር መውሰድ ነው፤ በማለት ስውር ቅስቀሳ አድርጓል፡፡ቤተ ክርስቲያኒቱን የሀገር ደኅንነት ስጋት አድርጐ በመሳልና ወደፊት ቤተ ክህነቱ ሀገር ላይ የሚያመጣውን ዳፋ ለመቀበል መንግሥት ዝግጁ ነው፤ በማለት የቤተክህነቱ መልካም ስምና ዝናን ጎድቷል የሚል ነው፡፡

ሙሉ ጽሑፉ ሲነበብ፣ዐውደ ርእዩ እንዲታገድ ቤተክህነት አዟል፡፡ የሚለውን ቃል እና ይዘት በጽሑፍ ውስጥ በቃል በቃል ሰፍሮ አናገኘውም፡፡ ጽሑፉ በአጠቃላይ የተጻፈው ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ ፓትርያርክ ነው፡፡በጽሑፉ የዐውደ ርእይ መዝጋት ክፍል ሥር ከመግቢያው አንድ የኦርየንታል አብያተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ምን ምን ተግባራት ማከናወን እንደሚጠበቅበት ተገልጿል፡፡ ከዚህ ይዘት ቀጥሎ ስለ ዐውደ ርእይ መዝጋት ተጽፏል፤ ከዚህ ተነሥቶ መረዳት የሚቻለው ለዐውደ ርእይ መዘጋት ጽሑፍ ተጠያቂ አድርጐ የሚኮንነው ፓትርያርኩን እንደኾነ ነው፡፡ለዐውደ ርእይ ፓትርያርኩ የፈጸሙትን በተመለከተ ምስክርነት የሰጡት የከሣሽ ምስክር፣ ፓትርያርኩ ስለ ዐውደ ርእዩ ቀድመው አያውቁም ነበር፤ በማለት አስረድተዋል፡፡ በመኾኑም አገላለጹ እውነታነት የለውም፤ በማለት ለመከራከር ካስፈለገ፣ ፓትርያርኩ በግላቸው ከሚከራከሩበት በቀር ከሣሽን የሚመለከት አይደለም፡፡

ቤተክህነቱ የሚያመጣውን ዳፋ ለመቀበል መንግሥት ዝግጁ ነው ወይ? ይህ አካሔድስ ለሀገሪቱ ደኅንነት የሚገኝ ነው ወይ? ሀገሪቱ ያለባት ችግር አይበቃትም ወይ? ተጨማሪ ችግር መምራት ያስፈልጋል ወይ? የሚለው የጸሐፊውን ይዘት በተመለከተ፣ ጸሐፊው ስም የሚያጠፋ ስለመኾኑ ያለመኾኑ ተጠይቀው 3 (ሦስት) ለጋዜጠኝነት ሙያ ቅርበት ያላቸው ተቋማት ተጠይቀው አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ተቋማቱ፥ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት፣ሐምሌ 6 ቀን 2008 ዓ.ም.በተጻፈ ደብዳቤ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጋዜጠኞች ኅብረት፣ሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም.በጻፈው ደብዳቤ፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሚዩኒኬሽን ት/ቤትሐምሌ 6 ቀን 2008 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ፤ የጽሑፉ ይዘት የግለሰብ አስተያየት የኾነ ትችት እንጂ የስም ማጥፋት ይዘት እንደሌለበት ሞያዊ አስተያየትን አቅርበዋል፡፡ በተመሳሳይ የ20 ዓመት የጋዜጠኝነት ልምድ ያለው ምስክር ቀርቦ እንዳስረዳው ጽሑፉ ትችት እንጂ ስም ማጥፋት አይደለም ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በፍ/ቤቱ የተረጋገጠው ይኸው ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያን ሕዝባዊ ተቋም እንደ መኾኗ፣ የሚሰጡ አስተያየቶች በሙሉ ሕዝባዊ የኾነ ቤተ ክርስቲያንን የሚመለከት ነው፡፡ ስለኾነም ተከሣሽ በቤተክህነት ላይ የተሰጠ አስተያየት ቢያቀርብ አስተያየቱ ፈጽሞ ሐሰት መኾኑን ከሣሽ ባላስረዳበት ተከሣሽ በስም ማጥፋት ጥፋተኛ አይደለም፡፡ዐውደ ርእዩ መዘጋቱ እውነት በመኾኑተከሣሽ የዘጋው ቤተ ክህነት ነው ብሎ ቢኾን እንኳ የተናገረውን ተከሣሽ በወቅቱ በርግጥ ሐሰት መኾኑን ያውቅ ነበር የሚለውን ማስረዳት የከሣሽ ሓላፊነት ነው፡፡

ቤተክህነት ዳፋ መከራ ለመቀበል መንግሥት ዝግጁ ነው ወይ? ተጨማሪ ችግር ማምረት ያስፈልጋል ወይ? የፍሬ ነገር የጽሑፉ ይዘት ላይ ስም ለማጥፋት እንደተጻፈ ፍ/ቤቱ ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡ ፍሬ ነገር ይዘትን ተከትለው የሚሰጡ አስተሳሰባዊ ግምቶች ደግሞ ተነጥለው ስም ለማጥፋት ነው የተጻፉት ማለት አይቻልም፡፡ በአኹኑ ጽሑፍ ላይ የፍሬ ነገር ድርጊቱ ተፈጽሞ ከኾነ ጸሐፊው የገለጹት ኹኔታ ሊከሠት ስለመቻሉ የራሳቸውን ግምት አስቀምጠዋል፡፡ ግምቱ ልክ ስለመኾን ያለመኾኑ ጉዳይ ግላዊ ሐሳብ ነው፡፡ ኾኖም ግምቱ ፍሬ ነገሩ እውነት ከኾነ ሊከሠት የሚችል ምክንያታዊ ድምዳሜ ነው፡፡ ይህ በኾነበት ግምቱ አልደረሰም በሚል ስም ማጥፋት ተፈጽሟል ለማለት አይቻልም የፍሬ ነገር ይዘት ላይ እንጂ የፍሬ ነገር ኹኔታን ተንተርሶ የሚሰጥ አስተያየት የሕግ ክልከላ አልተጣለበትም፡፡

በአጠቃላይ መገናኛ ብዙኃን፣በሕዝብ ዘንድ ሊያሳውቅ የሚችሉ አጋላጭ መረጃዎችን ጭምር የማግኘትእና የማሰራጨት መብት ያላቸው መኾኑ በመገናኛ ብዙኃን ዐዋጅ የተመለከተ ጽሑፍ ከሣሽን በሕዝብ ዘንድ ሊያሳውቅ የሚችል ቢኾንም፣ ተከሣሽ ጸሐፊውን ሲያትም የጸሐፊው ይዘቶች ሐሰት መኾኑን እያወቀ ማተሙ ስላልተመሰከረ፤ ይህ ባልተረጋገጠበት ሕዝባዊ ተቋም በኾነ ከሣሽ ላይ የተሰጠ እውነታነት የሌለው አስተያየት ቢኾን፣ ተከሣሽን በስም ማጥፋት ጥፋተኛ ስለማያሰኝ፣ በጽሑፉ ያሰፈሩ ሐሳቦች አንዳንዶች እውነታ መነሻ ላይ ተመሥርተው የተጻፈ በመኾኑተከሣሽ በስም ማጠፋት ድርጊት ጥፋተኛ ኾኖ አላገኘንም፡፡ ለዚህም ተከታዩ ተወሰነ፡፡

ው ሳ ኔ

ተከሣሽ በሰንደቅ ጋዜጣ 11ኛ ዓመት ቁጥር 551 ረቡዕ መጋቢት 21 ቀን 2008 ዓ.ም. በገጽ 20 በጋዜጣው ያተመው ጸሐፊ የከሣሽን ስም የሚያጠፋ ይዘት የለውም፡፡
ተከሣሽ የከሣሽም ስም የሚያጠፋ ይዘት ያለው ጽሑፍ ባለማተሙ የሚከፈል ካሣ የለም፡፡
ወጪ እና ኪሣራ የመጠየቅ መብት የከሣሽ ነው፡፡

ት እ ዛ ዝ

የይግባኝ መብት በችሎት ተነገረ፡፡
ለብፁዕወቅዱስ አቡነ ማትያስ የተላከ የጽ/ቤት ማጣሪያ ጥያቄ ተራ ቁጥር 3.2 የተጻፈው ቃል ውስጥ፣ ብልሹ አሠራር የሚለው ‹‹ስልቹ›› አሠራር በሚለው የተገለጸው በአጻጻፉ፣የታይፕ ስሕተት መኾኑን እንዲያውቁ የዳኛው የእጅ ጽሑፍ ግልባጭ ይላክላቸው፤ ችሎቱ ይቅርታ የሚጠይቅ መኾኑ ይህ ትእዛዝ ይድረሳቸው፡፡
መዝገቡ ተዘግቷል፡፡

የዳኛ ፊርማ፣ የማይነበብ አለበት

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 7 years ago on June 17, 2017
  • By:
  • Last Modified: June 17, 2017 @ 9:42 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar