www.maledatimes.com የትነበረሽ ንጉሴ ማን ናት? ስለሥራዋ፣ ስለ አስተዳደጓ፣ የዓይኗን ብርሃን እንዴት እንዳጣች፣ ስለ ልጆቿ ….. እንዲህ ትላለች። - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የትነበረሽ ንጉሴ ማን ናት? ስለሥራዋ፣ ስለ አስተዳደጓ፣ የዓይኗን ብርሃን እንዴት እንዳጣች፣ ስለ ልጆቿ ….. እንዲህ ትላለች።

By   /   September 28, 2017  /   Comments Off on የትነበረሽ ንጉሴ ማን ናት? ስለሥራዋ፣ ስለ አስተዳደጓ፣ የዓይኗን ብርሃን እንዴት እንዳጣች፣ ስለ ልጆቿ ….. እንዲህ ትላለች።

    Print       Email
2 1
Read Time:6 Minute, 32 Second

(ምንጭ ድንቅ መጽሔት አትላንታ)

ከሦስት ዓመት በፊት የድንቅ መጽሔት የአዲስ አበባ ሪፖርተር ጽጌ ዓይናለም የትነበርሽ ንጉሴን እና የሚያውቋትን አነጋግራ የሚከተለውን አጠናቅራ ነበር። የሰሞኑ የየትነበርሽን ስኬት ምክንያት አድርገን እንደገና አቀረብነው።

አሜሪካ የሚገኘው Center for the Right of Ethiopian Women የተባለ ድርጅት “የዘመኑ ጣይቱዎች”ብሎ በአሜሪካና በኢትዮጵያ የሚገኙ አስር ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶችን መርጧል፡፡ ከእነዚህ ሴቶች መካከል የትነበርሽ ንጉሴ ትገኝበታለች፡፡ የትነበርሽ ለዚህ የበቃችው አካል ጉዳተኛነቷ ሳይወስናት በትምህርቷም ሆነ በሥራዋ ከፍተኛ ብቃቷን ስላስመሰከረች ነው፡፡ Ethiopian Center for Disability & Development በተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ በሥራ አስኪያጅነት በማገልገል ላይ የምትገኘው የትነበርሽ ጥር 24 ቀን በ1975 ወሎ አማራ ሳይንት ተወልዳ በስድስት ዓመቷ ባጋጠማት የሜኔንጃይትስ ሕመም የተነሳ የዓይን ብርሃኗን በማጣቷ ነው ወደ አዲስ አበባ የመጣችው፡፡ አዲስ አበባ ከአያቶቿ ጋር ለመኖር ብትመጣም ለዓይነ ስውራን የሚሆን ት/ቤት ባለመኖሩ ወደ ሻሸመኔ ተልካ እስከ ስድስተኛ ክፍል ተምራ ተመልሳ አዲስ አበባ መጥታለች፡፡ ከ7ተኛ ክፍል እስከ 12ተኛ ክፍል በተማረችበት ዳግማዊ ምንሊክ ት/ቤት ለእሷ አዲስ ሕይወት እንደመጀመር እንደሆነ የትነበርሽ ትናገራለች፡፡

“ከዚህ በፊት ከ16- 20 ተማሪዎች ብቻ ባሉበት ክፍል እማር የነበርኩት ልጅ በአንዴ ከ70 ልጆች ጋር ስቀላቀል ገሃነም የጣሉኝ ነበር የመሰለኝ፡፡ በዚያ ላይ አይነስውር በመሆኔ እኔን ለማቅረብ ፈቃደኞች አልነበሩም፡፡”

ተማሪዎች እንዲህ ቢያገሏትም አልቅሳና ተለማምጣ እንዲቀርቧት ከማድረግ ይልቅ በትምህርቷም ሆነ ባሏት የተለያዩ ችሎታዎች ተጠቅማ ያራቃትን ማህበረሰብ ለማቅረብ ተነሳችና ድንቅ ብቃቷን አስመሰከረች፡፡ አንድ አብሯት የተማረ ወጣት ሲናገር፡

“ ያኔ የትነበርሽ በምታደርጋቸው እንቅስቃሴዎች በጣም እገረም ስለነበር ‹አይ ውሸቷን ነው ማየት ትችላለች› እል ነበር፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ‹እኔምአይነ ስውር ብሆን እንደ እሷ ጎበዝ እሆን ነበር ይሆን?› እያልኩ ራሴን እጠይቅ ነበር” ብሏል፡፡

እናም እንዳሰበችው በትምህርቷና በእንቅስቃሴዎቿ በአጭር ጊዜ በመምህሮቿም ሆነ በተማሪዎች ዘንድ እውቅናን አተረፈች፡፡ በዚህም የት/ቤቱ የተማሪዎች መማክርት ም/ፕሬዝዳንትና የህዝብ ግንኙኝነት ኃላፊ፣ የሙዚቃ ባንዱ ድምፃዊ፣ የስነፅሁፍ ክፍሉ ገጣሚ በመሆን መሳተፍ ጀመረች፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለች ማትሪክን በአጥጋቢ ውጤት አልፋ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገባች፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪዋን የሰራችው በሕግ ትምህርት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ በሶሻል ዎርክ ሁለተኛ ዲግሪዋ ሰርታለች፡፡

የኢሲዲዲ ውስጥ በስራ አስኪያጅነት የምትሰራው የትነበርሽ ድርጅቱ ስለሚያደርገው እንቅስቃሴ ይህን ብላለች፡፡

“ድርጅታችን በዋናነት የሚሰራው አካል ጉዳተኞችን አጠንክሮ የልማት አጋር ማድረግ ላይ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች አካል ጉዳተኞች ተረጂዎች ብቻ እንደሆኑ አድርገው ያስቧቸዋል፡፡ እውነታው ግን አካል ጉዳተኞች ተገቢውን ድጋፍ ካገኙ ከሚከፈለው ግብር እርዳታ ተቀባይ ሳይሆኑ ለግብር አስተዋፅዖ ማድረግ የሚችሉ ዜጎች መሆናቸው ነው፡፡ በዚህ የተነሳ አካል ጉዳተኞች በቡድን ተደራጅተው ሲመጡ እንደግፋቸዋለን፡፡ በዚህ ፕሮግራም በዓመት ከ3ሺህ በላይ የአካል ጉዳተኞች ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡
ከዚህም በተጨማሪም የሥራ ዕድል በማመቻቸት፣ እነሱን የሚመለከቱ የሥራ ማስታወቂያዎች ሲወጡ በኢሜልና በስልክ ማሳወቅ፣ ሕፃናትን ለትምህርት ማዘጋጀት በመሳሰሉት ዙሪያ እንሰራለን፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጀምረነው የነበረውን ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የሆነ የትምህርት አካባቢ ወደ መቀሌና አዋሳ ዩኒቨርስቲዎች አስፍተነዋል፡፡ ወደፊት ደግሞ በሌሎች ክልሎች ለመስራት ዕቅድ ይዘናል፡፡”

ከዚህም በላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ግምቱ ወደ 300ሺህ ብር የሚጠጋ ዲጂታል ስቱዲዮ አስገንብተው ለዩኒቨርስቲው አስረክበዋል፡፡ ከዚህ በፊት ለዓይነ ስውራን የሚዘጋጀው የብሬል መፅሀፍ ከፍተኛ ገንዘብና ቦታ የሚጠይቅ በመሆኑና በየጊዜው የሚለዋወጠው የትምህርት ፖሊሲና ካሪኩለም አመቺ ባለመሆኑ ተማሪዎች በቀላሉ በሞባይላቸውም ሆነ በሚሞሪ ላይ በድምፅ የተቀረፀ የትምህርት መረጃ ያገኛሉ፡፡ ወደፊትም ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ተመሳሳይ ዲጂታል ስቱዲዮ በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ለማስገንባት እየተነጋገሩ ነው፡፡

የትነበርሽ ሕብረተሰቡ አካል ጉዳተኞችን አስመልክቶ ያለው አመለካከት በፊት ከነበረው የተለወጠ ቢሆንም ዛሬም ችግሮች መኖራቸውን ለድንቅ መጽሔት ሪፖርተር ስትናገር እንዲህ ብላለች።

“የአካል ጉዳተኞች ቁጥር በጨመረና ተቋማት በተገነቡ ቁጥር ችግሮቹም አብረው እየተገነቡ ነው፡፡ እየተገነቡ ያሉት የትምህርት ተቋማት የአካል ጉዳተኞችን ፍላጎት ያሟሉ አይደሉም፡፡ ምቹ መፀዳጃ ቤትና የመታጠቢያ ቤት የላቸውም፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ መታጠቢያና መፀዳጃ ቤት ያስገነባነው እኛ ነን፡፡ በቀጥታ ከትምህርት ጋር የማይገናኙ የሚመስሉ ግን እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮች ብዙ ናቸው፡፡ ወደ ዩኒቨርስቲ የሚመጡ አካል ጉዳተኞች ተመርቀው እስከሚወጡ ድረስ ኑሯቸው እዚያው ነው፡፡ ስለዚህ ለእነሱ ተስማሚ የሆነ የመኖሪያ አካባቢ ሊገነባላቸው ይገባል፡፡ ከአንዳንድ ሆቴሎች በስተቀር አብዛኛዎቹ ሆቴሎች ለአካል ጉዳተኞች መወጣጫ የላቸውም፤ የሚገነቡት ሞሎችም እንደልብ ተዘዋውረን ለመግዛት ምቹ አይደሉም፡፡ ዛሬ ብዙዎቻችን ተከፍሎን የምንሰራ ስለሆነን አቅም ያለን ገዢዎች ሆነናል፡፡ ያለው ክፍተት ግን ለእነሱም ገበያ እያሳጣቸው ነው፡፡”

“የትነበርሽ ቦረና አካዳሚ” የሚባለው ት/ቤቷም ለማንኛውም ልጅ ምቹ ሆኖ የተሠራ ነው፡፡ ት/ቤቱን የከፈተችው በተለያዩ የአገር ውስጥና የውጪ መድረኮች ላይ ለምታቀርባቸው ጥናታዊ ፅሁፎች የሚከፈላትን ገንዘብ በማጠራቀም ሲሆን ከሁሉም በላይ ለስነምግባር ትምህርት ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጡ የምትናገረው የትነበርሽ “በእኛ ጊዜ የስነምግባር ትምህርት ስለነበር ትውልዱ አሁን ካለው ጋር ሲነፃፀር ጥሩ ሞራል የነበረው ነው፤ አሁን ግን ያ ጠፍቶ ለቀለም ትምህርት ብቻ ትኩረት ስለሚሰጥ በ26 አመቱ ዶክትሬት የሚይዝ ወጣት እውቀቱና ተግባሩ ለየብቻ ሆነው አገሩን የሚጎዳ ዜጋ ሆኗል፡፡ ያሉንን ምርጥ እሴቶች እያጣናቸው ስለሆነ የወደፊቱ ሁኔታ በጣም ስለሚያሳስበን ለተማሪዎቻችን ሰዎችን ስለማክበር፣ ስለ ሰላምታ አሰጣጥ፣ ስለይቅርታና ስለመሳሰሉት በሚገባ እንዲያውቁ እናተምራቸዋለን፡፡ በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች በምንሰጠው ሽልማት ከሌሎቹ ለየት እንላለን፡፡ ከዚህ በፊት ኮምፒውተሮችን ስንሸልም የቆየን ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ ከመዋዕለና ከአፀደ ሕፃናት አንደኛ ለወጡ ሕፃናት አቢሲኒያ ባንክ የአምስት መቶ ብር የቁጠባ ደብተር ከፍተንላቸዋል፡፡ ይህም ህፃናቱ ከአሁኑ የቁጠባ ባህል እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል፡፡”

ለየትነበርሽ እውቅና እነዚህ እንቅስቃሴዎቿ የትነበርሽን እውቅና አሰጥተዋታል፡፡ በ2003 በአካል ጉዳተኞችና በኤችአይቪ ዙሪያ ባደረገችው ከፍተኛ አስተዋፅዖ በደቡብ አፍሪካ የሂውማኒቴሪ አለም አቀፍ ሽልማት አግኝታለች፡፡ ከዚያ በኋላም በተለያዩ አገራት በምታቀርባቸው ፅሁፎች ከፍተኛ ተሰሚነት አግኝታለች፡፡ ለዚህም ነው በቅርቡ ከአስር ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች ጋር ልትመደብ የቻለችው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ “በቤት ውስጥም የተዋጣልኝ ባለሙያ ነኝ” ትላለች፡፡

“ቤት ውስጥ በጣም ባለሙያ ነኝ፡፡ እንዲህ እንድሆን ያደረገችኝ ደግሞ እናቴ ናት፡፡ (እናቴ የምትላቸው ያሳደጓትን አያቷን ነው) እሷ በፍፁም “አልችልም” የሚል ቃል እንዲወጣኝ አትፈቅድልኝ ነበርና ማኛውንም የቤት ስራ ሰርቼ ነው ያደግሁት፡፡ ዩኒቨርስቲ እያለሁም ለበዓል ወደቤት ስሄድ ዳቦ አቡክቼ ጋግሬ፣ ሽንኩርት ከትፌ ወጥ ሰርቼ ነበር በዓልን የምናሳልፈው፡፡ እና ዛሬ የቤት ውስጥ ረዳቶቼ ሲመጡ የሚገምቱትና ሲወጡ ይዘውት የሚሄዱት ነገር ይለያይባቸዋል፡፡ ፈፅሞ ስራ የምችል አይመስላቸውምና ዛሬ ፒሳ እንሰራለን፣ ይህን እጠቢ፣ይህን ክተፊ ስላቸው በጣም ይገረማሉ፡፡”

ከዚህም በላይ ጥሩ እናት ናት፡፡ ከባለቤቷ ከአቶ ብስራት ሸዋንግዛው የወለደቻትን የአንድ ዓመት ከሶስት ወሯን አሃቲን በጥሩ እንክብካቤ እያሳደገቻት ትገኛለች፡፡ ኤሌክትሪካል ኢንጂነር ከሆነው ባለቤቷ ጋር የተዋወቁት በሚያመልበት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን እንደሆነ ተናግራ እሱ እንግሊዝ ነዋሪ በመሆኑ ጋቻቸው ሊዘገይ እንደቻለም ጠቅሳለች፡፡ ጓዙን ጠቅልሎ ወደ አገሩ ከመጣ በኋላ ግን ጊዜ ሳያጠፉ ትዳር መስርተዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ልታስገነባ ባለችው ዩኒቨርስቲ ውስጥ በሲኒየር ማናጀር ሆኖ ይሠራል፡፡ ልጃቸውን እንዴት አሃቲ እንዳሏት ጠይቄያት ይህን ብላኛለች፡፡

“አሃቲ የግዕዝ ቃል ሲሆን፡- የመጀመሪያዋ፣ ቀዳሚዋ፣አንደኛዋ ማለት ነው፡፡ አሁን ለልጃች በብዛት እየወጡ ያሉት የዕብራይስጥና የአረብኛ ስሞች ናቸው፡፡ ይሄ ደግሞ ወደፊት የማንነት ጥያቄ ያነሳል የሚል ስጋት ስላለን ልጃችን አድጋ ይህ ሁኔታ እንዳይፈጠርባትና ከሴም ነገድ ጋር ያላትን ቀርኝት ማየት እንድትችል ነው አሃቲ ያልናት፡፡ ስሙ በወንድ አሃዱ በሚል ተለምዷል፡፡ አሃቲ አንድም ቀን የዱቄት ወተት አልጠጣችም፤ እስከ ስድስት ወር ድረስ ጡቴን ስትጠባ ቆየችና አርቴፊሻል ወተት ስንሰጣት እምቢ አለች፣ የተለያዩ ወተቶችን ብንሞክራትም እምቢ በማለቷ ከእናቷ በቀጥታ ወደ ላሟ ነው የተሸጋገረችው፡፡ ሐኪሞች ባይመክሩም እሷ ግን ስለተስማማት ንፅህናውን ጠብቀን ለአንድ ዓመት ከጠጣች በኋላ አሁን በምግብም፣ በእንቅልፍም፣ በመራመድም ራሷን ችላለች፡፡ “

የትነበርሽ አካል ጉዳተኛነቷን አንድም ቀን አማርራው አታውቅም፡፡ እንዲያውም “ለእኔ ስኬት ከጥረቴ ባሻገር 50 በመቶውን ድርሻ ያበረከተው አካል ጉዳተኛነቴ ነው” ትላለች፡፡ “ብዙዎች ሴት ሆነሽ በዚያ ላይ አካል ጉዳተኛ ሆነሽ እንዴት ይህን ሁሉ ለመስራት ቻልሽ? እያሉ እንደ ችግር የሚያነሷቸውን ነገሮች እኔ እንደ ዕድል ነው የማያቸው፡፡ ማንኛውንም ነገር ከተቀበልሽው ውስጡ ያለውን ማር ከፍተሸ ትበያለሽ፤ ካልተቀበልሽው ደግሞ ውስጡ ማር አይኖርም ብለሽ ስለምታምኚ እንደተራብሽ ትኖሪያለሽ፡፡ ዋናው ቅሉን የማመንና ያለማመን ጉዳይ ነው፡፡”

ከዚህ ቀደም በተለያዩ በጎ አድራጎት ላይ በስፋት ትንቀሳቀስ የነበረችው የትነበርሽ አሁን አሁን ጊዜዋን ለልጇ መስጠት እንደሚያደስታት ትናገራለች፡፡ “አሁን ጓጉቼ የምርለት ነገር የልጄ ጉዳይ ነው፤የምትሮጥበት፣ የምታወራበት፣በየቀኑ አዳዲስ ነገሮች የምታሳይበት ጊዜ ስለሆነ ያለኝን ጊዜ ከእሷ ጋር ለማሳለፍ እጓጓለሁ፡፡ እንደ በፊቱ ባይሆንም በሌሎች ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች እካፈላለሁ፡፡ እንዲያውም ለሌሎች ጊዜም ሆነ፣ ገንዘብም ሆነ፣ እውቀትም ሆነ ደም በመስጠት ደስተኛ ነኝ፡፡ ጎዶሏችን የሚሞላው በመቀበል ሳይሆን በመስጠት እንደሆነ አምናለሁ፡፡ አንድ የጎደለሽ ነገር ስትሰጪ እጥፍ ሆኖ ይመጣል፡፡ ያወቅሽውን ነገር ለሌሎች ስትናገሪ የበለጠ እያወቅሽ ትሄጃለሽ፡፡ ማስተማር የመማር አሪፉ መንገድ ነው የሚባለው ለዚህ ነውና ለሌሎች ማድረግ በጣም ያደስተኛል፡፡ ሌሎች ለእኔ ሰጥተውኝ ነው እዚህ የደረስኩት ብዬ አምናለሁ፡፡ እንዲያውም ይህ የሕይወቴ ፍልስፍና ነው፡፡ ቢደረግልኝ ደስ የሚለኝን ነገር ለሌሎች አደርጋለሁ፡፡ ለምሳሌ እኔ ሰዎች አክብረው ሲያናግሩኝ ደስ ስለሚለኝ እኔም የቤት ውስጥ ረዳቴን አክብሬ ሳናግራት ደስ ይላታል ማለት ነው፡፡ እኔ ዕረፍት እንደምፈልገው እሷም ሆነች በስሬ የሚሰሩት እረፍት ያስፈልጋቸዋል፡፡ በተቃራኒው እንዲደረግብኝ የማልፈልገውን ነገር ሌላ ሰው ላይ ማድረግ አልፈልግም፡፡ ስሰጥ ደግሞ መቼ ሊመልሱልኝ ይችላሉ? በሚል ስሜት አይደለም፤ ዝና ወይም እውቅናን ጠብቄም መሆን የለበትም፡፡”

“ተፅዕኖ ፈጣሪነት ያገኘውን ዝና ጠብቆ መቆየት ከባድ ነገር ነው” የምትለው የትነበርሽ ይህን ዝና ጠብቃ ለመቆየትና የአካል ጉዳተኞችን ችግር ለመቀነስ በምታደርገው ጥረት እንደምትቀጥል ትናገራለች፡፡ ተፅዕኖ መፍጠር በየጊዜው መማርን የሚጠይቅ እንጂ ትናንት የነበረውን ለውጥ ዛሬ መድገም አይደለም፤ ያ ከሆነ ከድራማ ወይም ከዘፈን አይለይም፡፡ ስለዚህ ዛሬ በወረቀት ላይ ያሉትን አካል ጉዳተኞችን አስመልክቶ የወጡ ሕችና ደንቦች ተፈፃሚነት እንዲኖራቸው ማድረግ እንዳለብን ይሰማኛል፡፡ በዚህም ዓለም ለአካል ጉዳተኞች ያለው ዓይነት አመለካከት በእኛም አገር እንዲኖር መጠንከር ያለብን ጊዜ ነው” ስትል ክድንቅ መጽሔት አትላንታ ጋር የነበራትን ቆይታ አጠናቃለች።
____________
በሰሞኑ ስኬቷም ደስታችንን በዚህ አጋጣሚኦ እንገልጻለን።

Happy
Happy
17 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
33 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
50 %
    Print       Email

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar