Maleda Times Media Group

ኢትዮጵያ ውስጥ በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች እንዲፈቱ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ጠየቀ። ድርጅቱ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተዉ የተሻለ የፖለቲካ መድረክ በሀገሪቱ ለመፍጠር ፤የኢትዮጵያ መንግስት በፀረ ሽብር ሕጉ «ጥፈተኛ ናችሁ »ብሎ ያሰራቸዉን ጋዜጠኞች ሊለቅ ይገባል።

ለጋዜጠኞች መብት የሚሟገተዉ ይህ ድርጅት ጋዜጠኞቹ እንዲፈቱ የጠየቀዉ፤የኢትዮጵያ መንግስት በወንጀል ድርጊት የተፈረደባቸዉና በዓቃቬ ህግ ጉዳያቸዉ ተይዞ በእስር የሚገኙ የፖለቲካ አባላትና ግለሰቦች «የተሻለ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠርና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት» በሚል ክሳቸዉ ተቋርጦ በምህረትና በይቅርታ እንዲፈቱ በወሰነዉ መሰረት ነዉ።

የድርጅቱ የአፍሪቃ ተጠሪ መሊሳዉንድ መቹበር እንደገለጹት ይህ የመንግስት መግለጫ ስለ ጋዜጠኞቹ መብት ለመጠየቅ ለድርጅታቸዉ ጥሩ አጋጣሚ ነዉ።

«በእርግጥ እነዚህ የታሰሩ ጋዜጠኞች እንዲፈቱ እንጠይቃለን። ምክንያቱም ይህ የኛ ሀላፊነት ነዉ። እንደምታዉቁት እኛ ለመረጃ ነፃነት ነዉ የምንታገለዉ። እንደምናስበዉ ማ የጋዜጠኞቹ መለቀቅ ለዴሞክራሲና ለፖለቲካ ምሕዳሩ መስፋት በጣም ጠቃሚ ነዉ።

ኢትዮጵያ የተወሰነ ቁጥር ያላቸዉን የፖለቲካ እስረኞች እንደምትለቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታዉቀዋል ። እናም የጋዜጠኞቹን መፈታት ለመጠየቅ ለኛ ጥሩ አጋጣሚ ነዉ። ሃገራዊ መግባባትና የፖለቲካ ዉይይት ለመክፈት የነዚህ ጋዜጠኞች መፈታት ጥሩ ጅምር ነዉ።» ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በመቶወች የሚቆጠሩ እስረኞችን ለመልቀቅ መዘጋጀቱን ጥሩ ጅምር ነዉ ያሉት ሀላፊዋ፤ይሁን እንጅ እስክንድር ነጋ፣ዉብሸት ታዬና ዘላለም ወርቅ አገኜሁን የመሳሰሉ ጋዜጠኞችና የድህረ-ገፅ ፀሀፊያንን በዚህ የምህረትና የይቅርታ ዉሳኔ ተካተዉ ሊፈቱ ይገባል ይላሉ።

እነዚህ ጋዜጠኞች በጎርጎሮሳዊዉ የዘመን ቀመር በ 2009 አ/ም በወጣዉ የፀረ-ሽብር ህግ« ተከሰዉ የተፈረደባቸዉ ናቸዉ» በሚል ከሰሞኑ ይቅርታና ምህረት ዉሳኔ አለመካተታቸዉ አግባብነት የለዉም ሲል ድርጅቱ ተችቷል።

በሀገሪቱ የተሻለ ብሄራዊ መግባባትና ፖለቲካዊ ዉይይት ለመክፈት ከተፈለገ ጋዜጠኞቹ በመጻፋቸዉ ብቻ ለእስር የተዳረጉ በመሆናቸዉ ሊፈቱ ይገባል ሲሉ ሀላፊዋ አመልክተዋል።

«እነዚህ ጋዜጠኞች ይፈታሉ ብለን እንጠብቃለን የታሰሩት በ ጎርጎረሳዊዉ የዘመን ቀመር በ2009 በወጣዉ የፀረ ሽብር ሕግ ነዉ።

ጋዜጠኞቹ የታሰሩበት ምክንያት ደግሞ መንግሥትን የሚተች ዘገባ ስለፃፉ ነዉ። እናም የመንግሥት ፈቃድኝነት ሃገራዊ መግባባትና ሁሉንም የሚመለከታቸዉ አካላት ያሳተፈ የፖለቲካ ዉይይት መክፈት ከሆነ፤ ይህንን ማሳየት አለበት ብዬ አስባለሁ። እነዚህ ጋዜጠኞች በዚህ ዉይይት አስፈላጊ ናቸዉ።

የታሰሩት በሚያስቡት እና በሚያንፀባርቁት ኃሳብ ነዉ። እነዚህን ጋዜጠኞች በኢትዮጵያ ያለዉን ሁኔታ በተመለከተ ለኅብረተሰቡ መረጃ ለመስጠት በጣም አስፈላጊ መሆናቸዉን መንግሥት መረዳት አለበት። » ሲሉ ገልጸዋል።

እንደ ሀላፊዋ ያለ መረጃ ነጻነት በሀገሪቱ የታሰበዉ ለዉጥ ሊመጣ ስለማይችል መንግስት ሊያስብበት ይገባል።
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በዉጭ ሀገር ለሚገኙ ኢትዮፕያዉያንና ትዉልደ ኢትዮጵያዉያን መረጃ በሚሰጥ «ኢትዮ ሚዲያ» በተባለ ድህረ-ገጽ ይጽፍ እንደነበር መግለጫዉ አስታዉሶ ፤የጸረ-ሽብር ህጉ «ጋዜጠኞችን ለማፈን ዉሏል» ብሎ በመተቸቱ ብቻ ከጎርጎሮሳዊዉ ሀምሌ 2012 ጀምሮ በ 18 ዓመታት እስራት መቀጣቱ አግባብነት የለዉም ሲል ገልጿል።

ሌላዉ በድርጅቱ መግለጫ የተጠቀሰዉ ጋዜጠኛ ዉብሸት ታዬ ሲሆን ፤ጋዜጠኛዉ መንግስትን የሚተች ጽሁፍ በመጻፉ ብቻ ከጥር 2012 ጀምሮ ለ 14 ዓመታት በሚቆይ እስር መቀጣቱ ፍትሃዊ አይደለም በሚል ተችቷል።

ከ 2016 ጀምሮ ለ 5 ዓመት ከ 4 ወር የተበየነበት የድህረ ገጽ-ጸሀፊ ዘላለም ወርቅ አገኜሁም ቢሆን በዚሁ የጸረ-ሽብር ህግ« የሽብርተኛ ቡድን መደገፍ» በሚል መታሰሩን ድርጅቱ ተቃዉሟል።

እነዚህና ሌሎች የድህረ ገጽ-ጸሀፊያንና ጋዜጠኞች መረጃ የመስጠት መብታቸዉን ስለተጠቀሙ ብቻ በወንጀል ተከሰዉ ለእስር የተዳረጉ በመሆናቸዉ በአስቸኳይ ሊፈቱ ይገባል ሲል ድርጅቱ በመግለጫዉ ጠይቋል።

ለዚህም ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብና ለመረጃ ነጻነት የሚታገሉ ድርጅቶች ድምጻቸዉን ሊያሰሙ እንደሚገባ ሀላፊዋ አሳስበዋል።

ፀሀይ ጫኔ
ነጋሽ መሀመድ