ማለዳ መረጃ ማእከል የእርስዎ የዜና አውታር
  • የኢትዮጵያና ግብፅ የሚኒስትሮች ስብሰባ ዛሬ ይጀመራል

የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድቡን በመገንባት ጫናውን ለብቻቸው እንደተሸከሙ፣ የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አል በሽር ተናገሩ፡፡

ፕሬዚዳንቱ ይህንን የተናገሩት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን መልዕክት ሲያደርስና በሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ በተነጋገረበት ወቅት መሆኑን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያውያን የህዳሴ ግድቡን የመገንባት ጫና ለብቻቸው ተሸክመዋል፤›› ያሉት ፕሬዚዳንት አል በሽር፣ ‹‹ሱዳናውያን የዚህ ዕዳ አለብን፤›› ብለዋል፡፡

የግድቡ መገንባት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሱዳንና ለሌሎች ሕዝቦችም የበለጠ ጠቀሜታን እንደሚገኝበትም መናገራቸውን፣ ውይይቱን የተከታተሉት አቶ መለስ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያና የሱዳን ዕጣ ፈንታ አብሮ የተገመደ መሆኑንና በመንግሥታት ለውጥ ወቅትም ሳይላላ እንደቀጠለ ፕሬዚዳንቱ መናገራቸውን አቶ መለስ ጠቁመዋል፡፡

የፕሬዚዳንት አል በሽር ንግግር ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አቋም ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡

አቶ መለስ የታላቁ ህዳሴ ግደብ የመሠረት ድንጋይን ከአምስት ዓመት በፊት ባስቀመጡበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹ፍትሕ ካለ የዚህን ግድብ ግንባታ ወጪ ሱዳን 20 በመቶ፣ ግብፅ 30 በመቶ ሊሸፍኑ ይገባል፤›› ብለው ነበር፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምን መልዕክት ይዘው እሑድ ጥር 6 ቀን 2010 ዓ.ም. ሱዳን ካርቱም ከተማ የተገኙት ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ ‹‹ኢትዮጵያና ሱዳን የአንድ ወንዝ ልጆች ናቸው፤›› ማለታቸውን አቶ መለስ አስታውሰው፣ ከሱዳኑ አቻቸው ጋርም በወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን አስረድተዋል፡፡

በኢትጵያና በሱዳን መካከል ቀደም ብለው የተፈረሙ ስምምነቶች በፍጥነት ተግባራዊ እንዲሆኑና የሁለቱን አገሮች ግንኙነት የበለጠ መጠናከር እንደሚገባው የተግባቡ መሆኑን፣ እንዲሁም በየጊዜው የፖለቲካ ምክክር ማድረግ እንደሚገባ መስማማታቸው ተገልጿል፡፡

በተያያዘ ዜና በስድስተኛው የኢትዮጵያና የግብፅ የሁለትዮሽ የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ላይ ለመገኘት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የሚመራ ልዑካን ወደ ግብፅ ማክሰኞ ጥር 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ማምሻውን ማቅናቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከረቡዕ ጥር 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ የሁለቱ አገሮች የሚኒስትሮች ስብሰባ የሚካሄድ ሲሆን፣ ሐሙስ በመሪዎች ደረጃ ውይይት እንደሚደረግ አቶ መለስ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ረቡዕ ጥር 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ወደ ካይሮ ያመራሉ፡፡

ይህ የኢትዮጵያና የሱዳን የጋራ ኮሚሽን የተጀመረው እ.ኤ.አ. በ1989 ነው፡፡ የአሁኑ ለስድስተኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን፣ በመሪዎች ደረጃ ሲካሄድ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በኢትዮጵያና በሱዳን የውስጥ ጉዳይ ግብፅ ጣልቃ አትገባም ማለታቸው ተደምጧል፡፡ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመረቁበት ወቅት ፕሬዚዳንቱ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹ከወንድሞቻችን ጋር ጦርነት ውስጥ አንገባም፣ በወንድሞቻችን ላይም አናሴርም፤›› ማለታቸውን የተለያዩ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡

ይህ የፕሬዚዳነቱ ንግግር የሱዳን መንግሥት በኤርትራ በኩል ያለውን ድንበሩን በመዝጋቱ ሳቢያ እንደሆነ ተገምቷል፡፡ ሱዳን ይህንን ድንበር የዘጋችው የግብፅ ጦር በኤርትራ እንደሠፈረ ከተረዳች በኋላ ነው፡፡