www.maledatimes.com ለለማ ቡድን ትንሽ ማሳሰቢያ ብሥራት ደረሰ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Addis Admas  >  Current Article

ለለማ ቡድን ትንሽ ማሳሰቢያ ብሥራት ደረሰ

By   /   August 23, 2018  /   Comments Off on ለለማ ቡድን ትንሽ ማሳሰቢያ ብሥራት ደረሰ

    Print       Email
0 0
Read Time:8 Minute, 55 Second

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢድ አል አደሃ (አረፋ) በዓልን በማስመልከት የመልካም ምኞት መግለጫ

 

ወዳጅ ሊሆን የማይችልን የለዬለት ጠላት በመለማመጥ ጊዜ ማባከን አያስፈልግም፡፡ ከንቱን ሰው ሲለማመጡት የፈሩት ይመስለዋል፡፡ ራሱን በጠባብ ዓለም ከርችሞ የሚኖር ሰው በውጭው የሚከናወነውን የመረዳት አእምሯዊ አቅምና ፍላጎትም የለውም፡፡ የዚህን ዓይነቱ ሰው ጋር ኅብረትና ሰላም እፈጥራለሁ ብሎ መታገል ኃይልንና ጊዜን በከንቱ ማጥፋት ነው፡፡

የነለማ ቡድን – የጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጎራ – እየወደቀ እየተነሣ አሁን ላይ ደርሷል – ዛሬ ነሐሴ 14/ 2010 መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ባለፉት ጥቂት ወራት ከነዐቢይ የለመድናቸው የዕለት ከለት እንቅስቃሴዎች ሲጓደሉብን በ“ልጆቻችንን ምን አገኘብን?” ሰቀቀን በፍርሀት እየተጨነቅን – ዳናቸው ሲጠፋብን እጅጉን ቅር እየተሰኘንና እየተከዝን – በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ሲሉ ደግሞ በ“ምንም አልሆኑም” የደስታ መንፈስ  እየቦረቅን ዛሬ ላይ አለን፡፡ ተመስገን፡፡

አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የለማን ቡድን – በተለመደው ጉራማይሌ አጠቃቀም “ቲም ለማ”ን – ለምን እንደወደደው መናገር የዐዋጁን በጆሮ ይሆንብኛል፡፡ ይሁንና የዚህን ቡድን ገድል በጥቂት ቃላት እዚህ ላይ መጥቀሱ ከውለታ-በልነት ያድናል፡፡ የመልካም ሰው ታሪክ ሠርክ ቢጠቀስ አይሰለችም፡፡

ሀገራችን ልትጠፋ አንድ ሐሙስ ገደማ ቀርቷት ሳለ እነዚህ ሣተና ወጣቶች ለነፍሳቸው ሳይሳሱ ከነጎልያድ ጋር ጦርነት ለመግጠም ከውስጥ ብቅ አሉ፡፡ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ሕዝብም ከሕወሓት ሠይፍ ታደጉ፡፡ ሕወሓትንም ሊከሰት አፋፍ ላይ ደርሶ ከነበረ የኢትዮጵያውያን የአልሞት ባይ ተጋዳይ መቅሰፍታዊ ዱብዕዳ አዳኑ፡፡ አለወንጀል በዘር ጥላቻና በቂም በቀል ታስረው ሰይጣን ራሱ እንኳን በማያቃቸው የስቃይ ዓይነቶች ሲዖላዊ የመከራ ዶፍ ይደርስባቸው የነበሩ ዜጎችን አስፈቱ፤ ፈቱ፡፡ ሕዝብ ከሸፈተበት የምናብ ዓለም መልሰው ስለሀገሩ እንዲጨነቅና ስለሕይወት እንዲያስብ አደረጉ፡፡ በሀገር ናፍቆት የናወዙና ሀገር እያላቸው እንደሌላቸው ሆነው በሰው ሀገር የሚኖሩ ስደተኞችን ወደሀገር እንዲመለሱ አደረጉ፣ ወያኔ ካልወደቀ ወደ ሀገር መግባት ቀርቶ – በቅጥር ነፍሰ ገዳዮች ወያኔያዊ ተልእኮና በእበላ ባዮች ዛቻ ምክንያት – ባሉበት የስደት ሀገርም በነፃነት የመኖር ዕድል ተነፍጓቸው የነበሩ ውድ ዜጎች ወዳገራቸው እንዲመጡና በፖለቲካውም እንዲሳተፉ ፈር ቀደዱ፣ ባጭሩ ጥቂት ዳዊቶች በፈጣሪ እገዛ፣ በሕዝብ ዕንባ እገዛ፣ በሕዝብ ደም እገዛ፣ በጸሎት እገዛ…. በጦርና በብዙ ገንዘብ የደለበውን የጎሊያድን ቡድን ቢያንስ እስካሁኒቷ ደቂቃም ቢሆን አንበረከኩ፤ ወደጎሬውም እንዲሰበሰብ አደረጉ፡፡ ይህ የላይ ትዛዝ እንጂ የታች ብርታት ብቻ እንዳልሆነ የእምዬ ኢትዮጵያን ታሪክ ያነበበ ሁሉ የሚረዳው ታሪካዊ እውነታ ነው፡፡ አለ ገና ብዙ ደግሞ!

የለማን ቡድን ማሳሰብ የምፈልገው፡-

የኔ ሃይማኖት ቁንጮ – ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ሳለ ያነበብንና ያመንን ሰዎች በምንረዳው መልክ እንዲያ ተሰቃይቶ ተልእኮውን በጀመረ በ33 ዓመት ከ3 ወሩ በጠላቶቹ ሤራና ተንኮል ተሰቅሎ ሊሞት የቻለው በትግስቱ ብዛት ነበር፡፡ የተቀነጠሰ የጠላት ጆሮን “በሠይፍ የሚቆርጡ በሠይፍ ይቆረጣሉ” በሚል ማስጠንቀቂያ ወደ ቦታው መመለስ የቻለ መለኮታዊ ኃይልና ሥልጣን የነበረው ክርስቶስ፣ የሞተውን አልዓዛር በ4ኛ ቀኑ ወደሕይወት መመለስ የሚያስችል የድንቅ ተዓምር ባለቤት የነበረው ክርስቶስ … በሚያሣዝን ሁኔታ በመስቀል ተቸንክሮ የሞተው የራሱ ዓላማ ቢኖረውም እንደሰውኛ አስተሳሰብ ግን መጠኑን ያለፈ ትግስት ስለነበረው ነበር፡፡ ይህ ሃይማኖታዊ ነገር ነው፤ የቀኖና ወይም የዶግማ አመሥጥሮ አለውና ወደዚያ መግባት አይገባንም፡፡ ወደሰውኛ አስተሳሰብና የነገሮች አካሄድ ስንለውጠው ግን የዚያ ዓይነቱ አካሄድ በምንም መንገድ አያዋጣም ብቻ ሣይሆን በ“ለምሣ ሲያስቡን ቁርስ አደረግናቸው” ደርጋዊ አባባል ለጭዳነት የሚዳርግና ካለፈ ታሪክና አስቀያሚ ክስተቶች አለመማርን የሚጠቁም የሞኞች አካሄድ ነው፡፡ “እጅግም ስለት ይቀዳል አፎት” በሚል ማኅበረሰብ ውስጥ ይህን ያህል ታጋሽ መሆን መጨረሻው እንደማያምር መገንዘብ ብልኅነት ነው፡፡ ሁሉንም ኃላፊነት ለፈጣሪ መስጠት ደግሞ አይመከርም፡፡

ይህ ለውጥ በዚህ መልክ ከሄደ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይቀለበሳል፡፡ ቢቀለበስ ደግሞ በፈረንጅኛው አጠራር የ“Pandora’s Box” ኢትዮጵያ ላይ ይፈታል፡፡ ከዚያም የሚተርፈው ጥቂት ይሆንና ሀገርን የመሥራቱ ሂደት ከእንደገና “ሀ” ተብሎ ይጀመራል – ከዜሮ፡፡ የኛ ሀገር ጎሣና ብሔር ብዙ ነው፡፡ ዳፋውም ያንኑ ያህል ብዙ ይሆናል፡፡ የሚያዋጣው ብቸኛ መንገድ ይህን ለውጥ እንደምንም ደጋግፎና ጠጋግኖ እውን ማድረግ ብቻ ነው፡፡ ውድ ወገኖች! የነብርን ጅራት አይዙም – ከያዙም አይለቁም፡፡

 

ሀ. ወያኔን መለማመጥ በአስቸኳይ ይቁም፡፡ እርግጥ ነው – የሚሩበትን ምክንያት እናውቀዋለን፡፡ የዘረፉትና የመዘበሩት ብዙ ገንዘብ አላቸው፤ የዘረፉት ብዙ የጦር መሣሪያ አላቸው፤ በዓላማ ቁርኝትና በገንዘብ የያዙት ብዙ ደጋፊ አላቸው፤ ብዙ የጥፋት አማራጭ አላቸው፤ ቢሮክራሲውንና ጦሩን፣ ፖሊሱንና ደኅንነቱን የያዙት በአብዛኛው እነሱ ናቸው፤ ንግዱንና ኢኮኖሚውን፣ ዲፕሎማሲውንና የመረጃ መረቡን የያዙት እነሱ ናቸው…፡፡ በ27 ዓመታት ውስጥ ብቻ በመቶ ዓመታት ውስጥም ሊደረጉ የማይችሉ እጅግ ትልልቅ ተፅዕኖዎችን መፍጠር የሚችሉ በጣም ብዙ ውስብስብ ሤራዎችን አከናውነዋልና ማንም ወገን ወያኔን ቢፈራ በበኩሌ አልፈርድበትም፡፡ ከዚህ አኳያ የእስካሁኑ ጥንቃቄ መልካም ነበር፡፡ በዚህ መልክ ከቀጠልን ግን የኛንም ኃይል ማሳሳት ይሆናል፡፡ የኛ ኃይል ብዙነታችን ነው፤ የኛ ኃይል የነፃነት ጥማታችን ነው፡፡ የኛ ኃይል መፈለጋችን ነው – ፍላጎት ኃይልም ነውና፡፡ መጽሐፉስ “እሹ ታገኛላችሁ” አይደል የሚለው?

የብዛትን ኃያልት በሚመለከት ቻይናዎች ምን ይላሉ “ሂማሊያ ተራራ ላይ ሆነን ብንሸና ዓለምን እናጥለቀልቃለን፡፡” እውነታቸውን ነው፡፡ እኛም ጥሩ አመራር ካገኘን እንደ አያት ቅድመ አያቶቻችን በዱላና በሚጥሚጣ ብቻ ጠላትን ማንበርከክ አያቅተንም፡፡ ወያኔዎች በጭካኔ አገዛዝ አንዳችንን ከአንዳችን በመለያየት እያናቆሩ እንደዚያ ወጥረው የያዙን እኮ ኃይላችንን እንዳናውቅና ተባብረን እንዳናጠቃቸው ሲሉ ነበር፡፡ ስለዚህ የለማ ቡድን የሕዝብን የጋለ ኃይል በወቅቱ መጠቀም ካልቻለ ከሁለት ያጣ ጎመን እንዳይሆን እሰጋለሁ፡፡ ተስፋ የቆረጠን ወገን ከእንደገና ተስፋው እንዲለመልም ማድረግ ደግሞ ከባድ ነው፡፡

ለ. ወያኔ ወታደር ይቀጥር የነበረው እንዲህ ነበር – ያ አሁን መለወጥ አለበት፡፡ ኢትዮጵያን ቢቻል የሚጠላ ባይቻል ስለኢትዮጵያ ታሪክ የማያውቅ፣ በትምህርቱ ከማንበብና መጻፍ ያልዘለለ ወይም ከነአካቴው ማይም፣ ብሔረሰቡ በተቻለ መጠን አማራና ኦሮሞ ያልሆነና ሥልጣኔ ካልገባው የሩቅ ገጠር የሚመለመል፣ ከማኅበረሰቡ ጋር ሊግባባ የማይችል፣ ስሙንና የትውልድ መንደሩን ከመለየት ውጪ ምንም ዓይነት ዕውቀትና ግንዛቤ የሌለው፣ ግደል ሲሉት ብቻ የሚገድል፣ ስለሀገርና ስለባንዲራ የሚያውቀው ነገር የሌለው፣ zero EQ, (Emotional Quotient), zero SQ (Spiritual Quotient), zero IQ, (Intelligence Quotient) ከማኅበረሰቡ ጋር በቋንቋም ሆነ በስሜት ሊግባባ የማይችል ሮቦታዊ ሜካኒካል ፍጡር፣ በመልክም በአስተሳሰብም በብሔራዊ ስሜትም ከአብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል ጋር የማይገጥም በአጭሩ በሰው አምሳል የሚንቀሳቀስ ዐውሬ ወታደር ነው  ሀገራችን የነበራት የመከላከያ ሠራዊት – ይህም የሆነው ሆን ተብሎ ነው፡፡ ይህን የሠራዊት አወቃቀር ይዞ የትም መድረስ አይቻልምና በአስቸኳይ ሊስተካከል ይገባዋል፡፡ በፖሊሱና በደኅንነቱም ከዚህ የሚከፋ እንጂ የተሻለ ነገር የለምና ሕዝብ ሕዝብ የሚሸት የጦር ሠራዊትና የፀጥታ ኃይል እንዲኖረን ማድረግ ጊዜ የማይሰጠው የለማ ቡድን የወቅቱ ተግባር ነው፡፡

ሐ. አሁንም ቢሆን ቢሮክራሲው በአብዛኛው የተሞላው በወያኔዎች ነው፡፡ በተራ ሠራተኝነትም ሆነ በኃላፊነት የሌሎች ጎሣዎች አባላት ቢኖሩም ተፅዕኗቸው እንደወያኔዎቹ አይደለምና ወያኔዎች ለውጡን የመገዳደር ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡ በዚያ ላይ ይህ ቢሮክራሲ ከላይ እስከታች በሙስና የበከተ ነው፡፡ በመብራት ኃይል፣ በቴሌ፣ በፍርድ ቤቶችና የፍትህ አካላት፣ በማዘጋጃ ቤቶችና በከፍተኛዎች እንዲሁም በወረዳዎች የሚገኘው ሠራተኛ ካለሙስና እስትንፋሱ ቀጥ የሚል የጉቦ ሱስ የተጠናወተው ነው፤ ማረጋገጥ ከፈለግህ አንዲት ጉዳይ ያዝና ወደነዚህ ቢሮዎች ብቅ በል፡፡ የወያኔው ባለሥልጣናትና ወታደራዊ ሹማምንትም በሙስና የተዘፈቁ ናቸው፡፡ ይህንንም መረዳት ብትፈልግ የግል ባንኮችንና የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን በምሥጢር ጠይቅ – ሁሉም በሚባል ሁኔታ በአስገዳጅ መንገድ ሕንፃ የሚከራዩት ከነዚህ መዥገሮች ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከሚገኙ 100 ሕንፃዎች መካከል በግርድፍ ግምት 75 በመቶ የሚሆኑት የወያኔ ቱባ ባለሥልጣናትና የዘረኝነት ብል ያነጎዳቸው ትግሬ ወያኔዎች ንብረቶች ናቸው፡፡ ይህን በቁሙ የሞተና አእምሮው የጫጫ ዜጋ ይዞ ሀገርን በዲሞክራሲና በፍትህ አራምዳለሁ ብሎ መፍጨርጨር ከህልም የማይዘል ከንቱ ቅዠት ነው፡፡ እንተዋወቃለን፡፡ ከሃይማኖት ቁንጮ እስከፖለቲካው ግርጌ ድረስ ኅሊናው በገንዘብ የተሰወረ የማኅበረሰብ ክፍል ይዘን ለውጥን በአጭር ጊዜና በተፈለገው ፍጥነት ከግቡ ማድረስ ከባድ ጥረትንና መስዋዕትነትን ይጠይቃል፡፡ አንደኛው የለውጡ ደንቃራ እንግዲህ ሙስና መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ብሂላችን አስቀምጦታል – “ሆዳም ሰው ፍቅር አያውቅም”፡፡ ሀገራችን በሆድ ምክንያት እየጠፋች ነው፡፡

መ. የቀድሞ ሥርዓት(ቶች) አገልጋዮች የተባረሩበት ዋና ምክንያት ሀገራቸውን መውደዳቸው እንደሆነ ይገመታል፡፡ ጥፋት የሌለባቸውና ጥፋት ቢኖርባቸውም ንስሃ ገብተው የተጸጸቱ ወገኖች ይህን ለውጥ ደግፈው እንዲቆሙና ክፍተቶችን እንዲሞሉ አፋጣኝ ጥረት ይደረግ፡፡ ወያኔ በራሱ ዘመንም ያባረራቸውን የጦርና የሲቪል ሠራተኞች መጠቀም ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ “የሰው ያለህ!” እያለች በምትገኝበት በዚህን አሳሳቢ ወቅት በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ እነዚያን አንጡራ የሀገር ሀብቶች መጠቀም አለመፈለግ የጤና ሊሆን አይችልም፡፡ አየር ወለዶች፣ አየር ኃይሎች፣ የቀድሞው መከላከያ አባላት፣ የጦርና የሲቭል መሃንዲሶች፣ መምህራን ወዘተ. የሚጋብዛቸውን እየጠበቁ እንደሚገኙ ይሰማኛል፡፡ ሀገርን ለመፍጠር ዜጎችን በዚህና በዚያ ምክንያት መጠየፍም ሆነ በኩራት መኮፈስ ተገቢ አይሆንም፡፡ ከወያኔ የማይሻል ደግሞ በፍጹም የለም፡፡ ከቀን ጅብ የሌሊት ጅብ ይሻላል፡፡ እየጠላህ ከሚበላህ እየወደደህ የሚባለህ የተሻለ ነው፡፡ ከነሱ ሌባ ያንተ ሌባ ያዝንልሃል፡፡ ዕድሜና ተሞክሮ አስተማሪ ናቸው – ብዙና በጣም ተማርን፡፡

ሠ. ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል፡፡ ምን ለማለት ነው – ይህ የሚሊዮኖችን ደም ጠይቆ የተገኘ የለውጥ ዘመን የሚጠለፈው በወያኔ ብቻ አይደለም፡፡ እውነትን ብቻ እንነጋገር ካልን የአንድ ለውጥ ተፃራሪዎች ከብዙ አቅጣጫ ይፈልቃሉ፤ ከሥልጣን ሽሚያ፣ ከጥቅም ሽሚያ፣ ከድል ባለቤትነት ሽሚያ፣  የራስን  ፍላጎት በሌሎች ላይ ለመጫን ከሚደረግ ሽሚያ፣ ለጠላት ድርጎ ተገዝቶ የጠላትን ፍላጎት እውን ለማድረግ ከመፈለግ አኳያ ወዘተ. የአንድ ለውጥ ተቃራኒ ሆኖ መቆም ሊከሰት ይችላል፡፡ … ዐቢይን እንደልጄ የምሳሳለት ኢትዮጵያዊ በመሆኑ እንጂ ሌላ በመሆኑ አይደለም፡፡ የብዙ ሰው ስሜትና እምነትም ይሄው ነው፡፡ በ97 ዓ.ም ያ ሁሉ ሕዝብ ለቅንጅት ጠብ እርግፍ ያለለት ብርሃኑ ነጋ አማራ ወይም ኦሮሞ ወይም ትግሬ ስለሆነ አልነበረም፡፡ ፖለቲከኞች ያልገባቸውና ምናልባትም በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የማይገባቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ መገለጫ ዋነኛ ባሕርይ ዘረኛ አለመሆኑ ነው፡፡ ሀገራችንን ማንም ይግዛት ማን የሚታየው ሥራው እንጂ የዘር ሐረጉ አይደለም – ኃጢኣት እንዳንገባ የኢትዮጵያን ሕዝብ በዘረኝነት አንፈርጅ፡፡ ስለዚህ “በጨው ደንደስ በርበሬ ተወደስ” እንዳይሆንብን በብዙኃን ደምና አጥንት የመጣልንን የእፎይታ ዘመን በሌላ ዘረኝነት እንዳይጠለፍና ወደነበርንበት አረንቋ ተመልሰን እንዳንዘፈቅ ሁሉም የተቻለውን ማድረግ ይገባዋል፡፡ ከዚህ አንጻር የለማ ቡድን ፈዛዛነት ከታከለበት ታጥቦ ጭቃ እንዳንሆን እፈራለሁ፡፡ በተለይ በነጃዋር መሀመድ በኩል እየተሰማ ያለው ነገር ግልጽ ቢሆን ጥሩ ነው፡፡ “ይቺ ጎንበስ ጎንበስ ዕቃ ለማንሣት ነው” ይላሉ አራዶች፡፡ ይህ በሳይከካ ተቦካ የሚታይ የሥልጣን እሽቅድምድም ነገራችንን ሁሉ የልጆች የዕቃቃ ጨዋታ አድርጎት እንዳይቀር ሥጋት አለኝ፡፡ በኦሮሞ ሕዝብ ስም እየተከናወነ ያለው ውልየለሽ ነገር በአፋጣኝ ዕልባት ካላገኘ የነለማ ድካም ከዳር የሚደርስ አይመስለኝም፡፡  አንድን የሕዝብ ክፍል በተለያዩ ቅስቀሳዎች ወደ አንድ በብዙኃን ዘንድ ወደማይፈለግ ጫፍ መውሰድ ይቻላል፡፡ ስለዚህ ፖለቲከኞች በጤናማ አስተሳሰብ እየተመሩ ሕዝብን ወደተሳሳተ አቅጣጫ ላለመምራት መጠንቀቅ ይገባቸዋል፡፡ …

ረ. የጋራ ቋንቋን በሚመለከት –

እስካሁን አልሣቃችሁም – አውቃለሁ፡፡ ትንሽ እንድትስቁ አንዲት መናኛ የጎረምሦች ቀልድ ልንገራችሁ፡፡ የጎረምሣ ቀልድ የማይወድ ቢኖር  አለማንበብም ይቻላል፡፡ … ባልና ሚስት ከሁለት ሕጻናት ልጆቻቸው ጋር ወደ ፍልውኃ ይሄዳሉ፡፡ ሕጻናቱ ወንድና ሴት ናቸው፡፡ ወንዱ ሕጻን ከእናቴ ጋር ነው እምገባው ይላል፤ ሴቷም ሕጻን ከአባቴ ጋር ነው የምገባው ትላለች፡፡ የፍልውኃው ሠራተኞች ግን “አለደምቡ አይሆንም” በማለት ሴቷ ከእናቷ ጋር፣ ወንዱም ከአባቱ ጋር እንዲገቡ ያደርጋሉ፡፡ መታጠቢው የቁም ነው፡፡ አባትና ልጅ እየታጠቡ ሳለ ሕጻኑ ሣሙናው ያዳልጠውና ሊወድቅ ሲል የአባቱን አንድ ነገር ይዞ ከትልቅ አደጋ ይተርፋል፡፡ አባት ይሄኔ “እናትህ ጋር ገብተህ ብትሆን ኖሮ ጥርስህን ለቅመህ ነበር!” በማለት ከርሱ ጋር መሆኑ ካልተጠበቀ ትልቅ አደጋ እንዳተረፈው አስረዳውና ጨርሰው ወጡ፡፡

ዐማርኛ ቋንቋ ባይኖር ኖሮ ይሄኔ ሰማንያና ዘጠናው የኢትዮጵያ ጎሣና ነገድ ምን ይውጠው እንደነበር በተለይ የቋንቋ መምህራን ብናስበው ሀገራዊ አደጋው እጅግ ከባድና ፈታኝም እንደሚሆን እንገነዘባለን – ባቢሎን በኢትዮጵያ ዓይነት፡፡ ይህን ተፈጥሯዊ የቋንቋ ጠቀሜታና አስፈላጊነት የማይረዱ ሞኞች “የኛ ቋንቋ፣ የነሱ ቋንቋ “በሚል ሚዛን የማይደፋ አታካሮ ውስጥ ገብተው ሲነታረኩ ማየት አሳዛኝ ነው፡፡ በመሠረቱ አንድ ቋንቋ ከአንድ ሌማት ወይም የቡና ሥኒ ያልተናነሰ የመገልገያ መሣሪያ እንጂ ከምንም ዓይነት የአካልም ሆነ የዘር ግንድ ጋር የሚገናኝ ትልቅ ነገር አይደለም፡፡ “ቋንቋ ባሕርያዊ አይደለም” መባሉም ለዚህ ነው፡፡ ለምሣሌ አንድ የአማራ ነገድ ተወላጅ በኦሮሞ ውስጥ ተወልዶ ቢያድግ ጆሮውን ቢቆርጡት አማርኛን አይናገርም፤ አይሰማምም – ለዚህ አባባል የሚጠቀሱ ብዙ አብነቶች አሉ፡፡ ሰው የሚፈጠረው ማንኛውንም የሰው ልጅ ቋንቋ ሊለምድ ከሚያስችለው ተፈጥሯዊ ችሎታ ጋር እንጂ የእናት የአባት የሚባል ቋንቋ በምድራችን የለም – ከዚህ ነጥብ አንጻር ያንተ ቋንቋ የኔም ነው፤ የኔም ላንተ እንዲሁ፡፡ ይህ በቋንቋ ላይ የሚታይ ልዩነት የስሜት ጉዳይ ነው፤ ይህ ነገር ከእውነት ይልቅ ለአስተዳደግ ሥነ ልናቦዊ ጣጣ የሚቀርብ ግን መፍረስ ያለበት ሰው ሠራሽ ድንበር ነው፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያውያን አንድ የጋራ ድልድይ እንደሚያስፈልጋቸው ካመንን በአሁኑ ሁኔታ አማርኛን የሚስተካከል የለምና መረረንም ጎመዘዘንም በዚህ ብንግባባ ይሻለናል – የቋንቋውን የመጀመሪያ ተናጋሪዎች እንርሳቸው፤ ያ አይጠቅመንም/አይጎዳንምም፡፡ ነገ ደግሞ ኦሮምኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ከነገ ወዲያ ጉራግኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚያ ወዲያ ደግሞ ሃዲይኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ የጋራ ቋንቋ አመራረጥ ሂደት የሚወሰነው በማኅበረሰብኣዊ የተፈጥሮ ህግ እንጂ በፖለቲከኞች ፍላጎትም ሆነ በጥላቻና በበቀል ባበዱ ጥቂት ሰዎች አይደለም፡፡ እንደነሱ ቢሆን ኖሮማ የአቦይ ስብሃት ልጅ ይሄኔ ከትግርኛ ውጭ አማርኛንም ሆነ እንግሊዝኛን መናገር ባልቻለ ነበር፡፡ እንደዚያማ ቢሆን ኖሮ ጃዋርና ሕዝቅኤል፣ ኢሣይያስና ዳውድ ኢብሣ አማርኛ አጣርተው መናገር ብቻ ሣይሆን ከአማርኛ አንድ ቃልም ሊያውቁ ባልተጠበቀባቸው ነበር፡፡ “የእኛን ቋንቋ ይህን ያህል ሚሊዮን ሕዝብ እየተናገረው ሲሆን የምሥራቅ አፍሪካ ያ ካልሆነ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቋንቋ መሆን የማይችልበት ምክንያት የለም” ብለው ለሚያምኑና ለሚከራከሩ ወንድሞቼና እህቶቼ የምለው ነገር ቢኖር “ማንደሪን የተባለው የቻይናውያን ቋንቋ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ቻይናዊ እየተናገረው በአሁኑ ወቅት 58 ሚሊዮን እንግሊዛዊ በአፍ መፍቻነት የሚናገረው እንግሊዝኛ  የዓለም ቋንቋ ሊሆን የቻለበት ምክንያት የብዙ ቋንቋዎች ተናጋሪ ሕዝቦችን እንደድልድይ ሆኖ ስላገለገለ ነው፤ በተረፈ ሁሉም ቋንቋዎች እኩል ናቸው” የሚል ነው፡፡ … ነገሩ ወዲህ ነው ምዕመናን – የነገ ሰው ይበለኝና በዚህ ጉዳይ ወደፊት በስፋት እመለስበታለሁ፡፡

 

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

♦ “ ትክክለኛ ፍትሕ አይሰጡም” የተባሉት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ከችሎት እንዲነሱ ተጠየቀ !

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar