www.maledatimes.com በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ውስጥ አደገኛ መርዝ መገኘቱን የፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ውስጥ አደገኛ መርዝ መገኘቱን የፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ

By   /   December 30, 2018  /   Comments Off on በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ውስጥ አደገኛ መርዝ መገኘቱን የፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ

    Print       Email
0 0
Read Time:5 Minute, 27 Second

30 December 2018

ታምሩ ጽጌ

የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጣሪዎች ተቋማትም ተጠያቂ መሆን አለባቸው አሉ

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ውስጥ አደገኛ መርዝ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡ የመርዙን ዓይነትና የጉዳት መጠን በባለሙያ ለማስመርመር እየሠራ መሆኑን በመግለጽ፣ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንደሚያስፈልገውም ገልጿል፡፡

መርማሪ ቡድኑን በመቃወም ተጠርጣሪዎች ለፍርድ ቤቱ በተቋሙ ውስጥ መርዝ እንዳለ የተናገሩት እነሱ መሆናቸውን አስረድተው፣ ይኼንንም ያደረጉት መርዙ አደገኛ በመሆኑ ዜጎች ሳያውቁ ቢነኩት ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል በማለት አስበው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን መርማሪ ቡድኑ ራሱ በምርመራ እንዳገኘው አድርጎ ለፍርድ ቤቱ በማቅረብና በማስረዳት፣ የተጨማሪ ጊዜ መጠየቂያ ማድረጉ ተገቢ አለመሆኑንና ፍርድ ቤቱ ሊቀበለው እንደማይገባ አሳስበዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በማጣሪያ ጥያቄ መርማሪ ቡድኑ መርዙን ያገኘው የፍርድ ቤት መበርበሪያ ትዕዛዝ ወስዶ ባደረገው ብርበራ መሆን አለመሆኑን ሲጠይቀው፣ ‹‹በተጠርጣሪዎቹ ጥቆማ ነው፤›› ብሏል፡፡ 

በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት ተጠርጣሪዎች፣ እነሱ በወንጀል ከተጠረጠሩ ይሠሩባቸው የነበሩ ተቋማትም ስለሚመለከት፣ እነሱም መጠየቅ እንዳለባቸው ለፍርድ ቤት ተናገሩ፡፡

በአቶ ጐሃ አጽብሃ የምርመራ መዝገብ የተካተቱ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስና የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር አባላት የነበሩ 33 ተጠርጣሪዎች ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አሥረኛ ወንጀል ችሎት እንዳስረዱት፣ ተጠርጥራችኋል የተባሉት ሕጋዊ ሆነው ሲሠሩባቸው በነበሩበት ተቋማት ውስጥ በመሆኑ፣ ተቋማቱም ሊጠየቁ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ብቻቸውን ተጠያቂ ሊሆኑ እንደማይገባ ለፍርድ ቤቱ የገለጹት፣ የተጠረጠሩበትን የወንጀል ድርጊት በማጣራት ላይ የሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን፣ ቀደም ብሎ ተፈቅዶለት በነበረው 14 ቀናት ውስጥ የሠራውን የምርመራ ሥራና በቀጣይ ለሚሠራው የምርመራ ሒደት ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን በመጠየቁ ነው፡፡

መርማሪ ቡድኑ በተፈቀደለት 14 ቀናት ውስጥ ምርመራውን ያደረገው፣ ተጠርጣሪዎቹን አራት ቦታ በመለየት መሆኑን ጠቁሟል፡፡ በርካታ ዜጎችን የኦነግና የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባል ናቸው በማለት አፍኖ በመያዝና ዓይናቸውን አስሮ ወደ ድብቅ እስር ቤት በመውሰድ፣ በጨለማ ቤት ውስጥ በማስቀመጥ እስከ አምስት ወራት ድረስ በማቆየት የተለያዩ ማሰቃያ ዘዴዎችን በመጠቀምና በማሰቃየት የአካል ጉዳት፣ ማምከንና ሕይወታቸው እንዲያልፍ ማድረጋቸውን በማስታወስ፣ ድርጊቱ የተፈጸመባቸውን የ51 ምስክሮች ቃል መቀበሉን ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል፡፡ በክልል የሚገኙና በደረሰባቸው ግርፋት ወደ አዲስ አበባ መጥተው የምስክርነታቸውን ቃል መስጠት የማይችሉትን ባሉበት ተገኝቶ የሚቀበል መርማሪ ቡድን በማቋቋም መላኩንም አክሏል፡፡ በደረሰባቸው ድብደባ ሕይወታቸው ያለፈ የሁለት ሰዎች አስከሬን ምርመራ ሁለት ዓይነት ውጤት በመቀመጡ፣ ጥርት ያለ መረጃ ለማግኘት በድጋሚ ጠይቆ እየተጠባበቀ መሆኑንም መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡

ራሳቸው ባቆሟቸው ጠበቆችና መንግሥት በመደበላቸው ተከላካይ ጠበቆች አማካይነት የመርማሪ ቡድኑን የምርመራ ሒደት የተቃወሙት ተጠርጣሪዎቹ፣ መርማሪ ቡድኑ በቡድን ‹‹ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት›› በማለት የመመርመር ሥልጣን የተሰጠውንና ያልተሰጠውን ተቋም ተጠርጣሪ አንድ ላይ መፈረጁ ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ቀደም ብሎ በነበረ ችሎት ማን በምን እንደተጠረጠረና ስንት ምስክሮች እንደመሰከሩበት፣ ስንት እንደቀሩና የተገኙ ማስረጃዎችን ለይቶ እንዲያቀርብ የሰጠውን ትዕዛዝ አለማክበሩን አስረድተዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ በጥቅል ስለሚያቀርብ መከራከር እንዳልቻሉ ጠቁመው፣ ለምን የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ እንዳላከበረ እንዲጠየቅላቸው አሳስበዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ‹‹በተደራጀ መልኩ›› በማለት በጥቅል የሚያቀርበውን መከራከሪያ ሐሳብ በተናጠል እንዲያቀርብ ጠይቀው፣ ከአምስት ወራት በላይ ምርመራ ሲያደርግ እንደነበር ሲገልጽ ከርሞ በየቀጠሮው ተጨማሪ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ መጠየቁ፣ የመንግሥትንም ተዓማኒነት የሚያሳጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የተጠርጣሪውን መብት ማስከበርና ፍትሕ እንዳይጓደል መርማሪ ቡድኑ የተሰጠውን ትዕዛዝ እንዲያከብር ማድረግ እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡

ከሕገ መንግሥቱና ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች አንፃር የእነሱም ሰብዓዊ መብት ሊከበር እንደሚገባ ጠቁመው፣ እንደተያዙ የተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት ሊነገራቸውና ቃላቸውንም መስጠት ሲገባቸው በ48 ቀናት ውስጥ ቃላቸውን ያልሰጡ ተጠርጣሪዎችም እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ የመርማሪ ቡድኑ አባላት የተጠርጣሪዎቹን የወንጀል ተሳትፎ መለየት ያቃታቸው በሁለት ምክንያት መሆኑን ጠቁመው፣ የመለየት ችሎታ ስለሌላቸው ወይም ወንጀል ስለሌለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አንዳንዶቹ ተጠርጣሪዎች እንዳስረዱት፣ በተቋማቸው ውስጥ እየተመሠገኑና ዕድገት እየተሰጣቸው ሥራቸውን በአግባቡ ሲሠሩ ከመቆየታቸው ባለፈ ምንም የፈጸሙት የወንጀል ድርጊት እንደሌለ ተናግረው፣ መርማሪ ቡድኑ 48 ቀናት ካሰራቸው በኋላ አዲስ ወንጀል ፍለጋ አዲስ መርማሪ ቡድን በማዋቀር ወደ ክልል እየላከ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ መግለጹ ተገቢ ካለመሆኑ በተጨማሪ፣ እነሱን ስለማይመለከታቸው የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ውድቅ ተደርጎ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡

አንዳንዶቹ ተጠርጣሪዎች የተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት ተለይቶ ባይነገራቸውም ቃላቸውን መስጠታቸውን፣ ፎቶግራፍ መነሳታቸውንና አሻራ መስጠታቸውን ገልጸው የቀራቸው ነገር ስለሌለ ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ‹‹የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚባል ወንጀል የለም፡፡ በሕግም የተደነገገ አይደለም፡፡ ነገር ግን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽማችኋል ከተባለ በመረጃና በማስረጃ ሊቀርብብን ይገባል፤›› በማለት ፎቶግራፍ ተነሱ መባላቸውንና አሻራ ስጡ መባላቸውን ተቃውመዋል፡፡፡ አሻራና ፎቶ የሚያስፈልገው ወንጀሉን ለመመዝገብ በመሆኑ፣ እነሱ ደግሞ ‹‹በቡድን›› ከማለት ባለፈ በግል የፈጸሙት ወንጀል ተለይቶ እስካልተነገራቸው ድረስ አስፈላጊ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

እያስጠየቃቸው ያለው ሕጋዊ ሆኖ በሚሠራ ተቋም ውስጥ ሲሠሩ በነበረ ድርጊት በመሆኑም፣ ተቋማቱም ሊጠየቁ እንደሚገባ ደጋግመው ተናግረዋል፡፡ የወንጀል ሕግ ዓላማ ማስተማር መሆኑን ተጠርጣሪዎቹ ተናግረው የወንጀል ድርጊት በራሱ የሚመጣ እንጂ በፍለጋ እንደማይገኝ፣ ነገር ግን መርማሪ ቡድኑ ባልተሠራ ወንጀል እነሱን አስሮ ወንጀል ፍለጋ ላይ እንደሆነ በማስረዳት ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል፡፡ ሲሠሩ የኖሩት በመመርያና በደንብ መሆኑን ጠቁመው አንድ ተጠርጣሪ ላይ በምን ያህል ቀናት ምርመራ ተሠርቶ መጠናቀቅ እንዳለበትና ወንጀሉ ከባድ ከሆነም ምን ያህል ጊዜ እንደሚወስድ እንደሚታወቅ በመናገር፣ በእነሱ ላይ ግን እየተንዛዛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የሰው ምስክርነት ከአንድ ማስረጃ ጋር ከተጣረሰ ‹‹ወንጀል የለም ማለት ነው›› በማለት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሟል እየተባለ፣ እነሱም ላይ ባልተጨበጠ የወንጀል ድርጊት ሰብዓዊ መብታቸው እየተጣሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤቱ አቶ ጐሃ አጽብሃን ጨምሮ 16 ተጠርጣሪዎች ያቀረቡትን ተቃውሞና የጠየቁትን ዋስትና ባለመቀበል መርማሪ ቡድኑ የጠየቀውን 14 ቀናት ፈቅዶ፣ ለታኅሳስ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ምክትል ኮማንደር ዓለማየሁ ኃይሉን ጨምሮ 16 ተጠርጣሪዎችም ያቀረቡትን ተቃውሞ በማለፍ መርማሪ ቡድኑ ከጠየው 14 ቀናት ውስጥ አሥር ተጨማሪ የምርመራ ቀናት በመፍቀድ ለታኅሳስ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዙን የሰጠው የምርመራ መዝገቡን አስቀርቦ ከተመለከተ በኋላ ነው፡፡ ከሕፃን ልጇ ጋር ታስራ በምትገኘው ዋና ሳጅን እቴነሽ አረፈዓይኔ ላይ መርማሪ ቡድኑ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቆ የተፈቀደለት ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ መዝገቡን አስቀርቦ ሲመለከተው የተሠራ ምርመራ አለመኖሩን በማረጋገጡ በ30,000 ብር ዋስ እንድትፈታና ከአገር እንዳትወጣ ለኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳዮች ዋና መምርያ እንዲጻፍ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በደኅንነት ተቋም ውስጥ ተገኘ የተባለው መርዝ ከተጠርጣሪዎቹ ጋር የሚያገናኘው ነገር ስለሌለ እንዳልተቀበለው አስታውቋል፡፡

በተመሳሳይ የወንጀል ጥርጣሬ በእስር ላይ የሚገኙት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የዋና ዳይሬክተሩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ነበሩ የተባሉት አቶ መአሾ ኪዳኔና በተቋሙ የስምሪት፣ የአትክልትና የፅዳት ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ሀዱሽ ካሳ ላይም 14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተጠይቆ አሥር ቀናት ተፈቅዷል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ቀደም ብሎ በነበረው ችሎት በተሰጠው ጊዜ የአምስት ሰዎች ምስክርነት ቃል መቀበሉን፣ ኃላፊነታቸውን ከተቋማቸው ጠይቆ መቀበሉን፣ የአቶ ሀዱሽ ባለቤት ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ በንግድ ባንክ ተቀማጭ ብር እንዳላቸው ማረጋገጡንና በተጠርጣሪው ስም የተለያዩ የቤት ሽያጭ ውል ስምምነት ሰነድ ማግኘቱን ተናግሯል፡፡ ተጨማሪ ድብቅ እስር ቤትም ማግኘቱን ገልጿል፡፡ ተጨማሪ የተጎጂ ምስክሮች ቃል መቀበል፣ የሕክምና ማስረጃ ሰነድ ማሰባሰብና የምርመራ ቡድን አቋቁሞ ወደ ክልል ሊልክ መሆኑን አስረድቶ የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ ደንበኞቻቸው የተጠረሩት የኦነግና የግንቦት ሰባት አርበኞች አባል የነበሩ ዜጎችን በማሰርና በማሰቃየት መባሉ በወቅቱ ሕጋዊ አሠራር ነበር፡፡ ምክንያቱም በሕግ አውጪው ምክር ቤት የተወገዙ ድርጅቶች ስለነበሩ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በቡድን እያለ የሚናገረው መርማሪ ቡድኑ ማን ከማን ጋር ተቧድኖ ምን እንደሠራ የገለጸው ስለሌለ ግልጽ አለመሆኑን አክለዋል፡፡ በመሆኑም የወንጀል መነሻ ጥርጣሬ ስለሌለ ምርመራ መጀመር እንደሌለበትም ገልጸዋል፡፡ አቶ ሀዱሽ በባለቤታቸው ስም ገንዘብ ተቀምጧል መባሉ ከተጠቀሱት ሴት ጋር ሕጋዊ የሆነ የጋብቻ ሰነድ ስለሌላቸው፣ እሳቸውን እንደማይመለከትም አስረድተዋል፡፡ እነሱ ከአዲስ አበባ ወጥተው የማያውቁ መሆናቸው እየታወቀ፣ መርማሪ ቡድን በማቋቋም ወደ ክልል እንደሚልክ መናገሩ ተገቢ እንዳልሆነም ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም መርማሪ ቡድኑ የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ውድቅ ተደርጎ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክ ያዳመጠው ፍርድ ቤት የተጠርጣሪዎቹን የመቃወሚያና ዋስትና ጥያቅ ውድቅ በማድረግ ከተጠየቀው 14 ቀናት ውስጥ በአብላጫ ድምፅ አሥር ቀናት በመፍቀድ ለታኅሳስ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 5 years ago on December 30, 2018
  • By:
  • Last Modified: December 30, 2018 @ 1:19 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar