
የአዲስ አበባ ከተማን ቁልፍ ከተረከቡ በኋላ ሪፖርታቸውን ለመጀመርያ ጊዜ ለምክር ቤት ያቀረቡት ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር)፣ በከተማው በ27 ዓመታት ያልተለመዱ አሠራሮች ተግባራዊ መሆናቸውንና ወደፊትም እንደሚቀጥሉ አስታወቁ፡፡
ምክትል ከንቲባው በተለይ በመታወቂያ አሰጣጥ፣ በመኖሪያ ቤት አቅርቦት፣ በመልሶ ማልማት ፕሮግራሞች፣ በገቢ አሰባሰብ፣ በውኃ አቅርቦት፣ በወጣቶችና በአረንጓዴ ልማት ሥራዎች አስተዳደሩ የሚከተለውንና እየተከተለ ያለውን አዳዲስ አሠራሮች በጥልቀት አብርተዋል፡፡
ምክትል ከንቲባው ካቢኔያቸውን ባዋቀሩ ማግሥት ከፍተኛ ቅሬታ ሲያስነሳ የቆየው የመታወቂያ አሰጣጥ ሥርዓት እንደሚለወጥ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ አዲሱ መታወቂያ አሰጣጥ ብሔርን የሚያስቀርና አሻራ የሚጠቀም፣ ከተለመደው ማንዋል ወደ ዲጂታል የሚለወጥ መሆኑን መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡
ሐሙስ ታኅሳስ 25 ቀን 2011 ዓ.ም. በተጠራው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ጉባዔ ላይ እንደተናገሩት፣ በከተማው የተጀመረው የመታወቂያ አሰጣጥ ለውጥ በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚጀመረው ብሔራዊ መታወቂያ (ናሽናል አይዲ) እንደ ሙከራ ፕሮግራም የሚወሰድ ነው፡፡
ከዚህ በዘለለ ምክትል ከንቲባው አዲስ አበባ ላይ ተወልደው፣ አድገው፣ ወይም ለረዥም ዓመታት ኖረው፣ ነገር ግን መታወቂያ ሊያገኙ የሚችሉበት ዕድል ለጠበበባቸው ዜጎች መፍትሔ እንደሚሰጥ፣ አንድ ገጠመኛቸውን በማንሳት ለምክር ቤት አብራርተዋል፡፡
ምክትል ከንቲባው እንዳሉት፣ አንዲት ወጣት ሴት በመሀል አዲስ አበባ ለ20 ዓመታት ኖራለች፡፡ ነገር ግን በመልሶ ማልማት ከቤተሰቧ ጋር ስትፈናቀል ቤተሰቧ ሌላ ቦታ ተጓዘ፡፡ እሷ ደግሞ ባል አግብታ፣ ልጅ ከወለደች በኋላ ባሏ ጋር ተፋታች፡፡
በዚህ ምክንያት ድህነት ላይ ወድቃ፣ በመቃብር ሥፍራ ላስቲክ ወጥራ ኑሮዋን ትገፋለች፡፡ የከተማው አስተዳደር የሴፍቲኔት ፕሮግራም በጀመረበት ወቅት ይህች ሴት አገልግሎቱን ለማግኘት ብትቀርብም መታወቂያ የላትም፡፡ መታወቂያ ስለሌላት ብቻ በኖረችበት ከተማ ባይተዋር ሆና ተቀምጣለች ሲሉ ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል፡፡
‹‹ለመታወቂያ ቤት ያስፈልጋል፣ ይቺ ሴት ቤት ከየት ታምጣ? ቤቱን በመልሶ ማልማት ያፈረስንባት እኛው ነን፣ ይህ መስተካክል አለበት፤›› ብለው፣ ‹‹ተመሳሳይ ችግር የገጠማቸውን ዜጎች የመታወቂያ ችግር ለመፍታት አስተዳደሩ ዕርምጃዎችን እየወሰደ ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ውጪ የከተማ አስተዳደሩ አሠልፎ መታወቂያ እያደለ ነው የሚባለው ወሬ መሠረተ ቢስ ነው ብለዋል፡፡ አስተዳደሩ ሌላው የተከተለው አዲስ አሠራር በመኖሪያ ቤት አቅርቦት መስክ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አስተዳደሩ የ20/80 ፕሮግራምና ለኪራይ አገልግሎት የሚውሉ 95,832 ቤቶች፣ እንዲሁም 38,240 ያህል የ40/60 ቤቶችን እየገነባ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በከተማው ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ እነዚህን ቤቶች በአንድ ጊዜ በተያዘው በጀት ለባለ ዕድለኞች እንደሚያስረክብ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ወደፊት ስለሚገነቡ ቤቶች ሲያብራሩ በዚህ ዓመት የቤቶች ግንባታ አለመካሄዱን፣ ምክንያቱ ግንባታ ታስቦ የነበረው በማስፋፊያ ቦታዎች እንደመሆኑ ከአርሶ አደሮችና ከኦሮሚያ ክልል ጋር በግልጽ በመነጋገር መግባባት ላይ መድረስ ማስፈለጉን ተናግረዋል፡፡
‹‹እንደ ከዚህ ቀደሙ ዘለን የምንቆፍርበት አሠራር ከዚህ በኋላ የለም፣ በግልጽ ከክልሉና ከአርሶ አደሩ ጋር መነጋገር ይኖርብናል፤›› በማለት የገለጹት ምክትል ከንቲባው፣ ‹‹በኮዬ ፊጬና በአካባቢው የተገነቡ ቤቶችን ለማስተላለፍ የተቸገርንበት ምክንያቱም ይኼው ነው፣ አለመግባባት ፈጥሯል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ከዚህ በኋላም የቤቶች ግንባታ የሚካሄደው በማስፋፊያ ቦታዎች ሳይሆን፣ በመሀል ከተማ በሚገኙ ቦታዎች ላይ ሰዎችን ሳያፈናቅል እንደሚካሄድ አስታውቀዋል፡፡ የቤት ልማቱም በተለይ የተገቡት ቤቶች ከተላለፉ በኋላ፣ ተመዝግበው ለሚጠባበቁ ነዋሪዎች አዲስ አሠራር መዘርጋቱን ምክትል ከንቲባው አስረድተዋል፡፡ በዚህ መሠረት ራሳቸው መገንባት ለሚችሉ ነዋሪዎች መሬት የሚቀርብ መሆኑን፣ በሚሰጣቸው ቦታ ላይ ራሳቸው ለመገንባት ለማይችሉ ደግሞ አስተዳደሩ እንደሚገነባላቸው አብራርተዋል፡፡
ምክትል ከንቲባው ከዚህ ባለፈ በመልሶ ማልማት ፕሮግራም እንደ ከዚህ ቀደም ነዋሪዎችን አፈናቅሎና ማኅበራዊ ሕይወታቸውን አናግቶ የሚከናወን ግንባታ እንደማይኖር አብራርተዋል፡፡
የትኛውም ግንባታ ሲካሄድ በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎችን አካቶ በሚመጣው ትምህርት ቤትና ሆስፒታል ተጠቃሚ እንደሚሆኑ፣ በሚፈጠረው የሥራ ዕድልም ነዋሪዎች ተቋዳሽ መሆን አለባቸው ብለዋል፡፡ መልሶ የሚለማው ሕንፃ ብቻ ሳይሆን፣ ሰውም መሆን አለበት ሲሉም የአስተዳደራቸውን አቋም አስታውቀዋል፡፡
ሌላው አወዛጋቢ ሆኖ የቆየው የከተማው ገቢ አሰባሰብ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ደረጃ ትልቁ የገበያ ሥፍራ መርካቶ፣ ከፍተኛ ገንዘብ ይንቀሳቀስበታል በሚል እሳቤ በነጋዴዎች ላይ ከአቅም በላይ ታክስ እንደሚጫን ይነገራል፡፡
ይህ ክስተት አወዛጋቢ ሆኖ የቆየ ቢሆንም ምክትል ከንቲባው ከዚህ ቀደም የነበረውን አስተሳሰብ በመተው፣ በቴክኖሎጂና በአቅም ላይ ብቻ የተወሰነ የታክስ ሪፎርም እንደሚካሄድ አስታውቀዋል፡፡
አስተዳደሩ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት 20.7 ቢሊዮን ብር የመሰብሰብ ዕቅድ አውጥቶ፣ አፈጻጸሙ 18.8 ቢሊዮን ብር ሆኗል፡፡ ይህ ገቢ ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር 3.1 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ተገልጿል፡፡
ምክትል ከንቲባው ይኼ ገቢ ከተማው ከሚያመነጨው ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ መሆኑን ጠቁመው፣ በትክክል መክፈል ያለባቸው እየከፈሉ አይደሉም ብለዋል፡፡ መጠነኛ መክፈል ያለባቸው ደግሞ ከፍተኛ ታክስ እንደተጫነባቸውና ይህም አሠራር መስተካከል እንደሚኖርበት ገልጸዋል፡፡
በውኃ አቅርቦት ላይ የተነሳው ነጥብ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አብዛኛውን ውኃ የሚያገኘው ከኦሮሚያ አጎራባች አካባቢዎች ነው፡፡ ነገር ግን ለዓመታት የኦሮሚያ አካባቢዎች አዲስ አበባን እያጠጡ እነሱ ግን ለውኃ ችግር ተጋልጠው መቆየታቸው፣ ባለፉት ከንቲባዎች ጊዜያት የኦሮሚያ ከተሞችን ውኃ ለማጠጣት የተጀመሩ ሥራዎች ቢኖሩም ያን ያህል ጎልተው የወጡ አለመሆናቸው በስፋት ይነገራል፡፡
ከዚህ በኋላ አስተዳደሩ በኦሮሚያ አጎራባች ከተሞች ጋር በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የሚሠራ መሆኑን፣ ውኃ ብቻም ሳይሆን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚም እንዲሆኑም ጭምር እንደሚሠራ ተመልክቷል፡፡
የአስተዳደሩ ሌላኛው ትኩረት አረንጓዴ ቦታዎች፣ የወጣቶች ሥራ ዕድልና የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን ማልማት ነው፡፡ ምክትል ከንቲባው እንደተናገሩት፣ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ከዚህም በላይ ያስፈልጋቸዋል በማለት ምሳሌ በመጥቀስ አስረድተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ሁለት ትልልቅ የእግር ኳስ ክለቦች እንዳሉ ጠቁመው፣ እነሱም ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና ናቸው ብለዋል፡፡ ‹‹እነዚህን ክለቦች አናውቃቸውም፣ ወጣቶች ከቡድናቸው ጋር ወደ ክልል ከተሞች ሲሄዱ አንደግፋቸውም፣ ይህ ሊሆን አይገባም፤›› ብለዋል፡፡
በከተማው ውስጥ ያሉ ወጣቶችን የሥራ ዕድል ለመፍጠር ተዘዋዋሪ ፈንድ እንደሚቋቋም የተናገሩት ምክትል ከንቲባው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የጀመሩት የዳያስፖራ የአንድ ዶላር አስተዋጽኦን፣ የከተማው አስተዳደር ደግሞ በኢትዮጵያ ብር ለመጀመር አስቧል ብለዋል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓመት ከ450 ሺሕ እስከ 500 ሺሕ የጉዞ ቲኬቶች ይሸጣል፡፡ ከአንድ ቲኬት አንድ ብር ቢታሰብ 450 ሚሊዮን ብር ይገኛል፤›› በማለት፣ ቀጣዩን አቅጣጫ አመላክተው ተቋማት ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
በአጠቃላይ ምክትል ከንቲባው እንዳሉት በአገሪቱ የተጀመረው የፖለቲካ ሪፎርም በሁለት እግሩ እንዲቆም፣ የኢኮኖሚ ሪፎርሙ በጥልቀት መሬት መያዝ አለበት፡፡
የዜጎች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሕይወት መለወጥም ይኖርበታል ያሉት ምክትል ከንቲባው፣ አዲሱ አስተዳደር ከማዕከል እስከ ወረዳ ድረስ የተለያየ የአቅም ደረጃ ባላቸው አመራሮች የተገነባ ስለሆነ ለውጡን ለማምጣት ቁርጠኛ ነው ብለዋል፡፡
የከተማው ምክር ቤት አባላትና የከተማው ነዋሪዎች የበለጠ ለመሥራት ከአስተዳደሩ ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
Average Rating