www.maledatimes.com በአዲስ አበባ የተበራከቱት የዕርቃን ዳንስ ቤቶች - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

በአዲስ አበባ የተበራከቱት የዕርቃን ዳንስ ቤቶች

By   /   January 26, 2019  /   Comments Off on በአዲስ አበባ የተበራከቱት የዕርቃን ዳንስ ቤቶች

    Print       Email
0 0
Read Time:10 Minute, 40 Second

2019-01-23Author: ሳምሶን ብርሃኔ

የወሲብ ንግድ በቀጥታ በሕግ ባይከለከልም፣ የወሲብ ንግድ ሠራተኞችን በድርጅት ደረጃ ማቅረብ ግን በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 634 ተከልክሏል። ይሁን እንጂ ቡና ቤቶች በአስተናጋጅነት ሥም፣ የዕርቃን ዳንስ ቤቶች ደግሞ በዳንሰኝነት ሥም የወሲብ ንግድ ሥራ ላይ የተሠማሩ ሴቶችን ቀጥረው ለደንበኞቻቸው የሚያቀርቡበት አሠራር በኢትዮጵያ በተለይም በመዲናዋ አዲስ አበባ የተለመደ ሆኗል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የዕርቃን ዳንስ ቤቶች እንደአሸን እየፈሉ የከተማው የምሽት “ባሕል” አካል እየሆኑ እንደሆነ በርካታ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይሁን እንጂ መንግሥት የሕግ ማስፈፀም ኃላፊነቱን ወስዶ እነዚህን የወሲብ ንግድ ሠራተኞችን የሚያቀርቡ ተቋማትን ለማስቆም የሞከረበት አጋጣሚ እምብዛም አይታወቅም። የጉዳዩን አንገብጋቢነት በመንተራስ የአዲስ ማለዳው ሳምሶን ብርሃኔ በአዲስ አበባ የሚገኙ የዕርቃን ዳንስ ቤቶችን በድብቅ በመጎብኘት የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎ አቅርቦታል።

ቦታው አውራሪስ ሆቴል አካባቢ፥ ቀኑ ሰኞ፣ ጥር 6 ከሌሊቱ ወደ ሰባት ሰዓት ገደማ ይሆናል።
ከበሩ በላይ ዕርቃናቸውን የሆኑ ሴቶች ምስል ያለበት መጠጥ ቤት ውስጥ አጫጭር ቀሚስ የለበሱ ስድስት ሴቶች ተቀምጠዋል። ምናልባትም ከዚህ በፊት ተገኝቶ ለማያውቅ ሰው፤ መጀመሪያ ገባ ተብሎ ሲታይ፥ በከተማው ሌላ አካባቢዎች ከሚገኙት መጠጥ ቤቶች ምንም የተለየ ላይመስለው ይችላል።
በርግጥ፣ ጠባቂም ሆነ መታወቂያ የሚጠይቁ ሠራተኞች በር ላይ ካለመኖሩ ጋር ተዳምሮ ከውጭ ለሚያዩት ቤቱ ምንም ልዩነት የሌለው ያስመስለዋል።
ይሁን እንጂ፣ የመጠጥ ቤቱን ልዩነት ለመረዳት ሁለት ደቂቃ ከበቂ በላይ ነው።
ከወጣት እስከ ጎልማሳ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ሰዎች በከፊል ዕርቃናቸውን ከሆኑ እንስቶች ጋር ሲደንሱ፣ ሙዚቃ በተቀየረ ቁጥር ወደ ኪሳቸው ገባ የሚሉ ተጠቃሚዎችን፣ በየ15 ደቂቃ ልዩነት መልኩ እና ጣዕሙ ለውሃ የቀረበ ቮድካ የሚያስቀዱ በወሲብ ንግድ ላይ የተሠማሩ ሴቶችን ለተመለከተ ሰው በርግጥም ቦታው የራቁት ጭፈራ ቤት መሆኑ ግልጽ ነው።
በ200 ሜትር ዙሪያ ውስጥ ተመሳሳይ ዘርፍ ላይ የተሠማሩ ከደርዘን በላይ ቤቶች መገኘታቸውን ለተገነዘበ ሰው፥ በርግጥም ከዛሬ ዐሥር ዓመት በፊት እንዲህ ዓይነት ቤቶችን ማግኘት አዳጋች በሆነባት አዲስ አበባ፣ ዛሬ እየተላመደችው መምጣቷን የበለጠ ግልጽ ያደርገዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም።
በቅርቡ የበረከቱትን የራቁት ጭፈራ ቤቶች በቦሌ ክፍለ ከተማ ብቻ ከሁለት ደርዘን በላይ ገደማ ሲሆኑ፥ አዲስ ማለዳ ባደረገችው የስውር ዳሰሳ ዓይነታቸው ለሁለት ከፍሎ ማየት እንደሚቻል ተረድታለች።
አንዳንዶቹ፣ ሰፊ የሆነ የመደነሻ ወለል፣ ቪ.አይ.ፒ. (የመክፈል አቅማቸው ከፍ ላሉ ሰዎች የተከለሉ) ክፍሎች ያሏቸው እና ንፅሕናቸው በአንፃሩ የተሻለ የሆኑ መኝታ ክፍሎች አሏቸው። ለአብነትም ያህል፣ ከኢምፔሪያል ሆቴል 100 ሜትር ከፍ ብሎ የሚገኘው ‘ቼኮሌት ወርልድ’ የምሽት ክለብን መጥቀስ ይቻላል።
በግምት 100 ካሬ ሜትር የሚሸፍነው ክለቡ፣ አዲስ ማለዳ ባለፈው ሰኞ (ጥር 6፣ 2011) ድንገተኛ ዳሰሳ ባደረገችበት ወቅት በውስጡ ወደ ስምንት በከፊል ራቁት የሆኑ ሴት ጨፋሪዎች እንደነበሩ ማየት ተችሏል።
የመጠጥ ዋጋውም ከ200 ብር አንስቶ እስከ 3600 ብር የሚደርስ ሲሆን፥ በውስጡ የሚገኙ ተስተናጋጆች የመግዛት አቅማቸው ከፍ ያለ መሆኑን ከሚያዙት መጠጥ እና ለዳንሰኞች ከሚሸልሙት ገንዘብ መረዳት ቀላል ነው።
ተመሳሳይ ዓይነት ቤቶች ቦሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሚያስገነባው ሆቴል ጀርባ፥ ከቃተኛ ምግብ ቤት አጠገብ ‘ኬቭ’ የሚባል የምሽት ክለብ የሚገኝ ሲሆን፥ አዲስ ማለዳ በደረሳት ጥቆማ በአትላስ ሆቴል አካባቢ ተቀራራቢ አገልግሎት የሚሰጥ ‘ኮድ’ ተብሎ የሚጠራ የምሽት ክለብ እንዳለም ማወቅ ተችሏል።
እንደዚህ ዓይነት ዕርቃን ዳንስ ቤቶች ውስጥ፣ ገበያ ሞቅ በሚልበት ወቅት ተጠቃሚዎች ለሚያገኙት የወሲብ ሽያጭ አገልግሎት እስከ 12 ሺሕ ብር በነፍስ ወከፍ ለአገልግሎቶቹ እንደሚከፈል ለመረዳት ተችሏል። ዋጋው ከአካባቢ አባባቢ ይለያይ እንጂ በአማካይ አንዲት በወሲብ ንግድ ላይ የተሠማራች ሴት ለአጭር ጊዜ የወሲብ አገልግሎት ከ1 ሺሕ እስከ 3 ሺሕ 500 ብር ስትጠይቅ፣ ለተመሳሳይ አገልግሎት ለአዳር በአማካኝ ከ2 ሺሕ 500 እስከ 6 ሺሕ ብር እንደምትጠይቅ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ተጠቃሚዎች ይናገራሉ።
በአንፃሩ፣ በተለምዶ ሃያ ኹለት አካባቢ አውራሪስ ሆቴል አካባቢ የሚገኙት መጠጥ ቤቶች፣ የሚያገኙት ገቢም ሆነ የሚያስከፍሉት ገንዘብ ያነሰ ሲሆን፥ የቤቶቹ ይዘት ለየት ያለ ነው። ብዙዎቹ አንድ የመኝታ ክፍል ያላቸው ሲሆን፣ ንፅሕናውም እምብዛም ነው።
የመጠጥ ዋጋቸውም 50 ብር ከሚሸጠው ቢራ አንስቶ አንድ ሙሉ ጠርሙስ ቮድካ እና ውስኪ እስከ 3000 ብር ይሸጥባቸዋል። የቤቶቹ ተጠቃሚዎችም አነስተኛ ገቢ ከሚያገኙ እስከ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች ድረስ ናቸው። በእንደዚህ ዓይነት ቤቶች፣ ወንበር ወይም ሶፋ ላይ ልቅ የሆነ ወሲብ የሚፈፅሙ ሰዎችን በብዛት ማግኘት እንግዳ ላይሆን ይችላል። በነፍስ ወከፍ አንድ ሰው በአማካይ ወደ 600 ብር በእነዚህ ዓይነት የእርቃን ዳንስ ቤቶች ለመዝናናት እንደሚያወጣ ተጠቃሚዎች ይናገራሉ።
ይሁን እንጂ የራቁት ጭፈራ ቤቶቹ በጥራት እና በዓይነት መለያየት ሳይሆን መብዛታቸው በአገሪቷ የሚያሳድረው ተፅዕኖ የከፋ መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል። ይበልጥኑ ሴቶቹ በእንደዚህ ዓይነት ተግባራት ላይ መሠማራታቸው ለአባላዘር በሽታዎች የበለጠ እንዲጋለጡ እንደሚያደርጋቸው ጥናቶች ያሳያሉ። በ2010 ይፋ በተደረገ የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ጥናት 25 በመቶ የሚሆኑት ሴተኛ አዳሪዎች በደማቸው የኤችአይቪ ቫይረስ አለባቸው። ይባስ ብሎም፣ በአፍ የሚፈፀም የወሲብ ድርጊት የራቁት ጭፈራ ቤቶች ውስጥ ከመብዛታቸው ጋር ተያይዞም ተጋላጭነታቸው ከፍ እንደሚል ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የወሲብ ንግድ ላይ የተሠማሩ ሴቶች ቁጥር መጨመር
የታሪክ መጻሕፍት እንደሚያሳዩት፣ የወሲብ ንግድ ከተሜነት በተስፋፋባቸው አካባቢዎች የተጀመረ ሲሆን በተለይም የንጉሣዊ ቤተሰቦችና ወታደሮች በሚኖሩባቸው ከተሞች በስፋት ይታዩ ነበር።
የአዲስ አበባ የጤና ቢሮ ባሳተመው ጥናት መሠረት አጀማመሩም በኢትዮጵያ የተለየ አይደለም። የተረጋገጠ መረጃ ባይኖርም፣ በኢትዮጵያ የወሲብ ንግድ አጀማመር ከነገሥታት እና የጦር መሪዎች ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ ይነሳል። ለአብነትም በጐንደር፣ በአክሱም፣ በላሊበላና በሌሎችም የአገሪቱ ነገሥታት መገኛ በሆኑ ከተሞች በወሲብ ንግድ ላይ የተሠማሩ ሴቶች በስፋት እንደነበሩ ይነገራል። ይሁን እንጂ ዓይነቱ አሁን ከተለመደው የወሲብ ንግድ ጋር አይመሳሰልም። ይልቁንም ቀድሞ የነበረው የወሲብ ንግድ በቅምጥነት፣ በጭን ገረድነት ሥም የሚደረግ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያመላክታሉ።
በመሆኑም፣ የወሲብ ንግድ በኅብረተሰቡ ዘንድ በእጅጉ የተወገዘ ተግባር በመሆኑ በአደባባይ የሚደረግ አልነበረም። በዚህም የተነሳ፣ ነገሮች የሚካሔዱትም ሰው ሳያውቅ በድብቅ ነበር። ይህ ግን ከአዲስ አበባ መቆርቆር በኋላ ሊቀጥል አልቻለም፤ በተለይም ደግሞ የኢትዮ-ጂቡቲ የባቡር ግንባታ እና የአምስት ዓመቱን የጣሊያን ወረራ ተከትሎ፣ በተለይም በርካታ ቤተሰቦች መበተናቸው እና ደጋፊ የሌላቸው ሴቶች ወደ ወሲብ ንግድ መሠማራታቸው የወሲብ ንግድ የአደባባይ ልምድ ሆኖ እንዲቀር አድርጎታል።
ከዚያ ወዲህ፣ መጀመሪያ በከተሞች የጠላ እና አረቄ መሸጫ ቤቶች መጨመር ከምሽት ጭፈራ ቤቶች መብዛት ጋር ተደማምሮ፣ በአስተናጋጅነት የሚሠሩ ሴቶች መጨመር ለወሲብ ንግድ መስፋፋት እንደ ምክንያት ይገለጻል። [ለአስተናጋጅነት የተሰጠው ‘ኮማሪነት’ የሚለው ሥያሜም ከማስተናገድ በተጨማሪ የወሲብ ንግድ ላይ የተሠማሩ እንደሆነ እንደሚያመለክት ብዙዎች ይስማሙበታል።]
በ1950 እና 1960ዎቹ ገደማ ውስጥ ደግሞ የሆቴሎች፣ ቡና ቤቶች፣ ሬስቶራንቶች እና ሌሎች ምግቦች እና የመጠጥ አቅራቢ ተቋማት በመጨመራቸው የሴተኛ አዳሪዎች ብዛት በከፍተኛ ቁጥር አድጓል።
በተለምዶ “ውቤ በረሃ” ተብሎ የሚጠራው የደጃች ውቤ መኖሪያ (‘አራዳ ጊዮርጊስ’) አካባቢ እና ካዛንቺስ አካባቢ በተስፋፉ ቡና ቤቶች ውስጥ፣ ሴተኛ አዳሪዎች በብዛት የሚገኙባቸው አካባቢዎች ነበሩ። ኮማሪቶች፣ በዕድሜ ምክንያት ከገበያ የሚወጡ ሴቶችና ደላሎች የገበያው አካል ነበሩ። ከዚያም ከ1990ዎቹ አንስቶ፣ የወሲብ ንግዱ መስፋፋት የ‘ላዳ’ ታክሲ ሾፌሮችን፣ ደላሎችን፣ ሆቴሎችን፣ የእንግዳ ማረፊያ ቤቶችን እና አስጐብኚዎችን ማካተት ችሏል።
በዚህም የተነሳ፣ በወሲብ ንግድ ላይ የተሠማሩ ሴቶች ቁጥር አሻቅቧል። በዚህም ሳይወሰን፣ ፊቱን የበለጠ በመቀየር፣ በመጠጥ ቤቶች እና በሌሎች ሥፍራዎች ይዘወተር የነበረው የወሲብ ንግድ፣ በመንገድ ላይ ይበልጥ ሊጨምር ችሏል።
ለአብነትም፣ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት በኋላ እንደ ፒያሳና ሃያ ኹለት መንገድ የሚሞሉትን በወሲብ ንግድ ላይ የተሠማሩ ሴቶችን መውሰድ ይቻላል። በቅርቡ ደግሞ፣ በገንዘብ አቅማቸው የተሻሉ ሰዎችን የሚያስተናግዱት የዕርቃን ዳንስ ቤቶችና ማሳጅ ቤቶች አዲሱ የሴተኛ አዳሪነት ገጽታ ሆነዋል።
ራቁት ጭፈራ መቼ ተጀመረ?
የፆታ ስሜት የሚንፀባረቅባቸው የዳንስ ዓይነቶች መነሻዎችን በእርግጠኝነት ማወቅ አይቻልም። በዓለማችን፣ በገንዘብ ክፍያም ይሁን በሌላ መንገድ የዕርቃን ዳንስ አገልግሎት ማግኘት እንዳሁኑ በተደራጀ ሁኔታ ባይቀርብም፣ ከዛሬ ሁለት ሺሕ ዓመታት በፊት ጀምሮ እንደነበር በታሪክ ድርሳናት ውስጥ ተዘግቦ ይገኛል።
በተለይም በምሥራቁ የዓለም ክፍል ለብዙ ምዕተ ዓመታት ይዘወተር እንደ ነበር የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ። ይሁን እንጂ በ19 ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ ነበር ‘ስቲሪፕቲዝ’ የተባለው የዕርቃን ዳንስ ዘመናዊ መዝናኛ ሆኖ ብቅ ያለው።
በተለይም በፈረንሳይ እንደ ሙሊን ሩዥ እና ፎሊስ በርጀር የመሳሰሉ ትዕይንቶች ለዚህ ዓይነቱ መዝናኛ መዛመት ምክንያት መሆናቸውን ቫኔሳ ፊሸር የተባለችው የፆታ እና የሥርዓተ ፆታ ባለሙያ ከዛሬ ኹለት ዓመት በፊት ያደረገችው ጥናት ያሳያል።
ይህ ዓይነቱ የመዝናኛ ዘርፍ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከተጀመረ ኹለት ሺሕ ዓመታት ቢያልፉትም፥ በኢትዮጵያ ግን የ20 ዓመታት ዕድሜ እንኳን እንዳልሆነው ማስረጃዎች ያሳያሉ።
ይህ ዓይነቱ መዝናኛ አገልግሎትን ለመጀመሪያ ጊዜ የዛሬ ዐሥር ዓመት ገደማ በአዲስ አበባ በማቅረብ ሁሌም ሥሙ የሚነሳው ሰሜን ሆቴል አካባቢ ይገኝ የነበረው አሮሰ ሆቴል ነበር።
በይበልጥ ደግሞ በ2004፣ የአዲስ አበባ ሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ከሌሎች ከሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር ባደረገው ጥናት በከተማው አራት ክፍለ ከተሞች ላይ የሚገኙ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ የቀንና የማታ ጭፈራ ቤቶችን ለመመልከት የበቃ መሆኑን ጥናቱ ያሳያል።
ከዚያም በኋላ፣ በከተማው መስተዳደር በተወሰደ እርምጃ ቁጥሩ በከፍተኛ ሁኔታ ቢቀነስም፣ አሁን ላይ ግን በማንሠራራት ላይ እንዳለ መረጃዎች ያሳያሉ።
ሴተኛ አዳሪነትና የዕርቃን ዳንስ ቤቶች ቁጥር ለምን ጨመረ?
የዓለም የሥራ ድርጅት ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ በግምት ወደ 50 ሚሊዮን ገደማ ሴቶች በወሲብ ንግድ ላይ ተሠማርተው ይገኛሉ። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ድኽነት በከፋባቸው አገራት ደግሞ የሴተኛ አዳሪዎች ቁጥር ከፍ ያለ እንደሚሆን በተለያዩ ጊዜያት በድርጅቱ የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ።
በርግጥ ከዓለም አምስት ድኽነት ከከፋባቸው አገራት ተርታ የምትመደበው ኢትዮጵያ፥ እንደ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ጥናት የአንድ ሰው ትንሹ የቀን ገቢ 20 ብር ቢሆን ይበቃል በሚል በተሰላ ስሌት ወደ 23.6 በመቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ከድኽነት ወለል በታች ናቸው።
በተቃራኒው፣ የዛሬ ዓመት ዓለማየሁ ገዳ (ዶ/ር) በተባሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያ፣ በዓለም ዐቀፍ መሥፈርት መሠረት ዝቅተኛ የቀን ገቢን 33.3 ብር በማድረግ በተሠራ ሌላ ጥናት ከድኽነት ወለል በታች ያሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከ70 በመቶ በላይ ይሆናሉ ተብሏል።
ይሁን እንጂ፣ ቁጥሩ ይብዛም ይነስ አንድ ሁሉም የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች የሚሥማሙበት ነገር ቢኖር ድኽነት እና ሴተኛ አዳሪነት ያላቸውን ቀጥተኛ ግንኙነት ነው። ‘እልልታ ውመን አት ሪስክ’ የተባለው አገር በቀል የዕርዳታ ድርጅት ዳይሬክተር የሆነው ነብዩ ኃይሌ ለዚህ ምስክር ነው።
ድርጀቱ ከተመሠረተ ወደ 23 ዓመታት እንዳለፈውና እስከ ዛሬ ከ1200 በላይ ሴተኛ አዳሪዎችን ሕይወት እንደለወጠ ያስታወሰው ነብዩ፣ ድኽነት ለወሲብ ንግድ መስፋፋት ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ይገልጻል።
“በተለይም ብዙዎቹ ሙያ የሌላቸውና የትምህርት ደረጃቸው አነስተኛ መሆኑ ጋር ተያይዞ፥ ኑሯቸውን ለማሻሻልና በትንሽ ጊዜ ውስጥ ብዙ ገንዘብ ለመሰብሰብ ያላቸው አማራጭ የወሲብ ንግድን ብቻ አድርጎ የማሰብ ችግር እንዳለ” ነብዩ ያነሳል።
በርግጥ፣ ይህ ዓይነቱ መስተጋብር በሌሎች አገራትም ቢሆን የተለመደ ነው። በኬኒያ ከፍተኛ ድኽነት ያለባቸው ከተሞች ባሎች ሴቶቻቸውን በወሲብ ንግድ ላይ እንዲሠማሩ እንዲፈቅዱ እስከመገደድ መድረሳቸውን መጋቢት 2010 የወጣ መረጃ ያሳያል።
እንዲህ ዓይነቱ ነገር በኢትዮጵያ ይኑር ወይም አይኑር ማረጋገጥ ባይቻልም፥ ብዙ ሴቶች፣ በተለይም ቀደም ብለው በቤት ሠራተኝነት የተሠማሩ ሴቶች ‘የወሲብ ንግድ ነጻነት ይሰጣል፤ እንዲሁም የተሻለ ገንዘብ አግኝቶ ሕይወት ለመቀየር ወሳኝ ነው’ በሚል ምክር ተታልለው ችግር ውስጥ እንደሚገቡ ባለሙያዎች ያስረዳሉ። ለዚህም የአቻ ጓደኛ ግፊት ከፍተኛ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ።
ነገር ግን ለማኅበራዊ ሥራ ባለሙያው መሰለ መንግሥተአብ (ዶ/ር) ከዚህ ባሻገር፣ መዋቅራዊ ባሕላዊ ልማዶች ለወሲብ ንግድ ሠራተኞች መጨመር እንደ ምክንያት ይገልጻሉ። ሴቶች በተለይም በሀብት ባለቤትነት ላይ ካላቸው አነስተኛ ድርሻ ጋር ተያይዞ ብዙ ንብረቶች በወንዶች በመያዙ፣ ሌላ የሕይወት አማራጮቹን እንዲሞክሩ አስገድዷቸዋል።
በርግጥ፣ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ከኹለት ወራት በፊት ባወጣው የኢትዮጵያ ሰብኣዊ ልማት ሪፖርት ሴቶች ሥራ ያለመቀጠር (የማጣት) ዕድላቸው ከወንዶች በሦስት ዕጥፍ ያህል ሊበልጥ እንደሚችል ገልጿል።
ይህ በግልጽ ሲቀመጥ፣ የሴቶች የነፍስ ወከፍ ጥቅል አገራዊ ገቢ ከወንዶቹ 1,886 ዶላር ጋር ሲነፃፀር 1,161 ዶላር ላይ ይገኛል። ይህ ሁኔታ ሴቶች መሠረታዊ የሠራተኛ መብቶቻቸውን ሊያስከብሩላቸው በማይችሉና እንደ ወሲብ ንግድ ዓይነት ሥራዎች ላይ እንዲሠማሩ ተጋላጭ ያደርጋቸዋል ሲል ሪፖርቱ ያሳያል።
ይሁንና፣ እነዚህ ምክንያቶች ለሁሉም የወሲብ ንግድ ዓይነቶች ይሠራሉ ማለት አይቻልም። የዶክትሬት ጥናታቸውን በሴተኛ አዳሪዎች ሕይወት ዙሪያ የሠሩት መሰለ ይህንን ሐሳብ ይጋራሉ።
ባለሙያው እንደሚያስረዱት፣ በመንገድና በትናንሽ መጠጥ ቤቶች የሚሠሩ ሴቶች በብዛት ከፍተኛ ድኽነት ካለበት አካባቢ የመጡ ሲሆን፣ እንደ ማሳጅ እና ዕርቃን ዳንስ ቤቶች ያሉ የጭፈራ ክለቦች ውስጥ የሚሠሩ እና የወሲብ ንግድ ላይ የተሠማሩት ሴቶች ደግሞ ከከተማ የመጡ እና ኑሯቸውም በአንፃሩ የተሻለ ነው።
በተለይም የዕርቃን ዳንስ ቤቶች ውስጥ የሚሠሩ ሴቶች የሚያስገባውን የበለጠ ገቢ ለማግኘት እንደ መደበኛ የሥራ መደብ ሊቆጥሩት እንደሚችሉ እና አንዳንዴም የትርፍ ጊዜ ሥራ ተደርጎ እንደሚወሰድ የጥናት ባለሙያው ገልጸዋል። ይህ በኢትዮጵያ እስከ 20 በመቶ ይደርሳል ተብሎ ከሚገመተው ሥራ አጥነት ጋር ተዳምሮ ሴቶችን በእንደዚህ ዓይነት አስከፊ የሥራ ገበታ ሕይወታቸውን እንዲመሩ እንዳስገደዳቸው ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
የወሲብ ንግድ ሕጋዊነት?
በኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ መሠረት ማንም ሰው ለጥቅም ሲል ወይም የሌላውን ሰው ፍተወተ ሥጋ ለማርካት በፍቃዳቸውም ቢሆን በዝሙት ኣዳሪነት እንዲሠማሩ በማነሳሳት፣ በማባባል፣ በማቅረብ ወይም በማንኛውም ዘዴ በመገፋፋት ሴቶችን በማቃጠር የነገደ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት እና 10000 ብር ድረስ ይቀጣል። ይሁን እንጂ በወሲብ ንግድ ላይ መሠማራት በሕግ አልተከለከለም።
የወሲብ ንግድ በሕግ ባይከለከልም ቅሉ፣ የወሲብ ንግድ ሠራተኞችን መቅጠር በሕግ የተከለከለ በመሆኑ የወሲብ ነጋዴዎችን የሚያቀርቡ የንግድ ድርጅቶች ሕጋዊ ቅቡልነት የላቸውም። ይሁን እንጂ ሕጉ ተፈፃሚነት የለውም ቢባል ማጋነን አይሆንም። በተለይም፣ በርካታ ቡና ቤቶች (በአስተናጋጅነት ሥም) እና የዕርቃን ዳንስ ቤቶች (በዳንሰኝነት ሥም) በገሐድ እየፈሉ እና የወሲብ ንግድን በተቋም ደረጃ እያጧጧፉት ይገኛሉ። እነዚህን የመቆጣጠር ኃላፊነት የተጣለባቸው ደንብ አስከባሪዎች እና ባሕልና ቱሪዝም ቢሮዎች ኃላፊዎች ይህንን ድርጊት የማስቆም ኃላፊነት ቢኖራቸውም የሚጠበቅባቸውን በአግባቡ እየተወጡ አይደለም።
ይሁን እንጂ የአዲስ አበባ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የባሕል ዕሴት ባለሙያ የሆነው ሸዋደግ ብርሃኑ ‘ቢሮዎቹ ኃላፊነታቸውን አልተወጡም’ በሚለው ሐሳብ በከፊል አይስማማም። “ቱሪዝም ቢሮው ሥልጣኑ እነዚህን ቤቶች ከመለየት የዘለለ አይደለም። ይህን ደግሞ ካደረግን ዓመታት ቢያልፉም፥ እርምጃ እንዲወስዱ ሥልጣን የተሰጣቸው አካላት እንደ ደንብ ማስከበርና ንግድ ቢሮዎች ሥራቸውን በአግባቡ ተወጥተው አያውቁም” ይላል ሸዋደግ።
“በተለይም የዕርቃን ዳንስ ቤቶች ተጠቃሚዎች ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችም ጭምር በመሆናቸው ለመቆጣጠር አዳጋች ነው” ሲሉ ባለሙያው ያነሳሉ። “ብዙዎቹም ላለመዘጋታቸው ምክንያት ለአስፈፃሚ አካላት በሚከፍሉት ጉቦ እንደሆነም” ያስረዳሉ። የፌዴራሉ ባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ስለ ጉዳይ ተመሳሳይ ግንዛቤ ያለው ይመስላል። ከዚህ በፊት በተደረገ ጥናት እንደ አዲስ አበባ፣ ሐዋሳና አዳማ ያሉ ከተሞች ላይ የዕርቃን ዳንስ ቤቶች ቢኖሩም ከጀርባ ባሉ ረጃጅም እጆች ምክንያት ለመቆጣጠርም ሆነ ለመዝጋት አዳጋች እንደሆነ የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባሕል ዕሴቶች ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ግዛቸው ኪዳኔ ይገልጻሉ።
በሌላ በኩል መንግሥት ቤቶቹን ለመቆጣጠር እንደተሳነው ያስታወሱት የጥናት ባለሙያው መሰለ፥ በእንደዚህ ዓይነት ቤቶች ውስጥ ያለው እንቅስቃሴ ቸል በመባሉ ምክንያት የብዙ ሴቶች፣ በተለይም “የዘመናዊ ባርነት” መገለጫ መሆኑ ጋር ተያይዞ፣ ሰብኣዊ መብት እየተጣሰ መሆኑን ይገልጻሉ። በተጨማሪም እንደዚህ ዓይነት ቤቶች በከተማው እየተበራከተ ለመጣው የተደራጀ ወንጀል፣ ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር መስፋፋት ምክንያት እንደሆኑ ይገልጻሉ።
መፍትሔው ምንድን ነው?
ድርጅታቸው የወሲብ ንግድ ሠራተኞችን ሕይወት በመለወጥ ውጤታማ የሆነው ነብዩ ኃይሌ የወሲብ ንግድንም ሆነ አሁን እየጨመሩ ያሉ የዕርቃን ዳንስ ቤቶችን ለመቆጣጠር በፍላጎት በኩል መሠራት እንዳለበት ያስረዳሉ። በተለይም ድርጊቱ ለመጨመሩ ምክንያት ከውጭ የሚመጡ ጎብኚዎች ቁጥር መጨመርና በገንዘብ የወሲብ ስሜትን ለማርካት ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ቁጥር መጨመር በመሆኑ ይህንን ለመቀነስ ማኅበረሰቡ ላይ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ መሠራት አለበት ይላሉ።
ይህንን ጨምሮ፣ መካከለኛ ገቢ የሚያገኘው የኅብረተሰብ ክፍል ማደግን ተከተሎ ፍላጎት ሊጨምር እንደሚችል ያስታወሱት መሰለ፥ በዚህም ሐሳብ ይስማማሉ። ሴቶችን ‘የወሲብ ስሜት ማርኪያ’ አድርጎ የማሰብ ልማድ ሊቀር እንደሚገባ ይገልጻሉ። ይህንን አስተሳሰብ ለማስቀረት ወይም ለመቀየር፣ ሴቶች ሌሎች የሕይወት አማራጮች እንዳሉ የሚያውቁበት መንገድ ሊስፋፋ ይገባል ይላሉ። በመንግሥትም ደረጃ፣ ጉዳዩ የፖሊሲ ምላሽ እንደሚያስፈልገው ያስረዳሉ። በርግጥ፣ ይህን መሰል አሉታዊ ተፅዕኖ ያላቸውን ተግባራት ለመቆጣጠር ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች አባል የሆኑበት ብሔራዊ ጥምረት ያቋቋመው መንግሥትም ይህን የተረዳው ይመስላል። ለዚህም ግዛቸው ምስክር ነው። “መንግሥት ይህን መሰል አሉታዎ ተፅዕኖ ያላቸውን ተግባራት ለመቆጣጠር ስትራቴጂ ነድፎ ወደ ሥራ ሊገባ እየተዘጋጀ ስለሆነ ችግሩ በቅርቡ ሊፈታ ይችላል” ይላሉ።

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 5 years ago on January 26, 2019
  • By:
  • Last Modified: January 26, 2019 @ 10:56 am
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar