www.maledatimes.com የደኅንነት ምክትል ዳይሬክተሩ ላይ ሁለት የምርመራ መዝገብ መከፈቱ ተቃውሞ ቀረበበት - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የደኅንነት ምክትል ዳይሬክተሩ ላይ ሁለት የምርመራ መዝገብ መከፈቱ ተቃውሞ ቀረበበት

By   /   January 28, 2019  /   Comments Off on የደኅንነት ምክትል ዳይሬክተሩ ላይ ሁለት የምርመራ መዝገብ መከፈቱ ተቃውሞ ቀረበበት

    Print       Email
0 0
Read Time:4 Minute, 13 Second

በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው የታሰሩት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊ የነበሩት አቶ ያሬድ ዘሪሁን ላይ ሁለት የምርመራ መዝገብ መከፈቱ በጠበቆቻቸው ተቃውሞ ቀረበበት፡፡

ጠበቆቹ በተቃውሟቸው ያቀረቡት ክርክር፣ በአንድ ተጠርጣሪ ላይ ሁለት የምርመራ መዝገብ መክፈት አለመቻሉን ነው፡፡ ሥልጣን ያለው የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ሳይፈቅድና ሳያውቅ በቅድመ ምርመራ ፍርድ ቤት ፋይል መከፈቱን አጥብቀው ተከራክረዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ከወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር (80) ጀምሮ እስከ (93) ድረስ ያሉ ድንጋጌዎችን ከመጥቀስ ውጪ፣ ድንጋጌዎቹን ሊከተል እንዳልቻለም አክለዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ የቀዳሚ ምርመራ ዓላማን አለመግለጹን የተናገሩት ጠበቆቹ፣ ዓላማው ለመርማሪ ፖሊስ የምስክርት ቃል የሰጡ ምስክሮች በጠና ታመው ይሞታሉ ተብሎ ሲገመትና ከአገር ይወጣሉ ተብሎ ግምት ሲወሰድ ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይኼንን ባላረጋገጠበት ሁኔታ ጥያቄ ማቅረቡ ተገቢ አለመሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ምስክሮቹ ቃላቸውን ለመርማሪ ፖሊስ ከሰጡ ከሁለት ወራት በላይ እንደሆናቸው ጠቁመው፣ የሚጠፉ ወይም ከአገር የሚወጡ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ሊፈጸም ይችል እንደነበር ተናግረው፣ ይኼ ሆን ተብሎ ጉዳዩን ለማጓተት የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ደንበኛቸው የተጠረጠሩት በሰብዓዊ መብት ጥሰት እንጂ፣ በከባድ ሰው የመግደል ወንጀልና ከባድ ውንብድና ባለመሆኑ ዓቃቤ ሕግ የጠየቀው ቀዳሚ ምርመራ እንደማይመለከታቸው ገልጸዋል፡፡ አቶ ያሬድ ለስድስተኛ ጊዜያት መቅረባቸውን ጠቁመው፣ በስድስቱም ጊዜያት ከሚቀርቡት ተጨማሪ ጊዜ መጠየቂያ ነጥቦች አንፃር የተለያዩ ስድስት የምርመራ መዝገቦች እንጂ፣ አንድ የምርመራ መዝገብ  እንደማይመለስላቸው ተናግረዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ይኼንን የሚያደርገው ለሚዲያ ፍጆታና ፍርድ ቤቱን ለማሳመን መሆኑን ሲገልጹ፣ ዓቃቤ ሕግ ተቃውሞ አቅርቧል፡፡ ዓቃቤ ሕግ የተቃወመበትን ምክንያት ሲናገር፣ ጠበቆች የሚከራከሩበትና የሚጠቀሙት ቃል ፍርድ ቤቱን የሚመጥንና ሕግን መሠረት ያደረገ አሳማኝ ክርክር መሆን እንዳለበት፣ ሚዲያም የሰማውንና ያመነበትን መዘገብ ይችላል ብሏል፡፡

ችሎቱን በሚመጥን ቋንቋ እንዲከራከሩ ለጠበቆቹ ትዕዛዝ እንዲሰጥለትም ጠይቋል፡፡ ጠበቆቹም በሰጡት ምላሽ ስህተት ከሠሩ ፍርድ ቤቱ ሊያርማቸው ይገባል እንጂ ዓቃቤ ሕግ አለመሆኑን ጠቁመው፣ መናገር የፈለጉት ነገሮችን አጋኖ በማቅረብ ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በሚዲያው ላይ የተናገሩትን እንደሚያርሙ በመግለጻቸው፣ ፍርድ ቤቱ ተቀብሎ በአግባቡና ተገቢ ቋንቋን እንዲጠቀሙ አሳስቧል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በተጠርጣሪዎች ላይ ምስክር የተቀበለው በቡድን መሆኑን ጠቁመው፣ በአቶ ያሬድ ላይ ስንት ምስክሮችን በቀዳሚ ምርመራ ፍርድ ቤት እንደሚያቀርብ አለመግለጹንም አስረድተዋል፡፡ ወንጀል የግል እንደመሆኑ በእሳቸው ላይ ምን ያህል ምስክሮችን እንደሚያሰማም መግለጽ እንዳለበትም አክለዋል፡፡ መርማሪ ፖሊስ ምርመራውን በማጠናቀቁ፣ ዓቃቤ ሕግ እንደገና በምርመራ ሊሳተፍ ስለማይገባ መዝገቡ መዘጋት እንዳለበትም አስረድተዋል፡፡ ከሕክምና ማስረጃ ጋር በተገናኘ የሕክምና ባለሙያን ቃል መቀበልና ደንበኛቸውን ምንም የሚያገናኛቸው ነገር ስለሌለ በዋስ ሊፈቱ እንደሚገባ ተከራክረዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ደንበኛቸውን ከንብረት ጋር በማገናኘት ስማቸውን እየጠለሸ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ እንዲያስቆምላቸው ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑም ሆነ ዓቃቤ ሕግ ሥራቸውን በአግባቡ እየሠሩ አለመሆናቸውን ለማወቅ ከታሰሩ ከሦስት ወራት በኋላ፣ ከቀናት በፊት ማንነታቸውን የጠየቁበት ሒደት ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በሰጠው ምላሽ ቀዳሚ ምርመራ ለማድረግ፣ ዋና ምርመራ ይጠናቀቅ የሚል ሕግ አለመኖሩን ገልጿል፡፡  በተጠርጣሪ ላይ እንዴት ምርመራ መካሄድ እንዳለበት ከወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 37 ጀምሮ ተደንግጎ እንደሚገኝና አንቀጽ 38 ደግሞ ለዓቃቤ ሕግ ሥልጣን መስጠቱን ጠቁሟል፡፡ ሌላው የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 ሲሆን፣ ዓቃቤ ሕግ በምርመራ እንደሚሳተፍና እንደሚመራ ስለተደነገገ፣ የፈለገውን ሥራ ሌላው ሳይጠናቀቅ መሥራት እንደሚችል አስረድቷል፡፡ ዋና ምርመራ እየተካሄደ፣ ቀዳሚ ምርመራውንም ፍርድ ቤት ማቅረብ እንደሚችልም አክሏል፡፡ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓቱ ‹‹ተከሳሹ›› የሚለው ተጠርጣሪን መሆኑንና ሕገ መንግሥቱም በተለዋጭነት ስለሚጠቀምበት፣ ጠበቆች ተጠርጣሪ ላይ ቅድመ ምርመራ ፍርድ ቤት ማቅረብ እንደማይቻልና የሚቻለው በተከሳሹ ላይ ብቻ ነው የሚለው ተገቢ አለመሆኑን ገልጿል፡፡

በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ላይ የተጠቀሱትን ድንጋጌዎች አንድ አንቀጽ አንብቦ መከራከር ብቻ ሳይሆን፣ ሁሉንም ንዑስ አንቀጾች አንብቦ መረዳት እንደሚያስፈልግ አስረድቷል፡፡ የሕክምና ሰነድ ማስረጃን በሚመለከትም በርካታ ደብዳቤዎች መጻፋቸውን፣ የደረሱትንም ሰብስቦ ቀሪዎቹን እየጠበቀ መሆኑንም ገልጿል፡፡

በአቶ ያሬድ ላይ ከ20 የሚበልጡ ምስክሮችን በቀዳሚ ምርመራ ፍርድ ቤት አቅርቦ እንደሚያሰማም ተናግሯል፡፡ በዋናነት ምስክሮችንና የሕክምና ማስረጃዎችን ማረጋገጥ የተፈለገው ከአሁኑ ተጎጂ የታከመበት ሰነድ መጥፋቱና እንደሌለ እየተገለጸ በመሆኑ እሱን ለማረጋገጥ ጭምር መሆኑን አስረድቷል፡፡

በተጠርጣሪው ላይ ተጨማሪ ጊዜ ለማስፈቀድ ሳይሆን እውነትን ለማፈላለግ በመሆኑና ሕግም ስለማይከለክል ሥራውን እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡

ሌላው ተጠርጣሪው በጠበቆቻቸው አማካይነት ዓርብ ጥር 17 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢንተርፖል አሜሪካ ተጋብዘው እንደነበር የገለጹት፣ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ከዋስትና ጥያቄ ጋር በተገናኘ ‹‹ከአገር ሊሸሹና ሊጠፉ ይችላሉ›› በማለት ዋስትና መጠየቃቸውን በፍርድ ቤት በመቃወሙ ነው፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ቀደም ብሎ ለፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን በፍርድ ቤት የተፈቀደለትን የምርመራ ጊዜ ተጠቅሞ የሠራውንና የሚቀረውን ሥራ የሚገልጽ ሪፖርት ለፍርድ ቤቱ ሲያቀርብ፣ በአቶ ያሬድ ላይ መርማሪ ቡድኑ የምስክርነት ቃል የተቀበላቸውን ምስክሮች ቃል ሕጋዊ ለማድረግ፣ በተቀዳሚ ምርመራ ፍርድ ቤት ፋይል መክፈቱንና ለምስክሮች መጥሪያ ለመላክ ጊዜ ስለሚያስፈልገው 14 ተጨማሪ ቀናት እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡

የአቶ ያሬድ ጠበቆች መርማሪ ቡድኑ ቀደም ብሎ በተሰጠው የምርመራ ጊዜ ሥራውን ከምን ላይ እንዳደረሰው ሳይናገር፣ ዓቃቤ ሕግ ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ የሚጠይቅበት የሕግ አግባብ እንደሌለ በመግለጽ ተከራክረዋል፡፡ ከዓቃቤ ሕጉ ንግግር እንደተረዱት የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ምርመራውን ማጠናቀቁን በመሆኑ፣ ዓቃቤ ሕግ ማድረግ ያለበት ክስ መመሥረት ወይም ተጠርጣሪውን በነፃ እንዲሰናበቱ መጠየቅ ስለሆነ እስከዚያው ድረስ (ዓቃቤ ሕግ ውሳኔውን እስከሚገልጽ) ደንበኛቸው በዋስ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ አቶ ያሬድ በዋስ እንዳይለቀቁ ባቀረበው አመክንዮ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር የያዛቸው በሌላ ቦታ ተሸሽገው ሊጠፉ ሊሰናዱ መሆኑን አስታውሶ፣ አሁንም በዋስ ቢወጡ ራሳቸውን ሊሰውሩ ወይም ሊያጠፉ ይችላሉ የሚል እምነት ስላለው ሊፈቀድላቸው እንደማይገባ በመግለጽ ተከራክሯል፡፡

አቶ ያሬድ ጠፍተው ተገኙ በማለት ዓቃቤ ሕግ የሚናገረው ዱከም በባለቤታቸው ቤተሰቦች ቤት ስለተገኙ መሆኑን የገለጹት ጠበቆቻቸው፣ በአንድ አገር ውስጥ ሊጠፉ ይችላሉ ሊባል እንደማይገባ ተናግረዋል፡፡ እነሱም (ጠበቆቹ) ዱከምና ደብረ ዘይት ሄደው ቆይተው የሚመለሱበት ከተማ ከመሆኑ አንፃር እንደዚያ መባሉ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡ አቶ ያሬድ ከመታሰራቸው በፊት በኢንተርፖል ኒውዮርክ ከተማ ለስብሰባ ተጋብዘው እንደነበር አስታውሰው፣ መደበቅና መሸሸግ ቢፈልጉ ኖሮ ኒውዮርክ ይሻላቸውና ይችሉም እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን አቶ ያሬድ መጠርጠራቸውን ያውቁ ስለነበር፣ ግብዣውን ትተው እስከሚያዙ መጠበቃቸውንና በወቅቱ የነበረውን ግርግር ለማሳለፍ ወደ ቤተሰቦቻቸው መሄዳቸውን አክለዋል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤቱ የተጠርጣሪዎቹን መቃወሚያ ውድቅ በማድረግ፣ ለቀዳሚ ምርመራ 12 ቀናት በመፍቀድ ለጥር 28 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 5 years ago on January 28, 2019
  • By:
  • Last Modified: January 28, 2019 @ 1:41 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar