www.maledatimes.com “ባለቤት ያቃለለውን አሞሌ ባለ ዕዳ አይቀበለውም” በዳንኤል ክብረት - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

“ባለቤት ያቃለለውን አሞሌ ባለ ዕዳ አይቀበለውም” በዳንኤል ክብረት

By   /   February 11, 2019  /   Comments Off on “ባለቤት ያቃለለውን አሞሌ ባለ ዕዳ አይቀበለውም” በዳንኤል ክብረት

    Print       Email
0 0
Read Time:5 Minute, 59 Second

“ትንቢተ ዳንኤል” እና የንጉሠ ነገሥቱ ሐውልት

ሙኃዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት የዛሬ ሰባት ዓመት ገደማ (የካቲት 2004 ዓ.ም) “ባለቤት ያቃለለውን አሞሌ ባለ ዕዳ አይቀበለውም” በሚል ርእስ ግሩም የሆነ ጽሑፍ አስነብቦን ነበር፡፡ ለጽሑፉ ምክንያት የሆነው በአፍሪካ ኅብረት ጽ/ቤት ለክዋሜ ንክሩማህ የቆመው መታሰቢያ ሐውልት ለንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ ያለመቆሙ ጉዳይ ነበር፡፡ ዘንድሮ ጊዜው ሲደርስና የመታሰቢያ ሐውልት ሲቆምላቸው የተስፋው ቶሎ መፈጸም ቢደንቀኝ ነው የዳኒን ትንቢታዊ ጽሑፍ እንደገና ለማንበብ መነሣቴ፡፡ እናንተም ታነቡት ዘንድ እነሆ!
**********//**********//**********

“አብዮቱ ከመፈንዳቱ አምስት ዓመታት ቀደም ብዬ በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሥራ ጀምሬ ነበር፡፡ ዋናው ምድቤ ደቡባዊው የአፍሪካ ክፍል ነበር፡፡ በዚህ ቦታ በመመላለስ ለዐሥራ አምስት ዓመታት በማገልገሌ አካባቢውን ያደግሁበትን ቦታ ያህል ዐውቀው ነበር፡፡ በ1976 ዓም በወቅቱ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ የነበሩት ሰው እኔን የደቡባዊ አፍሪካን ጉዳይ በሚከታተለው የመንግሥታቱ ድርጅት አካል ውስጥ ለመሾም ፈለጉ እና አናገሩኝ፡፡ ኃላፊነቱን መቀበሉ ለኔ መልካምም ቀላልም ነበር፡፡ ከባድ የሆነው ነገር የሀገሬን መንግሥት ድጋፍ ማግኘቴ ነበረ፡፡

እኔ ከሀገሬ ወጥቼ መሥራት ከጀመርኩ ያኔ ዐሥራ አምስት ዓመት ሆኖኛል፡፡ ከዚህም በላይ ደግሞ መንግሥትም ሥርዓትም ተለውጧል፡፡ አሁን ያሉትን ባለ ሥልጣናት አላውቃቸውም፡፡ እንደ እነርሱም ኮሚኒስት አይደለሁም፡፡ ጉዳዩን በመጠኑም ለምቀርባቸው አንድ የወቅቱ ባለሥልጣን በስልክ አማከርኳቸው፡፡ ሰዎቹን አናግረው እንደሚደውሉልኝ ነገሩኝ፡፡ ከሳምንት በኋላ ደውለው ሃሳቡን እንደ ተቀበሉት ነገር ግን አዲስ የተቋቋመው የኢሰፓአኮ አባል መሆን እንደሚጠበቅብኝ ነገሩኝ፡፡ እርሳቸውም ለእኔ በማሰብ “ምናለ አንተስ ዝም ብለህ ፎርሙን ብትሞላላቸው?” ብለው መከሩኝ፡፡

ከራሴ ጋር ለጥቂት ቀናት ተማከርኩ፡፡ “እኔ ለዚህ ቦታ ስታጭ መታየት ያለበት አገልግሎቴ እና ብቃቴ እንጂ የፓርቲ አባልነቴ ነው እንዴ?” ብዬ ጠየቅኩ፡፡ በመጨረሻም በራሴ ላይ ወስኜ ለዋና ጸሐፊው ነገርኳቸው፡፡ እያዘኑ ቦታውን ለሌላ ሰጡት፡፡ እኔንም በሌላ የሀገር ድጋፍ በማያስፈልገው ቦታ ሾሙኝ፡፡”

ይህንን ታሪክ በደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን በ1992 ዓ.ም ያወጉኝ አንድ አረጋዊ ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡ “ኢትዮጵያውያን በዓለም ዐቀፍ ተቋማት ለምንድን ነው ጎልተው የማይታዩት? ከሌሎቹ ቀድመን የዓለም ዐቀፍ ተቋማት አባል እንዳልሆንን ለምን ከሌሎቹ አንሠንታየን?” እያልኩ ስጨቀጭቃቸው ነበር ይህንን የራሳቸውን ገጠመኝ ያወጉኝ፡፡

ይህ ሰዎቹን ሁሉ ሀገራዊ በሆነ መሥፈርት ሳይሆን በዘመኑ በተጠለቀው የርእዮተ ዓለም መነጽር የማየት ችግር ኢትዮጵያውያን ጀግኖች በሀገራቸውም ሆነ በዓለም መድረክ ጎልተው እንዳይታዩ ካደረጋቸው ምክንያቶች አንዱ ነው፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስን እና ዐፄ ምኒሊክን እያሰቡ “ለእኩልነት እና ለዴሞክራሲ፣ ለሰብአዊ መብት እና ለነጻ ምርጫ ምን አስተዋጽዖ አደረጉ?” እያሉ ከመጠየቅ የባሰ ዕብደት የለም፡፡ ደገኛን በበቆሎ ቆለኛን በገብስ ማማት ይሉታል ይኼ ነው፡፡ ለመሆኑ አበበ ብቂላን እንደ ጀግና ስናየው በየትኛው መሥፈርት መዝነነው ነው? ታግሎ ሕዝቡን ከፊውዳሊዝም ነጻ ያወጣ፣ ለዴሞክራሲያዊ መብት መሥዋዕትነት የከፈለ፣ ለብሔር ብሔረሰብ እኩልነት ዋጋ የከፈለ፣ ለኢትዮጰያ ነጻነት የተዋደቀ፣ እያልን የምንቀጥል ከሆነ አበበ ብቂላን አንድም ቦታ አናገኘውም፡፡

ይህ ግን የአበበ ብቂላ ስሕተት አይደለም፡፡ ጀግና እና ሸማ በየፈርጁ መሆኑን የረሳነው የኛ የራሳችን እንጂ፡፡ ዐሉላ አባ ነጋን ስናስብ ስለ ኦሎምፒክ እና ስለ ሩጫ፣ ስለ ወርቅ እና ብር ሜዳልያ፣ ስለ ሮም እና ቶኪዮ የምንጠይቃቸው ከሆነ በዚህ ረገድ ጀግና የሚያሰኛቸው አንድም ነገር አናገኝም፡፡ ችግሩ ግን የዐሉላ አባ ነጋ አይደለም፡፡ ለሁሉም ዓይነት እህል ተመሳሳይ ሙቀጫ የምናቀርበው የኛ እንጂ፡፡ ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ የአፍሪካ አነድነት ድርጅትን በመመሥረት፣ አፍሪካውያን ከቅኝ ገዥዎች ተላቅቀው ነጻ እንዲወጡ በመርዳት፣ የአፍሪካውያንንም ድምጽ በዓለም ዐቀፍ መድረክ በማሰማት ያደረጉትን አስተዋፅዖ እንኳን እኛ ዛሬ ከመቃብር በታች የዋለው አፓርታይድም ዕድል ካገኘ ይመሰክረዋል፡፡

እዚህ ላይ ላመስግናቸውና ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስም ቢሆኑ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን መቀመጫ ከተማ ከአዲስ አበባ ለማዛወር በተነሣው አጀንዳ ላይ በስሜት እና በቁጭት ሲናገሩ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ በኢትዮጵያ ውስጥ ጨቋኝ ቢሆኑም ለአፍሪካ ነጻነት እና ለድርጅቱ መመሥረት ያደረጉት አስተዋጽዖ ግን ወደር የማይገኝለት መሆኑን ገልጠው ነበር፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በ1963 ዓ.ም ሲመሠረት የካዛብላንካ እና የሞኖሮቪያ ቡድን ተብላ አፍሪካ በሁለት ጎራ ስትናጥ በወቅቱ ከዐፄ ኃይለ ሥላሴ የተሻለ ተሰሚነት ያለውና አንድነትን ሊያመጣ የሚችል መሪ አልነበራትም፡፡ ልዩ ልዩ መልክተኞቻቸውን ልከው በየሀገሩ ገና በነጻነት ደስታ ተጥለቅልቀው ከፌሽታ ያልወጡትን ነጻ አውጭ መሪዎች እያግባቡ እና እያባበሉ፣ የተጣሉትን እያስማሙ ጉባኤው በአዲስ አበባ እንዲሆን ያደረጉት ንጉሡ ነበሩ፡፡

ከዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ በኋላም ጉባኤው በአዲስ አበባ ሲካሄድ “እንየው፤ እንምከርበት፤ ጊዜ እንስጠው” እያሉ ብዙዎቹ መሪዎች ነገሩን ሲያዘገዩት «ይህንን የአንድነት ሰነድ ሳንፈርም ከዚህ ጉባኤ አዳራሽ አንወጣም» ብለው በመገዘት ከሌሊቱ በዘጠኝ ሰዓት እንዲፈረም ያደረጉት ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ነበሩ፡፡ ንጉሡን «የአፍሪካ አባት» ብለው የሰየሟቸው ኢትዮጵያውያን አይደሉም፡፡ የአፍሪካ መሪዎች እንጂ፡፡ ይህ ለንጉሡ ብቻ የተሰጠ አይደለም፤ ለሀገራቸውም ጭምር እንጂ፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪካ ኅብረት ተሸጋግሮ፣ የምሥረታውን በዓል ለማክበርም አንድ ዓመት ያህል ሲቀረው በቀድሞው ከርቸሌ ግቢ ላይ ቻይና አዲሱን የኅብረቱን ሕንፃ አቆመች፡፡

«ለሰጭ ይስጠው ለንፉግ ልብ ይስጠው» ይል ነበር አጎቴ፡፡ በዚህ ታላቅ ሥራ ውስጥ ሰጭም ነፋጊም ተገኘና ደስታችንን ግማሽ አደረገው፡፡ ሴትዮዋ ባልዋ አዳኝ ነበር አሉ፡፡ ወንድ የተባለ የማያገኘውን አውሬ የገባበት ገብቶ የሚያድን፡፡ አንድ ቀን ነብር አድናለሁ ብሎ ወጥቶ እጅግ ብዙ ቀን ቆየ፡፡ ሚስት ተጨነቀች፡፡ ከብዙ ጊዜ በኋላ አያሌ ወታደሮች በሰልፍ ሆነው ወደ መንደርዋ መጡ፡፡ ሰልፉ መቼም ልዩ ነበረ፡፡ የመንደርዋ ሰዎች ግልብጥ ብለው ወጥተው ሰልፉን ተመለከቱ፡፡ የነብር ቆዳ፣ ካባ፣ የደረት ሜዳልያ ይዘዋል ወታደሮቹ፡፡

የአዳኙ ሚስት ተጠራች፡፡ እየፈራች ቀረበች፡፡ «ንጉሡ ይህንን ካባ፣ ይህንን የነብር ቆዳ፣ ይህንንም ሜዳልያ ሸልመውሻል፡፡ ይህንን ያህል ርስት ሰጥተውሻል፡፡ ቤትሽ በግንብ እንዲሠራም አዝዘዋል» አሉና ዐወጁ፡፡ ሕዝቡ እልል ብሎ ተቀበለ፡፡ ሴትዮዋ ግን ጨነቃት፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ባሏሳ፡፡ ወታደሮቹ ይህንን ሲጨርሱ ባልዋ ከንጉሡ ታዝዞ አደን ሲያድን ከነብር መንጋ ሌሎቹ ጓደኞቹን ለማትረፍ ብሎ ሕይወቱን ማሳለፉን አረዷት፡፡ አሁን ግራ ገባት፡፡ ትደሰት ወይስ ትዘን? ታልቅስ ወይስ ትሳቅ? አንዱ ያስተዛዝናታል፡፡ ሌላው እንኳን ደስ ያለሽ ይላታል፡፡ አንዱ ይቀናባታል፡፡ ሌላው ያዝንላታል፡ አንዱ ፈገግ ብሎ ይመጣል፣ ሌላው ተክዞ ይከተላታል፡፡ ሲጨንቃት
“ኀዘን እና ደስታ አንድ ላይ ውለው
ላልቅስ ወይስ ልዝፈን የቱ ነው ሞያው?” አለች አሉ፡፡

እኛም እንዲህ ነው የሆንነው፡፡ ክዋሜ ንክሩማህ ለአፍሪካ አንድነት መመሥረት አስተዋጽዖ አድረገዋል፡፡ እሙን ነው፡፡ አስተዋጽዖዋቸው ግን የዐፄ ኃይለ ሥላሴን ያህል እንዳልሆነ ራሳቸው ጋናዎች ይመሰክራሉ፡፡ “ከጣት ጣት ይበልጣል” ይላሉ ሀበሾች፡፡ ታላቁ መጽሐፍም “ኮከብ እም ኮከብ ይኼይስ ክብሩ-የአንዱ ኮከብ ክብር ከሌላው ኮከብ ይበልጣል” ይላል፡፡ ንክሩማህ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ የነበራቸውን ሥልጣን፣ ዐቅም እና ተቀባይነት አልነበራቸውም፡፡ ኢትዮጵያ የነበራትን የነጻነት ተምሳሌትነትም ጋና አልነበራትም፡፡

አሁን መነጋገር ያለብን ስለ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ፊውዳልነት፣ ጨቋኝነት፣ ባላባትነት፣ ባለ ርስትነት አይደለም፡፡ አሁን መመዘኛችን ለፍትሕ፣ ለዴሞክራሲ፣ ለብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት፣ ለምርጫ፣ ለመሬት ላራሹ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ምን አድርገዋል እያልን አይደለም፡፡ አሁን መከራከርያችን ንጉሡ ለአፍሪካውያን ነጻ መውጣት እና ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምን አስተዋጽዖ አድርገዋል? የሚለው ነው፡፡

የክዋሜ ንክሩማህ ሐውልት ሲቆም ሥራቸው ከአፍሪካ ነጻነት እና ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት አንጻር ተመዝኖ እንጂ እርሳቸውምኮ በሀገራቸው እንደ ንጉሡ ይታማሉ፡፡ ያሠሯቸው፣ ያስገደሏቸው፣ ፍትሕ ያዛቡባቸው አሉ፡፡ እርሳቸውምኮ በሀገራቸው የሚቃወማቸው አለ፡፡ መጽሐፉ እንዳለው ነቢይ በሀገሩ አይከበርማ፡፡

ሰውን መመዘን ያለብን በዋለበት መሥመር እንጂ በምልዐት አይደለም፡፡ አንድ ሰው በሂሳብ ትምህርት መቶ ለማምጣት በአማርኛም፣ በእንግሊዝኛም፣ በፊዚክስም መቶ ማምጣት የለበትም፡፡ ወይንም ደግሞ በሌሎች ትምህርቶች መቶ አላመጣህምና የሂሳብን ፈተና ሙሉ በሙሉ ብታልፍም መቶ አልሰጥህም አይባልም፡፡ በሂሳብ ውጤት የሚሸለሙ ሰዎች ሲጠሩ ይህ ተማሪ አንደኛ ተብሎ ሊሸለም፤ ሊጨበጨብለት፤ ሐውልት የሚሠራም ከሆነ ሊሠራለት ይገባል፡፡ የፊዚክስ ውጤት ሲመጣ ስሙን አለመጥራት፣ ውጤታማ አለመሆኑን መናገር ይቻላል፡፡

ለዐፄ ቴዎድሮስ መታሰቢያ ስናቆም ለኢትዮጵያ አንድነት ያደረጉትን አስተዋጽዖ በማሰብ እንጂ ፍትሕ፣ እኩልነት፣ ነጻነት፣ ዴሞክራያዊነት፣ ምርጫ፣ የብሔር ብሔረሰቦች መብት፣ ራስን በራስ ማስተዳደር፣ ፓርቲ፣ እያልን አይደለም፡፡ በተለይም የኢትዮጵያ መንግሥት እና ዲፕሎማቶች ሽንጣቸውን ገትረው ሊከራከሩ በተገባቸው ነበር፡፡ ክርክሩ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ለአፍሪካ ነጻነት እና ለአፍሪካ አንድነት ምን ሠርተዋል? በሚለው ነው፡፡ ክርክሩ ሐውልት ይቁም ከተባለ የማን ሐውልት መቆም አለበት በሚለው ነው፡፡ ስለ ንጉሡ በዋነኛነት መከራከር ያለባቸው የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ናቸው፡፡ ያለበለዚያማ ባለቤት ያቃለለውን አሞሌ ባለ ዕዳ እንዴት ይቀበለዋል?

ይህንን አለማድረግ አቶ በረከት ስምዖን «የሁለት ምርጫዎች ወግ» በሚለው መጽሐፋቸው ማጠቃለያ ላይ ያሠፈሩት የታላቁ ፈላስፋ የሲሴሮን ቃል አለመረዳት ይመስለኛል፡፡ ሲሴሮ እንዲህ ይላል «ባለፉት ዘመናት የተሠራው ሁሉ በሚገባ ካልተነገረና ቀደምት ሰዎች ባበረከቱት አስተዋጽዖ በአግባቡ መጠቀም ካልተቻለ፣ ዓለማችን ሁሌም ቢሆን የዕውቀት ብላቴና እንደሆነች ትቀራለች»፡፡

Image may contain: people standing, sky, cloud and outdoor

Image may contain: people standing, sky and outdoor

ዛሬ አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና እንድትሆን፣ ከብራስልስ ቀጥላ ትልቋ የዲፕሎማቲክ ከተማ እንድትሆን፣ ይህ ዛሬ የተሠራው ሕንፃም እዚሁ በከተማችን እንዲሠራ፣ አፍሪካውያን እንዲተባበሩ፣ ከቅኝ ግዛትም ነጻ እንዲሆኑ ታላቅ አስተዋጽዖ ያደረጉትን መሪ መርሳት ኢትዮጵያን «ሁሌም ብላቴና» ማድረግ ነው፡፡ አሁን ንጉሡ የሉም፡፡ አይደሰቱም አይቀየሙምም፡፡ ኢትዮጵያ ግን ቦታዋን አጥታለች፡፡ በገዛ ዳቦዋ ልብ ልቡን አጥታዋለች፡፡ እኔ ተስፋ አለኝ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተመሠረተበት አምሳኛ ዓመት በዓል ከመከበሩ በፊት የንጉሡ ሐውልት ከነአስተዋጽዖዋቸው በአፍሪካ ኅብረት ግቢ ውስጥ ይታያል ብዬ፡፡

ምንጭ፡- http://www.danielkibret.com (February 17, 2012)

ደግ ደጉን ያስመልክተን ፤ አሜን!
የካቲት 04/2011 ዓ.ም

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 5 years ago on February 11, 2019
  • By:
  • Last Modified: February 11, 2019 @ 8:29 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar