www.maledatimes.com አቶ ኢሳያስ ዳኘው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ በሰባት አባላት በፀደቀ ውሳኔ ሊጠየቁ እንደማይገባ ተናገሩ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

አቶ ኢሳያስ ዳኘው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ በሰባት አባላት በፀደቀ ውሳኔ ሊጠየቁ እንደማይገባ ተናገሩ

By   /   February 17, 2019  /   Comments Off on አቶ ኢሳያስ ዳኘው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ በሰባት አባላት በፀደቀ ውሳኔ ሊጠየቁ እንደማይገባ ተናገሩ

    Print       Email
0 0
Read Time:4 Minute, 40 Second

በተፈቀደው የ50 ሺሕ ብር ዋስትና ላይ ይግባኝ ተጠየቀ 

የሜቴክ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት የሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ወንድም አቶ ኢሳያስ ዳኘው፣ ኢዲኤም ለተባለ የአሜሪካ አማካሪ ድርጅት ከተፈጸመ ክፍያ ጋር በተያያዘ በሙስና መጠርጠራቸውን ተቃወሙ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጨምሮ በሰባት አባላት በፀደቀ ውሳኔና በተፈጸመ ክፍያ እሳቸው ሊጠየቁ እንደማይገባም ገልጸዋል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀደም ብሎ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አሥረኛ ወንጀል ችሎት ለአቶ ኢሳያስ ፈቅዶላቸው በነበረው የ100 ሺሕ ብር ዋስትና የካቲት 6 ቀን 2011 ዓ.ም. ከእስር እንዲፈቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት፣ ‹‹እፈታለሁ›› ብለው ሲጠብቁ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ግን በሌላ ወንጀል እንደሚጠረጥራቸው ገልጾ፣ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡

መርማሪ ቡድኑ በቁጥር 3-4802/2011 ባቀረበው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መጠየቂያ ደብዳቤ እንደገለጸው፣ አቶ ኢሳያስ በኢትዮ ቴሌኮም የኤንጂፒኦ ዳይሬክተር ሆነው ሲሠሩ፣ ከሌሎች ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን ኢዲኤም የተባለ የአሜሪካ አማካሪ ድርጅት ያለ ምንም ውድድርና ጨረታ የማማከር ሥራ ለመሥራት ውል እንዲፈጸም ማድረጋቸውን፣ የድርጅቱ 12 ሠራተኞች ምንም ዓይነት ሥራ ሳይሠሩ ከ2001 ዓ.ም. እስከ 2005 ዓ.ም. ድረስ በሰዓት ከ125 ዶላር እስከ 150 ዶላር ይከፈላቸው እንደነበር አብራርቷል፡፡ አማካሪ ድርጅቱ ሥራውን በአግባቡ ስለመፈጸሙ ካረጋገጠ በኋላ፣ የሚለቀቅለት ክፍያ (Retention Fee)ከጠቅላላ ክፍያው አሥር በመቶ ወይም 104,495 ዶላር የተያዘ ቢሆንም፣ ሥራው በአግባቡ መሠራቱ ሳይታወቅ እንዲከፈለው ማድረጋቸውንም መርማሪ ቡድኑ አክሏል፡፡

በተጨማሪም የአማካሪ ድርጅቱ ሠራተኞችን ለሚቆጣጠሩ ሥራ አስኪያጅም በሰዓት እስከ 150 ዶላርና ለተለያዩ አግባብነት ለሌላቸው ወጪዎችም ክፍያ እንዲፈጸም ማድረጋቸውን በመጠቆም፣ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

ይመሩት ነበር የተባለው ኤንጂፒኦ ዳይሬክቶሬት በተጠቀሰው ጊዜ አለመቋቋሙን በመጠቆም መቃወሚያቸው በጠበቆቻቸው አማካይነት ያቀረቡት አቶ ኢሳያስ፣ መርማሪ ቡድኑ ፈጽመዋቸዋል ያላቸውን ድርጊቶች እንዳልፈጸሙና ሐሰት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ድርጊቱ ፈጽመውታል ቢባል እንኳን ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮ ቴሌኮም ማስፋፊያም ሆነ ግዥዎች ወይም አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውሎችና ስምምነቶች የሚፈጸሙት በሰባቱ የቦርድ አባላት፣ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) (ጠቅላይ ሚኒስትር ከመሆናቸው በፊት)፣ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)፣ የፍትሕ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ብርሃን ኃይሉ፣ አቶ መኩሪያ ኃይሌ፣ ወ/ሮ አስቴር ማሞ፣ አቶ ጁላሎ (ከግሉ ሴክተር) እና አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ከወሰኑና በፊርማቸው ካፀደቁት በኋላ በመሆኑ፣ እሳቸው ሊጠየቁ እንደማይገባ አስረድተዋል፡፡ የቦርዱ አባላት ካልወሰኑና በፊርማቸው ካላፀደቁ በስተቀር ምንም ዓይነት ግዥም ሆነ ውል እንደማይፈጸም አክለዋል፡፡

አቶ ኢሳያስ ከሦስት ወራት በላይ በእስር ላይ መሆናቸውንና መርማሪ ፖሊስ ምንም ዓይነት የሚያስከስስ ወንጀል እንዳላገኘባቸው ለፍርድ ቤቱ የገለጹት ጠበቆቻቸው፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይፈቱ ከተባለ በኋላ መታሰራቸው ሕገወጥ መሆኑን በመግለጽ በዕለቱ (የካቲት 6 ቀን 2011 ዓ.ም.) እንዲፈቱ ብሎ የሰጠውን ትዕዛዝ ላለመፈጸም የተወጠነ ድርጊት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ አዲስ ጥቆማ እንደደረሰውና እያጣራ ስለመሆኑ ሲያስረዳ፣ ‹‹አቶ ኢሳያስ ከግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን ውል እንዲፈጸም ትዕዛዝ እየሰጡ፣ አሥር በመቶ ተይዞ የነበረን ‘ሪቴንሽን’ በመክፈል በመንግሥት ላይ ጉዳት አድርሰዋል፤›› ማለቱ ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ እንዲሆንላቸው ጠይቀዋል፡፡

የጥያቄያቸው ምክንያት ሁለት መሆኑን የጠቆሙት ጠበቆቹ፣ አንደኛው ድርጊቱ ከተፈጸመ አሥር ዓመታት ያለፈው ከመሆኑ አንፃር ተቋሙ እስካሁን ምን ሲያደርግ እንደነበር ለማወቅ፣ ሁለተኛው ደግሞ ተጠርጣሪው ለ93 ቀናት (እስከ የካቲት 6 ቀን 2011 ዓ.ም.) በእስር ላይ ሆነው ለምን እስካሁን ጥቆማው ሳይቀርብ እንደቀረ ለማወቅ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ከግብረ አበሮቻቸው ጋር ሆነው ከተባለም የአቶ ኢሳያስ ድርሻ ምን እንደነበር ግልጽ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በሰጠው ምላሽ አቶ ኢሳያስ ከግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን ውል መፈጸማቸውንና እንዲሻሻል ማድረጋቸውን፣ ሥራው መሠራቱን ሳያረጋግጡ ክፍያ እንዲፈጸም ማድረጋቸውንና ይኼንንም ለማድረግ ማስገደዳቸውን በመግለጽ ምላሽ ሰጥቷል፡፡

የአቶ ኢሳያስ ጠበቆች የፖሊስ መልስ አሳማኝ አለመሆኑን ጠቁመው፣ በተጠርጣሪው ላይ እየተፈጸመ ያለው ነገር ፍርድ ቤቱም የሚገምተውና እነሱም የሚረዱት ነገር እንዳለ ገልጸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የህሊናና የሕግ ፍርድ ይሰጣል የሚል እምነትም እንዳላቸውም አክለዋል፡፡ መርማሪው ተቋም ሥልጣኑን ያላግባብ እየተጠቀመ በመሆኑ ሊጠየቅ እንደሚገባም ጠይቀዋል፡፡ በኢትዮ ቴሌኮም ውስጥ ተፈጸመ የተባለን የወንጀል ድርጊት ከአሥር ዓመታት በኋላ ለማንቀሳቀስ መፈለጉ፣ ከተጠርጣሪው በስተጀርባ ሌላ ነገር እየተሠራ ነው የሚል ግምት እንዳሳደረባቸው ተናግረዋል፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ ተጠርጣሪው ከ93 ቀናት በላይ በእስር ላይ እያሉ ማቅረብ ይችል እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ ይኼ ቀላል ጉዳት ሳይሆን ትልቅና የመንግሥት ተቋም መሆኑን የገለጹት ጠበቆቹ፣ ባልፈረሰ ተቋም ውስጥ ተፈጽሟል የተባለ የሙስና ወንጀል አሥር ዓመት ሙሉ ዝም ሊባል እንደማይችልም አስረድተዋል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ከሌሎች ተቋማት ለየት ያለ ተቋም መሆኑን፣ ካዘዘ አዘዘ፣ ከከፈለ ከፈለ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ዝም ተብሎ የሚሠራ ሳይሆን በውል በሰነድ የታሰረ ስለሚሆን ፍርድ ቤት ማረጋገጥ ይችላል ብለዋል፡፡

አቶ ኢሳያስ መጀመርያውንም የተያዙት ምንም ዓይነት ወንጀል ሳይፈጽሙ መሆኑንና አዲስ ተገኘ በተባለውም ጥቆማ ምንም ዓይነት ወንጀል አለመፈጸሙን ተናግረዋል፡፡ ወንጀል ቢኖር ኖሮ እስካሁን ክስ ይመሠረትባቸው እንደነበርም አክለዋል፡፡ ተጠርጣሪው በትልቅ ተቋም ውስጥ ትልቅ ኃላፊነት የነበራቸው በመሆናቸው ጥፋተኛ ከመባላቸው በፊት ተከብረው መያዝ ሲገባቸው፣ እንደ ሕፃን ልጅ እየተጎተቱ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ  ተናግረዋል፡፡ መርማሪው ኦዲት ባልተደረገና ባልተጠና ጉዳይ ላይ ደምድሞ ተጨማሪ ምርመራ ላይ መድረሱም አስገራሚ እንደሆነባቸውም ገልጸዋል፡፡ ተጠርጣሪው ላይ ሕገወጥ እስር እየተፈጸመ መሆኑን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጭምር ማረጋገጡን ጠበቆቹ ጠቁመው፣ ከሕገወጥ እስር የሚያድናቸው ፍርድ ቤቱ እንጂ የጠበቆች መከራከርም ሆነ አለመከራከር ዋጋ እንደሌለው መረዳታቸውን አክለዋል፡፡

ከዚህ በላይ ማሰቃየት ብቀላ በመሆኑ ወንጀል በሌለበት ሁኔታ ታስረው እያሉ፣ የዋስ መብታቸው እንዲከበርላቸው የሚል ክርክርም ሆነ ጥያቄ እንደማያቀርቡ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ጥቆማ እንደደረሰው እንጂ፣ ጠቋሚው ከተጠርጣሪ ጋር ፀብ ይኑረው አይኑረው፣ ይተዋወቁ አይተዋወቁ፣ ሰነድ ይኑረው ወይም አይኑረው ሳያረጋግጥ ማሰር ሕገወጥ እስር መሆኑን ደጋግመው ተናግረዋል፡፡ የሕግ ሥርዓቱን ለማሻሻልና ዜጎች በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ እምነት እንዲኖራቸው ብዙ ነገር እየተሠራ መሆኑ በሚገለጽበት በዚህ ወቅት፣ አንድ ዕርምጃ ወደ ፊት ሦስት ዕርምጃ ወደኋላ›› መጎተት እንደሌለበት ተናግረዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ለፍትሕ ሥርዓቱ ተገልጋይ አመኔታ የሚገኝበት ፍትሕ እንዲሰጥላቸው በመጠየቅ ክርከራቸውን ጨርሰዋል፡፡

ጠበቆቹ ባቀረቡት ክርክር ላይ ምላሽ የሰጠው የፌዴራል መርማሪ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ፖሊስ ኃይል ይጠቀማል፣ እንደ ሕፃን ልጅ በመጎተት ተጠርጣሪን ያንገላታል የሚባሉ ቃላት የሕግ ደጋፊ ከሚባሉ ጠበቆች የማይጠበቅ በመሆኑ እንዲገሰፁ ጠይቋል፡፡ ተጠርጣሪውን የያዛቸው ለጥርጣሬ የሚያበቃ መነሻ ስላለው በመሆኑ፣ የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የመርማሪ ቡድኑን መዝገብ በአዳር አስቀርቦ ሲመረምረው፣ በተጠርጣሪው ላይ የቀረበውን የወንጀል ጥርጣሬ የሚያሳይ ሰነድ አለማግኘቱንና ጠቋሚ ምስክር የተባለውም ግለሰብ የሚናገረው በስሚ ስሚ በመሆኑ የመርማሪውን መከራከሪያ ሐሳብ እንዳልተቀበለው በመግለጽ፣ ተጠርጣሪ የ50 ሺሕ ብር ዋስትና በማስያዝ ከአገር እንዳይወጡ ለሁለተኛ ጊዜ ትዕዛዝ በመስጠት ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡

በሥር ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ቅር የተሰኘው የፌዴራል መርማሪ ፖሊስ ዓርብ የካቲት 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብሏል፡፡ በዕለቱ ዳኞች ሊሟሉ ባለመቻላቸው ለየካቲት 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡        FacebookTwitterLinkedInShare

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 5 years ago on February 17, 2019
  • By:
  • Last Modified: February 17, 2019 @ 5:15 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar