www.maledatimes.com አርበኞች ግንቦት ሰባት አመራር አካል አቶ ነአምን ዘለቀ የድርጅቱን መልቀቂያ አስመልክቶ ያቀረቡት ሃሳብን ይዘናል ! - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Addis Admas  >  Current Article

አርበኞች ግንቦት ሰባት አመራር አካል አቶ ነአምን ዘለቀ የድርጅቱን መልቀቂያ አስመልክቶ ያቀረቡት ሃሳብን ይዘናል !

By   /   March 18, 2019  /   Comments Off on አርበኞች ግንቦት ሰባት አመራር አካል አቶ ነአምን ዘለቀ የድርጅቱን መልቀቂያ አስመልክቶ ያቀረቡት ሃሳብን ይዘናል !

    Print       Email
0 0
Read Time:6 Minute, 50 Second

ለአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ አባላት፣ የሰራዊት አባላት፣ ደጋፊዎችና፣ በልዩ ልዩ መደረኮች ለምታውቁኝ ኢትዮጵያውያን በሙሉ፦
ከአቶ ነዓምን አለቀ

በሀገራችን የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የአርበኞች ግንቦት 7 የዴሞክራሲና የአንድነት ንቅናቄ አመራር አባላት በጁላይ ወር 2018 በአሜሪካን ሀገር ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ጋር በተደረገ ስብሰባ ላይ ከተደረሱት የስምምነት ነጥቦች መካከል አንዱ የአግ7 ንቅናቄ ሰራዊት ከኤርትራ በርሃና ከሀገር ውስጥም የነበሩት የአግ7 ታጣቂዎች ወደ ሀገር ወደ ሰላማዊ ኑሮ መመለስና ማቋቋምን የሚመለከት ነበር።

በዚህም መሰረት በኤርትራ የነበሩ የንቅናቄው ሰራዊት አባላት እንዲሁም በየበረሃው የነበሩ የንቅናቄው ታጣቂዎች ወደ ልዩ ልዩ ካምፖች በየጊዜው እንዲገቡ መደረጉ ይታወቃል። በብዙ መቶ የሚቆጠሩ የንቅናቄው አባላትም ከልዩ ልዩ እስር ቤቶች ቀደም ሲል በተከታታይም እንደተለቀቁ ይታወቃል። በሃላፊነት ስመራ በቆየሁት በውጪው ዘርፍ ስር የማህበራዊ ፈንድ ኮሚቴ እንዲቋቋም በማድረግ በውጭው አለም በሚገኙ በንቅናቄው አባላት፣ በደጋፊዎች፣ እንዲሁም አገር ወዳዶች ትብብር መጠነ ሰፊ ገንዘብ በማሰባሰብ በየእስር ቤቱ የነበሩት ተጋዮች ለሶስት ተከታታይ ወራት እንዲረዱ እንዲሁም ከኤርትራ በረሃ ለመጡትና በካምፕና ከካምፕ ውጭ ለሚገኙትም በልዩ ልዩ መንገዶች እርዳታዎች እንዲያገኙ ለማድረግ ተችሏል።

ከኤርትራ በረሃ ወደ አገር ቤት እንዲገቡ የተደረጉትን የአርበኞች ግንቦት 7 የቀድሞ ታጣቂዎች እንዲሁም የሌሎች የፓለቲካ ድርጅቶች ታጣቂዎችን መልሶ የማቋቋሚያ ፕሮጄክት ጽ/ቤት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ስር ከ 7 ወራት በፊት የተመሰረተ ሲሆን የውጭ መንግስታትም በተለይም የጀርመን መንግስት ለዚሁ የሚውል ገንዘብ ለመስጠት ከበርካታ ወራት በፊት ተስማምተው ነበር። ሆኖም ከተቋቋመው ጽ/ቤት አቅም ማነስ እንዲሁም ጉዳዩ ተገቢውን ውሳኔዎች ሳያገኝ እየተጓተተ በመቆየቱ ሳቢያ የአርበኞች ግንቦት 7 ሰራዊት አባላት (በተለይም ከካምፕ ውጪ እንዲቆዩ ተደርገው መልሶ የማቋቋሚያ ድጋፍ እንዲጠብቁ የተነገራቸው ጭምር ) ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸው ለህሊና እረፍት በሚነሳ ሁኔታ ውስጥ እራሴን አግኝቼ ነበር።

የንቅናቄው ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እንዲሁም ዋና ጸሃፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ችግሩ መፍትሄ እንዲያገኝ በየጊዜው ከጠቅላይ ሚንስትሩና ከሌሎች የመንግስት ሃላፊዎች ጋር የሚያደርጉት ግንኙነትና ክትትል እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በችግር ላይ የነበሩ የሰራዊት አባላት ሁኔታ አየተደራረበ የጭንቀት ድምጾች እየተበራከቱ በመምጣታቸው፣ ይህ ጉዳይ የንቅናቄውን ሊቀመንበርና ዋና ጸሐፊውን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን አባላትና ሰራዊቱ የመረጡን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን በሙሉ በተናጠልም ሆነ በጋራ የሚያስጠይቅ ፣ ለሰራዊቱም ሆነ ለአባላት ሃላፊነት አለብን በሚል መንፈስ ይህ ለውጡን ለሚመራው መንግስትም የጸጥታና የፓለቲካ ችግር የሚፈጥር ሁኔታ፣ ከሞራልም ሆነ ከፓለቲካ እኳያ የንቅናቄውንም ውስጣዊ ጤንነት እየተፈታተነ የነበረ ትልቅ ችግር እየሆነ በመምጣቱ፣ ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጥ እርዳታ ለመስጠት ቃል ከገቡና ለመርዳት ፈቃደኛ ከሁኑ መንግስታት በተለይም ከጀርመን አምባሳደር፣ ከስዊድን መንግስት ሃላፊዎችና የፓርላማ አባላት፣ ከልዩ ልዩ የመንግስት ሃላፊዎችና ከመንግስት መዋቅር ውጭ የሚገኙ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሚቀርቡ ግለሰቦች ጋር በመገናኘት ለማስረዳትና መፍትሄ እንዲያገኝ የበኩሌን አስተዋጽዖ ለማድረግ ጥረቶች ሳደርግ ቆይቻለሁ።

ብዙ ዝርዝሮች ያሉትና ወራት ያስቆጠረ ሂደት ቢሆንም ፣ በዚህ አጋጣሚ ለዚህ ችግር መፍትሄ በማፈላለግ ሊያዳምጡን በራቸውን ለከፈቱ የልዩ ልዩ የመንግስት ተቋማት ሃላፊዎች፣ በተለይም የብሄራዊ አደጋና መከላከል ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ፣ አምባሳደር ብርቱካን፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት አማካሪ አምባሳደር ግርማ ብሩ፣ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ፣እንዲሁም ከመንግስት መዋቅር ውጭ ያሉና ከለውጡ በኋላ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ሊያገኙን እንደሚፈልጉ በላለቤቴ በኩል መልክት የላኩብኝ የጠቅላይ ሚኒስሩ የአርቅ ኮሚቴ አባል አቶ ብርሃን ተድላ፣ በበርካታ የህዝብና የሀገር ጉዳዮች ያላሰለሰ አስተዋጽኦ የሚያደርጉትና የረጅም ጊዜ ወዳጄ ለሆኑት ዶ/ር አምባሳደር ካሳ ከበደ፣ በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥተው ለመርዳት ለተንቀሳቀሱት፣ በእርዳታና በመልሶ ማቋቋም ከፍተኛ ልምድና እውቀት ያላቸው ለሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ፣ እንዲሁም ለመለሶ ማቋቋም የተቋቋመው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ኣፍሪድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ ይልማ ፣ ሌሎችም ለችግሩ መፍሄ ለማግኘት ያገኙሁዋቸውን ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ሁሉ እስከአሁኑ ቀን ድረስ ለከፍተኛ ችግር ተዳርገው በሚገኙት የሰራዊት አባላት ስም ምስጋና ሳላቀርብ አላልፍም፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ትላንት ከለውጡ በፊት እንኳን እነሱን ደጅ ልንጠና ቀርቶ አጠገባቸው ለመድረስ እንኳን የምንጸየፋቸው፣ የተቀመጡበት የሃላፊነትና የአማካሪነት ቦታ የሀገርና የህዝብ ችግሮች ለመፍታት መሆኑ እምብዛም የሚያስጨንቃቸው የማይመስሉ፣ ራሳቸውን የኮፈሱ አድርባዮች፣ ከንቱና ግብዝ የመንግስት በለሟሎች በዚህ ሂደት ለመታዘብ ችያለሁ።

የሆነ ሆነ ይህ ከፍተኛ ችግር መፍትሄ እንዲያገኝና በውጭ የሚገኙትም ሆኑ በካምፕ ውስጥ የሚገኙት የንቅናቄያችን ሰራዊት አባላት ቢያንስ አቅም ባለው፣ ሰራዊቱ የሚገኝበትን ችግር ለማቃለል ብቃትና ተቋማዊ ቁመና ለአመታት ባካበተ የመንግስት ኮሚሽን በኩል እንዲሆን የሚያስችል እርምጃ እንዲወሰድ በቅርብ ቀን መወሰኑን አዲስ አበባ በነበሩኩባቸው ኣራት ሳምንታት ከሚመለከታቸው የመንግስት ሃላፊዎች ጋር በተደረገ ውይይት አረጋግጫለሁ። ይህም እርምጃ ለወራት የቆየን ከባድ የህሊና ሸክም ያቃለለ ቢሆንም፣ አሁንም ከካምፕ ውጭ የሚገኙ የሰራዊቱ አባላት የሚገኙበትን ዘርፈ ብዙ ማህበራዊ ችግሮች እስመልክቶ በየዕለቱ በርካታ መረጃዎች እየደረሰን በመሆኑ ከካምፕ ውጭም ሆነ ከካምፕ ውስጥ የሰራዊቱ አባላት ቃል የተገባላቸው እርዳታ እንዲደርሳቸው ፣ የመልሶ ማቋቋሙ ሂደት በቶሎ እንዲጀመር፣ የንቅናቄው የስራ አፈጻሚ ኮሜቴ እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት ሃላፊዎች የሚያስፈልገው ያልተቋረጠ ትኩረትና ክትትል እንዲያደርጉ በድጋሚ ለማሳሰብ እወዳለሁ።

አገራችን ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶችና ህልውናዋን የሚፈታተኑ ስጋቶች የተጋረጡባት ከመሆኗም በሻገር ከምንጊዜውም በባሰ መልኩ መስቀለኛ መንገድ ላይ የምትገኝ መሆኑን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጱያዊያን ዜጎች ሁሉ የሚስማሙ ይመሰለኛል። ይህን አደጋ ለመቋቋም ደግሞ በርካታና ዘርፈ ብዙ ሕዝብ አቀፍ እንቅስቃሴዎች ያስፈልጋሉ። ስለዚህም ውስብስብ በሆኑና ስር በሰደዱ መጠነ ሰፊ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፓለቲካዊ ችግሮች አውድና ከባቢ ውስጥ ተዘፍቀው ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ፣ ፍትህና፣ የህግ የበላይነትን ለማስፈን እየተደረገ በሚገኘው የለውጥ ጅማሮ እንዳይቀለበስ የለውጡን አራማጆች፣ ለውጡን ለማስቀጠል በተጨባጭ እርምጃዎች እስከተንቀሳቀሱ ድረስ ማገዝ አማራጭ የሌለው ነው ብየ አምናለሁ።

ሀገራችንን ቅርጫ ለማድረግ ሲሉ የ100 ሚሊዮን ህዝብ እጣ ፈንታ ላይ ቁማር የሚጫወቱ፣ የህዝብን የተሻለ ህይወት፣ ለሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች የታገሉለትን፣ የሚመኙትን ፍትህ፣ ነጻነትና የነገን ተስፋ እየረጋገጡ የሚገኙ እጅግ ራስ ወዳድ፣ ስግብግብ ህሊና ቢሶች፣ የኢትዮጵያን ልዩ ልዩ ማህበረሶቦች አብሮነት አጥፍተው ለራሳቸው ጠባብ ብሄረተኝነት እጀንዳ ጥቅምና ስልጣን ለማምጣትም ሆነ ለማስቀጠል በየአካባቢው ትርምስ የሚፈጥሩ፣ ክቡር የሆነውን ሰብአዊነት ረግጠው ወደ አራዊትነት በተጠጋ የለየለት ጽንፈኝነትና አክራሪነት የታወሩ ጥቂቶች፣ ከራሳቸው ግላዊ ፍላጎትና ጥቅም ውጭ ለሕዝብና የሀገር ደህንነት፣ ለሰላም፣ ለፍትህና፡ ለህግ የበላይነት ምንም ቁብ የማይሰጡ የጥፋት ሃይሎች በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች እንደአሸን በፈሉበት ሁኔታ ከኢትዮጵያዊነት ውጪ፣ ከፍትህ፡ ከእኩልነትና፣ ከሕዝብ አብሮነት የተለየ ሌላ አማራጭ እንደሌለ፣ ሌላ ሀገር፣ ሌላ ምድርም አለመኖሩን በሚገባ የተረዱ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ሁሉ በየአካባቢያቸው እያፈጠጠ፣ እያገጠጠ ከሚገኘውን የህልውና አደጋ ከእነዚህ አክራሪና ጽንፈኛ የጥፋት ሃይሎች ሊያመጡት ከሚችሉት ፣ የሀገራችንን የመኖር አለመኖር ህልውና የሚፈታተን የሲኦል ጎዳና ራሳቸውን፣ ቤተስባቸውንም ለመከላከል፣ ተከላካይ በሆነ መልኩ እርስ በእርስ መደራጀት፣ እንዲሁም ራስን በራስ ማደራጀትና፣ ብሎም ነቅቶ መጠበቅ ሌላው አስፈላጊና ወቅታዊ ተግባር ነው ብዬ አምናለሁ።

ለአገራችን ሕልውና፣ ለሕዝባችን ሰላም፣ ፍትሕና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሰፈነባት ኢትዮጵያ እንድትኖር የሚያስችል የፓለቲካ ስርዓት እንዲረጋገጥ የሚጨነቁ ኢትዮጵያውያን ሁሉ እልህ አስጨራሽ ሁኔታ ውስጥ ብንገኝም ከዚህም ከዚያም የሀገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ እየጣሉ የሚገኙ አክራሪና ጽንፈኛ ብሄረተኞችና የለውጥ ቅልበሳ ቡድኖች ወጥመድ ሰላባ ላለመሆን በስልት፣ በሰከነ ጥበብና በሃገራዊ ሃላፊነት መንቀሳቀስ የግድ ነው ብዬ አምናለሁ። ለኢትዮጵያዊነት፣ ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን ዜጎች እኩልነትና ሁለንተናዊ መብቶች የቆሙ የፓለቲካ ሃይሎች፣ የሲቪክ ተቋማት፣ እንዲሁም የፕሬስ ድርጅቶችን ማጠናከር እንዲሁ ሌላቅ የወቅቱ ዐቢይ ተግባራት ይመስሉኛል።

በሀገራችን የተጀመረው ለውጥ ከመጣ ከጥቂት ወራት በኋላ ንቅናቄው የፓለቲካ ፓርቲ እንደሚሆን ስምምነት በተደረሰ ጊዜ የፓለቲካ ፓርቲ አመራርም ሆነ አባል ሆኜ ለመቀጠል ፍላጎት እንደሌለኝ በአመራሩ ላይ ለሚገኙ ሁሉ በተላያዩ ጊዜያት ገልጨ ነበር። እስካሁንም ድረስ የቆየሁት ከመሪዎች አንዱ ሆኜ እንዳገለግል ለመረጡኝ አባላትና የሰራዊት አባላት ባለኝ ሃላፊነትና ተጠያቂነት ቢያንስ ከኤርትራ በርሃና በኢትዮጵያም ውስጥ ሆነው በጨለማው ዘመን ለኢትዮጵያ አንድነትና ለህዝብችን ነጻነት ህይወታቸውን ለመገበር ለቆረጡ እነዚህ ዛሬ በካምፕ ውስጥና ከካምፕ ውጭ የሚገኙ የሰራዊት አባላትና ታጋዮች ህይወት ተገቢውን መስመር እስኪይዝ ነበር።

ቀደም ሲል መልቀቂያ አስገብቸ የነበረ ቢሆንም እንኳን የንቅናቄው ዋና ጸሀፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ የተለያዩ የንቅናቄው አመራሮች በሀላፊነቴ እንድቆይ በነበራቸው ፍላጎት፣ እኔም ከነሱ ጋር ባደረኳቸው ውይይቶች በቦታው መቆየቴ ሰራዊቱን ይጠቅማል ብየ ስላመንኩ እስካሁን ድረስ በተሰጠኝ የሃላፊነት ቦታ ላይ የምችለውን እያገዝኩ ቆይቻለሁ። ሆኖም ለቆሙለት አላማ ፣ ለንቅናቄያቸውና ለሀገራቸው ክብር መተኪያ የሌላት ህይወታቸውን ለመክፈል የቆረጡ የትግል ጓዶቸ ላለፉት 7 ወራት በከፍተኛ ችግሮች ውስጥ ወድቀው ማየት ለኔ እንቅልፍ የሚነሳ ጉዳይ መሆኑ አልቀረም።

ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ለዴሞክራሲና ለኢትዮጵያ ህዝብ ሁለንተናዊ መብቶች መረጋገጥ የበኩሌን አስተዋጽኦ ሳደርግ ቆይቻለሁ። በአለፉት ሁለት አስርት አመታት በላይ በውጭው አለም በተደረገው ትግል ልዩ ልዩ የትግል መድረኮችን በመስራችነት፣ በአባልነት፣ በአስተባባሪነት፣እንዲሁም በአመራር ሃላፊነቶች የዜግነት ግዴታዬን ከሚጠበቅብኝ በላይ አስተዋጽኦ በማድረግ ለ26 አመታት ያልተቋረጠ የትግል አስተዋጽኦ አድርጌያለሁ። የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥንን(ኢሳት) በማቋቋም፣ በመገንባት ሂደትና እስከ 2015 ድረስም በዋና ስራ አስፈጻሚነት ፣ እሰከአሁኑ ድረስም በቦርድ ስራ አስፈጽሚ አባልነት የበኩሌን አስተዋጽኦ ተወጥቻለሁ።

ባለፉት 8 አመታት የአርበኞች ግንቦት 7 የአንድነትና ለዴሞክራሲ ንቅናቄ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና ልዩ ልዩ የስራ ሃላፊነቶች ላይ በመሰማራት፣ ከመስከረም ወር 2017 ከተደረገው የንቅናቄው ጉባኤ ላይ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆኜ ከተመረጥኩኝ በኋላም የንቅናቄው የውጪው ዘርፍ ሃላፊ በመሆን እስካሁን ድረስ በቅንነትና በምችለው እቅም ሃላፊነቴን ተወጥቻለሁ። በአሁኑ ወቅት ከአርበኞች ግንቦት 7 የስራ አስፈጻሚ ኮሜቴ አባልነት ፣ እንዲሁም ንቅናቄው የውጭ ዘርፍ ሃላፊነት በገዛ ራሴ ፈቃድ መልቀቄን ለአርበኞች ግንቦት 7 አባላት፣ ደጋፊዎች፣ በልዩ ልዩ የትግል መድረኮች ለምታውቁኝ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ለማሳወቅ እወዳለሁ።

የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ በቅርብ ጊዜ ጉባኤ በማድረግ ይከስማል። አዲስ ሀገራዊና በኢትዮጵያዊነት፣ በዜግነትና በማህበራዊ ፍትህ ላይ የቆመ የፓለቲካ ፓርቲ የምስረታ ሂደት ወደ ማገባደጃው በመድረሱ በአዲሱ ፓርቱ ለሚመረጡ አመራሮች እንዲሁም አባላትና ደጋፊዎች ሁሉ ያለኝን ጽኑና መልካም ምኞቴን እገልጻለሁ። ለወደፊቱ ለኢትዮጵያ ሀገራችን እንዲሁም ለህዝባችን ፋይዳና ጥቅም በሚያስገኙ ልዩ ልዩ ተግባራት ላይ በመሳተፍ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ድርሻዬን እንደምወጣ ለምታከብሩኝ፡ ለምትወዱኝና ለማከብራችሁና ለምወዳችሁ ወገኖቼ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ለማረጋገጥ እወዳለሁ።

እዚህ ላይ የንቅናቄው ወዳጆችም ሆናችሁ ሌሎች እንድታውቁት ላሰምርበትም የምፈልገው በንቅናቄው አጠቃላይ የፓለቲካ ራዕይና ተልእኮ፣ በሚመሰረተው የፓለቲካ ፓርቲ አላማና ተልዕኮ፣ እንዲሁም ከማንም የንቅናቄው አመራር አባላት ጋር በግል ሆነ በፓለቲካ ምንም አይነት ቅራኔ የሌለኝ መሆኑን ለማረጋገጥ እወዳለሁ።

ዘለአለማዊ ክብርና ሞገስ ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ለህባችን ነጻነትና፣ ለፍትህ ሲሉ አይተኬ የህይወት መስዋእትነት ለከፈሉ የኢትዮጵያ ልጆች ሁሉ!

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

ነአምን ዘለቀ ቦጋለ

ቨርጂኒያ ፣ ዮናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ፡ ማርች 18 ቀን፣ 2019

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

♦ “ ትክክለኛ ፍትሕ አይሰጡም” የተባሉት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ከችሎት እንዲነሱ ተጠየቀ !

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar