www.maledatimes.com የመንግስት አፈና የሚበዛው በትግራይ ነው ወይስ በአማራው ተወላጅ ወይንስ በሌላው ዘር ላይ ?አብርሃ ደስታ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የመንግስት አፈና የሚበዛው በትግራይ ነው ወይስ በአማራው ተወላጅ ወይንስ በሌላው ዘር ላይ ?አብርሃ ደስታ

By   /   March 7, 2014  /   Comments Off on የመንግስት አፈና የሚበዛው በትግራይ ነው ወይስ በአማራው ተወላጅ ወይንስ በሌላው ዘር ላይ ?አብርሃ ደስታ

    Print       Email
0 0
Read Time:19 Minute, 15 Second

“‘አብርሃ የመሃል አገር ሰዎችን ለማስደሰት ሲል የትግራይን ህዝብ ችግር በትግርኛ ከመፃፍ ይልቅ በአማርኛ ይፅፋል። የሚመረጠው በትግራይ ሁኖ ሳለ የሚሰራው ግን ለኢትዮጵያውያን ነው’ የሚል አስተያየት ይሰጣል። ምን ትላለህ?” የሚል አስተያየት ደረሰኝ።

ብዙ ግዜ የምፅፈው ስለ ትግራይ ህዝብ ችግር ነው። ግን በአማርኛ ነው የምፅፈው። አዎ! በትግራይ ህዝብ ችግር (ዓፈና) ላይ የማተኩርበት ምክንያት በትግራይ ብዙ ያልተጋለጡ ዓፈናዎች፣ በደሎች መኖራቸው ስለማውቅ ነው። በሌላ ክልል ዓፈናና በደል የለም ማለቴ አይደለም። አለ። ነገር ግን (አንደኛ) በትግራይና በሌሎች ክልሎች የተወሰነ ልዩነት አለ። በሌላ ክልል ዓፈና ሲደርስ የደረሰውን በደል የሚያጋልጡ ጎበዝ ጋዜጠኞች አሉ። በሌሎች ክልሎች በደል ሲፈፀም የመጋለጥ ዕድሉ ሰፊ ነው። በትግራይ ያሉ ጋዜጠኞች ግን የህዝብን ችግር በማጋለጥ ህዝብን ከማገልገል ይልቅ ገዢውን መደብ በመደገፍ ራሳቸው በኢኮኖሚ መበልፀግ ይመርጣሉ። ለህዝብ የቆመ የትግራይ ጋዜጠኛ አላየሁም። አሁን ግን ብዙ የትግራይ ሙሁራን የትግራይን ችግር በፌስቡክ እያጋለጡ ይገኛሉ። አሁን ትግራይ በጥሩ ደረጃ ትገኛለች (ዓፈናን በማጋለጡ ዘርፍ)። ዕድሜ ለፌስቡክ ጓደኞቼ።

(ሁለተኛ) ጨቋኞቹ ባለስልጣናት ትግርኛ ተናጋሪ እንደመሆናቸው መጠን በትግራይ ህዝብ ላይ የሚደርስ በደል እንደሌለ ተድርጎ ሊታሰብ እንደሚችል በመገንዘብ ነው። ስርዓቱ ለትግራይ የቆምኩ ነኝ እያለ ትግራይን ክፉኛ እንደሚበድል ላይታወቅ ወይ ላይጠረጠር ይችላል። ስለዚህ የትግራይን ህዝብ በደል ካልተጋለጠ በደል እንደሌለ ሊቆጠር ይችላል። በደል እንደሌለ ከተቆጠረ ህዝቡ እንደተበደለ ይቀጥላል። ችግሩ ካልተጋለጠ መፍትሔ አያገኝም። መፍትሔ ካላገኘ ህዝቡ ይጨቆናል። ህዝቡ ከተጨቆነ ነፃነት ያጣል። ነፃነት ካጣ ይዳከማል። ከተዳከመ አያድግም። ካላደገ ከድህነት አይላቀቅም። ከድህነት ካልተላቀቅ የገዢዎች ማጫወቻ ይሆናል። ይህም ያሳምማል። ስለዚህ የትግራይ ህዝብ ችግር መጋለጥ አለበት።

የመሃል አገር ሰዎች (ሌሎች ኢትዮጵያውያን ለማለት ተፈልጎ ከሆነ) የትግራይ ህዝብ ችግር ሲጋለጥ የሚደሰቱ ከሆነ በትክክል የትግራይ ህዝብ ወዳጆች ናቸው ማለት ነው። የትግራይን ህዝብ ችግር ሲጋለጥ የሚናደዱ የህወሓት ካድሬዎች ብቻ ናቸው። ምክንያቱም የህዝብ ችግር ሲጋለጥ ገመናቸው ነው አብሮ የሚጋለጠው። ጨቋኝነታቸው ሲጋለጥ የስልጣን ዕድሜያቸው ያጥራል። የህወሓት ካድሬዎች ሃይማኖታቸው ስልጣን እስከሆነ ድረስ የትግራይ ህዝብ ችግር ሲነሳ ይደነግጣሉ፣ ይፈራሉ። በደላቸው እንዲጋለጥ አይፈልጉምና። አንድ ህዝብ የሌላን ህዝብ ችግር ከተጋራ ለህዝቡ ያለውን ድጋፍ፣ አብሮነት እያሳየ ነው ማለት ነው።

“የሚመረጠው በትግራይ ሁኖ ሳለ ለኢትዮጵያውን ነው የሚያገለግለው” የሚል ሐሳብም ተነስቷል። ኢትዮጵያውያንን ባገለግላቸው ደስተኛ ነኝ። እንዳውም ከኢትዮጵያውያን አልፎ አፍሪካውያን፣ ከአፍሪካውያን አልፎ የዓለም ህዝብ ባገለግል ደስታው አልችለውም። ግን ባለኝ የዓቅም ዉሱንነት ምክንያት እስካሁን የምፅፈው ስለ ትግራይ ህዝብ ብቻ ነው።

ዓላማዬ ህዝብን ማገልገል ነው (ፖለቲካ ስለሆነ ብቻ አይደለም)። የህዝብ ነፃነት እንዲከበር እጥራለሁ። የህዝብ ነፃነት የሚከበረው ዴሞክራሲ ሲኖር ነው። ዴሞክራሲ የሚኖረው የህዝብ ድምፅ ሲከበር ነው። የህዝብ ድምፅ የሚከበረው ፍትሐዊ ምርጫ ሲኖር ነው። ፍትሓዊ ምርጫ የሚኖረው አማራጭ የፖለቲካ ፓርትዎች ሲኖሩ ነው። ፓርቲዎች ከሌሉ አማራጭ የለም። አማራጭ ከሌለ ምርጫ የለም። ምርጫ ከሌለ የህዝብ ድምፅ የለም። የህዝብ ድምፅ ከሌለ የህዝብ ስልጣን የለም። የህዝብ ስልጣን ከሌለ ዴሞክራሲ የለም። ዴሞክራሲ ከሌለ ነፃነት የለም። ነፃነት ከሌለ ትርጉም ያለው ህይወት የለም።

ህዝብ ለነፃነቱ ሲል የስልጣን ባለቤት መሆን አለበት። የስልጣን ባለቤት ለመሆን አማራጭ የፖለቲካ ሐሳቦች ያስፈልጉታል። ስለ ተለያዩ የፖለቲካ ሐሳቦች በቂ መረጃ ሊኖረው ይገባል። በቂ መረጃ እንዲኖረው ነፃና ገለልተኛ ሚድያ መኖር አለበት። ያለ ገለልተኛ ሚድያ ዴሞክራሲ እውን ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም ህዝብ ከጭቆና ለማዳን ከፈለገን ማስተማር አለብን። ህዝብ ሲያውቅና ሲደራጅ ብቻ ነው መብቱንና ነፃነቱን መጠየቅ የሚችለው። ስለዚህ የኔ ዓላማ ህዝብን ማስተማር ነው። የማድረገውን ይህንን ነው።

ዓላማዬ መመረጥ አይደለም። ስልጣን መያዝ አይደለም። ህዝብን የማስተምረው ለመመረጥ ቢሆን ኑሮ በተለያዩ አከባቢዎች አልንቀሳቀስም ነበር። ምክንያቱም ለመመረጥ አንድ ኮንስቲቱወንሲ በቂ ነው። እንበልና ለመመረጥ እፈልጋለሁ። የሚመርጠኝ ህዝብ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው። በኢዮጵያውያን ካልተመረጥኩ በትግራይም አልመረጥም። ምክንያቱም በኢትዮጵያውያን አትመረጥም ከተባልኩ ‘እነሱ ድምፅ አይሰጥሁም’ እየተባልኩ ነው። ኢትዮጵያውያን ድምፅ ካልሰጡኝ ትግራዮችም ድምፅ አይሰጡኝም። ምክንያቱም ኢትዮጵያ አንድ የምርጫ ጣብያ አይደለም፤ ትግራይም አንድ የምርጫ ጣብያ አይደለም። ወደ ድምፅ ቆጠራ ከገባን እኔ ልወዳደር የምችለው (ከተወዳደርኩ ማለቴ ነው) በአንድ ወረዳ ብቻ ነው። ስለዚህ ዓላማዬ ለመመረጥ ከሆነ በአንድ ወረዳ ብቻ መንቀሳቀስ በቂ ነው ማለት ነው። ትግራይ አንድ ወረዳ አይደለችም። ስለዚህ ዓላማዬ ለመመረጥ ብቻ እስካልሆነ ድረስ በሁሉም የኢትዮጵያ አከባቢዎች እዞራለሁ፣ አስተምራለሁ።

ስለ ቋንቋ ጉዳይም ተነስቷል። እኔ የምፅፈው በአማርኛ ነው። ወላጆቻችን በቋንቋችን እንድንናገር ታግለዋል ምናምን የሚል ነገር ይነሳል። ወላጆቻችን የታገሉት የቋንቋ ነፃነታችንን ለማስከበር ነው። የቋንቋ ነፃነት አለ የሚባለው አንድ ሰው ያለምንም ተፅዕኖ በመረጠው ቋንቋ በፈለገው ግዜና ቦታ መጠቀም ይችላል ማለት እንጂ ገዢዎችን በመረጡለት ቋንቋ ብቻ እንዲናገር ይገደዳል ማለት አይደለም። በፈለኩት ቋንቋ መናገር እችላለሁ። በትግርኛ ወይ በሌላ ቋንቋ የመናገር መብት አለኝ፤ ማንም አይከለክለኝም።

በመረጥኩት ቋንቋ እናገራለሁ። ቋንቋ የሚመረጠው አንባቢዎች መሰረት በማድረግ ነው። ለትግራይ ሰዎች ብቻ የሚፃፍ ከሆነ በትግርኛ ይፃፋል። ምክንያቱም በትግርኛ ቋንቋ በመፃፍ አንድን መልእክት ለትግራይ ሰዎች ማስተላለፍ ይቻላል። መልእክቱ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን እንዲዳረስ ተፈልጎ ከሆነ ደግሞ በአማርኛ ይፃፋል፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን አማርኛ ያነባሉ (የትግራይ ሰዎችም ጭምር)። ምክንያቱም በትግርኛ ከተፃፈ ከትግራይ ዉጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን አያነቡትም። ምክንያቱም ትግርኛ አይችሉም። ለዓለም ህዝብ ከሆነ ደግሞ በእንግሊዝኛ ይፃፋል። ምክንያቱም ማንበብ እንዲችሉ። የአፍ መፍቻ ቋንቋዬ ትግርኛ ስለሆነ ብቻ ለሌሎች ኢትዮጵያውያን ወይ የዓለም ህዝቦች በትግርኛ መፃፍ አለብህ ተብዬ አልገደድም።

የትግራይ ችግር በአማርኛ የምፅፍበት ምክንያት የትግራይ ችግር ሁሉም ኢትዮጵያውያን እንዲያውቁት ስለምፈልግ ነው። ምክንያቱም የትግራይ ህዝብ ችግር የመላው ኢትዮጵያውያን ችግር ነው። ምክንያቱም ተጋሩ ኢትዮጵያውያን ናቸው። በተጋሩ የሚደርስ ችግር በኢትዮጵያውያን የሚደርስ ችግር ነው። ስለዚህ ሁሉም የሚመለከተው አካል ማወቅ አለበት።

በአንድ ህዝብ አንድ አከባቢ ችግር ሲደርስ ሁሉም ወገኖች በአንድነት መቆም አለባቸው። በአንድነት ለመቆም መረጃ ሊያገኙ ይገባል። በትግራይ የሚደርስ በደል ለትግራዮች ብቻ የሚተው አይደለም። ሁሉም ኢትዮጵያውያን ይመለከታቸዋል። በኦሮሞዎች፣ በአማራዎች፣ በሶማሊዎች፣ በጋምቤላዎች፣ በደቡቦች፣ በዓፋሮች፣ በሃረሪዎች፣ በቤኑሻንጉሎች ወዘተ የሚደርስ ችግር ለትግራዮች ይመለከታቸዋል። ስለዚህ የትግራይ ችግር ሌሎች ወገኖች እንዲጋሩትና ከትግራይ ህዝብ ጎን እንዲሰለፉ ከተፈለገ በአማርኛ መፃፍ አለበት (አማርኛ ይችላሉ በሚል እሳቤ ነው)።

በኦጋዴን የሚደርስ ችግር የትግራይ ሰዎች እንዲያውቁትና ከኦጋዴን ህዝብ ጎን እንዲሰለፉ ከተፈለገ የኦጋዴን ህዝብ ችግር በአማርኛ መፃፍ አለበት። የቋንቋ ነፃነት ተብሎ የኦጋዴን ህዝብ ችግር በሶማሌኛ ቋንቋ ከተፃፈ እኛ የትግራይ ሰዎች ስለደረሰው ችግር መረጃ አይኖረንም። መረጃ ከሌለን አናግዛቸውም። ካላገዝኛቸው የህዝቦች አንድነት አይኖርም። የህዝቦች አንድነት ከሌለ በያንዳንዳችን የሚደርስ በደል መታገል ይከብደናል። ምክንያቱም የአንድን ህዝብ በደል ለማስወገድ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ህዝቦች ትብብር ይጠይቃል። ጭቆና ማስወገድ የሚቻለው በትብብር እንጂ በተናጠል አይደለም።

የህዝቦችን አንድነት በማስጠበቅ ጨቋኞችን ማስወገድ እንችላለን። ትግላችን በተናጠል ካደረግነው ግን ሊከብደን ይችላል። ምክንያቱም ስለያንዳንዳችን ችግር መረጃ ካልተለዋወጥናን ካልተጋራን በአንዱ ላይ የደረሰውን በደል ሌላኛው ስለማያውቅ ላይደግፈን (ወይ ባለማወቅ ጨቋኙን ስርዓት ሊደግፍ) ይችላል። ስለዚህ ካለመተዋወቅና ካለመረዳዳት እርስበርሳችን እየተፋጀን የጨቋኞችን መሳርያ እንሆናለን።

የህዝቦች ነፃነት እንዲከበር የህዝቦች አንድነት ይኑር። የህዝቦች አንድነት እንዲኖር የጋራ መግባባት ይኑር። የጋራ መግባባት እንዲኖር ስለሚደርሱብን በደሎች መረጃ እንለዋወጥ። መረጃ ለመለዋወጥ የጋራ የምንግባባበት ቋንቋ(ዎች) ይኑረን።

ስለዚህ በአማርኛ የምፅፈው የትግራይ ችግሮች ለሌሎች ኢትዮጵያውያን ለማካፈልና የህዝቦች አንድነት ለማስጠበቅ እንጂ አማርኛ የበላይ ወይ የበታች ቋንቋ ስለሆነ አይደለም። ቋንቋ መግባብያ ነው (ከፈለጋችሁ ማንነትም ጭምር ነው በሉኝ)።

ተግባባን???

It is so!!

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 10 years ago on March 7, 2014
  • By:
  • Last Modified: March 7, 2014 @ 10:17 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar