www.maledatimes.com ሃይለማርያም ደሳለኝ – ፖለቲካዊ ሰብዕና (በዮሴፍ ደግፌ) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ሃይለማርያም ደሳለኝ – ፖለቲካዊ ሰብዕና (በዮሴፍ ደግፌ)

By   /   September 1, 2012  /   Comments Off on ሃይለማርያም ደሳለኝ – ፖለቲካዊ ሰብዕና (በዮሴፍ ደግፌ)

    Print       Email
0 0
Read Time:10 Minute, 2 Second

ሃይለማርያም ደሳለኝ – ፖለቲካዊ ሰብዕና (በዮሴፍ ደግፌ)

                  የአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ፤ አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር (?) ፖለቲካዊ ሰብእና ብዙ የሚታወቅ ባለመሆኑና፤ የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ግን በቅርብ ርቀት የሚያውቃቸው ሰው በመሆናቸው ይህችን አጭር ፅሁፍ ለመፃፍ አነሳሳኝ።
          በደቡብ ኢትዮጵያ ከሚገኙት 48 ብሄረሰቦች መካከል አንዱ የሆነው የወላይታ ተወላጅ ናቸው።  ሀይለማርያም ደሳለኝ በእምነታቸው ፕሮቴስታንት (የፔንቴኮስታል ክርስቲያን) ሲሆኑ፤ በመንፈሳዊ ህይወታቸውም የሚፀልዩና መፅሀፍ ቅዱስ የሚያነቡ ትጉህ ሰው እንደሆኑ ብዙ ሰዎች ይመሰክሩላቸዋል። ከዚህ እምነታቸውም የተነሳ ሊሆን ይችላል፤ እንደ በርካታ የአቶ መለስ ባለስልጣናት በሙስና (corruption) ውስጥ አልተዘፈቁም።
አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ለህወሃት- ኢህአዲግ የድል አጥቢያ አርበኛ ሰው ናቸው። ማለትም እንደነ አቶ መለስ ለ17 አመታት በበረሃ ታግሎ የመጣ ሰው ሳይሆን፤ ከግንቦት 20 ቀን1983 ድል በሁዋላ ኢህአዴግን በአባልነትና በደጋፊነት የተቀላቀለ ሰው በሙሉ የ”ድል አጥቢያ አርበኛ” ስለሚባል ነው።
ሀይለማርያም ደሳለኝ እድሜው በአርባዎቹ መጨረሻ ላይ የሚገኝ፤ በትምህርት ዝግጅቱም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢንጀሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪና፤ ከአውሮፓም ሁለተኛውን ዲግሪውን በኢንጂነሪንግ ዘርፍ የያዘ ሰው ነው። የሙያ ልምዱም በማስተማር፤ በኮሌጅ ሃላፊነት፤ በደቡብ ክልል አስተዳዳሪነት ወይም ፕሬዜዳንትነትና፤ በጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ በሚንስትር ማእረግ አማካሪነት እና በቅርቡም የውጭ ጉዳይ ሚንስትርና ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ዋነኞቹ ናቸው። ሰብዕናውን በተመለከተ፤ ሀይለማርያም ቅን ትሁትና ሰውን አክባሪ፤ ምሁርና ተግባቢ፤ በራሱ የሚተማመን፤ ስብሰባ ሲመራም ሆነ ሀገር ሲያስተዳድር የማይናደድ፤ የማያስፈራራና የማይደነፋ፤ ተቃራኒ ሀሳብ የሚቀበልና ባግባቡ የሚመልስ፤ የበታችነት ወይም የበላይነት ስሜት የማይሰማው፤ በአግብኦ፤ በአሽሙር ወይም በሽሙጥ የማይናገር፤ ፈገግታ የማይለየውና ለማነጋገርም የማይከብድ ሰው መሆኑን እመሰክራለሁ።

ከሁሉ በላይ ደግሞ የአቶ ሀይማርያም ትልቁ ሰብእና የኢህአዲግ ባለስልጣንም ወይም ደግሞ ጠቅላይ ሚንስትር ቢሆንም ባይሆንም፤ ራሱን ችሎ፤ በሰላምና በነፃነት ለመኖር እንደሚችል የተረዳ ሰው መሆኑ ዋናው ሲሆን፤ አንባገነን ልሁን ቢልም ለመሆን የማይችልም ይመስለኛል። በነዚህ ዋና ዋና ባህርያትና እንዲሁም አቶ መለስ ዜናዊ ኦሮሞዎችንና አማራዎችን ለጠቅላይ ሚንስትርነት ስልጣን ባለማመናቸው ምክንያት አቶ ሀይለማርያምን ወደ ቤተመንግስታቸው ያስጠጉዋቸውም ይመስለኛል።

በእኔ መረዳትና ግንዛቤ፤ የአቶ ሀይለማርያም ትልቁ ድክመት ሊሆን የሚችለው ደግሞ፤ ሀይለማርያም አፍተልታይ ፖለቲከኛ ያለመሆናቸው ጉዳይ ዋናው ይመስለኛል። ለምሳሌ፤ ከበድ ያለ ውሳኔን ለመወሰን፤ የተሸረበ ፖለቲካዊ ነገርን አለመለየት፤ የህወሐት አንባገነን ሰዎች ጫና ለመቋቋም አለመቻል፤ ሰዎችን ለማግባባት ሲሉ የመዘግየትና የመፍራት ችግር ሊኖርባቸው ይችላል የሚል ግምት አለኝ።
እንደዚሁም ነገር አዋቂና ሰንጣቂ፤ እጅ-ጠምዛዥና አስጠምዛዥ፤ ትንሽ ቢሆን ተጠራጣሪም ሰው ባለመሆናቸው ከህወሀት-ኢህአዴግ አድርባይ፤ ቀንጨራ፤ እና ተንኮለኛ ሰዎች ጋር እንዴት ተግባብተው ሊሰሩ እንደሚችሉ ሳስብ ግርታ ይፈጥርብኛል። በአጠቃላይ አቶ ሀይለማርያም ከመሪነት ይልቅ ወደ አሰተዳዳሪነት የሚያደሉ ሰው እንጂ፤ የፖለቲካ ሴራ እየሸረቡ፤ ሰኞን ማክሰኞ ነው፤ ድንጋዩን ዳቦ ነው፤ ጭለማውን ብርሀን ነው፤ እያሉ አይናቸውን አፍጥጠው እየዋሹ በስውር፤ በማስመሰል ለመኖር የሚችሉ ሰው አይመስለኝም። እንደዚህም ስል ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች ለመስራት ይቸገራሉ የሚል ስጋት ግን የለኝም።
ምንም እንኳን አቶ ሀይለማርያም ሚኒልክ ቤተመንግስት በመግባት በእናታቸው ወላይታ ከሆኑት ከአፄ ሚኒልክ ቀጥሎ ሁለተኛው የወላይታ ተወላጅ ቢሆኑም፤ ስልጣኑን በችሮታ እንጂ፤ በምርጫ ወይም በትግል ያገኙት ባለመሆኑና፤ በአሁኑ ሰአት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ስልጣን ባላንጣ ከሆነው ከህወሀት የፖለቲካ አጥር ክልል ውጪ መጫወት እንዳይችሉ ሆነው የተቀመጡ መሆናቸውን በቅርብ የምናየው ይሆናል። ይህ እውነት ከሆነም ዲሞክራሲያዊ አስተዳደርና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ እኩል የሚጠቅም አኮኖሚያዊ እድገት ለማምጣት በጣም የሚቸገሩ ሰው ስለሚሆኑ በስልጣን ላይ የሚቆዩ አይመስለኝም። አለበለዚያ በስልጣን ለመቆየትም የአቶ መለስ ዜናዊን ሰብዕና ሙበ ሙሉ መላበስ ይኖርባቸዋል። ከዚህ ውጭ ከተመለከትንና የሚሆንም ከሆነ ደግሞ እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ፈፅሞ ሊታደግ በጊዜው ያስቀመጣቸው የመጀመሪያው ረድኤተ መሪ ሆነው ብቅ የሚሉ መልዕክተኛ ሆነው ይወጡ ይሆናል።
(ዮሴፍ ደግፌ – የአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ፖለቲካዊ ሰብዕናና የአፄ ሚኒልክ ዘር ስለመሆናቸው” በሚል ርእስ ኢትዮ ሚዲያ ላይ ካሰፈረው የተቀነጨበ )
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on September 1, 2012
  • By:
  • Last Modified: September 1, 2012 @ 6:00 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar