www.maledatimes.com የፍኖተ-ነፃነት ጋዜጣ መታገድ አምባገነናዊ ስርዓቱ አፈናውን አጠናክሮና አባብሶ መቀጠሉን የሚያሳይ ድርጊት ነው!!! - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የፍኖተ-ነፃነት ጋዜጣ መታገድ አምባገነናዊ ስርዓቱ አፈናውን አጠናክሮና አባብሶ መቀጠሉን የሚያሳይ ድርጊት ነው!!!

By   /   September 4, 2012  /   Comments Off on የፍኖተ-ነፃነት ጋዜጣ መታገድ አምባገነናዊ ስርዓቱ አፈናውን አጠናክሮና አባብሶ መቀጠሉን የሚያሳይ ድርጊት ነው!!!

    Print       Email
0 0
Read Time:10 Minute, 24 Second

ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት የተሰጠ መግለጫ

አምባገነኑ የኢህአዴግ ስርዓት መሪው የሆኑት የአቶ መለስ ዜናዊን እረፍት ተከትሎ በሀገሪቱ ሊስተካከሉ የሚገባቸው የሰብዓዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሀሳብን በነፃነት የመግለጥ መብቶች ከበፊቱ በባሰ ሁኔታ ተጠናክረው በአፈና መንገድ መቀጠላቸው የሚያሳስበን ሲሆን ሀገሪቱን ወደ ባሰ ሁኔታ የሚከታት በመሆኑ በአስቸኩዋይ እንዲቆም እና የኢትዮጵያ ህዝብም እንዲታገለው አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡

ሀዘን ላይ ቆይተናል ሲሉ የነበሩ የስርዓቱ መሪዎች ለአፈናው ስርዓት መቀጠል ማሳያ የሚሆነውን ጋዜጣችንን በመዝጋት የዴሞክራሲያዊ መብቶች የአፈና ስራቸው ማማóሻ አደርገውታል፡፡ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ልሳን የሆነችው እና በተጨማሪም በኢትዮጵያ ውስጥ የነፃ ጋዜጦችን መታፈን፣ መመናመን እና ድፍረት ማጣት ተከትሎ ዘወትር ማክሰኞ ጠንካራ የፖለቲካ ትንታኔዎችንና ዜናዎችን በመያዝ ለህትመት የምትበቃው ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት የህግ አግባብ በሌለው ውሳኔ አላትምም ማለቱ ህገ ወጥ በመሆኑ በአስቸኩዋይ ይታረም በማለት የማተሚያ ቤቱን ም/ዋና ሥራ አሥፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለን ያነጋገርን ቢሆንም ስራ አስፈፃሚው በትዕቢትና በምን ታመጣላችሁ አይነት መንፈስ ‹‹ሂዱ የምትፈልጉትን አድርጉ›› በማለት ጋዜጣዋ እንደማትታተም ስነ-ስርዓት በጎደለው ንግግር የአንድነት አመራሮችን መሸኘቱ ህገ ወጥ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ የግለሰቦች አምባገነንነት እንዴት እየሰፋ እንደሄደ የሚያመላክት ተግባር ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

ከማተሚያ ቤቱ ሌላ ሃላፊ የተነገረን ፍኖተ-ነፃነት ጋዜጣ የታገደችው በማተሚያ ቤቱ የማኔጅመንት አካላት ውሳኔ ነው የተባልን ሲሆን የጠቅላይ ሚንስትሩን ሞት ተከትሎ በወጡ ዘገባዎች ደስ ስላልተሰኙ እንደሆነ ተገልፆልናል፡፡ ከምክትል ስራ አስፈፃሚው ደግሞ ‹‹ማተም የማንችለው የመፅሀፍ ጨረታ ስላሸነፍን ነው›› የሚል ተልካሻ መልስ ተሰጥቶናል፡፡ ታዲያ ከሌሎች የህትመት ውጤቶች በተለየ ያውም ማተሚያ ቤቱ ብዙ ጫና በሌለበት ማክሰኞ ቀን የምትታተመውን ፍኖተ-ነፃነትን ብቻ የሚያሣግድ ምን ምክንያት አለ? ለሚለው ዋና ጥያቄ ም/ስራ አስፈፃሚው ያላቸው መልስ ግልምጫና ‹‹ሂዱና የምታመጡትን አያለሁ!›› የሚል የትዕቢት ምላሽ ነበር፡፡

ፓርቲያችን ከተጨባጭ ምንጮች ባገኘው መረጃ መሰረት ጋዜጣችን የተዘጋችው የማተሚያ ቤቱ ሃላፊዎች በሰጡት መሰረት የሌላቸው ምክንያቶች ሳይሆን የስርዓቱ ቁንጮዎች በሆኑት ግለሰቦች ቀጭን ትእዛዝ ነው፡፡ ስለዚህ የማተሚያ ቤቱ ሃላፊዎች ያላቸው ድርሻ ትዕዛዝ ማስፈፀም ይሆናል ማለት ነው፡፡

ለህትመት ከበቃችበት ጊዜ ጀምሮ በአባላትና ደጋፊዎች ዘንድ ተወዳጅነትን በማትረፍ ተናፋቂ ለመሆን የበቃችው የአንድነት ፓርቲ ልሳን ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ እንዳትታተም በብርሃንና ሰላም የታገደችበት ሁኔታ ከጠ/ሚ መለስ ሞት ጋር የሚያያዝ ሲሆን ጋዜጣዋ የፖለቲካ ፓርቲ ልሳን እንደመሆንዋና ፓርቲው ደግሞ ያለበትን ሃገራዊ ሃላፊነት ለመወጣት የጠቅላይ ሚንስትሩን ሞት ተከትሎ በሃገሪቱ የፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ምን መልክ እንደሚኖራቸው የሚያሳይ የፖለቲካ አመራሮች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና የጋዜጣዋ ክፍል ባልደረቦች የፃፉዋቸውን ትንታኔዎች በልዩ ዕትም ዓርብ ነሐሴ 18 ቀን 2004 ዓ.ም ለንባብ ማብቃቱ ፓርቲው ለተሸከመው ሃገራዊ ራዕይ እንዴት ቁርጠኛ እንደሆነ የሚያሣይና ሃላፊነቱን እንዴት በብቃት እንደተወጣ የሚያመላክት እንደሆነ እናምናለን፡፡ ከአንድ የፖለቲካ ፓርቲ የሚጠበቀውን አድርገናል፡፡ አበረታች ስራ እንጅ የሚኮነን ሊሆን አይችልም፡፡

ይሄ የአንድነት ጥንካሬ ያልተዋጠላቸው ተተኪ አምባገነኖችም በሀገሪቱ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ተከትሎ ጠንካራ ሃሳብ ያላቸውን ኢትዮጵያውያን ለማስተናገድ እንደገና ዓርብ ነሐሴ 25 ቀን 2004 ዓ.ም  የጋዜጣ ክፍሉ በመረባረብ ስራውን አጠናቆ ያዘጋጀው ልዩ ዕትም በማገድ እንደውም ከዚህ በሁዋላ አናትምም በማለት ጋዜጣችንን አፍነዋል፡፡ አፈናቸውንም በቃል እንጅ በወረቀት አልሰጡንም፡፡ ከፊት ለፊታች አስፈሪ አምባገነን ተተኪዎች እየመጡም እንደሆነ ይጠቁመናል፡፡

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ልሳኑ በስርዓቱ አምባገነንነት ሲዘጋ ዝም ብሎ እንደማያይ ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡ ይህንን አይን ያወጣና ያፈጠጠ ተግባርም ከኢትዮጵያችን እስከሚወገድና ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲሁም ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ሳይሸራረፍ እስከሚረጋገጥ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመሆን እስከ መጨረሻው እንታገለዋለን፡፡

                 አምባገነንነት የሀገርና የህዝብ ፀር ነው!!!

           

የፍኖተ-ነፃነት ጋዜጣ መታገድ አምባገነናዊ ስርዓቱ አፈናውን አጠናክሮና አባብሶ መቀጠሉን የሚያሳይ ድርጊት ነው!!!

  አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት)

                          የህዝብ ግንኙነት

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on September 4, 2012
  • By:
  • Last Modified: September 4, 2012 @ 9:40 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar