www.maledatimes.com መልካም የእናቶች ቀን (የልጆቻችሁ እስር አንጀታችሁን ላሳሰራችሁ) ጽዮን ግርማ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

መልካም የእናቶች ቀን (የልጆቻችሁ እስር አንጀታችሁን ላሳሰራችሁ) ጽዮን ግርማ

By   /   May 10, 2014  /   Comments Off on መልካም የእናቶች ቀን (የልጆቻችሁ እስር አንጀታችሁን ላሳሰራችሁ) ጽዮን ግርማ

    Print       Email
0 0
Read Time:10 Minute, 30 Second

እኔና ጓደኛዬ (ሊሊ) የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ)ን ደጅ የረገጥነው በጠዋት ነበር፡፡ ምግብ ማቀበል እንጂ ማግኘት ስለማይቻል የግቢው በር እንደተከፈተ ለልብ ወዳጃችን የወሰድነውን ቁርስ ሰጥተን ያደረ ተመላሽ ዕቃ እስኪመጣልን ከመግቢያው ፊት ለፊት ባለው ድንጋይ ላይ ቁጭ ቁጭ ብለናል፡፡ቀዝቀዝ ባለው አየር ላይ ጥቂት ካፊያ ስለነበር ቅዝቃዜው ኩርምት አድርጎናል፡፡ ጥቂት ቆይቶ አንዲት እናት በስስ ፌስታል አንድ አራት የሚኾን ፓስቲ (ቤት ውስጥ የሚጠበስ ቂጣ መሰል ብስኩት) ጠቅለል አድርገው ይዘው ወደኛ መጡ ፊታቸውን ጭንቅ ብሎታል፡፡ የመጨረሻውና የ22 ዓመት ወንድ ልጃቸው ሰሞኑን የታሰረባቸው እናት ናቸው፡፡ ‹‹ዛሬ ሴቷ ልጄ ቁርስ ይዤለት የምመጣው እኔ ነኝ ብላኝ ባዶ እጄን መጥቼ አረፈደችብኝ፡፡ እንደው እስከዛ ይቺን ይቀበሉኝ ይኾን?›› ሲሉ በፌስታል ጠቅልልው ወደያዟት ፓስቲ አሳዩን፡፡ እንደ ዕድል ኾኖ ማዕከላዊ በር ላይ አብዛኛው ቀን ምግብ ፈትሸው የሚያስገቡ ፌደራል ፖሊሶች ትሁትና መመሪያው በሚፈቅድላቸው ልክ ተባባሪዎች ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ትንሽ ኾነ ብለው ሊከለክሏቸው እንደማይችሉ ነግረናቸው ፌስታሏን ይዘው ወደ ውስጥ ዘለቁ፡፡ በሩ ክፍት ስለነበርና እኛም በክፍቱ በር ልክ ስለተቀመጥን እኚህ እናት ውስጥ ገብተው ምን እንደሚሠሩ በደንብ ይታየናል፡፡ የእስር ቤቱ ግቢ አካል ወደ ኾነችው አነስተኛ ሱቅ አመሩ፡፡ እንደ ውሃ፣ለስላሳ መጠጦች፣ጁስ፣ቆሎ፣ የመሳሰሉና ሌሎች ጥቃቅን ለእስረኛ አስፈላጊ የኾኑ ነገሮችን የሚሸጥባት ሱቅ ናት፡፡

እንደዚህ ያሉ ነገሮችን ከዚች ሱቅ ውጪ ከውጭ ይዞ መግባት አይቻልም፡፡ እናም እኚህ እናት የያዟት ቁርስ ስላነሰችባቸው መሰል ከዚች ሱቅ ዕቃ ገዛዝተው ፌስታሉ ውስጥ ሲጨምሩ ተመለከትኳቸው፡፡ ተመላሽ ዕቃ እንዲመጣላቸው ነግረው እኛ ወደ ተቀመጥንበት መጡ፡፡ዐይናቸውን ልጃቸው ትመጣበታለች ባሉት መንገድ ላይ ሰክተው አስቀሩት፡፡ ሐሳባቸውን ወደኛ መለስ እያደረጉም ስለልጃቸው መልካምነትና ከእርሳቸው ጋር ስለነበረው ቅርበት እያስታወሱ ያጫውቱናል፡፡ ‹‹ሦስት ልጆች አሉኝ፡፡ አንዷ አግብታለች፡፡ አንዱ የራሱን ሥራ እየሠራ ነው፡፡ አሁን የታሰረብኝ የመጨረሻው ነው›› አሉን፡፡ ልጃቸው ከገባበት እንዲወጣ ፈጣሪያቸውን እየተማጸኑ፡፡

‹‹ልጄን አንጀቴን አስሬ ነው ያሳደኩት፤ጓደኛዬ ነው፣ልጄ ነው፣ወንድሜ ነው፣አጫዋቼ ነው፡፡ ሁሉ ነገሬ ነው እንደውም ሌሎቹ ለእርሱ ታዳያለሽ ይሉኛል፡፡›› አሉን፡፡ ልጃቸው ተጠርጥሮ ከታሰረበት ጉዳይ ጋር ምን ግንኙነት እንዳለው ለማወቅ ተስኗቸዋል፡፡ልጃቸው በዕድሜ ትንሽ መኾኑን ደጋግመው እየነገሩን፡፡‹‹እርግጠኛ ነኝ ምንም እንዳላዳረገ ሲያውቁ ይለቁታል›› ብለው ተስፋን ሰነቁ፡፡ እኚህ እናት 500 ብር የሚከፈላቸው ጡረተኛ ናቸው፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት ከልጆቻቸው አባት ጋር ቢለያዩም እርሳቸው እንደነገሩን ለልጃቸው ሲሉ ያንኑ የቀበሌ ቤት ለሁለት ተካፍለው ምግብ እያዘጋጁ ልጃቸውን ይመግባሉ፡፡ ‹‹ልጄ መንግሥት ቤት ነበር የሚሠራው፡፡ እኔ ከምሠራበት መሥሪያ ቤት ጋር የጡረታ ክርክር ላይ ስለነበርኩ ሥራ አልነበረኝም፡፡ በዛን ሰኣት ሲደግፈኝ ቆየና ልክ የጡረታ መብቴ ሲከበር ‘እስካሁን ላንቺ ብዬ ነበር ሥራ ላይ ቆየኹት መልቀቅ አለብኝ’ ብሎ ሥራውን ትቶ ትምሕርት ጀመረ፡፡››ሲሉ ልጃቸው የነበረበትን ኹኔታ ነገሩን፡፡‹‹እኔ ለልጄ ብዬ ነበር በጣም የተጎዳኹት፡፡››አሉን እዝን ብለው፡፡ በትዳራቸው ደስተኛ እንዳልነበሩ ከንግግራቸው ያስታውቃል፡፡ ከፍቺውም በኋላ አብረው በአንድ ግቢ መኖራቸው እንዳልተመቻቸው ከስሜታቸው መረዳት ይቻላል፡፡

‹‹ልጄ የሚያድረው ከአባቱ ጋር ቢኾንም እንዳይራብብኝ ስለምፈራ የሚመገበው ግን ከእኔ ጋር ነበር፤ጡረታዬ ትንሽ ብትኾንም ቁጭ አልልም በተቻለኝ አቅም አየተሯሯጥኩ እሠራለሁ፡፡ ከመርካቶ ልብስ እያመጣሁና የምግብ ቂቤ ከክፍልሃገር እያስመጣሁ እሠራበት ለነበረው መሥሪያ ቤት ሠራተኞች እሸጣለሁ፡፡ ብቻ ፈጣሪ ይመስገን የከፋ ችግር አላጋጠመኝም››ሲሉ ፈጣሪያቸውን እያመሰገኑ ኑሮአቸውን ተረኩልን፡፡ ለእስረኛ በየቀኑ ስንቅ ማመላለስ በተለይ እንዲህ እንደሳቸው ቋሚና የረባ ገቢ ለሌለው ሰው እጅግ ከባድ ነገር ነው፡፡ እርሳቸው ግን ስለ ክብደቱ መስማትም ማውራትም አልፈልጉም ፤‹‹ እርሱ ይፈታልኝ እንጂ እኔ ስንቅ ማመላለስ አይከብደኝም፡፡

አንጀቴን አስሬ የቻልኩትን ሁሉ አደርጋለሁ፡፡ በፊት እንደምሯሯጠው እየተሯሯጥኩ ሠርቼ ስንቁን አመላልሳለሁ›› አሉን፡፡ ወኔያቸው ከዕድሜያቸው በእጅጉ የገዘፈ ነው፡፡ ገና ካሁኑ አንጀታቸውን ማሠራቸው ያስታውቃሉ፡፡ እናት መኾናቸው ችግራቸውን አስችሎ ጥርስ አስነክሷቸዋል፡፡ አንጀታቸውን አስረው ጥርሳቸውን ነክሰው ስንቅ የሚያመላልሱ እናት እርሳቸው ብቻ አልነበሩም፡፡ እንዲህ ያሉ እናቶች ትናንት ነበሩ፡፡ ዛሬም አሉ ምናልባትም ነገ ይኖራሉ፡፡ ዛሬ የእናቶች ቀን ነውና የልጆቻቸው እስር አንጀታቸውን ላሳሰራቸው እናቶች ‹‹መልካም የእናቶች ቀን፤ስንቅ አቃባይ አያሳጣችሁ›› እላለሁ፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 10 years ago on May 10, 2014
  • By:
  • Last Modified: May 10, 2014 @ 7:22 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar