www.maledatimes.com እስካሁን ጠ/ሚ/ር አለመሾሙ አነጋጋሪ ሆኗል – (ሰንደቅ ጋዜጣ) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

እስካሁን ጠ/ሚ/ር አለመሾሙ አነጋጋሪ ሆኗል – (ሰንደቅ ጋዜጣ)

By   /   September 12, 2012  /   Comments Off on እስካሁን ጠ/ሚ/ር አለመሾሙ አነጋጋሪ ሆኗል – (ሰንደቅ ጋዜጣ)

    Print       Email
0 0
Read Time:21 Minute, 42 Second

(ሰንደቅ ጋዜጣ) ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ እሳቸውን የሚተካ ጠቅላይ ሚኒስትር አለመሾሙ እያነጋገረ ነው። በተለይ የኢህአዴግ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ኢህአዴግ ሕዝባዊ ኃላፊነቱን አልተወጣም ሲሉ እየከሰሱት ነው። በድርጅቱ ውስጥ የስልጣን ሽኩቻ በመፈጠሩም አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳይሾም አድርጎ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን እየገለፁ ነው።
አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሾም ኢህአዴግ የዘገየባቸውን ምክንያቶች በተመለከተ የመድረክ፣ የኢዴፓ፣ የሰማያዊ ፓርቲ እና የኢትዮጵያ ፍትህ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ግንባር (ኢፍዴኃግ) አመራሮችን አነጋግረናል።
የመድረክ ሊቀመንበር አቶ ጥላሁን እንዳሻው አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሾም ኢህአዴግ ስለዘገየበት ምክንያት ተጠይቀው መዘግየቱ ኢህአዴግ ጤናማ ሁኔታ ላይ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል። በሌሎች አገሮች አንድ ጠቅላይ ሚኒስትር በተፈጥሮ ሞት ካለፈ በኋላ ቶሎ ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር መሾም የተለመደ ተግባር ነው ብለዋል።
መተካካቱም ግፋ ቢል በአንድና ሁለት ቀናት ውስጥ የሚፈፀም ቢሆንም፤ በኢትዮጵያ ይሄ ሁኔታ አለመኖሩ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው ብለዋል። በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 75 ንዑስ አንቀፅ (1)(ለ) ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማይኖሩበት ጊዜ ምክትሉ ተክቶ ይሰራል ቢልም፤ ወዲያውኑ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በአቶ መለስ ምትክ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን ይገባቸው ነበር ያሉት አቶ ጥላሁን ኢህአዴግ ሕገ-መንግስቱን የሚያከብር ድርጅት ቢሆን ይህንን እስከዛሬ መፈፀም ይገባው ነበር ብለዋል።

የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አለመሾም በምክንያትነት ሊቀርብ የሚችለው ጉዳይ በድርጅቱ ውስጥ የስልጣን ሽኩቻ ስለመፈጠሩ ተጨባጭ መረጃ አላገኘንም በማለት በግምት ላይ ተመስርቶ አስተያየት መስጠቱ ተገቢ አለመሆኑን አቶ ጥላሁን ገልፀዋል።
ኢህአዴግ በምስጢር የሚሰራ ድርጅት በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንኳ መታመማቸው ከውጪ ሀገር መሪ እንድንሰማ ከመደረጉ አንፃር በገዢው ፓርቲ አካባቢ ምን እየተከናወነ እንደሆነ ለመገመት ግን አስቸጋሪ መሆኑን ነው የጠቀሱት።
የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ይልቃል ጌትነት በበኩላቸው የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር መሾም ሊዘገይ የቻለበት ዋናው ምክንያት የገዢው ፓርቲ አባላትን መቆጣጠር የሚያስችል ተቋማዊ ስርዓት ባለመፈጠሩ ነው ብለዋል። ክስተቱም ኢህአዴግ ባለፉት 21 ዓመታት በተቋምና በመርህ የሚሰራ ድርጅት አለመሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ኢህአዴግ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጤንነት መታመም ከመደበቅ ጀምሮ ከሞቱም በኋላ በአስቸኳይ ተተኪያቸው በሕገ- መንግስቱ መሠረት መተካት አለመቻሉ ኢህአዴግ ተቋማዊ ቅርፅ ያለው፣ በሕግና በመርህ የሚመራ ስርዓት አለመዘርጋቱን የሚያሳይ እንደሆነ ገልፀዋል።
ይሄንን ፈተና ኢህአዴግ በሀገራዊ ኃላፊነትና በጥንቃቄ መወጣት ካልቻለ ለሀገራችንም ከባድ ሁኔታ ይፈጠራል ያሉት አቶ ይልቃል ተተኪውን ጠቅላይ ሚኒስትር አለመተካት ወደተለመደው የመንግስት ግልበጣ የስልጣን ሽግግር እንዳንገባ ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
“ኢህአዴግ በቶሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ያልሾመው በውስጡ ሽኩቻ ስለተፈጠረ ወይስ ድርጅቱ የሰከነ አመራር ስለሚከተል” በሚል ለአቶ ይልቃል ለቀረበላቸው ጥያቄ በኢህአዴግ ውስጥ ማንን ጠቅላይ ሚኒስትር እናድርግ የሚለው ጥያቄ በፓርቲው ውስጥ ውዝግብ መፍጠሩ እንዳልቀረ ነው የገለፁት።
ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ቀደም ሲል በሚኒስትሮች ም/ቤት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ ተወስኖ ለሕዝብ ይፋ ከተደረገ በኋላ ግልፅ ባልሆነ ሁኔታ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲጠሩ መደረጉና ፓርላማውም ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሾም ከተጠራ በኋላ በቂ ባልሆነ ምክንያት እንዲሰረዝ መደረጉ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ወሳኝ ጉዳይ ላይ ከተሰበሰበ በኋላ የእለት ተዕለት ስራዎች እንዲገመገም አድርጎ ስብሰባውን ማጠናቀቁ የሚያሳየው ተተኪውን ጠቅላይ ሚኒስትር በመምረጥ ላይ ድርጅቱ ችግር እንደገጠመው ያሳያል
ብለዋል።
በአጠቃላይ ችግሩ ከቁጥጥር ወጥቶ በሀገር ደረጃ የሚያስከትለው ጉዳት ቢጠበቅም በኢህአዴግ ውስጥ ተፈጥሮ ሊሆን ይችላል የሚለው የስልጣን ሽኩቻ በመጀመሪያ ድርጅቱን የሚጎዳ ሆኖ በመጨረሻም ሁሉም ተሸናፊ የሆነበት ሁኔታ ይፈጠራል ብለዋል።
የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሊቀመንበር አቶ ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሹመት መዘግየት አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል። በአቶ ሙሼ እምነት ሀገሪቱ የተሟላ አመራር ካጣች ሦስት ወራት መሆኑን በመግለፅ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር የመሾሙ ሂደት ዘግይቷል ሊባል እንደሚችል ነው የገለፁት። አቶ መለስ ከዚህ ዓለም ከተለዩ በኋላ ኢህአዴግ እንደ ድርጅት የመደናገርና ግልፅ ያልሆኑ የውሳኔ ኀሳቦች መታየታቸውን የጠቀሱት አቶ ሙሴ የተምታቱ ነገሮች መቅረባቸው በሹመቱ ላይ ጥርጣሬና ስጋት እንዲፈጠር አድርጓል ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሹመት መዘግየት የሀገሪቱ የፖለቲካ ስርዓት ፓርላሜንታዊ መሆኑና ፓርላማውም ለዕረፍት መበተኑ እንዲዘገይ ሊያደርገው እንደሚችል ነው የጠቀሱት።
ይህም ሆኖ አንድ ሀገር ለሦስት ወራት ሙሉ የሕዝብ ውክልና የሌለው ሰው ሀገሪቱን በተተኪነት ስም እያስተዳደረ መቆየቱ ግልፅነት የሚጎድለው ተግባር ነው ብለዋል። በተጨማሪም አቶ ሙሼ “ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ በድንገት ጦርነት ቢከሰት በተጠባባቂነት ያሉ አስተዳዳሪዎች የመወሰን ተልዕኮ አላቸው ወይ? የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታዎች በሀገሪቱ ቢከሰቱና ከባድ ውሳኔ የሚጠይቁ ጉዳዮች ቢከሰቱ ማንነው የሚወስነው? የሚለው ጥያቄ ግልፅ ምላሽ ባልተገኘበት ሁኔታ መቀጠሉ አደጋ አለው” ብለዋል።
“ገዢው ፓርቲ በፍጥነት አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ያልሾመበት ምክንያት በግንባሩ አባል ፓርቲዎች መካከል የስልጣን ሽኩቻ በመፈጠሩ ወይስ የተረጋጋ ቡድናዊ አመራር በመኖሩ ነው” ተብለው ለተጠየቁት አቶ ሙሼ ሲመልሱ፤ “የተረጋጋ ቡድናዊ አመራር ከሕገ-መንግስቱ አንፃር አይፈቅድም። ሀገሪቱ ልትመራ የሚገባት በጠቅላይ ሚኒስትር እንጂ በቡድናዊ አመራር አይደለም። እንደዚህ አስበው እየሰሩ ከሆነ ከባድ ስህተት ነው” ሲሉ መልሰዋል። ይሁን እንጂ በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል የሀሳብ ልዩነት ተፈጥሮ ከሆነ አይገርምም የሚሉት አቶ ሙሼ “አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሆንን አካል ለመሰየም ልዩነቶች ቢፈጠር አይገርምም። በውስጣቸው ውይይትና ክርክር እንዲሁም ለመወሰን የሚያስችል ፍጭት ቢፈጠር ተፈጥሮአዊ ነው” ሲሉ ገልፀዋል።
የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች በርዕዮተ ዓለም አንድ ቢሆኑም ባላቸው የብሔር ቁመና እና ብዛት የተለያዩ መሆናቸው ከውስጣቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሾምና በጋራ ለመወሰን አስቸግሯቸው ሊሆን እንደሚችልም አቶ ሙሼ ገምተዋል።

በግንባሩ ውስጥ የህወሓት ጥንካሬ ቢኖርም፤ ባለፉት 21 ዓመታት ሌሎቹ ፓርቲዎች ከልምድ ካዳበሩት አቅም ተነስተው ሕወሓትን ሊታገሉት የሚያስችላቸው አቅም የለም ብዬ አላስብም ብለዋል።
በአጠቃላይ ሀገሪቱ ያለመሪ መቀጠል ስለሌለባት፤ ፓርቲው ያለበትን ውስጣዊ ችግር ፈትቶ በአስቸኳይ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር መሾም አለበት ያሉት አቶ ሙሼ፤ ከዚህ በኋላ ሌላ ቀጠሮ የሚሰጥ ከሆነ ችግሩ ስር መስደዱንና በእነሱ አቅም ብቻ የሚፈታ ስላልሆነ ቆጭ ብሎ መነጋገር ያስፈልጋል ማለት ነው ሲሉ አጠቃለዋል። የኢትዮጵያ ፍትሕና ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ግንባር (ኢፍዴኃግ) ሊቀመንበር አቶ ግርማይ ሀደራ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ ከባድና ኃላፊነት የሚጠይቅ መሆኑን በመጥቀስ ሀገሪቱ ያለመሪ ለተወሰኑ ጊዜያት መቆየቷ ተገቢ አይደለም ብለዋል።
ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትሩ መታመማቸው መደበቁ ሕዝቡን መናቅ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ግርማይ፤ አቶ መለስ የአንድ ሀገር ጠቅላይ ሚኒስትር እንጂ የአንድ ፓርቲ መሪ ብቻ አልነበሩም። ፓርቲው የራሱ ወኪል ቢሆንም፤ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃላፊነታቸውና ተጠሪነታቸው ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንደነበረ ገልፀዋል።
ኢህአዴግ የጠቅላይ ሚኒስትሩን መታመም ደብቆ የነበረው ከድርጅቱ ባህል ጋር በተያያዘ ነው መባሉ ፈፅሞ አግባብ ያስታወሱት የጠቀሱት አቶ ግርማይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዳይ ከሕገ-መንግስቱ እንፃር መታየት እንደነበረበትም አስገንዝበዋል።
በአሁኑ ወቅት አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር አለመሾሙ ሌላው ስህተት መሆኑን የጠቀሱት አቶ ግርማይ፤ ፓርላማው በአስቸኳይ ተጠርቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሳይሰይም መበተኑ ሁኔታውን አጠራጣሪ አድርጎታል ሲሉ ተናግረዋል። “አንድ ሀገር ያለ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ ለሳምንታት ቀርቶ ለሰዓታት ክፍት እንዲሆን ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም” ያሉት አቶ ግርማይ፤ “አሁንም በአስቸኳይ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር መሾም አለበት” ብለዋል።
ለአዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር አለመሾም ገዢው ፓርቲ ጤናማ ሁኔታ ላይ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው ያሉት አቶ ግርማይ፤ ገዢው ፓርቲ አካባቢ የፖለቲካ መጨናነቅ ሳይኖር እንደማይቀር ገልፀዋል። ሆኖም ፓርቲው በአደባባይ የስልጣን ሽኩቻ መኖሩን ይገልፃል ተብሎ እንደማይገመትም አስረድተዋል። አቶ መለስ ካለፉ በኋላ በኢህአዴግ ውስጥ የስልጣን ሽኩቻ ተፈጥሮ ከሆነ ኢህአዴግ ለ21 ዓመት ተቋማዊ መሠረት አለመገንባቱን ያሳያል ብለዋል። አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር በቶሎ አለመሰየሙም በግንባሩ ውስጥ የስልጣን ሽኩቻ ስለመኖሩ አመላካች ነው ሲሉ አስረድተዋል።
ይሄንን ጉዳይ በተመለከተ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሰሞኑን ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ አመራር በሚሰየምበት አቅጣጫ ዙሪያ መክሮ የአመራር ምደባ ጉዳይ ለጋራ ዓላማ በማደረግ ትግል ውስጥ አንድን ጓድ ይበልጥ መስዋዕት ይከፍል ዘንድ ከመመደብ ያለፈ ትርጉም የሌለው ቀላል ጉዳይ መሆኑን ጠቅሶ የባለራእዩንና ታላቁን መሪ የጓድ መለስ ዜናዊን ድንገተኛ ህልፈተ ህይወት ተከትሎ የተጓደለው አመራር በሚሰየምበት አቅጣጫ ዙሪያ መምከሩን ሊቀመንበሩና ምክትል ሊቀመንበር የመሰየም ጉዳይ የግንባሩ ምክር ቤት ስልጣን በመሆኑ በያዝነው መስከረም ወር የመጀመሪያ ሳምንት
በሚካሄደው የምክር ቤቱ ስብሰባ ይፈፀማል ማለቱ አይዘነጋም።
ፓርቲው የፓርቲው ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር ይሰየማል ከማለቱ ውጪ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ስየማ መቼና እንዴት ይፈፀማል የሚለውን አልጠቀሰም። በሀገሪቱ ሕገ-መንግስት መሠረት በምርጫ ያሸነፈው ፓርቲ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመርጥ ሲሆን፤ አሸናፊው ፓርቲ በበኩሉ የሚያምንበትን ሰው በመጠቆም ለጠቅላይ ሚኒስትርነት በማጨት በአብላጫ ድምፅ ያፀድቃል። እስካሁን ባለው አሰራር የግንባሩ ሊቀመንበር የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሆኑበት ሁኔታ እንዳለ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መረዳት ይቻላል።

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on September 12, 2012
  • By:
  • Last Modified: September 12, 2012 @ 5:30 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar