www.maledatimes.com የማለዳ ወግ … የጅዳው ት/ቤታችን እንደ አረቡ አብዮት ከድጡ ወደ ማጡ ! - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የማለዳ ወግ … የጅዳው ት/ቤታችን እንደ አረቡ አብዮት ከድጡ ወደ ማጡ !

By   /   October 20, 2014  /   Comments Off on የማለዳ ወግ … የጅዳው ት/ቤታችን እንደ አረቡ አብዮት ከድጡ ወደ ማጡ !

    Print       Email
0 0
Read Time:5 Minute, 39 Second

*  ታዳጊዎች የተሟላ ትምህርት አያገኙም
* ወላጅም ዝምታን መርጧል

የጅዳ የኢትዮጵያ አለም አቀፍ ትምህርት ቤት በተወሳሰበ የአሰራር ፣ አመራር ሂደት ውስጥ በማለፍም ቢሆን የመማር ማስተማር ሒደቱን ከጀመረ ሁለት ወር ደፍኗል። በሁለት ወራት ልጆቻችን ተምረው ተመለሱ ብሎ ለጠየቀ ምላሹ ቆሽት ያሳርራል ። በእስካሁኑ የትምህርት ቅበላ ባለው ከስድስት ያላነሰ ክፍለ ጊዜ የሚማሩት ከሁለትና ሶስት ከፍለ ጊዜ ሲሆን አልፎ አልፎ አራት ክፍለ ጊዜ ብቻ ብቻ ተመረው ይመለሳሉ ። ይህን እውነታ ልጆቹን እንደማዋያ ጥሎ ዘወር የሚለው ባይተዋር ወላጅ ከልጆቹ ይሰማዋል። የልጆቹን ደብተር አገላብጦ የሚመለከት የእኔ ቢጤ ብስጩ አባት ደግሞ ከልጆቹ ከመስማት አልፎ በማስረጃ ደብተሩን  ሲያገላብጥ የሚታዘበው እውነታ ነው ።
በአንዳንድ ክፍሎች ዘመናዊውን ትምህርት ትምህርት የሚያሰኙት የእንግሊዝኛና የሒሳብን ጨምሮ ከፍ ሲል የኬሚስትሪ፣ የፊዚክስ  ፣ የባዮሎጂና የኮምፒውተር ትምህርቶች መሰጠት የተጀመረው በያዝነው ሳምንት ነው ። የሚያም እውነት ነው … ልጆች በተወለዱበት ሃገር ዜግነት ቀርቶ ፣ ቅንጣት ልዩ መብት አይሰጣቸውም ። ይህ በሆነበት የአረብ ሀገሩን ስደት መከራና  የኑሮ ውጣ ውረድ ላገናዘበው ፣ ማህበረሰቡ በራሱ ጥረት ት/ቤት መስርቶ አስፈላጊ ክፍያ ፈጽሞና ልጅን ትምህርት ቤት ሰዶ ያልተማረ ልጅን መቀበል ግፍ ነው ፣ አመቱን ሙሉ ወደ ትምህት ገበታ ሳይሆን  ወደ ማዋያው ማመላለስ የለየለት ዝቅጠት ነውና ከዚህ መከራ ይሰውረን  !

ዛሬ ማለዳ አንድ የፊስ ቡክ ወዳጀ ስለትምህርት ቤቱ መረጃ ያቀበሉኝ አዝነው ነው፣ ማምሻውን ደግሞ ብርቱ ውስጥ አዋቂ ወዳጀ ስልክ ደውሎ “ምነው የትምህት ቤቱን ጉዳይ ረሳህውሳ ? ቢያንስ ይጻፍ የሚሰማ ቢገኝ!  ” ሲል የውስጥ የውጩን የተተረማመሰ አሰራርና በየደቂቃው የምሰማውን የወላጁን ሮሮ አስተጋባልኝ …ገፋፍቶኝ ወደ ከሸፈው የኮሚኒቲ የአመታት የለውጥ መንፈስ ነጎድኩ … ተመለስኩና ሌላ የከሸፈ ታሪክ የአረቦች የጸደይ  አብዮት አቀናሁ … ከምናቡ ቅኝት ተመልሸ  የጅዳው ት/ቤታችን እንደ አረቡ አብዮት ከድጡ ወደ ማጡ  .. . ብየ ጀመርኩት  ፣ ህመሜን ልተንፍስ በሚል … ከቀደመው ልጀምር  …

የተሻለ ይመጣ መስሎን  በድክመቱ ላይ አተኩረን ሳናመሰግነው ያለፍነው የቀድሞው ኮሚኒቲ ትልቅ ስራ ሰርቶ ማለፉን ማሰታወስ ግድ ይላል ። የዛሬን አያድርገውና የጅዳ ኮሚኒቲ የውስጥ ችግሩ እንዳለ ሆኖ በትምህርት ቤቱ ዙሪያ ያደርግ የነበረው ትልቅ ድጋፍ የሚዘነጋ አይደለም ። የቀድሞው አሁን ካለውና በድርጅት ሰዎች ጫና ውሳኔ እንደ ሚያሳልፍ ከሚነገረን ኮሚኒቲ የተሻለ ነው የምንለው በርካታ መምህራንን ከማስመጣት ባለፈ በመማር ማስተማሩ ጠንካራ አቋም ነበረውና ነው ።

የቀድሞው ኮሚኒቲ ከአስር ያላነሱ መምህ ራንን ከሃገር ቤት አስመጥቶ ነበር … ግን አልበረከቱም ። አለመበርከታቸው ፈርጀ ብዙ  ምክንያት አለው። ድንቅ ድንቅ የሚባሉ መምህራን በትምህርት ቤቱ አስተዳደር፣ በኮሚኒቲ ጣልቃ ገብነትና በራሳቸው የግል ጉዳይ ሃገር ቤት ሄደው ላይመለሱ  እዚያው ቀርተዋል … ለነገሩ የትምህርት ቤቱን ዳይሬክተርን ጨምሮ ፣ ከሃገር ቤት መጥተው ከእኛ ጋር የከረሙትም ባለሙያ መምህራን ዛሬም አሉ ፣  ከማስተማሩ ክልል ግን በሹመት ሰበብ ገለል እያሉ ነው ።  “በምርጫ ” የትምህርት ቤቱን ዋና ዋና ኋላፊነት ቦታወች  ተቀዳጅተዋል፣ በውጭ ህይወታቸው ዲሞክታሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው በአብዮታዊው ዲሞክታሲያዊ የገዥው ፖለቲካ ፖርቲ አባልነት ሲመለመሉና ሲጠመቁ  አሁንም ” በምርጫ”  የገዠው ፖርቲ የኢህአዴግ የፖለቲካ ድርጅት ቁንጮ  ባለስልጣናት ሆነዋል ፣ በስራና ስብሰባም  ተወጥረዋል። ጥቂት ወደ ውስጥ ገባ ካልን የምናገኘው ደስ አይልም።  በዚህ ሁኔታ መምህር እያለ መምህር ፣ የማጣታችን እንቆቅልሽ ያማል    …

የቀድሞው ኮሚኒቲው ከሃገር ቤት የኬሚስትሪ መምህር ቢያስመጣም መምህሩ ከላይ በግርድፍ የተጠቀሰው የአስተዳደር ሹመት እና ሌላም በድርጅት ስልጣን ተንበሽብሸዋል።  “መሽ አላህ ብያለሁ  ፣ ሹመት ያዳብር ብያለሁ ” የማልለው ታዳጊዎች እየተጎዱ ስለመሆኑ ዋቢ ጠቅሸ ማስረዳት እችላለሁና ነው ።  …
በቀድሞው ኮሚኒቲ በአንድ ወቅት አስመጥቷ ቸው የነበሩት የሒሳብ መምህር በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቁ ወጣት ምሁርን ነበሩ ፣  አለመታደል ሆኖ ንቃት ትጋት ተቆርቋሪነታቸው ለትምህርት ቤቱ የበላይ ሃላፊነት መመጠናቸው አደጋ ላይ ጣላቸው ፣ ንቃት ተረጋት የህዝብ ወገንተኛነታቸው አልተፈለገምና ተማሪ ቀጡ ተብሎ በረቀቀ መንገድ ከትምህርት ቤቱ በራሳቸው ፈቃድ እንደተሰናበቱ ተደርጎ ተወገዱ … ወደ ሃገር ቤት በአስቸኳይ ተሸኙ …
የኮምፒውተር መምህርም በቀድሞው ኮሚኒቲ በኩል ከሃገር ቤት አስመጥተን ነበር ፣  ባለ ሙያውን በአግባቡ መያዝ ባለመቻሉ መምህሩ ሃገር ቤት ሄደው ቀሩ … እንበለው  !
ቀጠለና ከአመታት በፊት የኮምፒውተር አስተማሪ እዚሁ በወጣ ማስታወቂያ ተገኘና ቅጥሩ ተፈጸመ። ከጥቂት አመታት በኋላ ግን  ማለትም ካሳከፍነው አመት ጀመሮ በሙሉ ሃይላቸው ከማስተማሩ የሚገታቸው የትምህርት ቤቱ ” ዩኒት ሊደርነት” ሃላፊነት ተሰጣቸው ።  እነሆ ዛሬ የኮምፒተሩ መምህር በተሰጣቸው ሹመት መሰረት ማስታማሩን ትተው መምህር የሌላቸው ተማሪዎችን ሲያሯሩጡ ይውላሉ ! ይህስ አያም ፣ አያሳዝንም ?

በአሳር በመከራ ወላጅ ተጠርቶ ሲሰበሰብ ትውልድ የማነጹ ስራ ስለመጓተቱ ፣ ስለ መምህራን እጥረት ፣ ስለ ማስተማሪያ ቁሳቁስና ስለትምህርት ጥራት ፣ ስለ ደመወዝ ማነስ ፣ ስለ አጠቃላይ አሰራር መጓተት ሂደት መረጃ አጣቅሰው ትምህርት ቤቱ ያለበትን አደጋ ሲናገሩት መስማቱን ለምደነዋል ። በዚህ ደረጃ እየተመራ ያለውና እየመሩን  ያሉት የትምህርት ቤቱ ሹማምንት የሚሰሩትን ጠጋ ብለን ስንጠይቃቸው ሆድ የሚያሞላ ምላሽ አይሰጡንም ፣ ብቻ …አንደበተ ርቱዕ የትምህርት ቤቱ እና ኮሚኒቲው ሹማምንት ” ጎደለ” የሚሉትን ለማሟላት  ስላለመስራታቸው  አጥጋቢ የምለው ምክንያት አለኝ …

ትምህርት ቤቱ ከጀመረ ጀምሮ እንግሊዝኛ በማስተማር ትልቁን ክፍተት ይሸፍኑ የነበሩት ህንዳዊ መምህር ሚ/ር ሳንቱሽ ሲጓተት የተበለሻሸ የመኖሪያ ፈቃድ ማዛወር ሒደት አልተሳካም። ይህም ለጎደለው ትምህርት ፣ ለማስተማሩ ክፍተት መሆኑ ብዙዎች መናገር የምንፈራው እውነት ነው ። የኮሚኒቲው ሃላፊዎች  የእውቁና ባለ ውለታ መምህሩን  የሚ/ር ሳንቶሽ ፈቃድ ቅየራ ባጓተቱበት እጃቸው የትምህርት ቤቱ ስም በሚሰጠው ፈቃድ የካፍቴሪያው ሰራተኞችን እንደ ባለሙያ አድርጎ ፈቃድ ማስተካከሉ ተሳልጦላቸዋል።  ዛሬ ብርቱው መምህር ሁለመናው ከሽፎባቸው ” ከቤት ውለዋል!”  አሉ ። እኛም ትጉህ መምህር አጥተናል  ! በትምህርት ቤቱ ዙሪያ በዘመድ አዝማድ በተሳሰረው አሰራር የሚታየውና የሚሰማውን ሁሉ ፍትሃዊ የአለመሆን ሂደት ውስጥን  ያደማል ፣ ቢያብከነክንም አይጠቅምምና ወደ ውስጥ ዘልቄ አልነካካውም … ሁሉን ተናግሬ ሆዴ ባዶ እንዳይቀር ቢስተካከል በሚል እሳቤ ከተጨበጠው መረጃ ግን ጥቂት ጥቂት ብቻ  እየቆነጠርኩ መናገሬን ልብ በሉ …

የከሸፈው የጸደዩ አብዮት …

ዛሬ ዛሬ የእኛ ትምህርት ቤት ነገር እንደ አረብ ሃገሩ ” የጸደይ አብዮት” ሆኖብናል ። የጸደዩ የአረቦች አብዮት ማዕበል ሃይለኛ ነበር ። የቱኒዝያ ንጉስ ፕሬዚደንት ቢን አሊ ገርስሶ ፣ ሶስት ክፍለ ዘመን የተሻገረውን የግብጽን ፕሬዚደንት የሁስኒን አንባገነን መንግስት ደረማምሶታል። የማይመስል ፣ አይሆንም ተብሎ የሚገመተው በአብዮቱ ማዕበል ተንጦና ተደረማምሶ አይተናል። የአብዮት  ማዕበሉ ሊቢያ ላይ ሲያርፍ “የአፍሪካ ንጉሰ ነገስት ነኝ ” ባዩን ፕሬዚደንት ጋዳፊን ከነምናምናቸው ደብዛቸውን አጥፍቷቸዋል። የየመኑን ፕሬዚደንት አሊ አብደላ ሳላህን አላስቀረላቸውም ። ሳላህ ከተረጋጋውና በሳውዲ የሚደገፈው ወንበራቸው በማዕበሉ ተጠቅቶ ፣ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ጥገኝነት ጠያቂ ስደተኛ መሆናቸውን በሹክሹክታም ቢሆን ሰምተናል። የመን ግን ከአንድ ሃገርነት ልትወጣ መከራዋን እያየች ነው …   የቀድሞዋ ጥንታዊ አረብ ሃገር የሻሟ የአረቦች ቅምጥል ሃገረ ሶርያ የአብዮቱ ማዕበል ጎድቷት ከሃገር ተራ ወጥታለች … ሶርያ የሃያላኑ ምዕራባውያን የእነ አሜሪካና አጋሮቿ ፣  የራሻና ፣  ቻይናና የኢራን ጉልበት መፈተሻ የጦርነት ቀጠና ፣ የለየላቸው ጨካኝ አክራሪ ጽንፈኞች መፈንጫ የደም ምድር ሆናለች ….ሶርያ  !

ተጠልፏልና ያልጠቀመው አብዮት …

እነሆ አብዮቱ  ለሁሉም አልበጃቸውም፣ ይህን የምለው ሃገራት ከሃገርነት ተርታ በሚያወጣ እሰጣ ገባ ቋፍ የመገኘታቸው እውነታን ማየታችን ዋቢ በማድረግ ነው ። ብቻ አየሆነ ያለው በአብዮቱ የተገኘው የመልካም ለውጥ ትንሳኤ ምሳሌ ሳይሆን መልካሙ የለውጥ ጅምር በእኩዮች ተጠልፎ ለውጡ ውድቀት ዘመም መሆኑን ነው ።  “አብዮቱ ድሉን መትቷል !” እንዳንል አብዮቱ የተካሔደባቸው ሃገራት የገቡበት ከድጥ ወደ ማጥ የመሆኑን ሃቅ ስናጤነው ብቻ ነው  … ይህ በመሆኑ ከአብዮቱ መባቻም የነዋሪው መከራ ካለፈው የከፋ ሆኗል!  የሆነው የተፈለገው ሳይሆን ያልተጠበቀው ነውና … !

የተመሳሰለብኝ የእኛው ጉዳይ …

የማይገናኘውን ታላቅ የታሪክ ሂደት ከደቃቃው የእኛ ገጠመኝ ጋር ማመሳሰሉ አይገጥምምና  ይገርማችሁ ይሆናል … ትልቁን ከትንሹ ማዛመዴ የለውጡን ፍላጎት ፣ በለውጡ መባቻ በጀርባ የተጠለፈውን የለውጥ መንፈስ ተመሳሳይ ሂደት ለማጣቀስ ይረዳኝ እንደሁ ብየ ነው  …ቢጨነቀኝ  ! በጅዳና አካባቢዋ ለማህበረሰቡ ጥቅም መከበር በማሰብ ” የተሻለ ይመጣ ” መስሎን በቀድሞው ኮሚኒቲ ድክመት ላይ አተኩረን ለለውጡ መረባረባችን እውነት ነው ። ለውጥም መጥቶ ነበር ፣ ለውጡ ግን በጉልበተኞች ተጠለፈ  ! የተረባረብንበት የደከምንበት ሁሉ ለዛሬው ፍዳ አደረሰን ….ምርጫው ተጠልፎ ለውጥ ሊመጣ ቀርቶ እያዘገምን ያለው መንገድ በአሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል … መፍትሔ ጠቁም እንዳትሉኝ  ! መፍትሔው ከሁላችንም ምክክር መምጣት ይገባዋል ፣ ከሁሉም በላይ የ3000 ( ሶስት ሽህ)  ታዳጊ ተማሪዎችን የትምህርት ቅበላ በዋናነት የሚያገባቸው የጅዳ ቆንስልና በሳውዲ የኢትዮጵያ መንግስት የመንግስት ተወካዮች  አደባባይ በሚታየው የገዘፈ አደጋ ሊመለከቱት ይገባል ፣ የትውልድ ግንባታ አደጋ ላይ ወድቋልና  “ያገባናል ” ብለው ስላልመከሩ ቂም ይዘን አንወቅሳቸውም ፣ አሁንም ለተቀመጡበት ወንበር ፣ ለቆሙለት ዜጋ ፣ ለሚከፈላቸው ክፍያ ሁሉ ቀርቶ ላስተማረቻቸው ሃገር ትንሳኤ ለተተኪው ትውልድ ሲሉ የ3000 (የሶስት ሽህ) ተማሪዎችንና የትምህር ማዕከሉን ሊታደጉት ይገባል ! በዚህ ዙሪያ ገብ የጉዳዩ ባለቤቶችን ዜጎችን ማወያየት ከሹሞቻችን ይጠበቅባቸዋል ! ….. እኛ የሚያገባን ግን ፣ ይህ ሆነ አልሆነ ትናንትም ዛሬም እንደምናደርገው የሃገር ተረካቢ ልጆች ጉዳይ ስለሚያገባን ወላጅ በፍርሃት ተሸብቦ እንኳ ዝምታን ቢመርጥ  እንናገር ፣ እንመክር ፣ እንጦምርበት ዘንድ ግድ ብሎናል !    ጆሮ ያለው ይሰማል  ፣  ሰምቶ የዝሆን ጀሮን የተመኘ ጥቁር የታሪክ አሻራን መጣሉን ልብ ቢል መልካም ነው  !

ቸር ያሰማን

ነቢዩ ሲራክ

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar