www.maledatimes.com የመድረክ አመራር በሰሜን አሜሪካ የሚያደርጉትን ህዝባዊ ስብሰባዎችን በመቀጠል አቶ ገብሩ አስራት በአትላንታ ከተማ ተገኝተው ለተሰበሰቡት ኢትዮጵያውያን ያደርጉትን ታሪካዊ ታሪካዊ ንግግር ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል። - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የመድረክ አመራር በሰሜን አሜሪካ የሚያደርጉትን ህዝባዊ ስብሰባዎችን በመቀጠል አቶ ገብሩ አስራት በአትላንታ ከተማ ተገኝተው ለተሰበሰቡት ኢትዮጵያውያን ያደርጉትን ታሪካዊ ታሪካዊ ንግግር ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።

By   /   September 24, 2012  /   Comments Off on የመድረክ አመራር በሰሜን አሜሪካ የሚያደርጉትን ህዝባዊ ስብሰባዎችን በመቀጠል አቶ ገብሩ አስራት በአትላንታ ከተማ ተገኝተው ለተሰበሰቡት ኢትዮጵያውያን ያደርጉትን ታሪካዊ ታሪካዊ ንግግር ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።

    Print       Email
0 0
Read Time:79 Minute, 28 Second

የተከበራችሁ የተከበራችሁ የዚሁ የዚሁ ስብሰባ ስብሰባ ተሳታፊዎች !! !! !! !!

በቅርቡ በሀገራችን በተፈጠረው ክስተት ምክንያት የኢትዮጵያ ፓለቲካና የህዝባችን መፃኢ ዕድል ምን ሊሆን ይችላል? የሚለው ጉዳይ እጅግ አነጋጋሪ በሆነበት ወቅት ብዙ የምንለው ነገር ቢኖርም ለግንዛቤ ይረዳን ዘንድ መድረኮች ከየት ተነስተን የት ለመድረስ ነው የምንፈልገው? በምን ሁኔታ ላይ ሆነን ነው እየታገልን ያለነው? የመድረክ የፓለቲካ እንቅስቃሴ ካለፈው ምን ይለየዋል? ወደፊትስ ምን ይጠብቀናል? በሚሉ አንኳር ነጥቦች ዙሪያ ስላሳለፍናቸው ሂደቶች ትንሽ ልበልና  አሁኑ ወዳሉት ጭብጥ ጉዳዮች ልመልሳችሁ።

የ1997ዓ.ም አገራዊ ምርጫ ከመካሄዱ ቀደም ሲል በርካታ ኢትዮጵያውን ዜጎችና ድርጅቶች ብቁ ተወዳዳሪ ሆነው  ለመገኘት መሰባሰብን ጀምረው እንደነበር የሚታወስ ነው። በዚህ መሠረትም ሁለት ግዙፍ ተቃዋሚ ስብስቦች ተፈጠረዋል። አንደኛው ስብስብ ቅንጅት በሚል የሚታወቅ ሲሆን ሁለተኛው ስብስብ ደግሞ አማራጭ ሀይሎች ይባል ነበር። እነዚህ ስብስቦች ዓቅማቸውን አጠናክረው ገዢውን ፓርቲ ስለተወዳደሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሕዝብ ድጋፍ አግኝተው በርካታ የፓርላማ መቀመጫዎችን ለማሸነፍ ችለዋል። ምርጫው ነፃና ፍትሓዊ ያልነበረ ቢሆንም ህዝቡ ከነበረው ቀራጥነትና የፓለቲካ ፓርቲዎች ከነበራቸው ብረቱ እንቅስቃሴ የተነሳ በከተማና በገጠር ከፍተኛ ድጋፍ አግኝተዋል። ይህ የቃዋሚዎች ከፍተኛ ድምፅ ማግኘት ኢሕአዴግ ያልጠበቀው ስለነበረ ሥልጣኔን ይቀሙኛል ከሚል
ሥጋት በመነሳት ወዲያውኑ የአስቸኳይ አዋጅ መሰል ድንጋጌ በማወጅ እንቅቃሴያቸው እንዲገታ አድርጓል። በርካታ የቅንጅት አመራር ለእስር ሲዳረጉ በአስር ሽዎች የሚቆጠሩ የከተማ ነዋሪዎችም እንዲሁ ወደ ካምፓች ተወስደው ታጉረዋል። በአዲስ አበባ በተከሰተው ፀረ መንግሥት ተቃውሞ ምክንያትም 193 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። የ97ቱ ክስተት ሶስት ነገሮችን አሳይቶን አልፏል። አንደኛ ሀገርንና ህዝብን ማእከል ያደረገ ራእይ ይዞ ዓቅሙንና ሕብረተሰቡን አስተባብሮ የሚታገል መሪ ድርጅት ካገኘ የኢትዮጵያ ህዝብ ለለውጥ ያለው ጥማትና ዝግጁነት ምን ያህል እንደሆነ በተግባር አረጋግጧል። ሁለተኛ ያስተማረን ትልቁ ጉዳይ ደግሞ የመጨረሻ ውጤቱ ባያምርም በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ ታግሎ በምርጫ ካርድ ስርዓት መለወጥም እንደሚቻል ነው። ሶስተኛውና የመጨረሻው ደግሞ በሰላም የሚደረገው ትግልም ምን ያህል ውስብስብና ፈታኝ ከመሆኑም በላይ የዓላማ ጥራት፣ የዓላማ ፅናት፣ የተቀናጀና የነቃ የአመራር ጥበብ እንደሚጠይቅ ነው።
ኢሕአዴግ ከምርጫ 97 በኋላ ትልቅ ትምሀርት የወሰደ ይመስላል። ይኸውም ምሕዳሩን እንደበፊቱ ገርበብ ካደረገውና ትንሽ ክፍተት ከፈጠረ ያለ ጥርጥር ሊሸነፍ እንደሚችል በመገንዘቡ ተከታታይ አፋኝ እርምጃዎችን ወስዷል። ከነዚህ ምሕዳሩን ከሚያጠቡ እርምጃዎች መካከል የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ፣ የፀረ ሽብር አዋጅና የሲቢል ማሕበረ ሰብ አዋጅ ተጠቃሾች ናቸው። ኢሕአዴግ ምሕዳሩን ለማጥበብ አዋጆችን ብቻ በማወጅ አልተወሰነም። ተጨማሪ አፋኝ አሰራሮችንም ተግባራዊ አድርጓል። በተለይም ቀጣዩ የ2002ዓ.ም ምርጫ ከመድረሱ በፊት ሕብረተሰቡን አንድ ለአምስት በማደራጀት
የስለላና የአፈና ማዋቀሩን አጠናክሯል አሳድ። ከዚህም ሌላ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን በአባልነት በመመልመል በሕብረተሰቡ ላይ ከባድ ተፅዕኖ አሳድሯል። እንዲሁም የፓረቲው ተቀፅላ የሆኑትን የወጣት ሊግ፣ የሴቶች ሊግና ሌሎች ፓርቲው የሚቆጣጠራቸው ማሕበራትን አድራጅቷል። በአጠቃላይ በአንዱ ወይም በሌላ መልኩ ዜጎችን የሚቆጣጠርበት አሠራርና አደረጃጀት አበጅቷል። ፓርቲው መንግሥትና ሕብረተሰብ በአንድ ላይ ተጠቃልለው በአንድ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ማዕቀፍ ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ በማቆራኘት በሀገሪቱ ውስጥ “ጠቅላይ አገዛዝን” ወይም ቶታሊቶሪያን
ተብሎ የሚጠራውን ስርዓት ተግባራዊ ለማድረግ ሞክሯል። ገዢው ፓርቲ የዚህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ በሚያካሂድበት ወቅት በተናጠል ይንቀሳቀሱ የነበሩ ድርጅቶች ተሰባስበው መንቀሳሰቀስ እንዳለባቸው በማመን “የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት – መድረክ” የሚል የስብስብ ጥንስስ ተፈጠረ። ይህ ስብስብ መጀመሪያ ላይ በስምንት ድርጅቶችና በሁለት ታዋቂ ግለሰቦች የተጀመረ ቢሆንም በኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ መሠረት ሕጋዊነት አግኝቶ ሲመዘገብ ግን የስምንት ድርጅቶች ስብስብ ብቻ ሆኗል። የምርጫ ሕጉ የፓርቲዎችን ስብስብ እንጂ የግለሰቦችን ስብስብ ስለማይቀበል ቅንጅቱ (መድረክ) የተመሠረተው በፓረቲዎች ብቻ ነበር።
መድረክ ሲሰባሰብ ከአሁን በፊት የነበሩ ስብስቦች አሉታዊ ጎኖችን በሚገባ አጢኗል። በተለይም ስብስቦች እንደ መስቀል ወፍ አንዴ ታይተው የሚጠፉበትና ወደ ተፈለገው ግብ ሳይደርሱ በአጭር ጊዜ የሚፈርሱበትን ምክንያት ለማጤን ሞክሯል። ካለፉትና በስልጣን ላይ ካሉት ስርዓቶች የወረስናቸው ኋላ ቀር የፓለቲካ ባህሎችና የርስ በርስ የመናቆር ልምዶች ምን ያህል ጎጂ መሆናቸውን በሚገባ ለመዳሰስ ሞክሯል። ስለሆነም መድረክ ወደ ሕጋዊ አደረጃጀት ከመሸጋሩ በፊት የሚስማማባቸውን የፓለቲካ አቋሞች አንጥሮ ለማውጣት በርካታ ወራትን የወሰዱ ውይይቶችና ክርክሮች
አካሂዷል። መጨረሻ ላይም 66 አንቀፆችን የያዘ መለስተኛ መርሀ – ግብር ለማፅደቅ ችሏል። መደረክ በዚሁ ሰነድ የኢትዮጵያን አንኳር የፓለቲካ ጥያቄዎችን ለመመለስ ሞክሯል። በመርሀ ግብሩ የተካተቱን ፓለቲካዊ አቋሞች በዚሁ ፅሑፍ ለመዘርዘር ባይቻልም ዋናዎችን መጥቀስ ግን ተገቢ ይመስለኛል።
የመድረክ አባል ድርጅቶች ከተስማሙባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች አንዱ የኢትዮጵያን አንድነት አጠንክሮ መጠበቅን ይመለከታል። ኢሕአዴግ በመርሀ ግብሩና በሕገ መንግሥቱ የኢትዮጵያን አንድነት የሚፈታትን አቋም አስፍሯል። ይህ የብሄሮችና የብሄረ ሰቦች የመገንጠል መብት የሚለው አቋም እስከ አሁን ተግባራዊ ባይሆንም እንድምታው ኢትዮጵያን የሚበታትን ነው። መድረክ የብሄር ብሄረሰቦች መብቶች እንዲጠበቅ የሚታገል ቢሆንም መገንጠልን ግን አይደግፍም።
“ከተመቸን አብረን እንኖራለን ከከፋን ግን እንበታተናለን” የሚለው የኢሕአዴግ አቋም የሀገራችን እውነታ፣ የህዝባችን ታሪክ፣ ህዝባችን የደረሰበት የመቀራረብና ሀገራዊ ንቃተ ህሊናን የማይገልፅ፣ ከጊዜው ጋር የማይሄድና ኢትዮጵያውያን ችግር ሲያጋጥማቸው በጋራ ተቋቁመው የሚወጡበትን፣ ዕድገትና ልማት ሲኖርም በጋራ የሚጠቀሙበትን ድልድይ መኖር እንዳለበት በማመን መድረክ ለኢትዮጵያ አንድነት በፅናት እንዲቆምና መገንጠልን እንደማይደግፍ በጋራ ተስማምቷል። መድረክ ኢሕአዴግ እየተከተለ ያለውን የዜጎች ነፃነትን፣ የሕግ የበላይነትን፣ ፍትሕንና ተጠያቂነትን የሚያጠፋና ብልሹ አስተዳደርን ሙሱናን አፈናን የሚያነግስ አብዮታዊ ዴሞክራሲን በጋራ እንደሚቃውምና በአገራችን ዴሞክራሲ፣ ሰብኣዊ መብትና የሕግ የበላይነትን የሚያሰፍን የፓለቲካ አቅጣጫ እንደሚከተል በመርሀ ግብሩ ውስጥ አስፍሯል። በዚህ መሰረትም መድረክ የፓለቲዊ አቋሞቹ በግለሰቦች ይሁንታና ፍላጎት የተመሠረተ ሳይሆን ተቋማዊ ህልውና እንዲኖራቸው እንደሚያደርግ በእያንዳንዱ አንቀፅ አስፍሯል። መድረክ የግለሰብም ይሁን የፓርቲ አምባገነንነት እንዳይሰፍን የአገሪቱ መሪ ከሁለት የሥልጣን ዘመን በላይ እንዳይቀጥልና የፓለቲካ ሥርዓቱም በመድብለ ፓርቲ ላይ እንዲመሠረት በይፋ አስቀምጧል። በአገራችን የዴሞክራሲ ዋስትና በተቋም ደረጃ ካልተረጋገጠ አፈናና አምባገነንነት እንደሚሰፍን በመገንዘብ መፍትሄ ይሆናሉ ያላቸውን ሁሉ በስፋት አስቀምጧል።
መድረክ በመርሀ ግብሩ ውስጥ ካሁን በፊት የኢሕአዴግ መንግስት ከኤርትራ መንግሥት ጋር ያደረገውን የአልጀሪስ ስምምነት እንደማይቀበልና ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት የሚያደርጋትን ሰላማዊ አቅጣጫ ተከተሎ እንደሚሠራ በመርሀ ግብሩ ውስጥ አካትቷል። ዓሰብ ከሕግ፣ ከታሪክና ከፓለቲካ አንፃር የኢትዮጵያ አካል እንደሆነች በጋራ ተስማምቷል።
መድረክ በኢኮኖሚው መስክም በርካታ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል። ልማታዊ መንግስት የሚለው የኢሕአዴግ ሞኖፓላዊ ስርዓት የእውነተኛውን ልማት ትርጉም በመሸፍን ጥቅል የአገር ገቢ ምርት ብቻ እንደ መነሻ በመውሰድ በአሃዞች ላይ የሚጫወት የሚያመላክት ሳይሆን የምርት ዕድገት እንደተጠበቀ ሆነ ህዝብን የልማት ባለቤት በማድረግ ፍትሓዊ የሀብት ክፍፍልንና የዜጎች ክብርን ጭምር የሚያካትት መሆንን በማመን ከዚህ አቅጣጫ ዘላቂና አስተማማኝ ልማትን ለማምጣት የሚያስችሉን አንቀፆችን አስፍሯል። በትምህርት በጤናና በሌሎች አገልግሎቶች ያሉትን የጥራት መጓደል እንደሚፈታና ሥራ አጥነትን፣ የንሮ ውድነትንና ድህነትን የሚፈቱ አቅጣጫዎችን እንደሚከተል በግልፅ በሰነዱ አስቀምጧል። መድረክ እነዚን የተስማማባቸውን በርካታ ጉዳዮች በመርሀ ግብር ደረጃ በመቅረፅ የሚሠራ ሲሆን ገና ስምምነት ያልደረሰባቸው ጉዳዮችም አሉ። እነሱም በመሬትና በፌደራል አወቃቀር ዙሪያ ያሉ ልዩነቶች ናቸው። መሬትን አስመልክቶ መድረክ ግማሽ ስምምነት ላይ ደርሷል። ይኸውም መሬት የህዝብና የመንግሥት ነው የሚለውን የኢሕአዴግ አቋም በመፃረር መሬት የህዝብ እንጂ የመንግሥት መሆን እንደሌለበት ተስማምቶ በመርሀ ግብሩ አስፍሮታል። ሆኖም መሬት ይሸጥ ወይስ አይሸጥ በሚለው ጉዳይ ላይ ገና ስምምነት አልደረስም። መድረክ የኢትዮጵያ የአስተዳደር ስርዓት አቀራረፅ ፌደራላዊ ሆኖ የጋራና የራስ አስተዳደር የሚኖር መሆኑን ቢስማማም የፌደራል አስተዳደሮች አከላለል በተመለከተ እንዴት
ይሁን በሚለው ላይ ግን ገና ስምምነት ላይ አልደረሰም። ፌደራል አከላለሉ መልከኣ ምድርንና ሌሎች መመዘኛዎችን መሠረት ያደረገ መሆን አለበት በሚለውና አሁን ባለበት በብሄርና እንዲሁም በርካታ ብሄሮችን ባካተተ መልኩ መካለል አለበት የሚሉ ልዩነቶች ተንፀባርቀዋል።
መድረክ የጋራ መርሀ ግብሩን ከቀረፀ በኋላ የሚተዳደርበትን ባለ 29 አንቀፅ ሕገ ደንብም አፅድቋል። መድረክ ከመርሀ ግብሩ ይልቅ የበለጠ ጊዜ የፈጀበት ይህን መተዳደሪያ ደንብን ለመቅረፅ ያደረገው ውይይትና ክርክር ነበር። አባል ድርጅቶች የሚስማሙበት መተዳደሪያ ደንብ ለመቅረፅ አንድ ዓመት ያህል ወስዷል። ያም ሆኖም እያንዳንዱ ፓርቲ የሚፈልገውን ሳይሆን በስጥቶ መቀበል መርህ ላይ ተመሥርቶ በጋራ የሚስማማበትን ሕገ ደንብ ለመቅረፅ ተችሏል።
የተከበራችሁ የዚሁ የዚሁ ስብሰባ ስብሰባ ተሳታፊዎች ተሳታፊዎች!!!! !!!!
መድረክ ገና በቅንጅት ደረጃ ተደራጅቶ እያለ የተስማማበትን መለስተኛ መርሀ ግብር በማንገብ በአንድ ምልከት ስር በ2002ዓ.ም አገር አቀፍ ምርጫ ተሳታፊ ለመሆን በቅቷል። ምርጫው መድረክ በቅንጅት ደረጃ እያለ ሕጋዊ እውቅና ቢያገኝም ገና በቅጡ ያልተደራጀበት ስለነበር ዋናው ጥረት በእያንዳንዱ ድርጅት የተደረገው ነበር። በምርጫው ወቅት የምርጫ አካባቢዎችን በመከፋፈል ረገድ መጠነኛ ልዩነቶች የተከሰቱ ሲሆን በተደረጉት ውይይቶችና ድርድሮች የምርጫ ክልሎች ለየፓርቲዎች ተደልድለው ከ450 በላይ በሚሆኑ የምርጫ ክልሎች ተሳትፈናል። በዘሁ ምርጫ ተወዳዳሪዎች የተቻላቸውን ጥረት ያደረጉ ቢሆንም የነበሩን የመቀናጀት፣ የገንዘብና የጊዜ እጥረቶች ታሳቢ ሲደረግ ዝግጅቱ በቂ ነበር ማለት አይችልም።
መድረክ ምርጫውን ለማሸነፍ ጥረት ቢያደርግም ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ከ97ቱ ልምድ በመውሰድ ቀደም ሲል እያንዳንዷን ድምፅ፣ እያንዳንዷን መቀመጫ ለመንጠቅ ወስኖ በይፋ ይንቀሳቀስ ነበር። ኢሕአዴግ ይህን አቋሙን በ2002ዓ.ም የመስከረም/ጥቅምት እትሙ በሆነው “አዲስ ራእይ” በተባለው ልሳኑ ይፋ አድርጎታል። በዚሁ መፅሄት ኢሕአዴግ ምርጫውን ለመጠቅለል ዜጎችን አንድ ለአምስት ማደራጀት እንዳለበትና በወቅቱ የነበሩት አምስት ሚሊዮን የኢሕአዴግ አባላት እያንዳንዳቸደው አራት ወይም ከዚያ በላይ በማደራጀት ምርጫውን በግል ሳይሆን በተደራጀ መልኩ
በቡድን እንዲካሄድ ወስኗል። ከዚህም ሌላ የመንግሥትና የፓርቲው ሚዲያዎችና መገናኛዎች ተቃዋሚዎች የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች እየተከከታተሉ እንዲቀርፁና የመድረክ መሪዎችና አባላት ለመወንጀል ለሚደረገው ክስ ማስረጃ እንዲያሰባስቡ በይፋ አቅጣጫ ተቀምጧል። ምርጫው በማንኛውም መንገድ ኢሕአዴግ እንዲያሸንፍ ተወስኗል።
ኢሕአዴግ አገር በቀል ሲቢል ማሕበራትን በሕግ ካፈረሰ በኋላ ራሱ የሚቆጣጠራቸውና የርሱ ተቀጥላ የሆኑ በተለምዶ ጎንጎ (Governmental, Non–governmental organizations) እየተባሉ የሚጠሩ ማሕበራትን በታዛቢነት አሰማርቷል።
ድጋፍ ይሰጡኛል ያላቸውን የአፍሪቃ ሕብረት ታዛቢዎችንም እንዲሁ አሰማርቷል። ኢሕአዴግ የሚፈራው የአውሮጳ  ሕብረት ታዛቦዎችን ስለሆነ ሲፈራና ሲቸር በመጨረሻ ሰዓት እንዲታዘቡ ፈቅዷል። ሆኖም ምርጫው ሊጀመር አንድ ወር ሲቀረው ስለደረሱ ሂደቱን በሙሉ ሊመለከቱ አልቻሉም ነበር። የአውሮጳ ታዛቢዎች ከመድረሳቸው በፊት ኢሕአዴግ 210,000 ምርጫ አስፈፃሚዎችን በብቸኝነት መድቧል። እነዚህ ምርጫ አስፈፃሚዎች ከሞላ ጎደል የኢሕአዴግ አባላትና ደጋፊዎች ነበሩ። በተመሳሳይ 210,000 ታዛቢዎችን ኢሕአዴግ ብቻውን ለማስመረጥ አሰማርቷል ። የምርጫውን
መጭበርበርና መዝረፍ የሚያስፈፅሙት እነዚህ ነበሩ። በምርጫው ወቅት ሌላው አስገራሚና አስደንጋጭ የነበረው በገዢው ፓርቲ በይፋ ይሰነዘሩ የነበሩት የስነ ልቦና ጦርነቶችና የአካል ጥቃቶች ናቸው። ለምሳሌ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ምርጫው እንዳበቃ የመድረክ አመራር ይታሰራሉ ብለው አውጀው ነበር። ሀገር ውስጥ ያሉትን ሰጥ ረጭ አርገው ሲያበቁ በውጭም የአሜሪካንና የጀርመን ሬድዮ ድምፆችን በአፋኝ ሞገድ ለመቆጣጠር ሞከሩ። ይህ ብቻ አይደለም ምርጫውን ለማጭበርበርና በብቸኝነት ለማሸነፍ ያልሞከሩት ዘዴ አልነበረም። በዚሁ የምርጫ እንቅስቃሴ ሂደት የመድረክ ዕጩዎች ተገድለዋልል። ተገርፈዋል፣ ታስረዋል።
በዚሁ ምርጫ መድረክ ያቀረባቸው በርካታ ታዛቢዎችም ተዋክበዋል፣ ታስረዋል፣ ተሰደዋል። ባጠቃላይ ምርጫው ሰላማዊ ሂደት የጎደለው ስለነበር ልክ ጦርነት የታወጀ ይመስል እንደነበር ታሪክ ዘግቦት አልፏል። በዚህ ሂደት የተከናወነው ምርጫ ኢሕአዴግ 99.6% እንዳሸነፈ ይፋ አድርጓል። ኢሕአዴግ ቀደም ሲል ባቀደው መሠረት ሁሉንም ድምፅ በመጠራረግ የአንድ ፓርቲ አምባነነቱን አረጋግጧል። ምርጫው ነፃና ፍትሓዊ እንዳልነበረ ገለልተኛ ነው የተባለው የእውሮጳ ሕብረት ታዛቢ ቡድን አረጋግጦታል። “ምርጫው ዓለም ዓቀፍ ደረጃውን ያልጠበቀ ነው” በማለት ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ ገልፆታል። ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትም ገዢው ፓርቲ አገኘሁ ያለውን የምርጫ ውጤት አምባ ገነንነቱ ብቻ ሳይሆን በሕገ መንግስቱ የሰፈሩ መብቶች የውሸትና የይስሙላ መሆኖቸውን
ከማረጋገጡም በላይ ፓርቲው የዲሞክራሲ ጭላንጭልን በማጨለም ራሱን ወደ ጥፋት እያዘገመ እንደሆነም ዘግበው አልፈዋል። እኛም ባለው ሥርዓት ፍትሕ ይገኛል የሚል እምነት ባይኖረንም ለታሪክ ስንል ምርጫው ተዘርፈዋል በማለት ክስ መስርተን ተከራከረናል። ኢሕአዴግ የዘረፋቸው የታቃዋሚ የምርጫ ካርዶችንና ኢሕአዴግ የተጠቀመባቸው ሕገ ወጥ ካርዶችን ያካተቱ 81 ያህል ማስረጃዎችን በማቅረብ ክስ ብንመሰርትም የአገሪቱ ፍርድ ቤቶች ምርጫው ትክክለኛ ነበር በማለት ውሳኔ ሰጥተዋል። በገዢው ፓርቲ የተዋቀረው የምርጫ ቦርድም እንዲሁ ምርጫው ነፃና ፍትሓዊ ነበር በማለት
መስክሯል።
እንግዲህ ቀደም ብዬ ከላይ እንደገለፅኩት እኛ ወደ 2002 ዓ.ም ምርጫ ስንገባ የዓቕም፣ የድርጅታዊ ጥንካሬና የገንዘብ ማነስ ብቻ አይደለም የተፈታተነን። የተወዳደርነው ሕግና በዜጎች ልዕልና ከማያምንና ከማያከብር ፓርቲ ጋር ነበር። የተወዳደርነው ኳስ ሰጥቶ የመጫወቻ ሜዳ ከሚከለክልና የመጫወቻ ሕግጋትን ከማያከብር መንግስት ጋር ነበር። የተወዳደርነው ከአንድ ፓርቲ ጋር ሳይሆን የመንግስት ጡንቻ ተጠቅሞ የሀገሪትዋን ሰብኣዊና አንጡራ ሀብት በማንቀሳቀስ ለተቃዋሚዎች መጨቆኛና የምርጫ ካርድ መዝረፍያ ካዋለ መንግስት ጋር ነበር። ባጠቃላይ መድረክ ወደ ውድድሩ ሲገባ ነፃ የምርጫና የፍትሕ ተቋማት በሌሉበት፣ የዜጎች የሕግ የበላይነት ባልተረጋገጠበት፣ በተወዳዳሪ ፓርቲዎች መካከል ፍትሓዊና ሚዛናዊ የሆነ የሃፍትና የገንዘብ ክፍፍልና መደላድል በሌለበት መሆኑን እሙን ነው። ያ ሁሉ መከራ በትዕግስትና በጥበብ ተቋቁሞ ያገኘነው የምርጫ ውጤት የፓርላማ ወንበር የሚያስገኝ ባይሆንም ቅሉ የሌሎች ክልሎች ሳይጨምር በአዲስ አበባ መስተዳድር ብቻ ከ350,000 በላይ ካርድ ለማግኘት ችለናል። ይህ ቁጥር በኛ አመለካከት ቀላል ግምት የሚሰጠው አልነበረም። ምርጫው ነፃና ፍትሓዊ ቢሆን ኖሮና እኛም ተጠናክረንና ጎልበተን ብንሳተፍ ኖሮ ዉጤቱ ምን ሊሆን ይችል ነበር? የሚለውን ጥያቄ እንድናነሳ አድርጎናል።
መድረክ በምርጫው ውጤት ተስፋ አልቆረጠም። ምክንያቱም በየጊዜው የሚደረገው ምርጫ የትግል ሂደቴ አካል እንጂ የትግሉ መደምደሚያ አድርጎ አያየውም። ይልቁንስ በምርጫ 2002 በህዝብ ፊትና በዓለም ማሕበረሰብ ዘንድ ማንነቱን የተጋለጠውና የተስፋ መቁረጥ እርምጃ የወሰደውና 99.6% አሸነፍኩ ብሎ ያወጀው መንግስት ነው። በዚሁ ሁኔታ ምርጫው ከተጠናቀቀ በኋላ መድረክ ከእንግዲህ ምርጫ ይካሄድ ዘንድ ምሕዳሩን ሊያሰፋ ይችላሉ በሚባሉ ጉዳዮች ዙሪያ እንደራደር በማለት ለኢሕአዴግ ጥሪውን አቅርቧል። ለድርድር ካቀረብናቸው ነጥቦች መካከልም ነፃና ፍትሓዊ ምርጫ
ይካሄድ ዘንድ 1) ተቃዋሚዎች በነፃ ስብሰባ እንዲጠሩ፣ ሰላማዊ ሠልፍ እንዲወጡና ተቃውሞ እንዲያሰሙ መፍቀድ። 2) በምርጫ ሕጉ መሠረት መንግሥት ለተቃዋሚዎች ፍትሓዊ የገንዘብ ድጎማ እንዲያደርግ። 3) የመንግሥት ሚዲያዎች ተቃዋሚዎች ይጠቀሙባቸው ይችሉ ዘንድ ክፍት እንዲደረጉ ማድረግ። 4) የግል ሚዲያዎች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ መፍቀድ። 5) ሲቢል ማሕበረ ሰብ በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ማስቻል የሚሉ ነጥቦች ይገኝባቸዋል። ከፍ ብለው በተጠቀሱት ጉዳዮች ዙሪያ ለመደራደር በተደጋጋሚ ጥሪ ብናቀርብም መጨረሻ ላይ በሽማግሌዎች የተላከልን መልስ “ድርድር ለማድረግ ከፈለጋችሁ በቅድሚያ የምርጫ ኮዱን ተቀብላችሁ ፈርሙ” የሚል ነበር። መድረክ የአገራችን የፓለቲካ ችግር የምርጫ ኮድ በማውጣት እንደማይቀረፍ በመገንዘብ በእንግሊዞች አመቻችነት የቀረበውን ይህን
የምርጫ ኮድ የመወያየትና የመስማማት ጉዳይ ውድቅ አድርጎታል። ሆኖም ኢሕአዴግ ይህን የምርጫ ኮድ ከኢደፓ፣ ከቅንጅት፣ ከመኢኣድና ከመሳሰሉ ድርጅቶች ጋር ከተወያየ በኋላ የነሱን ይሁንታ አግኝቶ ለፓርላማ ቀርቦ እንዲፀድቅ አድርጎታል። ይህን በፓርላማ የፀደቀውንና ማንኛው ዜጋ ሊያስገድድ የሚችለውን ሕግ ካወጡ በኋላ ለመደራደር በቅድሚያ ፊርማችሁን አኑሩ ማለት ድርድር ለማካሄድ ፍላጎት እንደሌለ የሚያመላክት ሲሆን መድረክን በአባላቱና በህዝቡ ፊት ለማዋረድ የተቀየሰ ስልትም ነው። ማንኛውም ድርጅት በፀደቀ ሕግ ላይ ፈርም ተብሎ እንደማያውቅና እንደማይገደድ ለዚህ ማስረጃ ይሆናል። የተከበራችሁ የዚሁ የዚሁ ስብሰባ ስብሰባ ተሳታፊዎች ተሳታፊዎች!!!! !!!!
መድረክ በአሁኑ ጊዜ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ለወደፊት ሊያጋጥሙት የሚችሉ ፈተናዎችስ ምንድን ናቸው? ችግሮችን ለመፍታትና ለቀጣዩ ምርጫ አስተማማኝ አማራጭ ሆኖ ለመሳተፍስ ምን ያህል ተዘጋጅቷል? ተደጋግመው የሚቀርብልን ጥያቄዎች ናቸው። አዎ!! መድረክ ከምርጫ በኋላ ራሱን ለማጠናከርና ከህዝቡ ጋር ያለውን ትስስር ለማጎልበት ጥረቶች አድርጓል። ካደረጋቸው እንቅስቃሴዎች መካከል ትልቅ ትኩረት የሰጠው ግን ራሱን ወደ ላቀ አደረጃጀት ማሸጋገርን ነበር። በኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ መሠረት ፓርቲዎች በሦስት ደረጃ ሊደራጁ ይችላሉ። 1ኛ) ቅንጅት (Coalition) 2ኛ) ግንባር 3ኛ አንድ ወጥ (አሃዳዊ) ፓርቲ መሆን ነው። መድረክ በአሁኑ ጊዜ ከቅንጅት ወደ ግንባርነት ተሸጋግሯል። ቅንጅት በፓርቲ መሪዎች ስምምነት መሠረት የሚደረግ ጥምረት ሲሆን የጋራ መርሀ ግብርና ሕገ ደንብ ይኖር ዘንድ የግድ አይልም። በዚሁ ጥምረት ከጋራ ይልቅ የአባል ድርጅቶች ህልውና ጎልቶ ይወጣል። በግንባር አደረጃጀት ግን የጋራ መርሀ ግብርና የጋራ መተዳደሪያ ደንብ ያለውና ከግል ፓርቲዎች ይልቅ የጋራ ጥምረት ጎልቶ የሚታይበት ነው። በመሆኑም ወደ ግንባር መሸጋገር ማለት በርካታ የጋራ ሥራዎችን በጥምረት መሥራት የግድ ይላል። ከነዚህ ሥራዎች መካከል፡-
1ኛ ጠንካራ ማዕከላይ አመራርና ፅ/ቤት (Headquarter) በጋራ ማቋቋም
2ኛ ሁሉም አባል ድርጅቶች በጋራ በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች የጋራ ፅ/ቤት ማቋቋም
3ኛ የጋራ ልሳኖች የሆኑትን ሚዲያዎች፣ ጋዜጣ፣ ድሕረ ገፅ፣ ወዘተ በጋራ ማቋቋም
4ኛ በውጭ አገር የጋራ የተቀናጀ አደረጃጀትና እንቅስቃሴ እንዲኖር ማድረግ
5ኛ የጋራ የህዝብ ስብሰባዎችን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ማካሄድ ይገኙባቸዋል።
በአጠቃላይ እያንዳንዱ ድርጅት ከግሉ ይልቅ የግንባሩን እንቅስቃሴ ቅድሚያ ተሰጥቶት እንዲፈፀም ይደረጋል። የደረሰንበት አደረጃጀት በተመለከተ ከሚነሱ ጥያቄዎች አንዱ መድረክ በግንባር ደረጃ መደራጀቱ በቂ አይደለም ። እንዲያውም ከነበረበት የሕብረት ደረጃ የሚለየው የለም። ስለዚ ቶሎ በአንድ ፓርቲ መዋሃድ አለበት የሚል ነው።
በእርግጥ ከግንባር ይልቅ ውሁድ ፓርቲ የተሻለ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ሆኖም የመድረክን ታሪካዊ ሂደት ለሚያጤን ሁሉ በአንድ ጀምበር ብድግ ብሎ ከሕብረት ወደ ውሁድ ፓርቲ ለመሸጋገር ከነበርንበት ነበራዊ ሁኔታ ጋር ሲነፃፀር አዳጋች ቢሆንም ይህንን ሁኔታ በመገንዘብ መድረክ አሁን ከደረሰበት የግንባር አደረጃጀት ወደ አሃዳዊ ፓርቲ የሚሸጋገርበት ስትራተጂ በግልፅ ተቀምጧል። በዝቅተኛው የአደረጃጀት ደረጃ ጀምረን ቀስ በቀስ ወደ ውህደት ለማምራት በስምምነት ሰነዳችን ሠፍሯል። ይህ ተግባራዊ ለማድረግም ሁለተኛው ምዕራፍ ላይ ደርሰናል። ይህ የግንባር አደረጃጀታችን
ሳይሳካና ገና እግር ሳይተክል ዘለን ወደ አንድነት መሄዱ አስቸጋሪ ይሆናል። ሂደቱን ጠብቆ ወደ ውህደት ለመሸጋገር የሚያስፈልገውን ቅድመ ሁኔታ ማሟላት ያስፈልጋል። በመሆኑም በእነዚያ የማያስማሙንን ሁለት ጉዳዮች ላይ መወያየት ተገቢ ነው። መድረክ በነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ ለመወያየትና ለመከራከር በአጀንዳነት ይዞታል። መድረግ ከየት ተነስቶች ወዴት መድረስ እንዳለበት የኢትዮጵያ ውስብስብና ዘርፈ ብዙ የፓለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማሕበራዊ ችግሮችን መነሻ በማድረግ ዓለማዎች፣ ስትራጂዎችና መርሃ ግብር በመቅረፅ የመሪ ድርጅት ጥያቄ የመለሰ ቢሆንም ዓላማውን ለማሳካት የሚደረገው ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል ቀላልና አልጋ ባልጋ እንዳልሆነ ይገነዘባል። እስካሁን ካለን ልምድና ለወደፊት ሊያጋጥሙ ይችላሉ ብለን ከምንገምታቸው ፈተናዎች ውስጥ ስርዓቱ የሚከተለው ፓለቲካዊ
ምሕዳሩን የማጥበብ ፓሊሲ፣ ኋላ ቀር የፓለቲካ ባህላችን፣ የገንዘብና የማተሪያል ዓቅም ማነስ ሊጠቃለሉ የሚችሉ ናቸው።
በአንድ ሀገር በሰለጠነ አመለካከት ላይ የተመሰረተ ነፃና ፍትሓዊ የፓለቲካና የኢኮኖሚ ውድድር (ተፎኳኳሪ) ሲኖር ከማንም በላይ ተጠቃሚ የሚሆነው ሕብረተ ሰቡ ነው። ይህ እውን ሊሆን የሚችለው ደግሞ በሀገሪቱ ከትውልድ ትውልድ ሊሸጋገሩ የሚችሉ፣ በህዝብና በመንግስት መካከል ያለው ግንኙነት ሚዛን የሚጠብቁ ነፃ ህዝባዊ ተቋማት(ኢንስቲቱሽን) ሲያብቡ ነው። ነፃ የፍትሕ የዳኝነትና የዲሞክራሲ ተቋማት ሲመሰረቱ ነው። አማራጭ ሃሳብ የያዙ የፓለቲካ ድርጅቶች ወደ ህዝቡ በነፃ ቀርበው ሲዳኙና ህዝቡ የስልጣኑን ምንጭ ለመሆን ሲችል መሆኑን እሙን ነው።
ይሁን እንጂ በሀገራችን ያለው ፓለቲካዊ ምሕዳር ጠባብ ብቻ ሳይሆን ሊዘጋ የተቃረበ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። በምርጫ 2002ዓ.ም እና ከዚያም በኋላ እየተወሰዱ ያሉት አፋኝ እርምጃዎች የስርዓቱን ማንነትና አምባ ገነንነት የሚያመላክቱ ማስረጃዎች ናቸው። በተለይም የፕሮፓጋንዳ ዘመቻቸው በመድረክ ላይ በማነጣጠር በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነትና አሜኔታ እንዳያገኝ፣ የገንዘብና ድርጅታዊ አቕሙ እንዲዳከም፣ አባላቱ ተስፋ ቆርጠው እንዲበታተኑ ለማድረግ፣ ተቃዋሚ ድርጅቶች ወደ ዋናው ሀገራዊና ህዝባዊ ጉዳዮች እንዳያተኩሩና ለጋራ ችግራቸው በጋራ ተባብረው እንዳይታገሉ በመካከላቸው ሰርጎ በመግባትም ሆነ በማስፋራራት አለመተማመንና ጥርጣሬ እንዲሰፍን ለማድረግ በጋሃድና በረቀቀ መልኩ እንቅልፍ አጥተው ይሰራሉ።
ለምሳሌ በሰዎች አእምሮ ላይ የተሳሳተ ስዕል ለመፍጠር ተደጋግመው ከሚነሱ ስሞታዎች አንዱ መድረክ ደካማ ስለሆነ አገር ለማስተዳደር (ለመምራት) አይችልም የሚለው ነው። ይህ ስሞታ በምርጫው ጊዜም ሆነ ከዚያ በኋላ ተደጋግሞ ተነግሯል። በእርግጥ መድረክ ከድርጅታዊ ዕድገት አንፃር ገና አልጎለበተም መጎልበትና መጠናከር ይኖርበታል። ሆኖም በማንኛውም መመዘኛ ዓላማው ከኢሕአዴግ ልቆ ይገኛል። በኛ እምነት ዓላማዎቻችን በደጋፊዎቻችን ብቻ ሳይሆን የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ በኢሕአዴግ ደጋፊዎችም ጭምር ተቀባይነት ይኖራቸዋል ብለን እንተማመናለን። መድረክ ያሰባሰባቸው
ሰዎችም ከኢሕአዴግ አመራር የሚያንሱ አይደሉም። አገር ለመመራት የሚያስፈልገው ዋነኛው ሚስጢር ግን የጥቂት ብልህና ብቁ መሪዎች መኖርና አለመኖር ጉዳይ አይደለም። የሚልዮኖችን ዕምቅ ዕውቀትና ክህሎት ነፃነት በሰፈነበት ሁኔታ ሥራ ላይ እንዲውል የሚያደርግ ሥርዓት በአገር ደረጃና ከዚያም በታች ባሉ የአስተዳደር እርከኖች በርካታ መሪዎችን ሊፈጥር ይችላል። መድረክ አገርን ለመምራት በፓለቲካ መሪዎች ብቻ አይተማመንም። አገር ለመምራት ከህዝብና ከሌሎች ፓርቲዎች ጭምር እንዲሳተፍ ያደርጋል እንጂ። በዚህ አጋጣሚ መድረክ ኢትዮጵያን ለመምራት በቂ ዓቅም ያለው መሆኑ ለማረጋገጥ እወዳለሁ።
ሌላው የሚነሳው ጥያቄ የመድረክ መሪዎች እርስ በራሳቸው አይስማሙም አይተማመኑም የሚለው ነው። መድረክ በአንድ ግለሰብ ወይም ፓርቲ አምባገነንነት ሥር ስለማይመራ ልዩነቶች ወደ መድረክ እያወጡ ይወያይባቸዋል። በወሳኝ ጉዳዮች ዙሪያ መግባባት የሚደረሰው በጥልቀት ከተወያየ፣ ከተከራከረና ከዚያም አልፎ ከተደራደረ በኋላ ነው። ይህ መከፋፈልንና አለመስማማትን አያመለክትም። መድረክ ስልጣን እንደ ርስት የሚያዝበት የጥቂት መሪዎች ንብረት ሳይሆን በግልፅነት፣ በተጠያቂነትና በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ ውስጠ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ባህል በማጠናከር በቀጣዩ
ሂደትም በጠንካራ ዓለት ላይ የተገነባ አንድነት ለመፍጠር የሚያገለግል ይሆናል። መድረክ ላለፉት አምስት ዓመታት የዘለቀውም እየተወያየ፣ እየተከራከረና እየተደራደረ ነው። ይህ የሰለጠነ የፓለቲካ ባህል የግንባሩን የጥንካሬ ሚስጥር ስለሆነ ለወደፊቱም በዚሁ የሚቀጥልበት ይሆናል።
ሌላው ከተለያዩ ሰዎች የሚደርስብን ትችት ደግሞ መድረክ የሚከተለው ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል በስልጣን ላይ ላለው ስርዓት ተቃዋሚ አለ ለማለት የዲሞክራሲ ሽፋኝ በመስጠት ከመጥቀም አልፎ ለኢትዮጵያ ህዝብ ትግል ፋይዳ የለውም። የሚያዋጣም መንገድ አይደለም የሚል ነው። ምሕዳሩ ስለጠበበና ፕሬስ ስለተዘጋ በሰላም ታግሎ ለውጥ ማምጣት አይችልም የሚለው ነው። ምሕዳሩ እጅግ ጠባብ መሆኑ እንስማማለን። ጭራሽ የማያላውስ ነው። ሆኖም በአዋጅ እስካልተዘጋ ድረስ ሐሳባችንን ህዝቡ ዘንድ እንዲደርስ ለማድረግ እንቀጥላለን። የፓለቲካ ትግል ፋይዳ አማራጭ ሓሳብ ህዝቡ ዘንድ እንዲደርስ አድርጎ ህዝቡ ዉሳኔ ሰጪ እንዲሆን ማስቻል ነው። በዚህ ረገድ እየተረገጥንም፣ እየታሰርንና እየገደልንም ቢሆን ዓላማችንን እናስተምራለን። በቅርብ ተገኝተን ዓላማችን ህዝብ እንዲያውቀውና እንዲገነዘበው ማድረግ ማለት ከመድፍና ከሰራዊት በላይ የበለጠ ሓይል አለው ብለን እናምናለን። ስለሆነም አላማችን ሲቢሉን ብቻ ሳይሆን ታጣቂውንም ጭምር የማሸነፍ ሀይል አለው ብለን እናምናለን። አሁንም ቢሆን የመድረክ በአማራጭነት መታየት በየቤቱ ገብቷል። በዚህ አቅጣጫ ጠንክረን እንሠራለን።
ኢሕአዴግ ጠብመንጃ ያነገተ ሀይል መቆጣጠሩ ጠንካራ አድርቶጎ መመልከቱ የተሳሳተ ነው። በአርግጥ ነፃነት ፋላጊዎችን እያፈነ ያለው ታጣቂዎችን በመጠቀም ነው። ያም ሆኖም ግን ዓፈናም ድንበር አለው። የሰዎች ጭንቅላትና የማሰብ ነፃነት በጠመንጃ ሐይል አይገታም። የዓላማ የበላይነቲ ከተረጋገጠ የሀይል ሚዛን ለውጡ ይከተላል። የሀይል ሚዛን ለውጥ በወታደርና በመሳሪያ ብዛት የሚመዘነው ሥርዓቱን ለመቀየር የትጥቅ ትግል ሲመረጥ ነው። በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ በሚደረግ ትግል ግን የሃይል ሚዛን የሚለወጠው በሓሳብ የበላይነት ነው። መድረክም በዚህ መንገድ አምኖ
እየሰራ ይገኛል። እርግጥ ነው መድረክ የሓሳብ የበላይነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ መሥዋእትነት እያደረገ ቆይቷል። ከሚደርስበት የሥነ ልቦና ጫና ባሻገር የአባላትና ደጋፊዎች ከሥራ መፈናቀል፣ ዕድገት መከልከል፣ እስርና ግድያ ተጠቃሽ ነው። በርካታ የመድረክ ደጋፊዎች የነዚህ ሁሉ ሰለባዎች የሆኑ ሲሆን የሥራ አስፈፃሚ አባላቱ የነበሩት አቶ አንዱ ዓለም አራጌና አቶ በቀለ ገርባሞ በአሸባሪነት ተከሰው በእስር እየማቀቁ ይገኛሉ። የምክር ቤቱ አባል የሆኑት አቶ ኦልባና ሌሎችም እንዲሁ በእስር ላይ ይገኛሉ። የመድረክ አባላት ባይሆኑም ለነፃነትና ለፍትሕ በመታገላቸው ምክንያት የታሰሩ ጋዜጠኞችም
ተጠቃሾች ናቸው። በዚህ ረገድ ታዜጠኛ እስክንድር ነጋና ሪእዮት ዓለሙም መጥቀስ ይቻላል። ነገር ግን አንድ ሐቅ አለ። እሱም አምባ ገነኖች ምሕዳሩን ባጠበቡና በህዝብ ላይ ግፍ እየፈፀሙ በሄዱ ቁጥር ከላይ እንደጠቀስኩት ጭቆና ድንበር አለውና የህልውናቸው ማክተሚያ እየተቃረበ እንጂ እየጠነከሩ አይደለም የሚሄዱ። አሁን ያለንበት ዘመንም አደንቁረህና አፍነህ ረጅም ጊዜ ለመግዛት የሚመች አይደለም። ዘመኑ አምባ ገነኖች እየከሰሙ በአንፃሩ ለነፃነትና ለዲሞክራሲ የሚደረገው ትግል እየጎለበተ በመሄድ ላይ ነው። ዛሬ በዓለማችን ዙሪያ የሚታየው የነፃነትና የፍትሕ ጥያቄ፣ የህዝቦች
መነሳሳትና መተባበር፣ የቴክኖሎጂ ዕድገት፣ የሶሻል ሚዲያዎች መስፋፋትና ሌሎች የሳይንስ ውጤቶች ተደማምረው አምባ ገነኖች ሊቆጣጠሩት በማይችሉት ሁኔታ የሰዎች ንቃተ ህሊናና አልገዛም ባይነት መንፈስ በማጎልበት ትልቅ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛሉ። ስለሆነም እኛ ኢትዮጵያውያንም የገንዘብ ዓቅም ካልሆነ በስተቀር የቴክኖሎጂና ሶሻል ዕድገት ተጠቃሚ ለመሆን የሚገድብብን ነገር አይኖርም።
ሌላው መድረክን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የሀገራችን የፓለቲካ ሂደት እየጎዳና እየተፈታተነ ያለው ካለፉትና አሁን ካሉት የፓለቲካ ስርዓቶች የወረስነው ኋላ ቀር የፓለቲካ ባህል ነው። ልዩነት ይዞ በሰለጠነ መንገድ ለጋራ ሀገርና ህዝብ ሲባል አብሮ መስራት፣ አለ መግባባቶችን በሰከነና በሰጥቶ መቀበል መርህ በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብሎ መፍታት። ከራስህ ስህተትና ከሌሎች ተመኩሮ መማር የመሳሰሉ ጉዳዮች በሀገራችን የፓለቲካ ባህል እንደ ፀጋ ሳይሆን እንደጠላትነት፣ እንደፍርሃትና እንደውርደት የሚቆጠሩ ናቸው። በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በሀገራችን ጉዳይ ላይ ያገባናል የሚሉ የሲቢክና የፓለቲካ
ሀይሎች ሕገ መንግስቱ የፈቀደላቸውን መብት አክብሮ እነሱን የሚሳተፉበት ሁኔታ ከማመቻቸትና አብሮ በመወያየት ለሁሉም የሚበጅ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ አውራ ፓርቲ ነኝ በማለት ሌላውን በአጃቢነት ወይም በጠላትነት በመፈረጅ በጡንቻ እየገዛ ይገኛል። ይህ እርምጃ ለሀገራችንም ሆነ ከማንም በላይ ለራሱ ለኢሕአዴግም የማይበጅ አደገኛ አካሄድ መሆኑን ደጋግመን ገልፀናል። በፅሑፉም አሳውቀናል።
በተለያየ አደረጃጀት በተቃዋሚ ጎራ ያለን ሰዎችም ብንሆን ከዚሁ ኋላ ቀር የፓለቲካ ባህል የፀዳን ነን ማለት አይቻልም። አብዛኞቻችን የምንግባባቸውን የጋራ ጉዳዮቻችን ከማጎልበትና ከማጠንከር ይልቅ የሚለያዩንን ነገሮች ስናጎላ እንታያለን። የሀገርና የህዝብ ጉዳይ ከማስቀደም ይልቅ የየግላችን ድርጅታዊ ፍቅር ያጠቃናል። ያለፈውን ስህተት ለታሪክ ትተን ስለነገ ዕድላችን ከማሰብና ከማውራት ይልቅ ስላለፈው ቁሱልና ብሶት እያነሳን ስንናቆር የነገውን ዕድል ያመልጥብናል። ይህ በመሆኑም በኛ ድክመት፣ መኰራረፍ፣ ልዩነትና መነጣጠል የተጠቀመው የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል ሳይሆን በስልጣን ላይ ያለው ጨቋኝ ስርዓትን ነው። በተናጠል መንቀሳቀሳችን በስልጣን ላይ ያለው ሀይል እኛን ነጣጠሎ ለመምታትና ለማፈን ምቹ ሁኔታ የምንፈጥርለት እኛው ራሳችን ነን። ለምሳሌ አስር የሚለያዩን ነጥቦች ቢኖሩና በአንድ ነጥብ ብቻ እንኳን ተግባብተን በጋራ ለመስራት ብንሞክር ሌሎች ልዩነቶችን ቀስ በቀስ መፍታት እንችላለን የሚል እምነት አለኝ። ይህም ላለፉት ጥቂት ዓመታት በመድረክ ዙሪያ በተግባር ያየነው ስለሆነ ከሌሎቻችሁ ጋርም በተመሳሳይ ልዩነት ይዞ በሚያግባባን የጋራ ጉዳይ ብቻ ተስማምተን አብሮ መስራት ይቻላል የሚል ፅኑ እምነት አለን።
የተከበራችሁ የዚሁ የዚሁ ስብሰባ ስብሰባ ተሳታፊዎች ተሳታፊዎች!!!! !!!!
መድረክ ዕቅዶችን ለማስፈፀም ከፍተኛ ተግዳሮትና ማነቆ ከሆኑት ሌላው ዓቢይ ጉዳይ የፋይናንስ ዓቅም ደካማ መሆን ነው። እስካሁን ድረስ ሥራዎቹን ሲያካሂድ የቆየው በአባል ድርጅቶች መዋጮና ደጋፊዎቹ በሚያደርጉለት መጠነኛ ድጋፍ ነው። በእርግጥ በምርጫ ጊዜ መንግሥት የሚያደርገው የተወሰነ ገንዘብ አለ። ይህ ገንዘብ ምርጫ ለማካሄድ ቀርቶ የተፃፉ ፓስተሮች ለማሳተምም በቂ አይደለም። ከምርጫ ውጭ ፓርቲዎች የዕለት ተዕለት ሥራ ለማከናወን መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል የሚል ሕግ ያለ ቢሆንም ኢሕአዴግ ይህንን ሕግም በሚያስገርም ሁኔታ ረግጦታል። በየዓመቱ ለፓርቲዎች
ሥራ ማስኬጃ የሚመደበው ገንዘብ 11 ሚልዮን ብር ሲሆን ይህን ገንዘብ ከሞላ ጎደል የሚወስደው ኢሕአዴግ ነው። ከዚህ ገንዘብ በየዓመቱ የመድረክ ድርሻ በሚል የሚሰጠን ገንዘብ 3500 ብር (195 አሜሪካን ዶላር) ብቻ ነው። ቀሪውን ገንዘብ ኢሕአዴግ ከወሰደ በኋላ ወዳጆቼ ለሚላቸው ለነ ኢደፓና ቅንጅት ያከፋፍላል። መድረክ ዓላማውን የሚደግፉ በርካታ ደጋፊዎች ቢኖሩትም ያለውን አፈና በመፍራት ተገቢውን የገንዘብ ድጋፍ አያደርጉለትም። ስለሆነም በድርጅቶች መዋጮ ብቻ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
የመንግሥት ሚዲያዎች ለራሱ ለገዢው ፓርቲ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ የሚሉ እንጂ የኛ ዓላማን ለማሳወቅ ያለው ዕድል ጭራሽ የተዘጋ መሆኑን ቀደም ብዬ በመግቢያው ገልጫለሁ። መድረክ የመንግሥት ሚዲያዎችን የመጠቀም መብቱ እንዲረጋገጥለት በተደጋጋሚ ጥያቄዎች ቢያቀርም አሁንም የምርጫ ኮዱን ካልፈረማችሁና በጋራ ለመሥራት ካልወሰናችሁ ሚዲያው አይከፍትላችሁም በማለት በሩን ዘግቶት ይገኛል። አነሰም በዛም ቅንጅት፣ ኢደፓና ሌሎች በመንግሥት ሚዲያ ሲጠቀሙ በአንፃሩ መድረክ ግን የሚያወጣቸውን መግለጫዎች ሊተላለፉ ቀርቶ የሚዲያውን ደጃፍ እንኳን ለመድረስ
አልተፈቀድለትም።
መድረክ በኢትዮጵያ ከገዢው ፓርቲ በላይ የዓላማና የሞራል የበላይነት አለኝ ብሎ የሚተማመን አማራጭ የፓለቲካ ድርጅት ቢሆንም ቀደም ብዬ ከላይ እንደገለፅኩት በህዝቡ ፊት ቀርቦ ተወዳድሮ ለማሸነፍ በአሁኑ ጊዜ ከጦር መሳሪያ በላይ የሚዲያ ተደራሽነት መኖር ወሳኝነት አለው። በመሆኑም መድረክ ገንዘብ የሚፈልገው ዓላማው ህዝቡ ዘንድ እንዲደርስ ለማድረግና ህዝቡ ዓላማውን ተገንዝቦ እንዲደግፈው ለማድረግ ነው። ህዝብ ዘንድ ለመድረስ ወሳኝ ከሆኑት መሳሪያዎች መካከል ሬድዮ፣ ቴሌቪዠን፣ ጋዜጦች፣ በራሪ ፅሑፎች፣ ድረ ገፆች፣ ሶሻል ሚዲያዎች፣ ሳይቨር መልእክቶች፣ ፓስተሮች፣ ማስታወቂዎች፣ ወዘተ ተጠቃሾች ናቸው። በግንባር ተገናኝቶ ከህዝብ ጋር ፊት ለፊት ለመወያየትና መልዕክት ለማስተላለፍም ስብሰባዎች ማዘጋጀትም አስፈላጊ ናቸው። መድረክ እነዚህንና ሌሎች ጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠት ዕቅድ ይዞ የተነሳ ቢሆንም ተግባር ላይ ለማዋል ይችል ዘንድ የናንተው የዲያስፓራው ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ አሁንም የተለመደውን ድጋፋችሁ እንዳይለየን በመድረክ ስም ጥሪዬን አቀርባለሁ።
በመጨረሻ አንድ ነጥብ ልጨምርና ንግግሬን እቋጫለሁ። ኢትዮጵያ ሀገራችን አሁን ካለችበት ጭቆናና አፈና ተላቃ ሁላችንም የምንመኘው ለውጥ ሊመጣ የሚችለው በአንድ ድርጅት ጥንካሬ ወይም በጥቂት መሪዎች ትግል ብቻ የሚመጣ አይደለም። ለጋራ ሀገር፣ ለጋራ ችግር በጋራ እጅ ለእጅ ተያይዘን እያንዳንዳችን የበኩላችንን ድርሻ ስንወጣ ብቻ ነው።
ሁላችንም በግልም ሆነ በሕብረት ለሀገራችን ደሕንነት፣ ለነፃነታችንና ለመብታችን አናስነካም በማለት እኛው ራሳችን የትግሉ ባለቤት በመሆን ዘብና ጋሻ ሆነን ስንቆም ብቻ ነው የምንከበረው። በተናጠል የከፈልነውና አሁንም እየከፈልን ያለነው መስዋእትነት የሚዘነጋ አይደለም። በተለይም በዲያስፓራ የምትኖሩ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን “ስደትና የንሮ ሁኔታ ከህዝባችን አይለየንም” በማለት በተለያየ መልኩ የምታደርጉት እንቅስቃሴና የትግል አስተዋፀዖ መድረክም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ ይገነዘበዋል። ይህ በተናጠልም ሆነ በጋራ የምናደርገው እንቅስቃሴ እንዲጎለብትና መድረክ አሁን
በሀገራችን የተፈጠረውን ፈታኝ ሁኔታ በማጤን ህዝቡን የትግሉን ባለቤት በማድረግ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በሰላማዊ ትግል ዙሪያ አሁንም በሀገር ቤት የሚደረገው ትግል ወሳኝ ነው ብሎ ያምናል። ይህ እውን ለማድረግም በውጭ ሀገር በግልም ሆነ በማሕበር የሚደረገው እንቅስቃሴ ከሀገር ውስጥ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ጋር መደጋገፍና የትግል አጋርነት ለመፍጠር ይቻል ዘንድ መድረክ አሁንም ከናንተ ጋር አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ። በተረፈ በውጭ የምትኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሆናችሁ ሀገር ወዳድ ወገኖች መድረክን ብዙ ውጣ ውረድ አልፎ
አሁን የደረሰበትን ደረጃ እንዲደረስ ለማድረግ ተስፋ ሳትቆርጡ በሞራል፣ በሓሳም ሆነ በገንዘብ አስተዋፀዖ ስታደርጉ የቆያችሁና አሁንም ወርቃማ ጊዚያችሁና ገንዘባችሁን መስዋእት በማድረግ ይህን ታላቅ ህዝባዊ ስብሰባ በማዘጋጅት ጥረት ያደጋችሁ ወገኖቻችን ሁሉ ለመድረክ ብቻ ሳይሆን ለመላ ታጋይ ሐይሎችና ህዝባችን የሚያኮራና ተስፋ ሰጪ ተግባር ስለሆነ ያለኝን አድናቆትና ምስጋና የላቀ ነው።

በፅሞና ስላዳመጣችሁኝ አመሰግናለሁ
የመድረክ አመራር አመራር በሰሜን በሰሜን አሜሪካ አሜሪካ የሚያደርጉትን የሚያደርጉትን ህዝባዊ ህዝባዊ ስብሰባዎችን ስብሰባዎችን በመቀጠል በመቀጠል አቶአቶ አቶአቶ ገብሩ ገብሩ አስራት አስራት በአትላንታ በአትላንታ ከተማ ከተማ ተገኝተው ተገኝተው ለተሰበሰቡት ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያውያን ያደርጉትን ያደርጉትን ታሪካዊ ታሪካዊ ንግግር ንግግር ሙሉ ቃል ቃል ቃልቃል እንደሚ እንደሚተለው ተለው ቀርቧል ቀርቧል።። ።። click here PDF MALEDA TIMES

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on September 24, 2012
  • By:
  • Last Modified: September 24, 2012 @ 4:03 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar