www.maledatimes.com የመቀሌ ጥንታዊ ቀልዶች - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የመቀሌ ጥንታዊ ቀልዶች

By   /   September 25, 2012  /   Comments Off on የመቀሌ ጥንታዊ ቀልዶች

    Print       Email
0 0
Read Time:10 Minute, 11 Second

            በመቀሌ ከተማ የቀልድ ነገር ሲነሳ፣ ካሳ ደበስ እና አስፋቸው ፈቃዱም አብረው ይነሳሉ። በእነዚያ የሩቅ ዘመናት ከማለዳው አራት ሰአት ጀምሮ የጠላ ገበያ ይደራባት በነበረችው መቀሌ ቀልድ ትልቅ ስፍራ ይሰተው ነበር። ጥርስ የማያስከድኑ ቀልዶችም በጠላና በአረቄ ቤቶች ይንቆረቆራሉ። ሁለቱ የቀልድ አባቶች ዛሬ በህይወት ባይኖሩም፣ ከተማይቱ ነዋሪዎች ግን ዛሬም ድረስ በፈገግታ ያነሳሱዋቸዋል። በአማርኛ ሲቀርቡ ያስቁ ይሆን?
• • •
        አስፋቸው ፈቃዱ ማመልከቻ በመፃፍ የታወቁ ነበሩ ይባላል።ታዲያ ከእለታት አንድ ቀን አንዲት የመንደሩ ነዋሪ፣ “ለፍርድ ቤት ማመልከቻ ይፃፉልኝ” ብላ ትጠይቃቸዋለች፣

“ትከፍይኛለሽ?”
“ገንዘብ ስለሌለኝ በነፃ ይፃፉልኝ?”
አስፋቸው ተስማምተው የሚከተለውን ማመልከቻ ፃፉላት፣
“ለበነፃ ፍርድ ቤት….
በነፃ፣ በነፃነት በነፃ። በነፃ በመሆኑ በነፃነት በነፃ ተፅፎአል።
አመልካች፣
ነፃ ነፃነት።
አመልካቿ አስፋቸውን አመስግናና መርቃ ከማመልከቻዋ ገርጌም ፊርማ አስቀምጣ ማመልከቻዋን ለፍርድ ቤት አቀረበች። የዚህ ማመልከቻ ታሪክም እነሆ! እስካሁን በመላ ትግራይ በወግ መሃል ይነገራል።
• • •
ሌላ ጊዜ ደግሞ አስፋቸው በሬ ስለወጋቸው ክፉኛ ተጎዱ። ከህመመቻው እንዳገገሙም የበሬውን ባለቤት፣ “በቆየ ቂም ተነሳስቶ በሬውን ልኮ አስወግቶኛልና ይካሰኝ” ሲሉ ከሰሱ። ድፍን መቀሌ ጉድ ብሎ የዚህን ክስ መጨረሻ ለማወቅ ተሰበሰበ። ዳኛው ግን፣ “እንስሳ መልእክት መቀበል ስለማይችል አይክስህም” ሲሉ ጉዳዩን በአንድ ቀን ዘጉት።
        በውሳኔው የተከፉት አስፋቸው ታዲያ፣ “ጥይቱ” የተባለ ውሳቸውን አስከትለው ባላንጣቸውን አድብተው ይጠብቁ ጀመር። እናም አንድ ቀን ብቻውን አገኙት። ውሻቸውን፣ “ጃስ! ያዘው!” ሲሉትም ተወርውሮ የባለ በሬውን እግር ቦጨቀ። አስፋቸው በዚህ ተከሰው ፍርድ ቤት ቀረቡ። ሲጠየቁ እንዲህ የሚል መልስ ሰጡ፣ “…እንስሳት መልእክት መቀበል አይችሉም። እንዴት ነው ውሻዬን የምልከው?” ሆኖም ቅጣቱ አልቀረላቸውም።
• • •
        አስፋቸው የሚያከራዩት ቤት በደርግ ተወርሶባቸው ስለነበር ለኑሮ ብዙ ስራዎችን ይሰሩ ነበር። ቆዳ እያለፉም ይሸጡ ነበር። አንድ ቀን ታዲያ በአህያቸው ቆዳ ጭነው ወደ ገበያ ሲያዘግሙ አንዱ፣ “ቆዳ ይሸጣል?” ሲል ይጠይቃቸዋል።
        “የለም! ለርቢ ነው” የሚል ነበር የአስፋቸው ምላሽ።
• • •
        የአስፋቸው በዚህ ይብቃና የካሳ ደበስን ደግሞ እነሆ!
        ካሳ ደበስ በመቀሌ ከተማ የታወቁ ነጋዴ ነበሩ። በቀይ ሽብር ዘመን የካሳ ደበስ ሁለት ልጆች የተለያዩ ቦታዎች ይታሰሩባቸዋል። አንደኛው ልጅ ወህኒ ምርመራ፣ ሌላው እንዳ እየሱስ የተባለ ራቅ ያለ ስፍራ። ካሳ ደበስ በወቅቱ ለነበረው ሹም የሚከተለውን ደብዳቤ ፃፉ፣
        “…ያለኝ የምሳ ሳህን ማመላለሻ አንድ ብቻ በመሆኑ፣ ሁለቱ ልጆቼ ከተቻለ በአንድ ላይ ቢታሰሩልኝ። ካልተቻለ ግን አንደኛው ቢገደል…”
        ይህ ደብዳቤ የደረሰው ሹም በደብዳቤው በጣም ተገርሞ ሁለቱንም ልጆች ፈታቸው።
• • •
        በዚያው ሰሞን መቀሌ ከተማ መጠጥ ቤት ውስጥ አንድ ወታደር ከሲቪሎች ጋር ተጋጭቶ ይቆስላል። በዚህ የተነሳ ከተማዋ ስትታመስ ታድራለች። ወታደሮችም በየቤቱ እየዞሩ ያስሳሉ። ፈታሾች ካሳ ደበስ ቤት እንደደረሱም፣
        “ክፈት!” ይላሉ።
“አልከፍትም!” ይላሉ ካሳ ደበስ።
“አንት ቡሽቲ! ክፈት”
“ደግ ነዋ! ቡሽቲ ከመጣችስ እከፍታለሁ”
በዚህ ጊዜ ከፈታሾቹ አንዱ ካሳ ደበስ መሆናቸውን አውቆ፣ “ያ ቀልደኛ ነው፣ እባካችሁ ተውት!” ይላቸዋል። በር ሲደበድብ የነበረው ወታደር፣ “ቆይ አንተ ቡሽቲ! ሲነጋ እናገኝሃለን” ብሎአቸው ይሄዳሉ።
ካሳ ደበስ ማልደው ቤተክስያን ሲያስቀድሱ መከፋታቸውን የተመለከቱ ጎረቤቶች፣ “ምነው ደህናም አላደሩ?” ሲሉ ይጠይቋቸዋል።
“ምን ደህና አድራለሁ? ቡሽቲ የምትባል በሽታ ስታሰቃየኝ አደረች እንጂ!”
• • •
        የካሳ ደበስ እዚህ ላይ ይብቃንና ወደ አክሱም እንጓዝ። ቄስ ምህረይ ወልደዮሃንስ ይባላሉ። በዘመኑ የኢድዩ አባል ተብለው ይታሰራሉ። ፖለቲካ አላውቅም ቢሉም፣ ሰሚጠፍቶ ሌትና ቀን ተደበደቡ። ከሳምንት በሁዋላ ግን፣ “እብድ ናቸው” ተብሎ እንዲፈቱ ተወሰነ። ሲፈቱም በድብደባ በጣም ተጎድተው ስለነበር የፖሊስ መርማሪው፣ “ሰው ምን ሆኑ ብሎ ቢጠይቆት ‘መኪና ገጨኝ’ በሉ” ይላቸዋል። ምህረይ ወልደዮሃንስም ከተለቀቁ በሁዋላ እንደተመከሩት፣ “መኪና ገጨኝ” እያሉ መናገር ቀጠሉ።
        አንድ ቀን ታዲያ ሰው በተሰበሰበበት እከተማ ማህል ከመርማሪው ፖሊስ ጋር ይገናኛሉ። ይህን ጊዜ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው፣ ጣታቸውን ወደ መርማሪው ፖሊስ በመቀሰር፣ “የገጨችኝ መኪና መጥታለች! ገለል በሉ እንዳትገጩ!” አሉ ይባላል።
(ተስፋዬ ገብረአብ፣ “እፍታ – ቅፅ አንድ፣ 1991)
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on September 25, 2012
  • By:
  • Last Modified: September 25, 2012 @ 7:50 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar