የተሰበረ ልብ ( እውነተኛ ታሪክ)

Sara Rahel

በልጅነታችን እኔና ወንድሞቼ ፀጉር ቤት ስላማንሰደድ ቤታችን ውስጥ ድንጋይ ላይ ቁጭ ብለን በአባታችን መርሃ ግብር አዘጋጅነት ፀጉራችንን ያስተካክለን የነበረውን የአክስቴን ልጅ ‘ጋሽዬን’ መቼም አልረሳውም !! (ጋሽዬ የመጠሪያ ስሙ ሳይሆን እኛ ለከበሬታ የምንጠቀምበት ነው!) እንጂ ስሙ በስተመጨረሻ ላይ ልፅፍ መነሻ ከሆነኝ ሰሞነኛ ጉዳይ በኋለ እናገራለሁ፦ ለጊዜው በጋሽዬ ልቀጥል:- በዛ በህፃንነታችን አእምሮ እይታ (ከ 7-10 ዓመት ቢሆነን ነበር) ከቤተሰባችን በጥሩ ትምህርት ተምሮ የተመረቀ, ጥሩ ስራ የነበረው, ብዙ ጊዜም የሚነበቡ ትልልቅ መፃህፍት ከእጁ የማይለየው, ራሱን የሚጠብቅ, ብዙ ከኤሌክትሪክ ጋር የተገናኘ ቴክኒካል እውቀት የነበረው, ከመብራት ጋር በተገናኘ ለሚገጥም ችግር ሁሉ መጥቶ የሚሰራልን:- ጋሽዬ ካደግን በኋላ ከቤታችን ጠፋ ለምን ጠፍቶ እንደነበር ምክንያቱን ያወቅነው (እኔና ወንድሞቼ እንዲሁም እህቴ ማለቴ እንጂ) ወላጆቼ ያውቁ ኖሯል! ቆይቶ ነበር !ጎጆ ወጥቶ ነው! ለካ ከዛም ልጅ ወልዷል መባሉ ተሰማና ልንጠይቅ ከእናቴ ጋር ወደሚኖርበት ሰፈር ሄድን ያው በነበረኝ ግምት ከበፊቱ የተሻለ ኑሮ የሚኖርበት መኖሪያ ሰፈር እና ቤት እንደሆነ ጠብቄ ነበር ::ሰው ሲማር, ሲያገባ ,ከዛ ደግሞ ሲወልድ… ብቻ በሁሉ ነገር እየተሻሻለ እንደሚሄድ ይመስለኝ ነበር !ግን ያየሁት ሁኔታ በተቃራኒው ነበር ::የአራስ ጥሪ ይዘን (ካልረሳሁት ድፎ መሰለኝ) ከእናቴ ጋር በ 35 ቁጥር አውቶብስ ከመሳለሚያ ተንስተን መዳረሻው ድረስ ሄድን (የድሮ መዳረሻዋን የሚያውቅ ሰፈሩን አወቀው ማለት ነው)የ10 ወይም የ11 ዓመት ልጅ ያይውን ማመን አቃተው! ያንን ሰፈርም ለመጀመሪያ ጊዜ ማየቴ ነበር! እና ከቤቶቹ ተጠጋግቶ መሰራት ባሻገር ለመኖሪያ ምቹ አለመሆን ትዝ ይለኛል ‘ምን ሆኖ ነው ጋሽዬ እዚ ሰፈር የሚኖረው’ ብዬ ስጠይቅ የተመለሰልኝ መልስ ልጅ ስለወለደ ሌላ ከዚ የተሻለ መኖሪያ ቦታ ልፈልግ ቢል ከነልጁ የሚያከራየው የለም … የመሳሰለ መልስ ነበር ዋናው ምክንያት ግን ሌላ ነበር! ለልጆቹ ጥንቃቄ ስል ዋናውን ምክንያት ልለፈው ከዛም የተወለደው ወንድ ልጅ መሄድ ሲጀምር በየተወሰን ጊዜ እኛ ቤት ይዞት ይመጣ ነበር,,, ጊዜያቶች አለፉ ከወንድ ልጅ ሌላም ተጨማመሩ የአክስቴ ልጅ ጋሽዬም እየተጎሳቆለ መዘነጡ ቀርቶ በቅጡ መልበስ ሳይችል መቅረት ጀመረ! ይሰራበት ከነበረው አደይ አበባ ጥጥ ፋብሪካ ስራ ተቀነሰ !ልጆቹ ለማሳደግ ፍዳውን ይበላ ጀመር ባለቤቱም በሞት ተለየችው እንግዲህ ልጆቹን ለማስተማር እና ሰው ለማድረግ ያገኘውን ነገር ይሰራ ጀመር ያ ‘የተማረ ሰው’ ብለን እንደዋና የምናየው ሰው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጎዳ በኋላም ልጆች የማሳደግ ነገር ከኑሮ ውጥረት ጋር ተረባርበው የሰውነቱ ሁሉ አዛዥ የሆነው አዕምሮውን ጎዱት አማኑኤል ሆስፒታል ገብቶ ይታከም ጀመረ ከ 5 ዓመት በፊት ይመስለኛል አማኑኤል ሆስፒታል ልጠይቀው ስሄድ ልቤ በጣም ተሰብሮ መመለሴን አልረሳውም!ልጅ ለማሳደግ የተከፈለ ዋጋ ይሆንን?? ከጊዜያት ቆይታ ጤንነቱ እየተሻሻለ ወደስራም ለመመለስ ቻለ! ልጆቹም ደረሱለት እናም የጋሽዬ ልጅ የሆነው ሲወለድ ልንጠይቀው የሄድነው ህፃን የዛሬው ባለታሪክ የቤተሰቡን ኑሮ ሊያሻሽል የ24 ዓመቱ ኤልያስ የጨርቆሱ ወደሊቢያ አቀና! ከሄደ እንኳ 3ወር ሳይጨርስ ‘ዓጋንንት በሚጠቀምባቸው’ ሳይሆን ‘ዓጋንንትን በሚጠቀሙበት’ በሰው አራጆች እጅ ወደቀ ! ሰው ከስብዕናው ጀምሮ ጤንነቱን እንኳ ዋጋ እስኪከፍል ድረስ ልጅን ያሳድጋል! እንደዚህ የሆነበትን ልጁን ግን በዚህ ሁኔታ መነጠቅ የሁል ጊዜ ማንም ሊረዳው የማይችል ሀዘን እና ስብራት ነው ::እኔ በተወሰነ መልኩ የማውቃትን ነው ለመናገር የሞከርኩት የተቀሩት የ29 ወገኖቻችን ወላጆች ልጆቻቸውን እንዴት ባለ ጭንቅ አሳድገዋቸው ይሆን??? የፍትህ አምላክ ፍትህን አድርግ! መፅናናትን ለጋሽዬና በሊቢያ ለተሰዉት ውድ ወንድሞቻችን ቤተሰቦች በሙሉ እግዚአብሔር ይስጥ ! ‘ጋሽዬ’- ተጫነ ዘለቀ
”እግዚአብሔር ሆይ በእኛ ላይ የደረሰውን አስብ ውርደታችንን እይ ተመልከትም ”ሰቆቃወ ኤርሚያስ 5:1

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar